spot_img
Thursday, July 25, 2024
Homeነፃ አስተያየትየባሕር ማዶ ደብዳቤ ለክቡር ዶ/ር ዓብይ

የባሕር ማዶ ደብዳቤ ለክቡር ዶ/ር ዓብይ

የባሕር ማዶ ደብዳቤ ቁጥር 7
ከሰማነህ ታ. ጀመረ
ነሐሴ 2012

semaneh

ጉዳዩ፥ በልዩ ልዩ ምክንያት የተበተነውን የኢትዮጵያ ሰራዊት ለሃገሩ ዘብ እንዲቆም ስለማድረግ!

ክቡር ዶ/ር ዓብይ ሆይ፤

በቅድሚያ የከበረ ሰላምታየ ከባሕር ማዶ ይድረስዎት። ኢትዮጵያዊያንን ሲአስጨንቅ የነበረውን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት እንዲፈፀም በማድረግዎ እንኳን ደስያለን። በግድቡ ግንባታ፤ በዓለማቀፍ ድርድርና ውይይት ለተሳተፉ ሁሉ ክብርና ምስጋና ይድረሳቸው። ከሁሉም በላይ መቀነት ፈተው የረዱ እናቶች፤ ኮረጇቸውን አራቁተው የገንዘብ ድጋፍ ላደረጉ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ክብረት ይስጥልን።   

እኔ የያትውልድ አካል ነኝ። ትውልዱ በግራ ዘመም ፖለቲካ ያበደበት። ግራ እጅ ተራማጅ፤ ቀኝ እጅ አድሃሪ ሆኖ አካሉን ከሁለት ጎራ ከፍሎ የተፋጀበት። አንድ የተደራጀ የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ድርጅት ሳይኖር ስርነቀል ለውጥ የጠየቀ ትውልድ። ስለሆነም አሁን ላይ ሆኘ ይህን ሃሳብ ሳቀርብ የድሮ ስርዓት ናፋቂ ተብየ እንደምፈረጅ እረዳለሁ። ሃሳቤ ተቀባይነት አግኝቶ ኢትዮጵያ ከዳነች ፍረጃውን በፀጋ የምቀበለው ይሆናል። ስለሆነም ወደ ዋናው ሃሳቤ ልምራዎት።

ከሁለተኛው የጣልያን ወረራ በኋላ ለኢትዮጵያ ጠንካራና ዘመናዊ የመከላከያ ሃይል ማስፈለጉን የተረዱት ንጉሥ ሃገሪቱ ባላት አነስተኛ ሃብትና በእርዳታ የሚያኮራ ሠራዊት ገንብተው እንደነበር ይታወሳል። ይህ ሰራዊት የተደራጀና በብዙ ልፋት ሕብረብሔር ሆኖ መቋቋሙ ብቻ ሳይሆን የሃገርን ሰላምና ሉዓላዊነት ለመጠበቅ ያለውን ብቃትም በተለያዩ አውደጦርነቶች አስመስክሯል። በካራማራ፤ በአፋቤት፤ በምፅዋ፤ በመቀሌ፤ በተሰነይ፤ በነጌሌ እየተዘዋወረ ሃገሩንና ባንዲራውን ሲጠብቅ ከፍተኛ ልምድ አዳብሯል። 

በዓለም አቀፍ ደረጃም በኮንጎና በኮርያ ተሰልፎ ባሳየው ብቃት የኢትዮጵያን ክብር ከፍ ያደረገና የተደነቀ ነበር። ተራው ሰራዊት በአገር መውደድና በብርቱ ዲሲፕሊን የታነፀ (esprit de corps)፣ መሪዎቹም በዓለም ዕውቅ በሆኑ የጦር ትምህርት ቤቶች ተምረው በከፍተኛ ብቃት የሰለጠኑ በመሆናቸው ሰራዊቱ ከኢትዮጵያም አልፎ የአፍሪካ ኩራት ለመሆን የበቃ እንደነበር ይታወሳል።   

