spot_img
Wednesday, June 12, 2024
Homeነፃ አስተያየትፖለቲከኞች ነን ባዮች በፖለቲካ ስም የሚሰሩት ታላቅ የታሪክ ወንጀል!!

ፖለቲከኞች ነን ባዮች በፖለቲካ ስም የሚሰሩት ታላቅ የታሪክ ወንጀል!!

ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር
ሰኔ 29, 2012 ዓ.ም. ( ሐምሌ 06፣ 2020)

መግቢያ

አብዛኛውን ጊዜ በታሪክ ውስጥ የሚሰራው ትልቁ ወንጀል የራስን ምንነትና ችሎታ አለማወቅ ነው። አንድ ሰው ራሱንና ችሎታውን ሲያውቅ ብቻ ነው ሌላን ሰው ሊያውቅ የሚችለው። ስለዚህም ይላል ሶክራተስ፣ መጀመሪያ ራስህን ዕወቅ።  ሁለተኛው፣ ትልቁ የታሪክ ወንጀል ደግሞ ግልጽ የሆነ ፍልስፍና ወይም መመሪያ ሳይኖር ትግል ብሎ መጀመር። በሶስተኛ ደረጃ፣ ታጋይ የሚባለው በአንድ ድርጅት ዙሪያ የሚሰባሰበው ወይም ደግሞ ተዋጊ ሆኖ የሚመለመለው ኃይል ስለትግሉ ዋና ዓላማ በቂ ግንዛቤ እንዳይኖረው ማድረግ። በአራተኛ ደረጃ፣ ለመዋጋት የሚመለመለው ኃይል ከዕውቀት እንዲርቅ ማድረግ። መንፈሱ በጦርነት አስተሳሰብ ብቻ እንዲመረዝና ጨካኝ እንዲሆን ማድረግ። በአምስተኛ ደረጃ፣ በድርጅቱ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ውይይትና ክርክር እንዳይለመድ ማድረግና መጠየቅን አለመፍቀድ፤ ከአመራር የመጣን ትዕዛዝ ብቻ ተግባራዊ ማድረግ። 

የሰላማዊ ትግል የሚያካሂዱ ድርጅቶችም ጋ ስንመጣ ተመሳሳይ የአሰራር ስልት እንመለከታለን።  የተለያየ ስም ይዘው በኢትዮጵያ ስም የሚንቀሳቀሱ ወይም የሚነግዱ ድርጅቶች እንደዚሁ ግልጽ የሆነ ፍልስፍናና ዓላማ የላቸውም። በአብዛኛዎች ድርጅቶች ውስጥ አንድ ሰው መሪ ሆኖ ከተመረጠ በኋላ ዕድሜ ልኩን መሪ ሆኖ ይቀራል። መሪ ሆኖ የሚመረጠው ሰው ወይም አካል ከመጀመሪያውኑ ፐርሰናሊቲ ከልት ያዳብራል። የማይጠየቅና የማይከሰስ ይሆናል። በድርጅቱ ውስጥ ውይይት ወይም ክርክር ሳይደረግ ከውጭ ኃይሎች ጋር ልዩ ግኑኝነት ይፈጥራል። ወይም እዚህና እዚያ በመሯሯጥ ይይድረሱልኝ ጩኸቱን ያስማል። በዚህ መልክ በራስ መተመማን የሚለው መርህ በያንዳንዱ አባል መንፈስ ውስጥ እንዳይቀረጽ በማድረግ ለዕውነተኛ ነፃነት የሚደረገው ትግል ፈሩን እንዲስት ይደረጋል። አብዛኛዎች ድርጅቶች ስለዓለም አቀፍ ፖለቲካና የኢኮኖሚ አደረጃጀት ይህን ያህልም ግልጽ የሆነ ግንዛቤ የላቸውም። በተለይም እያንዳንዱ አገር የራሱን ዕድል በራሱ መወሰን እንዳለበትና፣ ነፃና ለህዝባችን አለኝታ የሚሆን በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተደገፈ ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት እንዳለበት ግልጽ የሆነ አቋም የላቸውም። እንደ ነፃ አውጭ ድርጅቶችም በሰላማዊ መንገድ እንታገላለን የሚሉት ድርጅቶችም በውስጣቸው ስለዛሬው የአገራችን ሁኔታና ስለተከታታዩ ትውልድ ዕጣ ምንም ዐይነት ጥናትና ክርክር አያደርጉም። በተለይም መሰረታዊ በሆኑ እንደ ኢኮኖሚክስ፣ ማህበራዊ ጉዳዮች፣ ስለጤናና ስለትምህርት፣ ስለከተማዎች ግንባታና የቤት አሰራር ዘዴዎች፣ ስለማዕከለኛና ትናንሽ ኢንዱስትሪዎች…ወዘተ. መተከል አስፈላጊነት ጥናት አይደረግም። የአገራችንን የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የፖለቲካና የባህል ሁኔታ የሚያትት ጋዜጣም ሆነ መጽሄት የላቸውም ወይም በየጊዜው አያወጡም።  በተጨማሪም መንግስት ከዓለም አቀፋዊ ተቋማት ጋር እየተስማማ ተግባራዊ በሚያደርገው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ላይ ምንም ዐይነት ውይይትና ጥናት አያቀርቡም። ስለሆነም የአብዛኛዎቹ ድርጅቶች አቋም ምን እንደሆን በግልጽ የሚታወቅ ነገር የለም። 

የትጥቅም ሆነ የሰላማዊ ትግል የሚያካሄዱ ድርጅቶች ዋናው ችግር ስልጣንን በመያዝ ላይ ያተኮረና መቼ ነው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስተር የምሆነው በሚለው ላይ ያነጣጠረ ስለሆነ ይህንን ያህልም የሰፊው ህዝብ ኑሮና መሻሻል ስላለበት ጉዳይ እምብዛም አያስጨንቃቸውም። የአገራችንን ሁኔታ በሰፊው በማጥናት ይህች አገር የግዴታ መሰረታዊ ለውጥና ዘመናዊ ተቋማት ያስፈልጓታል ብለው በምሁራዊ ስሜትና በጥልቅ ጥናት ላይ በመመርኮዝ አይታገሉም። ስለሆነም አስተሳሰባቸውና የትግል ስልታቸው ተራማጅ ባህርይ ወይም መሰረታዊ ለውጥን የማምጣት ኃይል የለውም። የኢትዮጵያ ህዝብ ደሀና ለማኝ ሆኖ እንዲቀር የሚያደርግ የትግል ስልትና አሰራር ነው በአብዛኛዎቹ ድርጅቶች ውስጥ የሰፈነውና የተለመደው ማለት ይቻላል።

በተለይም ወደ ነፃ አውጭ ድርጅቶች ጋ ስንመጣ አነሳሳቸው በሙሉ የአገራችንን ታሪክ በተሳሳተ መልከ ከመተርጎም የመነጨ ነው። በእነሱ „ፍልስፍና“ መሰረት እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያን ሲገዛ የነበረው ከአንድ ብሄረሰብ የተውጣጣ ነው። ይህ ዐይነቱ ከአንድ ብሄረሰብ የተውጣጣ አገዛዝ የሌሎችን ብሄረሰቦች የዳበረ ባህልና ስልጣኔ በመጨፍለቅ ወይም ድምጥማጡን በማጥፋት የራሱን ባህልና ቋንቋ እንዲቀበሉ በማድረግ ጭቆናን ያሰፈነ ነው። ወደፊት እንዲራመዱና የስልጣኔን ብርሃን እንዲያዩ ከማድረግ ይልቅ በጨለማ ዓለም ውስጥ እንዲኖሩ ያደረገ ነው። ስለሆነም ትግሉ ይህንን ዐይነቱን የአንድ ብሄረሰብ አገዛዝ የሰፈነበትን ስርዓት በማስወገድ በተራችን ደግሞ የራሳችንን የበላይነት ማስፈን ነው። በዚህ ዐይነት መንፈስ የሚነደፈው  የትግል ስልት ፀረ-ሳይንስ፣ ፀረ-ፍልስፍናና ሀተታ አልባ ነው። ከዕውነተኛ ዕውቀት የራቀ በመሆኑ ቆሜለታለሁ የሚባለውን ብሄረሰብ ነፃ ሊያወጣው የሚያስችል አይደለም። ሰብአዊነትን ያስቀደመ ሳይሆን ቂም-በቀለን ያስቀደመና በጥላቻና በውሸት ላይ የተመሰረተ የትግል ዘዴ ስለሆነ ህዝብን የመከፋፋልና የእርስ በእርስ የማጋጨት ኃይሉ ከፍ ያለ ነው። ይህ ዐይነቱ የህብረተሰብን ሳይንስና የህብረተሰብን ዕድገት የሚቃረን የትግል ዘዴ የት እንዳደረሰን ባለፉት አርባ ዐመታት፣ በተለይም ወያኔ 28 ዐመታት ያህል አገራችንን ሲገዛ ያየነው ነው። 

ሁለቱም የተለያየ ፍልስፍናና ዓላማ ያላቸው ልዩ ልዩ ድርጅቶች የመጨረሻ መጨረሻ አንዳች ዐይነት ፖለቲካ የሚባል ነገር እናካሂዳለን ይሉናል። ጥያቄችን ግን ስለፖለቲካ በሚያወሩበት ጊዜ ፖለቲካ ማለት ምን ማለት እንደሆን ገብቷቸዋል ወይ? ፖለቲካ ከተለያዩ ዕውቀቶች ጋር መያያዝ እንዳለበት ተረድትዋል ወይ? ስለፖለቲካ በሚያወሩበት ጊዜ የብዙ ሚሊዮንን ህዝብ ዕድል እንደሚወስኑ ተገንዝበዋል ወይ? ዛሬ በፖለቲካ ስም የሚካሄደው ትግል የተከታታዩንም ትውልድ እንደሚነካ ተረድተዋል ወይ? አንድ ህዝብስ በምን መልክ ቢደራጅ ነው ዕውነተኛ ነፃነቱን ሊቀዳጅ የሚችለው? ወይንስ መሪዎች ነን የሚሉት ስልጣንን ከጨበጡ በኋላ በደመ-ነፍስ በመመራት የሚፈልጉትን ነገር ለማድረግ ነው ወይ ዋና ዓላማቸው? በመሪዎችና በተቀረው ህዝብ ዘንድስ የሚኖረው ግኑኝነት በምን መልክ ይዋቀራል? በፖለቲካና በነፃነት መሀከልስ ያለው ግኑኝነት ምን ይመስላል? ፖለቲካስ ከዕውነተኛ ነፃነት ተነጥሎ የሚታይ ነገር ነው ወይ? እያልን ደረጃ በደረጃ ለመመርመር እንሞክር።  ፖለቲካ ማለት ምን ማለት ነው? ሁሉም ፖለቲከኛ መሆን ይችላል ወይ? የሚሉትን ጥያቄዎች በማንሳት ለመወያየት እንሞክር።

ለመሆኑ ፖለቲካ ማለት ምን ማለት ነው? ማንኛውም ሰው ፖለቲከኛ መሆን ይችላል ወይ?

