spot_img
Monday, May 29, 2023
Homeነፃ አስተያየትለመሆኑ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ምንድነው?

ለመሆኑ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ምንድነው?

- Advertisement -
Samuel Tibebe Ferenji

ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ 
ሃምሌ 12 ቀን 2012 (07/19/2020)

ኢትዮጵያን አትንኩ ነው! ኢትዮጵያን መንካት ዋጋ ያስከፍላል! ቀድሞ ጊዜ ጥሪ አሳልፈናል፤ አሁን የሚታየው ግን በዚህ እድሜዬ በእጅጉ ያሳስበኛል” የቀድሞ የሜጫና ቱለማ ሊቀመንበር ሻምበል ለማ ጉያ።

በታሪክ ውስጥ በአንድም ወቅት፤ የኦሮሞ ሕዝብ ወክሉኝ ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆኑ ግለሰቦች የሉም፤ በስሙ የሚነግዱት እና በስሙ ጥፋት የሚፈጽሙት ራሳቸውን የሾሙ “ተወካዮች”፤ የራሳቸውን እና የተወሰኑ ግለስቦችን ጥቅም ከማስጠበቅ ውጭ፤ ለኦሮሞ ሕዝብ የሚበጅ ምንም ሕልም የላቸውም። የኦሮምን ሕዝብ “እንወክለሃለን” ብለው የሚፈነጩ ሁሉ፤ ስለኦሮሞ ሕዝብ ደንታ የሌላቸው፤ ግፈኞች ለመሆናቸው፤ ከተግባራቸው በላይ የሚመሰክር የለም። ማነው የኦሮሞን ሕዝብ ምን ትፈልጋለህ ብሎ ጠይቆት የሚያውቅ? መቼ ነው የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄዬ ይሄ ነው እና፤ ጥያቄዬን ለሚመለከተው ክፍል አቅርቡልኝ ያለው? ለመሆኑ ለኦሮሞ ሕዝብ ምጣኔ ሃብት መቀጨጭ እና በሃገሩ የፖለቲካ ጉዳይ ላይ በነፃነት እንዳይሳተፍ እንቅፋት የሆነው ማን ነው? በእርግጠኝነት መናገር የምችለው፤ ለኦሮሞ ሕዝብ ዋናው ጠላቱ፤ እናውቅልሃለን የሚሉ “እንጭጭ ምሁሮች” እና የምሁርነት ጭንብል የለበሱ ደናቁርት ናቸው። ለመሆኑ፤ እነዚህ ስለ ኦሮሞ ሕዝብ ተቆርቋሪ ነን የሚሉ ጎጠኞች፤ የኦሮሞን ሕዝብ በቅጡ ያውቁታል? ድርጊታቸው የሚያሳብቀው፤ ስለኦሮሞ ሕዝብ ምንም እንደማያውቁ ነው፡፡ በስሙ ይገላሉ፤ ያስገድላሉ፤ ይዘርፋሉ፤ ያዘርፋሉ፤ ንብረት ያስወድማሉ፤ በአንድም ወቅት ግን፤ የኦሮሞን ሕዝብ ባሕል እና ወግ እንዲሁም፤ የሞራል እሴት አንጸባርቀው አያውቁም፡፡ ኦሮሞው አያቴ በግዛታቸው፤ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የገነቡ፤ በነበራቸው ልምድ፤ በግዛታቸው የመሰረተ ልማት የዘረጉ፤ ነበሩ፡፡ ልጆቻቸው “ከዘራቸው” ውጪ ሲጋቡ፤ የልጆቻቸውን የትዳር አጋሮች፤ አቅፈው እና ደግፈው፤ ከቡና መሬታቸው መሬት ሰጥተው፤ ከተለያየ ብሔር ማህበረሰብ ጋር በሰላም እና በፍቅር የኖሩ ናቸው፡፡ አያቴ፤ ልጆቻቸውን ክርስትና “የያዙላቸው” ኦሮሞ የሆኑ ብቻ አልነበሩም፡፡ ለኢትዮጵያ አንድነት፤ ከጣልያን ጋር ተዋግተዋል፤ ለዚህም የቀኛዝማችነት ማእረግ አግኝተዋል፡፡ አያቴ ኢትዮጵያዊነት እና ኦሮሞነት አንድም ወቅት ተጋጭቶባቸው አያውቁም። አባቴም፤ የወረሰው ይህንኑ ነው፡፡ ኦሮሞን እንወክላለን የሚሉ ጽንፈኞች፤ አያቴንም ሆነ አባቴን፤ አጎቴንም ሆነ አክስቶቼን፤ አንድም ቀን ምንድነው የምትፍልጉት፤ ጥያቄያችሁ ምንድነው ብሎ የጠየቃቸው የለም፡፡ ዛሬም በተለያየ የኢትዮጵያ ክፍል የሚኖሩ የቅርበ እና የሩቅ ኦሮሞ ዘመዶቼንም ሆነ ወንድሞቼን፤  ጥያቄያችሁ ምንድነው ያላቸው የለም፡፡ ‘እኛ እናውቅላችኋለን፤’ የሚሉ ደናቁርት፤ በማያውቁት ነገር “ጥያቄያችሁ ይህ ነው” ብለው በራሳቸው ፍላጎት እና የከሸፈ መስመር ሕዝቡን ወደማይፈልገው አቅጣጫ ሂድ ሲሉ ዓመታት አስቆጠሩ፤ ስንት ሰው አስገደሉ፤ እምቢ አትወክሉኝም የሚላቸውን፤ “አንተ ኦሮሞ አይደለህም” የሚል ታርጋ እየለጠፉ፤ በጀሌነት የሚከተላቸውን የአሞራ እራት ያደርጋሉ። ለመሆኑ ጽንፈኛ ሃይሉ፤ ኦሮሞነትን ለመደልደል ሥልጣን የሰጠው ማን ነው?

