spot_img
Thursday, November 30, 2023
Homeነፃ አስተያየትየሥልጣን ሩጫ ወይስ ህገ መንግስታዊ ፍጥጫ? (ኤፍሬም ማዴቦ)

የሥልጣን ሩጫ ወይስ ህገ መንግስታዊ ፍጥጫ? (ኤፍሬም ማዴቦ)

advertisement
Ephrem Madebo
ኤፍሬም ማዴቦ

ኤፍሬም ማዴቦ (emadebo@gmail.com)
ሚያዚያ 29 ፤ 2012 ዓ.ም.

ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ መሳፍንቶች የከፋፈሏትን ኢትዮጵያ አንድ አድርገው ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ ተብለው ኢትዮጵያን መግዛት ከጀመሩ በኋላ በነበሩት 165 አመታት ውስጥ አገራችን ኢትዮጵያ ከግጭትና ከጦርነት ተላቅቃ ሙሉ ሃይሏን ለዕድገትና ብልፅግና ያዋለችበት ሃምሳ ተከታታይ አመታት አልነበሩም። በፈጣን ዕድገታቸው አለማችንን ያስደነቁትና የ“ኢሲያ ነብሮች” በመባል የሚታውቁት አገሮች ዛሬ ያሉበት ደረጃ ላይ የደረሱት እኛ በተለያየ መልኩ ግጭትና ጦርነት ውስጥ በነበርንባቸው ባለፉት 75 አመታት ውስጥ ነው። ኢትዮጵያ በታሪኳ የተዋጋቻቸው ጦርነቶች አብዛኛዎቹ ካልገዛናችሁ ወይም ካልተቆጣጠርናችሁ ብለው ባህር አቋርጠው ከመጡብን የውጭ ተስፋፊዎችና ቅኝ ገዢዎች ጋር የተደረጉ ጦርነቶች ቢሆኑም፣ አንዳንዶቹ ጦርነቶች ግን እኛው ኢትዮጵያዊያን እርስ በርስ የተጋደልንባቸው ጦርነቶች ናቸው። እነዚህ ጦርነቶች እንደ ህዝብ ምንግዜም የማንረሳቸውን ትልልቅ ጀግኖች እና ዛሬም ስማቸው ሲነሳ የምናፍርባቸውን ከሃዲ ባንዳዎች አሳይተውናል። ታሪክ የእኛን የኢትዮጵያዊያንን ስም የሚያነሳው፣ ኢትዮጵያዊያን የቱንም ያክል ባይስማሙና ባይግባቡም የውጭ ጠላት ሲመጣባቸው ግን የውስጥ ልዩነቶቻቸውን ረስተው ፊታችውን በጋራ ወደ ጠላታቸው ያዞራሉ በሚል ሌሎች በማይጋሩን እሴት ነው። ይህንን ለዘመናት አብሮን የቆየ እሴት ዛሬ አገር በቀል ሃይሎች አደጋ ላይ ጥለውታል።

ይህ የማንነታችን መታወቂያ የሆነውና ዛሬን ለማየታችን ዋስትና የሆነን አኩሪ ባህል፣ በታሪክ ሚዛን ቢመዘኑ የቁምነገር ዘመናቸው አራት ቀን በማይሞላ ነገር ግን በየቀኑ አራት ኪሎ ካልገባን እያሉ በሚያላዝኑ ስግብግብ “የቅዳሜ ፖለቲከኞች” እየተሸረሸረ ነው። ይህንን ሁለት ስርነቀል አብዮቶች እንኳን ሊያጠፉት ያልቻሉትን ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ ማህበራዊ ወረት ከሥልጣን ጥማትና ከባዶ ጩኸት ውጭ ምንም ሃሳብና መላ የሌላቸው ፖለቲከኞች በ”ህገ መንግስት” ሰበብ ካላጠፋነው እያሉ ነው። እነዚህ ባለፉት ሁለት አመታት ቁጥራቸው እንጂ ስራቸው ተነግሮ የማያውቅ ፖለቲከኞቻችን ከሰሞኑ የሥልጣን ሱስ አስተባብሯቸው “ሁላችንም እኩል ነን” የሚል አዲስ ነጠላ ዜማ በጋራ ለቅቀዋል።

