በደነቀ ተሰማ
ሐምሌ 15 , 2012 ዓ.ም.
የአሜሪካ ህገ-መንግስት አርቃቂዎችን ካማለሉ ፍልስፈናዎች የፈረንሳያዊው የፖለቲካ ፈላስፋ ዲ-ስኮንዳት ሞንተስኪው እና የሌሎች ውጥን የሆነው ከስልጣን ክፍፍል ጋር የሚናበብ የመንግስት አሰራር ክትትልና ቁጥጥር (Check and balance) ጽንሰ-ሃሳብ ነው፡፡ ይህው ጽንሰ-ሃሳብ የአሜሪካ ህገ-መንግስት የፍልስፍና አካል በመሆኑ ለሃገሪቱ የዲሞክራሲ እድገት ብዙ ፈይዷል፡፡ ይህው የክትትል ወይም ቁጥጥር መርህ በየትኛውም የመንግስት በተቋማት ላይ ቢተገበር ውጤታማ የማይሆንበት ምክንያት የለም፡፡ የመከላከያ እና ደህንነት ተቋማት አሰራሮች በግልጽነት እና በተጠያቂነት የሚመሩ ሊኖራቸው፡፡ ግልጽ በሆነ የህግ ድንጋጌ ሚስጥራዊ የሆኑ እና ሚስጥራዊ ያልሆነ አሰራሮች ድንበር እንዲኖራቸው የማድረጉ ጉዳይ የመከላከያ ተቋማትን ዲሞክራሲዊ የማድረግ ተግባራት ቅድሚያ ይሆል፡፡ የተቋማቱ አሰራሮች፣ በጀት ወጭ-ገቢ፣ የቁሳቁሶች የውጭ ግዢ በዲሞክራሲያዊ የቁጥጥር እና የማስተካከል መርሆች (Principles of democratic oversight to the security institutions) እንዲቃኙ የማድረግ ስራ ይሰራል፡፡ በዚህ አይነት ስምሪት የተለያዩ ተቋማት የሚሳተፉ ሲሆን መንግስታዊና መንግስተዊ ያልሆኑትን ያካትታል፡፡
የዲሞክራሲያዊ ክትትል ምንነት እና ፋይዳው
በጸጥታው አካላት ላይ የሚደረግ ክትትል ስንል የተቋማዊ የተጠያቂነትና የአሰራር ግልጽነት የማረጋገጥ ሂደት ነው፡፡ በዚህ ውስጥ የሚጠቀሱት ተግባራት 1). የጸጥታ ተቋማቱ የአሰራር ስርዓት ከፖሊሲዎችና ህግጋት ጋር የተጣጣመ እና የተገራ መሆኑን ማጤን፤ 2). አሰራሩ ከመርህ አፈንግጦ ሲገኝ መግራት፤ እና 3). የውጤታማነት እና የብቃት ፍተሻ ወዘተ ናቸው፡፡ ክትል ሂደትም ኡደትም ነው፡፡ ሂደቱና ኡደቱ መቃኘትን፣በሳይንሳዊ መለኪያ መዝኖ ውጤት መስጠትን፣መግራትን እና ግብረ መልስ ሰጠቶ መቀበልን ያካትታል፡፡
ዲሞክራሲያዊ ክትትል ለምን ? በጸጥታ ተቋማት ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ህጸጾች የተለመዱ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ በማደግ ላይ ባሉ ሃገራት ችግሩ የጎላ ነው፡፡ የአሰራር ስርዓቱ በመንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ አካላት ተሳትፎ በክትትልና ድጋፍ ችግሮችን የመግራት ስራ በተከታታይነት እንዲከናወን ያለመፍቀድ አጠቃላይ ሀገራዊ ስርዓትን ጤናማነት የሚጉዳ ነው፡፡ የተጠያቂነት ማነስና እና ግልጸነት የጎደለው የጸጥታ ተቋም አሰራር እና የዲሞክራሲያዊ ህግጋት ኮቴ ያለመኖር ሙስና፣ የግለሰብ አምባገነንነት ብሎም የእዝ ሰንሰለት መቃወስ ይከሰታል፡፡ ይህ ሁኔታ የከፋ ውጤት የሚኖረው በጦር መሳሪያ ፍላጎት ፕሮፎርማ ስብሰባ፣ በጦር መሳሪያ ግዢ እንዲሁም በሰው ሃይል ምልመላና የሰራዊት አባላት ሽኝት ላይ ነው፡፡ እነዚህ እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ በጀት የሚጠይቁ በመሆናቸውም የተወሰነ ክስረት ቢከሰት እንኳ በሀገር ሃብት ላይ የሚያሰድረው ጫና ግዙፍ ነው፡፡
