spot_img
Sunday, July 21, 2024
Homeነፃ አስተያየትክቡር ዶ/ር ዓብይ-አስቸኳይ አዋጁን ተጠቅመው ጣምራ ቫይረሶችን (COVED-19 & COVID -ጎሳ) ያስወግዱ

ክቡር ዶ/ር ዓብይ-አስቸኳይ አዋጁን ተጠቅመው ጣምራ ቫይረሶችን (COVED-19 & COVID -ጎሳ) ያስወግዱ

ሰማነህ ጀመረ: ካናዳ
ቀን፤ ሚያዝያ 7፤ 2012

ፖለቲካ የሚንቀሳቀሰው በውስጡ ባለ የተገደበና ያልተገደብ የስልጣን መስተጋብር እንደሆነ ጆንሰን የተባለ ፀሐፊ በኤዞስ ምናባዊ ቧልት የእንቁራሪቶች መልካም አስተዳዳሪ ፍለጋ ተማፅኖ በአፈታሪክ አጫውቶናል። እንቁራሪቶቹ ለዚውስ አቤቱታና ተማጽኖ ያቀርባሉ። ልመናቸውን የሰማው ዚውስ ንጉስ ግንድን (king log) አስተዳዳሪ አርጎ ላከላቸው። ንጉስ ግንድ አንድም እንቁራሪት ሳያስከትል ብቻውን ውሃ ላይ ተንሳፎ ከመንበሩ ይሰወራል።

በዚህ የተበሳጩት እንቁራሪቶች የተሻለ አስተዳዳሪ እንዲሰጣቸው ዚውስን በድጋሚ ተማፀኑ። ዚውስም ንጉስ ስቶርክን (king stork) ላከላቸው። የተሻለው ሄዶ የባሰው መጣ እንዲሉ ስቶርክ እንቁራሪቱን ሁሉ ሰልቅጦ ተሰወረ። ተረቴን መልሱ… ለማለት ፈለግሁና የኤዞስ አፈታሪክ ለሃገራችን ፖለቲካ ያለውን ፋይዳ ማየት መረጥሁ።

ኢትዮጵያዊያን ከዓፄ ኃይለ ሥላሴ የተሻለ አስተዳዳሪ ለማግኘት ፈጣሪአቸውን አርባ ዓመት ከለመኑ በኋላ “መንግስቱ” የተባለ መሪ ሰጣቸው። ሲጀመር ከፈጣሪው ጋር የተጣላው መንግስቱ እንደ ንጉሥ ግንድ በኮምኒዝም መርከብ ላይ ተሳፍሮ አስራ ሰባት ዓመት ብቻውን ተንሳፎ ሕዝቡን አስለቀሰው። ሕዝቡም ለሁለት አስርት አመታት ከመንግስቱ የተሻለ አስተዳዳሪ እንዲሰጠው ፈጣሪውን ሲለምን ኖረ። በኮምኒስት ፍልስፍና የተዘፈቀው እና ከሕዝብ የተገለለው መንግስቱ ብቻውን እንደተንሳፈፈ ዝምባብዌ ሄዶ ተሰወረ። ፋጣሪም ንጉሥ ስቶርክን የመሰለ  “መለስ” የተባለ መሪ ላከላቸው። በሚአስገርም ሁኔታ አጅሬ ስትሮክ የኢትዮጵያን ሕዝብ ጨርሶ ለመሰልቀጥ ሰላሳ ዓመት ሞከረ። ሕዝብ የሚመካው በመሳሪያ አፈሙዝ ሳይሆን በፈጣሪ ሃይል በመሆኑ ተስፋ ያልቆረጠው ሕዝብ እንደ እንቁራሪቶቹ የተሻለ መሪ ለማግኘት ፈጣሪውን መለመኑና መማፀኑን ቀጠለበት።