 እንደማንኛውም ሳይንሳዊ ዕውቀት ፖለቲካም ሳይንስ ነው። ፖለቲካን ሳይንስ የሚያሰኘው በአንድ አገር ውስጥ የሚኖርን ተጨባጭና በሰዎች፣ በተለይም በገዢው መደብና በተቀረው የህብረተሰብ ክፍል፣ በብዙ መልኮች ሊገለጽ የሚችልውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ግኑኙነትን መተንተኛ መሳሪያ ስለሆነ ነው። እንደ አንድ አገር ወይም ህብረተሰብ የማቴሪያል የዕድገት ደረጃና ፖለቲካዊ ንቃተ-ህሊናና ህዝባዊ አደረጃጀት ሁኔታ የአተናተኑም ዘዴ ይለያል። ስለሆነም በአንድ አገር ውስጥ ስልጣንን የጨበጠ ኃይል ጨቋኝና ለተስተካከለና ለተሟላ ዕድገት እንቅፋት ከሆነ ለምን እንቅፋት ለመሆን እንደቻለ ወይም ደግሞ ለምን ዲሞክራሲያዊ ባህርይ እንደሌለው መመርመር የሚቻለው ፖለቲካ ሳይንሳዊ ባህርይ እንዳለው ግንዛቤ ከተገባ ብቻ ነው። ፖለቲካ ሳይንሳዊ ባህርይ ሊኖረው የሚችለው ከሌሎች ዕውቀቶች፣ ማለትም ከፍልስፍናና ከህብረተሰብ ሳይንስ ወይም ከሶስዮሎጂ ጋር በቀጥታ የተያያዘ መሆኑን ግንዛቤ ካለ ብቻ ነው። በተለይም ፖለቲካ በፍልስፍናና በማህበራዊ ሳይንስ እስካልተደገፈ ድረስ የህዝቡን የኑሮ ሁኔታና፣ በህብረተሰቡ ውጥ ያለውን የኃይል አሰላለፍ በደንብ ለማንበብና በቲዎሪ አማካይነት ለመተንተን በጣም ያስቸግራል። በምድር ላይ የሚታየውን ተጨባጭ ሁኔታ መተንተን ካልተቻለ ደግሞ ያለውን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፖሊሲ ለመንደፍ ያዳግታል። ስለሆነም ስልጣንን የጨበጠው ኃይልም ሆነ ስልጣን ላይ ለመውጣት የሚታገሉ የተለያዩ ድርጅቶች በምን ዐይነት ፍልስፍናና ርዕዮተ-ዓለም እንደሚመሩ በግልጽ ማሳየት አለባቸው። በግልጽ የሚታዩ ህዝባዊ ችግሮችንም በቲዎሪ ደረጃ መተንተንና እንዴትስ መፈታት እንደሚችሉ በግልጽ ማስቀመጥ አለባቸው። ይህንን ሲያደርጉ ብቻ ነው ድርጅቶቻቸው በእርግጥም ፖለቲካዊ ይዘት እንዳላቸውና ለህዝብና ለአገር መቆርቆራቸውን ማወቅ የሚቻለው።  

    በረጅሙ ጊዜ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ታሪካችን ተጨባጭ ሁኔታዎችን፣ ማለትም ድህነትንና ረሃብን፣ አጠቃላይ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ድቀትን፣ የጠቅላላውን ህዝብ የአኗኗር ሁኔታና ባህላዊና የስነ-ልቦና ነክ ነገሮችን የማንበብና የመተንተን ልምድ በፍጹም የለንም። እንደሚታወቀው አንድ ሰው አሞት ሀኪም ቤት ሲሄድ ሃኪሙ መድሃኒት ከማዘዙ ወይም አጠቃላይ ህክምና ከማድረጉ በፊት ለምን እንደመጣና የትስ ቦታ ላይ እንደሚያመው መጠየቅ አለበት። የአኗኗሩን ሁኔታ፣ ስለሚመገባቸው ምግቦች፣ አልክሆል ይጠጣ አይጠጣ እንደሆን፣ ሲጋራ ያጨስ አያጨስ እንደሆነና፣ ስፖርትስ ይሰራ እንደሆን… ወዘተ. ይጠይቀዋል። የሚያስፈልጉትን ጥያቄዎች ከጠየቀው በኋላ በልዩ ልዩ መሳሪያዎች ይመረምረዋል። የልቡን ትርታና የትንፋሹን ሁኔታ ይለካል። እንደየሁኔታው ዐይኑንና ጠፍሮችን፣ እንዲሁም ጉልበቱን ነካ ነካ ያደርጋል፤ ወይም ያያል። ይህንን ሁሉ ካደረገ በኋላ ምርመራው በቂ መስሎ ካልታየው ሌላ ምርመራ ያደርግለታል። በቂ ምርመራ ካደረገለትና በእርግጥም የበሽታውን ምክንያትና ዐይነት ካወቀ ብቻ መድሃኒት ያዝለታል፤ ወይም ህክምና ያደርግለታል።  ለአንድ ህብረተሰብም በደፈናው አንዳች ዐይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከመንደፉ በፊት የአገሪቱንና የህብረተሰቡን ችግር በጥልቀት መመርመር አለባቸው። ለድህነትና ለኋላ-ቀርነት ምክንያቶች የሆኑ ነገሮች መታወቅ አለባቸው። ለችግሮች ዋና ምክንያት የሆኑ ነገሮች ከመመርመራቸውና ከመታወቃቸው በፊት በአቦሰጡኝ ተግባራዊ የሚሆን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ድህነትን በፍጹም አይቀርፍም፤ ከኋላ-ቀርነትንም አያስወግድም። እንደዚሁም ትግል የሚሉት ፈሊት ከመጀመሩ በፊት የትግሉ አስፈላጊነት መመርመር አለበት። አገዛዙ ለምን ድህነትን ፈልፋይና ጨቋኝ ስርዓት እንደሆነ ማጥናት ያስፈልጋል። ምክንያቶቹ ከታወቁ በኋላ ደግሞ የግዴታ ችግሮችን ለመረዳትና ለመተንተን የሚያስችሉና መልስም ለመፈለግ የሚያመቹ ትክክለኛ የሆኑ የፍልስፍና፣ የሳይንስና እንዲሁም የቲዎሪ መመሪያዎች መፈለግ አለባቸው።  እንዲያው በደፈናው ድርጅት እንመስርት ወይም ደግሞ የጫካ ትግል ማድረግ አለብን ብሎ ወደ ጫካ ወይም በረሃ መግባት ላለው ችግር መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ ውስብስብና በቀላሉ የማይፈታ ያደርገዋል። 

ስለሆነም ትግል የሚሉትን ፈሊጥ አንግበው በስላማዊ መንገድም ሆነ የጦርነት ትግል የሚያካሂዱ ድርጅቶች ስለፖለቲካ ያላቸው ግንዛቤ የተጣመመ ወይም አልቦ ነው ማለት ይቻላል። አነሳሳቸው በስሜት ላይ የተመረኮዘ እንጂ ምርምርን መሰረት ያደረገና በአንዳች ዐይነት ፍልስፍና በመመራት አይደለም። ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ በጨቋኝና በተጨቋኝ መደብ መሀከል ያለ ችግር አድርገው በመቁጠር፣ አሊያም ደግሞ ኢትዮጵያ የብሄረሰቦች እስር ቤት ናት በማለት በደፈናው ትግል ይጀመራሉ። በዚህ ዐይነት የትግል ስልት ውስጥ ጨቋኝ የሚባለው መደብ የንቃተ-ህሊና ሁኔታ ቁጥር ውስጥ አይገባም። በተጨማሪም የንቃተ-ህሊናውን የዕድገት ደረጃ ሊወስን የሚችለው በምድር ላይ የሚታየው የማቴሪያል ሁኔታ በፍጹም አይነበብም። እንዲያው በደፈናው ትግሉ በጨቋኝና በተጨቋኝ መሀከል ያለ ነው በማለት ይደመደማል።  ያለውም አማራጭ ጨቋኝ የሚባለውን መደብ በጦር ትግል ማውረድና የተጨቋኙን መደብ መንግስት ማቋቋም ነው። በታሪክ እንደተረጋገጠው ከሆነ ግን ተጨቋኝ የሚባለው መደብ ስልጣንን አይይዝም። ስልጣን ላይ ቁጥጥ የሚለው በጭፍን አስተሳሰብ የሚመራው ኋላ-ቀር የሆነ የንዑስ ከበርቴ መደብ ወይም ከዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን አቋርጦ የወጣ ኤሊት ነው። በዚህ መልክ የተደረገና የሚደረግ ትግል ከመጀመሪያውኑ ፖለቲካ የሚባለውን ታስሪክ መስሪያ ሳይንስ ትርጉም እንዳይኖረው ያደርጋል። ህብረተሰብአዊ ችግሮችን መተንተኛና መፍቻ ከመሆኑ ይልቅ ወደ መጨቆና መሳሪያነት ይለወጣል። 

