spot_img
Wednesday, November 29, 2023
Homeነፃ አስተያየት“የሁለት ሰንደቅ ዓላማዎች ወግ” (ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ)

“የሁለት ሰንደቅ ዓላማዎች ወግ” (ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ)

advertisement
Samuel Tibebe Ferenji
ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ

ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ
ሃምሌ  28 ቀን 2012 ዓ.ም.

“አንቀጽ 29 – የአመለካከት እና ሀሳብን በነፃ የመያዝና የመግለጽ መብት

  1. ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት ለመያዝ ይችላል፡፡
  2. ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሀሳቡን የመግለጽ ነፃነት አለው። ይህ ነፃነት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በሕትመት፣ በሥነ ጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ፣ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሀሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት ነፃነቶችን ያካትታል፡፡” ከኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የተቀነጨበ፡

ዕድሜዬ፤ 17 ዓመት ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ በኖርኩባት ሃገረ አሜሪካ፤ የሃገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ፤ መቅደድ፤ ማጣጣል እና ማንደድ ሕጋዊ ነው፡፡ ዜጎች፤ በማንኛውም መንገድ በሰላም ሃሳባቸውን የማንፀባረቅ መብት አላቸው። ማንም ሰው የአሜሪካንን ሰንደቅ ዓላማ አቃጠልክ ተብሎ በሕግ ሊጠየቅ አይችልም፡፡ ይህ ግን እንዲሁ በቀላሉ የተገኘ ሃሳብን የመግለጽ ነፃነት አይደለም፡፡ ይህንን የሃሳብ መግለጽ ነፃነት በሕግ እንዲረጋገጥ ያደረግው፤ የአሜሪካን ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአውሮፕያኑ አቆጣጠር ሰኔ 11 ቀን 1990 ዓም ነው፡፡ በአሜሪካን ሃገር ውስጥ፤ የሃገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ ማራከሰ እና መቅደድም ሆነ ማቃጠል፤ በኅብረተሰቡ ውስጥ አጨቃጫቂ ሆኖ የቆየ፤ በተለያየ አካባቢም ለብጥብጥ እና ለረብሻ ምክንያት የሆነ ነበር፡፡ ቀደም ሲል የተለያዩ የአሜሪካ ክፍለ ግዛቶች፤ ሰንደቅ ዓላማን ማራከስ፤ መቅደድ እና ማቅጠል፤ በሕግ የሚያስቀጣ፤ እንደሆነ የሚደነግጉ ደንቦች ነበሯቸው፡፡ በሃምሌ 1989 (እአአ) የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፤ መንግስት ዜጎች፤ ሰንደቅ ዓላማን “የማጣጣል” እና “የማራከስ” መብታቸውን ሊያግድ አይችልም ብሎ በመወሰኑ፤ ቀዳማዊ ጆርጅ ቡሽ፤ ሰንደቅ ዓላማን ማራከስ እና ማጣጣል በሕግ የሚያስቀጣ ወንጀል እንዲሆን፤ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ እንዲደረግ ሃሳብ ቢያቀርቡም፤ የህግ አውጪው ምክር ቤት፤ ቡሽን በመቅደም፤ ሰንደቅ ዓላማን ማራከስ እና ማጣጣል በሕግ የሚያስቀጣ ወንጀል እንዲሆን በዛው ዓመት ሕግ አርቅቆ አፀደቀ፡፡ ይህ የአሜሪካን የሕግ አውጭ ምክር ቤት (ኮንግረስ) የወሰደው እርምጃ በጣም ብዙ አሜሪካውያንን አስቆጣ። 

