spot_img
Monday, June 24, 2024
Homeነፃ አስተያየትበድህነትና በጦርነት የወደመው ጎንደር -ሁሉም ነገር ወረርሽኙን ለመከላክል ይዋል (አክሎግ ቢራራ)

በድህነትና በጦርነት የወደመው ጎንደር -ሁሉም ነገር ወረርሽኙን ለመከላክል ይዋል (አክሎግ ቢራራ)

Aklog-Birara-_-Ethiopia-

አክሎግ ቢራራ (ዶር)

በ March 25, 2014, Al-Jazeera በጥናት ተደግፎ ለዓለም ያሰራጨው ቪዲዮ ይዘት እስካሁን ድረስ በመሬት ላይ የሚታይ የህዝብ ኑሮ ለውጥ እንዲመጣ አላደረገም። ይህ “Amhara region, not only the poorest in Ethiopia but the poorest in the world” ተብሎ የተሰየመው የጥልቅ ድህነት ዶኪውሜንተሪ ለምን የአማራውን ክልል መሪዎችና የፌደራል መንግሥቱን መሪዎች ህሊና አልቀሰቀሰም? መሰረታዊ የሆነ የእድገትና የልማት እንቅስቃሴ ፍትሃዊና ሚዛናዊ በሆነ ደረጃ ለምን አልተጀመረም? በሚል ጥያቄ ሃተታየን እጀምራለሁ።

ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ የፖለቲካ የበላይነቱን ከያዘበት ከ 1991ዓ.ም. ጀምሮ የፌደራሉ መንግሥት መረጃዎች ብቻ ሳይሆን፤ የዓለም ባንክ፤ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅትና ሌሎች መረጃዎች በተደጋጋሚ የሚያሳዩት፤ ድህነት እንደ ቀነሰ፤ ለአስር አመታት እጥፍ ድርብ የእድገት መጠን እንደተካሄደና ፍጹም ድህነት እንደወረደ ነው። ይህን ሃቅ ነው ብየ ልቀበለው። በትምህርትና በሌሎች መሰረተ ልማት መስፈርቶች ኢትዮጵያ እድገት አሳይታለች። ይህ መስፈርት ግን በቂ አይደለም። ፍትህን አያሳይም። ሚዛናዊ እድገት መኖሩን አለመኖሩን አያሳይም።

አልጀዚራ የአማራው ክልል በድህነት መስፈርት–የጤና አገልግሎት፤ የንጹህ ውሃ አቅርቦት፤ የመጸዳጃ፤ የበልቶ ማደር፤ የመጠለያ፤ የመንገድ፤ የኤሌክትሪክ መብራት ስርጭት፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ስርጭት፤ የዘመናዊ እርሻ ሁኔታ፤ የመኖሪያ ቤት ዘመናዊነት ወዘተ በቅርብ ሲመረመር የአማራው ክልል “የተረገመ ሕዝብ” የሚኖርበት አካባቢ እንዲሆን የተፈረደበት ይመስላል። ይህን የምልበትን ምክንያት ላቅርብ። የአማራው ክልል የሰው ኃይል አለው፤ ዝናብ አለው፤ ለም መሬት አለው፤ ወንዞች አሉት፤ እንደ አባይ ያሉ፤ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመርቱና ለመስኖ እርሻዎች አመች የሆኑ ብዙ ወንዞችና ጅረቶች አሉት። ይህ እንዳለ ሆኖ፤ በኤሌክትሪክ መብራት አገልግሎት ብቻ ቢመረመር፤ ከአማራው ክልል የሚመረት ኤሌክትሪክ የአማራውን ሕዝብ አልፎ እንዲሄድ፤ አማራው የበይ ተመልካች እንዲሆን ተደርጓል። ሰባ በመቶ የሚሆነው የጎንደር ህዝብ ኤሌክትሪካ መብራት የለውም።

አልጀዚራ ያቀረበውን አንድ በንጽህና አገልጎሎት ሊፈታ የሚችል የትራኮማ በሽታን ተግዳሮት ስመለከት ይህ የሚዘገንን በሽታና የፖሊሲና የፕሮግራም ግድፈት ለምን ተከሰተ? የሚለውን ጥያቄ አቀርባለሁ። ለዚህ ጥያቄ መነሻየ፤ ዛሬ የዓለምን ሕዝብ ኑሮና ህይወት ሙሉ በሙሉ ያናጋው COVID-19 ስርጭት ነው። ይህ ወረርሽኝ በተለየ ደረጃ የሚያጠቃው ማንን ነው? በ አሜሪካ ከተማዎች፤ ለምሳሌ በችካጎና በኒውዮርክ በወረርሽኙ ምክንያት የሞቱትን ሰዎች ተመልክቶ የተደረጉ ዘገባዎች የሚያሳዩት ገጽታ አሳሳቢ ነው። የገቢ መጠናቸው ዝቅተኛ፤ የጤና አገልግሎት መድህን የሌላቸው፤ ለክፉ ቀን የሚሆን ገንዘብ በባንክ የሌላቸው፤ ከስራቸው ታግበው በቤታቸው ለመቀመጥ የማይችሉ፤ ኢንተርኔት ተጠቅመው ስራ ለመስራት የማይችሉ፤ በአብዛኛው የአገልግሎት ሰራተኞች ግለሰቦችና ቤተሰቦች በአሰቃቂ ደረጃ ይታመማሉ፤ ይሞታሉ። ለምሳሌ፤ ሰላሳ በመቶ የሚገመት አፍሪካዊ አሜሪካኖች በሚኖሩባት በችካጎ ሰባ በመቶ የሚሆኑት ሟቾች ጥቁር አሜሪካኖች ናቸው። ዘረኝነት፤ ድህነትና እልቂት ተያያዙ ማለት ነው። ዘረኝነት ድህነትን ያመጣል።

ይህ ኢ-ፍትሃዊ የሆነ እልቂት የተከሰተበትን አገር አናስበው። በዓለም የዲሞክራሲ፤ የነጻና የፉክክር ገበያ፤ የሳይንስና የቴክኖሎጂ፤ የህክምና ባለሟያዎች ተቋማት፤ የመሳሪያ ክምችት ብዛት ወዘተ መሪ ሃገር የሆነችው አሜሪካ ለወረርሽኙ በሽታ ተከላካይ መሳሪያዎችን በገፍ ለማምረትና የዜጎቿን ህይወት ለመታደግ አልቻለችም። በኮቪድ-19 የተበከለው የሕዝብ ብዛት የሚኖረው አሜሪካ ነው፤ የሞተው ብዛት የሚገኘው አሜሪካ ነው፤ በገፍ የሚሞተው ጥቁርና ሂስፓኒክ አሜሪካዊ ነው።