ታሪካዊ ጠላቶቻችን ኢትዮጵያን በገዛ የተፍጥሮ ኃብቷ “እኛን ካልሰማሽ . . . ወዮልሽ” እያሉ በጋራ እየዛቱብን ነው። ልባቸው በፈጸሙት ግፍና በዘረፉት ኃብት ልክ ያበጠ አገር በቀል የጨለማ ሃይሎች የሁላችንም የጋራ ጠላት የሆነውን ድህነትን እና ኋላ ቀርነትን ትተው በአንድነታችን ላይ ዘምተዋል። ኮሮና የሚባል የተፈጥሮ መቅሰፍት ብዙዎቻችንን ከቤታችን እንዳንወጣ አድርጎናል። በእንዲህ አይነቱ መንግስት፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ሃይሎች፣ምሁሩና የአገር ሽማግሌው ቁጭ ብለው መላ መፈለግ በሚገባቸው ወቅት፣ መስከረም 30 ካለፈ “ሁላችንም ንጉሶች” ነን፣ ከመስከረም 30 በኋላ የሁላችንም ቤት ሚኒልክ ቤተ መንግስት መሆን አለበት፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ከመስከረም 30 በኋላ ወታደሩም አይታዘዝም የሚሉ አሳፋሪ የፖለቲካ ቁማርተኞች ተፈጥረው ፖለቲካችንን እያመሱት ነው። እንዲህ ከውጭም ከውስጥም በተከበብንበት የታሪክ አጋጣሚ፣ ታሪክን ወደኋላ ዘመንን ወደፊት የማይመለከት እና ለጠላት የሚመች አገር በቀል ሃይል መፈጠሩ እነ ደጃዝማች ኃ/ሥላሤ ጉግሳ ከዚህ የባሰ ምን አደረጉ የሚል ጥያቄ እንድንጠይቅ አስገድዶናል።

አገራችን ኢትዮጵያ ሁሌም የሚያስቡላት አዋቂዎችና የሚሞቱላት ጀግኖች ስላሏት ከሃዲዎችን እየረሳናቸው ነው እንጂ ክህደት፣ ሴራና ዛቻ ለኢትዮጵያ አዲስ ነገር አይደሉም። የዛሬውን ዛቻና ሴራ ልዩ የሚያደርገው የውጭ ሃይሎች በኛው በራሳችን የተፈጥሮ ኃብት ላይ “እኛን ስሙን” ማለታቸውና የአገር ውከስጥ ሃይሎች ደግሞ የራሳችንን ህገ መንግስት ተጠቅመው እኛንም እነሱንም የሚያጠፋ ቀውስ ውስጥ ሊከቱን እየሞከሩ መሆናቸው ነው። ለመሆኑ ከመስከረም 30 በኋላ ሁላችንም እኩል ነን ሲባል ምን ማለት ነው? ማን ከማን ጋር ነው እኩል የሚሆነው? በተለይ ከመስከረም 30 በኋላ ወታደሩም፣ፖሊሱም ዜጎችም አይታዘዙም የምትለዋ አባባል ያቺ የለመድናት ቀጭን ትዕዛዝ ናት? ማሳሰቢያ ናት? ወይስ ምንድናት? ለምድነው ወታደሩና ፖሊሱ የማይታዘዘው? ደግሞስ ለማነው ይህ ሃላፊነት የጎደለው መልዕክት የተላለፈው?