 ስለፖለቲካ በሚወራበት ጊዜ ሁለት ዐይነት የትግል ዘዴዎች አሉ። አንደኛው አብዮትን ማካሄድ ነው። ይሁንና ግን ለብዙ መቶ ዐመታት የአንድን ህብረተሰብ ዕድል ሲወስን የኖረ ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፈን ስርዓት ከመቅጽበት መለወጥ በፍጹም አይቻልም። ሺለር የሚባለው ገጣሚና የቲአትር ደራሲ „ተፈጥሮ መዝለልን አትችልም“  እንዳለው አንድን ማህበረሰብ ከአንደኛው ወደ ሌላኛው ስርዓት በጉልበት መለወጥ አይቻልም። ጨቋኝ የሚባለው መደብ ቢወገድም ለብዙ መቶ ዐመታት ስር የሰደዱ አስተሳሰቦችና የአኗኗር ስልቶች፣ እንዲሁም የእርስ በእርስ ግኑኝነትን ከመቅጽበት በመለወጥ በሌላ መተካት በፍጹም አይቻልም። ባህላዊ የአኗኗር ስልቶች ለረጅም ጊዜ ተተክለው የሚቆዩበት ጊዜ አለ። በሌላ ወገን ግን ባህልንና የእርስ በእርስ ግኑኝነቶችን እንዳሉ ለማውደም መሞከር የማያስፈልግ ማህበራዊና የስነ-ልቦና ቀውስ ውስጥ ሊከት ይችላል። ከዚህ ስንነሳ ፖለቲካ በዝግታና በተከታታይነት፣ ይሁንና ደግሞ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መካሄድ ያለበት ጉዳይ ነው። ይኸኛው ሁለተኛው መንገድ ኢቮሉሽነራዊ ስለሆነ ፖለቲካ የሚባለው ጽንሰ-ሃሳብ ከብዙ ነገሮች ጋር ተጣምዶና ተዋህዶ ተግባራዊ ከሆነ በእርግጥም መሰረታዊና ዘላቂ ለውጥ ማምጣት ይችላል። ሰፊው ህዝብና ምሁሩ በየጊዜው የሚነሱ አዳዲስ ችግሮችን ለመቋቋና መፍትሄም ለመስጠት ይችላሉ። በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ብዙ ነገሮች ተጣምረው በአንድ ላይ መካሄድ ያለባቸው መሆናቸውን በመረዳት በተቻለ መጠን አማራጭ መፍትሄን ለመፈለግ ይጥራሉ። በዚህ መልክ ፖለቲካዊ ለውጥ በአንድ ወቅት የሚገበዳድ ሳይሆን ከፍተኛ ጥበብን የሚጠይቅ መሆኑ ግልጽ ይሆናል። በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የሚገኙ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተለያየ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ስታተስ ቢኖራቸውም አንደኛው ካለሌላኛው ለመኖር እንደማይችልና፣ አንድን ህብረተሰብ በስራ-ክፍፍልና በተለያየ ሙያ በመሰማራት መገንባት እንደሚቻል ግልጽ ይሆናል። በመሆኑም ፖለቲካ አንደኛው የህብረተሰብ ክፍል በሌላው ላይ እንዲነሳ በማድረግ የማያስፈልግና ለማንም የማይጠቅም ግብግብ ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ከስራና ከፈጠራ ተግባር የሚያስተጓጓል ሳይሆን አንድ ህዝብ ማንነቱን እንዲያውቅ የሚደረግበት ልዩ ዕውቀት ነው። ፖለቲካ ህዝብን ማንቂያና ማደራጃ፣ ይሁንና ግን ደግሞ ወደ አንድ ወጥ ርዕዮተ-ዓለም በመለወጥ መጨቃጨቂያ መሳሪያ የሚሆን አይደለም። የተለያየ አስተሳሰቦች ወይም አመለካከቶች መንሸራሸርና መዳበር፣ ከቲዎሪም አንፃር መተንተን መንፈስን ያዳብራል። መቻቻል እንዲኖር ያደርጋል። 

አብዛኛውን ጊዜ በአገራችንም ሆነ በተቀሩት የአፍሪካ አገሮች በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ለውጥ ማምጣት የማይቻለው የፖለቲካ ስርዓቱና የመንግስታት መኪናዎች ከታች ወደ ላይ ከማህበራዊና ከኢኮኖሚ ለውጥ ጋር ተያይዘው ያደጉ ሳይሆኑ ከላይ የተቀመጡና አብዛኛውን ጊዜ የመጨቆኛ ባህርይነት ያላቸው በመሆናቸው ነው። በዚህም ምክንያት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥን የማምጣት ኃይላቸው በጣም ደካማ ብቻ ሳይሆን፣ እንዲያውም መሰረታዊ ለውጥን የሚቀናቀኑና የሰፊው ህዝብ ኑር እንዳይሻሻል ከፍተኛ እንቅፋት የሆኑና የሚሆኑ ናቸው። በዚህም ላይ ከውጭ የሚመጣን ትዕዛዝ ተግባራዊ በማድረግ የባሰውኑ ድህነት እንዲፈለፈልና ጠቅላላው ሁኔታ እንዲዘበራረቅ የሚያደርጉ ናቸው። ስለሆነም ይህንን የመሰለ መሰረታዊ ለውጥን የሚቀናቀንና ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ዕድገት እንቅፋት የሆነን የመንግስት መኪና አወቃቀርና የፖለቲካ ስርዓት፣ እንዲሁም የአገዛዙና የጠቅላላውን ህዝብ ንቃተ-ህሊና በፖለቲካ ቲዎሪና በፍልስፍና መመርመር በጣም አስፈላጊ ነው። በመንግስት መኪናውና በፖለቲካ ስርዓቱ ላይ ሁለ-ገብ የሆነ የመንፈስ ተሃድሶ ዘመቻ ካልተካሄደና የመንግስትም መኪና ከጨቋኝ ባህርይው እስካልተላቀቀ ድረስና ህዝባዊ ባህርይ እስከሌለው ድረስ እንደኛ ያለውን አገርና ህዝብ ከተተበተበበት ችግር ማላቀቅ በፍጹም አይቻልም።   የአለፉት አርባ ዐመታት የምርጫ ታሪክም እንዳስተማረን በአገራችንም ሆነ በተቀሩት የአፍሪካ አገሮች በምርጫ አማካይነት በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ኢኮኖሚና አገር መገንባት በፍጹም አይቻልም። በተቃራኒው በየአራት ዐመቱ የሚካሄድ ምርጫ ድህነትን ቀራፊና ህዝብን በፖለቲካ አሳታፊ ከመሆኑ ይልቅ ያለውን ድህነት የባሰውን የሚያጠናክርና ጠቅላላው ኢኮኖሚ ግልጽነት እንዳይኖረው የሚያደርግ ነው። አዳዲስ የፖለቲካ ተዋንያኖች በመፈራረቅ በረቀቀ መንገድ የአገር ሀብት እንዲበዘበዝና ህዝቡም ዕውነተኛ ነፃነቱን እንዳያገኝ ያደርጋሉ። ስለሆነም የአገራችንንም ሆነ የተቀሩትን የአፍሪካ አገሮች የኢኮኖሚና የማህበራዊ ችግሮች በምርጫ አማካይነት በፍጹም መፈታት አይችሉም። የሳይንስና የቴክኖሎጂ አብዮትም ማካሄድ በፍጹም አይቻልም። በየአራት ዐመቱ የሚደረግ ምርጫ ሊሰራ የሚችለው በካፒታሊስት አገሮች ብቻ ነው።    

የካፒታሊስት አገሮችን ለየት የሚያደርጋቸው የብዙ መቶ ዐመታት የፖለቲካ ትግል ልምድ ያላቸው በመሆናቸው ነው። በአብዛኛዎቹ አገሮች ነፃ የሆኑ ተቋማት አሉ። በህግ አውጭው፣ በህግ አስፈጻሚውና በኤክስኩቲቩ መሀከል ግልጽ የሆነ የስራ ክፍፍል አለ። በደንብ የዳበረና የተገለጸለት የሲቪል ማህበረሰብ አለ። ይህ ዐይነቱ የሲቪል ማህበረሰብ የመንግስታትን ፖሊሲ የመቆጣጠር ብቃትና ኃይል አለው። ከዚህም በላይ በሙያ ማህበር የተደራጁ ኃይሎች አሉ። በጀርመን የሰራተኛው የሙያ ማህበር የራሱ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የምርምር ተቋም አለው። አማራጭ ፖሊስ አውጥቶ ለመንግስት ያቀርባል፤ ወይም እንዲታከል ይታገላል።  ሳይንስና ቴክኖሎጂ የኢኮኖሚው ዋና አንቀሳቃሽ ኃይሎች ናቸው። የስራ-ክፍፍል የዳበረና ሰፋ ያለው የውስጥ ገበያ አለ። ኢኮኖሚው እርሱ በእርሱ የተያያዘ ነው። መንግስታት በከፍተኛ ደረጃ ለምርምር ባጀት ይመድባሉ። ሳይንስና ቴኮኖሎጂ በደንብ እንዲዳብሩ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። የሰፈው ህዝብ መሰራታዊ ችግሮች የተሟሉ ናቸው። ማንም ሰው ደሀ በመሆኑ መንገድ ላይ አይጣልም። ወይም ካላበቂ ምክንያት ከቤቱ እንዲወጣ አይደረግም። ችግር ካለበት ከመንግስት ድጋፍ ያገኛል። ፓርላሜንት የኤክስኩቲቩን ፖሊሲዎች ይቆጣጠራል። የኤክስኩቲቪ ስራዎችን የሚቆጣጠሩ ፓርላሜንታሪ ኮሚሽኖች አሉ። ህገ-መንግስትን የጣሱ ስራዎች ከተሰሩ እንደስራ ክፍፍላቸው የፓርላሜንታሪ ኮሚሽኖች የኤክስኩቲቩን ስራዎች ይመረምራሉ። መንግስት ራሱ ህገ-መንግስቱን በሚቆጣጠረው ፍርድቤት የመክሰስ ግዴታ አለበት። ህገ-መንግስትን የሚጥሱ ስራዎች ከተሰሩ ወይም ህግ ከጸደቀና ከተከሰሰ ፍርድ ቤቱ ህጉ ከህገ-መንግስቱ ጋር የሚስማማ አይደለም በማለት እንዲሻሻል ወይም ተግባራዊ እንዳይሆን የማዘዝ መብት አለው።  የመንግስት መኪና ወደ ተራ ጨቋኝነትና በዝባዥነት የተለወጠና የሚለወጥ አይደለም። ፖሊስ እንደፈለገው እየተነሳ በሰው ላይ አይተኩስም ወይም ካለበቂ ምክንያት አያስርም። ባጭሩ በካፒታሊስት አገሮች ከሞላ ጎደል የህግ የበላይነት አለ። መንግስት እንደበላይ አካል ብቻ የሚቆጠር ሳይሆን የዜጋውን መብት የማስጠበቅ ኃላፊነት አለበት። ስላምና ደህንነት እንዲሰፍን አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ አለበት። ስለሆነም ምርጫ ቢካሄድና ሌላ ፓርቲ ስልጣንን ቢይዝ ይህን ያህልም መሰረታዊ ለውጥ አያመጣም፤ ወይም ያለው እንዲናጋ አያደርግም። የዚኸኛውን ወይም የዚያኛውን የህብረተሰብ ክፍል በቀረጥና በሞኔተሪ ፖሊሲ አማካይነት የሚጠቅም እርምጃ ብቻ እንዲወስድ ይገደዳል። ይህም ቢሆን ከንጹህ የኢኮኖሚ ስሌት በመነሳት ብቻ  ነው። የስራ መስክ ሊከፈትና ኢኮኖሚውም በዚህ መልክ ብቻ ነው ሊያድግ የሚችለው ከሚለው ስሌት በመነሳት ብቻ ተግባራዊ የሚሆን ፖሊሲ ነው። ፓርላሜንት ውስጥ መቀመጫ ያላቸው ሌሎች ፓርቲዎች የመቃውም መብት አላቸው። ፖሊሲው ተቀባይነት የሚኖረው የድምጽ ብልጫ ካገኘ ብቻ ነው። እንደኛ አገር በግምትና በአወቅሁኝ ባይነት የሚሰራ አይደለም። ቻንሰለሩ ወይም ቻንስለሯ እንደፈለጉት የመወሰን መብት የላቸውም። እነሱም ራሳቸው የህግ የበላይነትን የሚያከብሩና በህግ የሚገዙ ናቸው።