ይህ ሁኔታ ወደ አገሬ ኢትዮጵያና ወደ ተወለድኩበት አካባቢ ወደ ጎንደር እንዳተኩር ያስገድደኛል። አገር አቀፍ የሆነ ቅድመ ዝግጅትና የመከላከል ምህዳር ካልተዘረጋ የወረርሽኙ ተጠቂ ማን ይሆናል? በአዲስ አበባ የተጀመረው ዝግጅት ጥሩ ነው።መጀመሪያ ከታች ወዳጀና አርቲስቱ፤ ፕሮፌሰር አቻምየለህ ደበላ፤ የዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት የተባለውድርጅታችን የቦርድ አባል ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አገልግሎት እንዲውል ያቀረበው ስእል እንደሚያመለክተው መጀመሪያ ራሱን ከእልቂቱ ለማዳን፤ ሕዝቡ ማህበረሰባዊ መራራቅን (Social Distancing)፤እጅን ቢቻል በሳሙና መታጠብን፤  ካልተቻለ እንዶድና ተመሳሳዮችን መጠቀምን፤ በየአካባቢው ቴስቲንግ ማካሄድን፤

የገበያውን ሁኔታ አስተካክሎ ሕዝብ በማይጨናነቅበት ሁኔታ ማካሄድን፤ ቢቻል፤ በያካባቢው የክልልና የፌደራል ፖሊስ፤ ልዩ ኃይል፤ ሰራተኞችና ባለሥልጣናት በሙሉ ወዘተ ተደጋግፈው ምግብ ለዜጎች በየቤታቸው ለማሰራጨት መሞከርን ፕሮግራሞችና አማራጮች ማስተናገዱ ይጠቅማል።

አንዳንድ ተመልካቾች እንደሚገምቱት ከሆነ በጥቁር አፍሪካ እስከሚቀጥለው ሰኔ መጨረሻ .. . 16.3 ሚሊየን  የሚገመት ህዝብ በወረርሽኙ ይበከላል። ከዚህ ግምት ውስጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ ድርሻ ምን ያህል ይሆናል? የሚለውን ለማወቅ የሚቻልበት መረጃ የለኝም። ቁም ነገሩ ግን ትኩረትና ቅድሚያ የሚሰጠው አስኳል ጉዳይ ወረርሽኙን መከላከልና የዜጎችን ህይወት መታደግ ነው።

ሰብአዊ መብትና የኮቫድ-19 ተግዳሮት

የጤና አገልግሎት ማግኘት ሰብአዊ መብት ነው። ወረርሽኙን መከላከል ከሰብአዊ መብት ጋር የተያያዘ የጤና አገልግሎት አቅርቦት አቅምና ቅንጅት ጉዳይ ነው። ከመንደር ጀምሮ እስከ አገር ድረስ ይህን የማድረግ ግዴታው የፌደራሉ መንግሥት ነው። ክልሎች ብቻቸውን አቅም የላቸውም። አቅም የላቸውም የምልበትን ምክንያት የጎንደርን የተለየ ሁኔታ በማሳየት ትንተናየን ላቅርብ።

አልጀዚራ ወዳቀረበው ዘገባ ስመለስ፤ የአማራው ክልል፤ በተለይ ጎንደር መጸዳጃ፤ ንጹህ ውሃ፤ የኤሌክትሪክ መብራት አገልግሎት፤ ዘመናዊ መንገድ፤ የጤና አገልግሎት ጣቢያዎች፤ ለወጣቱ ትውልድ የስራ እድል የሚፈጥሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮችና ኢንዱስትሪዎች፤ ከጭቃ ቤት ያለፈ ዘመናዊ ቤት ለመስራት የሚያስችል የጡብና የስሚንቶ ፋብሪካ ወዘተ የሌለው ክፍለ ሃገር ነው።

ከጥቂት አመታት በፊት በአማራው ክልል የእናቶችንና የወጣቶችን የጤና ሁኔታ ያደረገ ጥናት የሚከተለውን መረጃዎች አቅርቦ ነበር፤ ሁኔታው የዚህን ያህል አለመለወጡን የጎንደርን አካባቢ የጎበኙ ግለሰቦችና ባለሞያዎች ነግረውኛል።

 • የእናቶችና የህጻናት ምግብ እጦት የጎንደርን ድህነት ስፋትና ጥልቀት አባብሶታል። በ 2009 መጨረሻ እ. አ. አ. 24 በመቶ ለሚሆኑት ህጻናት ሞት ዋና ምክንያት የምግብ እጦት ነበር። ይህ እጥረት የኢትዮጵያን ጠቅላላ የአመት ገቢ 16 በመቶ በሚገመት ቀንሶታል።
 • አምሳ አራት (54) በመቶ የሚሆኑት የአማራ ክልል ሴቶች የትምህርት እድል አያገኙም። ስለማያገኙ የኢኮኖሚ አማራጫቸው ከእጅ ወደ አፍ ብቻ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት እድል የሚያገኙት ሴቶች 28 በመቶ ናቸው። የሁለተኛ ደረጃ የትምህርት እድል የሚያገኙት የአማራ ሕዝብ አባላት 13 በመቶ ይገመታል። የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ተሳታፊዎች የሚማሩት በጠለላ ነው። 
 • የትምህርት እድል የሌለው ሕዝብ ለድህነት ይዳረጋል።
 • በጎንደር ክፍለ ሃገር የኢንዱስትሪው ሁኔታ ዝቅተኛ ነው ሊባልም አይችልም፤ የለም ቢባል ይመረጣል።

ኢትዮጵያ በነበርኩበት ወቅት፤ በተለይ፤ የንግድ ባንክ ዋና ስራ አስክያጅ ሆኘ ሳገልግል ትዝ የሚለኝ፤ በጎንደር ከተማ አንድ የጥጥ ማዳመጫ ፋብሪካ ነበር። ሊዘጋ ነው ተብሎ ተነገረኝ፤ የደርግን ባለሥልጣናት አማክሬ የንግድ ባንክ ብድር እንዲሰጥ አድርጌ ነበር። ይህ ትንሽ ፋብሪካ ሳይዘጋ ቀረ። ከዚያ በፊት፤ በኋላና ዛሬም ስከታተል፤ ሌላው ቀርቶ ጣልያኖች የሰሯቸው ህንጻዎች፤ ሕዝቡ የሰራቸው ታላላቅ ገዳማትና ቅርሶች በመፈራረስ ላይ ይገኛሉ የሚሉ የአይን ምስክሮች አሉ። ብዙ የጎንደር ህጻናትና ጎልማሶች የሚማሩት በዳስና ከእንጨት በተሰራ ጠለላ ነው። ወጣት ሴቶች ምግብ የሚያበስሉት ኩበት ለቅመው፤ ቢገኝ እንጨት ሰብስበው ነው። ሁለቱንም ለማግኘትና ተሸክመው ወደ ቤት ለመውሰድ ይቸገራሉ። አንዳንድ አካባቢዎች ከብት፤ በቅሎና ሌላ እንስሳ እንዳይሰረቅ በመስጋት ከሰው ጋር አብረው ቤት ውስጥ ያድራሉ።

ውሃ ብርቅ ነው። ነዋሪዎች የሚጠጡት ውሃ የተበከለ ነው። ብዙ ህጻናት በረሃብ እየተሰቃዩ ይሞታሉ፤ ካልሞቱም እድገታቸው ይበከላል (Stunted growth). በያመቱ፤ ብዙ መቶ እናቶች የወሊድ አገልግሎት ስለማያገኙ ለሞት ይዳረጋሉ። በ 1990ወቹ የመጨረሻ አመታትና ከዚያ በኋላ፤ የአሜሪካ መንግሥትና ዓለም ባንክ ለህክምና ይሰጧቸው የነበሩት እርዳታዎች ለአማራው ክልል በጠቅላላ፤ በተለይ ለጎንደር ክፍለ ሃገር ሊደርሱለት ያለመቻላቸው ምክንያት ጥናትና ምርምር ይጠይቃል። ፕሬዘደንት ጆርጅ ቡሽ ኤች አይ ቢ ኤድስን ለማጥፋት የለገሱት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት ድጋፍ ለምን ለአማራው ሕዝብ፤ በተለይ በበሽታው ለተጠቃው ለጎንደር ሕዝብ አልተሰጠም?