በመሃሉ በምንም ሊተመን የማይችል ጥፋት በሃገርና በሕዝብ ላይ ደረሰ። የሚፈለገው መሪ እስኪገኝ ሕዝቡ በጎሳ ፖለቲካ እርስ በርሱ እንዲባላ ተደረገ። ሃገር የሚለው ነገር ኮስምኖ ክልል ሃገር ሆነ። ክልል እየኮሰመነ መጦ ጎጥ ከሃገር በላይ ተወደሰ። የኢትዮጵያ ታሪክ ተንቋሾ ወንበዴ፤ ዘረኛና ዘራፊ ጡንቻና ቦርጭ አውጥተው ሃገር ሁነው ነገሡ።

በሃያና በሃያአንደኛው ክፍለ ዘመን መኖራችን ተረስቶ ወጣቶች የዘመኑን እውቀትና ሳይንስ እንዳይቀስሙ ተደረገ። አገር ተረካቢው ትውልድ በጨለማ ውስጥ አደገ። ለጋራ ታሪካችንና ትውፊቶቻችን ባይተዋር ሆነ። የመጤና እርካሽ ባህል ሰለባ ሆኖ ተበላሸ። ማንነት ጠፋ፤ ሃገርና ሕዝብ የቁልቁለት ጉዞ ጀምረው በሙሉ ሊከስሙ ገደል አፋፍ ላይ ተንጠለጠሉ። ስቶርኮች ‘መለስ ሃ/ማሪያም’  ሕዝቡን ጠርገው ሊውጡት መዘጋጀታቸውን እያወቀም ኢትዮጵያዊያዊው እጁን ወደ ፈጣሪው ከመዘርጋት አላቆመም።

ሕዝብህን አድን እርስትህንም ባርክ እንዲሉ ምንጊዜም የኢትዮጵያን ጩኸት የሚሰማው አምላክ እርስዎን ከጨለማ አውጥቶ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አስተዳዳሪ አርጎ አነገሰዎት። ሕዝቡም ሙሉ ለኩልሄ በሚመስል መልኩ በእልልታ ተቀበለዎት። የንግስና ንግግርዎን ዓለም ሁሉ አደነቀው። ኢትዮጵያም ከስልሳ ዓምት ጉስቁልና በኋላ ስርየት ያገኘች መሰለ። ከጎሳ ፖለቲካ አራማጅ በስተቀር በርስዎ ንግሥና ያልተደሰት ኢትዮጵያዊ አልነበረም።

አባቶች፤ እናቶች፤ ካህናትና ምእመን ለርስዎ እድሜና ጤና እየተመኙ ፀለዩ። እናቶች የቡና ወግ ሲጀምሩ ያ-ልጃችን ደህና አድሮ ይሆን እያሉ የመንደር ወሬ እና የአፍ ማሟሻ እስከመሆን ደረሱ። የእናቶች ወግ ጭንቀትና መቆርቆር የወለደው ሲሆን መልእክቱም ልጃችንን ክፉ አይንካው እንደሆነ ሳይረዱት አይቀርም። ከሁሉም በላይ የኢትዮጵያን አንድነት፤ ክብርና ዝና ለማስመለስ ቃል ሲገቡ ይበልጥ ተወደዱ። ለሰላሳ ዓመት እንደማሽላ ውስጡ እያረረ ላይ ላዩን ሲስቅ የነበረ ህዝብ ከመደሰቱ የተነሳ ምድራዊው ሙሴ ሲል አሞካሸዎት። እስከዚህ ድረስ የተመለኩና የተመረጡ መሪ የመሆንዎን ምስጢር በጥልቀት ማየት እያቃተን ደገፍንዎት።  