ተገቢና ግምገማና ፍተሻ ማይደረግላቸው የጸጥታ አካልና መስሪያ ቤቶች ወደራስ ማስተዋል ይሳናቸዋል፣አደጋ መጋፈጥ ይፈራሉ፣ ለውጥን አይቀበልም፣ ሀገራዊ አደጋ ስጋትን መተንበይ የሚያስችል የአወቃቀርና የሙያ ዝግጀት ማደረግ ይሳናቸዋል፡፡ ዘፈቀዳዊ የፖሊሲ ማዕቀፍ፣ ለፖለቲካዊ አመራር ጀርባ መስጠትና አሮጌና የተለመዱ አሰራሮች ላይ መጣበቅም ይኖራል፡፡ በአለም ላይ የተከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ከመረመርን ከወታደራዊ ስምሪት ጋር የሚገናኙት እጅግ የበዙ ናቸው፡፡ የሰብአዊ መብት ጠሰቶቹ መነሻዎች በቂ የሲቪሊያን ክትትል ያለመኖር፣ የእዝ ሰንሰለቱ ከሚፈቅደው ውጭ እርምጃ የመውሰድ፣ እርምጃ የወሰዱ የሰራዊት አባላት እና አመራሮች በህግ ሳይጠየቁ መቅረት፣የጦርንት ህግን የጣሰ (action against the rule of Jus ad bellum and Jus in bello) ዘፈቀዳዊ በቀለኝት ወዘተ ናቸው፡፡ በዚህ የተነሳ ዲሞክራሲዊ ክትትል የግድ ይሆናል፡፡
በሌላው ገጽ ደግም የዴሞክራሲያዊ ክትትል ማነስ የመከላከያ እና የደህንነት ተቋማቱ በውስን ሲቪል ፖለቲከኞች እጅ ውስጥ ይወድቁና አሰራራቸው ፖለቲሳይዝ ተደርጉ የፖሊስና የወታደር መሰረታዊ መርሆችን የጣሱ ፖሊቲካዊ ወገንተኝነቶች የጨዋታውን ሜዳ ይቆጣጠረዋል፡፡ የግልጸ ምንጭ መረጃዎች፣ የሰብአዊ መረጃ፣ የሲግናል መረጃ፣ የሳተላይትማ የፎቶ መረጃ‹ የሳይበር መረጃዎች የኢንዶክትሪኔሽን እና የዘመቻ መምሪያ ክፍሎች የፖለቲካ ማሳሪያ ስለሚሆኑ የአፈና ተቋማትነት ምግባር ይላበሳሉ፡፡ ህዝብ በሚከፍለው ግብር ይታፈናል፡፡
የቁጥጥር እና ክትትል ባለድረሻ አካላት
በዲሞክራሲያዊ ቁጥጥር፣ ክትትል እና በማስተካከል ተሳታፊ ሊሆኑ የሚችሉ አካላት 1) የፓርላማ (Parliamentary Oversight)፤ 2) የመንግስት አስፈጻሚ አካላት (Oversight by the executive bodies) ለምሳሌ የጠቅላይ ሚኒስተር የመረጃና ደህንነት አማካሪ ኮሚቴ፣ መከላከያ እና የደህንነት ተቋማት የውስጥ ኦዲት ክፍሎች)፤ 3) የዲሞክራሲ ተቋማት ማለትም የኦዲት ድርጅቶች (ዋና ኦዲተር)፣ እምባ ጠባቂ እና የሰብአዊ ኮሚሽን እና ወዘተ… (4) በሲቪክ ማህበራት (Oversight by the Civil Societies) በጸጥታው ተቋማት ስርዓት ውስጥ የሚኖራቸውን ተሳትፎ የሚመለከት ነው፡፡
ፓርላማ