የጎጃምና የጎንደር ሕዝብ በወባና በኮሌራ በሽታ በገፍ ሲሰቃይና ሲሞት ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ ለምን ቸል አለው? በወቅቱ የጤና ጥበቃ ሚንስትር የነበረው ዶር ቴዎድሮስ አድሃኖም ይህን ሕዝብ ለምን የውጭ እርዳታው ተጠቃሚ እንዳይሆን ከለከለው? ያ ግዙፍ የውጭ እርዳታ ወደ ማን ተላከ? በማን ተማረከ?

የትራኮማ በሽታ በቀላሉ የሚወገድበት እድል ነበር። ግን ችላ ተብሎ እንደ ነበር መረጃዎች አሉ። ይህ ከድህነትና ከኑሮ ጋር የተያያዘ በሽታ እንዳይቀረፍ የተደረገበት ለአበዳሪዎችና ለለጋሶች ግልጽ ሳይሆን እስካሁን የቆየበት ምክንያት ምንድን ነው? የትራኮማ በሽታ ለአይነ-ስውራን ብዛት መነሻ መሆኑን፤ አልጀዚራ በ 2014 ዘግቦት ነበር። ይህ በሽታ ለምን አልተቀረፈም? ብየ ራሴን ስጠይቅ የማገኘው መልስ አንድ ብቻ ነው። የአማራውን ሕዝብ ለመጉዳት፤ ቢቻል በሚኖርበት ሁሉ እንዲሰቃይ ለማድረግ ነው። ድህነት ቀንሷል ብሎ መለፍለፈ ቀላል ነው የምልበት ዋና ምክንያት፤ ቅነሳው ዘውግ ተኮር ስለሆነ ጭምር ነው።

ባለሥልጣናት የሚሉትን ብቻ መቀበል አልችልም። የድህነት ቅነሳው ትርክት፤ ልክ ሰላምና እርጋታ፤ ዲሞክራሳዊ መብትና እንደልብ መናገር ይቻላል ተብሎ እንደሚነገረው ለፈፋ ነው። ሰላም ለማን፤ እርጋታ ለማን፤ ዲሞክራሲ ለማን፤ ድህነት ቅነሳ ለማን? ብሎ የመጠየቅ ሃላፊነት አለብን። በሌላ አነጋገር፤ ድህነት መቀነሱን እቀበልና፤ በመሬት ላይ የሚታየው የድህነት ቀረፋው አንዱ መስፈርት ግን ትራኮማ፤ የወባና የኮሎራ በሽታ ወዘተ ሙሉ በሙሉ ሲቀረፉ ነው። ሌላው መስፈርት በልቶ ማደር ሲቻል ነው። ሌላው ኩበት ለቅሞ፤ ጭራሮ ሰብስቦና ተሸክሞ ምግብ ከማብሰል በመሸጋገር በኤሌክትሪክ ለመጠቀም ሲቻል ነው፤ ያውም ከአካባቢው የወንዝ ግድቦች ከሚገኝ ኃይል።

እኔ ከማስታውሰው ብቻ ብነሳ፤ ኢትዮጵያ ተመልሸ አገሬን ሳገለግል ትዝ የሚለኝ ጎንደርና የጎንደር ከተማ፤ ደብረ ታቦር፤ ጋይንት ወዘተ የጦር መናኸርያ፤ የመጣና የሄደውን ሁሉ የሚያስተናግድ ሕዝብ የሚኖርበት ጨዋና መንፈሳዊ ሕዝብ የሚኖርበት፤ ካለችው ቆርሶ ለሌላው የሚሰጥ ሕዝብ ያለበት አካባቢና ሕዝብ እንደ ነበር ነው። ኢህአፓ፤ ብአዴን ወይንም የብአዴን አባትና ፈጣሪ፤ ኢድህ፤ ሻብያ፤ ኦነግ፤ ግ-7 እና ሌሎች የሚገቡበትና የሚወጡበት ክፍለ ሃገር ነበር።  የሱዳንን ዳር ድንበርና ጠረፍ በራሱ አቅም የሚያስከብር ሕዝብ ነበር። ይህ አካባቢ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ክብርና ነጻነት ደጀን ሆኖ ሞቷል፤ መስዋእት ከፍሏል። ባለውለታው ሊሆን የሚገባው የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ለጎንደር ክፍለ ሃገር በእድገትና በልማት መስፈርት ያደረገለን ነገር ፈልጌ ላገኘው አልቻልኩም።

የግብጽ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ያነጻጸረው ግፍ፤ በደል፤ ሰርጎ ገቦችን እየላከ ግድያዎችና ህውከቶችን መፍጠር፤ የጦርነት ፖሮፓጋንዳ በሰፊው ማካሄድ፤ በሃሰት የተመረዘ መረጃ ማሰራጨት ቀጥሏል። አንዱ መግቢያ ወንፊት የጎንደር ክፍለ ሃገር ነው። የጦፈው የድንበር ጉዳይ ሙግት ሲካሄድ የቆየው በዚህ አካብቢ ነው። ከጅርባ ሆነው ግብጾችንና የኢትዮጵያ ለም መሬት ለኛ ይገባናል የሚሉ ኃይሎችን በአንደኛ ደረጃ የሚደግፍ ህወሓት ነው። ጎንደሬው በጎንደሬ ላይ እንዲነሳ ያደረገው ህወሓት ነው። ቅማንቱን አስለጥኖ ወንድሞቹን፤ ሌሎቹን ጎንደረዎች እንዲገድል ያደረገው ህወሓት ነው። ጃዋር ሞሃመድም ድርሻውን ሲያበረክት ቆይቷል፤ አሁንም የሁከት አጋር ቢሆን አይደንቀኝም። ወሎ የኦሮሞ አካል ነው የሚሉትስ?

ባለፉት ሳምንታት፤ የሱዳን ወታደሮች ዳር ጥሰው ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው ሲወራ ቆይቷል። እኔ የምጠይቀው፤ ሱዳን በአንድ በኩል ኢትዮጵያ የሕዳሴን ግድብ የመገደብ መብት አላት ብላ ከኢትዮጵያ ጋር መቆሟን ይፋ ካደረገች በኋላ ማን ከጀርባ ሆኖ ወትውቷት ነው? ወታደሯን አስገብታ የተነጠቅሁትን መሬት ኢትዮጵያ ትመልስ? የምትለው። ግብጾችና ህወሓት እንዳሉበት እገምታለሁ። 

ይህን ለማለት ያስገደደኝ፤ ባለፈው እሁድ April 12, 2020 “Al-Fashqa Returns to Sudanese Sovereignty After Agreement With Ethiopia” በሚል ርእስ፤ አህመድ ዩኒስ የተባለ ጋዜጠኛ የጻፈው ነው።

“The years-long border conflict between Ethiopia and Sudan is expected to end with the return of the disputed Al-Fashaqa region to Sudanese sovereignty within two weeks. The two countries took practical steps to start the processes of demarcating borders. These steps included setting up border markers and withdrawing forces to behind the separation line. According to sources, who requested anonymity, the Ethiopian Chief of the General Staff General Adem Mohammed has discussed with Sudanese officials an action plan which sees the forces of each of Sudan and Ethiopia retreat to demarcated borders.”