 በመሰረቱ በካፒታሊስት አገሮች የሚንቀሳቀሱት የተለያየ ስም ያላቸው ፓርቲዎች የካፒታሊዝም ውጤቶች ናቸው። ካፒታሊዝም ከማደጉ በፊት የተፈጠሩ አልነበሩም። ካፒታሊዝም እያደገና የአብዛኛውን ህዝብ ዕድል እየወሰነ ሲመጣ ህብረተሰቡም መሰበጣጠር(Social Differentiation)ጀመረ። በዚህም መሰረት የዚህን ወይም የዚያኛውን መደብ ጥቅም እናስጠብቃለን የሚሉ፣ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ፣ ወግ አጥባቂ ፓርቲ፣ ሊበራል ፓርቲ፣ የግራ ወይም የኮሙኒስት ፖርቲ፣ አሁን ደግሞ የቀኝ አክራሪ ወይም የፋሽሽታዊ አዝማሚያ ያለው በመደራጀት ይወዳደራሉ። ካፒታሊዝም በራሱ ኃይል የሚንቀሳቀስ እንደመሆኑ መጠንና በአብዛኛዎች አገሮችም ከሞላ ጎደል የተስተካለ ዕድገት ስላለ አንደኛው ፓርቲ በምርጫ ጊዜ ቢያሽንፍ መሰረታዊ ለውጥ ሊያመጣ አይችልም፤ ወይም እንደፈለገው ጠቅላላውን ፖሊሲ ሊቀይር በፍጹም አይችልም።

ከዚህ ሁለት ተፃራሪ ሁኔታዎች ስንነሳ በአገራችን ምድር መካሄድ የሚችለው ፖለቲካ ለየት ያለ ነው ማለት ይቻላል። በመጀመሪያ ደረጃ አንድ ድርጅት የአገሩን ተጨባጭና ያለውን የሰው በሰው ግኑኝነት መመርመር የሚያስችል ፍልስፍናና ሳይንሳዊ መመሪያ ዘዴ እንዲኖረው ያስፈልጋል። አንድ ስልጣንን ይዛለሁ፣ የብዙ ሚሊዮንንም ህዝብ ዕድል እወስናለሁ የሚል ድርጅት በዘፈቀደ ሊጓዝ አይችልም። የሚመራበትና በግልጽ የሚታዩ ችግሮችንና ምክንያቶቻቸውን በማጥናት መልስ ለመመለስ የሚችል መሆን አለበት።  ግልጽ የሆነ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፖሊሲ፣ በአጭሩ አጠቃላይ የሆነ የአገር መገንቢያ ፖሊሲ እንዲኖረው ያስፈልጋል። ምክንያቱም ፖለቲካ ፖለቲካ መሆኑ የሚታወቀው ሰፊው ህዝብ ከመደራጀቱ ባሻገር ለመኖር የሚያስፈልጉት መሰረታዊ ነገሮች ሲመለሱለት ብቻ ነው። አገሩ መኖሪያና መንቀሳቀሻ ሆኖ ከተዘጋጀለት ብሄራዊ ስሜቱ ይዳብራል። አገሩን አገሬ ብሎ ይጠራል። የመሰደድና ሌላ አገር ሄዶ የመስራት ፍላጎት አይኖረውም። ባጭሩ ፖለቲካ የሚባለው ፅንሰ-ሃሳብ ውስጣዊና ውጫዊ ሁኔታዎችንና ጉዳዮችን መመርመሪያና መልስም መፈለጊያ መሳሪያ ነው።፡

በመሆኑም ስለፖለቲካ በሚወራበት ጊዜ ከሰው ጋር ወይም ከህዝብ ጋር የተያያዘ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ፖለቲካ ለጥቂት ፖለቲከኞች ነን ለሚሉ ሰዎች የሚሰጥ ወይም የተሰጠ ሳይሆን ህዝባዊ ባህርይ ያለውና በእርግጥም ሰፊውን ህዝብ ማሳተፍ የሚችል መሆን አለበት። አብዛኛውን ጊዜ እንደኛ ባሉ ወደ ኋላ በቀሩ አገሮች ስለፖለቲካ ያለን ግንዛቤ በጣም የተሳሳተና ወደ ኋላ የቀረ ነው። በፖለቲካ ዓለም ውስጥ እሳተፋለሁ የሚል ከመጀመሪያውኑ እራሱን አጉልቶ ያያል። ሰለፖለቲካ ሲያወራ የብዙ ሚሊዮንን ህዝብ ዕድል የሚመለከት እንደሆነ በፍጹም አይገነዘብም። በተጨማሪም አገርንና ህዝብን፣ ባንዲራንና ህዝብን በመነጠል፣ የሰፊው ህዝብ ፍላጎት እንዳይመለሰ ያደርጋል። ከዚህም በላይ አብዛኛው ስለፖለቲካ ያለው ግንዛቤ በጣም ደካማ ስለሆነ በመጀመሪያ ደረጃ ከምን መነሳት እንዳለበት በፍጹም አይገነዘብም። እንደዚህ ዐይነት ድርጅት ወይም ግለሰብ ስልጣን ላይ በሚወጣበት ጊዜ ሰፊውን ህዝብ የሚመለከትና፣ ችግሮቹን የሚፈታለትን ፖሊሲ ተግባራዊ አያዳርግም። ትዕዛዝ ተቀባይ በመሆን አንድን አገር ያዘበራርቃል፤ ህዝቡም ወዴት እንደሚያመራ ለመገንዘብ እንዳይችል ያደርጋል። ተግባራዊ በሚያደርገውም ፖሊሲ ህብረተሰብአዊ ቅራኔ እንዲፈጠር ያደርጋል። የተበላሽና ፈሩን የለቀቀ የህብረተሰብ ክፍል እንዲፈጠር በማድረግ የጠቅላላው ህዝብ አስተሳሰብ እንዲበላሽ ያደርጋል። ይህ ሁኔታ በተለይም ህውሃት ወይንም ወያኔ ስልጣንን ይዞ 27 ዐመታት ያህል ሲገዛ በግልጽ የታየና ዛሬ አገራችን የምትገኝበትን ሁኔታ የሚገልጽ ነው። ባጭሩ ግልጽ የሆነ ርዕይና ፍልስፍና የሌለው ድርጅት ወይም ግለሰብ አንድን ህብረተሰብ ከማዘበራረቅ አልፎ እንድትወድም ያደርጋል። ማንም እየመጣ ሀብቷን እንዲዘርፍ በማድረግ የብዙ ሺህ ዐመታት ታሪክና ባህል እንዲወድም ያደርጋል። 

  ለማንኛውም ፖለቲካ እንደተራ ነገር መታየት ያለበት ነገር ሳይሆን ሳይንስ ነው። በተፈጥሮ ሳይንስ አማካይነት የተፈጥሮን ምንነትና ውስጣዊ ህግ መረዳት የሚቻለውን ያህል ፖለቲካም ልክ እንደተፈጠሮ ሳይንስ የአንድን ህብረተሰብ ውስጣዊ ህግና ሂደት ለመረዳት የሚያስችል መመርመሪያ መሳሪያ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ፖለቲካ በቀጥታ ከተፈጥሮ ሳይንስ ጋር የሚያገናኘው ነገር ባይኖርም፣ በሌላው ወገን ግን አንድ ሰው የተፈጥሮን ምንነትና በተፈጥሮ ውስጥ የሚገኙ ነገሮችን አፈጣጠርና በራሳቸው ውስጣዊ-ኃይል ያላቸውን የማደግ ኃይል ችሎታ ሲረዳ ብቻ የፖለቲካን ምንነትንና በፖለቲካ አማካይነት አንድን ህብረተሰብ መለወጥ ወይም ማሻሻል እንደሚቻል ሊገነዘብ ይችላል። ስለሆነም ይላል በሮማውያን አገዛዝ ዘመን የነበረው ሴናካ የሚባለው ታላቅ ፈላስፋ፣ በፖለቲካ ዓለም ውስጥ የሚነሱ ውዝግቦች በሙሉ ዋናው ምክንያት የተፈጥሮን ህግ ካለመረዳት የሚመነጩ ናቸው።  ከሱ በፊት የነበሩ ታላላቅ ፈላስፋዎችም በቀጥታ ስለፖለቲካ ከማውራታቸውና ከመጻፋቸው በፊት አትኩሮ የሰጡት የተፈጥሮንና የኮስሞስን ህግ መረዳት ነበር። በጠቅላላው ተፈጥሮ የሚባለውን ነገር ምን ምን ነገሮች እንዳያያዟቸውና፣ በምን ዐይነትስ ህጎች እንደሚተዳደሩ መመራመርና ከዚህ በመነሳት በጊዜው በህብረተሰባቸው ውስጥ የነበረውን በፖለቲካና በጎሳ ስም የሚካሄደውን መጨራረስና አላስፈላጊ ጦርነቶች መነሻቸውን ማወቅ ዋናው የፍልስፍናቸው መመሪያ ነበር።  ስለሆነም በፍልስፍና አማካይነት ወይም ጥበብን በመሻት የሰውን አስተሳስብ ማነፅና የተፈጥሮን ምንነት ለመገንዘብና በህብረተሰብ ውስጥ ያሉና ሊነሱ የሚችሉ ችግሮችን ለማስተካከል ወይም መፍትሄ መፈለግ ከፖለቲካዊ አስተሳሰብ ጋር መዋሃድ እንዳለባቸው ከብዙ ሺህ ዐመታት በፊት የተደረሰበት መሰረታዊ ሀቅ ነው። ስለዚህም የግዴታ ዕውነተኛ ዕውቀትን መፈለግና ዕውነተኛ ዕውቀት ከተሳሳተ ወይም ሶፊስታዊ ከሆነ አስተሳሰብ የሚለይበትን መንገድ በማሳየት ህብረተሰብአዊ ችግሮችን በሳይንሳዊና በፍልስፍናዊ መንገድ መፍታት መቻል ዋናው የትግላቸው ወይም የአስተሳሰባቸው መመሪያ ነበር። 