ወታደራዊ መንግስት ስልጣን ላይ በቆየብት ዘመን ለስልጣን የታገሉት ኢህአፓና ሕወሃት የራሳቸውን ሰራዊት አደራጅተው የዛንትውልድ የኢትዮጵያ ሰራዊት በጫካና በከተማ ተዋግተውታል። ሁለቱም ሃይሎች ደርግን ቢአሸንፉ ህብረብሔራዊ የሆነውን የኢትዮጵያን መከላከያ ሰራዊት በትነው በቀይ ሠራዊት ለመተካት ዓልመው ነበር። የተወሰደውም ከማኦ ሴቱንግ ቀይ ጦር መርሕ የተኮረጀ እንደሆነ ይታመናል። ለዚህም ነው በ1983 ዓ. ም. ሕወሃት በለስ ቀንቶት አራት ኪሎን ሲቆጣጠር የመጀመሪያ ስራው የኢትዮጵያን ሰራዊት በትኖ በራሱ የሽፍታ ጦር በብርሃን ፍጥነት የተካው።  

በብዙ ሺህ የሚጠጋ ብቁና የሰለጠነ ሰራዊት እና የፖሊስ ሃይል በአንድ ጀምበር ተበትኖ በጎጥ ስነልቡና በታነፀ የሕውሃት አማፂ ሰራዊት ተተካ። በአሜሪካ ይደገፍ የነበረውን የሶማልያን ወራሪ ዶጋ አመድ ያደረገውና በአፍሪካ ጠንካራው የአየር ሃይል እንዳልነበረ ተደረገ። የኢትዮጵያ መከላከያም ከሕብረብሔርነት ወርዶ ወደ ጎጥ ሰራዊትነት ተቀየረ። ለሃገሩና ለባንዲራው ሳይሆን ለጎጡና ለመንደሩ የሚቆም ሰራዊት እና ፖሊስ ሆኖ ተደራጀ። 

ክቡርነትዎ በአንድ ወቅት እንዳሉት ‘ለአንድ አስተሳሰብና ለአንድ ተቋም እንዲአገለግል ሆኖ የተዋቀረ’ መከላከያ ስለተረከቡ በቆሸሸና በላሸቀ ቢሮክራሲ ውስጥ ሆኖ ማፁዳት ከባድ እንደሆነ የሁለት ዓመት ድካምዎ ምስክር ነው። ይህን ሰራዊት ከጎጥ እሳቤ ወደ ሃገር ጠባቂነት የማሸጋገሩ ስራ ብዙ ጊዜ ይወስዳል። ስለሆነም ኢትዮጵያን ለማጥፋት ሰፊ ዘምቻ እየተካሄደ ባለበት በአሁኑ ስዓት ሰራዊቱ አጋዥ ሃይል የሚአስፈልገው መሆኑ ጥርጥር የለውም።

በልዩ ልዩ ምክንያት ከመከላካያ እና ፖሊስ ሠራዊት አባልነት የተሰናበቱ በብዙ ሽህ የሚቆጠር የበቃ፤ የሰለጠነና የነቃ ሰራዊት መኖሩ ይታወቃል። ይህ ሰራዊት በተበተነበት ጊዜ ባለሌላ መዕረጉ በሃያዎች፤ መኮንኖቹ ደግሞ ከ3050 የዕድሜ ክልል እንደነበሩ ይገመታል። በአሁኑ ጊዜ ወታደሮች በሃምሳዎቹ መኮንኖች ደግሞ ከ50-75 ዓመት የዕደሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው።

አሁን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ወታደሮች በሃገር ቤትና በውጭ በጥሩ ወታደራዊ እና ለግዳጅ ብቁ በሆነ ሁኔታ ላይ እንዳሉ ይታመናል። የሃገራቸውን ዳር ድንበር ለመጠበቅ፤ የሕዝባቸውን ሰላም ለመታደግና ባንዳዎችን