እኔ ይህን ጉዳይ በጥንቃቄና በብልሃት እንመልከተው እላለሁ። ቢሆን ኖሮ፤ ሆኗል የሚል መረጃ የለኝም፤ ስለ ድንበሩ ድርድርና ህጋዊ ችካል የሚመለከተው አካል የጎንደርን ሕዝብ የሚወክለው የአማራውን ክልል መንግሥት ተሳትፎ ቢኖር ነው።  ይህ ዘገባ እውነት ይሁን ውሸት ገና አልተረጋገጠም። ሱዳን በዘመናዊ መሳሪያ የተደገፈ የጦር ኃይል ድንበሯን አልፋ ኢትዮጵያ እንዳስገባች ሲወራ ቆይቷል። የአይን ምስክሮችና የኢትዮጵያ ኢንቬስተሮች አቤቱታ ሲያቀርቡ ቆይተዋል። ሆኖም የክልሉ ሆነ የፌደራሉ ባለሥልጣናት ለክፍለ ሃገሩና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያሳወቁት ነገር የለም።

ሱዳን ይገባኛል የምትለው መሬት የኢትዮጵያን የሉዐላዊነትንና የግዛታዊ አንድነትን ጥያቄን ያስነሳል። ስድስት መቶ ስኩየር ኪሎ ሜትር (600 SQ. Km of virgin farmland, water, forests and other natural resources) ለም መሬት፤ ደን፤ ተራራና ሌላ የተፈጥሮ ኃብት እንዲሁ የሚሰጥ አይደለም፤ የኢትዮጵያን መብቶችና ክብር ሁሉ ይመለከታል። የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን ጉዳይ በቀላሉ የሚያየው አይመስለኝም። ስለዚህ፤ እኛ ሁኔታውን በቅርብ ከመከታተል ውጭ አቋም የምንወስድበት ጉዳይ አይደለም። ማዘናጊያም ሊሆን ይችላል። ማዘናጊያ አቅም ይበታትናል።

ዛሬ መላው የዓለም ሕዝብ በወረርሽኙ በተበከለበት ወቅት ለምን ሱዳንና ኢትዮጵያ የቆየውን አወዛጋቢ የድንበር ውል ስኬታማ ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ አጋጠማቸው፤ ለማን ጥቅም? ቢያንስ ቢያንስ የአካባቢው ሕዝብ እንዲያውቀውና ውሳኔው የተደረገበትን ምክንያት እንዲገነዘበው የማድረግ ግዴታ እንዳለ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ያውቃሉ የሚል እምነት አለኝ። በተጨማሪ፤ የአሁኑ ጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ አህመድ የሚመሩት መንግሥት፤ ተከታታይ የኢትዮጵያ መንግሥታት አስከብረውት የቆዩት የሱዳንና የኢትዮጵያ የድንበር ጉዳይ በሕግ የተከበረ እንዲሆን ፓርላማው እንዲወያይበትና አቋም እንዲወስድበት ያደርጋል የሚል ግንዛቤ አለኝ። ምክንያቱም፤ ግልጽነት ተአመኔታን ያጠናክራል፤ የሕዝብን ድጋፍ ያስገኛል።

አህመድ ዩኒስ እንዲህ ብሎ የጻፈው ልክ ግብጽ ጠቁማ ያጻፈችው ይመስላል። “Ethiopian forces control Al-Fashaqa, which stretches over about 600 square kilometers of highly fertile agricultural land.” መሬቱ የኢትዮጵያ ነው ብለን ለብዙ አመታት ስንከራከር ለቆየነው ኢትዮጵያዊያን፤ ለምሳሌ የኢትዮጵያ የድንበር ጉድዮች ኮሚቴ፤ ይህ አባባል ትክክል አይደለም። መሬቱ የኢትዮጵያ ከሆነ የኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይልና ተራው ሕዝብ፤ ፋኖዎችን ጨምሮ፤ በተከታታይ መሬቱንና ድንበሩን ሲያስከብሩት ቆይተዋል ማለት ነው። ተቆጣጠሩት ማለትና አስከበሩት ማለት የተለያዩ ትርጉም አላቸው። የኢትዮፕያ መከላከያ በአካባቢው መገኘቱ የሚፈለግና አግባብ ያለው ስራ ነው።

ሱዳን “አል ፋሽካ” ብላ የምትጠራውን ለም መሬቴ ዛሬ ለመውሰድ ያስቻላት በኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተው ሁኔታ ምንድን ነው? ወይንስ፤ በኢትዮጵያና በግብጽ መካከል የተከሰተው የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ነው? መልሱን ለማወቅ አስቸጋሪ ነው።  

ይህ እንዳለ ሆኖ፤ ለኔ ከሱዳን ጋር ሆነ ከግብጽ ውይንም ከሌላ የውጭ ኃይል ጋር ፍትጊያ ሲደረግና ሕዝብ አሰቃቂ በሆነ ወረርሽኝ ምክንያት በስጋትና በፍርሃት ሲበከል፤ የአማራው ክልልና የፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት ትኩረት “በስርአት አልበኛነት፤ በህገወጥነትእና ሌላ አመካኝቶ የጎንደርን ሕዝብ ማስጨነቅ ሊሆን አይችልም። ለሕዝብ ተገዢ ሁኑ አላለሁ።

ሁለት ትኩረቶች አሉ፤

አንድ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከወረርሽኙ አደጋ ማዳን፤ የተቻለንን ማድረግ፤

ሁለት፤ የኢትዮጵያን ግዛታዊ አንድነት፤ ሉዐላዊነት፤ ዘላቂ ጥቅም፤ ነጻነትና ክብር  በአንድነት መታደግ።

የጎንደር ሕዝብ፤ በተለይ ወጣቱ ለአገራችን ዳር ድንበር መከታ ነው። የጎንደር ሕዝብ ከማንኛውም በላይ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር፤ በኢትዮጵያ የሚኮራና ለሃገሩ ሉዐላዊነትና ጥቅም ከፍተኛ መስዋት ሲከፍል የኖረ ሕዝብ ነው። “ፋኖ” የሚለው ብሂል ከጎንደሬውና ከሌላው የአማራ ሕዝብ ወኔና አገር ወዳድነት ጋር የተያያዘ መሆኑን ከልጅነቴ ጀምሬ አውቃለሁ። እርግጥ ነው፤ ህወሓቶች ጎንደሬውን ዘውጋዊ በሆነ የከፋፍለህ ግዛው መርህ ለመከፋፈል፤ ለማዳከምና መሬቱን ለመንጠቅ ስላቀዱ፤ ልክ ግብጽ እንደምታደርገው ሰርጎ ገቦችን አሰማርተዋል። ቅማንት፤ አማራ፤ አገው እያሉ አጀንዳ ፈጥረውልናል። ሰርጎ ገቦች ከሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች ማካከል አንዱ “የፋኖ’ን” ስም ተጠቅሞ ህዝቡን መዝረፍና ማስጨነቅ ነው። ስርዓት አልበኛነት የሚጎዳው ተራውን ሕዝብ ነው፤ የሚጠቅመው ግን ህወሓትን፤ ግብፅንና ሌሎቹን የኢትዮጵያን ጠላቶች ነው። 