በየትም ሃገር፤ የሕዝቡን ጥያቄ የሚያነሳው፤ ከሕዝቡ ውስጥ የተሻለ ንቃት ያለው፤ የኅብረትሰብ ክፍል ነው። ይህ የነቃ የኅብረተሰብ ክፍል ግን፤ ከህዝቡ ጋር የሚኖር፤ የሕዝቡን ደስታ እና ሃዘን አብሮ የሚጋራ፤ ፈተናዎቹን እና ድሎቹን፤ አብሮ የቀመሰ፤ የሕዝቡን ፍላጎት በቅጡ የተገነዘበ የሕብረተሰብ አካል ነው። ይህ የነቃ የኅብረተሰብ ክፍል፤ ከራሱ ፍላጎት እና ጥቅም ይልቅ፤ የሚኖርበትን ማኅበረሰብ ጥቅምና ፍላጎት የሚያስቀድም፤ መሰረታዊ ጥያቄውም የሕዝቡን መሰረታዊ መብት የሚያስጠብቅ፤ የኢኮኖሚ፤ የማህበራዊ ሕይወት፤ እና የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲጎለብት የሚያደርግ ነው። የኦሮሞ ጽንፈኞች ግን፤ አውሮፓ እና አሜሪካ ተቀምጠው፤ ስለማያውቁት ሃገር ስለማያውቁት ሕዝብ የራሳቸውን ፍላጎት እና ጥቅም ለማስጠበቅ ብቻ ተግተው የሚሰሩ ናቸው። ብዙዎቹ፤ ለዓመታት ከሃገራቸው ርቀው የቆዩ፤ ከጓደኞቻችው ጋር በሚያደርጉት ብሽሽቅ ቂም ቋጥረው፤ እነሱን መሰል ጽንፈኛ ሥልጣን ይዞ፤ ጠላት ብለው የፈረጁትን የፖለቲካ ሃይል እንዲበቀልላቸው የሚፈልጉ ናቸው። ስለሕዝቡ ደንታ ቢኖራቸው፤ ነጋ ጠባ፤ አጀንዳቸው ምኒሊክ ባልሆኑ ነበር። እነሱ፤ የተለያየ ቀለም፤ የተለያየ ዜግነት፤ የተለያየ ባሕል እና እሴት ካለው ሕዝብ ጋር በሰለጠነው ሃገር፤ ከሃገራቸው ውጭ በሰላም ይኖራሉ፤ እነሱ ግን፤ የእኔ ከሚሉት “የትውልድ” መንደራቸው፤ ተዋልዶ እና ተጋምዶ በኖረው ሕዝብ መሃከል፤ እሳት እየጫሩ፤ በሃገር ውስጥ የሚኖረውን ሰላማዊ ዜጋ እንዲፈናቀል እና እንዲገደል፤ ለጀሌያቸው የውሻ ፊሽካቸውን ይነፋሉ። በሰለጠነ ሃገር እየኖሩ፤ ሥልጣኔ የሚባል ነገር፤ በውስጣቸው ዘልቆ ሊገባ ያልቻለ፤ ዲግሪ ከመቁጠር ባሻገር፤ ዕውቅት እና ብልህነት የሚባል ነገር ያልተካኑ፤ አዕምሯቸው በጥላቻ እና በዘረኝነት ድር የተተበተበ፤ የሞት መላእክተኞች፤ ምንም እንኳን በ21ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ ቢኖሩም፤ ራዕያቸው፤ ገና ከ11ኛው ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ ዘልቆ ያልወጣ ነው። ሕዝቡ እጅግ ቀድሟቸው ሄድዋል፤ በሕዝቡ ውስጥ ስለማይኖሩ፤ የሕዝቡን የሞራል እሴት አያውቁትም፤ በሰለጠነ ሃገር ስለሚኖሩ ብቻ፤ የሰለጠኑ የሚመስላቸው፤ የአስተሳሰብ ድንኮች ናቸው። ገሚሶቹ፤ በራሳቸው የኑሮ ፈተና የወደቁ፤ ይህ ነው የሚባል ስኬት የሌላቸው፤ በመሆናቸው ውስጣቸው ሰላም የለውም። ውስጡ ሰላም የሌለው ሰው፤ ለሌላ ሰላም አይሰጥም። እሱ በሕይወቱ ስለወደቀ፤ የሌላውን ስኬት አይፈልግም። የራሱን ሕይወት ማሸነፍ ስላልቻለ፤ ያለው ምርጫ በሕዝብ ሰም መነገድ ነው። የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ምን እንደሆነ አያውቅም። ግን ለኦሮሞ ሕዝብ ተቆርቋሪ ነኝ ይላል። የኦሮሞ ሕዝብ ፍላጎቱ ከተቀረው ወንድም እና እህት ሕዝብ ጋር፤ በእኩልነት እና፤ በሰላም መኖር ነው። ለዚህም ነው ሃገሩን ለመገንባት ሌት ተቀን የሚደክመው። የጥፋት ሃይሎች ግን፤ እንዲያድግ አይፈልጉም፤ ሰላም እንዲኖረው አይፈልጉም፤ ምክንያቱም፤ ስላም ካለ፤ የሕዝቡ ኑሮ ከተሻሻለ፤ መብቱ ተጠብቆ ከኖረ፤ ጽንፈኞቹ የለበሱት፤ የሃሰት ጭምብል ይገፈፋል፤ የተደበቁበት ጨለማ፤ በብርሃን ይሞላል፤ ያኔ መደበቅያ አይኖራቸውም፤ ያኔ፤ በምስኪኑ ወጣት ኦሮሞ ሬሳ መነገድ ይቆማል፤ ያኔ የገቢ ምንጫቸው ይደርቃል። ለዚህም ነው ትርምሱን የሚፈልጉት። ለዚህም ነው መሰረት ልማት እንዲወድም ሌተ ተቀን ተግተው የሚሰሩት፤ በሕዝቡ መሃል የሚኖረው የኦሮሞ አንቂ፤ የሕዝቡን ኑሮ የሚኖረው የኦሮሞው ልሂቅ፤ በሰላማዊ የፖለቲካ መስመር ዛሬም ለኦሮሞ ሕዝብ የኑሮ እድገት፤ ሰላም፤ እና እኩልነት ተግቶ ይሰራል። ይህ ሕዝቡን በደንብ የሚያውቅ፤ ከራሱ በላይ ለሕዝብ የቆመ፤ ለሕዝቡ ጥቅምና ፍላጎት ቅድሚያ የሚሰጥ፤ እውነተኛ የሕዝብ ልጅ ነው። እነዚህን እወነተኛ የኦሮሞ ሕዝብን ልጆች፤ በእነ ጃጋማ ኬሎ፤ በእነ ለማ ጉያ፤ በእነ አብዲሳ አጋ ውስጥ እና በቀደምት አባቶቻቸው ውስጥ አይተናል።  የኦሮሞ ጽንፈኛ፤ በንጹሃን ደም ተንሳፎ፤ ወደ ስልጣን ክርቻ ከመምጣት ውጭ የተለየ ዓላማና ፍላጎት እንደሌለው ሥራው ያሳብቅበታል።

