(በመስከረም አበራ)
ሰኔ 14 2012 ዓ. ም .
የሰኔ 15ቱን ግድያ በተመለከተ ብ/ጄ ተፈራ ማሞ “ያየሁት የሰማሁት” ብለው የፃፉትን ጦማር በዘ-ሃበሻ ድረ-ገፅ ሲነበብ ሰማሁት፡፡እውነት ለመናገር የሰኔ 15ቱ ድርጊቱ “ባይደረግ ደግ ነበር፤ ከሆነ ደግሞ የሞቱትን ሁሉ ነፍስ ይማር” ተብሎ ቢታለፍ እመርጣለሁ፡፡ሆኖም ነገሩ ከተፈፀመ ዕለት አንስቶ ከወደ መንግስት በኩል የሚነገሩ መረጃዎች(ያን ቅጠቢስ ዶክመንተሪ ጨምሮ)፣የዓይን ምስክር ነን ከሚሉ የአማራ መኳንንት የሚሰጠው ምስክርነት ሚዛናዊነት ማጣት “ነፍስ ይማር” ብሎ ብቻ ነገሩን መተው የሚፈልግን ሰው ላልፈለገው ምርምር የሚጋብዙ ናቸው፡፡የዛሬው የብ/ጄ ተፈራ ማሞ ምስክርነትም ከዚህ በፊት ከሰማኋቸው ወደ አንድ አቅጣጫ ካጋደሉ የመንግስት ፕሮፖጋንዳዎችም ሆነ የካድሬ ግለሰቦች ምስክርነቶች ብዙም የማይርቅ ሆኖ አግቸዋለሁ፡፡
“የሞተን ሁሉ ነፍስ ይማር” ብለን እንዳንቀመጥ ምስክር ነን ባዮች ከመጡ ዘንዳ ሚዛናዊ የሆኑ፣ለእውነቱ የሚቀርቡ ምስክርነታቸውን ቢያቀርቡ መጭው ትውልድ ከሰኔ 15ቱ ስህተት እንዲማር ያግዙ ነበር፡፡በተቀረ መንግስት ራሱ በዶክመንተሪ ፣የአማራ ክልል ባለስልጣናትን አማራ መገናኛ ብዙሃን ድረስ እያመላለሰ በማናዘዝ ያደነቆረንን የአንድ ወገን ፕሮፖጋንዳ ይዞ መምጣት አስተዛዛቢ እንጅ አስተማሪ ሊሆን አይችልም፡፡የዚህ የተንጋደደ አካሄድ ሌላው ጉዳት “የሁሉንም ነፍስ ይማር” ብሎ የተቀመጠውን ህዝብ ለሌላ ምርምር፣ለባሰ መከፋፈል የሚጋብዝ ነገር መሆኑ ነው፡፡
ከሰኔ 15 ማግስት ስለ ግድያው የሚሰጡ ምስክርነቶች ራሳቸውን መከላከል በማይችሉ ሟቾች ላይ የሚሰጡ በመሆናቸው ከአድሎ የፀዱ፣በተቻለ መጠን የግራ ቀኙን እውነት ያካተቱ ቢሆኑ ለምስክሮቹም ልዕልና፣ ለእኛ ለአድማጮችም ይህን ስህተት ላለመድገም ትምህርት የምንወስድበት በጎ አጋጣሚ ይሆን ነበር፡፡ብ/ጄ ተፈራ የፃፉት የምስክርነት ጦማር እነዚህን ልዕልናዎች ካሉት በሚል በጥንቃቄ እና በተደጋጋሚ ነበር ያዳመጥኩት፡፡ ሆኖም የጠበቅኩትን ያህል አዲስ መረጃ የያዘም ያሰብኩትን ያህል ሚዛናዊ ሆኖም አላገኘሁትም፡፡ በነገራችን ላይ ብ/ጄ ተፈራ ማሞ እና ኮሎኔል አለበል የዛሬ አመት የሰኔ 15ቱ ግድያ ተፈፀመ እንደተባለ በአማራ መገናኛ ብዙሃን ቀርበው ነበር፡፡ እናም ኮሎኔል አለበል በንግግራቸው ውስጥ ብ/ጄ አሳምነው ግድያውን በመፈፀም ተጠርጥረው እየተፈለጉ እንደሆነ ሲገልፁ ብ/ጄ ተፈራ ማሞ ግን አሳምነው ገዳይ እንደሆነ ባስረገጠ ሁኔታ ተናግረዋል፡፡በዚህ ንግግራቸቸው እንኳን ጓደኛ አንድ ህግ አክባሪ ሰው ለአንድ ለማያውቀው ሰው የሚሰጠውን ከፍርድ በፊት ነፃ ተደርጎ የመቆጠር መብት ሲነፍጉ አስተውያለሁ፡፡