ፖለቲካ ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን ከሞላ ጎደል ካየን በኋላ፣ ለመሆኑ ማንኛውም ሰው ፖለቲከኛ መሆን ይችላል ወይ? የሚለውን ጥይቄ ለመመለስ ልሞክር። ማንም ሰው ስለፖለቲካ ማውራት ይችላል፤ ሁሉም ሰው ግን ፖለቲከኛ መሆን አይችልም። በሌላ ወግን ግን በፖለቲካ ስም የሚወራ ነገር ሁሉ ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ ይዘት አለው ማለት አይደለም። ስለዚህም አንድ ሰው ፖለቲካ እያለ ስለለፈለፈ ፖለቲከኛ  ነው የሚያሰኘው አንዳችም ነገር ሊኖር አይችልም።  በእርግጥ በዛሬው ዓለም በየአገሩ ያሉ መሪዎችንና ፖለቲካቸውን ስንመለከት ምናልባት ፖለቲካ በዚህ መልክ መካሄድ ያለበት ይመስለን ይሆናል። በተለይም ፖለቲካ የሚባለው መሰረታዊ ሃሳብ ከሳይንሳና ከፍልስፍና ተነጥሎ መታየት ከጀመረበት ከብዙ ዐመታት ጀምሮ ፖለቲካ የጥቂት ሰዎች ፍላጎት ማርኪያ ለመሆን በቅቷል ማለት ይቻላል፡ አንዳንዱ አጋጣሚንና የኃይል ክፍተትን ወይም በየአገሩ ያለውን ዝቅተኛ ንቃተ-ህሊና በመጠቀም ስልጣን ከጨበጠ በኋላ ጠቅላላውን ህዝብ ሳይሆን የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል ጥቅም ማስጠበቂያ መሳሪያ ሲያደርግ እንመለከታለን። ባጭሩ ፖለቲካ ህዝባዊ መሆኑ ቀርቶ መንግስትና ፖለቲካ ወደ ግል-ሀብትነት የቻሉበትን ሁኔታ እንመለከታለን። መንግስትና ፖለቲካ ስላምን የሚያሰፍኑና ብልጽግናን የሚያመጡ መሆናቸው ቀርቶ ጦርነትን ፈልፋይና ወደ ዘራፊነት የተለወጡበት ዘመን ውስጥ ነው ያለነው። በአብዛኛዎቹ አገሮች አምባገነኖች ነግሰዋል። የቱርክ፣ ብራዚልንና የአሜሪካንን ፖለቲካ ብቻ መመልከቱ በቂ ነው። 

ለማንኛውም አንድ ሰው ወደ ፖለቲካ ዓለም ውስጥ ከመግባቱ በፊት ስለፖለቲካ በቂ ግንዛቤና ተሰጥዖ ይኑረው አይኖረው እንደሆን መመርመር አለበት። ጭንቅላቱም ለፖለቲካ ተስማሚ ይሁን አይሁን በልዩ የምርመራ ዘዴ አዕምሮው መመርመር አለበት። ከዚህም በላይ የህይወት ታሪኩ መጠናት አለበት። ይህም ባይሆን እንኳ ፖለቲካ በስሜትና በግብዝነት የሚካሄድ ሳይሆን ውስጣዊ ፍላጎትንና ዝንባሌን የሚጠይቅ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። በተጨማሪም ከፍተኛ የሆነ የሞራል ብቃትና ባህልን ይጠይቃል። ከዚህም በላይ ፖለቲከኛ ለመሆን የሚፈልግ ሰው ከፖለቲካ አስተሳሰብ ጋር ማደግ አለበት። የፖለቲካን ትርጉም ለመረዳት ከልጅነቱ ጀምሮ ከፖለቲካ ፍልስፍናና ከህብረተሰብ ሳይንስ ጋር መተዋወቅ አለበት። ፖለቲካ ራሱን የቻለ ሙያ እንደመሆኑ መጠን አንድ ሰው ችሎታውን ከመረመረ በኋላ ያለ የሌለ ኃይሉን በዚህ ላይ ማዋል አለበት። ብዙ ዕውቀትን ማዳበር አለበት። በዕውቀትም አማካይነት ባህርዩን መኮትኮት ይችላል። በዚህ መልክ ፖለቲከኛ ለመሆን ከሚያስችሉት መሰረተ-ሃሳቦች ጋር ለመተዋወቅ ይችላል። ማዳመጥና ትችትን መቀበል፣ አንዳች ዐይነት ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት ከሁሉም አንፃር መመርመር እንዳለበት ይገነዘባል። ፖለቲካ ሳይንስ እንደመሆኑ መጠን የተወሰነ ሎጂክንንም መከተል ያስፈልጋል። መቅደም በሚገባቸውና በማይገባቸውን ነገሮች መሀከል መለየትን ያስፈልጋል። እነዚህንና ሌሎች ቅድመ-ሁኔታዎችን ሲያሟላ ብቻ ፖለቲከኛ ለመሆን እፈልጋለሁ ብሎ መወሰን ይችላል። ስልጣን ላይ ከወጣም በኋላም በየጊዜው ልምምድ መውሰድ አለበት። በህዝብ ውስጥ የሚነሱ ቅሬታዎችን የማዳመጥና የማስተካከል ኃላፊነት እንዳለበት መገንዘብ አለበት። 

ያም ሆነ ይህ ስለፖለቲካ በሚወራበት ጊዜ ትልቅ ኃላፊነትን የሚጠይቅና የአንድን ህብረተሰብ ዕድል፣ ምኞቱንና ህልሙን፣ የዛሬውን ብቻ ሳይሆን የተከታታዩንም ትውልድ ዕድል የሚመለከት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ፖለቲካ በአንድ ሰውና በአንድ ድርጅት ዙሪያ ብቻ የሚሽከረከር ሆኖ የሚታይ ነገር ሳይሆን፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሌሎችንም ማሳተፊያና ማነጋገሪያ ወይም ማወያያ መሳሪያ ሆኖ መታየትና በጭንቅላት ውስጥ መቀረጽ ያለበት ጉዳይ ነው። ከዚህም በላይ ፖለቲካ መጨቃጨቂያ መሳሪያ ሳይሆን ችግር መፍቻ መሆኑን በመረዳት አንድ ሰው ወደ ውይይት ወይም ክርክር ውስጥ ከመግባቱ በፊት በቂ ዝግጅትና ጥናት ማድረግ አለበት። ከአሳሳችና አንድን የህብረተሰብ ክፍል ወደ ጠብ ውስጥ እንዲያመራው ከሚያደርግና ቡድናዊ ስሜትን ከሚቀሰቅስና ጠብ ከሚያስጭር ሁኔታ መራቅ ያስፈልጋል። ፖለቲካ መለፍለፊያና አንድ ሰው እንደፈለገው በአወቅሁኝ ባይነት ካለማቋረጥ የሚናገርበት መሳሪያ ሳይሆን ሎጂካዊንና ሳይንሳዊ አነገጋርን የሚጠይቅ ነው። የአራዳዎችና የአፈ ጮሌዎች መሳሪያና ሌሎችን የሚያርቅና የሚያስፈራራ መሳሪያ አይደለም። ፖለቲካ ሙሉ በሙሉ ከተንኮል የጸዳና በመተማመንና በርዕይ ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት። ፖለቲካ የግዴታ የአንድን ሰው አምባገነናዊ ባህርይና ሁሉንም አውቃለሁ ባይነትን የሚቃወምና፣ በፖለቲካ ዓለም ውስጥም ሆነ ስልጣን ላይ ባሉት መሀከል በእኩል ደረጃና በመከባበር ግን ደግሞ በመሰረተ-ሃሳብ ላይ በመመርኮዝ የሚካሄድበት መሳሪያ ነው።  ስለሆነም ፖለቲካ አንድን ህብረተሰብ ጥበባዊ በሆነ መልክ ለመገንባት የሚያስችልና በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር ህዝብ ማንነቱን በማወቅ መንፈሳዊ ነፃነቱንና ራሱን በራሱ በማግኘት ፈጣሪና ታሪክን ሊሰራበት የሚችልበት መሳሪያ መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል። አንድ ፖለቲከኛ ነኝ የሚል ሰው የዛሬው ሁኔታ ካለትላንትናው፣ የትላንትናው ሁኔታ ቀድሞት ከነበረው ጋር ያልተያያዘ ሳይሆን፣ የተያያዘና፣ (Time-Binding) የቀደመውና ያለፈው ትውልድ የተወሰነ ስራ ሳይሰሩ የዛሬው ሁኔታ ሊፈጠር እንደማይችልና፣ ታሪክ ተከታታይነት ያለው መሆኑን የተገነዘበ መሆን አለበት። በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ በየታሪክ ኤፖኮች ውስጥ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ መጥፎም ሆነ ደግ ነገሮች ይሰራሉ። እነዚህ ነገሮች የግዴታ ወደ ተከታታዩ ትውልድ ይተላለፋሉ። ተከታታዩ ትውልድ በታሪክ ውስጥ ካለማወቅ የተነሳ መጥፎ ነገሮች ተደርገው እንደሆን በማረም አዲስና ህብረተሰብን አዳሽ ታሪክ ሰርቶ ለመጭው ትውልድ የማስተላለፍ ግዴታ አለበት። በሌላ አነጋገር፣ ከሶስት መቶና ከአራት መቶ ዐመታት በፊት ከንቃተ-ህሊና ማነስ የተነሳ የተሰሩ ጥፋቶችን በማንሳትና በመጨቃጨቅ እንዲሁም የትግል ፈሊጥ በማድረግ ስራን አደናቃፊ የሚሆንበት መሳሪያ አይደለም።  ፖለቲከኛ ነኝ ባይ በማንኛውም ወቅት ችግሮችን ለመፍታት ዝግጁ የሆነና መልስም ለመፈለግ ሳያቋርጥ እራሱን የሚያስጨንቅ መሆን አለበት። ፖለቲከኛ ነኝ ባይ ካሉቧልታዎችና ሳይንሳዊ ካልሆኑ አነጋገሮችና ትረካዎች የራቀ መሆን አለበት። የሚናገራቸውና የሚጽፋቸው በሳይንስ መነጽር የሚመረመሩና የሚፈተኑም መሆን አለባቸው። ይህም ማለት ማንኛውም ህብረተሰብ የዛሬውን ችግሮቹን በትረካና እንደዚህ ተደርገን ነበርን በማለት የሚፈታ ሳይሆን፣ በሳይንስ፣ በፍልስፍናና በሶይሎጂ እንዲሁም በተለያዩ ዕውቀቶች አማካይነት ብቻ ነው። ስለሆነም እነዚህን መሰረተ-ሃሳቦች በጭንቅላት ውስጥ ሳይቋጥሩ በፖለቲካ ውስጥ እሳተፋለሁ የሚል ሰው በአስቸኳይ ከፖለቲካ ዓለም መወገድ አለበት። ተከታዮች አሉኝ፣ ህዝብም እኔን ይወደኛል፣ ቦታ ካልተሰጠኝ ብጥብጥ እፈጥራለሁ የሚል ግለሰብ ስለፖለቲካ ምንነት ያልገባውና አጀንዳውም ሌላ የሆነ ሰው ብቻ ነው።

