spot_img
Friday, June 21, 2024
Homeአበይት ዜናከኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ እራስዎን ቤተሰብዎን የሥራ ባልደረባዎንና አገርዎን ያትርፉ የሃኪሞችን ምክር ተግባራዊ...

ከኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ እራስዎን ቤተሰብዎን የሥራ ባልደረባዎንና አገርዎን ያትርፉ የሃኪሞችን ምክር ተግባራዊ ያድርጉ

ኢትዮጵያዊነት የዜጎች መብት ማስከበሪያ ጉባኤ
ሚያዚያ 9, 2012 ዓ.ም.

     ከታህሳስ ወር መግቢያ ፳፻፲፪ ዓም ክቻይና በመጀመር ዓለምን በማዳረስ ላይ ያለውና COVID 19 (ኮቪድ፲፱) በ2019 የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ በሚል ስም የታወቀው ተላላፊ ደዌ እስከመጋቢት ፴፤ ፳፻፲፪  በ 4 ወራት ጊዜ የሚከተለውን የሕመምና የሞት ጉዳት በዓለማችን ላይ አድርሷል፦( በ Johns Hopkins ዩኒቨርሲትይ ጥናት ላይ የተመረኮዘ- ይህ አሃዝ በየጊዜዉ ይቀያየራል።  ለወቅታዊው አሃዝ ይህን ይጫኑ)

በምርመራ በቫይረሱ የተያዙት ቁጥር ፡   1,724,736

ለሕይወት ህልፈት የተዳረጉት ቁጥር፡       104,938

ወረርሺኙ ወደመላው ዓለም መሰራጨት ከጀመረ በኋላ ከእስያ ቀጥሎ ያውሮፓ አገሮች ከዚያም የሰሜን አሜሪካ አገሮች በደዌው እየተጎዱ እንደነበሩና እንዳሉም ይታወቃል። አሁን ባለንበት ጊዜ ዩናይትድ ስቴትስ 503,594 በምርመራ የተረጋገጡ ተጠቂዎችን በማስመዝገብ በቀዳሚነት ትገኛለች። ካፍሪካ ቀደም ቀደም ያሉት ግብጽ 1794፣ ሞሮኮ 1527 ሲያስመዘግቡ በዛ ያሉት ሌሎች ያፍሪቃ አገሮች በመቶና በሺ መካከል ናቸው።

ኢትዮጵያ በ 69፣ ኤርትራ በ 34 በዝቅታ ካሉት ውስጥ መሆናቸው ተስፋን የሚያዳብር መሆኑ የተያዘ ሆኖ፤ ኢትዮጵያውያነት የዜጎች መብት ማስከበሪያ ጎባኤ በዚህ አስከፊ ጊዜ ከ “ሰውለሰው” ድርጅት (people to people) [1]የድጋፍ እቅዶች ጋር ጥምረት በመፍጠር የኮሮና ደዌ “ሳይቃጠል በቅጠል” የሚለውን ያባቶች አባባል በመከተል የጤና አጠባበቅ ሚኒስቴር በሚመራው የህዝብ የደዌው መከላከል ትምሕርትና እውቅና አሰጣጥ ላይ ተሳትፎ ለማድረግና ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ከሚያንጃብበው የወረርሺኝ ደዌ በመራቅ ጤናቸው ይጠበቅ  ዘንድ ይህቺን ትምሕርት አዘል ጽሁፍ ድርጅታችን ሊያዘጋጅ ወሰነ።

ስለ ኮቪድ_ 19፣ አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ማንነትና የትውልድ ሐረግ ብዙም የተደበቀ ባይሆንና ከእንስሣትም የሌሊት ወፍን ጨምሮ ወደ ሰው መተላለፉ ቢደረስበትም ለየት ያለ የመሰራጨት ኃይልና የአየር መቀባበያ ሕዋሳቶችን ሳምባንም ጨምሮ የማጥቃት ችሎታው በቅርቡ በቂ እውቅናን እያገኘ ሄዷል፡፡ በተጨማሪም  በተለይ በዕድሜ ጠና ያሉትንና በልዩልዩ የውስጥ ደዌ ችግር፣ እንደልብ ደዌ የሳምባ በሽታ የደም ብዛት የስኳር በሽታ የአስም በሽታ የመሳሰሉት ያሏቸው ላይም  እንደሚበረታ ታውቅዋል፡፡ 

የኮቪድ_19 ደዌ ኮሮና ቫይረስ፤ ከጥቂት ኣመታት በፊት ሳርስ በመባል ያወቅነው የኮሮና ቫይረስ ዝርያም ቢሆን ገና የመከላከያ ክትባትም የመግቻ ወይም የማጥፊያ መድኃኒትም ተቀምሞ አልደረሰለትም፡፡ ለዚህም ነው በተለይም በኑሮ በኤኮኖሚና በጤና አገልግሎት ያልደረጁ አገሮች ኢትዮጵያን ጨምሮ ደዌውን ከመሰራጨት ቀደም ብለው ሊያስቡበት ሊያውቁትና እያንዳንዱ ዜጋ ስርጭቱን ለመግታት በተሟላ ሕብረሰባዊ መንፈስ መታገል ያለበት፦ ምን በማድረግ ! አሁን ባለንበት ጊዜ ያለው አማራጭ ከቫይረሱ ጋር ቅርበት እንዳይኖረንና ከቫይረሱ ጋር የመገናኘት እድልን በተቻለ መጠን መዝጋት ነው። ይቻላል ፣