ስለሆነም የብ/ጄ ተፈራን ምስክርነት ሚዛናዊነት ጥርጣሬ ውስጥ መክተት የጀመርኩት ከያኔ ጀምሮ ነው፡፡ሌላው ቀርቶ በብ/ጄ አሳምነው እና በብ/ጄነራል ተፈራ ማሞ መካከል ያለው ግንኙነት ራሱ እሳቸው ዛሬ እንደሚያወሩት የወዳጅነት ብቻ መሆኑ አጠራጣሪ ነው፡፡ይህን የምልበት ምክንያት በግድያው ማግስት በአማራ መገናኛ ብዙሃን ቀርበው የተናገሩት ንግግር የፖለቲካ ካድሬዎቹ እየተመላለሱ ከሚነግሩን የአንድ ወገን ፕሮፖጋንዳ የተለየ አለመሆኑን ስላስተዋልኩ ነው፡፡ይልቅስ ዝም ባሉት ኮሎኔል አለበል ላይ የተሻለ የገለልተኝነት እና ከፍርድቤት ቀድሞ ያለመፍረድ ህጋዊነት አስተውያለሁ፡፡ መሆን ያለበትም ይኽው ነው፡፡ በሰኔ 15ቱ ግድያ ያጣናቸው ሰዎች ሁሉም ይበጃል ያሉትን ለመስራት የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ነበሩ፡፡ ከሁሉም በላይ አሁን ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ በመሆናቸው ስለ እነሱ ማውራታችን ግድ ከሆነ እንኳን ማውራት ያለብን እውነቱን እና የምናውቀውን ሁሉ በምሉዕ ሁኔታ መሆን አለበት፡፡በከፊል የምንናገረው እውነት፣አድበስብሰን የምናልፈው ሃቅ፣አንጋደን የምናቀርበው ምስክርነት ጉዳት እንጅ ጥቅም ስለሌለው በብ/ጄ ተፈራ ምስክርነት ላይ ያየኋቸውን እንከኖች ወደ መዳሰሱ ልለፍ፡፡
ከመነሻው ጥያቄ ሆኖ የሚመጣው የአማራ ክልል የፖሊቲካ እና ወትድርና ባለስልጣናት ለግምገማ ለምን አዲስ አበባ ድረስ ተጓጓዙ የሚለው ነው?ግምገማው አዲስ አበባ በሚኖሩት አቶ ደመቀ መሪነት እንደተደረገ ተነግሮናል፡፡ቢሆንም ይህ ሁሉ ባለስልጣን ተንጋግቶ አዲስ አበባ ከሚሄድ ሰብሳቢው አቶ ደመቀ አንድ ግለሰብ ናቸውና ባህርዳር ቢመጡ የተሻለ ነበር፡፡በአሁኑ ወቅት ባህርዳር ለአማራ ባለስልጣናት እጅግ አስፈሪ ቦታ እንደ ሆነች በሰፊው ይወራል፡፡ይህ መሆን የጀመረው ከመቼ ወዲህ እና ለምንድን ነው? የሚለው መመርመር ያለበት ነገር ነው፡፡የተገምጋሚ ባለስልጣናት ወደ አዲስ አበባ ማምራትም ከባህርዳር አስፈሪ መሆን መጀመር ጋር የተያያዘ ነው ወይስ ሌላ ምክንያት አለው? የሚለው መጠየቅ አለበት፡፡አስፈሪነቱስ ለነአቶ ደመቀ ነው ወይስ ለክልሉ ባለስልጣናትም ጭምር ነበር?