በሰኔ 2018 ዋሽንግቶን ከተማ ሄደው የትውልደ ኢትዮጵያዊያንን ቀልብ በሚደንቅ ሁኔታ ተቆጣጠሩት። ይሄን ፀሐፊ ጨምሮ የሰዓታት መንገድ ተጉዞና ወፍ ሳይጮህ አዳራሽ ግብቶ እርስዎን ለማየት የተሰለፈውን ኢትዮጵያዊ ብዛት ላየ ሕዝብ መሪውን ሲወድና ሲአፈቅር ምን እንደሚመስል ግንዛቤ እንድናገኝ ሆነ። በኢትዮጵያዊያን መካከል የነበረው መፈቃቀር፤ መተሳሰብ፤ መደጋገፍና የኢትዮጵያዊነት ስሜት ቃላት ከሚገልጸው በላይ ነበር። ለዓመታት በጎሳ ፖለቲካ ተለያይተውና ተነፋፍቀው ስለነበር ኢትዮጵያዊያን በመድረኩ ተገናኝተው ሲተሳሰቡ ማየት ልብ የሚነካ ትይንት እንደነበር በቦታው የነበረ ያውቀዋል።  ሰላሳ ሽህ ሕዝብ ወደያዘው አዳራሽ ገብተን ያየነውን ትዕይንት መግለጽ አስፈላጊ ስላልሆነ በደፈናው ታሪክ ሆኖ ይቀመጥ።

ክቡር ዶ/ር ዓብይ ፤

ይህ ሁሉ የሆነው በርስዎ ምክንያት እንደሆን አያጡትም። ለሰላሳ ዓመት ተቀብራ የነበረችው ባለብዙ ዘመን ታሪከኛዋ ኢትዮጵያ ከመቃብር ወጣ በአደባባይ ታየች።  በዚህ ሁኔታ የተቀበለዎትን ሕዝብ ሲአስተዳድሩ ሁለት ዓመት ሆኗል። በዚህ ጊዜ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡትን ያህል መጠነ ሰፊ ፈተናዎችና ተግዳሮቶች እንደገጠመዎት እናምናለን።  

በመደመር መርህ ከተናገሩትና ከጻፉት በተቃራኒው እየተሰራ፤ አንድነትን የሚሸረሽር፤ የጎሳ ፌድራሊዝምን የሚአፋፋ ተግባር በአስተዳደርዎ ይፈጸማል። ይህ ሁሉ በእርስዎ ይሁንታ ይፈጸም ወይስ የእርስዎን ስምና ዝና ተጠቅመው በአካባቢዎ የሚገኙ ጭልፊቶችና የጎሳ ፖለቲካ አራማጆች ያደረጉት መሆኑን ለማወቅ እንደተቸገርን አለን።

ጉዳዩ ጠርጥር ገንፎም አለው ስንጥር በሚል የእርስዎ እጅ ሳይኖርበት አይቀርም እያለ የሚጠራጠረው ሕዝብ ቁጥር ተበራክቷል። መጠራጠሩ ሥር የሰደደው ደግሞ ሰፊ ድጋፍ በሰጠዎት ዓማራ ሕዝብ እንደሆነ አያጡትም። የአማራውን ድጋፍ ማጣት በሃገሪቱ ፖለቲካና በስልጣንዎላይ የሚኖረው አንድምታ እጅግ ከፍተኛ ነው። ለጥርጥሩና ላለመተማመኑ ዋናው ምክንያት የሃገር አስተዳዳሪዎች እና የፖለቲከኞች አሰራር በጎሳ ፖለቲካ ስሌት ስለሚቀመር ነው። የጎሳ ፖለቲካ ክትባት የሌለው ሃገርና ሕዝብ አውዳሜ ካንሰር ስለሆነ እርስዎን ጨምሮ ሁሉም ሊፀየፈው ይገባል።