በግብርና ስራ ላይ የተሰማራው ገበሬው “ፋኖ” በህገ-ወጥነት፤ በሌብነት፤ በስርዓት-አልበኝነት ወዘተ እንዴት ሊጠቀም ይችላል? አይችልም። የጥምቀት በዓልን ያስከበረው ወጣቱ ጎንደሬ፤ “ፋኖውና” ሌላው ህግን የሚያስከብር ክፍል በወንበዴነት እንዴት ይጠቀማል? አይጠቀምም።

ስርዓት አልበኝነት አለ ወይንስ የለም? መልሱ አለ ነው። ቁልፉ ከጀርባ ሆኖ የሚቀሰቅሰው፤ ፋይናንስ የሚያደርገው ማነው? የሚለው ነው። ገበሬው ሆነ ወጣቱ ጎንደሬ፤ ከሁሉም በላይ የሚመኘውና የሚፈልገው በሰላም ሰርቶ፤ በልቶ፤ መብቱ ተከብሮ መኖርን ነው። የክልሉና የፌደራሉ ባለሥልጣናት ሃላፊነት ደግሞ ለወጣቱ ትውልድ የስራ እድል፤ የመፍጠር እድል፤ የማምረትና የመንቀሳቀስ እድል ወዘተ ማመቻቸት ነው።

ከጥንት ጀምሮ እስከማውቀው ድረስ፤ እውነተኛ ነው የሚባለው “ፋኖ” በአንድ በኩል የግብርናውን ስራ እየሰራ፤ በሌላ በኩል የጦር መሳሪያ ይዞ ዳር ድንበሩን የሚያስከብር አገር ወዳድ ኃይል ነው። ስለሆነም፤ የመንግሥት አጋር እንጅ ጠላት አይደለም። ለውጡን ካመጡት ወሳኝ ኃይሎች መካከል አንዱ መሆኑን መርሳት የለብንም። ይህ አካል የለውጡ አጋር ነው።

ለእንግዳ አስተናጋጁ የጎንደር ሕዝብ ማን ደረሰለት?  

ለማስታወስ፤ ቀደም ሲል የጎንደር ክፍለ ሃገር ሕዝብ በሙሉ እንግዳ ተቀባይና አስተናጋጅ፤ ከሱዳን ሕዝብ ጋር ሰፊ የንግድ ግንኙነት የመሰረተ መሆኑን አስምሬበታለሁ። “አትንኩኝ ባይ መሆኑ ያስከብረዋል እንጅ አያስንቀውም። እኔን ሲያሳስበኝ የቆየው ክስተት፤ መጭውንና ሂያጁን ማስተናገዱ የእድገትና የልማት ድጋፍ ያላስገኘለት መሆኑ ነው። የተጠቀመበት ኃይል ሁሉ በጭንቀቱ ወቅት ድምጽ አላሰሙለትም፤ ድጋፍ አልሰጠውም። ነዋሪው ሕዝብ ምን ይፈልጋል? ምን አናድርግልህ? ብሎ  የጠየቀው የፖለቲካ መሪና ድርጅት የለም።

በዚሁ ልክ ግን የታዘብኩት ክስተት፤ ተባባሪና አጋፋሪ ሆኖ ይታይ የነበረውና አሁንም የሚታየው ጎንደሬው ነው ብል አልሳሳትም። በአንድ ወቅት ታዋቂው ሃኪምና መሪ፤ ፕሮፌሰር አስራት ገብረየስ “የአማራው” ሰርጎገብ ቢያስቸግራቸው ሆዳም አማራ ያሉበት ምክንያት ይኼው ነው። ጎንደሬው ሆነ ሌላው አማራ መሪ ለማፍራት ያልቻለበት መሰረታዊ ምክንያት ሰርጎገብነት ብቻ አይደለም። ሁሉም መሪ፤ ሁሉም አዋቂ፤ ሁሉም ተናጋሪ፤ ሁሉም አትንኩኝ ባይ ወዘተ መሆኑ ነው። ይህ ክፍፍል ለህዝቡ ተጠቂነት መጋቢ ሆኗል፤ ሃቁን እንቀበል።

የጎንደሬውንና የሌላውን አማራ የባህሪ፤ የአመለካከትና የስነልቦና ዝብርቅርቅ የተመለከቱ አንድ ምሁር (ሃኪም) እንዲህ ብለዋል የአማራው ዋና ጠላት እራሱ አማራው ነው።   ህብረት ከሌለ ድህነት ይባባሳል።

የጎንደር ሕዝብና ሌላው የአማራ ሕዝብ ሆዳሙንና ስግብግቡን ከሌላው የሚለይበት ወቅት አሁን ነው። ማንም ሊክደው የማይችለው ሃቅ አለ። ይኼውም፤ በጎንደር ክፍለ ሃገር ህወሓት ያሰለጠነውና ያሰማራው ሁሉ ህዝቡን እየጎዳው ነው። ፋኖ ሳይሆን በፋኖ ስም የሚነግደው ማነው? የሚለውን ጥያቄ ታዳሚው እንዲመልሰው አሳስባለሁ።

በአጭሩ ለማስቀመጥ፤ ሌላውን አስተናጋጅ፤ መውጫ መግቢያ ሆኖ ያገለገለ ክፍለ ሃገር ጥራ ብባል የምሰይመው ጎንደርን ነው። ይህ እንዳለ ሆኖ ግን በተከታታይ የነፍስ ወከፍ እድገትና የማህበረሰባዊ የልማት ዝቅተኛነት ክፍተት የሚታይበት ክፍለ ሃገር ደግሞ ጎንደር ነው። በምን መስፈርት?