ማን ማንን ነው የሚፈራው?በምን ምክንያት? የሚለው በውል መጤን አለበት፡፡ ሁሉም ለአማራ ህዝብ ጥቅም በመስራት ላይ ልዩነት የላቸውም ከተባለ የሚያስተዳድሩት ክልል ዋና ከተማን እንደጦር የሚፈሩት ለምንድን ነው? የሚለው ነገር በጥብቅ መመርመር ያለበት ነገር ነው፡፡ይህንን የምለው በአማራ ብልፅግና አመራሮች እና የአማራ ህዝብ የልብ መራራቅ ሳቢያ የአማራ ክልል ለባለስልጣናቱ ወደማይታዘዝ የለየለት የብጥብጥ ቀጠና እንዳይቀየር ከፍተኛ ስጋት ያለኝ በመሆኑ ነው፡፡ይህ ደግሞ ከሰኔ 15ቱ አሰቃቂ ትዝታ ሳንወጣ ሌላ አሰቃቂ ነገር የሚያመጣ አደጋ አዝሎ ስለሚታየኝ ነው፡፡
ወደ ብ/ጄ ተፈራ ምስክርነት ስንመለስ ምስክርነታቸውን የሚጀምሩት አስራ ሶስት ሰዓት ፈጀ በተባለው ግምገማ ነው፡፡ በዚህ ግምገማ ብ/ጄ አሳምነው የሁሉም ባለስልጣናት ትኩረት ተደርጎባቸው እንደነበረ ነግረውናል፡፡በገምጋሚዎቹ የሚነሳው ዋናው የብ/ጄ አሳምነው ችግር ከፖለቲካ አመራሩ ጋር ተግባብተው መስራት የተሳናቸው ሰው መሆናቸው ነው፡፡(ይህን መስካሪው ብ/ጄ ተፈራም የሚያምኑበት ይመስላል)፡፡ የሁሉ ነገር ማጠንጠኛ ያለው በዚህ አለመግባባት ተብሎ በታለፈው ጉዳይ ላይ ይመስለኛልና ብ/ጄ አሳምነውን ከፖለቲካ አመራሩ ጋር የማያግባባቸው ምክንያት ምን እንደሆነ በብ/ጄ ተፈራ ምስክርነት ጦማር ውስጥ በደምብ ተፍተታቶ መቅረብ ነበረበት፡፡ ሆኖም ብ/ጄ ተፈራ ያለመግባባቱን ምክንያት በጨረፍታ እንኳን አይነግሩንም፡፡ያልነገሩን ግን ስለማያውቁት አይመስለኝም፡፡
ብ/ጄ ተፈራ በፅሁፋቸው መሃል መሃል ከብ/ጄ አሳምነው ጋር የረዥም ዘመን ጓደኛሞች/ወንድማማቾች እንደሆኑ እስከነገሩን ድረስ ብ/ጄ አሳምነው ከፖለቲካ አመራሩ ጋር የማያግባባቸውን ነገር ለጓዳቸው ተፈራ ማማከራቸው የሚጠበቅ ነገር ነው፡፡መስካሪው በፅሁፋቸው አብረን ተቀምጠን ታደምን ባሉት ግምገማ ላይ ብ/ጄ አሳምነው ያጋጠማቸውን ነገር እንደ አዲስ ስልክ ደወለው “ሁሉም እኔ ላይ ተረባረቡ” በማለት ደግመው እንደ ነገሯቸውና እሳቸውም ደግመው እንደሰሟቸው መናገራቸው ሁለቱ ሰዎች በመከፋት መደሰታቸው ዙሪያ የማውራት ልምድ እንዳላቸው አመላካች ነው፡፡ይህ አይሆንም ብንል እንኳን ራሳቸው ፀሃፊውም ቢሆኑ የክልሉ የልዩ ሃይል አዛዥ የነበሩ በመሆኑ ከመስተጋብሩ የራቁ ሰው አይደሉምና ብ/ጄ አሳምነው ከፖለቲካ አመራሩ ጋር የማያግባባቸውን ምክንያት በተመለከተ የራሳቸው መረዳት ሳይኖራቸው አይቀርም፡፡ይህን በምስክርነታቸው ላይ ጨምረው ማስረዳት ይጠበቅባቸው ነበር፡፡
