spot_img
Sunday, April 14, 2024
Homeነፃ አስተያየትየደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጉዳይ መረሳት የለበትም!! (በህይወት አበበ መኳንንት -ካናዳ)

የደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጉዳይ መረሳት የለበትም!! (በህይወት አበበ መኳንንት -ካናዳ)

Dembi Dollo University Kidnapped students
ግራፊክስ ከማህበራዊ ሚዲያ የተገኘ

በህይወት አበበ መኳንንት (ካናዳ)
afomith@gmail.com

የዛሬ ሰባት ወራት ገደማ ከሚማሩበት ደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ወደ አማራ ክልል በመጓዝ ላይ የነበሩት 17 ሴት ተማሪዎች ለመንግስት እንኳ ግልፅ ባልሆነ መንገድ ባልታወቁ ሰዎች ተጠልፈው እስካሁን ድረስ የት እንደገቡ ሳይታወቅ መቅረቱ በሃገራችን ኢትዮጵያ ለሰዎች ደህንነት በትጋት የሚሰራ የመንግስት መዋቅር እንደሌለ ከማመላከቱም በላይ ስርአት አልበኝነትና ወንጀለኝነት እየተበራከት በሄደ ቁጥር ባጠቃላይ የሃገራችን የህልውና ጥያቄን አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል ግልፅ ነው።

ላለፉት ሁለት ዓመታት አዲስ የተሃድሶ ፕሮግራም ይዣለሁ በሚል ቡድን የተጀመረው የለውጥ ሂደት በመጀመሪያዎቹ መቶ ቀናት ውስጥ አስደናቂና የሚመሰገን ስራ ቢሰራም ከዚያ በኋላ ግን ቀስ በቀስ የሃገራችን አንድነትና ሉዓላዊነትን የሚሸራርፉ ተግባራት እየተፈፅሙ መመልከት ለውጡ እንደተፈለገውና እንደተጠበቀው እየሄደ እንዳልሆነና አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉትም የለውጡ ሂደት ጨንግፏል ቢባል የሚያስደንቅ አይደለም። 

ባለፉት ሁለት ዓመታት በሃገራችን ሰላምና ዲሞክራሲ ይሰፍናል ዜጎችም በሃገራቸው የሁሉም ፀጋዎቿ ፍትሃዊ ተጠቃሚ ይሆናሉ በሚል ተስፋ ውስጥ የቆየነው ኢትዮጵያውያን በዚህ ወቅት ሁሉም ነገር እንደጠበቅነው ሳይሆን በተቃራኒው ሃገራችንን ሊበታትን የሚችል የፖለቲካ ሽኩቻ ውስጥ መግባታችንን ነው እየተገነዘብን የመጣነው። ይህ አባባል በጣም አስፈሪና አስጨናቂ ቢሆንም ጥሬ ሃቅ በመሆኑ የግድ እውቅና ሰጥተን ሁላችንም ዜጎች ስለመጪው ዘመን መነጋገርና መፍትሄ መፈለግ አለብን የሚል ዕምነት የአብዛኛው ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ አመለካከት እንደሆነ ይገመታል።

አሁን በስልጣን ላይ ያሉት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ ኣሕመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ በተናገሯቸው መልካም ንግግሮችና በሰጡት ከባባድ ተስፋ አማካኝነት ሁላችን በአንድ ልብ ቆመን ልንደግፋቸውና አይዞህ ልንላቸው ተገደን እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። ይሁን እንጂ ስልጣን ከያዙ ከጥቂት ወራት በኋላ እንደነገሩን መልካም ምኞት ሊኖራቸው ቢችልም የፖለቲካ ምህዳሩን አሰፋሁ ባሉበት አንደበታቸዉ ብዙ የፖለቲካ ግጭት የሚቀሰቅሱ ተግባራት ሲከናወኑ በሰከናና በሰለጠነ መንገድ ሲፈቱት አላየንም። በሳቸው የስልጣን ዘመን ከተጠበቀው ውጭ በሃገራችን ከተፈጠርን ጀምሮ አይተናቸው የማናውቅ ስርዓት አልበኝነትና ወንጀሎችን ለማየት ችለናል። እሳቸው እነዚህን ችግሮች በወቅቱ የእርምት እርምጃ በመውሰድ የዜጎችን ደህንነትና ሰላም ማረጋገጥ ሲገባቸው ጊዜያቸውን የራሳቸው ምስል በሚያጎሉ የፎቶግራፍ እና የሚዲያ ፕሮፖጋንዳ ላይ በማሳለፋቸው የሃገሪቱ አንገብጋቢ ጉዳዮች ትኩረት ባለማግኘታቸው ሃገሪቷ ወደተባባሰ የፖለቲካ ቀውስ እንድትገባ ተገዳለች።

