spot_img
Sunday, May 28, 2023
Homeነፃ አስተያየትየዘር አገዛዝ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ - ‘ጽንፈቱ’፣ አደጋውና ውገዳው

የዘር አገዛዝ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ – ‘ጽንፈቱ’፣ አደጋውና ውገዳው

- Advertisement -

ተስፋዬ ደምመላሽ
መጋቢት 2, 2012 ዓ .ም.

የ“ኦሮሚያ” ወገንተኞችና ምሁራን ተባባሪዎቻቸው ዘውጌ ብሔርተኝነትን ከተለመደው የወያኔ አብዮታዊ ተብዬ ርዕዮታዊም ሆነ ድርጅታዊ ውቅር በማራቅ፣ ሁሉ ነገር፣ በተለይ የጎሣ አገዛዙ ተራ፣ “የኛ” ነው በማለት የማንነት ፖለቲካቸውን ወዳፈጠጠና ያገጠጠ ግልብ ጎሠኝነት እያወረዱት መሆኑ ገልጽ ነው። ይህ የፖለቲካ አኪያሄዳቸው ኢትዮጵያ ዛሬ በትንሳኤ ግድቧ ዙሪያ ከውጭ ኃይሎች፣ በተለይ ከግብጽና ከአሜሪካ፣ ግፊትና የጥቃት ማስፈራሪያ እየደረሰባት ባለበት ወጣሪ ሁኔታም ጋብ አላለም። እንዲያውም የአንዳንድ ኦሮሞ ብሔርተኛ ስብስቦች ፖለቲካዊ አኪያሄድ የውጭ ኃይሎች መጠቀሚያና ተጠቃሚ በመሆን ተባብሶ ሊቀጥል እንደሚችል መገመት አዳጋች አይደለም።      

የኦሮሞ ‘ሊህቃን’ ብሔርተኝነት የአገር ችግሮችን አገራዊ መንፈስ በተላበሰ የጋራ ግንዛቤ ለመጨበጥና ለመቋቋም፣ መፍትሔዎቻቸውንም ለማፍለቅ ከሚረዳ ቅርጽና ይዘት ጋር አካቶ ያልተገናኘ ነው። የሚነዳውም በዘላቂ ምክንያታዊ ተስፋ ሳይሆን ባንዳፍታ የስነልቦና እርካታ ከመስጠት ምንም ያህል በማያልፍ ምኞታዊ እሳቤና ስሜት ብቻ እንደሆነ ስውር አይደለም። በዚህ መልክ የኢትዮጵያ መዲና የሆነውን አዲስ አበባን ሳይቀር እንዳለ “የኛ” ነው ብለው ይህን ምኞታቸውን እውን ለማድረግ ላይ ታች ይላሉ። ለምሳሌ የአዲስ አበባን የሕዝብ ስብጥር ለመለወጥ በገሃድም ሆነ ውስጥ ውስጡን የዴሞግራፊ መሃንዲስነት ሥራ እየሠሩ ነው፤ አያይዘውም የከተማው ኗሪነት መታወቂይ ሰነዶችን ለከተማው መጤ ለሆኑ ኦሮሞዎች በገፍ ሲያደሉ እንደነበር ይታወቃል።

ባለፈው ሰሞን ጠ/ሚንስትር አብይ “ብልጽግና” [ፓርቲ] የኦሮሞ ነው….ጠላቶቻችን….በሃገሪቱ ላይ መወሰን እንዳይችሉ የተፈጠረ ነው…እጃችሁ የገባውን ነገር ጠብቁ….ያገኘነውን ይዘን የቀረውን ሞልተን ወደፊት መሄድ እንድንችል አንድነታችንን እንጠብቅ” ሲል ይህንኑ የኛ፣ የኛ ባይነት እያስተጋባ ይመስላል። አቢይ አሕመድ ይህን ያለው አምኖበትም ይሁን የኦሮሞ ብሔርተኞች ‘መስማት የሚፈልጉትን’ ለመንገር ብሎ፣ አባባሉ የመላ አገር ጠ/ሚንስትር ከሆነ ሰው ፈጽሞ የማይጠበቅና ኢትዮጵያዊነትን የማይመጥን ብቻ ሳይሆን ጨርሶ የአገራዊነትን መንፈስ የራቀው ነበር።     

ሆኖም ችግሩ በጠ/ሚንስትሩ ፖለቲካዊ አስተሳሰብና ብሔርተኝነት የተወሰነ ሳይሆን በጥቅላላ የ“ኦሮሚያ” ወገንተኞችንና ምሁራን ግብረ አበሮቻቸውን የሚመለከት ነው። እነዚህ የማነት ፖለቲካ አቀንቃኞች በግማሽ ምዕተ አመት የዝግመት ሂደት ወደማያወላዉል ኢትዮጵያዊነት ማደግና መሸጋገር የተሳናቸው ናቸው። ቅር ሳይላቸውና ሳያጉረመርሙ ታሪካዊ ኢትዮጵያዊነታቸውን  በሙሉ ልብ የመቀብል ችግር ምን ጊዜም ተለይቷቸው አያውቅም። ለምሳሌ ከጥቂት ወራት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ በጠ/ሚንስትሩ ጽሕፈት ቤት በተቀናበረ የውይይት መድረክ አዛውንቱ የኦሮም ፖለቲከኛ ሌንጮ ለታ “ኢትዮጵያዊነት” ዝሬም አከራካሪ ነው የሚል አረጋዊ “ዕውቀት” ችረውናል። የራስን አገር ‘ማወቅ’ ይሏል የኼ ነው!

ባለፈው ሰሞን ደግሞ በተመሳሳይ መንገድ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና “እስከ ዛሬ ኢትዮጵያዊ ማን ነው የሚለውን ጥያቄ አልፈታንም” አሉ። እንግዲህ በአንድ በኩል ወያኔዎች ጠቦ ሕዝብ አጥባቢና ከፋፋይ ለሆነ ዘረኛ አገዛዛቸው እንደተመቻቸውና እንድፈለጉት ትናንትና የፈጠሩትና ዛሬም በእጅ አዙር ጣልቃ የሚገቡበት ውጥንቅጥ “ኦሮሚያ” ለጥያቄና ክርክር ፈጽሞ ክፍት አይደለም እያሉን ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ግዛቱ ይስፋም ይጥበብ በሺዎች አመታት ለሚቆጠሩ ዘመናት ብሔራዊ ህላዌና ሥልጣኔ ያልተለየው ኢትዮጵያዊነት አካቶ ስክነት የሌለው አከራካሪ ማንነት ወይም ምንነት ነው እየተባልን ነው። ነገሩ የተገላቢጦ ነው።

በተለይ በዚያን ሰሞን ፕሮፌስር መረራ ጉዲና ያቀረቡት አስተያየት ኢታሪካዊነትና የአመክንዮ ዘበት ትንፋሽ ቆራጭ ነው። ክርክራቸውን ወደ ጽንፍ ድምዳሜው ብንወስደው እንደሚከተለው የሚል ይሆናል – “ኢትዮጵያዊ ማን ነው የሚለውን ጥያቄ አልፈታንም”፣ ስለዚህ ግልጽ የሆነ ኢትዮጵያዊ ማንነት የለም፣ ይህም ማለት የፕሮፌሰሩን ጥያቄ እንደ ኢትዮጵያዊያን  “ልንፈታው” ቀርቶ ልናስተናግደው አንችልም፣አገራዊህልውናችን ወይም ማንነታችን ራሱ ጥያቄ ውስጥ ገብቷላ!        

ቀደም ብዬ እንደጠቆምኩት፣ እዚህ ላይ ቁም ነገሩ ግን የአንድ (የዚህ ወይም የዚያ) ኦሮሞ “ምሁር” እሳቤ ትርጉም የለሽነት አይደለም። ይልቅስ ራሱን ከኢትዮጵያ አርቆ በማቆርቆዙ የታላቅ አገራዊ ሥልጣኔ አካል ሆኖ በአስተሳሰብም ሆነ በፖለቲካ ማደግና መተለቅ ያልሆነለት የኦሮሞ ልሂቃን ዘውጌ ብሔርተኝነት እንዳለ ነው። ማደግና መዳበር ያልቻለው የፕሮፌስር መረራ ጉዲና የግል ምሁርነት ወይም ፖለቲካ አዋቂነት ብቻ አይደለም። የለየለት ሕዝብ አሸባሪና በፖለቲካው እንደ እስስት ተለዋዋጭ የሆነውን ጃዋር መሐመድን ሳንጠቅስ፣ አገር አወዛጋቢና አተራማሽ ‘ጽንፈኛነት’ በፕሮፈሰር በቀለ ገርባ፣ በኦሮሞ “ክልል” ርዕሰ መስተዳደሩ ሺመልስ አብዲሳ፣ በመከላከያ ሚንስትሩ ለማ መገርሳ፣ በጠቅላይ ሚንስትሩ አብይ አህመድና በሌሎች “የኦሮሚያ” ወገንተኞች የፖለቲካ አስተሳሰብ፣ ዲስኩርና አሠራር ልምዶች ይገለጣል። በተለያዩ ቅርጾችና ሁኔታዎች በየጊዜው ይንጸባረቃል።

ኢሕአዴግ እንደ ድርጅት ከስሞ በብልጽግና ፓርቲ ተተክቷል ቢባልም ድርጅቱ ከፓርቲው ሹም ሽር በፊት የነበረው ጎሠኛ ርዕዮታዊ ድባብ አብሮ አልከሰመም። ኢንዲያውም የፖለቲካ ዘውጌነቱ መንፈስ አገርና ሕዝብ ይበለጥ አመሳቃይ፣ ጎጂና አጥፊ ሆኖ ቀጥሏል። በውጤትም ይሁን በእቅድ የተወሰነ የነገድ ብሔርተኝነት አገዛዝ ቅብብሎሽ ውይም “ሽግግር” ተደርጓል፣ ተረኝነት ከሞላ ጎደል ሰፍኗል።

ኢትዮጵያን፣ በተለይ ደግሞ አዲስ አበባን፣ በሚመለከት እርግጥ በአለፈው ሰሞን ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በቃለ ምልልስ ያሏቸው ነገሮች አነጋጋሪ ሆነው ሰንብተው ነበር። ከነዚህ የሚከተሉትን ለናሙና መጥቀሱ የፕሮፌሰሩን የግል አመለካከት ብቻ ሳይሆን በጠቅላላ የኦሮሞ ብሔርተኝነትን አስተሳሰብ ትርምስ በመጠኑም ቢሆን ይገልጥ ይመስለኛል። (1) የሕገ መንግሥቱ “አንቅጽ 39 ለኦሮሞ ምንም አላመጣለትም…ወያኔዎች ለምን እንደጻፉት አላውቅም”። (2) “ኢትዮጵያ ስትፈጠርም ከችግር ጋር የተፈጠረች ናት…”። (3) “የጎሣ ፖለቲካ” ማለት “ስድብ ነው… የዜጋ ፖለቲካ ብትሉ ይሻላል”።

እነዚህ የኦሮሞ ብሔርተንነት ብሶቶች የተዘባረቁ ነጥቦች ያካተቱ ናቸው። ሆኖም ቅጥ የለሽነታቸውን በዝች አጭር ጽሑፍ ጠጋና ገባ ብሎ ማሳያ ቦታ ስለሌለ በተባሉት ነገሮች ላይ ትችቶች መሰንዘሩን ለአንባቢዎቼ ልተወው። ግን ፕሮፌሰር መረራ በተለይ ስለ አዲስ አበባ ይበልጥ ወጥ በሆነ መልክ ወዳሉት ማስፈራሪያ ያዘለ ዝባዝንኬ ከማለፌ በፊት ከተጠቀሱት ሦስት ነትቦች በአንደኛውና ሁለተኛው ላይ ብቻ መልስ የማይጠብቁ ጥቂት ጥያቄዎች ላንሳ። ነጥቦቹ ዝምብለው በአንድ የኮሌጅ መምህር የተቀመጡ ሳይሆኑ ከሞላ ጎደል በርካታ የኦሮሞ ምሁራን የሚጋሯቸው ናቸው። ሦስተኛው ፈጽሞ ትርጉም የለሽ ስለሆነ ምንም ትችት አይገባውም።

የመጀመሪያውን ብሶት በሚመለከት፣ “ኦሮሚያ” እንደ ብቸኛ የጎሣ “ክልል” ለመፈጠሩና የዘውጌ አገዛዝ ለመሆን መብቃቱ ሕወሓት የጻፈው ሕገ መንግሥት ተብዬ፣ በተለይ አንቀጽ 39፣ ወሳኝ አስተውጽዎ ማድረጉ የሚካድ ነው ወይ? የኦሮሚያ ወገንተኞች ስታሊናዊ “ብሔራዊ ራስ ዉሰና” ለማድረግ (ማለትም፣ ለመገንጠል) ለአስርተ ዓመታት ላይ ታች ኳትነው ሳይሳካላቸው ቢቀርም የፈለጉት በዘር የተከለለ ግዛት በኢትዮጵያ ውስጥ ስለተበጀላቸው የወያኔዎች ውለታ የለባቸውም ወይ? ሌላው ነገር ደግሞ፣ ሕወሓቶች አንቀጹን የጻፉት እነሱ የበላይ የሆኑበት ዘረኛ አምባገነናዊ አገዛዝ ለማቋቋም እንደነበረ እንኳን ለፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር ለማንም ኢትዮጵያዊ የሁለተኛ አመት ኮሌጅ ተማሪ (ሶፎሞር ) ግልጽ አልነበረምን? ምሁሩ መረራ ጉዲና ይህ ዕውቂያ ምነው ተሳናቸው?