አብዛኛው ኦሮሞ የሻምበል ለማ ጉያን ዓይነት አስተሳሰብ ነው ያለው፤ አዎ እሳቸው እንዳሉት “ኢትዮጵያን አትንኩ ነው! ኢትዮጵያን መንካት ዋጋ ያስከፍላል!” ኢትዮጵያ እንደ ሃገር እንድትቀጥል፤ ብዙ መስዋዕትነት የከፈሉ ኦሮሞዎችን እነዚህ ጽንፈኞች አይወክሉም፤ እነ አባጅፋር፤ ኩምሳ ሞረዳ፤ ጎበና ዳጬ፤ አብዲሳ አጋ፤ ጃጋማ ኬሎ፤ አሰፋ አያና፤ ወዘተ፤ ለኢትዮጵያ አንድነት እና ሏአላዊነት የከፈሉት መስዋዕትነት፤ አሰትሳሰባቸው በባእዳን ትርከት በተጨናገፍ፤ እኩይ ጽንፈኛ ኦሮሞዎች አዕምሮ የሚመዘን አይደለም። ዓፄ ምኒሊክም እኮ፤ የኦሮሞ ደም አለባቸው፤ እነ እራስ መኮንን፤ በከፊል ኦሮሞ ናቸው፤ ዓፄ ኃይለስላሴም፤ የአማራ፤ ኦሮሞ እና ጉራጌ ቤተስብ ልጅ ናቸው። የሚኒሊክ ሚስት ኦሮሞ መሆናቸውን የማያውቅ፤ የምሁር ደንቆሮ፤ ‘ዓፄ ምንሊክ ለአማራ ነው ወይስ ለኦሮሞ የሚቀርቡት ተብሎ ሲጠየቅ፤ “እኔ ምኒሊክን አላቃቸውም” የሚል መልስ የሚሰጡን ሰዎች ናቸው፤ ስለኦሮሞ ሕዝብ መብት እንከራከራለን የሚሉን። የምኒሊክ አብዛኞቹ አማካሪዎች ኦሮሞዎች እንደነበሩ የታሪክ ምሁሩ  ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ በሰፊው ጽፈውታል። የተችገርነው እኮ፤ በራሪ ወረቅተ እያነበበ እራሱን የታሪክ ምሁር አድርጎ በማቅረብ፤ በማያውቀው ነገር የሚንበጫረቅ “አክቲቪስት በመብዛቱ” ነው። እንዲህ ዓይነት ሰዎች ናቸው ኢትዮጵያን ማሳነስ የሚፈልጉት። የኢትዮጵያ ትልቅነት የቆመው፤ እና ወደፊትም የሚቀጥለው፤ በሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ደምና አጥንት ነው። ይህን በጽናት የተገመደን፤ የብረት ድር፤ ማንም ሊበጥሰው አይችልም። የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ የተለየ አይደለም። ሕዝቡ የሚፈልገው፤ ንፁሕ ወኃ መጠጣት፤ መሰረተ ልማት እንዲገንባለት፤ በሕግ ፊት ከሁሉ ጋር እኩል እንዲሆን፤ ቋንቋውን፤ ባህሉን እና እሴቱን እንዲያዳብር፤ ሰብዓዊ መብቱ እና ነፃነቱም እንዲከበር ነው። ይህ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ፍላጎት ነው። የኦሮሞ ሕዝብ አለተበደለም ብሎ መከራከር አይቻልም፤ ግን መሰረታዊ ጥያቄው፤ የኦሮሞ ሕዝብ ከሌላው ወንድም እና እህት ሕዝብ የተለየ በደል እና ጥቃት ደርሶበታል ወይ ነው። ያማያወላዳ መልሱ ከሌላው የተለየ በደል አልደረስበትም የሚል ነው። አንፊሎ ያለ ገበሬ፤ መንዝ ካለ ገበሬ፤ ወይም ሶዶ ውስጥም ሆነ ማንኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ ካለ ገበሬ የተለየ ኑሮ የለውም፤ አልነበረውም። ከተሜውም ቢሆን፤ እንደውም የኦሮሞው “ልሂቅ” ከሌላው ከ75 በላይ ከሆነው ብሔር ብሔረስብ ልሂቅ የተሻለ እድል ነበረው፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ እድሉም፤ እጣውም ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተለየ አይደለም፡፡