አንዳንዴ ከእይታ አድማስ መጥበብ አንዳንዴም ከራስ ስንፍና ወይም ከኑሮ ጫና የተነሳ የሰው ልጅ የወደፊቱን ማየት ሊሳነው ይችል ይሆናል፣ እግዜር ያሳያችሁ ምን ጉድ ቢፈጠርና ምን አይነት ዘመን ቢመጣ ነው ምርጫው በተያዘለት ሰሌዳ ቢደረግ ኖሮ

በምርጫው ተወዳድረን አገር እንመራለን ብለው ሲሰብኩን የሰነበቱ ፖለቲከኞች ዛሬ በአገርና በህዝብ ላይ እየመጣ ያለውን ትልቅ አደጋ ማየት ተስኗቸው በህልማቸውም በውናቸውም “ሥልጣን ስጡን” እያሉ የሚጩኹት? እነዚህ የማያዩ፣የማይሰሙና የማያስተውሉ ፖለቲከኞች መስከረም 30 ቢመጣስ እኛንም እንደነሱ የማናይና የማንሰማ ከማድረግ ውጭ ሌላ ምን ሊያደርጉ ይሆን? ይህንን የሁላችንንም አለማየትና አለመስማት ይሁን እኩልነት የሚሉት?

የሰሞኑን አነጋጋሪ ህገ መንግስታዊ ቀውስ በተመለከተ በየሜዲያው እየቀረቡ “ህዝብ” ያውቃል፣ “ህዝብ” ከጎናችን ነው እያሉ ጆሯችንን ሲያደነቁሩ የሰነበቱ ፓርቲዎች ምን ያክል የኢትዮጵያን ህዝብ እንደሚያውቁትና ምን ያክል እንደሚያስቡለት የምናውቀው ያ የሚያስቡለትና የሚጨነቁለት ህዝብ እንዲያነበው የጻፉትን መግለጫ ስናነብ ነው። ብዙዎቹ መግለጫዎች የተጻፉት የኢትዮጵያ ህዝብ በማያውቀውና በማይሰማው በውጭ አገር ቋንቋ ነው። ይታያችሁ እነዚህ እፍረተ ቢሶች ናቸው በነጋ በጠባ በህዝብ ስም የሚምሉት። ከእናንተስ ጎመን በጤና!

ከሰሞኑ ጀዋር መሐመድና ልደቱ አያሌው OMN ላይ ቀርበው በድፍረት ሊነግሩን እንደሞከሩት የኢትዮጵያ ህገ መንግስት የሥልጣን ክፍተት እንዳይኖር ሆን ተበሎ ታስቦበት የተጻፈ ህገ መንግስት አይደለም። እንዲያውም ይህ ህገ መንግስት ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው ሁኔታ እንደሚመጣ የገመቱ ሰዎች ሆን ብለው የጻፉት ህገ መንግስት ነው። አንዳንድ የህገ መንግስቱን አንቀጾች ልብ ብሎ ለተመለከተው ሰው፣ ህገ መንግስቱ ሆን ተብሎ አንድ ሰው ብቻ ወይም አንድ ቡድን ብቻ ሁሌ ኢትዮጵያን ይመራል በሚል እሳቤ የተጻፈ የሚመስል ህገ መንግስት ነው። ለምሳሌ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ፓርላማውን በትኖ አዲስ ምርጫ እንዲጠራ የማድረግ ሥልጣን ያለው ጠ/ሚኒስትሩ ነው እንጂ የህግ አውጪው አካል እንዲህ አይነት ሥልጣን የለውም። የፓርላማ ሥርዓት ባለባቸው አገሮች ውስጥ የህግ አውጪው አካል የህግ አስፈጻሚውን አካል ከሚቆጣጠርባቸው ህገ መንግስታዊ መንገዶች አንዱ በመስተዳድሩ ላይ የ”እምነት የለኝም ድምፅ” ሰጥቶ መስተዳድሩን በትኖ አዲስ ምርጫ እንዲጠራ የማድረግ ሥልጣን ያለው መሆኑ ነው። የኢትዮጵያ ህገ መንግስት እንዲህ አይነቱን ትልቅ ሥልጣን የሰጠው ለጠ/ሚኒስትሩ ነው። ይህ ማለት ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ የህግ አስፈጻሚው አካል እንዳሻው ቢጨማለቅ፣ይህንን አካል የፈጠረው ፓርላማ ሊቀጣው ወይም ከሥልጣን ሊያባርረው አይችልም ማለት ነው። ይህንን በየትም አገር የሌለ የተገላቢጦሽ ሥልጣን ለጠ/ሚኒስትሩ የሰጠውንና እያንዳንዱ ክልል ያለ ምንም ቅደመ ሁኔታ ተገንጥሎ አገር የመሆን መብት አለው ብሎ የደነገገውን ህገ መንግስት ነው አቶ ልደቱ አያሌውና ጀዋር መሐመድ አፋቸውን ሞልተውና በኩራት በአዋቂዎችና በአርቆ አሳቢዎች የተጻፈ ህገ መንግስት ነው ያሉት። ድንቄም አርቆ አሳቢዎች! አርቆ ማሰብ ማለት ወደፊት ሊሆን ወይን ሊከሰት የሚችልን ነገር ከግምት ውስጥ ማስገባት ማለት ነው። ይህ ህገ መንግስት በአርቆ አሳቢዎች ተጽፎ ቢሆን ኖሮ ዛሬ የገባንበት ቅርቃር ውስጥ በፍጹም አንገባም ነበር።