ወደ ሁለተኛዉ ነጥብ ስንመጣ የምናየው ዝምብሎ የአንድ ተቺ አቋም ሳይሆን በርካታ ኦነጋዊ የማንነት ፖለቲካ ወገንተኞችና ምሁራን ለአስርተ አመታት ያለማቋረጥ፣ ነጋጠባ፣ ሲገዘግዙት የኖሩት ነገር ነው። በእውነቱ አገር ወዳድ ኦሮሞዎችና ኢትዮጵያዊያን በጠቅላላ በተመጣጣኝ ቀጣይነትና ሃሳበ ጽኑነት ፈታሽ ታሪካዊም ፖለቲካዊም ጥያቄዎች ልናነሳበትና አካቶ ትርጉም የለሽነቱን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግልጽ ልናደርገው የሚገባ ነጥብ ነው። ግን አሁን ሰፊ ትንተና ውስጥ ሳልገባ አግባብ ያላቸው አንድ ሁለት ጉዳዮች ብቻ ላንሳ።

መረራ ጉዲና ኢትዮጵያ “ከችግር ጋር የተፈጠረች” አገር ናት ሲሉ ይህ ሁኔታ በተለይና በብቸንነት ኢትዮጵያን የሚመለከት ነው የሚል አንድምታ ያለው ክርክር እያቀረቡ ይመስል ነበር። በኦሮሞ ብሔርተኞች የሚታየው የኢትዮጵያ ዋና “ችግር” አገሪቱ ስትፈጠርና ስታድግ ኦሮሞዎች የተሳተፉባት ሳይሆን እሷ “ያለፈቃዳቸው” የተስፋፋችባቸው መሆኗ፣ እነሱ በነበሩበት አርፈው ቁጭ ብለው “ከሌሎች” ወረራ እና ጉዳት ተቀባይ ‘መሆናቸው’ ነው።

ይህ ቅሬታ ከኢትዮጵያ እውነተኛ ታሪክ አንጻር ሲታይ መሠረተ ቢስ እንድሆነ ማሳየት ይቻላል። ነገር ግን እዚህ ይህን ክርክር ለማቅረብ ሳንሞክር አንድ አግባብ ያለው ጠቅላላ ጥያቄ ማስቀመጡ ይበቃል። ይኸውም፣ በዓለም ላይ ሲፈጠሩ፣ ሲያድጉና ሲዳብሩ ከሆኑ ያልሆኑ ችግሮች፣ ግጭቶችና መስፋፋቶች አካቶ ያመለጡ ወይም መላ ዜጎቻቸውንና ነገዶቻቸውን ከጅምሩ በፈቃደኝነት ወይም በእኩልነት አሳትፈው አንድነትን የገነቡ አገሮች ስንት ናቸው? የትኞቹ ናቸው? ሩሲያ? ዩናይተድ ስቴትስ? ደቡብ አፍሪካ? ሌሎች?    

ኦሮሞው ራሱ በኢትዮጵያ ምድር ሲስፋፋ አካቶ ሰላማዊ በሆነ መንገድና የሌሎች የአገሪቱ ነገዳዊና ባህላዊ ማኅበረሰቦችን “ፈቃደኝነት” እና እኩል ተሳታፊነት በማረጋገጥ ነበር ወይ? ኦሮሞው ሲስፋፋ ስንት ሌሎች ባህላዊ ማኅበረሰቦችና ቋንቋዎች እንዳልነበሩ ሆነዋል? አልጋ ባልጋ በነበረ እንከን የለሽ ሂደት የዳበሩ ብሔራዊ ባህሎች በዓለም ላይ አሉ? ታዲያ በዓም ዙሪያ ያልታዩ የአገር ማቅናት ሁኔታዎች በኢትዮጵያ መፈጠር ነበረባቸው ተብሎ እንዴትስ ይታሰባል? ከዚህ አንጻር በምን አመክንዮ ነው ኢትዮጵያዊነት ላይ ሂስ የሚሰነዘረው? ሂሱ ተጨባጭ ፍሬ ነገር ወይም ገንቢ አላማ ሳይኖረው መጀመሪያ ፋሽስታዊ (ከሮማን ፕሮቸስካ ጀምሮ) በኋላም ስታሊናዊ/ኮምኒስታዊ (የሻቢያ፣ የሕወሓት፣ የኦነግ) አማራ ጠልና አገር አፍራሽ ርዝራዥ አቋም አንጸባራቂ አይደለምን?   

ለነገሩማ ከአራት ምእተ ዓመታተ በፊት ኦሮሞዎች ራሳቸው ከኬንያ ድንበር አጠገብ ቦረና አካባቢ ተነስተው ወደ ኢትዮጵያ መካከለኛ፣ ሰሜን፣ ምዕራብና ምሥራቅ ክፍለ ሀገራት በመስፋፋትና በመስፈር ከሌሎች የኢትዮጵያ ነገዶች ጋር መሰባጠራቸውንና በዚህም ሂደት ለአገሪቱ ዘር ዘለል ብሔራዊ ማንነት መዳበር ወሳኝ አስተውጽዎ ማድረጋቸውን ታሪክ መዝግቧል። በኢትዮጵያ መንግሥት አመራርና አስተዳደር በኩል፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ አብዮት፣ ኦሮሞዎች ንቁ አገራዊ ተሳትፎ እንዳደርጉም ይታወቃል።

እንግዲህ ዛሬ ዋናው “ችግር” በኢትዮጵያ ታሪካዊም ዘመናዊም ብሔራዊ ልምድ የኦሮሞ ማንነት ወይም ባህል እውቅና፣ ክብር ወይም ዋጋ ማጣት አይመስለኝም። ይልቅስ ጣጣው የነገድ ብሔርተኛ ኦሮሞ ልሂቃን ያላቸውን ከዘር ማንነት ያለፈ አገራዊ ራስነት አለመቀበል ነው። ይህን ሲያደርጉ በታሪክ መረጃ ካልተደገፈ፣ ፋሽስታዊም ኮምኒስታዊም ፍልቀት ከነበረው ወልጋዳ ትርክት ተነስተው እንደሆነ እንረዳለን። ማኅበረሰባዊና ባህላዊ ማንነታቸውን ያካተተ ነገድ ዘለል ኢትዮጵያዊነትን ነባራዊ እውነታ፣ ትርጉምና እሴቶች በቅጡ መገንዘብና በሙሉ ልብ መቅረብ የማይፈልጉ ወይም የማይችሉ መሆናቸውን እናያለን።

እንግዲህ የኦሮሞ ብሔርተኛ ምሁራን በአንድ በኩል ኢትዮጵያዊነታቸውን ቀናንሰው ራሳቸውን ወደ ጎሣ ተኮር ማንነት ለማሳነሳቸው፣ በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ምትክ “ኦሮሚያ”ን  በአፍሪካ ቀንድና ምሥራቅ አፍሪካ አውድ ለማተለቅና የበላይ ለማድረግ መመኘታቸው ሁለት የተዛመዱ ምክንያቶች መጠቆም ይቻላል። አንደኛው፣ ለከት በሌለው የተጎጅነት ስሜትና አማራ ጠል ፖለቲካ የተዋጠ የኢትዮጵያ ታሪክ ግንዛቤና ትርክት ነው። ሁለተኛው ደግሞ በተጠራመሰ የዝመና አኪያሄድ ምዕራባዊ ተጽዕኖን (ለምሳሌ፣ የላቲን ሥርዓተ ጽሕፈትን) በኦሮሞ “ብሔራዊ ራስ ዉሰና” ስም በመቀበልና ሥራ ላይ በማዋል የኦሮሞን ማኅበረሰብ ከኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላ ከጥቁር አፍሪካ ሕዝብ (የግዕዝ ፊደል በሰፊው ፍልቀቱ አፍሪካ ስለሆነ) ያለያየና ያራቀ “ማንነት” ፈጠራ ነው።

አዲስ አበባን አስመልክቶ የኮሌጅ አስተማሪው መረራ ጉዲና ባለፈው ሰሞን ወዳስተላለፉት አስፈራሪ እንቶ ፈንቶ እንመለስና አንዳንድ ያሏቸውን ነገሮች እንቃኝ። “የኦሮሞ ሕዝብ ከዓለም ጋር የሚገናኘው በአዲስ አበባ ነው…አዲስ አበባ የአፍሪካ እምብርት ናት…” እዚህ ላይ ፕሮፌሰር መረራ ከጎሣ “ክልል” ወደ አፍሪካ አህጉር፣ ከአፍሪካ ወደ ዓለም ባደረጉት መረማመድ አዲስ አበባ መዲናዋ የሆነችው አገር ኢትዮጵያ ራሷ በአዲስ አበባ ባለቤትነቷ ወይም አይነታ ድርሻ ያዥነቷ አለመጠቀሷ፣ ስሟ አለመነሳቱ፣ ጎልቶ የሚታይ ነው።

በነገራችን ላይ ጠ/ሚንስተር አብይም ሰሞኑን በቦረና በአደረገው ሲበዛ የኦሮሞ ጎሠኝነት መንፈስ የተላበሰ ንግግር “[እኛ]ከዓለም ጋር ግንኙነት አለን” [‘እኛ’ ኦሮሞዎች] ማለቱ የሚታወስ ነው። አዲስ አበባ ከዓለም ሕዝብ ጋር የምታገናኘው ኦሮሞዎችን ብቻ ወይም “ኦሮሚያ” የተባለ “ክልል”ለይታ ሳይሆን መላ ኢትዮጵያዊያንን መሆኑን፣ መዲናዋ “የአፍሪካ እምብርት” ይሆነችውም መጀመሪያ የኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ በመሆኗ እንጂ የአንድ ክፍለ ሀገር ወይም የጎሣ ጉረኖ ከተማነቷ እንዳልሆነ ፕሮፌሰ መረራ “ዘነጉት”?   

ጉዳዩ ዝምብሎ የመዘንጋት ነገር አይመስለኝም፤ ነው ቢባልም ሆን ተብሎ የተደረገ፣ ነጥብ ያለው “ዝንጉነት” ነው። ለመረራ ጉዲና እና ለበርካታ “የኦሮሚያ” ወገንተኛ አቻዎቻቸው፣ ትንሽ ትልቅ ሳይል በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ኢትዮጵያዊነትን “ረስቶ”፣ ማለትም ችላ ብሎ፣ አኮስሶና ጥግ አስይዞ የኦሮሞ ዘር ተኮር አድራጊ ፈጣሪነትንና ብሔርተኝነትን እንደ እውን አገር ማጉላት፣ ማደለብና ማማከል ገሃድ የፖለቲካ ዕቅዳቸው ከሆነ ዉሎ አድሯል።

ስለዚህ በኦሮሞ ብቸኛ ጎሣዊ ብሔርተኝነትና በኢትዮጵያ ነገድ ተሻጋሪ አገራዊነት መካከል ያለዉን (የፉክክር?) ግንኙነት ባመዛኙ የሚያዩት እንደ ዜሮ ድምር ጨዋታ (ያንዱ ትርፍ የሌላው ኪሳራ እንደሆነ) አድርገው ነው ማለት ይቻላል። ከዚህ አተያይ ተነስተው “የኦሮሚያ” ማደግና መጠናከር የሚያስከፍለው ዋጋ የኢትዮጵያን መቀጨጭ፣ መዳከምና ብሎም መፍረስ ነው የሚል ግምት ላይ ቢደርሱ (አስቀድመው ሳይደርሱ አልቀሩም!) በጣም አያስደንቅም። “ኦሮሚያ” የተባለው የፖለቲካ እቅዳቸው የመጨረሻ ግብም ይኸው ይመስለኛል። ግቡን መምታት ከቻሉ ደግሞ የምናውቃት ኢትዮጵያ በመሠረቱ እንደማትኖር ያውቃሉ።

አዲስ አበባን በሚመለከት ያፈጠጠና ያገጠጠ ዛቻ በማካተቱ በቀላሉ “ጽንፈኛ” ዘውጌ ብሔርተኝነት አንጽባራቂ ሊባል የሚችለው የፕሮፌሰር መረራ ንግግር ደግሞ በሚከተሉት አባባሎች ይገለጻል። “አዲስ አበባ ከኦሮሚያ ጋር መጣላት የለበትም….ሁለቱ ሕዝቦች…. ከመጣላት ይልቅ የተሻለ የሃብትና የስልጣን ክፍፍል ካላደረጉ ወደ ግጭት ይሄዳሉ….፤ ምግብ፣ ውሃና መብራት ከኦሮሚያ የምታገኘው አዲስ አበባ በኦሮሚያ የተከበበች ስለሆነች ከሌላው ኢትዮጵያ ጋር የማትገናኝበት ሁኔታ ይፈጠራል….”። ማለትም፣ መግቢያና መውጫ በሮቿ ሁሉ ሊዘጉባት ይችላሉ። ከተማዋ በግጭት፣ደም መፋሰስና መናወጥ “እንደ የሩሳለም ትሆናለች”።

እነዚህ የፕሮፌሰር መረራ አባባሎች በሃሳብም ሆነ በእውነታ ደርጃ ሲታዩ መሠረተ ቢስና አካቶ አገራዊ መንፈስ የሌላቸው ናቸው። አዲስ አበባን እና እየሩሳሌምን በተባለው መልክ ማመሳሰሉ ዝምብሎ ጅምር የለሽ ነው። አግባብ የሌለው፣ ከመሬት የማይነሳ ምስስል እንደሆነ በቀላሉ ማሳየት ይቻላል። የአዲስ አበባን እና “ኦሮሚያ” የተባለውን የጎሣ ግዛት “መጣላት” ምን አመጣው? መቼና እንዴትስ ነው ሁለቱ ግዛቶች በፍጹም ተለያይተውና ዋልታ ረግጠው ድፍን ጠበኞች የሆኑት? ‘ጠበኝነታቸው’ እውን ሳይሆን የፕሮፌሰሩን ጠብ ጫሪ የሆነ “ጃዋራዊ-ቄሯዊ” ትምክተኛነት የሚያንርጽባርቅ አዲስ አበቤዎችን ማስፈራሪያ ነው ሊባል የሚችል ነው።  

እርግጥ ከጥቂት አመታት በፊት የአዲስ አበባ ከተማ መስፋፋት በከተማው ዳር ለሚኖሩ ኦሮሞ ገበሬዎች ችግር ፈጥሮ እንደነበረ ይታወሳል፣ አስቀድሞ ዘላቂ መፍትሔ ካልተበጀለት ወደፊትም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን የአዲስ አበባ እና “ኦሮሚያ” ኗሪዎች የጋራ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ብቻ ሳይሆን ኢኮሚያዊ መኅበራዊና ባህላዊ ኑሮ ያስተሳሰራቸው የአንድ አገርና ሕዝብ አካላት ስለሆኑ አለመግባባት ቢያጋጥማቸውም ስምምነት የሚፈጥሩት ፕሮፌሰሩ በዘር ብሔርተኝነት መንፈስ እንዳመለከቱት በድፍኑ ደሴታዊ ማንነት ያላቸውና የተጋለሉ “ሁለት ሕዝቦች” ሆነው እንዳልሆነ መታወቅ አለበት።