ሆኖም ብ/ጀነራል ተፈራ ማሞ ጓዳቸው ብ/ጄ አሳምነው ከፖለቲከኞች ጋር መግባባት የማይችሉ ሰው መሆናቸውን ብቻ ነግረውን አልፈዋል፡፡ጭራሽ የፖለቲካ አመራሮች ቅኖች ሆነው ሳለ ጓዴ የሚሏቸው አሳምነው ይህን ቅንነት መረዳት የማይችሉ ሰው እንደሆኑ በምክር መልክ እንደነገሯቸው ፅፈዋል፡፡አክለውም አሳምነው የሚገመገሙበትን ጭብጥ መረዳት የማይችሉ ወይም የማይፈልጉ፤ለሚመጣባቸው ግምገማም የግምገማውን ጭብጥ ያማከለ መልስ መስጠት የማይችሉ፣ስለ ባሌ ሲወራ ስለ ቦሌ የሚዘባርቁ ሰው እንደሆኑ አስቀምጠዋል፡፡ይህ በግሌ በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ሚዲያዎች(በOMN፣ቪኦኤ፣በአማራ መገናኛ ብዙሃን )ከሰማሁት የብ/ጄነራል አሳምው ንግግር አዋቂነት ጋር የሚጣረስ ምስክርነት ነው፡፡እዚህ ላይ ብ/ጄ ተፈራ ማሞ ሟቹን ጓዳቸውን ተራ ዘባራቂ አድርገው በማቅረብ ሟች ብ/ጄ አሳምነው እና የአማራ ክልል የፖለቲካ አመራሮች ሊግባቡ ያልቻሉበትን እውነተኛ ምክንያት ሊደብቁን ፈልገዋል፡፡
ብ/ጄ ተፈራ የነገሩን ተጨማሪ የብ/ጄ አሳምነው ጥፋት የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ምግባሩ ከበደ እና ርዕሰ መስተዳድሩ ዶ/ር አምባቸው ስብሰባ ሲጠሯቸው የማይገኙ መሆናቸውን ነው፡፡ሆኖም ዶ/ር አምባቸው እና ብ/ጄ አሳምነው የሚግባቡ ወዳጆች እንደነበሩ፣ጭራሽ አቶ ገዱ በዶ/ር አምባቸው እንዲተኩ ዋነኛው ጎትጓች ብ/ጄ አሳምነው እንደ ነበሩ በአማራ ክልል ከፍተኛ አመራር የሆኑ ሰው አጫውተውኛል፡፡የሁለቱ ሟቾች ወዳጅነት መቼ፣ለምን እና እንዴት አብቅቶ ስብሰባ ላይ አብሮ ለመቀመጥ እስከ መቸገር እንደ ደረሱ ለብ/ጄ አሳምነው ቅርብ ነኝ ያሉት ብ/ጄ ተፈራ የማያውቁት ነገር ሊሆን አይችልም፡፡ነገር ግን ጓዳዊ ምስክርነት ሲፅፉ ይህን ሳይነግሩን እንዲሁ ብ/ጄ አሳምነው ስብሰባ መግባት አሻፈረኝ የሚሉ እምቢተኛ እንደሆኑ ብቻ ነግረውን አልፈዋል፡፡የሚያውቁትን ሁሉ እውነት የማይናገሩበት ምስክርነት ችግሩ አንባቢን አለማጥገቡ ብቻ ሳይሆን ቅንነቱም አጠራጣሪ መሆኑ ነው፡፡