አቶ ልደቱ አያሌውና ጀዋር መሐመድ የምርጫውን መራዘምና ህገ መንግስቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላል የሚለውን በተመለከተ ባደረጉት ውይይት ላይ የነበራቸውን ትኩረት አልወደድኩትም። ህገ መንግስቱ የምርጫ መራዘምን በተመለከተ ምንም ነገር አለማለቱ እኔም የምደግፈው ሃሳብ ነው። የጠ/ሚኒስትር አቢይ አህመድ መንግስትም ምርጫው በተያዘለት ሰሌዳ መካሄድ አለበት ከማለት ውጭ አንድም ቀን ምርጫው ይራዘም የሚል ክርክር ውስጥ ገብቶ አያውቅም። ምርጫው በሚቀጥለው ነሐሴ ወር ላይ የማይካሄደው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በብዙ አገሮች ውስጥ ከአቅም በላይ የሆነ የአስቸኳይ ግዜ ሁኔታ ስለተፈጠረ ነው። የኢትዮጵያን ህገ መንግስት የጻፉ ሰዎች መመልከት የነበረባቸው እንደዚህ አይነት ሁኔታ ሲፈጠር ምን መደረግ አለበት የሚለውን ነበር። ይህንን አለተመለከቱም፥ አለመመልከታቸው ስህተት ነው። ይህ ስህተት ነው ዛሬ የገባንበት ህገ መንግስታዊ ቀውስ ውስጥ የከተተን። ሌላው ያለወደድኩላቸው ነገር ሁሉቱም ሰዎች ይህንን ስህተትና የህገ መንግስቱን ደካማ ጎን እንደጠንካራ ጎን መውሰዳቸው ነው፥ ይህንን አቋም እንዲይዙ ያደረጋቸው ደግሞ ወይይታቸውን ሲጀምሩ “ምርጫውን ማራዘም” የሚል ቁንፅል ሃሳብ ይዘው በመጀመራቸው ነው። ምርጫ በብዙ ሁኔታዎች የተነሳ ሊራዘም ይችላል። ለምሳሌ፥ እንደኮሮና አይነት ሰዎች ከተወሰነ ቁጥር በላይ አንድ ቦታ ላይ እንዳይሰበሰቡ የሚከለክል የተፈጥሮ አደጋ ወይም ሌሎችም የተፈጥሮ አደጋዎች በስፋት ሲከሰቱ፥ አገራችን በሁለትና ሶስት ግምባሮች ጦርነት ውስጥ ከገባች፥ ባለፉት ሁለት አመታት እንዳየነው የርስ በርስ ግጭቶችና መፈናቀሎች ሲኖሩ ወዘተ ምርጫ ሊራዘም ይችላል። ስለዚህ ህገ መንግስቱ እንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ምን መደረግ እንዳለበት በግልጽ አለማስቀመጡ ስህተት ነው፥ ስህተት ደግሞ ጠንካራ ጎን አይደለም።