ክቡር ዶ/ር ዓብይ ፤

ኢትዮጵያን እዚህ ደረጃ ያደረሳት በጎሳ ፖለቲካ የተቀረፀው ሕገ መንግስት መሆኑን የሚጠራጥሩ አይሆንም። ይህ አቋምዎ ከሆነ የጎሳ ፖለቲካ አራማጆችን ማንቆለጳጰስ አያስፈልግዎትም። የአንድ ክልል ተማሪዎች ታግተው ደብዛቸው ሲጠፋ እያዩ ዝም አሉ-ለምን? የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አደራጀ በሚል ውንጀላ ክልሉ እንዲዳከም ሆኗል። በአንፃሩ የኦሮሚያ ክልል በፌድራል በጀት ልዩ ኃይሉን ሲአደራጅ እያዩ ዝምታን መረጡ- ለምን? ኦነግን ሳያፀዱ የአማራ ፋኖን ማፁዳት ፈለጉ-ለምን?። እነዚህ ድርጊቶች የሚከናወኑት እርስዎ ሳያውቁት ከሆነ ሃገሪቱን እየመሩና እያስተዳደሩ ነው ማለት አይቻልም። ቸልተኝነት እየበዛ ሲሄድ ይበልጥ ለጥርጥር ተጋላጭ ይሆናሉ።

አሁን ያለው አሰራር ሌላ ትርጉም ካልተሰጠው በስተቀር አስተዳደርዎ የሕግ የበላይነት ማክበርና ማስከበር የተሳነው ይመስላል። የህግ የበላይነት ሲላላ የጎሳና የሃይማኖት ፖለቲካ አራማጆች ጥርስ አውጥተው ይናከሳሉ፤ ኃይልና ጉልበት አግኝተው አገር እንዲአፈርሱ ዕድል ይሰጣል። በተኩላ ተከበው ከሆነ የተኩላዎች ፀረ-ኢትዮጵያ አቋምና ፖለቲካ ለስርዎም ለሃገርም የሚበጅ አይደለምና እሹሩሩ ይብቃ። ኢትዮጵያን ለመታደግ በድጋሚ ወደ እውነተኛው የፖለቲካ አቋምዎ እና እምነትዎ ይመለሱ። ያመነ በእምነቱ ይድናል ነውና።

ስለዚህ አላሰራ ያለዎት የኮቪድ-19 ቫይረስ ሳይሆን ሕጋዊ እውቅና ተሰጦት የተሰራበት የጎሳ ፖለቲካ ቫይረስ ነው። ፍፁም አውዳሚ የሆነውን ኮቪድ- ጎሳን በአስቸኳይ ያስወግዱ። ኮቪድ-19 ክትባት ተገኝቶለት ሁላችንም እንድን ይሆናል። ኮቬድ- ጎሳ ክትባት የማይገኝለት ሕዝብና አገር ሳያወድም አይመለስም።

ሁሉም ለበጎ ነው እንዲሉ ኮቪድ-19 ጎሳ ለይቶ ስላላጠቃ  የኢትዮጵያን ሕዝብ አቀራርቧል ብለን እናምናለን። ስለሆነም የሕዝብ ተወካዮች አደራ ከመስከረም ጀምሮ የፀና ስለማይሆን አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተጠቅመው የጎሳ ፌድራሊዝም የሚደነግገውን ሕግ  ከኢትዮጵያው የፖለቲካ አውድማ ይንቀሉልን። ይህን ካላደረጉ እርስዎም ሆነ ሃገሪቱ ስርየት አታገኙም። አገር የሚተዳደረው በውስጣዊና ውጭዊ መገደቢያ ታግዞ እንጂ ልቅ በመተው ስላልሆነ የህግ ገደብ ይደረግ። እንደዚዎስ ያለገደብ በቸልተኝነት መምራት ከቀጠሉ ሊአድኑት የፈለጉትን ሃገርና ሕዝብ ይዘውት ይጠፋ እንደሆን እንጂ ሃገርዎንና ሕዝቧን አይታደጓቸውም። አንድ ቀን ንግሥ ትሆናለህ ብለው የተነበዩትን እናትዎን ከኢትዮጵያ ሕዝብ እርግማን ይታደጓቸው። አበቃሁ-ነን ሶቤ!

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

1 COMMENT

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here