ብ/ጄ ተፈራ አዲስ አበባ ላይ የተደረገውን የሰኔ 12ቱን ግምገማ በተመለከተ የነበራቸውን ምስክርነት ጨርሰው ወደ ባህርዳሩ ትዕይንት ሲመለሱ ምስክርነታቸውን የሚጀምሩት ሟች አሳምነው ስብሰባ ጠርተዋቸው በነበረበት ቦታ “መጣሁ” ብለው እንደሄዱ፣ከዛም ከግማሽ ሰዓት በኋላ በተደወለ ስልክ አሳምነው ርዕሰ መስተዳድር ቢሮ መች ቡድን አሰማርተው ዶ/ር አምባቸውን እንደገደሉ እንደተነገራቸው ነው፡፡ይህ ደዋይ ብ/ጄ ተፈራ የሚመሩት የክልሉ ልዩ ሃይል ትስንቅ እና ትጥቅ(Logistic) መምሪያ ሃላፊ ናቸው፡፡ ነገር ግን በግማሽ ሰዓት ውስጥ አሳምነው ያሰማራውን የገዳይ ቡድን ቁጥር ሳይቀር አውቀው ቅልብጭ ያለ መረጃ ለብ/ጄ ተፈራ በስልክክ ያሳወቁት የትሆነው አይተው/ማን ነግሯቸው ነው? የአይን ምስክር ናቸው? ወይስ የስሚ ስሚ የሰሙትን ለአለቃቸው ማስተላለፈቸው ነው? “በኋላ ሳጣራ ብዙ ነገር አወቅኩ” የሚሉት ብ/ጄ ተፈራ ይህን ሁሉ አብራርተው ሊነግሩን ይገባ ነበር፡፡
ሌላው ምስክርነት ብ/ጄ አሳምነው በሶስት ቡድን የተከፋፈለ መች ቡድን አሰማርተው እንደ ነበር የተነገረበት ነው፡፡ አንዱ ገዳይ ቡድን በራሳቸው በብ/ጄ አሳምነው የሚመራው ወደ ርዕሰ መስተዳድር ቢሮ ሄዶ አሰቃዊውን ግድያ ያደረገው ቡድን ሲሆን፤ ሁለተኛው ሃገር ሰላም ብሎ የብ/ጄ አሳምነውን ወደ ስብሰባ መመለስ ሲጠባበቅ የነበረውን መስካሪው ብ/ጄ ተፈራ ጭምር ያሉበትን ቡድን እንዲገድልየተላከው ነው፡፡ ሶስተኛው ቤታቸው የተቀመጡ የክልሉን አመራሮች በየቤታቸው እንዲገድል የተላከው ነው ተብሏል፡፡ እዚህ ላይ ብዙ ጥያቄ አለ፡፡ ብ/ጄ አሳምነው ሶስት ገዳይ ቡድኖችን እንዳሰማሩ በርካታ የአማራ ክልል የመኳንንት እየተመላለሱ የነገሩን ነገር ነው፡፡ ነገር ግን ርዕሰ መስዳድር ቢሮ ከተደሉት እነ ዶ/ር አምባቸው በቀር ሌሎቹ ሁለት ገዳይ ቡኖች ተሰማሩ በተባለበት ቦታ ሰው አልገደሉም፤ለምን? ብ/ጄ ተፈራም ሲመሰክሩ እነሱ ለስብሰባ በተቀመጡበት በክልሉ የፖሊስ ኮሚሽን ቢሮ ሊገድላቸው የመጣ መች ቡድን ከእርሳቸው ጠባቂዎች ጋር “ቁም ቁም” ሲባባሉ መስማታቸውን ነግረውናል፡፡ ያልነገሩን ነገር ብ/ጄ አሳምነው እነ እነ ብ/ጄ ተፈራን እንዲገድል ላኩት የሚሉት ሁለተኛው ገዳይ ቡድን የኮሚሽኑ ህንፃ መግቢያ በር ላይ ያሉ ዋርድያዎችን ብቻ ገድለው፣እነ ብ/ጄ ተፈራ ያሉበት ህንፃ ድረስ ደርሰው ማንንም ሳይገድሉ የተመለሱበትን ምክንያት ነው፡፡