ህገ መንግስት የአገር መሪዎች፣በሥልጣን ላይ ያለ ፓርቲ፣ ወይም ማናችንም ማድረግ የምንፈልገውን ለማድረግ የማንፈልገውን ደግሞ ለመከልከል በፈለግን ቁጥር ጎትተን የምናሻሽለው ተራ ሰነድ አይደለም። ህገ መንግስት የህዝብ ቃል ኪዳን ሰነድ ነው።ይህ ሰንድ እንዲሻሻል ህዝብ መፍቀድ አለበት፣ከተሻሻለ በኋላም በህዝብ መጽደቅ አለበት። ይህ ለሁላችንም ግልፅ ሊሆን ይገባል። ሆኖም ግን አንድ ህገ መንግስት እንዲህ አይነት ክብርና ጥበቃ የሚሰጠው ሁላችንም በስምምነት ጽፈነው በህዝበ-ውሳኔ ሲጸድቅ ነው። ዛሬ በስራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ህገ መንግስት በምንም መልኩ እንዲህ አይነት ሰነድ አይደለም። ግን ይህም ሁሉ ሆኖ ለኛም ለአገራችንም በሚበጅ መልኩ ልናሻሽለው ይገባል እንጂ “ሁላችንም ያልጻፍነው” እና “ህዝብ ያላጸደቀው” ሰነድ ነውና ለህገ መንግስቱ አንታዘዝም እያልን እንዳሰኘን የምንደልዘውና የምንቀይረው ሰነድም አይደለም።

ዛሬ በአንድ በኩል ህገ መንግስቱ በሚላቸውና በማይላቸው ጉዳዮች የተነሳ አገራችን ኢትዮጵያ ትልቅ የህልውና አደጋ ላይ ወድቃለች፣ በሌላ በኩል ደግሞ “በገዛ ዳቦዬ ልብ ልቡን አጣሁት” እንዲሉ ኢትዮጵያ በራሷ የተፈጥሮ ኃብት የተነሳ የጥፋት ድግስ እየተደገሰባት ነው። ከዚህ በተጨማሪ ኮሮና የሚባል አለማችንን ከአራት ወር በላይ በአንድ ሙዚቃ ያስጨፈረ፣ ብዙ ህዝብ የለከፈና የገደለ ወረርሽኝ እኛም አገር ገብቶ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖብናል። እንዲህ አይነት በሦስት አቅጣጫ የመጣ አደጋ አገርን ሲያስጨንቅ የአንድ አገር ህዝብ፣ መንግስትና የፖለቲካ ልህቃን ምንድነው ማድረግ ያለባቸው?