እንዴት ይቻላል ወደሚለው መመሪያ ከመግባታችን በፊት በቫይረሱ ስለሚከሰተው ተላላፊ በሽታ በመጠኑ እንረዳ

 • ቫይረሱ ኮሮና ቫይረስ ሳርስ ፪ በመባል ሲታወቅ የሚያስከትለው ደዌ፣ ኮሮና ተላላፊ በሽታ፲፱ (ኮሮና ኢንፈክሽየስ ዲዚዝ፲፱ covid-19) ይባላል፡፡
 • ቫይረሱን ከያዘ ሰው የህመም ምልክቶች ቢያሳይም ባያሳይም ወደሌላ ሰው ሊተላለፍ ይችላል
 • ብዙውን የሚተላለፈው በሳል በማንጠስ ወደሌላ ሰው አፍ አፍንጫ ዓይን በመግባት ወይም የተበከለ ዕቃና ልብስ ነካክቶ ፊትን አፍንጫን ዓይንን ሳይታጠቡ በመነካካት፣ ወይም ገንዘብ የሰገራ ቤት በራፍና ዕቃ ነካክቶ ሳይታጠቡ ፊትን በመነካካትና፤ በዓይነምድርም ቫይረሱ ሊወጣ ስለሚችል በሌላ ንክኪ ሊተላለፍ ይችላል።
 • ቫይረሱ ወደሰውነት በገባ ቢያንስ በ 2 ቀን ቢዘገይ በ 14 ቀን ባብዛኛው በ 5-7 ቀናት የህመም ምልክት ይታያል የሕመሙ የመጀመሪያ ምልክቶች ትኩሳት 38 ዲግሪ ወይም በላይ፣ ደረቅ ሳል እራስ ምታት የጉሮሮ ህመም፣ ውሎ ሲያድር የሰውነት ድካም ተቅማጥ የአየር እጥረት ናቸው፤ በአንዳንድ ሰዎች  በተለይ አዛውንትና የቆየ ደዌ  ያላቸው ላይ  የመተንፈስ ችግሩ እየገፋ እየጨመረ መሔድ
 • ደዌው ሳምባዎችን አጥቅቶ የኦክስጂን ድጋፍ የሚያስፈልግበት ደረጃ ወይም ከዚያም በላይ በመተንፈሻ መሳሪያ  (ቬንቲሌተር)የመረዳት ደረጃ ከመደረሱ በፊት ደዌው ለሚያመጣው ህመም መቋቋሚያ ይረዱ ይሆናል በማለት በጥናትም በጥቅም ላይ የዋሉም መድኃኒቶች እንዳሉና  ወደፊትም ራሱን ደዌውን የሚያጠፉ አዲሶች መድኃኒቶች በሙከራ ላይ እንዳሉ ታውቋል

እንግዴህ ያ መድሃኒት ተገኝቶ እስኪሰራጭ በ COVID 19 ደዌ የተያዘ ህብረተሰብ በደዌውና ደዌው በሚያስከትለው የሕመም የሞት የኑሮ መመሳቀልና የኢኮኖሚ ችግሮችን እያደረሰ ስለሚሆን እነዚህን ከግንዛቤ በመውሰድ ችግሮችን ለማቃለል በተቻለ ትጋትና ሕብረት በሩቅ ከመከላከል ሌላ ዘዴ አለመኖሩን የደረጁትና በኢኮኖሚ የዳበሩትም አገሮች ከስህተታቸው እየተማሩ ያሉት ሃቅ ነው፡፡ እኛም ወደታወቀው ስህተት እንዳንገባ እንጠንቀቅ።

የኮሮና በሽታ ገብቷል ወይንም እየተንሰራፋ ነው በተባለበት አጥቢያ ያሉ አዛውንትና ቀድሞውንም ሌሎች የተለያዩ ደዌዎች ጥቃት ያደረሱባቸው ሰዎች ሁሉ ከቤት ሳይወጡ በጤንነት ያሉ ወጣትና ጤናማ ዘመዶች ሊረዷቸው ይገባል።