የአንድ ሀገር ፓርላማ የጸጥታ ተቋማትን ቅርጽ ይዘት እና ግጋዊ መሰረቶች የመወሰን ስልጣን እንዳለው ሁሉ የአፈጻጸማቸውን ግልጽነት፣ ውጤታማነት እና ህጋዊነት የመከታተል ኃላፊነት አለበት፡፡ ጥርስ ያለው ፓርላማ ክትትል ተጠያቂነት እንዲጎለብት፣ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን /የዲሞክሪሲ እሴት እንዲገነባ እና እንዲጎለብት/ እና ኃላፊነት የሚሰማው የጸጥታ ተቋም እውን እንዲሆን አስቻይ ነው፡፡ እዚህ ላይ የፓርላማ ሚና ህግ ከማውጣት ያለፈ መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል፡፡ በፓርላማ የሚደረግ ክትትል በቸክ-ሊስት እንደሚመዘን የስራ አፈጻጸም ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባ ነው፡፡ ማለትም ከህግጋቶች እና በፓርላማ ከጸደቀ በጀት አንጻር የደህንነት እና የመከላከያ መስሪያ ቤቶችን አፈጻጸም መፈተሸ እንዲሁም ክፍተቶች ሲመዘገቡ የማስተካከያ እርመጃዎችን ማድረግን ወዘተ.. የሚመለከቱ ስራዎችን የማከናወን ሚና ይጠበቅበታል፡፡ በተጨማሪ ለምሳሌ በናሚቢያ ፓርላማው በጸጥታው ዘርፍ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች (በተወካዮቻቸው አማካኝነት) ሃሳብ የሚንሸራሽሩባቸውን እና የመንግስት አስፈጻሚዎች እና የጸጥታው ቁልፍ አካላት አስተያየቶችን የሚሰሙባቸው መድረኮች ያመቻቻል፡፡ በዚህ አይነት ሁኔታ የማህበረሰቡ ተወካዮ የጸጥታ ስራዎችን ይሁንታ እንዲሰጡ፣የባላቤትነት ስሜት እንዲዳብር ማድረግ ከመቻሉ በተጨማሪ የመንግስት አካላት ውሳኔዎቻቸውን ከህብረተሰቡ ፍላጎት አንጻር እንዲቃኙ የመረጃ ሰጭ ምንጭ የመሆን ሚና ነበረውም፡፡
በአብዛኛው አለም በተለይ በበለጸጉ ሃገራት ፓርላማ የሰራዊቱን ቅሬታ ይሰማል፣ የሲቪሊያን ተሳትፎ እንዲረጋገጥ ያዛል፣ የጸጥታ ክፍል አስፈጻሚ ሚና እና የፓርላማ ስራዎች እንዳይሳከሩ መርሆችን ይዘረጋል፣ በሪፎርም የሚታገዝ የጸጥታ ስራ ቀጣይነትን ያረጋግጣል፣ የበጀት ቁጥጥር ያደርጋል፣ የቡድን አስራርን ያበረታታል፣ በሚስጥራዊ እና ሚስጥራዊ ባልሆኑ የጸታ ስራዎች መካከል ግልጽ ወሰን እንዲበጅ ያደርጋል፣ ወጥና ልዩ ሪፖርቶችን የማስቀረብና የመስማት ወዘተ… ስራዎችን በመከወን የዲሞክራሲያዊ አሰራርን የጎለብታል፡፡
ለዚህ አይነት ስራ ሁሉም የፓርላማ አባላት የሚሰማሩ እንዳይደለ የሚታወቅ ነው፡፡ በመሆኑም እንደ የሃገራት ፓርላማ ፍላጎት በተለያዩ ስያሜዎች ኮሚቴዎች ሊደራጁ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ የመከላከያ እና የደህንነት ቋሚ ኮሚቴ፣ የሰላምና የደህንነት የፓርላማ ቡድን፣ ጸጥታ ቋሚ ኮሚቴ፣ የመከላከያ እና የውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ፣ ወዘተ የሚደራጁ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ሲቪል አደረጃጀቶች፣ መንግስታዊ ልሆኑ ድርግቶችና ሌሎች ተቋማት
ለዲሞክራሲያዊ ክትትል አላማ መንገስታዊ ያልሆኑ ሲቪል አደረጃጀቶች የሚለው ገለጻ