አንድ፤ በመሰረተ ልማት በኩል ያለውን ፍትሃዊ የሆነ ግድፈት ላቅርብ፤

 • መሰረተ ልማትን ለማስፋፋት የሚቻለው የፌደራሉ ባጀት ግልጽነት፤ ሃላፊነትና ፍትሃዊነት ባለው መስፈርት ለሁሉም ክፍላተ ሃገራት ሲመደብና ያለምንም ሙስና ስራው በቅልጥፍና ስኬታማ ሲሆን ነው፤
 • ተከታታይ መረጃዎችና ዘገባዎች የሚያሳዩት፤ የጎንደር ክፍለ ሃገር፤ ከሕዝብ ብዛቱና ከመሬት ስፋቱ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የመንገድ ስራ አይታይበትም። በአሁኑ የባጀት ፈሰስና የፕሮጀክቶች እቅድ መሰረት ሲታይ፤ ለአማራው ክልል ከተመደበው ባጀትና ከተዘጋጀው 9 የመንገድ እቅድ መካከል 7 መንገዶች የሚገኙት በጎጃም ክፍለ ሃገር ነው፤
 • ከጎጃም ተመጣጣኝ ሕዝብ የሚኖርበት የጎንደር ክፍለ ሃገር ከአሙሲት እስከ መካነ እየሱስ የሚደርስ መንገድ ይሰራለታል። አንድ መንገድ ብቻ!!
 • መንገድ ለጎጃም ለምን ተሰራ? አይደለም ጥያቄው፤ መሰራት አለበት። የጎንደር ክፍለ ሃገር ለምን በተከታታይ ይቀጣል? የሚለው ነው አነጋጋሪው።
 • ኢትዮጵያን ከድህነትና ከኋላ ቀርነት አሮንቃ ለመቅረፍ የሚቻለው ኢንዱስትሪ ሲስፋፋና የእርሻው ክፍል ዘመናዊ ሲሆን ነው። መንገድ ወሳኝ የሚሆነው ለቅንጦት አይደለም። ለምርትና ለንግድ፤ ለሕዝብ እንቅስቅሴ ወዘተ ነው። መሰረታዊና መዋቅራዊ ለውጥ ያስፈልጋል እያልኩ ስከራከር ቆይቻለሁ (Fundamental and structural transformation a must).
 • የጎንደር ክፍለ ሃገር እንደሌላው ክፍለ ሃገርና ሕዝብ የሕዝብ ስርጭቱ የሚያሳየው ወጣቱ ትውልድ፤ ማለትም እድሜው 35 አመት በታች የሚገመተው 70 በመቶ የሚሆን መሆኑ ነው። ይህ ወጣት ትውልድ መማሩ ብቻ በቂ አይደለም። ትኩስ የሰው ኃይል የመፍጠር፤ የማምረት እምቅ አቅም አለው። ግን፤ ተምሮ የስራ እድል እንዲኖረው ማድረግ፤ ገቢውን አሳድጎ ራሱን፤ ቤተሰቡንና ህብረተሰቡን እንዲያገልግል ማጎልመስ ወሳኝ መርህ መሆን ይኖርበታል። ሁኔታውን የሚፈጥረውና የሚያመቻቸው መንግሥት ነው።
 • ስራ ፈት የሆነ ትኩስ ጉልበት በልቶ ማደር ስላለበት፤ የሚኖረው ሌላው አማራጭ ስደት ወይንም መንግሥትን መቃወም፤ ወደ አልተፈለገ ሕገወጥ ስራ መሸጋገር ነው። ለስደት ያለው እድል ዜሮ ነው። በሳውዲ አረቢያና በገልፍ አገሮች ተሰደው የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከእነዝዚህ አገሮች እንዲወጡ እየተገደዱ ነው። ይህ አማራጭ ሊሆን አይችልም።
 • ሌብነትና ወንበዴነትም አማራጭ አይደለም። አማራጩ የአቅም ግንባታን መሰረት አድርጎ የማምረትና የመፍጠር እድሎችንና ፕሮጀክቶችን መፍጠር ነው። የጎንደር ክፍለ ሃገር ብዙ ያልተነኩ እድሎች አሉት።
 • ልክ በሌሎች ክፍለ ሃገሮች እንደሚደረገው ሁሉ በጎንደር ክፍለ ሃገር ብዙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፤ ዘመናዊ እንዱስትሪዎች፤ ለምሳሌ የዘይት መጨመቂያዎች፤ የስሚንቶ ፋብሪካዎች፤ የጡብ ምርት ፋብሪካዎች፤ የጨርቃ-ጨርቅ ፋብሪካዎች፤ የደሮና የከብት እርባታ ስራዎች ወዘተ በእቅድና በስልት ለማስፋፋት መቻል አለበት። ክፍለ ሃገሩ በተፈጥሮ ሃብት፤—ዝናብ፤ ወንዞችና ጅረቶች፤ ለም መሬቶች፤ ማእድኖች፤ ዶሮ፤ ፍየል፤ ከብቶች፤ የጋማ ፈረሶችና አህዮች ወዘተ አለው። እነዚህ ሁሉ በድምራቸው ብዙ የስራ እድል ሊፈጥሩ ይችላሉ፤ ካፒታል በአክሲዎን ሊገኝ የሚችልበት እድል አለ።  የአማራው ባንክ ትኩረት ከዚህ ላይ ሊሆን ይገባል።

ለ/ በኢንዱስትሪያል ፓርክ ስርጭት በኩል ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?