በዚህ አዲስ የለውጥ ሂደት ሰዎች በየፊናቸው የጎበዝ አለቃ በመሆን፣ በመታጠቅ፣ በመደራጀትና የደቦ ፍርድ በመስጠት በንፁሃን ዜጎች ላይ የግድያ፣ የዝርፊያ፣ የአፈናና ሴቶችን የመድፈርና አሰቃቂ ወንጀል ተፈፅሟል፡ አሁንም በመፈፀም ላይ ናቸው። እንደነዚህ ያሉ ችግሮች መንግስትን በቀጥታ ስለሚመለከቱ እንዴት ማረምና እርምጃ መውሰድ እንዳልተቻለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲጠየቁ አንዳንዴ ከቤተመንግስታቸው በሃያና ሰላሳ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የተፈፀመን ወንጀል አልሰማሁም አላየሁም ብለው እስከ መካድ አንዳንዴ ደግሞ እሳቸዉን የሚያስፈሩ ሌሎች ሃይሎች ያሉ በማስመሰል እጃቸውን ወደ ሌሎች “ሃይሎች” በመቀሰር እራሳቸውን ተጠያቂ እንዳልሆኑ ለማስተባበል ሲሞክሩ ይታያሉ። 

እንዲህ ያለ የመንግስት ድራማ በሃገራችንም ሆነ በሌሎች ሃገራት ታይቶም ሆነ ተሰምቶ አያውቅም። አንድ የህዝብ መሪ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ብቃቱ ወይም ፍላጎቱ የሌለው እንደሆነ ስልጣኑን ለሚችሉና ብቃት ላላቸው ሰዎች አስረክቦ በሰላም ለመኖር ይሞክራል እንጂ ስልጣንን አጥብቀው እየፈለጉ የስልጣናቸው ምንጭ የሆነውን የህዝብ ደህንነትን የማስጠበቅ ስራ ወደ ጎን መተው እርስ በርሱ የሚጋጭ አመለካከት ነው። ባለፉት ሁለት ዓመታት በሻሸመኔ፣ በለገጣፎ፣ በቡራዩ፣ በጌዶኦ ዞን፣ በሰሜን ጎንደር፣ በወለጋ፣ በባሌ እንዲሁም በበርካታ የሃገራችን ክፍሎች የታዩ ከባባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና ወንጀሎችን ማየት በራሱ የመንግስታችንን ህዝብን ለመጠበቅ አቅም ማነስ አመላካች ናቸው። 

አንድ ሰው በሃገሩ ለመኖር መንግስት በሰላም ወጥቶ እንዲገባ የሚያደርግ የፀጥታና የደህንነት መዋቅር ዘርግቶ ደህንነቱን በበቂ ሁኔታ ማረጋገጥ መቻል አለበት። እንዲህ ማድረግ ካልተቻለ ከመኖር ባሻገር ያለው የመማር፣ የመስራት፣ ልጆችን የማሳደግ፣ ሃብትን የማፍራትና ባጠቃላይ ለሰው ልጅ ፍላጎት የሚመጥኑ ነገሮችን ሁሉ አቅዶና ፈልጎ ለማድረግ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ይፈጠራል። ሰው ስልጡን ማህበራዊ እንሰሳ እንደመሆኑ በሚኖርበት አከባቢ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር ይፈልጋል። ይህንን ማድረግ የሁሉም መልካም ዜጎች ሃላፊነት ቢሆንም ለመንግስት ግን ተቀዳሚና በጣም ወሳኝ የስራ ድርሻው ነው። የህዝቡን ሰላም ዋስትና መስጠት የሚችል መንግስት በጠፋባቸው ሃገራት ሁሉም አሁን በኢትዮጵያ እየታዩ ያሉ ዓይነት ግድፈቶች እየታዩ በነበሩባቸው ጊዜያት አፋጣን የእርምት እርምጃ ባለመውሰዳቸው ምክንያት ችግሩ ገዝፎና ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ወደከፋ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ እንዲገቡ ምክንያት ሆኗል። ትናንት ትላልቅ የነበሩና ዜጎቻቸው የተደላደለ ህይወት ይመሩባቸው የነበሩ ሃገራት በመንግስታቶቻቸው ቸልተኝነትና የሴራ ፖለቲካ ሳቢያ ፈራርሰው ህዝባቸውን ለሞትና ለስደት እንዲጋለጡ ምክንያት ሆነዋል።

በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ የሶሪያና የየመን ዜጎች ሳንቲም ሲለምኑ ከማየት የተሻለ ሌላ አስተማሪ ክስተት ሊኖር አይችልም። ሃገራችን ከሶሪያና ከየመን የተለየች አይደለችም። አሁን በኢትዮጵያ እየታዩ ያሉ ከባባድ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች መንግስት ባፋጣኝ ለማረም የፖለቲካ ወይይቶችና ማህበራዊ ዘዴዎችን በመጠቀም ለማርገብና ለማስወገድ ካልሰራ፣ በየቦታው የሚታዩ የህግ መተላለፎች መንግስት ተገቢና ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ለማረምና ለመቆጣጠር ካልሰራ፣ ነገ ችግሩን ለመቆጣጠር ከማንችልበት ደረጃ ላይ ደርሶ ሃገራችንን ወደ መበታተንና ስርዓት አልበኝነት እንደማትገባ ዋስትና መስጥት የሚችል ሃይል የለም። የችግሮቻችንን ምንጭ በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ ለማድረቅ ከዛሬ የተሻለ ሌላ ጊዜ የለም። 

የዛሬ ሰባት ወር ገደማ ከደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ወደ አማራ ክልል ሲጓዙ የነበሩ ሴት ተማሪዎች ከመንገድ ተጠልፈው ባልታወቁ ሰዎች ወዳልታወቀ ቦታ ሲወሰዱ በመጀመሪያ እንዴት መንግስትና ህግ ባለበት ሃገር ሰው ከህዝብ ትራንስፖርት ጠልፈው የሚወስዱ ወንጀለኞችን መቆጣጠር አልተቻለም? የሚል ጥያቄን ያጭራል;; ከዚህም ባሻገር መንግስት ሁኔታው ከተፈጠረ በኋላ የወሰደው እርምጃና የሰጠው ማብራሪያ ህዝቡ በመንግስት ላይ እምነት ማጣቱ ብቻ ሳይሆን ባላስፈላጊ መንገድ ሄዶ የመንግስትን የፖለቲካ ጤንነትንም ወደሚጠራጠርበት ደረጃ እንዲደርስ መንግስት ቀጥተኛ አስተዋፆኦ አድርጓል። 

እነዚህ ልጆች ከመንገድ ታፈኑ ሲባል በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ ህዝቦች የራሱ ልጆች የታፈኑበት ያህል በከፍተኛ ድንጋጤ ተዋጠ። መንግስት አለን ብለን በምንኖርበት ሃገር እንዲህ ያለ ተግባር ሲፈፀም ማየት በጣም አስፈሪና አስደንጋጭ ከመሆኑም ባሻገር ለቀጣይም በሰላም ወጥተን ስለመግባታችን ብንሰጋ ተገቢ ስጋት ይሆናል። ከሁሉም በላይ በመጀመሪያ በዜጎች ላይ እንዲህ ያለ ወንጀል ሲፈፀም መንግስት እውቀቱም ሆነ መረጃዉ የነበረው አይመስልም። ምክንያቱም እንዲህ ያለ ሃገራዊ ውድቀትን የሚያመለክት አፈና ወዲያውኑ መግለጫ ለመስጠትና ጉዳዩን በቅርበት ለመከታተል የተደረገ ጥረት አልነበረም። መንግስት የተዛቡና እርስ በእርስ የሚጣረሱ መግለጫዎችን ማውጣት የጀመረው እንኳን የህዝቡ ቁጣ መገንፈል ከጀመረ በኋላ ነው።