        ፖለቲካ ምሁራዊነትንና የአዕምሮ መጎልመስን ይጠይቃል!

የፖለቲካ ጥያቄ በቀጥታ ከነፃነት ጋር የተያያዘ እንደመሆኑ መጠን አንድ ሰው ወይም ድርጅት ስለፖለቲካ ሲያወራና እታገላለሁም ሲል ስለምን ነገር እንደሚያወራ ማወቅ አለበት። ነፃነት ደግሞ ለምን፣ ለማንና እንዴትስ የሚሉትን መሰረታዊ ጥያቄዎች የያዘ መሰረታዊ ሃሳብ ነው። ባጭሩ አንድ ደርጅትም ሆነ ግለሰብ ስለፖለቲካ ሲያወሩ ስለአንድ የህብረተሰብ ክፍል ወይም ህዝብ እንደሚያወሩ መገንዘብ አለባቸው። በአጠቃላይ ሲታይ የሰው ልጅ የማንኛውም ነገር ዋናው መለኪያ እንደመሆኑ መጠን መነሻውም ሰው ነው። ስለሆነም ስለፖለቲካ የሚያወራ ሰው ወይም ያገባኛል የሚል ሰው የነፃነትን ትርጉምና የሰውን ልጅ ማዕከላዊ ቦታ በቅጡ መገንዘብ አለበት። ይህም ማለት እራሱን እንደ በላይ አካልና ባለስልጣን የሚገምት ሳይሆን የነፃነትን ምንነት የሚያስተምርና በተግባርም ደረጃ በደረጃ እንዴት ሊፈታ እንደሚችል የሚያረጋግጥ መሆን አለበት። አንድ ሰው ሙሉ በሙሉ መንፈሱን ከኋላ-ቀር አስተሳሰብ ሳያፀዳና ሳይንሳዊ ይዘት ከሌላቸው አነጋገሮች ወይም አጻጻፎች ሳይላቀቅ ስለ ነፃነት አስፈላጊነት ቢያወራ እንደዚህ ዐይነት ፖለቲከኛ ነፃነት የሚለውን ትርጉም የተገነዘበ አይደለም ማለት ነው። ለዕውነተኛ ነፃነት የሚደረገው ትግል ደግሞ ከጎሳ ባሻገር መታየት ያለበትና እያንዳንዱን ግለሰብ የሚመለከት ነው። ስለሆነም ነፃነት በመስፈሪያ ተለክቶ ለተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል ብቻ የሚሰጥ ሳይሆን በአንድ አገር ውስጥ የሚኖርን ማንኛውንም ዜጋ የሚመለከት ነው። ወደድንም ጠላንም በጎሳ ተሳቦ የሚካሄድ ትግል በሳይንስና በቴክኖሎጂ፣ በቲአትርና በግጥም፣ በቆንጆ ከተማዎች ግንባታ፣ በልዩ ልዩ ምርቶች የሚገለጽ የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያግድና ህዝባዊ መተሳሰርንና ተጋግዞ አንድን አገር በጋራ ለመገንባት እንቅፋት የሚሆን ነው። ስለሆነም ዕውነተኛ ነፃነትና ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት የሚያስችል አይደለም። በአንፃሩ አምባገነናዊና ዘራፊ ስርዓት እንዲመሰረት የሚያመቻች ነው። በጎሳና በሃይማኖት ስም ተሳቦ የሚካሄድ ትግል ብዙ አገሮችን እያመሰና ለዕድገትና ለነፃነት እንቅፋት እንደሆነ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው።  ከዚህም በላይ ዛሬ በግልጽ እንደምናየው ብሄራዊ ክብራችን እንዲገፈፍ ያደረገና ዛቻም እንዲሰነዘርብን መንገዱን ያመቻቸ ትናንሽ ጭንቅላት ባላቸው ሰዎች የተነደፈ አገርን እንዳለ የሚያፈራርስ አደገኛ ስሌት ነው። 

ዕውነተኛ ፖለቲካ ከመንፈሳዊ ነፃነት ጋር በጥብቅ የተሳሰረ እንደመሆኑ መጠን በሁለ-ገብ ዕውቀት የሚደገፍ መሆን አለበት። አንድ ሰው አነሰም በዛም ሁለ-ገብ ዕውቀት ካለው ምሁራዊ ባህርይም ይኖረዋል። አንድን ነገር ከተለያዩ ጎኖች በማየት አመርቂ ትንተና መስጠት ይችላል። አንድን ሰው ምሁር ነው የሚያሰኘው ዲግሪ ስለጨበጠ ወይም ፖለቲከኛ ነኝ ስላለ ሳይሆን፣ የአንድን ህብረተሰብ ሁኔታ በደንብ የሚገነዘብና መተንተንም የሚችል ከሆነ ብቻ ምሁር ነው ሊያሰኘው ይችላል። ይሁንና በምሁራዊ ዓለም ውስጥ የርዕዮተ-ዓለምን ጉዳይ ወደ ጎን ትተን አንድን ነገር ሁለንታዊ በሆነና ክስተታዊ በሆነ መልክ የመረዳት ጉዳይ አለ። አብዛኛውን ጊዜ በፖለቲካ ውስጥ የሚሳተፉ ሰዎች ይህንን ዐይነቱን ግዙፍ ልዩነት ስለማይረዱ ዝም ብለው ብቻ ስለፖለቲካ ይዘባርቃሉ። ፖለቲካዊ ሁኔታን ከሁለንታዊና ከክስተታዊ አንፃር መረዳትና ተጨባጭ ሁኔታዎችን መተንተን እነሶክራተስና ፕላቶ ፍልስፋናን የፖለቲካ መመሪያ አድርገው ማስተማር ከጀመሩ ወዲህ ያለ ችግርና፣ በእነሱና በሶፊስቶች መሀከል የጦፈ ትግል የተካሄደበት ጉዳይ ነው። ዛሬም ያለና ብዙ አገሮችን የሚያወዛግብና እንዲፈረካከሱ ያደረጋቸውና፣ አንዳንዶች ደግሞ ፖለቲካን በተሳሳተ መልክ በመተርጎም እኛ ብቻ ነን የዓለምን ህዝብ ዕድል መወሰን ያለብን በማለት የበላይነታቸውን የሚያረጋግጡበት መሳሪያ ሊሆን በቅቷል። ስለሆነም ሶክራተስና ፕላቶ አንድን ነገር መረዳት የሚቻለው ከሁለንታዊ አንፃርና ከተጨባጭ ሁኔታዎች ባሻገር መሄድ የተቻለ እንደሆን ብቻ ነው ብለው ሲያስተምሩ፣ ሶፊስቶች ደግሞ በግልጽ ከሚታይ ወይም ከክስተት ብቻ በመነሳት ነው አንድን ነገር መረዳት የሚቻለው ብለው ያስተምሩ ነበር። በእነሶክራተስ ዕምነት ዕውነተኛ ነፃነት ሊገኝ የሚችለው ጥያቄን በመጠየቅና መልስም ለማግኘት በመጣርና በነገሮች መሀከል መተሳሰር ያለ መሆኑን ግንዛቤ ከተገባ ብቻ ነው። ለምሳሌ በአንድ አገር ውስጥ አንድ ሰው ተሽሮ በሌላ ሰው ወይም በአንድ ቡድን ቢተካ ይህ ማለት ግን ለውጥ ይመጣል ማለት አይደለም። ስለለውጥና ስለነፃነት ሲወራ ጠቅላላውን ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ ማስገባትና በአንድ ግለሰብ ወይም ድርጅት አማካይነት ብቻ ለውጥ ሊመጣ እንዳማይችል ቀድሞውኑ ግንዛቤ ሲገኝ ለነፃነት የሚደረገው ትግል የተቃና ሊሆን ይችላል። ይህም ማለት፣ ስለግለሰቡ ወይም ስለድርጅቱ ምሁራዊ ብቃትነት፣ የአተናተን ዘዴ፣ ስለቆመበት ህብረተሰብ የማቴሪያልና የስነ-ልቦና ሁኔታ፣ ስለመንግስት መኪና አወቃቀርና ስለልዩ ልዩ ተቋማት ብቃት፣ የውጭ ኃይሎች ስለሚኖራቸው አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ተፅዕኖ…ወዘተ. እነዚህና ሌሎች ነገሮች ግንዛቤ ውስጥ እስካልገቡ ድረስ አንድ ሰው ወይም አንድ ፓርቲ ብቻ ስልጣንን ስለጨበጠ መሰረታዊ ለውጥ ይመጣል ብሎ ማሰብ ትልቅ ስህተት ነው። ስለዚህም ስለፖለቲካ ሲወራ ጠቅላላውን ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ ማስገባትና መተንተን ያስፈልጋል። በሌላ ወገን ግን ሶፊስቶች የሚነሱት ከተናጠል ሁኔታ ብቻ ነው። በእነሱ አስተሳሰብ በነገሮች መሀከል መተሳሰርና አንደኛው በሌላኛው ላይ ተጽዕኖ አይኖረውም። ፍትሃዊ አገዛዝም ከጠንካራ መንግስት የሚመጣ ነው። ዕውነተኛ ዕውቀትን ከመፈለግ ይልቅ በእንካስላንቲሃ ላይ ያተኩራሉ። ዋና ዓላማቸው ዕውነተኛ ነፃነትን ማምጣት ሳይሆን እያስተማሩ ገንዘብ ማግኘት ብቻ ነበር። 