 • የምስራቅ ኤዢያ አገሮች–ታይዋን፤ ሲንጋፖር፤ ቻይና፤ ማሌዢያ፤ ታይላንድ፤ በቅርቡ ቬትናም ወዘተ–ለተማረው ወጣት ትውልድ ግዙፍ የስራ እድል የፈጠሩት መዋቅራዊና መሰረታዊ ለውጥ ስላደረጉና ኢንዱስትሪዎችን አስፋፍተው የተማረው ወጣት ትውልድ፤ በተለይ ወጣት ሴቶች የማኒፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ሰራተኞች የሆኑበትን አስተማማኝ የስራ እድል ስለፈጠሩ ነው፤
 • ይህ ከገጠር ኢኮኖሚ ወደ ዘመናው ኢኮኖሚ የተደረገ ሽግግር የገቢ መጠን እንዲጨምር አድርጓል፤
 • በአማራው ክልል ከተሰሩና ከሚሰሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል የጎንደር ክፍለ ሃገር ድርሻ ምንድን ነው? በክልሉ የፌደራሉ መንግሥት የመዋእለንዋይ ፈሰስ ከሚያደርግባቸው 9 የኢንዱስትሪያል ፓርኮች መካከል 8 በጎጃም ክፍለ ሃገር—በቡሬ፤ በሞጣ፤ በፍኖተ-ሰላም፤ በቻግኒ፤ በዳንግላ ወዘተ ይገኛሉ፤ ይህ ጥሩ ነው፤ እደግፈዋለሁ፤
 • ጥያቄየ ግን፤ ሌላውም የአማራ ሕዝብ ልማት ያስፈልገዋልና ለምን ትኩረት አይደረግለትም? ነው። ተመሳሳይ የሕዝብ ብዛት በሚኖርበት በጎንደር ክፍለ ሃገር በደርግ መንግሥት ከተሰራው የጥጥ ማዳመጫ ውጭ የኢንዱስትሪ ፓርክ አላየሁም፤ ከታቀደ ግልጽ ቢሆን ይመረጣል፤
 • ለማለት የምፈልገው፤ እንደ ማንኛውም ክፍለ ሃገርና ህዝብ፤ የጎንደር ሕዝብ፤ በተለይ በቁጥሩ ግዙፍ የሆነው ወጣቱ የኢንዱስትሪ የስራ እድል ያስፈልገዋል፤ ጥጥ፤ ሰሊጥ፤ ሩዝ፤ ስንዴና ሌላ ያመርታል፤ ከገጠር ኢኮኖሚ ወደ ዘመናዊ ኢኮኖሚ ለመሸጋገር ፍላጎት ብቻ ሳይሆን እምቅ ችሎታም አለው፤
 • የጎንደር ክፍለ ሃገር ሕዝብ ከጭቃ ቤት ወደ ዘመናዊ ቤት መሸጋገር ይፈልጋል። የጡብና የስሚንቶ ፋብሪካ ከሌለ ግን ይህ ህልም ሆኖ ይቆያል፤
 • በጎጃም የአባይ ኢንዱስትሪያሊስቶች ማህበር በደጀን ከተማ 11 ቢሊየን ብር የስሚንቶ ፋብሪካ ይከፍታሉ። ይህ ጥሩ ተምሳሌት ነው፤ የጎንደር ክፍለ ሃገር ኢንዱስትሪያሊስቶችስ ምን ጫና ደርሶባቸው ነው የሲሚንቶ ፋብሪካ ለመገንባት የማይችሉት፤ የጎንደር ክፍለ ሃገር ዲያስፖራስ ምን ይላል?
 • የዜጎችን የኑሮ ፍላጎት ለማሟላት በሚል እቅድ፤ በደብረማርቆስና በቡሬ የዘይት ፋብሪካዎች እየተሰሩ ነው። ይኼም የሚመሰገንና ለሌሎች ምሳሌ ሊሆን የሚችል ፕሮጀክት ነው፤ ሰሊጥ አምርቶ ለውጭ ገበያ መሸጥ አስፈላጊ ቢሆንም፤ መጀመሪያ ግን የዜጎችን ፍላጎት ማሟላት ተገቢ ነው፤
 • ከላይ የጠቀስኳቸው ኢንዱስትሪዎችና ፋብሪካዎች ለምን ተሰሩ? የሚለው ጥያቄ አግባብ የለውም፤ አስፈላጊ ናቸው። ችግሩ ከስርጭቱ ላይ ነው፤
 •  የጎንደር ክፍለ ሃገር ሕዝብ ፍላጎት ኢንዲሟላ ጥረት ከማድረጉ ላይ ነው ትኩረት መደረግ ያለበት። ይህ የፖሊሲና የፕሮጀክት ጥያቄ መመለስ አለበት፤
 • ለዚህ አቤቱታ የሚረዳው በመንደር ደረጃ መከፋፈል አይደለም። የዓላማ አንድነት፤ አቅምን ሰብስቦ፤ ገንቢ የሆኑ አማራጮችን በማቅረብ ብቻ ነው፤
 • ለጎጃም ለምን ተሰራ የሚለውን ከፋፋይ ብሂል ማንሳት ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል። የጎጃም ህዝብ ልማት ለሌላው ሕዝብ ጠቃሚ መሆኑን ተቀብሎ የልማት መዋእለንዋይ ፈሰስ ፍትሃዊና ሚዛናዊ እንዲሆን መከራከር አግባብ አለው፤
 • በጎንደር ክፍለ ሃገር ስርዓት አልበኝነት ነግሷል የሚለውን ትርክት በማህበረሰባዊ ሜድያ ከማባዛትና ከማራባት ይልቅ፤ ድሃና ኋላቀር የሆነውን የጎንደርን ክፍለ ሃገርና መላውን ሕዝቡን እንዴት ካለበት ሁኔታ ተባብረን እናውጣው የሚለውን ብናስብበት ይሻላል።