 1. ጉንፋን መሰል ሕመም በተለይ ከትኩሳት ጋር የያዛቸው በማንኛውም ዕድሜ  ያሉ ሁሉ እቤት በመቆየት ሁኔታቸውን ያዳምጡ፡ ውሎ ካደረ ወይም የመተንፈስ ችግር ከጀመረ ደግሞ ቢቻል የጤና ባለሙያ አነጋግሮ እርዳታ መሻት፣ ባይቻል አፍና አፍንጫን በማስክ ወይም በሻርፕ ከሸፈኑ በኋላ እጅን ሙልጭ አድርጎ በሳሙና ታጥቦ ወደ ሐኪም መሄድ ይገባል፡፡
 2. ማንኛውም ሰው እጅን በሳሙና ሁልጊዜ አገላብጦ እሽት አድርጎ በመታጠብ፤ ጎጂ ተውሳክን ለማስወገድ ይቻላል። እጅን በውሃ አርሶ መተው ወይም በቅጡ አለመታጠብ ቫይረሱን ሌሎችንም ጎጂ የማይታዩ ህዋሳትን ሊያስወግድ ስለማይችል፤  እጅ ደግሞ ከፊት ካፍንጫ ካይን መነካካት ስለማይወገድ፤ ቫይረሱ ከጅ ወደሰውነት የመግባት ዕድል እንዳያገኝ መፍትሄው  እጅን እሽት አድርጎ መታጠብ ነው።
 3. ባልታጠበ እጅ ፊትን አፍንጫን ዓይንን አፍን መነካካት ማቆምን ልማድ እናድርግ። ከቤት የመውጣት የማይቀርበት ጉዳይ ካጋጠመ እስካርፍም ባይገኝ በተደራረበ ያንገት ልብስ ወይም ንጹህ ጨርቅ አፍና አፍንጫን ጠበቅ አድርጎ በማሰር ሸፍኖ መሔዱ በመጠኑ ቫይረሱ እንድይገባ ይበልጡኑ እኛ ይዘነው ከሆነ እንዳናስተላልፍ ጠቃሚ መሆኑ ተደርሶበታል።   
 4. ሁላችንም ከሌላ ሰው በምንገናኝበት ጊዜ ራቅ ብለን በማጎንበስ ሰላምታ መለዋወጥን እንምረጥ፡ እጅ አለመጨባበጥን  አለመተቃቀፍን፣ አለመሳሳምን አጥብቀን በተግባር እናዉላቸዉ፡፡ ይህን አጥቂ ጠላት በኩርፊያም ይሁን በጡጫ እስክናስወግድ እነዚህን የመቀራረብ ባህሎቻችንን ተወት እናድርጋቸው።
 5. ሳልና፣ ማስነጠስ መናፈጥ ሲያስገድዱ ወይም ሲታሰቡ  ዞር ብሎ አፍና አፍንጫን በክንድ መሐል አፍኖ መሳል፣ ወይም በወረቀት መሀረብ አፈን አድርጎ ከማይነካካ፣ ልጆችም ከማይደርሱበት ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ውስጥ መጣል ።
 6. በጅ የሚነካኩ እቃዎችን መሳሪያዎችን መጠቀሚያዎችን በአልኮል ወይም ሳኒታይዘር መጥረግ፡፡ እነዚህ እቃዎች በማይገኙበትም ስፍራዎች በተቻለ መጠን ባለው ሳሙና ሳያነካኩ ባንድ አቅጣጫ መጥርግና ማጽዳት ያስፈልጋል፡፡
 7. እጅግ አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር ሰው ተበራክቶ ከሚገኝበት አለመሔድ። በተለይም ወረርሽኙ ጠፋ እስካልተባለ ድረስ መጠጥና ዳንስ ሰርግና ጭፈራ ቤቶች የበለጠ ለቫይረሱ መተላለፍ ምቹ ስለሚሆኑ አይሂዱ። የሺሻና የጫት ቤቶችም እንዲሁ ከራሳቸው የጤና ችግር ሌላ ሰዎች የሚሰበሰቡባቸው ስለሚሆኑ ቫይረሱም የተበራከተ ሊሆን ይችላል። መንግሥት ወይም የክፍለሀገሩ የጤና ድርጅትና አስተዳደር የሚያወጡትን የጤና አጠባበቅና ያለመሰባሰብ ሕጎች ተከታትሎ በተግባር ማዋል።       
 8. በቂ ፈሳሽ መጠጣት ፣ አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ ነጭ ሽንኩርት መመገብ ደዌውን ያስወግዳል ባይባልም ለመቋቋም ብርታት ይጨምራል።
 9. በየጊዜው የከፋ ተላላፊ በሽታ ገለጻ ምክርና እውቅናን እያነበቡና እያዳመጡ ሕጋዊ የጤና መምሪያ የሚሰጠውን በመከታተል ፈጣሪያችን ልንከላከለው ከምንችለው በድጋፉ፤ ልንከላከለው ከማንችለው በጸጋው  ይጠብቀን:: አሜን

ከኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ እራስዎን ቤተሰብዎን የሥራ ባልደረባዎንና አገርዎን ያትርፉ የሃኪሞችን ምክር ተግባራዊ ያድርጉ

Coronavirus prevention _ Ethiopia

[1] ኢትዮጵያዊነት የዜጎች መብት ማስከበሪያ ጉባኤ  https://www.ethiopiawin.net People to People, Inc (P2P)  http://p2pbridge.org

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here