ይህንን አስመልክቶ፤ በርካታ ሰዎች ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተው፤ የአሜሪካንን ሰንደቅ ዓላማ ማቃጠል ጀመሩ፡፡ ይህንንም ያደረጉት፤ በወንጀል ተከሰው፤ ጉዳዩን የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ እንደገና እንዲያየው ለማድረግ ነበር፡፡ በወቅቱ፤ የሪፓብሊካን ፓርቲ፤ ለፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር እጩ የሚሆነውን ሰው ለመምረጥ ስብሰባ አድርጎ (ኮንቬንሽን) በነበረበት ቦታ ላይም በሰላማዊ ሰልፈኞች፤ ትልቅ ብጥብጥ ተፈጠረ፡፡ ሶስት ሰዎችም፤ ሕዝብ በተሰበሰበበት፤ የአሜሪካ ምክር ቤት ጽ/ቤት በር ላይ፤ ሰንደቅ ዓላማውን ሲያነዱ፤ ታሰሩ፡፡ በዲሲ እና በሲያትል ዋሽንግተን፤ ወንጀለኛ የተባሉ ሰዎች ክስ ተመስርቶባቸው ለፍርድ ቀረቡ፤ ፍርድ ቤቶቹም፤ ቀደም ብሎ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ ላይ የሰጠውን ውሳኔ በመጥቀስ፤ ተከሳሶቹን ነፃ ናቸው ብሎ ክሱን ውድቅ አድርጎ ተከሳሾቹን አሰናበተ፡፡ ይህንን ተከትሎ የአሜሪካ የፍትሕ ሚኒስትር መስርያ ቤት በቀጥታ ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይግባኝ አቀረበ፡፡ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም 5-4 በሆነ ውሳኔ፤ የአሜሪካንን ሰንደቅ ዓላማ፤ ማዋረድ፤ ማራከስ፤ መቅደድ እና ማቃጠል፤ የዜጎች ሕገ መንግስታዊ መብት ነው ሲል አፀደቀ፡፡ ምንም እንኳን የአሜሪካ ሰንደቅ ዓላማ፤ ሲራከስ እና ሲቃጠል፤ ከልባቸው የሚያዝኑ እና የሚበሳጩ ዜጎች ቢኖሩም፤ ሰንደቅ ዓላማ ማራከስ እና ማቃጠል፤ ወንጀል አይደለም፡፡ 

ይህን ምሳሌ ለማንሳት የፈለግኩት፤ ሰዎች፤ እግዚአብሔር የሰጣቸውን ሃሳብን የመግለጽ መብት፤ ማንም ሊገድብባቸው እንደማይገባ ለማሳየት ነው፡፡ ሰዎች እኛ የወደደንውን ብቻ መውደድ የለባቸውም፤ የምንወደውን የመጥላት መብታቸው የተከበረ ነው፡፡ ማንም ሰው ሃገሩን የመጥላት መብት አለው፡፡ በእውነተኛ የሃሳብ ነፃነት የምናምን ከሆነ ይህን ሃቅ መቀበል አለብን፡፡ ማንም ዜጋ ሃገሩን የመጥላት መብት አለው ማለት ግን አገርን የመጉዳት፤ ወይም ለመጉዳት የማሴር መብት አለው ማለት አይደለም፡፡ ማንም ሰው ሃገሩን ወዶም ሆነ ጠልቶ የመናገር መብቱ የተጠበቀ ሊሆን ይገባል፡፡ በኢትዮጵያ ይህን እውነት ለመቀበል ምን ያክል ጊዜ እንደሚፈጅ እግዚአብሔር ይወቀው፡፡ እኔ የወደድኩትን ካልወደድክ “ኢትዮጵያዊ አይደለህም” የሚል አስተሳሰብ፤ ሊታረም ይገባዋል፡፡ ዜጎች በተለያየ ምክንያት፤ በሃገራቸው እና በሃገራቸው አስተዳደር ሊያዝኑ እና ሊማረሩም ይችላሉ፤ ያን ምሬት አትግለፁ ማለት ደግሞ ፍጹም አምባገነናዊ አመለካከት ነው፡፡ 