ብ/ጄ ተፈራ የሚሉት ገዳዮቹ የመሰብሰቢያው ህንጻ አካባቢ ደረሰው ከእርሳቸው ጠባቂዎች ጋር “ቁም ቁም” ከተባባሉ በኋላ “ማነው ያለው?” ብለው ሲጠይቁ “ተፈራ ነው” ሲሉዋቸው ተመለሱ ነው፤አክለውም “ገዳዮቹ ማንን እንደሚገድሉ እንኳን አያውቁም” ይላሉ፡፡ይህ እጅግ አደናጋሪ የሆነው የብ/ጄ ተፈራ ምስክርነት ነው፡፡
የነገሩን ነገር እውነት ከሆነ ሰዎቹ የሚገድሉትን ስለሚያውቁ ነው ስለማያውቁ የእርሳቸውን መኖር ሲያውቁ ማንንም ሳይገድሉ የተመለሱት? ደግሞስ አለቃው ሄደህ ግደል ብሎ ወታደራዊ ትእዛል ያዘዘው ሰው እንትናንማ አልገድልም የማለት ስልጣን አለው? የሚገድለውን የማያውቅ ሰው የጠባቂዎቹን ተኩስ መቋቋምና ጥሶ መግባት ከቻለ ጥሶ ገብቶ ውስጥ ያለው ማንም ይሁን ማን በታዘዘው መሰረት ይገድላል እንጅ ያለው እንትና ነው ሲባል አለቃው ያዘዘውን የመከለስ ስልጣን አለው? ሌላው ጥያቄ የክልሉ አመራሮችን በየቤታቸው እንዲገድል የተላከው ቡድን ከአቶ ደስየ በተጨማሪ ማን ማን ቤት ሄደ? አቶ ደስየን ጨምሮ ሌሎች ቤታቸው ገዳይ የተላከባቸው የክልሉ አመራሮች እንዴት ከሞት ተረፉ? በገስት ሃውስ እገታ ተደረገባቸው የተባሉት እነ ኮሎኔል አለበልስ ሁሉን ለመግደል ከቆረጠው የብ/ጄ አሳምነው እርምጃ እንዴት ተረፉ? ብ/ጄ አሳምነው እነ ብ/ጄ ተፈራን እና አበረን ጨምሮ ጠሩት በተባለው ስብሰባ ላይ ምክትላቸው ኮሎኔል አለበል እንዴት/ለምን ሳይገኙ ቀሩ?
ሌላው አደናጋሪ ነገር ብ/ጄ ተፈራ ከእዝ ሰንሰለታቸው ውጭ፣በብ/ጄ አሳምነው ግዳጅ ተቀበሉ የተባሉ ሰዎችን እያዘዝኩ የአሳምነው ያስነሳው ብጥብጥ እንዳይዛመት አደረግኩ ያሉት ነገር ነው፡፡ይህ ከወታደራዊ የዕዝ ባህል እጅግ ያፈነገጠ አካሄድ በምን አስማት ለእሳቸው ተሳክቶ በብ/ጄ አሳምነው ዕዝ ሰንሰለት ያሉ፣ጭራሽ ግዳጅ የተቀበሉ ሰዎችን በስልክ ትዕዛዝ ብቻ ወደሚፈልጉት አቅጣጫ እንዳመጧቸው ተዓምር መሰል ነገር ነው፡፡ ከሁሉም የሚገርመው ብ/ጄ ተፈራ ጓዳቸው ብ/ጄ አሳምነው ያሰማሯቸውን ሰዎች በስልክ እያዘዙ ከአለቃቸው ትዕዛዝ ውጭ እንዲሰሩ በሚያደርጉበት ሰዓት ብ/ጄ አሳምነው ምን ይሰሩ እንደነበር ግራ የሚያጋባ ነገር ነው፡፡በብ/ጄ አሳምነው ታዘው ግዳጅ ላይ የተሰማሩ ቡድኖች አለቃቸው አሳምነው በህይወት እያሉ የእዝ ሰንሰለታቸውን በቀላሉ ወደ ብ/ጄ ተፈራ ቀይረው፣ ወዲያውኑ ተፈራ በሚሏቸው መንገድ መሄድ የጀመሩበት ምትሃት ምንድን ነው? በወቅቱ አሳምነው በህይወት ስላልነበሩ ያሰማሩትን ቡድን መሪዎች ማዘዝ አልቻሉም እንዳይባል አሳምነው ህይወታቸው ያለፈው ከሁለት ቀን በኋላ እንደሆነ ነው የተነገረን፡፡