ከሁሉም በላይ በጣም አሳፋሪና ለአንድ መንግስት ቁመና መለኪያ ከሚሆኑት ባህሪያት ዋነኛውን የጣሰው መግለጫ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ በአቶ ንጉሱ ጥላሁን በኩል ተሰጥቶ የነበረው የሃሰት መግለጫ ነው። ቃል አቀባዩ ተጠልፈው የነበሩት ሀያ አንድ ተማሪዎች ወደሚማሩበት ዩኒቨርሲቲ ተመልሰው ገብተው ትምህርታቸውን በሰላም እየተከታተሉ እንደሆኑ እና የቀሩትን 6 ተማሪዎች  ለማስለቀቅ ስራ እየተሰራ መሆኑን በማስ ሚዲያ ወጥተው ተናገሩ። በዚያ ወቅት እውነት መስሎን ሁላችንም ተደሰትን። መንግስት የህዝቡን ቁጣ የውሸት መግለጫ በመስጠት ሊያረግብ ሞክሮ ነው ወይስ ለሌላ ፖለቲካዊ ትርፍ ነው በነዚህ የድሃ ልጆች ህይወት እንዲህ ያለ ድራማ የሚሰራው ለሚለው ጥያቄ መልሱ መንግስት እጅ ላይ ነው። መልሱ ያሻውን ቢመስልም ታዲያ በሰለባዎቹ እንደ መቀለድና ለህዝብ ከበሬታ ከማጣት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ለመረዳት የህግ ባለሙያ መሆንን አይጠይቅም። 

እነዚህ ተማሪዎች አቶ ንጉሱ እንደገለጿቸው ወደ ዩኒቨርሲቲው አልተመለሱም፣ ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለውም መንግስት እራሱ የት እንዳሉ አያውቅም ነበር። በኋላ የህዝቡ ቁጣ እየጨመረ ሲመጣ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እራሳቸው ታገሱን ልጆቹን ለማግኘት ጥረት እያደረግን ነው ሲሉ የሌለና በተግባር የማይደገፍ ተስፋ ሰጡን። አንዳንድ የፖለቲካ ሰዎች ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ህዝብን የሌለ ተስፋ በመስጠት ከጊዜ በኋላ የህዝቡ ቁጣ እየተነፈሰና እየተዳከመ ሲሄድ ይረሳሉ በሚል ዘዴ የተናገሩት መግለጫ እንደሆነ ገልፀው ነበር። ያም ተባለ ያ እንደገና በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስለቅቀናል ስለተባሉት 21 ተማሪዎች ምንም ዝርዝር መረጃ ለህዝቡ ሳይሰጡ ቀሪዎቹን ተማሪዎች የት እንዳሉ ለማፈላለግ ህዝቡ እንዲተባበራቸው ጠይቀዋል። ህዝቡ ከሁሉም በላይ የተቆጣው መንግስት እንዴት አስራ ሰባት ዜጎች ተጠልፈው ሲወሰዱ በመረጃ ደረጃ እንኳ ዕውቀት የለውም ብሎ እንጂ ህዝቡ የት እንዳሉና ማን እንዳፈናቸው ቢያውቅማ መንግስትን ሳይጠይቅ ሆ ብሎ ተነስቶ ያስለቅቃቸው ነበር። 

እነዚህ ያልፍልናል ብለው ሴቶች ከመሆናቸውም ጋር እየተንከባለለ የመጣውን የባህል ተፅዕኖ አሸንፈው ሰው ለመሆን ብቸኛው መንገድ ትምህርት ነው ብለው መማርን የመረጡት ወጣት ሴቶች ካለምንም ተከላካይና የሚያድን የመንግስት መዋቅር በሌለበት እንደ ወጡ ሲቀሩ ሃገራችን ኢትዮጵያ በአስፈሪ የታሪክ ወቅት ላይ እንዳለች ለመረዳት ቀላል ነው። አሁን የኢትዮጵያ መንግስት የተያያዘው ስራ ለፖለቲካ ፍጆታ የሚሆኑ ጥቃቅን ስራዎችና የፕሮፓጋንዳ ድራማ ላይ ተጠምዶ መዋል ነው። በባህሪው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ መንግስት  ከመሰረታዊ የህዝብ ጥያቄ ይልቅ የመንግስትን አመራር የሚያጎላ የፕሮፓጋንዳ ስራ ላይ መዋልን ያዘወትራል። በዚህም ምክንያት በሃገራችን ችግሮች መኖራቸው ብቻ ሳይሆን ችግሮቹን ሊፈታ የሚችል ጠንካራ የመንግስት መዋቅር አለመኖሩ ዜጎች በመንግስት ላይ ተስፋ እንዲቆርጡ ምክንያት እየሆነ ነው። 