ከዚህም የደከመ አስተሳሰብ በመነሳት ይመስለኛል፤ በሰንደቅ ዓላማዎች ንትርክ የከረረ ግጭት ውስጥ እየገባን ያለነው፡፡ አንድ ግልጽ መሆን ያለበት ነገር፤ ማንም ዜጋ ልሙጡን፤ አረንጓዴ ብጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማም ሆነ ባለኮከቡን አርማ ያለበትን፤ አረንጓዴ ብጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ፤ ወይም ሌላ ማንኛውንም ዓይነት ሰንደቅ ዓላማ የማውለብለብ ተፈጥሯዊ መብት አለው፡፡ ይህ መብት በተለይ በመንግሥት አካላት በአደባባይ ሲጣስ እያየን ከመሆኑም በላይ፤ “የባለ ኮከቡ ሰንደቅ ዓላማ ጠበቆች” ነን የሚሉ ጽንፈኞች፤ በሚሰማቸው የተረኛነት ስሜት፤ ልሙጡን ሰንደቅ ዓላማ እና የⶁዓ አንበሳ አርማ ያለበትን ሰንደቅ ዓላማ ሲነጥቁ እና ሰንደቅ ዓላማውንም ሲያጣጥሉ እያየን ነው። ከዚህም አልፎ፤ የተለያዩ የፀጥታ አካላት፤ ልሙጡን ሰንደቅ ዓላማ ከግለሰቦች ላይ ሲነጥቁ፤ ከመኪናም ላይ ሲያወርዱ፤ በግርምት በአደባባይ አይተናል። ይህ ድርጊት ግን የሃገሪቱን ህገ መንግሥት የጣሰ እና፤ የሃሳብ ነፃነትን የገደበ ሕገ ወጥ ሥራ ነው። የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29 ቁጥር 1 እና 2 በግልጽ እንደሚያስቀምጠው፤ ማንም ሰው በፈለገው መልኩ ሃሳቡን የመግለጽ መብት አለው፤ ይህም የፈለገውን ሰንደቅ ዓላማ፤ የማውለብለብ መብቱንም ይጨምራል፡፡ 

ወደድንም ጠላንም፤ ሁለቱም ሰንደቅ ዓላማዎች፤ ለኢትዮጵያ ዳር ድንበር በተዋደቁ ጀግኖቻችን ተነግቦ፤ በጦር ግንባር ውለዋል፡፡ ልሙጡ ሰንደቅ ዓላማ፤ በተለያዩ የጦር ሜዳዎች ምልክታችን ሆኖ አባቶቻችን እና አያቶቻችን የተዋደቁበት ሲሆን፤ በግንቦት 1990 ከኤርትራ ጋር በተደረገ ጦርነት፤ የኢትዮጵያ ሰራዊት ባለኮከቡንም፤ ልሙጡን ሰንደቅ ዓላማም ይዞ ዘምቷል፡፡ የኢትዮጵያ ሰራዊት፤ በየካቲት 1991፤ የኤርትራን ሰራዊት ከባድሜ አስወጥቶ፤ ባድሜን ሲቆጣጠር፤ ባድሜ ላይ ያውለበለበው ሰንደቅ፤ ልሙጡን ሰንደቅ ዓላማ ነው፡፡ ባለኮከቡ ሰንደቅ ዓላማ፤ በባድሜ፤ ፆረና፤ ቡሬና ሌሎች ግንባሮች የኢትዮጵያ ሰራዊት ያውለበለበው ሰንደቅ ሲሆን፤ በነዚህ የጦር ግንባሮች ላይ፤ ልሙጡ ሰንደቅ ዓላማም በሰራዊቱ ተውለብልቧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በሶማሊያ እና ሩዋንዳ፤ የሰላም ማስከበር ግንባር፤ ባለኮከቡ ሰንደቅ ዓላማ ተወለብልበዋል፤ ዛሬም በሶማልያ እየተውለበለበ ነው፡፡ ከዚህም አልፎ፤ ባለኮከቡ ሰንደቅ ዓላማ፤ የኢትዮጵያ ኦፊሳልያዊ ሰንደቅ ዓላማ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በማንኛውም ኦፊሳልያዊ ጉዳዮች እና በመንግስት መሥሪያ ቤቶች፤ ሊውለበለብ የሚችለው ባለኮከቡ ሰንደቅ ዓላማ ብቻ ነው፡፡ ይህንን እውነታ፤ ሰንደቅ ዓላማውን የማንቀበለው፤ ወይም፤ በጉልበት ተጭኖብን ነው የምንል ልንቀበለው ይገባል፡፡ ምክንያቱም አሁን ሃገራችንን ወደ ዲሞክራሲያዊ ስልተ ስርዓት ለማሸጋገር፤ አብዛኞቻችን የሃገሪቱ የበላይ ሕግ ብለን የተቀበልነው አሁን ያለውን ሕገ መንግስት ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ጥልቅ እና ሰፊ ውይይት እንደሚያስፈልገው ሁሉ፤ የሰንደቅ ዓላማም ጉዳይ፤ ጥልቅ እና ሰፊ ውይይት ያስፈልገዋል፡፡ እስከዛው ድረስ ግን ዜጎች፤ የፈለጉትን ሰንደቅ ዓላማ የማውለብለብ መብታቸው ሊጠበቅ ይገባል።