ወይም ደግሞ ከ‘መግባባት’ የሚደርሱት አዲስ አበባ ላይ የራሱ አስገዳጅ ‘ልዩ ኃይል’ ያለው የ“ኦሮሚያ” ግዛት አዲስ አበቤዎችን ‘ተከባችኋል፣ ስለዚህ የኛን የይገባናልና ይሰጠን ጥያቄዎች ካልተቀበላችሁ ከቀሩት የኢትዮጵያ ግዛቶች ጋር እንዳትገናኙ ማድረግ እንችላለን’ ብሎ በማስፈራራት አይሆንም። በነገራችን ላይ፣ ይህን አይነት ማስፈራሪያ ያካተተ (‘አዲስ አበባ የመብራት ኃይል የምታገኘው ከኦሮሚያ ነው’ የሚል) ንግግር ሰሞኑን የአድዋን ድል ለመዘከር በአሜሪካ (ማሪላንድ) በተደረገ የኢትዮጵያዊያን ስብሰባ ላይ ታዬ ቦጋለ ማስደመጡ ይታወሳል።

የሚያሳዝን ባይሆን ኖሮ የሚያስቀው ነገር ደግሞ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ለአዲስ አበባ ‘ችግር’ ዛቻ ያዘለ ‘መፍትሔ’ ያቀረቡት “እንደ ፖለቲካ ሳይንስ ምሁር” ሆነው መሆኑን የነገሩን ነው። የኦሮሞ ሕዝብ የዚህ አይነት ‘ሳይንሳዊ ዕውቀት’ ተጠቃሚ ሆኖ ምን የድንቁርና ችግር አለበት? የመረራ ጉዲና የአዲስ አበባ ችግር አገላለጽም ሆነ ‘መፍትሔ’ አሰጣጥ አገራዊ አብሮነትን ቀደምትነት ከመስጠት ይልቅ “አብረን ከኖርን” የሚል ጥርጣሬ ኢትዮጵያ አንድነት ላይ የሚጥል ነው። ኢትዮጵያዊነት ራሱን የቻለ እሴት መሆኑን የሚቀበል ሳይሆን በሆኑ ያልሆኑ ወገንተኛ-ጎሠኛ ድርድሮች – በፖለቲካ ጥቅሞች፣ ፍላጎቶች፣ ምኞቶችና ሁኔታዎች – ተወሳኝ የሚያደርግ ነው። መፍትሔ አፈላለጉ የኢትዮጵያን አንድነትና ሉአላዊነት ለድርድር መክፈትን ያስከትላል። በኢትዮጵያ ውስጥ ማኅበረሰባዊ፣ ባህላዊና አካባባዊ ማንነትን ሊጠብቅና ሊያዳብር የሚጥረው “ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች” የሚላቸውን በጎሣ ለያይቶ፣ ከልሎና መሽጎ በመያዝ ነው።

በእውነቱ በዚህ አይነት “ራስ” ንጠላና ክለላ ውይም “ውሰና” ለዘለቄታው የኦሮሞን፣ የትግራይን ወይም የማንኛውንም ሌላ የኢትዮጵያ ባህላዊ ማኅበረሰብ ደህንነትና እድገት ማረጋገጥ የሚቻል አይደለም። በጠባብና ብቸኛ ወገንተኛ ፖለቲካ የጠቅላላ ነገዳዊ ማኅበረሰብን ማንነት ለመጠበቅ መሞከሩ ራሱ ተጣራሽ ሙከራ ነው፤ ምክንያቱም በዚህ የአብሮነትን አስፈላጊነትና ጥቅም በማይረዳ አኪያሄድ ራስ ጥበቃ ይበልጥ ሲሞከር የሚፈለገው ደህንነት ለዘለቄታው ይበልጥ የማይረጋገጥና የማያስተማምን ይሆናልና።        

የዘውግ ብሔርተኝነት ጽንፈትመደበኛነት

ከሕወሓት የአገዛዝ ዘመን ጀምሮ እስክ ዛሬ ባለው የኢትዮጵያ አውዱ የነገድ ብሔርተኝነት “አክራሪ” ወይም “ጽንፈኛ” በሚሉና በሌሎች ተመሳሳይ ቅጽሎች ሊፈረጅ ወይም ሊገመት ይችል ይሆናል። ሆኖም ግምቱ በገለጻና አረዳድ ጎዳና ሩቅ አይወስድም። አገር ከፍፋይና አወዛጋቢ የዘር ብሔተኝነትን በጥራት ተገንዝቦ በስልትና ቆራጥነት ለመግጠምም አይረዳም። በዘውጌ ፓርቲዎች መካከል ብቻ ሳይሆን በየውስጣቸውም  በብሔርተኝነት አያይዝና አተገባበር የሚያጣሉ ልዩነቶችና መጣረሶች ሊኖሩ ይችላሉ፣ ነበሩም። በሕወሓት ጎሠኛ ብሔርተኝነት ዉስጥ ልዩነት ነበር፣ ዛሬም አለ። በኦነግ ራሱ ዉስጥና የግንባሩ ዉልድ በሆኑ ድርጅቶችም (ለምሳሌ መረራ ጉዲና በሚመሩትና ጃዋር መሐመድ በቅርቡ በተቀላቀለው ኦፌኮም) እንዲሁ ነው።

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያን አንድነት በተመለከተ ለአስርተ ዓመታት ማቆሚያ የሌላቸው የተንዛዙ ብሶቶችና ቅሬታዎች በማመንዠግ አገራዊ አንድነታችንን ሆን ብሎም ሆነ በውጤት በማዳከምና በኢምክንያታዊ ፍራቻም ጥላቻም አማራን ለይቶ በማጥቃት በታወቁት የትግሬና የኦሮሞ ልሂቃን ዘረኛ ብሔርተኝነቶች መካከል የቅጽል መለዮዎች የሚያስፈልጋቸው መሠረታዊ ልዩነቶች የሉም። በማንነት ፖለቲካ ወስጥ ትልልቅ የመርህ ወይም የሃሳብ አለመስማማቶች ተከሳች አልነበሩም፣ ዛሬም አይደሉም። በአማራ ጠልነቱና አጥፊነቱም ሆነ ከኢትዮጵያ ሉአላዊነት ጋር ባለው ተቃርኖ የትግሬና ኦሮሞ ልሂቃን ጎሠኛ ብሔርተኝነት ጽንፈኝነትን ያካተተው ከፀረ አንድነት ጽንሱና ከአፈጣጠሩ፣ እንዳለ በምንነቱና ባህሪው ኢንጂ እንድ ትርፍ ገላጭ “ቅጽል” አይደለም።  

ይህን ስንል ግን በሁለቱ የነገድ ብሔርተኝነት ጎራዎች ግለሰብባዊና ድርጅታዊ የአመራር ወይም የአገዛዝ አለመመሳሰሎች አልተከሰቱም፣ የሉም፣ ማለታችን አይደለም። ለምሳሌ አብይ አሕመድ የሚያራምደው የዘር ፖለቲካና አገዛዝ መለስ ዘናዊ ካራመደው የማንነት ፖለቲካ የሚለይባቸው ነገሮች አሉ። በዕኩይነትና መሰሪነትም ቢሆን የመለስ ዘናዊ ፈላጭ ቆራጭ የትግሬ ብሔርተኝነት “አብዮታዊ” በተባለ ርዕዮት ተብላልቶ የተቀረጸ ሃሳባዊነት፣ ወገንተኝነትና የአላማ ታማኝነት ነበረው። የጠ/ሚንስትር አቢይ ግለሰባዊ አገዛዝ ግን በፖለቲካ መስክ ላይ የሚንቅሳቀሰው በተመሳሳይ መልክ ወይም መጠን በተቀናበረ የመስመር፣ የአስተሳሰብና አላማ ውቅር ሳይሆን ከዚህም ከዚያም ተቀነጫጭበው እንደነገሩ “በተደመሩ” ልቅምቅም ሃሳቦች፣ እሴቶች፣ የልማት እቅዶች እና እንደየሁኔታው ተለዋዋጭ የሆኑ የሕዝብ ስሜት ሳቢ ሰበካዎች፣ ያነጋገር ዘይቤዎችና የትርክት መላዎች ነው።    

ከድርጅታዊ ባህል ወይም ባህሪ አኳያም፣ አስርተ አመታት በወሰደው ልምዱ የኦነግ “ብሔር ነፃ አውጪ” እንቅስቃሴ ከሕወሓት “ብሔር ነፃ አውጪ” የትግል አኪያሄድ የሚለይባቸው ነገሮች እንዳሉ ግልጽ ነው። በኦሮሞው ወገኖች ጎራ ውስጥም ቢሆን፣ የለማ መገርሳ ነገዳዊ አኪያሄድ ከዳውድ ኢብሳና ጃዋር መሐመድ የኦሮሞ የጎሠኝነት ዲስኩር፣ አቀራረብ፣ ቀመርና ታክቲክ ጋር የማይመሳሰሉባቸው ገጽታዎች የሉም ማለት አይቻልም። “ነፍጠኞችን በሰበሩን ቦታ ሰብረናቸው ዳግም ነግሠናል” የሚል ድንፋታ ያሰማው የሺመልስ አብዲሳ ኦሮሞ ብሔርተኝነት “ባላደራ ብላችሁ ከመጣችሁ ግልጽ ጦርነት ውስጥ እንገባለን” የሚል እስክንድር ነጋ የሚመራው የባልደራስ ንቅናቄ ላይ የተቃጣው የጠ/ሚንስትር አቢይ ዛቻ ለየት ያለ ይሆን የሆናል።

ነገር ግን ኢትዮጵያዊነትንና አማራን በሚመለከት በትግሬና ኦሮሞ ብሔርተኞች ወስጥም ሆነ መካከል የየቅልነት ቢኖርም ከመሠረታዊ የአስተሳሰብ ወይም የአላማ ልዩነት ይልቅ የፖለቲካ አደረጃጀት፣ አመራርና አሠራር ልምዶችን ወይም የአገዛዝ ቅጦችንና ሁናቴዎችን ተለዋዋጭነት ይበልጥ የሚያንጸባርቅ  ነው። የኢትዮጵያን አንድነት በቅን መንፈስ ከመቀበል ይልቅ በተንኮለኛ አስመሳይ አቀራራብ የመቀናቀን አዝማሚያ ያለው የዘውግ ብሔርተኝነት በጥቅሉ ከአብዮታዊ ተብዬ ጽንሱና አፈጣጠሩ ሕወሓቶችና ኦነጎች ከሞላ ጎደል በወል የተጋሩትና ዛሬም ከሞላ ጎደል የሚጋሩት ነው።

ፓርቲዎቹ ሥልጣን በተራ ሲይዙም ይኸው አገር ከፋፋይና አጥፊ ጠባያቸው በመንግሥት ተቋማትና በውጭ ሃይሎች ተደግፎና ተባብሶ ቀጠለ እንጂ ምንም ያህል ጋብ አላለም። የ“ታላቋ” ትግራይ  እና የ“ኦሮሚያ”ፓርቲዎች ብሔርተኝነት ከዚህ አንጻር ሲታይ ጽንፈትን ያካተተው እንደ ትርፍ አንጀት በተቀጥላ ወይም ተጨማሪ አካል መልክ ሳይሆን መሠረታዊ ውቅሩና ይዘቱ አድርጎ ነው። ወያኔዎችና ኦነጎች ፖለቲካዊ ብሔተኝነታቸውን በጋራ ያዋቀሩበትና ተቋማዊ ያደረጉበት “ሕገ መንግሥት” ጎሣዊ ማንነትን ከአገር በላይ ሉአላዊ ያደረገው በዚሁ ፀረ አንድነት ሥርዓታዊ የጽንፈት አኪያሄድ ነበር።

ቀደም ብዬ እንደጠቆምኩት፣ የነገዳዊ ፖለቲከኞችና ምሁራን አጋሮቻቸው ብሔርተኝነት ጽንፈት እርግጥ አንድ ወጥ ሳይሆን በተለያዩ የወገንተኛነትም የአገዛዝም ደርጃዎችና ቅርጾች ሊገለጥ ይችላል። በአንድ በኩል በጣም በወረደና በተደናቆረ ትንሽነት ተከሳች የሆነ ነው።  ለምሳሌ የኮሌጅ መምህሩ በቀለ ገርባ በአማርኛ መጽሐፍ እየጻፈ ‘አማርኛ አትናገሩ፣ ከአማሮች ጋር አትገበያዩ፣ አትጋቡ’ አለበለዚያ የኦሮሞ ቋንቋ ሊስፋፋ አይችልም የሚል እዚህ ግባ የማይባል ምክር ለኦሮሞ ኢትዮጵያዊያን ሲለግስ ይህን አይነት ወራዳ የማንነት ፖለቲካ ጽንፈት እያንጸባረቀ ነበር።

በሌላ በኩል ደግሞ አክራሪ የዘውግ ብሔርተኝነት በጣም ከፍ ብሎና ከብዶ ሕዝብ ጎጂ ሊሆን ይችላል፤ ሆኗልም። በድምቢዶሎ የአማራ ተማሪዎች በኦነግ ታጣቂዎች እገታና የሴቶች መደፈር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የአቢይ አገዛዝን ለአገር ችግሮች ኅላፊነት ያለመውሰድና ለችግሮቹ ሁነኛ መፍትሔዎች ያለመፈለግ ጉልህ አዝማሚያ ‘ጽንፈኛ’ ሊባል የሚችል ነው። ኦሮሚያ የሚል ስም በተሰጠው የጎሣ ጉረኖ ውስጥ ቀውስ አድራጊ ፈጣሪዎች እንድልባቸው እየተዘዋውሩ በንጹህ የአገሪቱ ዜጎች፣ በተለይ በአማሮች፣ ላይ አሰቃቂ የግድያ የማፈናቀልና የማገት፣ እንዲሁም የእምነት ቤቶች የማቃጠልና ንብረት የማውደም ከፍተኛ ወንጀሎች በየጊዜው በገሃድ ሲፈጽሙ፣ ጠ/ሚንስትሩ አይቶ እንዳላየ፣ አውቆ እንዳላወቀ የሚሆነው እንቆቅልሽ አለ። “የከተማ ከንቲባ ስላልሆንኩ የለገጣፎ ነዋሪዎችን መፈናቀል አሰማሁም”፣ “የኢምግሬሽን ሠራተኛ ስላልሆንኩ ወደ ትግራይ ሲሄዱ በአውሮፕላን ማረፊያ ስለታገቱ ቻይናዊያን አላውቅም”፣ ወዘተ የሚለው የማይገባ ነገር አለ። አብይ ዋና የመንግሥት መሪነቱን፣ (የጠ/ሚንስትርነቱን) ተቋማዊ ሚና እና ኅላፊነት አቃሎለመንግሥት አስተዳደር ችግሮችእሱ በግለሰብ ደረጃ ተጠያቂ አለመሆኑን ደጋግሞ ይነግረናል።    