በድጋሚ ለመዋጋት ዝግጁ እንደሆኑ ሲገልጹም እንሰማለን። ይህ ሃይል ብዙ ስልጠና የማያስፈልገው፤ ለሃገሩ ሉዓላዊነት ቀናዒ፤ ለባንዲራው ሟች፤ የነቃና የተደራጀ ስለሆነ በትንሽ ወጪና በአጭር ጊዜ ወደ ግዳጅ ማሰማራት ይቻላል የሚል እምነት አለ። 

ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር በተለይ መንግስትዎ በሁሉም አቅጣጫ ተወጥሮ ባለበት ወቅት ይህ ሃይል ብዙ እገዛ ሊአደርግ ይችላልና ቢታሰብበት መልካም ነው። በተለይ መደበኛው መከላከያ ሰራዊትና ፖሊስ ከየአቅጣጫው በሚነሱ ግጭቶች ተወጥሮ ባለበት ስዓት የቀድሞው ወታደር በደጀንነት ሊረዳ ይችላል። ለምሳሌ እንደ ሕዳሴው ግድብ ያሉትን የልማት አውታሮች፤ የምንግስት መስሪያበቶች፤፤ የባንክና የገንዘብ ተቋማትን፤ የገበያ ማዕከልን፤ የእምነትና ት/ቤቶችን፤ የጤናና ዩኒቨርሲቲ ተቋማትን፤ የመናህሪያና የቱሪዝም አውታሮችን፤ የአካባቢ ሰላምና ፀጥታን ወዘተ በመጠበቅና በማስጠበቅ እንዲሳተፉ ቢደረግ ለሃገራችን ሰላም ከፍተኛ አስተዋጽዖ በድጋሚ ሊአበረክቱ ይችላሉ። 

ከዚህ በተጨማሪ በከተማና በገጠር ከፍተኛ የሆነ ሕገወጥ የመሳሪያ ዝውውር እንዳለ ፖሊስ በየጊዜው ይገልጻል። ይህ ዓይነት መሳሪያ በበዛ ቁጥር ስርዓት አልበኝነት ያነግሳል። እየቆየ ሲሄድ የመንግስትን ሃይልም ይገዳደራል። በተለያየ ምክንያት ከሰራዊቱ የተገለሉ መለዮ ለባሾች ሕገወጥ መሳሪያ በመሰብሰብ ሊረዱ ስለሚችሉ ይህን እምቅ ሃይል አደራጅተው ቢጠቀሙበት ያተርፉበታል እንጅ አይከስሩበትም። 

ከሠራዊት የተለየውን ሃይል በተጠባባቂነት (reserve army) እና በሕዝባዊ ሰራዊትነት (people’s force) መጠቀም በብዙ ሃገሮች የተለመደ ነው። ካናዳ፤ እስራኤል እና ዩኤስ አሜሪካን የመሳሰሉ ሃገራት ተለዋጭ ሃይል በየጊዜው እየመለመሉ ለብዙ ተግባር የሚጠቀሙባቸው በመሆኑ በእኛ የሚጀመር አይሆንም። ይህን ቢአደርጉ እንደዓይንዎ ብሌን የሚሳሱላትን ኢትዮጵያን ከመፍረስ ይታደጓታል።

እርግጥ ነው ጽንፈኞች፤ የጎሳ ፖለቲካ አክራሪዎች ብዙ ስም እየለጠፉ ሊአደናቅፉዎት ይሞክራሉ። አሁን ከሚአደርሱት መደናቀፍና ወካባ የበለጠ ግን ሊአዋክቡዎት አይችሉም። በእርግጠኝነት መናገር ይሚቻለው ጉዳይ ቢኖር ሃገር ወዳዱ ኢትዮጵያዊ ይህን በማድረግዎ የሚደሰት መሆኑ ግልጽ ነው። ስለሆነም ሳይውል ሳያድር በተለያየ ምክንያት የተበተነውን የኢትዮጵያ ሰራዊት ለሃገሩ ዝብ እንዲቆም ያደርጉ ዘንድ ጥሪየን አቀርባለሁ። 

በጋራ ኢትዮጵያን እናድን፤ ሰማነህ ታ. ጀመረ
ኦታዋ፤ ካናዳ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here