የበጉ አድራጎት ተቋማትን፣ ሚዲያን፣ የሰላም ክለቦት፣ የጥናትና ምርምር ድርጅቶችን ወይም ማዕከላትን፣, የትምህርት ተቋማትን የሚያካትት ነው፡፡ በአንድአንድ ስልጡን ሀገራት የግል የማረሚያ፣ ማሰልጠኛ ተቋማት እና ቤተ-ክርስቲያናትም በጸጥታ ስራዎች ሚና እንዲኖራቸው ይፈቀዳል፡፡ እስከዚህ የደረሰ የተለጠጠ ተሳትፎ መፍቀድ ያስፈለገበት አንዱ ምክንያት በአንድም በሌላም መልኩ የሀገሪቱ የጸጥታ ስራ የሁሉንም የማህበራሰብ ክፍሎች የሚነካ በመሆኑና ልዩ ልዩ ፍላጎቶች መንጸባረቅ ስለሚኖርባቸው ነው፡፡
የሲቪል አደረጃጀቶች እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን የቁጥጥ እና ክትትል ሚናን በተመለከተ የተለያዩ አረዳዶች እንዳሉ የሚታወቅ ነው፡፡ በአንድ በኩል ጥሪ ሲደረግላቸው ማገዝ ብቻ እንጂ ቀጣይነት ያለው የቁጥጥር ሚና ሊኖራቸው አይገባም የሚል በሌላ በኩል የጸጥታ ተቋማት ሚስጥራዊና ሚስጥራዊነት የሌላቸው ስራዎችን በህግ ለይተው እስካስቀመጡ ድረስ ሚስጥራዊ ባልሆነ ስራ ላይ ሁሉ አቀፍ ተሳትፎ አስፈላጊ ነው የሚል ሙግት አለ፡፡
ያም ሆነ ይህ ሁለቱም ወገኖች የመከላከያ እና ደህንነት አሰራሮች ግልጥነትና ተጠያቂነት እንዲላበሱ የሲቪል አደረጃጀቶች ተሳትፎን እውቅና አይነፍጉም፡፡ እንደየሁኔታው የሲቪል አደረጃጀቶች በጽትታው ዘርፍ ላይ የቁጥጥር፣ የክትትል፣ የውክልና የተለያዩ ፍላጎቶችን የማስተናገድ፣ ምክር ሃሳብ አመንጭነት፣ የጥናትና ምርምር፣ የፖሊሲ ትንተና፣ ለፖሊሲዎች ይሁንታ የመቸርና ድጋፍ የማስገኘት፣የእውቀት ሽግግርን የማስፋት፣ ተዋስዖዎችን በመፍጠር (forming public discourses) እና የግንዛቤ ፈጠራ ሚናዎችን የመወጣት ተሳትፎ እንዲኖራቸው ይጠበቃል፡፡
በኢትዮጵያ አነማን የክትትል እና ድጋፍ ባለድርሻ ይሁኑ?
ከ1983 ዓም. ወዲህ ያለው የመከላከያ ስርዓት እንኳ ብናስታውስ የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ መስሪያ ቤቶች እና የደህንነት መስሪ ቤቶች በዲሞክራሲዊ ተጠያቂነት ረገድ ውስንነት የነበረባቸው ተቋማት ናቸው፡፡ እነዚህ መስሪያ ቤቶች ላይ ይደረግ የነበረው የፍተሻ፣ ክትትል እና የእርምት ስርዓት በማነሱ የተነሳ ተቋማቱ የፈጸሙት የሰብአዊ መብት ጥሰትና የኢኮኖሚ ኪሳራ የሃገሪቱን የዲሞክራሲ እና የኢኮኖሚ እድገት የገታ መሆኑን በሳይንሳዊ መተንተኛ ማሳየት ይቻላል፡፡ እውነት ነው ጉዳዩ የከፋ ነበር፡፡ ከ2010 ዓ.ም. ወዲህ የሀገሪቱ መንግስት ይፋ ያደረጋቸው መረጃዎች የጉዳዩን ግዝፈት የሚያመለክትቱ መሆኑን ጠቁሞ ማለፍ ይበቃል፡፡ እናም ይህ ጽሁፍ የተቋማቱን ህጸጾት የማብራራት አላማ ስለሌለው ጉዳዩን እዚሁ ላይ በማቆ ከታች በሉት አንቀጾች የደሞክራሲዊ ክትትል ባለድርሻ አካላትን ለመጠቆም ይመከራል፡፡
መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅቶት፡- የወጣቶች ማህበራት፣ የሴቶች ማህበራት፣ በጉ አድራጎቶች፣ የጥናትና የምርምር ድርጅቶች ተጋብዘው የጸጥታ ተቋማትን የተመጠኑ አሰራሮችን እንዲተዘቡ እንዲከታተሉ እና ክፍተቶች ሲኖሩ የእርምት አማራጮችን እንዲያፈልቁ ማድረጉ ከተቻለ ሁለት አይነት ፋይዳ አወንታዊ ውጥት ይኖረዋል፡፡ይህም አንደኛው ተጠያቂነትንና ግልጸነትን ለማስፈን ዘእገዛ ሲኖረው በሁለተኛ ደረጃ እነዚህ አካላት በተሳታፊነት መጋበዛቸው የእኔነት ስሜት እንዲጎለብትና በሀገራዊ የጸጥታው ስራዎች ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኖ ያስችላል፡፡
በመንግስት በጀት የሚንቀሳቀሱ የዲሞክራሲ ተቋማት ማለትም ጸረ-ሙስና፣ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣የተወካዮች ምክር ቤት፣ እምባ ጠባቂ፣ ዋና ኦዲተር ወዘተ… በጸጥታ ተቋማት ላይ የሚደረግ የዲሞክራሲያዊ ክትትል ባለድርጻ ናቸው፡፡ በአስፈጻሚው ረገድም ከጠቅላይ ሚንስትሩ ልዩ ጸጥታና የደህንነት አማካሪ ክፍል ወይም ጽ/ቤት በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስተሩ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ እንደመሆናቸው መጠን የክትትሉ አካል ናቸው፡፡
የዲሞክራሲዊ ክትትል ስርዓት ዋና ጉዳይ የህግ መሰረት መኖሩ ነው፡፡ በመሆኑም የቀድሞ ማለትም በአዋጅ ቁጥር 1100/2011 ዓ.ም. የተተካው መከላከያ ህግ፣ በአዋጅ ቁጥር 809/2005 ዓም. አንቀጽ 71 (3) ሚኒስተሩ የፋይናንስ እና የሰው ኃይል በመንግስት አካል ጭምር እንዳይታወቅ (ለዋና ኦዲተር ጭምር) መከልከሉ የኢ.ፌ.ደ.ሪ. ህገ-መንግስት አንቀጽ 101 (2)ን ስለሚጻረር እርምት ተደርጎበት እንዲሁም ሚስጥራዊና ሚስጥራዊ ያልሆኑ አሰራሮችን በግልጽ ተደንግገው ዲሞክራሲያዊ ክትትል እውን እንዲሆንም ያስፈልጋል፡፡ መጠቅለያ፡ ጤናማ የዲሞክራሲ ስርዓት እድገት ወይም ቀጣይነት አውን ይሆን ዘንድ በፓርላማ (የፓርላማ የመከላከያ እና የደህንነት ቋሚ ኮሚቴ ወይም ሌላ ስያሜ ሊሰጠው ይችላል) እና በሌሎች የዲሞክራሲ ተቋማት፣ በሲቪክ ድርጅቶች፣በመንግስት አስፈጻሚ አካላት የሚደረግ ስርዓታዊ (systemic) የዲሞክራሲያዊ ክትትል ስርዓታዊነት አስፈላጊ ነው፡፡ የነዚህ አካላት የተሳትፎ ድርሻ በተለያየ ደረጃ እየተመጠነ የጸጥታ ተቋማቱ አሰራር ግልጽነትን እና ተጠያቂነትን ለማስፈን ዴሞክራሲያዊ ክትትል፣ የማስተካከያ ስራዎች መከወን ለሃገራዊ የዲሞክራሲ ስርዓት እድገት የጎላ ፋይዳ አለው፡፡ በመሆኑም እንደኢትዮጵያ ያሉ በተለይም ፈርታማ ተቋማትና ሞራጅ ተቋማዊ ባህል ያልገነቡ ታዳጊ ሃገራር በጸጥታ መስሪያ ቤቶች ላይ ሳይንሳዊ እና ዲሞክሪሲያዊ የክትትል ስርዓት ማስፈን የውዴታ ግዴታቸው ይሆናል፡፡ ይህን አይነት አሰራር ለመተግበር ያመች ዘንድ በጸጥታ መስሪ ቤቶች አይነኬ የሆነ ውስን ሚስጥራዊ ጉዳዮችን ለይቶ የመደንገግ ስራ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