እንዲህ አይነቱ ትልቅ አደጋ የመጣው እንግሊዞች ላይ ቢሆን ኖሮ እኔ እርግጠኛ ነኝ ቦሪስ ጆንሰንና ጀርሚ ኮርብን ከሌሎቹ ፓርቲዎች ጋር ሆነው “ምን ይሻለናል” ብለው መምከር ይጀምሩ ነበር፣ አሜሪካ ውስጥ ቢሆን ኖሮ ደግሞ በ2001 መስከረም ወር ላይ እንዳየነው የአሜሪካ ህዝብ፣ ዲሞክራቶችና ሪፑብሊካን አንድ ላይ ይቆሙ ነበር። የኛዎቹስ? የኛዎቹማ ነገሩንኮ! ሁሉም ለመንገስ ዘውዳቸውን አሰርተው መስከረም 30ን እየጠበቁ ነው። የኛዎቹማ እነሱ እራሳቸውም ስሙ ቢባሉ የማይሰሙትን የመግለጫ ጋጋታ ይደረድራሉ። የፖለቲካ ፓርቲያቸውን ከአገር በላይ፣ የፓርቲ መሪዎችን ደግሞ ከፓርቲው በላይ አድርገው የሚመለከቱ የኛ ፖሊቲከኞችማ አገርና ህዝብ ግራ ተጋብተው የመሪ ያለህ እያሉ ሲጮሁ እነሱ ጭራሽ የባሰ ግራ ያጋቡናል። በየቴሊቪዥኑ መስኮት ላይ ብቅ እያሉ ከችግር መውጪያ ሳይሆን የባሰ ችግር ውስጥ የሚከት የወሬ ቱማታቸውን ይለቁብናል። ልህቁ ይሳለቃል፣ ፖለቲከኛው ይዝታል፣ የክልል መሪ ነኝ ባዩ “ህገ መንግስቱ ይከበር” እያለ ቀንና ማታ ህገወጥ ስራ ይሰራል፣ መሪዎቻችን እንዳረጀ የግድግዳ ላይ ሰአት በቀን አንዴ ነው በትክክል የሚያስቡት። ለመሆኑ የነማን አገር ናት እንዲህ መጫወቻ የሆነችው? እኛስ የነማን ልጆች ሆነን ነው ማንም ወፍ ዘራሽ በተናገረ ቁጥር “አፍህን ዝጋ” ማለቱን ትተን ጡት እንደሚጠባ ህፃን ኮሽ ባለ ቁጥር የምንደነግጠው?

ወደድንም ጠላን አገራችን ኢትዮጵያ የምትሆነው እኛ ልጆቿ እንድትሆን የፈቀድነውን ብቻ ነው። አንባቢ ሆይ ይቺ አባቶችህ ያቆዩልህ አገር ኢትዮጵያ አንተ/ቺ እንድትሆን የምትፈልገውን እየሆነች ነው? ካልሆነች ከዛሬ ጀምሮ በዝምታ ማለፍ ይብቃህ/ሽ! ዝምታ መስማማት ነው። ዝምታ አንቺም አንተም የማትፈልጉት ነገር እንዲሆን መፍቀድ ነው። የዛሬዋ ኢትዮጵያ የኛ ዝምታና የተራ ካድሬዎች ድፍረት ውጤት ናት። ኢትዮጵያ የሁላችንም አገር መሆኗ የሚረጋገጠው የኛ ዝምታ ሲሰበርና የካድሬ ደፍረት ሲተነፍስ ብቻ ነው።

ዛሬ አገራችን ኢትዮጵያን ከገባችበት አጣብቂኝ ጎትተን ለማውጣት ብዙ አማራጮች አሉን፣ ብዙ መንገዶችም አሉን። እኛ ኢትዮጵያዊያን ተስማምተን መንገድ መምረጥና በመረጥነዉ መንገድ ላይ በስምምነት መሄድ ነው የተሳነን እንጂ መንገድማ ሞልቷል። ማዕበል በሚያናጋው ውቅያኖስ ላይ በመርከብ ስንጓዝ ህይወታችን አደጋ ላይ ከወደቀ መጀመሪያ ማዳን ያለብን መርከቡን ነው፣ መርከቡን ከማዕበሉ ከታደግነው ሁላችንም እንድናለን። የተሸከመንን መረከብ ረስተን ሁላችንም እራሳችንን ለማዳን የየራሳችንን እርምጃ መወሰድ ከጀመርን ግን እኛም መርከቧም የመጥፋት ዕድላችን ትልቅ ነው። የአገራችን የኢትዮጵያ ጉዳይ ከመርከብም በላይ ነው። የኢትዮጵያ ህልውና አደጋ ላይ ሲወድቅ ያለን ብቸኛ አማራጭ ኢትዮጵያን ማዳን ነው። ህግ መንግስትና ፖለቲካ ኢትዮጵያን ለማዳን መሳሪያ ይሆኑናል እንጂ ኢትዮጵያን ከማዳን ሊያቆሙን አይገባም። ኢትዮጵያን ማዳን የሁላችንም ተቀዳሚ ስራ ነው። ይህንን ለማድረግ የፓርላማ ውሳኔ መወሰን ካለብን እንወስናለን፣ የፖለቲካ ስምምነት ማድረግ ካለብን እናደርጋለን፣ መንግስት ኢትዮጵያን ለማዳን የሚወስደው እርምጃ ኢትዮጵያን ያድናል ብለን ካመንን ከመንግስት ጎን እንቆማለን። ህገ መንግስቱን ማሻሻል ካለብን እናሻሽላለን፣ አዲስ ህገ መንግስት መጻፍ ካለብን እንጽፋለን፣ ህገ መንግስቱን ማገድ ካለብንም እናግዳለን እንጂ “ህገ መንግስታዊ ቀውስ” በሚል ሰበብ አራት ኪሎን መኖሪያው ለማድረግ ለፈለገ የቀን ህልም አላሚ ሁሉ መንገድ አንጠርግም። እኛ እራሳችንም ብንሆን አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት ከመስከረም 30 በኋላ ህጋዊነት ወይም ቅቡልነት የለውም ብለን የ“ደቦ መንግስት” እናቋቁም የሚል ቅዠት ውስጥ አንገባም። አራት ኪሎ እኛ የፈለግናቸውን ሰዎች መርጠን የምናስገባበት የህዝብ ተመራጮች መኖሪያ ቤት ነው እንጂ ያየውና የተመኘው ሁሉ “መስከረም 30”ን ጠብቆ የሚገባበት የምሽት ክለብ አይደለም።