ራሳቸው ተፈራም አሳምነው ከኋላው ኤፍሴስ አር ሙሉ ወታደር አስከትለው ከፊት በፒክአፕ መኪናሆነው ከባህርዳር እንደወጡ፣ከኋላ ያሉት ወታደሮች ሲያዙ አሳምነው እንዳመለጡ ጠቆም አድርገውናል፡፡ከሁሉ ግራ የሆነው ስለ ሰኔ 15ቱ ግድያ ሊነግሩን የተነሱት ብ/ጄ ተፈራ በዚሁ ክስተት የሞቱትን፣ ጓዴ የሚሏቸውን የብ/ጄ አሳምነውን አሟሟት ከዓመት በኋላ ተመልሰው ሲመጡም ሳይነግሩን መቅረታቸው ነው፡፡የሃገር መከላከያ ሰራዊት ረብሻውን በመቆጣጠሩ ረገድ ምንም ሚና አልነበረውም፤ሙሉ በሙሉ ነገሩን የተቆጣጠረው የአማራ ልዩ ሃይል እንደሆነ አድርገው ያቀረቡት ነገርም የዛሬ አመት በመንግስት ሚዲያዎች ከተዘገበው ጋር የሚጋጭ በመሆኑ እጅግም አሳማኝ ነገር አይደለም፡፡ በወቅቱ የመንግስት ሚዲያዎች የዘገቡት ግርግሩ በቁጥጥር ስር የዋለው በመከላከያ ሰራዊት እና በክልሉ ልዩ ሃይል ጥምር ጉልበት እንደሆነ ነው፡፡ሌላው ምስጢር ከሞት ከተረፉት የአማራ መኳንንት ሁሉ ተለይተው ብ/ጄ ተፈራ እና ኮ/ሎ አለበል ብቻ በአሳምነው ግብረ አበርነት ተጠርጥረው የታሰሩበት ምክንያት ምን እንደሆነ መስካሪው ተፈራ ሳይናገሩ መቅረታቸው ነው፡፡የፀጥታው ክንፍ አባላት ስለሆኑ ተጠረጠሩ ከተባለም የፖሊስ ኮሚሽነሩ አበረ አዳሙ አልታሰሩም፡፡
በስተመጨረሻም ብ/ጄ ተፈራ ምስክርነታቸውን ሲጨርሱ ሁለት ቀልቤን የሳቡ ነገሮችን አስቀምጠዋል፡፡ አንደኛው ለውጡ ፈጣሪዎቹን የበላው እንዴት ነው ሲሉ የጠየቁት ነገር ነው፡፡ይህ መልስ ሊሰጠው የሚገባው ጥያቄ ነው፡፡ሁለተኛው ከላይ ብ/ጄ አሳምነውን የተቹት በቅንነት እንደሆነ የመሰከሩላቸውን የክልሉን የፖለቲካ አመራሮች በአራሙቻነት የከሰሱበት ነው፡፡”አራሙቻ” የሚለው አገላለፅ ከምን አንፃር የተባለ እንደሆነ ግልፅ አይደለም፡፡ ሆኖም መስካሪው ተፈራ ያሉትን ተከትለን ነገሩን ብናየው የአማራ ክልል የፖለቲካ አመራሮች “አራሙቻ” ከሆኑ ብ/ጄ አሳምነው ከአራሙቻዎቹ የፖለቲካ አመራሮች ጋር እንዴት ብለው ተግባብተው እንዲሰሩ ነው ብ/ጄ ተፈራ “ከአሳምነው ጋር ባደረግኩት የመጨረሻ ስንብት ከፖለቲካ አመራሩ ጋር ተግባብተህ ስራ ብየ መከርኩት” የሚሉት? ከአራሙቻ ጋር መግባባት የሚቻለው እንዴት ነው?