ዲሞክራሲ ሂደት እንጂ በአንድ ሌሊት ዓዋጅ ታውጆና ተግባር ላይ ውሎ የሚቀጥል አስተሳሰብ አይደለም። ጠቅላይ ሚኒስትሩና ቡድናቸው ማለትም ቲም ለማ ወደ ስልጣን ሲመጡ የዲሞክራሲ ምህዳሩን እናሰፋለን፣ ከእንግዲህ ወዲያም ሰው በአመለካከቱ ምክንያት ማለትም የተለየ አመለካከት ስላለው ብቻ ለእስርና ለስቃይ የሚዳረግበት ስርዓት አብቅቷል ሲሉና መንግስት እራሱ አሸባሪ ነበር በማለት ይቅርታ ሲጠይቁ ሃገራችን ኢትዮጵያ በታሪኳ አይታው የማታውቅ መልካም ስርዓት መጣልን ሲል ህዝቡ ከአፅናድ እስከ አፅናፍ ወጥቶ ድጋፉን ገልፆላቸው ነበር። ይሁን እንጂ የተጠበቀው ሳይሆን እንደውም ያ መጥፎ ስርዓት በነበረበት ወቅት ታይቶም ሆነ ተሰምቶ የማያውቅ የሰብአዊ መብት ጥሰትና ወንጀል ሃገሪቱን ከዳር እስከዳር አጥለቅልቋታል። አስፈሪው የችግሩ መኖር ሳይሆን መንግስት እያንዳንዱን ችግር በተሳሳተ መልኩ በማየትና ሆን ብሎም ህዝብን የሚያደናግር መረጃ በማሰራጨት መፍትሄ እንዳይገኝ እንቅፋት እየሆነ መምጣቱ ነው። መንግስት የመፍትሄው አካል ብቻ ሳይሆን የመፍትሄው ሂደት መሪ መሆን ሲገባው ለእንዲህ ዓይነቱ አደገኛ ማህበራዊ ንቅዘት ደንታ ቢስ ሲሆን ግን የኢትዮጵያ ህዝብ እራሱን ከሚመጣው የከፋ የመተላለቅ አደጋ ለመጠበቅ ሲል አንዳች ሰላማዊና ህጋዊ መንገድ መፈለግ አለበት። 

የኢትዮጵያ ህዝብ ባህላዊ እሴቱና ማህበራዊ ትስስሩ እንደ ሌሎች በርካታ የአለማችን ህዝቦች የላላ ቢሆን ኖሮ እንዲህ መንግስት በከፋ ሁኔታ በተዳከመበትና ስራውን መፈጸም ባልቻለበት ወቅት ብዙ የከፋ ችግር ይከሰት ነበር። የኢትዮጵያ ህዝብ በርካታ የቆዩና ቦታ ያላቸው የግጭት አፈታት ባህል ስላለው መንግስት እንዲህ ተዳክሞም ቢሆን ብዙ ችግሮችን በአካባቢያዊ ባህል በኩል ለመፍታት ብዙ ጥረት እያደረገ ይገኛል። ለዚህም የኢትዮጵያ ህዝብ ምስጋና ይገባዋል። 