ስለኦሮሞ ሕዝብ እንቆረቆራለን የሚሉ ጽንፈኞች፤ ለኦሮሞ ሕዝብ ቢያስቡ ኖሮ፤ ገንዘብ እና ጉልበታቸውን ለግጭትና ለጥፋት ከማዋል፤ የተለያዩ የኦሮሞ አካባቢዎች፤ የውኃ ጉድጓድ ባስቆፈሩ ነበር፤ ሌላው ቢቀር፤ ገበሬው በሞፈርና ቀንበር መሬት ከመግፋት የሚላቀቅበትን ሁኔታ ባመቻቹለት ነበር፡፡ እነሱ ግን የሚፈልጉት፤ የኦሮሞን ሕዝብ፤ በተለይ ወጣቱ፤ በድህነት እንዲኖር፤ በትምህርት እንዳይጎለብት፤ እና ተስፋ ቢስ እንዲሆን ነው፡፡ ምክንያቱም፤ ከተማረ፤ ከድህነት ከወጣ እና ተስፋ ካገኘ፤ በምንም መልኩ የእነዚህ ጉግ ማንጉጎች መሳሪያ አይሆንም፡፡ ስንቶቻችሁ ናችሁ፤ በተለያዩ የኦሮምያ ከተማዎች ዱላ እና ቆንጨራ ይዘው የወጡትን ወጣቶች ፎቶዎች በትኩረት ያያችሁ? ማናቸው ናቸው ጥላቻን እና ግጭትን የሚሰብኩ ጽንፈኞችን የሚመስሉት? ግደል ሲባል ለመግደል የሚወጣው ወጣት፤ የረባ መጫምያና ልብስ እንኳን የለውም፡፡ ይህንን የድሃ ልጅ፤ ይህንን የገበሬ ልጅ ነው ፊት ለፊት አጋፍጠው፤ በሞቱት ወጣቶች ስም ገንዘብ እየለመኑ አሜሪካና አውሮፓ የደላ ኑሯቸውን የሚኖሩት፡፡ የትኛው የኦሮሞ ሕዝብ ተቆርቋሪ ነኝ የሚል “አክቲቪስት ነው” የኦሮሞ ሕዝብ ከሶማሌ ሲፈናቀል፤ አንድ የውሃ ኮዳ እንኳን ያቀበለ? መቼ ነው በነዚህ ጽንፈኞች፤ ስለሆስፒታል፤ መንገድ፤ እና ትምህርት ቤት ግንባታ፤ ንፁህ ወኃ አቅርቦትን ስለማሻሻል ውይይት ሲደረግ ያየነው? ዛሬም ትላንትም፤ እኛው የፈረደባቸው ምኒሊክ እና “ነፍጠኛ” የሚሉት ኅብረተሰብ ላይ ነው ትኩረታቸው፡፡ ስለ ዓፄ ምኒሊክ “ወራሪነት” ሊነግሩን የሚሞክሩ ጽንፈኞች፤ ምነው ስለበከሬ ጎደና የአርሲና የጂማ ወረራ አይነግሩን? የሌቃ ነቀምት ንጉሥ የነበሩት በከሬ እኮ፤ የሰላም ችቦ እየተከሉ አልነበረም፤ ግዛታቸውን አስፋፍተው፤ የቤኒሻንጉልን እና ጉሙዝን መሬት የነጠቁት፤ አርሲን እና ጂማን የወረሩት፡፡ ምኒሊክም ይሁን የተለያዩ የኦሮሞ ሞቲዎች የሰሩት ሥራ፤ በ21ኛው ክፍለ ዘመን መነጽር እየታዩ እኮ አይደለም መመዘን ያለባቸው፡፡ እነሱ ምን ዓይነት የትምህርት ደረጃ ላይ ነበሩ፤ የወቅቱስ የኅብረተሰብ እድገት እምን ደረጃ ላይ ነበር ብሎ እኮ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ የኦሮምን ሕዝብ እድገት የምታረጋግጠው፤ ዛሬ ስለሚኒሊክ በማውራት ነው ወይስ፤ ከሞፈሩና ቀንበሩ ሊላቀቅ የሚችልበትን መንገድ ስትተልም?    