ልሙጡን ሰንደቅ ዓላማ የማይቀበሉ ኃይሎች፤ የሰንደቅ ዓላማውን ዓላማ ካለመረዳት፤ የአንድን ሃይማኖት እና የአንድን ብሔር  ብቻ የሚወክል እንደሆነ አድርገው የሚረጩት የተሳሳተ ትርከት፤ በታሪክ ምሁሮቻችን አስተማሪነት እርምት እያገኘ እንዲሄድ መደረግም ይኖርበታል፡፡ አብዛኛው የአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ልሙጡን ሰንደቅ ዓላማ የሚቃወም ወጣት፤ ለምን እንደሚቃወም እንኳን በቅጡ አያውቀውም፡፡ ይህ ወጣት፤ ይህን ሰንደቅ ዓላማ ያለመውደድ እና ያለመቀበል መብት ቢኖረውም፤ ሌሎች እንዳያውለበልቡት የመከልከል እና የማገድ መብትም እንደ ሌለው ሊገነዘብ ይገባል፡፡ በተለይ፤ በዚህ ረገድ በሃገራችን ያሉ የሲቪክ ድርጅቶች፤ የሰበዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፤ እና የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ሥራቸውን በሚገባ አልሰሩም ለማለት ያስደፍራል፡፡ ከዚህም አልፎ፤ በተለይ የአዲሰ አበባ መስተዳደር እና የፌደራል መንግሥቱ፤ ደጋፊዎቻቸውን ለማስደሰት በሚመስል መልኩ፤ ልሙጡን ሰንደቅ ዓላማ፤ የሚያውለበልበውን ዜጋ፤ ሕገ መንግስታዊ መብቱ ተጥሶ ሲዋከብ፤ አልፎም ሲደበደብ እያዩ በዝምታ ማለፋቸው፤ ከሰንደቅ ዓላማው ጋር በተያያዘ ለሚደረጉ የተለያዩ ጥቃቶች አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ ይህም በአስቸኳይ እርምት ሊወሰድበት ይገባል፡፡ የፌድራል መንግሥቱም ሆነ፤ የክልል መንግስታት፤ ዜጎች በሰላማዊ መንገድ፤ የፈለጉትን ምልክት ተጠቅመው ሃሳባቸውን የመግለጽ መብት እንዳላቸው፤ ለሕግ አስከባሪውም አካል ሆነ ለባለስልጣናቱ፤ በማያወላዳ መንገድ አስረግጠው ሊናገሩ፤ አስፈላጊውንም ስልጠና ሊሰጡ ይገባል፡፡ ማንም ዜጋ፤ ሃሳቡን በሰላማዊ መንገድ በመግለጹ ሊዋከብም ሊጠቃም አይገባውም፡፡ 