በተደጋጋሚ ተከሳች የሆነውን የዜጎች ሕይወት መጥፋት፣ መጎዳትና መፈናቀል ብርቱ ጉዳይ ጠ/ሚንስትር አብይ በአስቸኳይነት ስሜት ሲያነሳውና በሃሳብም ሆነ በተግባር መፍትሔ ሲያፈላልግለት አይታይም። ጠ/ሚንስትሩ በጉዳዩ ለመረዳት የሚያስቸግር ግድ የለሽነት፣ ማለትም የሕዝብ ደህንነት ጥበቃ ግዳጅ ቸልተኛነት ያሳያል። አለበለዚያ ደግሞ በማክያቬሊያዊ አስተሳሰብ የቀውሱን ሁኔታ የአገዛዙ ማቆያ (እኔ በሥልጣን ከሌለሁ ቀውሱ ይባባሳል በሚል አስፈራሪ አመክንዮ) መሣሪያ አድርጎ ይገምት ይሆናል። ያም ሆነ ይህ፣ የአብይ አገዛዝ በአገር ድህንነት ጥበቃ በኩል ያለበትን መሠረታዊ ኃላፊነት በቅጡ መቀበልና መወጣት የማይፈለግ ወይም የማይችል መሆኑን በተደጋጋሚ አሳይቷል። እንግዲህ በእቅድም ሆነ በውጤት፣ በመደረግም ይሁን በአለመደረግ ዛሬ በኢትዮጵያ እየሆነ የምናየው የጎሣ ብሔርተኝነት አገዛዝን ጽንፈት ነው።

እንግዲህ እነዚህ ባለፉት ጥቂት አመታተ የተከሰቱ አደገኛ አገር አወዛጋቢና ቀዋሽ አዝማሚያዎች በኢትዮጵያ የዘውግ ብሔርተኝነት በጠቅላላ ዛሬ ስላለበት ሁኔታ ምን አንድምታ አላቸው? ምን አስተምህሮ እናገኝባቸዋለን? አዝማሚያዎቹ ለተለያዩ አተረጓጎሞች ክፍት ይሆኑ ይሆናል፣ ግን በኔ መላ ምት ወይም ግምት አንድ ዋና ፍሬ ነገር ያመላክታሉ። የኸውም ዘር ተኮር ብሔርተኝነት እንዳለ በሞራል፣ በአእምሮና በፖለቲካ ዘርፎች እያቆለቆለ መምጣቱ፣ በመርህ፣ በሃሳብና በገቢር ከስሮ አገር አክሳሪ መሆኑን ነው።

እርግጥ ቀኖናዊ እና ድርጅታዊ ውቅር ካለው ነባራዊ የሕወሐት “አብዮተኛ” የጎሣ ብሔርተኝነት በተለየ መልክ ዛሬ ተረኛ የዘር አገዛዝ የሆነው የኦሮሞ ብሔርትረኝነት ባመዛኙ ርዕዮታዊ ይዞታ የሌለውና በተመሳሳይ መጠን በጥብቅ ተደራጅቶ የተማከለ አለመሆኑ እውቅ ነው። ይህ ልዩነት አሌ የሚባል አይደለም። የሥራ ክፍፍል ያደረጉ የ“ኦሮሚያ” ፓርቲዎች አገዛዝ በዚህ ሁኔታ የሚያራምደው ለከትና ቅጥ የሌለው፣ የቆጡንም የባጡንም ‘የኔ የብቻዬ ነው’ የሚል ኢምክንያታዊ የማንነት ፖለቲካ ኦሮሞ ያልሆኑ የአገዛዙ አማካሪና ደጋፊ ምሁራን “አይታያቸው” ይሆናል። ነገር ግን በየጊዜውና በየክፍለ ሀገሩ የአገዛዙን ግፍና በደል ተቀባይ ለሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በተለይ ለአማራው፣ ስውር አይደለም። የመጤዎቹ ገዢዎች የማንነት ፖለቲካ፣ ጥሬ ዘረኝነት ከሚያንጸባርቅ ወንድ ወይም ሴት፣ ወጣት ጎልማሳ፣ ሕጻን አረጋዊ ሳይል ዜጎችን በደመ ነፍስ፣ እጅ እንዳመጣ በየጊዜው ከሚገድል፣ ከሚጎዳ፣ ከሚያፈናቅልና ከሚያሰቃይ ጨካኝ ኃይለኝነትና ሥርዓተ አልበኝነት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ሊካድ አይችልም።

እዚህ ላይ በሚገባ ማጤን  ያለብን ግን በነባሩና ወቅታዊው ዘር ተኮር ገዢ ፓርቲዎች መካከል ያለው ግብታዊም ይሁን ሆን ተብሎ የተፈጠረ ተናባቢነትና ተመጋጋቢነት ነው። ቀውስ አድራጊ ፈጣሪ ወኪሎቻቸውን በማሰማራት በውስጥ ለውስጥም ሆነ በገሃድ ሕዝብ አጣይ ውዝግብን መጫርና ማነሳሳት እንደ ታክቲክ የሚጠቀሙ እንደ ጃዋር ያሉ በገሃድ ጽንፈኛ የሆኑ የኦሮሞ ብሔርተኞች ብቻ አይደሉም። ያረጁ ያፈጁ የትግሬ ብሔርተኝነት አክራሪ የሕወሐት መሪዎች፣ ወገንተኞችና ከኢትዮጵያ የተለየን “አክሱማዊያን” ነን የሚሉ የትግራይን ሕዝብ ፈጽሞ የማይወክሉ ዘላማጅ ‘ምሁራን’ ደጋፊዎቻቸውም ናቸው።

እንግዲህ ‘ጽንፈኝነት’ ነባራዊ ወይም መደበኛ ከተባለ የማንነት ፖለቲካ ሥርዓት ያፈነገጠ፣ ወይም የተለመደ የዘውግ ብሔርተኝነትን ያልተከተለ፣ አኪያሄድ ሳይሆን የሥርዓቱን መሠረታዊ ምንነትና ባህሪ የሚያንጸባርቅ መሆኑን እነረዳለን። አገር ከማፍረስ ጫፍ የደረሰው መጠንና ቅጥ የለሹ ጎጠኝነት እንዳለ ኦነግና ሕወሐት ከጽንሳቸውና አነሳሳቸው ጀምሮ ለአስርተ አመታት ሲቆሰቁሱት የነበረን ፀረ አማራ የፖለቲካ እሳት ነው ዛሬም በማፋፋም ላይ ያለው። በዘዴኛ ተጓዳኝነትም ይሁን በፉክክር ሁለቱም ወገኖች ለመፈጸም የሚጥሩት ጽንፈኛ ግብ ኢትዮጵያን እንዳልነበርች አድገው አንድ የዘውግ ፓርቲ የበላይ ገዢ የሆነበት ልል የጎሣዎች ትብብር (confederacy) ለመፍጠር ይመስላል። ሁለቱም ወገኖች የኢትዮጵያ አንድነት ምንም ያህል ጉዳያቸው እንዳልሆነ በተለያዩ መንገዶች አሳይተዋል፤ ዛሬም እያሳዩን ነው ያሉት።

ይህም ማለት በኢትዮጵያ አውዱ የዘውግ ብሔርተኝነት ራሱን መልሶ አንጾ ከአንድነት ደጋፊ አገር ወዳድ ወገኖችና ኃይሎች ጋር በቀና መንፈስ ተወያይቶና ተደራድሮ የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥ ለማምጣት ፈቃደኛ ይሆናል ወይም ይችላል ብሎ መጠበቅ ምክንያታዊ ተስፋ ሳይሆን ምኞታዊ ጥበቃ ነው። መቅሠፍት ሊያስከትል የሚችል፣ በተለይ ለአማራው በጣም አስጊ የሆነ ተስፋ ማድረግ ነው። የአማራን ሕዝብ ለይቶ የጥፋት ኢላማ ያደረገ አምባገነናዊ የዘር ብሔርተኝነት በግማሽ ምዕተ አመት እድሜው እንዴት ተጸንሶ፣ ተነስቶና ተንቀሳቅሶ ዛሬ የት እንደደረሰ፣ የመጨረሻ ግቡ ወይም ውጤቱም ምን ሊሆን እንድሚችል በደንብ ያልተረዳ አደገኛ ተስፈኝነት ይመስለኛል። ጥሩውን መመኘት እርግጥ ችግር የለውም፣ ምንጊዜም መልካም ነው። ነገር ግን ተስፋ ማድረግ አስጊ የአገር አቀፍ ሁናቴዎችንና አዝማሚያዎችን አስተውሎ ሊተካ አይገባውም።  

አማራው ለብቻው ‘ብሔርተኛ’ ሳይሆን ራሱንና ኢትዮጵያን ይታደግ!

ተስፋፊ፣ ሕዝብ ከፋፋይና አጋጭ የዘር ብሔርተኝነት አገር አቀፍ “ግዛት” ስላለው ሊወገድ የሚችለው በመላ ኢትዮጵያ በያዘው ቦታና ባሳደረው ተጽዕኖ ልክ እንደሆነ ገልጽ ነው። የዘር ፖለቲካን ችግር አንድ የነገድ ፓርቲ ወይም አካባቢ በብቸኝነት ሊቋቋመው ቀርቶ አሟልቶ ሊገልጸውም የሚችል አይደለም። ወይም ደግሞ የሆነ ጎሠኛ ድርጅት ሌሎች ተለጣጣፊ የዘውግ ድርጅቶችን በበላይነት እየጠመዘዘ የሚቋቋመው አይደለም። ጠምዛዡ ፓርቲ ስሙን ቢለዋውጥም (ሕወሐት፣ ኢሐአዴግ፣ ብልጽና፣ ወዘተ) ይህ አይነት አኪያሄድ መፍትሔ ሳይሆን የችግሩ ዋና ምንጭ፣ አካልና መገለጫ መሆኑ መስተዋል አለበት። በመሠረቱ ዘላቂ የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥ የሚመጣውና የአገር ችግር የሚፈታው በዘር ዘለል አገራዊ ትግል እንደሆነ እንገነዘባለን።

ሆኖም፣ ኢትዮጵያ የተጠናወታትን የዘር ብሔርተኝነት አባዜና የመወጫውን ንቅናቄ በሚመለከት ለአማራው ለየት ያለ ተጋጣሚነትና ተገዳዳሪነት በርካታ ምክንያቶች አሉ። እዚህ አሉታዊና አወንታዊ የሆኑ ሁለት ዋና ጉዳዮች ብቻ መጥቀስ ይበቃል። አንደኛውና አሉታዊው ምክንያት ከተማሪው ንቅናቄ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የሆነ ያልሆነ የጎሣ ፖለቲካ አራማጅ ወገንና አገዛዝ ሁሉ መነሻው አማራ ላይ ያነጣጠረ የተንዛዛ የቅሬታና የተጎጂነት ስሜት ነው። ስሜቱ ባመዛኙ ከጦዘ ፖለቲካዊነት የመነጨ ሸውራራ የአገር ታሪክ አተያይ የወለደው እንደሆነ ለብዙዎቻችን ስውር አይደለም።   

ወልጋዳ የፖለቲካ ትርክቱ ነፍጠኛ፣ ወራሪ፣ ጨቋኝ፣ መጤ እያለ እስከ ዛሬ ድረስ አማራነትን እንዳለ አስከፊ ምስል ሲሰጥ ኖሯል። ዛሬም ይህን የፕሮፓጋንዳ ጥቃቱን አላቋረጠም፤ እንዲያውም አባብሶ ቀጥሎበታል። በዋናነት የትግሬና ኦሮሞ ብሔርተኝነት ጥቃት የተቀናበረ ፀረ አማራ የፖለቲካ ተረትና ወሬ ከመንዛት አልፎ አማራ ሕዝብ ላይ ጠብ ጫሪ የመስፋፋት፣ የዘር ማጽዳት፣ የመግደልና የማፈናቀል እርምጃዎች ሲወስድ ቆይቷል። ለከት በሌለው ኢምክንያታዊ የተጎጅነት መንፈስ የተዋጠ አማራ ጠል ተንኮለኛነቱን፣ ጠብ ጫሪነቱንና አገር ቀዋሽነቱን ዛሬም በዘመነ “ብልጽና” አፋፍሞ ቀጥሏል።

እንግዲህ የጎሠኛ አገዛዝ ‘ሥርዓቱ’ (በእውነቱ፣ አገራዊ ሥርዓት የለሽነቱ) በጠቅላላ የአገር ጠንቅ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በተለየ መልክ፣መጠን ትኩረት ለአማራው አደገኛ መሆኑን የታወቀ ነው። የተረኝነት “ሽግግር” ያኪያሄደው የዘር ፖለቲካ መንኮራኩር የሚሽከረከርበት የስሜት ነዳጅ ባመዛኙ አማራ ፍራቻና ጥላቻ እንደሆነ፣ በዚህም ምክንያት ለአማራው ማኅበረሰብ ደህንነት የተለየ ደመኛነት ያለው ለመሆኑ በርካታ መረጃዎችና ማሳያዎች አሉ። ይህም ማለት ማኅበረሰቡ እንደ አገር አካል ብቻ ሳይሆን እንደ ማኅበረሰብ ራሱን ከጥፋት ለመከላከል የአገዛዙ ተገዳዳሪ እንዲሆን ተጨባጭ አስጊ ሁኔታዎችና አዝማሚያዎች አስገድደውታል።