ወደ ዋና ርእሰ ጉዳዬ ስመለስ ግን በነዚህ 17 የአማራ ክልል የዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች መታፈንና ደብዛ መጥፋት በመጀመሪያ ደረጃ ቤተሰቦቻቸው ዘመን ለማይፍቀው የስነ ልቦና ችግር እንዲጋለጡ ተዳርገዋል፣ የኢትዮጵያ ህዝብ በመንግስት ላይ ያለው ዕምነት በመላላቱ በተለያዩ የዜና አውታሮች በተደጋጋሚ እንደሰማነውና እንዳየነው ሁሉም ሰው ራሱን ለመጠበቅ ካለው የደመነፍስ ፍላጎት ምክንያት የጦር መሳሪያዎችን እየገዛ ያከማቻል። ልጆቹንና ቤተሰቡን ለመጠበቅ ሲል መንግስት ይጠብቀኛል የሚለውን ትቶ በጣም ብዙ ህዝብ መሳሪያ በመግዛት ላይ እንደሆነ ሲታሰብ አንዳች ሁኔታ ቢፈጠር ሊሆን የሚችለውን መገመት አያዳግትም። በዛላይ ደግም ወጣት ሴቶች ላይ እንዲህ ዓይነት ከፍተኛ ወንጀል ሲፈፀም የኢትዮጵያ መንግስት ምንም ባለማድረጉና ከናካቴውም የተጣራ መረጃ የሌለው መሆኑ ሲታሰብ ደግሞ በትምህርት እራሳችንን እናሳድጋለን ብለው በተስፋ የሚታትሩት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣት ሴቶች ስነ ልቦና ላይ የተስፋ መቁረጥና የጥበቃ ማጣት ስሜት ስለሚያሳድር በጥረታቸው ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅእኖ ያሳድራል። 

እነዚህ በመንግስት ድክመት ምክንያት ደብዛቸው ጠፍቶ ሰባት ወራት ያለፋቸው ወጣት ሴቶች ጉዳይ መንግስት ሊከታተለው አቅም ቢያንሰው ወይም ፍላጎት ባይኖረውም እንኳ በትንሹ ከሚመለከታቸው የሃገር ሽማግሌዎችና ከሚመለከታቸው የህዝብ ተወካዮች የተውጣጣ አጣሪ ቡድን ተቋቁሞ ሁኔታቸው ላይ አንድ ዕልባት እንዲኖር መሰራት አለበት። እንደተለመደውና ተገቢ እንደሆነውም ህዝብ እንዲህ ያሉ የወንጀል ድርጊቶችን የማጣራት ተግባር የመንግስት ነው ብሎ ለመንግስት ስለሚተወው ለሰባት ወራት መንግስት አንዳች ተአምር ይዞ ብቅ ይላል በሚል ተስፋ ህዝቡ ቢጠባበቅም በመንግስት በኩል እስካሁን የተገኘ ፍንጭ የለም። አሁንም ህዝቡ በመንግስት ላይ ሰላማዊና ህጋዊ ጫና ለመስፍጠር ካልተጋ ነገም ሌሎች ተማሪዎች ተጠልፈው እንደነዚህ ልጆች ቁጥር ብቻ ሆነው እንዳይቀሩ ዋስትና ሰጪ ምንም አዎንታዊ ሁኔታ የለም። 

እነዚህ ወጣት ሴቶች የያንዳንዳችን ልጆች፣ እህቶችና ዘመዶች ቢሆኑ በስነ ልቦናችን ውስጥ ሊፈጠር የሚችለው ከባድ አደጋ በማሰብ አሁንም ሁላችንም ለነዚህ ምስኪን በመንግስት የደህንነት መዋቅር መዳከም ምክንያት ሰለባ የሆኑ ሴቶች መጮኽና የማያዳግም እርምጃ ተወስዶ ቁርጡ እንዲታወቅ መታገል አለብን። ዛሬ የሌሎች ቤተሰቦች ጓዳ ሲንኳኳ ዝም ብለን ነገ የራሳችን ጓዳ እስኪነኳኳ መጠበቅ የለብንም እና ማህበራዊ አንድነታችንን በማጠንከር ማህበራዊ ደህንነታችንን ማረጋገጥ እንድንችል ለያንዳንዷ በደል በትጋት መቆምና እምቢ ማለት መቻል አለብን። ማንኛውም ጥያቄ በስላማዊ፣ በሰከነና በህጋዊ መንገድ ደጋግሞ በማቅረብ ካሁን በፊት ስርዓትን መለወጥ ተችሏል አሁንም በስርዓቱ ላይ የአሰራር ለውጥ እንዲመጣ ተፅዕኖ መፍጠር ይቻላል። 

ልጆቻችንና እህቶቻችህ  አስኪመለሱ ድረስ ዝም አንልም! 

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here