ለማጠቃለል፤

 1. የወቅቱ ዋና ትኩረት ወረርሽኙን መከላከል ነው፤ የጎንደር ክፍለ ሃገር በስርዓት አልበኝነትና በጦርነት ከተበከለ የወረርሽኙ አጥፊነት ይባባሳል። ከተባባሰ ደግሞ፤ ስርእስት አልበኛነት፤ ሌብነትና ዘረፋ ይባባሳል፤ ከቁጥጥር ውጭ ይሆናል፤
 • በጠቅላላ ስመራመረው፤ የአማራው ክልል፤ በተለይ፤ የጎንደር ክፍለ ሃገር ተደራራቢ ችግሮች አሉበት። በጤና አገልግሎት መስፈርት ሲገመገም፤ የጎንደር ክፍለ ሃገር ፍጹም ኋላ-ቀር ነው። ከወረርሽኙ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ አገልግሎት ለማቅረብ የሚቻል አይመስለኝም። ትኩረቱ ከላይ በስእል እንዳቀርብኩት ሁሉ ችግሩን አስቀድሞ ከመከላከሉ ላይ ቢሆን ይመረጣል፤
 •  ወረርሽኙ ድህነትን እንዳያባብሰው ቅድመ ዝግጅት ማድረግ አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ፤ ገበሪዎች ግብርናቸውን እንዲቀጥሉ ማበረታታት፤ አስፈላጊ ቁሳቁሶች መደበቅ እንደ ወንጀል እንደሚቆጠር በግልጽ መናገር፤ ፋብሪካዎች ስራቸውን በጥንቃቄ እንዲሰሩ መመሪያዎችን ማውጣትና ቁጥጥር ማድረግ፤
 • የመንግሥት አመራርና አስተዳደር መርህ “በፋኖና” በሌሎች ሁኔታዎች ዙሪያ፤ ሁሉም ተግዳሮቶች በሽምግልና ብቻ እንዲፈቱ ያልተቆጠበ ጥረት ማድረግ፤ የአማራው ምሁራን ማህበር ወይንም ስብስብ ጥናትና ምርምር እንዲያደርግ፤ አመቻችና ድልድይ የሆነ ሚና እንዲጫዎት መቀስቀስ ማበረታታት፤
 • ጎንደሬውና ሌላው ወጣት የአማራ ትውልድ፤ ዲያስፖራውን ጨምሮ፤ በለው፤ በለው እና ፋኖ ተሰማራ የሚል ጊዜ ያለፈበት መፈክር እንዲያቆምና የመፍትሄው አካል እንዲሆን ያልተቆጠበ ጥረት ማድረግና፤
 • ህወሓት፤ ኦነግና ሌሎች ብሄር-ተኮር ኃይሎች የአላማ አንድነት ይዘው መሰብሰብ መቻላቸውና ኢላማ ባደረጉት ሕዝብ ላይ፤ በተለይ በጎንደሬውና በሌላው አማራ ላይ የሚያካሂዱትን ግፍና በደል ለመቋቋም የሚቻለው በአላማ አንድነት መርህ ስለሆነ፤ ጎንደሬውና ሌላው አማራ ከጎጠኝነት ባሻገር የተበታተነውን ኃይሉን እንዲሰበስብ ዘመቻ ማድረግ፤ ለምሳሌ፤ ሰሜንና ደቡብ ጎንደር፤ ጎጃምና ጎንደር እያሉ መከፋፈልና መናገር ምን ዋጋ አለው? የለውም።
 • በዘላቂነት ሲታይ፤ የጎንደር ክፍለ ሃገር፤ በስራ እድል፤ በመንገድ ስራዎችና ስርጭት፤ በኢንዱስትሪ ፓርኮች፤ በማህበረሰባዊ እድገትና በሌሎች የዘመናዊ ኢኮኖሚ ግንባታ ዘርፎች ድርሻውን አላገኘም። ስለሆነም፤ የኢትዮጵያ የፌደራል መንግሥት የምጣኔ ኃብት እንቅስቃሴ ይህን ክፍለ ሃገር በሚመለከት ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባውን ዘርፎች ጠቁሞ የተዛባው የልማት እንቅስቃሴ የሚሰተካከልበትን ዘዴ በአስቸኳይ ማሳሰብ አስፈላጊ ነው።  
 •  ስለ ኢትዮጵያ እድገት በቅርብ የተደረጉ ጥናቶችና ምርምሮች የሚጠቁሙት አስኳል ጉዳይ አለ። በመሬት ላይ የሚታዩት የእድገት ውጤቶች ምን ግድፈት ያሳያሉ? የሚለውን ፖሊሲና መዋቅር ነክ የጎንደረን ክፍለ ሀገር ሁኔታ ተጠቅሜ፤ ምሳሌዎችን በመጠቆም ልመልስ። የኤሊክትሪክ ስርጭትን ብንወስድ፤ 70 በመቶ ከሚገመተው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከማያገኘው የኢትዮጵያ ሕዝብ መካክል፤ የጎንደር ክፍለ ሃገር ሕዝብ አንዱ ነው። አብዛኛው የክፍለ ሃገሩ ነዋሪዎች “90 በመቶው የኢትዮጵያ ንጹህ ውሃ ይጠቀማል” ከሚለው እርከን ውጭ ነው። ይህን ክፍተት ለማሟላት የሚቻለው፤ የገጠሩ ሕዝብ በጋራ ሆኖ የሚጠቀምባቸውን የንጹህ ውሃ አገልግሎት ኪዎስኮች እንዲከፈቱና እንዲጠቀሙ በማድረግ ነው። ይህን ፕሮጀክት የጎንደሬው ዲያስፖራ ሊያሟላ ይችላል።
 •  የንፅህና አገልግሎት ለጤናማነት ወሳኝ ነው። በ 2015/16 እ. አ. አ. አምሳ በመቶ የሚገመተው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለንጽህና (Sanitation) የሚጠቀመው ዱርና መስክ ነበር። ይህ ሁኔታ ተባብሶ ከሚገኝባቸው አካባቢዎች መካከል የጎንደር ክፍለ ሃገር አንዱ ነው። ይህ ሁኔታ ቢያንስ በአንድ ሶስተኛ እንዲቀንስ የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል፤ ብዙ ወጭ አይጠይቅም። ጉዳቱ ግን ከፍ ያለ ነው።
 1.  በኢትዮጵያ የገቢና የኑሮ ልዩነቶች (Income Inequality) እየተባባሱ መሄዳቸው የአደባባይ ምስጢር ነው። በዚህ መስፈርት ፍትሃዊና ሚዛናዊ የገቢና የኑሮ መጠን የሚታይበት ክልል ኦሮምያ ነው። የትግራይ ክልል ከፍተኛ ልዩነት ያሳያል።
 1.  በአማራው ክልል፤ በተለይ በጎንደር ክፍለ ሃገር የኢክኖሚው እድገት መጠን ለሁሉም ዜጎች ዝቅተኛ ነው። አብዛኛው የገጠሩ የጎንደር ህዝብ ድሃ ስለሆነ በድህነት ምንም ልዩነት የለም ከማለት ይልቅ፤ ድህነቱ እንዲቀረፍ ያልተቆጠበ ጥረት ማድረግ ነው።
 1.  የገቢና የኑሮ ልዩነት የሚታየው ግን፤ ጎንደርን፤ ደብረ ታቦርንና ሌሎችን የጎንደር ከተማዎች ጨምሮ በከተማዎች በሚኖረው የአማራ ሕዝብ መካከል ነው። ይህ እየከረረ የሄደ፤ አስጊና አደገኛ የገቢና የኑሮ ልዩነት ድህነትን ለመቅረፍ ማነቆ ሆኗል፤ ወደፊትም ይሆናል። ለሰላምና ለእርጋታ፤ ለህግ የበላይነትና ለአብሮነት ችካል መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።
 1. ጎልቶ የሚታየው የገቢና የኑሮ ልዩነት የሚሻሻለው የድሃውን ገቢ እንዲጨምር በማድረግ ነው።

ለማስታወስ ያህል፤ የአማራው ሕዝብ በጠቅላላ፤ በተለይ የጎንደር፤ የወሎ፤ የጎጃም፤ የሰሜን ሸዋ፤ የሃረርና የድሪዳዋ አማራ ሕዝብ በተከታታይ፤ በዘውጉ፤ በባህሉ፤ በኃይማኖቱ፤ በመለያ ሰንደቅ ዓላማው ብቻ እየተለየ ለብሄር-ተኮር እልቂት ተጋልጧል፤ ተሰቃይቷል፤ ተገድሏል፤ ተሰዷል። ከዛሬ አምስት ወር ጀምሮ ከደምቢዶሎ ዩንቨርስቲ ተነጥቀው በህይወት ይኑሩ ወይንም የባሰ የሞት ፍርድ ይፈረድባቸው የማናውቀው፤ በአብዛኛ የአማራ ወጣት ሴቶች ሁኔታ የወንጀሉ ምሳሌ ነው። የፌደራሉ መንግሥት ምን መልስ አለው?

ህወሓት ስልጣን ከመያዙ በፊትና በኋላ የመሬት ነጠቃን መርህ በመከተል፤ በተከታታይ በጎንደርና በወሎ የአማራ ሕዝብ ላይ ያደረገውንና አሁንም፤ ቅማንት፤ አማራ፤ አገውና ሌላ የማንነት መለያ አጀንዳ እየፈጠረ የሚያካሂደውን ወንጀል ከላይ ካቀርብኩት የድህነት ሁኔታ ጋር ማያያዝ ተገቢ ነው። ህወሓት/ኦነግና ሌሎች የዘውግ ድርጅቶች መተከልን ወደ ቤኒ-ሽንጉል ጉሙዝ አቀላቅለው ዛሬ የአማራ ገበሬዎች፤ ወጣት ሴቶችና እናቶች፤ ሽማግሌዎች በሚዘገንን ደረጃ በቀስትና በሌላ መሳሪያ ይገደላሉ። ከጭካኔም በላይ ጭካኔ ይካሄዳል። ይህም ሁኔታ ድህነትን አባብሶታል። የአማራው ክልል መሪዎች ምን ይላሉ?

የወረርሽኙን አሰቃቂ ሁኔታ ስናስብ፤ የዘውግ ጥላቻውና መከፋፈሉ አደጋውን እንደሚያባብሰው በህሊናችን እንድንቀርጽ፤ የሚከተለውን ዛሬ የተላከልኝን ግጥምና መርህ አባሪ አደርጌ ሃተታየን እደመድማለሁ።

“የኛ ኬኛ የዜግነት መጋኛ
ትውፊተ ከንቱ ዘውገኛ
ከሐዲ ለመሆን የማይተኛ
በራስ ጥላቻ ተውጦ የተዘወረ ዘረኛ
በጎሳ ልክፍት ስብእናውን ሸጦ አውቆ የተኛ
የዜግነት አልባ አንጋሽ የኔ ለኔ በኔ ኬኛ
ፍልስፍና መስሎት የሚሆን ተራ በላተኛ
አጥፍቶ ጠፊ የጥላቻ ዘበኛ።”

April 15, 2020

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here