በዛሬው አገራዊ የለውጥ ትግል ውስጥ ለአማራው ለየት ያለ ተጋጣሚነት አወንታዊ የሆነ ሁለተኛ ምክንያት አለ። ይኸውም፣ የአማራ ህልውና ወይም ራስነት የላቀ አገር አቀፍ ወርድና ስፋት ስለነበረውና ዛሬም በአስጨናቂው ዘመን ይህ ማንነቱ አካቶ ስላልጠፋበት፣ ከአገሪቱ ሌሎች ነገዶች ጋር ቅርብ ግንኙነትና ትስስር ያለው መሆኑ ነው። ማለትም፣ የአማራው ትልቅነት የቁጥር ብዛት ላይ ብቻ የቆመ ሳይሆን ከብዝሃን የኢትዮጵያ የባህል ማኅበረሰቦች ጋር ባዳበረው ግንኙነትና የተጽዕኖ ልውውጥ ላይ የተመሠረተ መሆኑ መዘንጋት የለበትም። ይህ ትልቅነቱ ለአገር ውጥረት ዘላቂ አፈታት ዋና አስተዋጽዎ አድራጊ መሆን የሚያስችለው ህላዌና ዝንባሌ ሰጥቶታል። ሌሎች የባህል ማኅበረሰቦችን አቃፊነቱና አገር አቅኝነቱ እንከን የለሽ ነበሩ ባይባልም፣ የአገሪቱን የተለያዩ ነገዶች በኢትዮጵያዊ ብሔራዊ ሥልጣኔ ያቀራረበ፣ ያገናኘ፣ ያዋሃደና ያተለቀ መሆኑ ሊካድ አይችልም። በዛሬው አስከፊ የዘር አገዛዝ ዘመንም ቢሆን ይህ ሰፊ አገር አቀፍ ማንነት በአማራው ማኅበረሰብ ውስጥ ከፍተኛ የጎሣ ብሔርተኝነት ተቋቋሚና አስወጋጅ እምቅ አቅም ያለው መሆኑን እንረዳለን።

ሆኖም፣ አሳዛኙ ነገር አማራው በማኅበረሰብም ሆነ በአገር ደረጃ ይህን እምቅ ተጋጣሚ አቅሙን እውን አድርጎ ከወደቀበት የውጥረት ቋጥኝ መውጣት፣ ብሎም ራሱን ሆኖና ጠብቆ አገሩን ማዳን፣ ተቸግሯል። ከሊህቃኑ መካከል ስሙን ብቻ የያዙ ግለሰቦችና ስብስቦች የአማራን ኩሩ ማንነት በሚጣረስ አኪያሄድ የዘረኞች ውሃ ተሸካሚና ተላላኪ ሆነዋል። አማራው ለዚህ ዋና ችግሩ እርግጥ የነባሩም የመጤውም ጎሠኛ አገዛዝ ከባድ አስተዋጽዎ ማድረጉ አሌ የሚባል አይደለም። ያም ሆኖ ግን የአማራው ብርቱነት አንዱ ማሳያ ለውድቀቱ ራሱን ተጠያቂ የማድረግ ብቃት ያለው መሆኑ ነው። በሰፊ አገር ጠበው የሚኖሩ፣ አንሰው ሕዝብ አሳናሽ የሆኑ የኦሮሞና ትግሬ ጎሠኛ ብሔርተኞች ለተዋጡበት የተጎጅነትና ዝቅተኛነት ስሜት አማራን ነጋ ጠባ መወንጀልና መውቀስ ይቀናቸዋል፤ የወቀሳው ሱሰኞች ናቸው። አማራው ግን ለደረሰበት ውድቀት ሌሎችን ከመውንጀል ይልቅ ራሱ ኃላፊነት በመውሰድ ትልቅነቱን ማሳየትና ከገባበት ውጥረት መውጣት የሚችል ሕዝብ ነው። ጉዳዩ እንግዲህ ይህን እምቅ አቅሙን እውን አደራረጉ ይመስለኛል።

እዚህ ላይ መነሳት ያለበት፣ ግን በተለምዶ የማይነሳው፣ መሠረታዊ ትያቄ የአማራን ራስነት የሚመለከት ነው። አማራው በምን አይነት ማንነት ነው ራሱን ጠብቆ ለራሱና ለአገር አንድነት የሚንቀሳቀሰው? የአማራው ህላዌና አድራጊ ፈጣሪነት ከማንም የዘር “ክልል”  ማንነት ወይም የጎሣ ብሔርተኝነት የሚለየው እንዴት ነው? ልዩነቱ ለአገር መልሶ ግንባታ ምን አንድምታ አለው? በነዚህ ወሳኝ ጥያቄዎች ዙሪያ በተወሰነ መጠንም ቢሆን  በመገናኛ ብዙሃን ከሚደረጉ የአገዛዙ ደጋፊም ተቃዋሚም ፖለቲከኞችና ምሁራን ቃለ ምልልሶች እና ውይይቶች አርኪ መልሶች ምንም ያህል አይፈልቁም። ሌላው ቀርቶ ጥያቄዎቹ ራሳቸው ሰፋና ጠለቅ ያሉ ውይይቶች ጫሪ ሆነው በአስተውሎና በጥራት ተቀርጸው አይስተናገዱም። በተለምዶ በየሚዲያው ከሚሰነዘሩ ገለጻዎችና አስተያየቶች የሚተርፈው የአማራነት አረዳድም አብዛኛውን ጊዜ የተድበሰበሰና ብዥ ያለ ነው። በኔ ግምት አገነዛዘቡ በሃሳብም ሆነ በተግባር የአማራን ሙሉ ራስነትና አገራዊ ወርድና ስፋት አይመጥንም።   

ለዚህ የአማራ ማንነት ጉዳዮች ግንዛቤና አገላለጽ ውስንነት የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። እዚህ ባጭሩ ሁለት ዋና የጉዳዮቹን የአቀራረብ ወይም የአቀራረጽ ችግሮች መጠቆም በቂ ነው። አንዱ አቀራረብ አንዳንድ የአማራ ተቆርቋሪዎችና ተሟጋቾች በቀና መንፈስ ከሚይዙት ውስን አቋም ጋር የተገናኘ ነው። ሌላው ደግሞ ከአማራ ራስ ጠበቅ ትግል ጋር በመጥፎ መንፈስ፣ በአስመሳይነት፣ “ተባባሪ” በመሆን ትግሉን ለወገንተኛ ጥቅሞቻቸውና አላማዎቻቸው መከታተያ መሣሪያ ማድረግ በሚጥሩ የጎሣ አገዛዙ ኃይሎችና ሌሎች ፓርቲዎች (ለምሳሌ የድሮው ግንቦት ሰባት) አካባቢዎች የሚታይ ነው።

የፊተኛው አቀራረብ የአማራውን አስጊ የመኖር ወይም አለመኖር ጉዳይ አስቸኳይነት በመረዳት ይህንን አጣዳፊ ስጋት በአስተሳሰባቸው፣ በድርጅቶቻቸውና እንቅስቃሴዎቻቸው የሚያንጸባርቁ የአማራ‘ብሔርተኞችን’ ይመለከታል። የኋለኛው፣ በተማሪው ንቅናቄ ዘመን በኮምኒስት ርዕዮት ተጠንስሶና በሕወሐት/ኢሕአዴግ/ብልጽግና አገዛዝ ተቋማዊ ውቅር ይዞ እስከዛሬ የቀጠለው ቀውስ ፈጣሪ አምባገነናዊ የጎሣ ፖለቲካና አገዛዝ ሥርዓት ጋር የተገናኘ ነው። ከተማሪው ንቅናቄ ዘመን ቀድሞም አውሮፓዊ የፋሽስት አስተሳሰብ ፍልቀት የነበረው ይህ ሥርዓት በተለየ አጥፊነትና አስከፊነት አማራው ላይ ከጫነው ጠላታዊ የክልል “ማንነት” ጋር በቀጥታ ይያያዛል።

የኋለኛው አቀራረጽ የጎሣ ፖለቲካ ሥርዓቱ የአማራ ጉዳዮችን በበላይነት የሚቆጣጠርበትና የሚጠመዝዝበት የፖለቲካ ዘዴ ነው። በዚህ ቁጥጥርና ጥምዘዛ የሥርዓቱ ቀንድኛ ተባባሪ አማራነትን ፈጽሞ የማይመጥንና የማይወክል፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አዴፓ ይባል የነበረ አስመሳይ የፖለቲካ ድርጅት ነው። ድርጅቱ የአማራ ጠላቶችን፣ በተለይ የኦነግንና የሕወሐትን፣ ዘረኛ ጥቅሞች ለመጠበቅ በአማራ ስም የአማራን ቦታ ያዥ ሆኖ የሚሠራ ነው። ይህ የጀርባ አጥንት የሌለው ወገን በቁርጠኛ መሪ አባላቱ ግድያ ሳቢያም እንኳን ከገዳዩ የጎሣ አገዛዝ ተለጣፊነት የመውጣት ምንም ፍንጭ የማያሳይ ወራዳ “አመራር” እንዳለው ይታወቃል። የአዴፓ አመራር የአማራውን ማኅበረሰባዊም አገራዊም ደህንነት ከውስጥ ሲያስጠቃ እንጂ ሲጠብቅ አይታውቅም። ድርጅቱ ከጽንሱ የጨቋኙ ጎሠኛ አገዛዝ ተባባሪ ሆኖ የተሠራና የተንቀሳቀሰ ነው። ዛሬም (በብልጽግና ፓርቲ ስም) የሚያንጸባርቀው የአማራ ጉዳዮች አያያዝ በመሠረቱ የአማራውን ጥቅም የሚያስከብር ሳይሆን በቀጣይነት የሚጎዳ ነው። ድርጅቱ በፖለቲካ ‘ዲኤኔው’ የማይታረም ወይም የማይጠገን ስለሆነ ከአመራር ቦታ ያዢነቱ፣ ከአስመሳይነቱ፣ አካቶ መወገድ አለበት።

የአማራ ተሟጋቾችና ‘ብሔርተኞች‘ አቀራረብ በጥቅሉ ይህ አይነት አስመሳይና አሉታዊ የፖለቲካ ይዞታ የለውም፣ ምንም እንኳን በዚህ ጎራ ውስጥ ከአዴፓ ጋር ግንኙነት ያላቸው አንዳንድ ተሟጋች ግለሰቦችና ስብስቦች ባይጠፉም። ሆኖም፣ ‘አማራው እንዴት ራሱን ሆኖ አገር ቀዋሽ የጎሣ ብሔርተኝነትን ይጋጠም?’ ከሚለው ጥያቄ አንጻር የአማራ ‘ብሔርተኞች’ እና አክቲቪስቶች  አቀራረብ እንዳለ ውስንነቶች ያሳያል። ዋናው ችግሩ የአማራውን ህልውና በሚመለከት የሚያሳየው የዋህ እውንነት ወይም ተጨባጭነት ነው። ይህን ስል ምን ማለቴ እንደሆነ ባጭሩ ልግለጽ።

የአማራው ማኅበርሰባዊ ህልውና ወይም መኖር አለመኖር የሚገለጠው እንዴት ነው? አማራው ራሱን ጠብቆ የዘረኞችን አጥፊ ጥቃት የሚከላከለውስ በምን መንገድ ይሆን? እዚህ ላይ የማኅበረሰቡ ተሟጋቾች የሚያቀርቡት ክርክር የተጣራ ወይም የጠለቅ ባይሆንም  በቀጥታ ተከሳች የሆኑ ፀረ አማራ ድርጊቶችና ሁኔታዎች ላይ ያተኩራል። ተከራካሪዎቹ የሚንቀሳቀሱት አማሮች በነገዳቸው፣ ማለትም በአማራነታቸው፣ ተለይተው በገሃድ የዘር ማጥፋት ኢላማ መሆናቸው፣ በአሰቃቂ መንገዶች በገፍ እየተገደሉ፣ የአካል ጉዳት እየደረሰባቸው፣ እየተፈናቀሉና እየታገቱ መሆኑ፤ እንዲሁም ታሪካዊ ግዛቶቻቸው በተስፋፊ የጎሣ ብሔርተኖች ተወረው መያዛቸው ለአስቸኳይ የህልውና አደጋ ያጋለጣቸው መሆኑን በመገንዘብ ነው። ግንዛቤው አግባብ አለው፤ በብዙ መረጃና ማሳያ የተደገፈ ነው።  

ሆኖም፣ አረዳዱ ሁለት የተዛመዱ መሠረታዊ ውስንነቶች ወይም ክፍተቶች አሉት። አንዱ ውስንነቱ ከመነሻው የአማራውን ሙሉ ራስነት፣ ማለትም የማኅበረሰቡን ነፃ ራስ ኋኝነትና ራስ አንቀሳቃሽነት፣ አስቀድሞ እንደተሰጠ ወይም በቀጥታና ባንዳፍታ ተሟልቶ እንዳለ አድርጎ ይወስዳል። አማራነት ራሱ በገዢውም በተቃዋሚውም ጎራ የአስመሳዮችና የፖለቲካ ነጋዴዎች አጀንዳዎች ማራመጃ መሣሪያ መሆኑን፣ በከፊልም ቢሆን አማራነት ራሱ በሆኑ ያልሆኑ የጎሠኛ አገዛዙ ወኪሎችና ደጋፊዎች እየተጠመዘዘ መሆኑን እንደ ችግር ታሳቢ አያደርግም። አረዳዱ የአማራው የህልውና ትግል መጀመሪያ በሐቅ ራሱን የመሆን ንቅናቄ መሆኑን “ይረሳል”። አማራው ቀደም ብሎ ተገዳዳሪ የሚሆነው ከራሱ ጋር እንደሆነ በሚገባ አያሳውቅም። የግንዛቤው ሌላውና ተዛማጁ ክፈተት የአማራን ገለሰባዊም ማኅበረሰባዊም ህላዌ ከግብታዊ የነገድ ማንነት አለፎ ሰፋና ጠለቅ ባለ ትርጉም ወይም አቀራረብ አይጨብጥም። የአማራን መኖር የሚያየው በአንዳፍታና በቀጥታ ተከሳች በሆነ ነገዳዊ/ማኅበራዊ እውንነት ወይም አካልነት ነው።

ይህ የአማራ ህልውና አተያይ ለሃሳብ፣ ለባህል ለአገራዊነትና ለፖለቲካ ምንም ያህል ቦታ አይሰጥም፤ እነዚህ ነገሮች በመሠረቱ የአማራውን አስቸኳይ የመኖር አለመኖር ትግል አይመለከቱም የተባሉ ናቸው። እየተባልን ያለነው ትግሉ በቀደምትነትና በአስቸኳይነት የአማራውን ማኅበረሰባዊ አካልነትና ድርጅታዊ አንድነት ወይም ትብብር የሚመለከት ነው። አማራው የሚሳተፍባቸው ሌሎች እንቅስቃሴዎች፣ በተለይ በአገር ጉዳዮችና የፖለቲካ ሃሳቦች ዙሪያ የሚደረጉት፣ በሁለተኛ ደረጃ የሚታዩና የአማራውን የህልውና ተጋድሎው መበረዝ ወይም ማስተጓጎል የሌለባቸው ናቸው ነው ክርክሩ። ለአገር መታደግ ለመብቃትም ቢሆን አማራው መጀመሪያ ራሱን ከጥፋት ማዳን አለበት። በዚህ አይነት ቅደም ተከተል የሚደረግ የአማራ ራስ አድን ንቅናቄ እንግዲህ የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥን በቅጡ ታሳቢና አላማ የማያደርግ ብቻ ሳይሆን የአማራን ራስነት ከኢትዮጵያ የህልውና ትግል የሚለይ ነው።

ይህ አይነት ገራገር እውንነት ወይም ተጨባጭነት ላይ ላዩን የአማራን የመኖር አለመኖር ጉዳይ የሚያጎላ ቢመስልም በእውነቱየማኅበረሰቡን ልዩ፣ ሰፊና ጥልቅ ህልውና የሚያጠብ፣ የሚያራቁትና ለተፈራው የመጥፋት አደጋ ይበልጥ የሚያጋልጥ ነው የሚሆነው። በዚህ አይነት ግልብ ማኅበራዊ ፈርጅ የአማራን “ህልውና” ወይም ነገዳዊ ኩነት ማሳነስና ማቀጨጭ ከጽንሱ በአስተሳሰብ የተዛባ ብቻ ሳይሆን በውጤት ራስን ከጎሠኛ አገዛዙ ጥምዘዛና ጥቃት መከላከል የሚያስችል ሳይሆን ለጥቃቱ ይበልጥ የሚያመቻች ነው።  

አማራነት በተሳሰሩ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ዘመናዊ ዘርፎች ተመጋጋቢ የሆኑ እሴቶች ያዳበሩት የማይካድ እውነታ ነው። ለምሳሌ መሬት አራሽነትን፣ የአገር ድንበር ጠባቂ ነፍጠኛነትንና ጀግንነትን፣ መንፈሳዊነትን እንዲሁም ምሁራዊነትን ወይም ጽንሳዊ ሃሳብ አስተናጋጅነትን ያካትታል። ይህ እውነታ አካቶ በቀጥታ የሚዳሰስ ወይም የሚጨበጥ አይደለም፤ ዝምብሎ አካላዊ፣ ነገዳዊ ወይም መኅበራዊ ፈርጅ ሆኖ ሊታይ አይችልም። በቀላሉ “ተጨባጭ” የሚባል ሳይሆን ባንዴ በማኅበረሰብነትም በኢትዮጵያዊነትም በጥልቅ የሚሰማን፣ የምንኖረውና የምናስበው እውነታ ነው።    

እንግዲህ የአማራ ሕዝብ ራሱን ሆኖ ከመላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመተባበር አገሩን ለማዳን የሚንቀሳቀሰው የማንነቱን ዘርፈ ብዙ መገለጫዎች አቀናብሮና አንድ አድርጎ በመሰማራት እንደሆነ ማስተዋል ይጠቅማል። ለምሳሌ ሃሳብ ታሪካዊ የአማራ ራስነት ውስጥ የተካተተ ነው፤ አማራነት ምንጊዜም ራስን አዙሮ አዪ አስተውሎ ተለይቶት አያውቅም። ነገር ግን የዛሬው አማራ በመኅበራዊም በአገራዊም ጎኑ ለሚደርሱበት የህልውና ጥቃቶች የሚሰጠው “ምላሽ” ወይም የሚያደርገው መቋቋም በመጠኑ፣ ዓይነቱ (ጥራቱ) እና ቅንብሩ የሚፈለገውን ያህል አይደለም። የመልሱ ብቁና ወጤታማ አለመሆን ምንጮች በርካታ ናቸው። በዋናነት ሊጠቀስ የሚችለው ምክንያት ግን በምላሹ የተለያዩ የማኅበረሰቡ ህልውና ገጽታዎችና ኃይሎች የሚሠሩት በተመዛዘነና የተሟላ አንድነት ወይም ትስስር ሳይሆን ተነጣጥለውና ተጋለው መሆኑ ነው። እዚህ ላይ የህልውና አገላለጹ አንድ ወጥነት ችግር አማራነትን ብቻ ሳይሆን በሰፊው ኢትዮጵያዊነትንም ይመለከታል።

የዚህ ችግር አንድ ማሳያ እንደ ማኅበረሰብም ሆነ እንደ ሀገር ደህንነታችንን ማረጋገጥ ስንፈልግ “በሕይወት የሚያተርፈን እግዜር ብቻ ነው” በሚል በቀላሉና በንጹሁ “መንፈሳዊ” በሆነ መንገድ የመሄድ ዝንባሌ ነው። አኪያሄዱ ከራስ ማዳን ትግሉ አካላዊ ሁኔታዎች፣ ተግባራዊ ልምዶችና ስልታዊ እሳቤዎች ያገለናል። ሆኖም፣ ይህ በተናጠልና በረቂቁ መለኮታዊ የሆነ ደህንነት ፈለጋ የሚያስከትለው ተጨባጭ ዉጤት አለ። ይኸውም አማሮች (በሰፊው ደግሞ ኢትዮጵያዊያን) ላይ ከእውን ህልውና አትራፊ እንቅስቃሴዎች የሚያርቅ ስነልቦናዊም ፖለቲካዊም ተጽዕኖ ያሳርፋል። የግለሰቦችንና ማኅበረሰቦችን አካላዊ የህልውና አደጋ ምከታ ተሳትፎን የሚያበረታታ መንፈሳዊነት ሳይሆን ሰጥ ለበጥ ባለ ቆዛሚ የተጎጅነት ስሜት ‘ሃይማኖተኛ’ የሚያደርግ ነው። ይህ አንድ ወጥ፣ ሁሉን ነገር ለእግዜር የሚተው፣ አንገት አስደፊ ሃይማኖተኛነት ደግሞ የአማራነትም ሆነ የሙሉ የኢትዮጵያዊነት መታደጊያ መሆኑ ቀርቶ በብቃት መገልጫ እንኳን ሊሆን አይችልም።

የጎሣ አገዛዝ ውገዳ የመዋቅራዊ ለውጥ ትግል እንዴት?

ሦስተኛ ዓመቱን የያዘው በጠ/ሚንስትር አብይ አሕመድ የሚመራው “ለውጥ” ብዙ ተቺዎች እንደሚከራከሩት “ከሽፏል” ወይም “ተቀልብሷል” የሚባል አይደለም። የጎሣ አገዛዝ ሥርዓቱን የፈጠረውና ወደ ሦስት አስርተ ዓመታት ለሚጠጋ ዘመን የበላይ ፈላጭ ቆራጭ ኃይል ሆኖ እንደፈለገው ሲጠመዝዘው የነበረው ሕወሐት እርግጥ የበላይነቱን አጥቶ ጥግ ያዥ ሆኗል። ማንም እንደሚያውቀው የፖለቲካ እስረኞች መለቀቅ፣ የአንዳንድ አፋኝ ሕጎች መሻርና ሌሎች መለስተኛ መሻሻሎች ተደርገዋል። በጅምራቸው እነዚህ ለውጦች የኢትዮጵያን ሕዝብ አበረታችና ተስፋ ሰጪ እንደነበሩ አይካድም።

ዳሩ ግን ሕወሐት የፈጠረው ዘር ተኮር የፖለርቲካ ሥርዓት በመሠረቱ እንዳልተቀየረ እውቅ ነው። የቅየራውን ጅምር አመራር የሰጡት ኦሮሞ ወገኖች፣ ጠ/ሚንስትሩን ጨምሮ፣ ሥርዓቱን በተረኛ የበላይነት ጠጋግኖ ለመቆጣጠር እንጂ ለመለወጥ ፍላጎትም እቅድም እንዳልነበራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። በዘር ንቃተ ህሊና ተኮትኩተው ካደጉ ቄሮ የተባሉ ወጣቶች የወያኔ አገዛዝ የደረሰበት “የለውጥ” ግፊትም ዘር ዘለል የፖለቲካ አስተሳሰብ ተጽዕኖ አሳዳሪ የነበረ ሳይሆን ባመዛኙ ራሱ የኦሮሞ ጎሠኝነትን የሚገፋ ንቅናቄ ነበር።   

“የኦሮሚያ” ወገንተኞችና ምሁራን በጠቅላላ የጎሣ አገዛዙን ምሰሶዎች፣ ማለትም ሕገ መንግሥት ተብዬውን እና “ፌደራላዊነቱን” እንዲሁም “ክልላዊነቱን” ከመዋቅራዊ ለውጥ ተከላክለው ቀጣይ ለማድረግ ከመጣር ቦዝነው አያውቁም። ይህ ከአገር ወዳድ ወገኖችና የአንድነት ኃይሎች ጋር ያቃቃራቸው ቀጣይ ጥረት የሕወሐት/ኢሐአዴግ አገዛዝ መንፈስ እና አስተሳሰብ ምንም ያህል እንዳልተለያቸው ያሳያል። የኦነግ/ኦዴፓ/የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አሕመድ አገዛዝ እውነታ ይሄ ነው። በቅርቡ ኢሕአዴግ ብልጽግና የሚል ስያሜ መሰጠቱ ይህን እውነታ አያስክድም። እንዲያውም ብልጽግና የተባለው ፓርቲ “የኦሮሞ” መሆኑንና “የኦሮሞን ጠላቶች ከሥልጣን  ለማባረር የተፈጠረ” መሆኑን ጠ/ሚንስትር አብይ ባለፈው ሰሞን ለባሌ ሽማግሌዎችና ወጣቶች ባደረገው የመላ ኢትዮጵያ መሪነትን የማይመጥን ዲስኩር አድርጓል።    

ባጭሩ እንግዲህ፣ በተረኛው የአብይ/የኦሮሞ የጎሣ ብሔርተኝነት አገዛዝ በሃሳብ ተጸንሶና ታቅዶ በቅጡ ሥራ ላይ የዋለ መሠረታዊ የሥርዓት ለውጥ ጅምር ካልነበረ “ከሸፈ” የሚባለው በእቅጩ ምንድነው? ያልተጀመረ ነገር ከሽፈ ማለት የአመክንዮ ፍቺም ሆነ እውን ትርጉም የለውም። ነባሩ የዘውግ ብሔርተኝነት ሥርዓት በጠ/ሚንስትር አብይ አሕመድ መሪነት ራሱን ከውጥረት ለማውጣትና ቀጣይ ለማድረግ እርግጥ ውስጣዊ የጥገና ቅየራዎችና ማሻሻዮች አክናውኗል። መጤው አገዛዝ ሥርዓተ አልበኝነትና ቀውስ ያልተለየው አዲስ የተረኝነት ሕይወት ራሱ ላይ ዘርቷል። ከዚህ በተረፈ ግን ተቀልብሷል ሊባል የሚችል የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥ በአለፉት ሁለት ወይም ሦስት ዓመታት አልተደረገም፤ እንዲያውም አልተሞከረም።  

ተረኛው የኦሮሞ ብሔርተኝነት አገዛዝ ከነአጫፋሪዎቹ ወደ ሥርዓታዊ ለውጥ የሚወስድ የሽግግር መንግሥት መቋቋምን ሃሳብ እንኳን አጥብቆ ይቃወማል። አገዛዙ የሚፈልገው በሱ የፖለቲካ መረብና “ተፎካካሪ” በሚላቸው ደካማ ወገኖች ጥርቅምና እየተባዙ ባሉ የፓርቲዎች ቅንጅቶች መካከል ያለው የኃይል አሰላለፍ እጅግ በጣም ባልተመጣጠነበትና አገራዊ ሰላምና መረጋጋት በሌለበት ሁኔታ “ምርጫ” የተባለ ተውኔት ሠርቶ “ማሸነፍ” እና ራሱን ላልተወሰን ጊዜ ሥልጣን ላይ ማቆየት ነው። ዘር ተኮር አምባገነናዊነቱን በአስመሳይ አገራዊና ዲሞክራሲያዊ  የምርጫ ጭንብል ለመሸፈን ነው።   

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ለረጅም ጊዜ ከዚህ አምባገነናዊነትን ከተላበሰ የአንድ ፓርቲ ብቸኛ አድራጊ ፈጣሪነት አባዜ መላቀቅ አልቻለም። ከአብዮቱ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ለአስርተ ዓመታት የተጓዝንበት የ“ዲሞክራሲ” እና “ብሔር ነፃ አውጭ” ጎዳና የአገር ውቃቤ የራቀውና በጎ የሃሳብና መርህ መሠረት ወይም ይዘት ኖሮት የማያውቅ ነው። አሁንም የምንዳክረው ከሞላ ጎደል በዚሁ ገጭጋጫ በሆነ የፖለቲካ መንገድ እንደሆነ በየቀኑ በሚከሰቱ የሥርዓተ አልበኝነት ድርጊቶች እያየነው ነው።