የ2012ቱ ምርጫ ለምን በተያዘለት የግዜ ሰሌዳ እንደማይደረግና መስከረም 30 ላይ የሥልጣን ዘመኑ የሚያልቀው የኢትዮጵያ ፓርላማና የጠ/ሚኒስትር አቢይ አህመድ መንግስት የሚቀጥለው ምርጫ እስኪደረግ ድረስ ለምን በሥልጣን ላይ መቆየት እንዳለባቸው ሁላችንም እናውቃለን። ህገ መንግስቱ ፈቀደ አልፈቀደ ዛሬ የመጣብንን የየፈጥሮ መቅሰፍት እንኳን እኛ ካለነሱ እርዳታ የማንኖረው መናጢ ድሃዎች፣ በእድገት ወደ ፊት የገፉ ኃብታም አገሮችም መቆጣጠር አልቻሉም። ታዲያ ምርጫው ለምን እንደተራዘመና አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት እስከሚቀጥለው ምርጫ ድረስ ለምን መቆየት እንዳለበት እያወቅን ለምድነው “መስከረም 30” የሚል “የሞኝ ዘፈን” የምንዘፍነው? ፈረሱም ሜዳውም እኛው እጅ ላይ እያለ ለምንድነው ሌላ ፈረስና ሌላ ሜዳ የሚያሰኘኝ? በእርግጥም ፖለቲከኞቻችን በነጋ በጠባ እንደሚምሉት ህዝብ ከነሱ ጋር ከሆነ፣ ለምንድነው የጠ/ሚኒስትር አቢይ አህመድ መንግስት ከተለያዩ ባለድርሻዎች ጋር የፖለቲካ ድርድር ውስጥ እንዲገባ ከህዝብ ጋር ሆነው የማያስገድዱት? ያለንበት ግዜ የግድ የፖለቲካ ስምምነት የሚያስፈልገው ግዜ እንደሆነ ሁላችንም ይገባናልኮ! ግን ይህ የፖለቲካ ስምምነት በግድ፣በአሉባልታና በዛቻ አይደለም የሚመጣው።