ይህ ዐይነቱ የፖለቲካ አስተሳሰብ በተለይም ከ17ኛው ክፍለ-ዘመን ወዲህ ግልጽ የሆነና በተለይም የሊበራል አስተሳሰብ በአሸናፊነት የወጣበትን ሁኔታ እንመለከታለን። በሊበራሎች ዕይታ እያንዳንዱ ሰው በራሱ ዓለም የሚከንፍና የራሱን ጥቅም የሚያሳድድ ብቻ ነው። በሊበራሎች አስተሳሰብ ህብረተሰብ ወይም ህዝብ፣ ወይም ደግሞ መደብ የሚባሉ ነገሮች የሉም። በእነሱ ቲዎሪ መሰረት አንድን ግለሰብ ብቻ በመውሰድ ነው ሳይንሳዊ ትንተና መስጠት የሚቻለው። ስለሆነም ታሪክና ባህል፣ ህብረተሰብአዊ እሴቶች ቦታ የላቸውም። ታሪክ ተያያዥነት እንዳለውና ያለፈው ሁኔታ በዛሬው ላይ ተፅዕኖ እንደሚኖረውና፣ በነገሮች መሀከል መተሳሰር እንዳለ በሊበራሎች ዘንድ ተቀባይነት የለውም። ሊበራሎች የመንግስትን ጣልቃ ገብነትን አጥብቀው ቢጠሉም፣ በሌላ ወገን ደግሞ የመንግስት ጣልቃ ገብነት በኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ ያለውን ሚና አይቀበሉም። ካለመርከንታሊዝም የኢኮኖሚ ፖሊሲ የአውሮፓ መንግስታት ጠንካራ ህብረ-ብሄርን(Nation-State) መገንባት እንደቻሉ አይገነዘቡም። በእነሱ ዕምነት ታሪክ የሚሰራው በእያንዳንዱ ግለሰብ አማካይነት የራስን ጥቅም በማሳደድ ብቻ ነው። ይሁንና ግን ይህንን ዐይነቱን በተለይም በእነሆበስና በእነ ጆን ሎክ የፈለቀውን አስተሳሰብ የሚቃወሙና ትክክልም እንዳይደለ ያስተማሩ የሊበራል አስተሳሰብ ያላቸው ሌሎች ፈላስፋዎችም ሆነ የኢኮኖሚ ጠቢባን እንዳሉ መታወቅ አለበት። በሳይንስና በፍልስፍና፣ እንዲሁም በድራማና በአርኪቴክቸር፣ በክላሲካል ሙዚቃ መቃኘት ግለሰቦች የማይናቅ የፈጠራ ስራ ሰርተዋል። ሳይንስና ፍልስፍና በግለሰቦች አማካይነት ብቻ ነው ሊፈጠሩና የኋላ ኋላ ሊዳብሩና ከየአገሮች አልፈው ዓለምን ለማዳረስ የበቁት። ለማንኛውም በእነዚህኛዎቹ ሊበራሎች አስተሳሰብ ባህል ወይም ትራዲሽን የሚባለውን ነገር እንዳለ ማስወገድ እንደማይቻልና አስፈላጊም እንዳልሆነ ያመለክታሉ። የሰው ልጅ ማቴሪያላዊ ወይም ለሰውነቱ መጎልመስ የሚያስብ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊም ስለሆነ ሁለቱን ሚዛናዊ በሆነ መልክ ጠብቆ መጓዝ እንዳለበትና ይህም ለማህበራዊ ስምምነት አስፈላጊ መሆኑን ያመለክታሉ።

ለማንኛውም ስለፖለቲካ በሚወራበት ጊዜ ፖለቲካ እንደሌሎች ዕውቀቶችም በየኢፖኩ የዳበረና እንደ ህብረተሰቦች አወቃቀር ልዩ ልዩ ትርጉም እየተሰጠው መምጣት እንደቻለ መገንዘብ እንችላለን። ለምሳሌ የአውሮፓው የሊበራልና የልዩ ልዩ ፖለቲካ አስተሳሳብ መዳበር ካለ ግሪክ የፖለቲካ ፍልስፍናና የታሪክ አተረጓገም ዘዴ ውጭ ሊታሰብ በፍጹም አይችልም። ለአውሮፓው የካፒታሊዝምና የሊበራል አስተሳሰብ ዕድገት መነሻው የግሪክ ስልጣኔና በእሱ ላይ የተመረኮዘው የተሃድሶ እንቅስቃሴ ነው። ከዚህም በላይ ካለ ሃይማኖት የጥገናዊ ለውጥ ወይም ሬፎርሜሽን የአውሮፓው ህዝብ ከጭፍን አስተሳሰብ በመላቀቅ እዚህ ደረጃ ላይ ባልደረሰ ነበር። በመቀጠልም የኢላይተንሜንት እንቅስቃሴ ባይኖር ኖሮ ዲስፖታዊ አገዛዞችን በመጣል ለካፒታሊዝምና ለሊበራል ዲሞክራሲ መሰረት መጣል ባልተቻለ ነበር። ይህ ባይሆን ኖር የተፈጥሮ ሳይንስና የኋላ ኋላ ደግሞ ማቴማቲክስና ቴክኖሎጂ ባልዳበሩና ዓለምን ባላዳረሱ ነበር። ይህ ዐይነቱ ሂደትና ዕድገት የግዴታ ከምሁራዊ እንቅስቃሴ ጋርና ከአዕምሮ መጎልመስ ጋር ይያዛሉ።  እንደማንኛውም ህይወት ያለው ነገር አዕምሮም ለመጎልመስና ነገሮችን ተረድቶ ትችታዊ ትንተና ለመስጠትና የሌላውን አስተያየት ለመቀበል የግዴታ ብዙ ደረጃዎችን ማለፍ አለበት። አንድ ፍሬ የሚሰጥ አትክልት ፍሪያማ ብቻ ሳይሆን ፍሬውም እንዲጣፍጥ ወይም ልዩ ጣዕም እንዲሰጥ ከተፈለገ በየጊዜው እንክብካቤ እንደሚደረግለት ሁሉ ጭንቅላትም ከአምባገነናዊና ከተንኮል ባህርይ ለመላቀቅ የግዴታ ከመጀመሪያውኑ በጥሩ ዕውቀት መኮትኮት አለበት። ለምን በግሪክ ቀጥሎም ደግሞ በአውሮፓ ምድር ፍልስፍና፣ ሳይንስና ማቲማቲክስ፣ ድራማና ሙዚቃ፣ አርከቴክቸርና ስዕል፣ እንዲሁም የፖለቲካ ቲዎሪ፣ ሶስዮሎጂና ልዩ ልዩ የኢኮኖሚ ቲዎሪዎች ለመፈጠርና ለመዳበር ቻሉ ብለን ጥያቄ በምናቀርብበት ጊዜ በትክክለኛው ጊዜ እነሶክራተስና ፕላቶን የመሳሰሉት ስለተፈጠሩና ከተፈጠሩም በኋላ ከትክክለኛው ዕውቀት ጋር በመገናኘታቸውና መመራመርም በመቻላቸው ነው። እንደሚባለው የግሪክ ህዝብ በከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ ውስጥ በሚገኝበት ጊዜ ከገባበት ውዥንብርና ትርምስ ለማላቀቅ ሲል እግዚአብሄር ሶክራተስን ከሰማይ አውርዶ የጣለው ነው ይባላል። እንደዚሁም የኢጣሊያን ህዝብ በከፍተኛ አደጋ ውስጥ በወደቀበት ጊዜና ህዝቡም የሚሰራውን በማያውቅበት ዘመን ዳንቴን የመሰለ በመፈጠርና የአምላኮች ኮሜዲ የሚባለውን መጽሀፍ በመድረስ ለተከታታዩ ትውልድ መመሪያ እንዲሆን ለማድረግ በቅቷል። ከዚያ በኋላ አዳዲስ የተገለጸላቸው ምሁራን በመፈጠር ሬናሳንስ ወይም የግሪክ ስልጣኔን ከተኛበት በመቀስቀስ ዕውነተኛ ነፃነትን ለማወጅ ቻሉ።  ከእንግዲህ ወዲያ መመሪያው ፍልስፍና፣ ሳይንስና ጥበብ፣ አርክቴክቸርና ድራማ ናቸው በማለት አዲስ የስልጣኔ ፈለግ ቀየሱ። ከዚያም በኋላ ሪፎርሜሽንና ኢንላይተንሜንት የሚባሉት ምሁራዊ እንቅስቃሴዎች በመፍለቅና በመዳበር ለካፒታሊዝም፣ ለሊበራሊዝምና ለዲሞክራሲ መንገዱን አመቻቹ። ጊዜው በጭፍን የሚታመንበት ሳይሆን የአርቆ-አስተዋይነት ዘመን(The Age of Reason) ነው በመባልና ተቀባይነት በማግኘት አፋኝና ጨቋኝ አስተሳሰቦችን ቀስ በቀስ ማስወገድ ተቻለ። በዚህ መልክ የአወሮፓ ህዝብ የአስተሳሰብ አድማስ በመስፋት ፈጠራዊ ስራዎች መዳበር ቻሉ።