በተለይ አሁን የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ አልተመለሰም እያሉ የሚፈነጩብን ጽንፈኞች፤ ያልተመለሰው የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ምን እንደሆነ እንኳን አይነግሩንም፡፡ ዛሬ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ፤ አብዛኛው ቁልፍ የሆነው የመንግሥት ሥልጣን በኦሮሞ ቁጥጥር ስር ሆኖ፤ ይቅርታ ይደረግልኝና፤ አብዛኛው የመንግስት መስሪያ ቤት ጠረኑ “ኦሮሞ፤ ኦሮሞ” ይላል እየተባለ በሚነገርበት በዚህ ጊዜ፤ የኦሮምያ ክልል ተብሎ፤ መልክአ ምድር ተበጅቶለት፤ የኦሮሞ ፖለቲከኞች “ኦሮምያን” በሚያስተዳድሩበት ዘመን፤ ሕዝቡ ፈልጎና ወዶ የሚመርጣቸው መሪዎቹን ዲሞክራሲያዊ እና ነፃ በሆነ ምርጫ እንዲመርጥ ሁኔታዎች እየተመቻቹ ባሉበት ወቅት፤ ለኦሮሞ ሕዝብ ድምፅ ነን ያሉ እንደ አሸን የፈሉ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ በሃገር ገብተው በሚንቀሳቀሱባት ኢትዮጵያ፤ የኦሮሞ ጥያቄ አልተመለሰም ማለት ምን ማለት ነው? ያልተስማማህ የፖለቲካን ሂደት፤ በሰላማዊ መንግድ ቀይር ስትባል፤ ፖሊሲ ነድፈህ የመንቀስቀስ አቅም እንደሌለህ ስለምታውቅ፤ በነውጥ ሥልጣን ለመያዝ እና፤ ሕዝቡን እረግጠህ ለመግዛት፤ በሃገር ውስጥ የሞት ድግስ ትደግሳለህ፡፡ አዎ፤ ሙሾ ከማውረድ ባለፈ አቅም የለህም። በሕዝብ እየነገድክ፤ የሕዝብ ልጆችን ታስገድላለህ። “የእናንተን የኦሮሞ ነፃነት ጥያቄ” ትላንት በኤርትራ እና በትግራይ ሕዝብ አይተነዋል። የኤርትራ ህዝብ ለ30 ዓመታት ተነገደበት እንጂ፤ የተባለለትን ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር አላገኘም፤ ዛሬም የኤርትራ ሕዝብ፤ ነፃነቱን ይጠብቃል፡፡ ሕወኃት፤ ከ17 ኣመታት በላይ የነገድበት የትግራይ ሕዝብ፤ ዛሬም መሰራታዊ መብቱን ተነፍጎ፤ “ነፃ እናወጣሃለን ባሉት ሃሳዊ መሲሃን” ልጆቹ እየተረገጠ ነው፡፡ ስለኦሮሞ “ነፃነት” የሚሰብኩን እነዚህ የአስተሳሰብ ድኩማኖች፤ ለኦሮሞ ሕዝብ ከዚህ የተለየ ድግስ አልደገሱለትም፡፡ ለኦሮሞ ዘመዶቼ፤ ወንድምና እህቶቼ የምነግረው፤ ይህ ታሪካዊ ዕድል እንዳይጨናገፍብን፤ ጽንፈኞችን እምቢ እንድትሉ ነው፡፡ በራሳችን ፍላጎት እና ፈቃድ፤ የምንፈልገው የፖለቲካ ሃይል እንዲያስተዳድረን ፈቅደን የምንመርጥበት ጊዜ እሩቅ አይደለም፡፡ ከዚህ ውጪ፤ ሥልጣን ለመያዝ የሚፈልጉ ሃይሎች፤ ረግጠው ሊገዙህ እንጂ፤ በፈቃድህ ሊያስተዳድሩህ እንዳልሆነ ተረዳ፡፡ የሃገሬ ወጣቶች፤ ያላችሁን የሃሳብ ልዩነትም ሆነ ተቃውሞ፤ ያለ ነውጥ አሰሙ፡፡ እናንተ እየሞታችሁ፤ ሙቱ የሚሏችሁ ሰዎች፤ በሞታችሁ ያተርፋሉ፤ እንጂ ለእናንተ ደንታ እንደሌላቸው ተረዱ፡፡ ትላንት ያነደደከው ቤት፤ አባትህ፤ እናትህ፤ ወንድም እና እህትህ፤ ወይም ዘመዶችህ ሲስሩበት የነበረውን መሥሪያ ቤት ነው፡፡ ትላንት ያቃጠልከው ፋብሪካ፤ የአንተን የሥራ እድል የዘጋ ነው፡፡ ጽንፈኞች በራስህ ሕይወት ቁማር እንድትጫወት የሚፈልጉት፤ መሳሪያ ልትሆናቸው የምትችለው፤ ስትደኽይ መሆኑን በጥሞና ስለሚያውቁ ነው፡፡ ጥያቄህን፤ አውቅልሃለሁ ለሚሉ ግብዞች አሳልፈህ አትስጥ፡፡ ተደጋግሞ እንደተባለው፤ ብዙዊቹ፤ ተላንትናቸውን ኖረው፤ የአንተን የነገ ሕይወት ነው የሚቆምሩበት፡፡ ትላንት በኦሮምያ ክልል የተፈጠረውን የኢኮኖሚ ድቀት፤ በቀላሉ መገንባት ይቻል ይመስልሃል? ማን ነው ዛሬ ኦሮምያ ክልል መዋኧለ ነዋዩን ለማፍሰስ የሚሞክር? በዚህስ የሚጎዳው ማን ይመስልሃል? ሚኒሶታ ቁጭ ብሎ የሚፈልገውን የቡና ዓይነት አጣጥሞ እየጠጣ፤ በመፈክር የደመቀ ቲ፟፟-ሸርት ለብሶ፤ አንተን መንገድ ዝጋ፤ ንግድ ቤት ዝጋ ሲልህ፤ በጠኔ የምትጠቃው አንተ ነህ፡፡ ያንተ ሞት፤ ለእሱ መበሻሸቅያው ነው፡፡ እመነኝ፤ በአንተ ሞት የሰከንድ እንቅልፍ አያጣም፡፡ ስለዚህ፤ እናውቅልሃለን ለሚሉ ጽንፈኞች፤ የወደፊት እጣህን አሳልፈህ አትስጥ፤ በአንተ ሞት፤ እነሱ ወደ ”ክብር” የሚመጡ ለሚመስላቸው ጽንፈኞች፤ በቃችሁ፤ የእናንተ የስልጣን መረማመጃ አልሆንም በል፡፡

ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን ቸሩ እግዚአብሔር ይጠብቅ፡፡    

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
12,864FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

1 COMMENT

  1. Thanks! It is the truths. All Ethiopians want to live better sharing the resources equally in democracy with other ethical groups in peace. Please summarize your article in afan Oromo. Someone have to teach the Querros how to be a good human being/Ethiopiawit/ASP before they cause more problems for all of us.

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here