እኔ እንደሚገባኝ፤ ሁለቱ ሰንደቅ ዓላማዎች፤ ቢያንስ በሁለት የተለያየ ትውልድ ላይ የተለያየ ተጽእኖ አላቸው፡፡ ሁለቱም ሰንደቅ ዓላማዎች፤ በተለያየ ወቅት፤ እንዲሁም በ1990 ከእኢርትራ ጋር በተደረገ ጦርነት ሁለቱም ሰንደቅ ዓላማዎች በሃገራችን ጀግኖች ተይዘው ጦር ሜዳ ላይ ውለዋል፡፡ አድዋ ላይ ልሙጡን ሰንደቅ ዓላማ ይዘው የዘመቱ ዜጎቻችንን ስንዘክር እና ስናከብር፤ ባለኮከቡን ሰንደቅ ዓላማ ይዘው ዘምተው፤ ለሃገር ድንበር ሕይወታቸውን የገበሩ ውድ ዜጎቻችንን፤ የማንዘክርበትና የማናከብርበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ወደድንም ጠላንም፤ ሁለም መሬታችን ላይ፤ የሃገርን ድንበር ላምስከበር እና ሏአላዊነታችንን ለማስጠበቅ የፈሰሰው የኢትዮጵያውያን ደም ነው፡፡ “በሁለቱ የሃገር ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማዎቻችን” ከምንጣላበት ይልቅ፤ የሚያስተሳስሩን ምክንያቶች የሚበልጡበት ግርማ ያላቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ሁለቱም ሰንደቅ ዓላማዎች፤ በኢትዮጵያውያን ደምና አጥንት፤ ለሃገር ሏአላዊነት በተከፈለ መስዋዕትነት የደመቁ ምልክቶቻችን ናቸው። ወደፊት ለመራመድ፤ አንዳችን የሌላችንን ስሜት እና ፍላጎት እናክብር፡፡ ብዙ የማንስማማባቸው ነገሮች ይኖራሉ፤ በልዩነታችን ስንከባበር እና፤ ልዩነታችንን ስናቻችል፤ የተሻለች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ እንችላለን፡፡ ለዚህም ትልቁ መሰረት፤ መንግስት የሁሉንም ዜጎች የሃሳብ ነፃነት ሲያከብር እና፤ የዜጎችን መብት መጣስ ሲያቆም ነው፡፡ ስለዚህ፤ የሁለቱንም ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማዎች፤ ለሃገር ያላቸውን ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ በሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ ላይ ተወያይተን የጋራ መግባቢያ ላይ እስክንደርስ ድረስ፤ ዜጎች፤ ከመንግስት ኦፊሳሊያዊ ሥራዎች ውጭ፤ ልሙጡን ሰንደቅ ዓላማም ሆነ፤ ማንኛቸውንም ሃሳባቸውን በሰላም የሚገልጹበትን ምልክት የመያዝ መብታቸው ይከበር፡፡ ለዚህም መንግሥት ግልጽ የሆነ እና የማያሻማ መመሪያ ይስጥ።

ከላይ የአሜሪካንን፤ ሃሳብን በሰንደቅ ዓላማ በኩል የመግለጽን አመጣጥ ያነሳሁት ያለምክንያት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያም ውስጥ ዜጎች መብታቸውን ሊያስከብሩ የሚችሉት፤ በራሳቸው ጥረት እና ትግል ነው፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች በልሙጡ ሰንደቅ ዓላማ ምክንያት እንግልት፤ ወከባ እና ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች፤ እንግልቱን፤ ወከባውንም ሆነ ጥቃቱን በዝምታ ሊያልፉ አይገባም፡፡ አዋካቢውን እና አጥቂውን የከተማ ፖሊስም ሆነ የፌደራል ፖሊስን በሕግ ይጠይቁ፡፡ በዚህ ረገደም፤ በኢትዮጵያ የምትገኙ የሕግ ባለሙያዎች፤ በሙያችሁ አግዙ፡፡ ዲሞክራሲ ሊጎለብት የሚችለው በዜጎች ሙሉ ተሳትፎ ብቻ ነው፡፡ ሮዛ ፓርክ እምቢ ስላሉ፤ ማርቲን ሉተር ኪንግ ኢፍትሃዊነትን በየፍርድ ቤቱ ስለተሟገቱ፤ የአሜሪካ ጥቁሮች መብት እንዲከበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ “ገለልተኛ” እንደሆነ የሚነገርለትንም ፍርድ ቤት እንፈትነው፡፡ የዜጎች ሕገ መንግስታዊ መብት ጥሰት፤ በዲሞክራሲ “ልምድ አላቸው” በሚባሉ ሃገሮችም በተደጋጋሚ ይደረጋል፡፡ ዜጎችም መብታቸውን ለማስጠበቅ፤ በመብት ጣሾች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ በማድረግ ነው መብታቸውንም፤ የሌላውንም መብት የሚያስከብሩት፡፡ ይህ አካሄድ እኛም ሃገር ሊለመድ ይገባዋል፡፡ ስለዚህም የሁለቱን ሰንደቅ ዓላማዎች ወግ፤ ሳንጣላ፤ ስንዳማ፤ መቋጫ እንድናበጅለት፤ ሁላችንም ተከባብረን፤ መፍትሔ እንፈልግለት፡፡ በማንኛውም ወቅት፤ ዜጎች በሰንደቅ ዓላማም ሆነ በሌላ ሰላማዊ መንገድ ሃሳባቸውን የመግለጽ ሕገ መንግሥታዊ መብት እንዳላቸው ይሰመርበት እላለሁ፡፡ 

ቸሩ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን ይባርክ!

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here