ይህ ለዘለቄታው የትም የማይወስድና መውጫ የሌለው አገር ቀዋሽ የፖለቲካ ጎዳና የደርግን “መአከላዊ ዲሞክራሲያዊነት” እና የሕወሐትን “አብዮታዊ ዲሞክራሲ” አቀበትና ቁልቁለት ወጥቶና ወርዶ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከባድ ዋጋ አስከፍሎ፣ ንጹሃን ዜጎችን በገፍ ሲገደሉ፣ ሲፈናቀሉና ሲታገቱ ዝምብሎ የሚያይ አገዛዝን የወቅቱ መዳረሻችን አድርጓል። ለዚህ በጣም አስቸጋሪ የፖለቲካ ገጭ ገጭ ጉዞ ነገደ ብዙው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለያዩ ረድፎች ከፍተኛ ዋጋ መክፈሉና ዛሬም እየከፈለ መሆኑ እርግጥ አሳዛኝ ነው። ግን ይበልጥ የሚያሳዝነው ክፍያው በከንቱ መሆኑ ነው፤ ከዋጋ ክፍያው ሕዝቡ ምንም ትርፍ ወይም እሴት አለማግኘቱ፣ ይባስ ብሎም ዋናዉን ማጣቱ፣ ማለትም አገሩን ኢትዮጵያን በሆኑ ያልሆኑ ዘረኛ ወገኖች፣ ኃይሎችና አገዛዞች መነጠቁ ነው ።

ከዚህ የተለመደ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጠንቅ የሆነ ፖለቲካ አዙሪት እንደ አገር ለመውጣትና በእውን የሚሠራ፣ ለመላ የአገሪቱ ዜጎች የሚበጅ፣ ፍትሐዊ ሥርዓት ለመገንባት መሠረታዊ የፖለቲካ ለውጥ ማምጣት ወሳኝ እንደሆነ ለብዙዎቻችን ግልጽ ይመስለኛል። በነገራችን ላይ፣ የአገር ጉዳዮችን በሚመለከት ብዙውን ጊዜ አስተዋይ ትንተናዎችና ትችቶች የሚያቀርበው ፖለቲከኛ ይልቃል ጌትነት ባለፈው ሰሞን በሆነ ሚዲያ “አገር አይፍረስ እንጂ ማንም ይግዛን” ሲል ሰማሁት። ይህን ሲል በአንድ በኩል ኢትዮጵያ ያለችበትን ተስፋ የሚያስቆርጥ ሁኔታና የገጠማትን አስፈሪ የህልውና አደጋ በመረዳት መሰለኝ። በሌላ በኩል ግን እንደ አገር ወዳድ ምሁር እና ፖለቲከኛ የሥርዓት ለውጥ አሳቢነትም አራማጅነትም ሥራውን ተወት አድርጎ ለጎሣ አገዛዙ እጁን የሰጠ መስሎ ታየኝ። ይህ የአገሪቱ ምሁራን/ፖለቲከኞች የሚያሳዩት አዝማሚያ (የአገር መፍረስ ፍራቻና ተስፋ እጥረት) ራሱ አሳዛኝ ነው።

“ማንም” ኢትዮጵያን ሲገዛኮ አገሪቱን በገሃድ፣ በቀጥታና ባንዳፍታ ‘ሳያፈርስ’ ከፋፍሎና አዳክሞ የቁም ሞት ሊያደርስባት ይችላል! ይህ ተቻይ ነገር ብቻ ሳይሆን በእውን የተደረገ ነገር ነው። “ማንም” ሊባሉ የሚችሉት የባንዳዎች ዝርያ ያላቸው ወያኔዎች ኢትዮጵያን በዘር ከፋፍለው ገዢ በመሆን የአገሪቱን ሕይወት ሰጪ ህልውና እና የራስነት ኃይሏንና መንፈሷን ከውስጥ ቦርቡረው በቁሟ እንዳልነበረች አድርገዋታል። በተወሰነ መጠንና መልክ እንደ ቅኝ ገዢ አፍርሰዋታል። ከተረኞች የጎሣ ብሔርተኖች ኦነግና ኦዴፓ ወይም ከነሱ ቢጤ ሊሎች ‘ማንሞች’ በመሠረቱ ምን የተለየ የፖለቲካ እቅድ ተፈጽሚ እንዲሆን ይጠበቃል?

የአገር መናድ አኪያሄድ እንግዲህ አይነት አይነት እንዳለው መዘንጋት የለበትም። ዛሬ አገር እየፈረሰ ያለው እንዳለፈው ጊዜ (የኢትዮጵያ አካል በነበረችው ኤርትራ እንደተደረገው) ብሔር ነፃ አውጪ ተብዬዎች በሚያደርጉት ገሃድና ቀጥታ የመገንጠል እንቅስቃሴ አይደለም። ይልቅስ ፍርሰት እየደረሰ ያለው አገራዊ የመንግሥት ሥልጣንን ባመዛኙ ተቆጣጥረው ከላይና ውስጥ ውስጡን የአገር አንድነትን የሚቀናቀንና የሚንድ የጎሣ ብሔርተኝነት በሚያራምዱ ኃይሎች (በተለይ በተወሰኑ የኦሮሞና ትግሬ ወገኖች) ነው።            

ከባዱ ጥያቄ እነዚህን የተወሰኑ ጎሠኛ ኃይሎች እንደ አገር ተቋቁመን ለመላው ነገደ ብዙ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚበጅ ለውጥ የምናመጣው እንዴት ይሆን የሚል ነው። ጉዳዩን በይበልጥ ትኩረት ለመግለጽ፣ በጎ መስሏቸው ወይም ሳያውቁ ነባሩን/ያለውን የጎሣ ብሔርተኝነት ሁኔታ ለሚደግፉ ወይም ለሚከተሉ ዜጎችና የማኅበረሰቦች አካላት ስለ ሥርዓታዊ ለውጥ አስፈላጊነትና ጠቃሚነት ልናግባባቸው የምንችለው በምን መንገድ ነው? በኤርትራም በትግራይም እንደታየው የለመዱት ፈላጭ ቆራጭ የማንነት የፖለቲካ አኪያሄድ ለዘለቄታው የማያዋጣና ከጥቅሙ ጉዳቱ በጣም ያመዘነ መሆኑን ይረዳሉ። ችግሩን – ሽብሩን፣ ቀውሱን፣ የሕይውትና ንብረት ጥፋቱን፣ የሕዝብ መፈናቀሉን፣ ሙስናውንና ጠቅላላ ሥርዓተ አልበኝነቱን በአይናቸው እያዩት ነው።

ታዲይ ይህን የሕዝብ ትዝብት አጠናክሮና አስፋፍቶ የአገሪቱ ዜጎችና ባህላዊ ማኅበረሰቦች ታማኝነታቸውን ወደ ተረጋጋ፣ ሰላማዊ ኢትዮጵያዊ አብሮነት እንዲያዛውሩ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ይሆን? አገራዊነትን ጠንካራ መሠረቱ ያደርገ ዘላቂ፣ ዘር ዘለል፣ ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት ግንባታ ደጋፊና ተባባሪ እንዲሆኑ ዜጎችንና የባህል ማኅበረሰቦችን መቀስቀስና ማነሳሳት የሚቻለው እንዴት ነው?

ከቻሉ ከኢትዮጵያ ውጪ (አገሪቱን አካቶ አፍርሰው)፣ ካልሆነላቸው ደግሞ በኢትዮጵያ መልክዓ ምድር ላይ ዘር ተኮር ቅርጽና ይዘት ያላቸው “አገሮች” (“ኦሮሚያ”፣ “የትግራይ ሪፑብሊክ”) መፍጠር ምንጊዜም ምኞታቸው የሆነ ጎሠኛ ብሔርተኞችን ዘር ዘለል የኢትዮጲያዊ አብሮነት አቅጣጫ እንዲይዙ በምክንያታዊ ክርክር ማግባባት በጣም አስቸጋሪ ነው። በተለይ “ፌደራላዊም” ሆነ “ክልላዊ” የተባለ የመንግሥት ኃይል በአመዛኙ ከጃቸው ከገባ በኋላማ ተግባቢነት መቻላቸውም አጠራጣሪ ሆኗል። ወያኔዎችና ኦነጋዊ ወገኖች ከአገር ወዳድ የአንድነት ኃይሎች ጋር በአስመሳይነት ሳይሆን በቀና መንፈስ ተወያዪና ተግባቢ ይሆናሉ ተብለው አይጠበቁም።

እነዚህ ወገኖችና አገዛዞች ለአስርተ አመታት “ተራማጅ” የፖለቲካ ርዕዮት አማኝ በመሆን (በመምሰል?) እና እንደነገሩም ቢሆን ይህንኑ እምነት ዛሬም በመከተል እንደ “ነፃነት”፣ “ዲሞክራሲ፣” እና “እኩልነት” ያሉ ትላልቅ ዓለም አቀፍ ሃሳቦችን ተከታይ ነን ባዮች ናቸው። ታዲያ ይህ ከሆነ ከአንድነትና ዲሞክራሲ ደጋፊ ወገኖች ጋር በሃሳቦች መስክ ሰፋና ጠለቅ ያለ ክርክር፣ ውይይትና ድርድር ውስጥ ይገባሉ ብለን የማንጠብቀው ለምንድን ነው? ለዚህ ጥያቄ ባጭሩ ሁለት የተያያዙ ዋና መልሶች መስጠት ይቻላል፤ አንዱ ምላሽ የፖለቲካ ርዕዮትን ውይም አስተሳሰብን ጣጣ የሚመለከት ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ የፖለቲካ ስነልቦና  ችግርን አመላካች ነው።

ከርዕዮት አንጻር የችግሩ ምንጭ ወይም ምክንያት የዘውግ ብሔርተኞች ሃሳቦች አያያዝና አፈጻጸም ውስንነት ነው። የጎሣ ብሔርተኞች/አገዛዞች ሃሳቦች አያያዝ ለፍሬያማ አገራዊ ክርክር፣ ድርድርና መግባባት ወይም ስምምነት ምንም ያህል ሊከፈት አይችልም፤ ምክንያቱም ሃሳቦቹ በብቸኝነት የብሔርተኛ ማንነት ወይም ራስነት መቅረጫ፣ መግለጫና ማረጋገጫ በመሆን በዝጉ እንደ ርዕዮታዊ መሣሪያ የሚያገለግሉ ናቸው። የሃሳቦቹ ይዘት ወይም ትርጉም ከሆነ የፓርቲ መዋቅርና ቀኖና ውጪ ምንም ያህል ለጥያቄና ድርድር ክፍት ሊሆን ወይም ለአገር አንድነትና ድህንነት በሚበጅ መልክ ሊተረጎምና ሥራ ላይ ሊውል አይችልም።

ለምሳሌ በኢሕአግ ውስጥ ተካቶ የነበረው “ሞክራሲ” ከግንባሩ የዘውግ ውቅርና አሠራር አልፎ በሰፊ አገራዊ ዲስኩርና ተቋማዊ ሥርዓት በጎ ፍቺ ሊሰጠው ወይም ሊሻሻልና ሊዳብር የሚችል ጽንሰሃሳባዊም ሆን መርሃዊ ይዘት ፈጽሞ አልነበረውም። ግልብ ጎሠኝነት፣ ብቸኛ ወገንተኝነትና አምባገነናዊ አገዛዝን የሚያራምድ ሕወሐታዊ፟-ኢሕአዴጋዊ የርዕዮት ፎርሙላ ነበር። ከዚህም ከዚያም የተለቃቀሙ ሃሳቦችንና አመሳሰሎችን እንደነገሩ ያካተተው የጠ/ሚንስትር አብይ የ“መደምር” እና የ“ብልጽግና” (ፓርቲ) አስተያየትም እንዲሁ በመፈክራዊ አቀራረጹና አቀራረቡ ሰፋና ጠለቅ ካለ አገር አቀፍ ተመን ወይም አጣሪ ክርክርና የሃሳቦች ልውውጥ በመሥረቱ ‘የተከለለ’ ፎርሙላዊ ዝግነትና ውስንነት ያሳያል።

በዘር ዘለል መሠረታዊ የአገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የዘውግ ብሔርተኞችንና አገዛዞችን በክርክር ለማግባባት አዳጋችነት ሁለተኛውና ተያያዡ ምክንያት እንደጠቆምኩት የፖለቲካ ስነልቦና ጣጣ ነው። በተወሰኑ ኦሮሞና ትግሬ ሊህቃን መካከል አንዱ የዘውግ ብሔርተኝነት ምሰሶ ፋሺስታዊም ኮምኒስታዊም (እስታሊናዊ) ፍልቀት ያለው ርዕዮት ሲሆን ሌላው ዋና ምሰሶው ደግሞ ከተወላገደ የኢትዮጵያ ታሪክ አተያይ ወይም ትርክት የመነጨና አማራ ማኅበረብ ላይ ያተኮረ የማያባራ የቅሬታና ቅያሜ ስሜት ነው።

ቀድሞ በተማሪው ንቅናቄ ዘመን ጀምሮ በአብዮቱና ድህረ አብዮቱ ረጅም ጊዜ የተስፋፋው የሊህቃኑ ኢምክንያታዊ አማራ ጠልነት በሂደት ለሕወሐት እና ኦነግ ብሔርተኝነት ቅርጽና ይዘት ሰጪ እንደሆነ ብዙ የማያከራክር ሐቅ ይመስለኛል። በተጎጅነትና ቅሬታ ስሜት የተዋጠው ይህ ‘ራስን በራስ’ አለያይ ወይም አተያይ የጎሣ ብሔርተኞች ለሚያሳዩት በምክንያታዊ ክርክር ተግባቢ መሆን ካለመፍቀድ ወይም ካለመቻል ጋር ግንኙነት  እንዳለውም መገምት አዳጋች አይደለም።