በእኛ አገር ያለው ትልቁ ችግር ከልጅነት ጀምሮ ጭንቅላት በትክክለኛ ዕውቀት መኮትኮት እንዳለበት ግንዛቤ አለመኖሩ ነው። በአብዛኛዎቻችን ዕምነት ማንኛውም ዶክተር የሚባል ነገር የለጠፈ ሁሉ በደንብ ማሰብ የሚችልና ምሁራዊ ግንዛቤውም ከፍተኛ የሆነ የሚመስላቸው አሉ። አንድ ሰው ዶክትሬቱን የሚሰራው በአንድ አርዕስት ላይ ተመርኩዞ ስለሆነ የሚያገኘውም ዕውቀት በዚያ ዙሪያ የሚሽከረከር ብቻ ነው። ወደ ፍልስፍና ሶስዮሎጂ ዓለም ስንመጣ ግን የተያያዙ ስለሆና የዕውቀትም መሰረቶች ስለሆኑ፣ አንድ በፍልስፍና የስለጠነ ምሁር በቀላሉ ብዙ ነገሮችን መመልከትና የሚያመረቃ ትንተና መሰጠት ይችላል። ለምሳሌ የመጀመሪያዎቹ የተፈጥሮ ሳይንስ ተመራማሪዎችን ስንመለከት ከፍልስፍና በመነሳትና በፍልስፍና አማካይነት ብቻ ነው የተፈጥሮ ሳይንስንና ማቲማቲክስን ማፍለቅና ማዳበር የቻሉት። ስለሆነም ፍስልፍናን መሰረት ያደረገ ዕውቀትና የፖለቲካ ትግል በፍጹም ወደ ብጥብጥና ጭቅጭቅ አያመራም። ጭንቅላት ከመጀመሪያውኑ በትክክለኛው ዕውቀት የተኮተኮተ ስለሆነ ስራው ሁሉ አርቆ-አስተዋይነትን ወይም አሳቢነትንና ሚዛናዊነትን ያካተተ ስለሚሆን ከአመጽና ሰውን ከመጉዳት ይቆጠባል።

በእኛ አገር የመጀመሪያው ዙር ታጋይ የፖለቲካ ትግል ሲጀምር መሰረቱን ፍልስፍናና የተፈጥሮ ሳይንስን ባለማድረጉ ነገሮችን በጥቁርና በነጭ በመሳል ወደ አመጽ ለማምራት ተገዷል። ፍልስፍናዊ ዕውቀት የሌለው ወይም ደግሞ ተምሮ በደንብ ያልገባው ከሆነ ስለነፃነት ያለው አስተሳሰብ የተወላገደ ይሆናል ማለት ነው። ትግል ብሎም ሲጀምር የግዴታ ትግሉን ከጠብመንጃ ጋር በማያያዝ አስተሳሰቡ እንዳለ በአመጽ መንፈስ እንዲቀረጽ በማድርግ ተከታዮቹንም ይመርዛል።  ፍልስፍናን መሰረትን ያላደረገ ትግል ስልጣኔን ለማምጣት ሳይሆን ስልጣንን ለመጨበጥ ብቻ የሚደረግ ትግል ስለሚሆን የመጨረሻ መጨረሻ ወደ እርስ በእርስ መበላላት ሊያመራን ችሏል። በጥቂት ዐመታት አንድ ምሁራዊ ትውልድ እንዳለ እንዲሟጠጥ ለማድረግ በቅቷል። በጨቅላ አዕምሮ የተጀመረና የተካሄደ ትግል ታሪክንና ባህልን በማበላሸት ለወያኔ መነሻና ስልጣንን ይዞ አገርን እንዲያተረማምስ መሰረቱን እንደጣለለት ይታወቃል። በመሰረቱ በአብዮቱ ወቅት በአፍላው ካልሆነ በሰተቀር የተካሄደው ትግል በምንም መልኩ ፖለቲካ የሚያሰኘው ምንም ነገር አልነበረም። ወቅቱ የንዑስ ከበርቴውን ዕውነተኛ ባህርይዉን ያሳየበት ጊዜ ነበር። ከአውሬም በላይ አልፎ በመሄድ አንድን ሰው ብቻ በመግደል የሚደሰትና አርፎ የሚቀመጥ ሳይሆን ጠላቴ ነው ብሎ የገመተውን በሙሉ እስካልደመሰሰ ድረስ የመንፈስ እርካታን ለማግኘት እንደማይችል አረጋግጧል። በተለይም በቅርቡ ሁለት ተከታታይ ቃለ-መጠይቆችን፣ አንደኛው በአራት ክፍል የተከፈለ፣ ሁለተኛው ደግሞ በሁለት ክፍል የተከፈለውን ካዳመጥኩኝ በኋላ በጊዜው የቱን ያህል ወንጀል እንደተፈጸመ፣ በተለይም ፖለቲከኛ ነኝ የሚለው ከተማሪው እንቅስቃሴ የወጣው አንድ ኃይል የቱን ያህል በደመ-ነፍስ እየተመራ ለወንድማማቾችና እህትማማቾች መገዳደል መንገዱን እንዳመቻቸና ዛሬ ለደረስንበት አሳፋሪ የታሪክ ምዕራፍ ከፍተኛውን አስተዋፅዖ እንዳበረከተ ለመገንዘብ ችያለሁ። ከድርጅቱ ውስጥ በወጡና የአመራር ቦታም በነበራቸው ግለሰቦች የተደረሱት መጽሀፎችም ይህንን ያረጋግጣሉ። ለማንኛውም የመጀመሪያውና በአራት ክፍል የተከፈለው ወይዘሮ መዐዛ ከኢንጂነር ካሳ ገብሬ ጋር ያደረገችው ቆንጆ ቃለ-መጠይቅና መልስ ነበር። ቃለ-መጠይቁም ሆነ መልሱም የሚያረካና፣ ኢንጂነር ካሳ ገብሬም ከሙያቸው አንፃርና በጊዜው በዚያ ትርምስ ወቅት የቱን ያህል የአገር ግንባታ ስራ ይሰራ እንደነበር በጥሩ አማርኛና ለዛ ባለው አመላለስ ብዙ ነገር አስተምረውናል። ይህንን ካዳመጥኩኝ በኋላ እታገላለሁ የሚለው ኃይል ምኑ ላይ እንደታገለና ለአገር ግንባታም ያበረከተውን አስተዋፅዖ ብፈልግ ማግኘት አልቻልኩም። መግደልንና አገርን ማተረማመስ፣ እንዲሁም ለውጭ ኃይል መስራትን እንደ ትግል የምንቆጥር ከሆነ አዲስ የፖለቲካ ቲዎሪ መጻፍ አለበት  ማለት ነው። እንደዚህ ስል ግን ደርግ በራሱ ወንጀል አልፈጸመም ማለቴ አይደለም።  ከተማሪው እንስቃሴ ውስጥ ብቅ ያለው አንድ የተወሰነ ኃይል ቀድሞ የተደራጀ ድርጅችን ለራሱ በመጠቅለልና መስራቾቹን በማስወገድ ለተቀደሰ ዓላማ የተመሰረተውን ድርጅት ወደ ማይሆን አቅጣጫ እንዲያመራው ለማድረግ እንደበቃ ከሁለተኛው የቃለ-መጠይቅ ምልልስና ከሌሎችም ስለአብዮቱ ከተጻፉ መጽሀፎች በቂ ትምህርት ለመቅሰም ችያለሁ። 

 ሁለተኛው ቃለ-መጠይቅ ደግሞ የአስራት ቴሌቬዥን በደርግ አገዛዝ ዘመን በመረጃ ደህነነት የህግ መመሪያ ክፍል ኃላፊነት ከነበሩት ከሻምበል ተስፋዬ ርስቴ ጋር ያደረገው ቃለ-መጠይቅና መልስ ነው። በእሳቸው አገላለጽ በእነ ሰናይ ልኬና በሻምበል ዳንኤል፣ እንዲሁም በእነ ሲሳይና ከውጭ ሆኖ በሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ይሸረብ የነበረውን ተንኮል ስሰማ እነዚህ ሰዎች በምን ዐይነት የፖለቲካ ፍስልፍናና ቲዎሪ ቢሰለጥኑ ነው እንደዚህ ዐይነቱ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የበቁት ብዬ እራሴን ስጠይቅ ለዚህ የሚሆነኝ በቂ መልስ ለማግኘት በፍጹም አልቻልኩም። በእነሱ ስሌት በዚያን ጊዜ የማይፈልጓቸውንና ምሁራን ናቸው የሚሏቸውን በሙሉ መደምሰስና፣ እነሱ በሚፈልጉት መልክ ብቻ ፖለቲካ የሚሉትን ነገር ተግባራዊ ማድረግ ነበር። እስቲ ቆም ብለን እናስብ! ተማሩ የሚባሉ ወይም ምሁራን እንዳሉ ከተደመሰሱ በኋላ ምን ዐይነት አገር ነው መገንባት የሚቻለው? ለማንኛውም በእኔ ዕምነት ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብና ድርጊት ፋሽሽታዊ ነው ብሎ መደምደም ይቻላል። የታሪክን ጠመዝማዛ ጉዞ፣ ባህልን፣ ከብዙ መቶ ዐመታት በኋላ ቀስ በቀስ በአንድ ህዝብ መሀከል እየዳበረ የመጣውንና በብዙ መልኮች የሚገለጸውን ግኑኝነት፣ በተለይም በፖለቲካው መስክ የነበረውን ንቃተ-ህሊና፣ በአካባቢውና በተቀረው ዓለም የሚሸረብብንን ተንኮል ያላገናዘበ በፖለቲካ ቲዎሪና ፍልስፍና ሊደገፍ የማይችል አገር አፍራሽ አካሄድ ነው ብሎ መደምደም ይቻላል። ለዚህ ዐይነቱ በደመ-ነፍስ መመራት ዋናው ምክንያት ጭንቅላት በደንብ ተኮትኩቶ ስላላደገና ስላልዳበረ ብቻ ነው። በደንብ ያልተኮተኮተ ጭንቅላት ደግሞ አንድን ህብረተሰብ ከተለያዩ አንፃሮች አኳያ ማንበብና መተንተን አይችልም። ጥያቄ ለመጠየቅና መልስም ለመፈለግ የሚችል አይደለም። ዝም ብሎ በደመ-ነፍስ በመመራት ዓላማው ወደ ማይታወቅ ሁኔታ ውስጥ መጋለብ ነው። ይቀጥላል!!          

                                                      fekadubekele@ gmx.de

                     www.fekadubekele.com

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here