ከህገ መንግስቱ ውጭ ሌላ ምንም መንገድ የለም የምትለው አንተ የኢትዮጵያ መንግስት ሆይ፣ ከህገ መንግስቱና ከኢትዮጵያ ህልውና ለማነው ቅድሚያ የምትሰጠው? ይቺ አገርኮ ከህገ መንግስት ጋር የኖረችው 89 አመት ብቻ ነው። እሱም በትክክል ከተቆጠረ ነው። ምክንያቱም ህገ መንግስት ኖሮን በህገ አራዊት የኖርንባቸዉ በጣም ብዙ አመታት አሉ። ኢትዮጵያን አሁን ከገጠማት አደጋ ለማዳን ህገ መንግስቱም የኢትዮጵያ መንግስትም አማራጮች እንጂ ብቸኛ የመፍትሄ ባለቤቶች አለመሆናቸውን የኢትዮጵያ መንግስት መገንዘብም መረዳትም አለበት። አገራችን ኢትዮጵያ ዛሬ ከገባችበት ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውስ ለማውጣት ሌሎች ብዙ አማራጮች አሉ። አንዱና ትልቁ ሃላፊነት ከሚሰማቸውና ህዝባዊ አደራ መሸከም ከሚችሉ የፖለቲካ ባለድርሻዎች ጋር ቁጭ ብሎ መምከር ነው።

ኢትዮጵያ ዛሬ ከገጠማት አደጋ የምትድነው በተጻፈ ህገ መንግስት ብቻ ሳይሆን እንደገና በሚጻፍ ወይም በሚሻሻል ህገ መንግስት ሊሆን ይችላል፣ በፓርላማ ውሳኔ ሊሆን ይችላል ላይሆንም ይችላል፣ መንግስትን ጨምሮ ሌሎችም የፖለቲካ ሃይሎች በሚፈጥሩት የፖለቲካ ስምምነት ሊሆን ይችላል፣ ህዝብ ባልመረጣቸው ነገርግን ህዝብ በቀናነታቸውና በአርቆ አተዋይነታቸው የሚተማመንባቸው የሃይማኖት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን፣ታዋቂ ግለሰቦችና የፖለቲካ ልህቃን ተወያይተው በሚያገኙት የመፍትሄ ሃሳብ ሊሆን ይችላል። መንግስት እነዚህ ከላይ ስማቸው የተጠቀሰው የማህበረሰብ አባላት የሚገናኙበትን እና በአገራቸው ጉዳይ ላይ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ የሚያስችል ሁኔታ ማመቻቸት ነው ያለበት እንጂ የችግሮች ሁሉ መፍትሄ እኔ ብቻ ነኝ ብሎ በሩን ቀርቅሮ መኮፈስ አይደለም!

ስለዚህ በፈረንጅ ቋንቋ መግለጫ እየጻፋችሁ በመግለጫ የምትገሸልጡን የፖለቲካ ፓርቲዎች ሆይ፣ መስከረም 30 ካለፈ ወታደሩም አይታዘዝም እያላችሁ ግራ ገብቷችሁ ግራ የምታጋቡን ልህቃን ሆይ፣ ከህገ መንግስት ውጭ ሌላ አማራጭ የለም እያልክ የሃሳብ ድህነትን የምትሰብከው መንግስት ሆይ፣ እስኪ ለዚህች ብዙ ጀግኖች የህይወት መስዋዕትነት ለከፈሉላት አገር ስትሉ ቁጭ ብላችሁ ተማከሩና አገራችን ከተፈጥሮም (ኮሮና) ከፖለቲካም ቀውስ ነጻ የምትወጣበትን መንገድ በጋራ ፈልጉ። አገራዊ ምርጫም ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግርም መኖር የሚችሉት በተረጋጋ አገር ውስጥ ነውና እባካችሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ። ይህንን ማድረግ እንድትችሉ እግዚአብሄር መልካም ልብና አርቆ አስተዋይነትን ይስጣችሁ። አሜን!!!

ማሳሰቢያ ፡ በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሃሳቦች የጸሃፊውን/ የጸሃፊውን ሃሳብ እንጂ የድረ፟ገጹን ሃሳብ ያንጸባርቃል ማለት አይደለም፡፡ በድረ ገጹ ላይ ሃሳብዎን ለማሳተም ጽሁፍዎትን በሚከተለው የኢሜይል አድራሻ ይላኩልን ፡ info@borkena.com

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here