እዚህ ላይ የምንረዳው እንግዲህ መነሻውንም መዳረሻውንም ኢትዮጵያዊ አብሮነትን ያደረገ አገር አትራፊ የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥ ለማጣት የሚቻለው የዘር ብሔርተኞችን በፖለቲካ ርዕዮት መስክ በሚደረጉ የሃሳቦች ልውውጥና ከልውውጡ በሚገኝ መግባባት እንዳልሆነ ነው። በዚህ መልክ የመግባባት ተስፋ ጨርሶ ከስሟል ማለት አይቻል ይሆናል። ሆኖም በፖለቲካዊና ስልታዊ ስሌት ባልተቃኘ ንጹህ ምክንያታዊነት ለመኖርና አለመኖር አደጋ የተጋለጠ አገርንም ሆነ ማኅበረሰብን ከጥፋት ማዳን አይቻልም። እንዲያውም በዚህ አይነት ንጹህነት “የተቃውሞ” እንቅስቃሴ መቀጠል በታሪክ ሂደት ራስን ጥግ ያዥ ማድረግ ነው። ራስን የስር ነቀል አገራዊ ለውጥ አምጭነት ዕድል ነስቶ የጎሠኛ ኃይሎችን አድራጊ ፈጣሪነትና አጀንዳ ሰጪነት ዝምብሎ መቀበል ነው የሚሆነው። እነዚህ ኃይሎች ምክንያታዊ ሃሳብ ምንም ያህል አይሰርጣቸውም። ለአገራዊ አንድነትን ጥሪ ከልብ የመነጨ አወንታዊ መልስ መስጠት ያለመፈለግ ወይም ያለመቻል አዝማሚያ ተለይቷቸው አያውቅም።  

ሆኖም፣ በለውጥ ትግሉ የፍቅር፣ የጭዋነት፣ የእርቅና የአንድነት እሴቶችን የሚያጎላ ሞራላዊ ዲስኩር በየሚዲያው ብዙውን ጊዜ ይደመጣል። ድስኮራው ራሱ ችግር የለውም። በሞራላዊ ንጹህነት የተቃኘ ንግግር የዘውግ ብሔርተኞችን ለማግባባት መጣሩ ምንም ያህል ተስፋ ያለው ጥረት ባይሆንም መሞከሩ አይጎዳም። በመጠኑም ቢሆን ተግባቢዎችና አማኞች ያፈራ ይሆናል። ነገር ግን ይህ ዲስኩር ከሌሎች አገራዊ-ባህላዊ ድምጾችና እሴቶች (ለምሳሌ ከነፍጠኛነትና እና ከቆራጥ አገር ጠባቂነት) ጸድቶ ወይም ተለይቶ በንጹህ ሞራላዊ ይዘት አይሠራም፤ ተጨባጭ ትርጉም ወይም ዉጤት ሊኖረው አይችልም። አገር ወዳድ ጀግንነትና ጭዋነትን አብረው ይሄዳሉ፤ ለአገር አንድነት ታጋይ ነፍጠኞች ጎሣ ሳይለዩ ቢጤዎቻቸው ኢትዮጵያዊያንን በፍቅር አቃፊ መሆን ልምዳቸው ነው። ግድ ሲል ደግሞ የአገር ሰላምና ደህንነት ለማስከበር ሰይፍ መዘው ከውስጥም ሆነ ከውጭ ጠላት ጋር ከመፋልም ወደኋላ አይሉም። አገር ለመጠበቅ ሲንቅሳቀሱ መንፈሳዊነታቸው ወይም ሞራላዊነታቸው ተጨባጭ ስልታዊ ትግላቸውን ያጠናክረዋል ኢንጅ አይተካውም።    

የተናጠል ሞራላዊንትን መንገድ ስንከተል ብዙውን ጊዜ ተጨባጭ አገር ውዳድ ድርጊቶች አንፈጽምም፤ ምንም እርምጃ ባለመውሰዳችን ደግሞ ማንንም የሚጎዳ ወይም የሚያስቀይም ነገር አናደርግም በሚል ‘የፖለቲካ ትክክለኛነት’ ሃሳብ እንመራ ይሆናል። ነገር ግን ከተንቀሳቃሽነትና አድራጊነት ወድኋላ ማፈግፈግ በተለይ ራስን (እንደ ማኅበርሰብም ሆነ እንደ አገር) የባሰ ጎጂ ሊሆን ይችላል። በይበልጥ አስጊነት ራስን ለጅምላ ሰው ጭፍጨፋ ወይም የዘር ማጽዳት ጥቃት ያጋልጣል፤ ከማጋለጥ አልፎም ጥቃቱን በእውን ሊጭር ይችላል። የጨለመ የጥፋት ደመና እላያችን ላይ ሲያንዣብብን ምንም ሳናደርግ ቁጭ ብሎ ማየት ወይም ለደመኞቻችን ደካማ ሆነንም ይሁን መስለን መታየት ለማኅበረሰባዊና አገራዊ ደህንነታችን በጣም አደገኛ ነው፤ አስከፊ ጥቃት ይጋብዛልና።   

ሞራላዊ ንጹህነት የሆነ አንድምታ አለው፣ የአገር ማዳን ትግል በጎ የሆነ ውጤት ብቻ ማፍራቱን የማረጋገጥና ተግሉ ሲኪያሄድ ማንኛውም ወገን ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ወይም ንጹሃን ላይ ችግር እንዳይፈጠር ዋስትና የመፈለግ አንድምታ። ነገር ግን በእውን አገራዊ የለውጥ ንቅናቄ ውስጥ እንደዚህ አይነት ኢታሪካዊ እርግጠኛነት ወይም ዋስትና ሊኖር አይችልም። በእቅድም ባይሆን በጎንዮሽ ዉጤቱ ንቅናቄው በማንኛውም ወገን ተፈላጊ ያልሆነ ምንም ነገር አያስከትልም ብሎ ማረጋገጥ አይቻልም። መሳሳት በኑሮም ሆነ በከባድ የአገር አድን ትግል አየቀሬ ነው፤ ያለን አማርጭ ንጹሃን ላይ ጉዳት እንዳናደርስ አካቶ አለመታገል ሳይሆን አልፎ አልፎ የሚከሰቱ የተወሰኑ ችግሮችን እንዳመጣጣቸው መፍታት፣ እንዳይደገሙም ጥረት ማድረግ ብቻ ነው። ዘረኝነት አስወጋጅና አገር አትራፊ ትግል ማኪያሄድ ማለትም ይኸው ነው፤ አኪያሄዱ እንከን የለሽና አልጋ ባልጋ ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም።         

እንግዲህ እንደ አገር የምንፈልገውን እና የሚበጀንን ለውጥ ለማምጣት በተለያዩ የንቅናቄ መስኮች – ሃሳቦችንና ምክንያታዊ ክርክሮችን ጨምሮ ግን እነዚህን ተሻግሮ ፟– የተለያዩ የእንቅስቃሴ ዘዴዎችና መላዎች አቀናብሮ መጠቀምን ይጠይቃል ። በአገር ጉዳዮች በቀና መንፈስ ውይይትና ድርደር ማድረግ የማይፈቅድ ወይም የማይችል የዘረኛ ብሔርተኝነት አገዛዝን ለዘለቄታው ተቋቁሞ መወጣት የምናመልጠው ትግል አይመስለኝም። በዚህ ከባድ፣ ትውልድ ዘለል የአገር ህልውና ትግል እንደሁኔታው አስፈላጊ የሆኑ ምንገዶችንናመሣሪያዎችን ሁሉ መጠቀም ግድ ይላል።

ከነዚህ መሣሪያዎች አንዱ የኢትዮጵያዊ አብሮነትንና አንድነትን መልዕክት በቀጣይነት ለሕዝብ አድራሽ በሆኑ የስርጭት፣ የማስፍፋትና የማራባት ዘዴዎች ከማስተላለፍ አለመቦዘን ነው። ይህ ሊደረግ የሚችለው ደግሞ የአገር አንድነት ኃይሎቻና ዲሞክራሲ ደጋፊ ወገኖች በቂ የመልዕክት መግለጫና ማሰራጫ አቅሞች፣ ማለትም ታክቲካዊ ንግግሮችና ክርክሮች በውጤት የሚሰራጩባቸው መገናኛ ብዙሃን ወይም የሚዲያ አውታሮች፣ ሲኖሩ ነው። በዚህ መንገድ ሕዝብ የመስበክ፣ የማስተማርና የማንቃት ጥረት ብዙውን ጊዜ የፕሮፓጋንዳ  ሥራ ይባላል። አባባሉ ትክክል ነው፤ ሆኖም ስለ ትርጉሙና አጠቃቀሙ ግልጽ መሆን አለብን።

ፕሮፓጋንዳ በተለምዶ ፍቺው ወይም አረዳዱ ሃሰት ወሬ ከመንዛት ጋር ይያያዛል። ግን ትርጉሙ በዚህ አሉታዊ አገላልጽ አይወሰንም። በፖለቲካ ትግል አውድ ርዕዮታዊ ወይም ሃሳባዊ ይዘት ያላቸውን መልዕክቶች በስልት ለሕዝብ ማስተላለፍን የሚመለከት ፍቺ ያለው መሆኑም መዘንጋት የለበትም። የኢትዮጵያን ሕዝብ በአንድነትና በመዋቅራቂ ለውጥ ዙሪያ ማግባባት የሚቻለው ዝምብሎ ረቂቅ የፖለቲካ ሃሳቦች ለማዛመት በመሞከር ሳይሆን ሃሳቦቹን ከአገራዊና ባህላዊ እሴቶች፣ ምስሎች፣ ስሜቶች፣ ልምዶችና የሕዝብ ትግሎች ጋር በማዛመድ ወይም በማያያዝ ነው።

ይህን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ ባመዛኙ ስነልቦናዊ ስለት ባለው የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ወይም የፕሮፓጋንዳ  እንቅስቃሴ እንደሆነ እንረዳለን። የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ወይም ስብከት ዜጎችንና ማኅበረሰቦችን በአገር ጉዳዮች መሠረተ ዕውቀት አንጾ የማነሳሳት እምቅ ኃይል አለው፤ የተወሳሰቡ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ሊያቃልልና ለሕዝብ ይበልጥ ተደራሽ ሊያደርግ ይችላል። ስለዚህ ጥልቅ የመዋቅር ለውጥን በሚመለከት ምክንያታዊ ክርክሮችና ተጨባጭ እውቀት እያዳበርንም ቢሆን የፖለቲካ ስብከት ማኪያሄዱ አስፈላጊም ጠቃሚም እንደሆነ እንረዳለን።

በመጨርሻ፣ ዘረኝነትን ፈንቅሎ ከጎሣ ብሔረተኝነት አገዛዝ ቅየራ ባሻገር ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚበጅ ዘላቂ ሥርዓታዊ ለውጥ ለማምጣት መሟላት ያለባቸው ሁለት ዋና ሁኔታዎች ይታዩኛል። አንዱ በጽንሳዊ ሃሳብ መስክ በመንቀሳቀስ የዘውግ ብሔርተኝነትን የፖለቲካ ርዕዮት ድንበሮች ጥሶ (በጣጥሶ) መውጣት ነው። የአስተሳሰብ ክልሎችን እና ኬላዎችን ጥሎ ማለፍ ግድ ይላል። ይህ እንቅስቃሴ በተለይ የነገደ ብዙ አገር ወዳድ ምሁራንን ጥረት የሚመለከት ቢሆንም ለምሁራን በመኖፖል የተያዘ ሥራ አይደለም፤ በሰፊው ዜጎችና ማኅበረሰቦች በተለያዩ ባህላዊና አካባባዊ አቅሞች ሊሳተፉበት ይችላሉ።

በፖለቲካ ሃሳብ ሜዳ መደረግ ያለበት እንቅስቃሴ ነባሩን (ያለውን) የዘረኝነት ርዕዮት ከመተቸት፣ ከመንቀፍና ከማስወገድ አልፎ አዲስ፣ አማራጭ፣ አስተሳሰብ አርቅቆ ማውጣትን ይጠይቃል። ይህ የፈጠራ ሥራ አካቶ ያልነበሩ ወይም የማይታወቁ ሃሳቦች ለማፍለቅ የሚሞክር ሳይሆን በኢትዮጵያ የአብዮተኝነት ልምድ በባዶ ድስኮራ ይዘት የለሽ የአነጋገር ዘይቤ ብቻ ሆነው የቀሩ የጽንስሃሳብ ፈርጆችን (ለምሳሌ “ዲሞክራሲን”፣ “ሕገ መንግሥትን” እና “ፈደራላዊነትን”) በይበልጥ ትርጉም አዘልና ተፈጻሚ በማድረግ መልሶ የሚቀርጽ ነው። ከሥርዓታዊ ለውጥ አኳያ መልሶ ቀረጻው የሚያተኩረው ተናጠል ሃሳቦች ላይ ሳይሆን በጠቅላላ በፖለቲካ ርዕዮት ፓራዳይም ወይም የሃሳቦች ውቅር ዙሪያ (ፋሽስታዊ እና/ወይም ስታሊናዊ አስተሳሰብ) መሆኑም መዘንጋት የለበትም።

የሚፈለገውን መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት መሟላት ያለበት ሁለተኛው የትግል ሁኔታ ደግሞ የለውጡ አድራጊ ፈጣሪዎች ሊኖራቸው የሚችልና የሚገባ ተባብሮ የመንቀሳቀስ መንፈስና በጋራ ትግሉ ዙሪያ ተጓዳኝ የመሆን ፈቃደኝነትና ችሎታ ነው። ይህ ደግሞ የራስን (ግለሰባዊም ሆነ ድርጅትዊ) ሃሳብ፣ አቋምና እንቅስቃሴ ለጋራ አገራዊ አላማና ትብብር በሥርዓት ተገዥ ማድረግን ይጠይቃል። ድር ቢያብር አንበሳ ያስር እንዲሉ።

ይህን ማድረግ ለማንም አገር ወዳድ ዜጋ ወይም ስብስብ ቀላል አይደለም፣ በተለይ ጠባብ የማንነት ፖለቲካና ብቸኛ ወገንተኝነት በተንሰራፋባት የዛሬቱ ኢትዮጵያ። ብዙ አገር ወዳድ ዜጎች፣ ስብስቦች፣ ምሁራን፣ መንፈሳዊ መሪዎች እና አክቲቪስቶች  የሚፈለገውን አገር አቀፍ መዋቅራዊ ለውጥ የማምጣት አቅማቸውና ተሳትፎዏቸው እስከዛሬ በጣም ውስን ሆኖ የቆየው ይህን የአብሮነትን ሁኔታ በዘላቂነት መፍጠር ባለመቻላቸው ነው። ስለዚህ ውስንነቱን በድርጁ ጽንሳዊ ሃሳብና ስልታዊ ንቅናቄ መወጣቱ የለውጡ ትግለ ወሳኝ መነሻና መንደርደሪያ እርምጃ ነው።

tesfayedemmellash@gmail.com   

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
12,856FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

1 COMMENT

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here