ከዶ/ር ምህረቱ በለው፣
ጥቅምት 23 2013 ዓ ም
አማራ ኢትዮጵያን የተከበረች ሏአላዊ አገር ሆና እንድትኖር በተለያዩ ያገራችን ጠረፎች በታማኝነት ደሙን ሲያፈስ አጥንቱን ሲከሰክስ የኖረ ህዝብ ነው። ጎሽ ለልጇ ስትል ተወጋች እንደሚባለው፣ አሁንም የአገሩን የኢትዮጵያን አንድነት ቅድሚያ በመስጠቱና በመታገሱ በየቦታዉ ባሉ በዘር ፖለቲካ በታወሩ አረመኔዎች እንደከብት እየታረደ ነው። ነገ በሌላዉም ማህበረሰብ ላይ ይደርሳል። በዕርስ በርስ ጦርነት አትራፊ አይኖርም።
ይህን በአማራ ላይ የሚደረግ የተቀነባበረ የዘር ማጥፋት ማስቆምና የኢትዮጵያን አንድነት ማስቀጠል ታሪክ የተጣለበዎት የመጀመሪያ ግዴታዎና ሃላፊነትዎ ነው። ለዚህ ችግር ሁልጊዜ ወደ ወያኔ ብቻ መጠቆም መፍትሄ ሊሆን አይችልም። ወያኔ ኢትዮጵያን የሚያፈርስ ስርዓትና ስራ ሰርቶ ሂዷል። ይህን የማይረዳ የለም። የችግሩ ምንጭ ዘረኛው ህገመንግስትና በቋንቋ ላይ የተመስረተው አከላለል ነው። ይህን ችግር ካልፈቱ መፍትሄ የለም። ዘረኛውን ህገመንግስት፣ አገሪቱን በጎሳ የከፋፈላትን አስተዳደርና በአማራ ጥላቻ የተሞሉትን የጎሳ ፖለቲካ መሪዎች ከጎን ይዞ መፍትሄ ማምጣት በፍጹም አይቻልም።
ጠቅላይ ሚኒስተር አቢይ፤
ኢትዮጵያንና ህዝቧን ለማዳን የቀረዎት ብዙም አማራጭ የለም። በዚህ ሁኔታና ዉጥረት መጪዉን ምርጫ ሰላማዊ ማድረግ አይቻልም። ስለዚህ ኢትዮጵያንና ህዝቧን ለማዳን የሚከተሉትን እንዲያደርጉ በትህትና እጠይቃለሁ።
- ህዉሃትና ኦነግ የተከሉት የጎሳ አከላለልና የጎሳ ህገመንግስት የፈጠረብንን አደጋና የደረሰብንን ጉዳት፣ የደቀነብንን አገር የማፍረስ አደጋና የህዝብ ስደት፣ ከአገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያንና ሲቪክ ማህበራት ጋር በመሆን፣ ለኢትዮጵያዊያንና ለዓለምአቀፍ ማህበረሰብ መግለጽ ማስረዳት፣
- የክልል ሚሊሻዎች አደረጃጀትን በማፍረስ ወደመከላከያዉ በማዋሃድ ከመንደራቸዉ በማራቅ በአገሪቱ ዙሪያ ማሰራጨት፣
- መከላከያዉን አጠናክረዉ፣ በጠንካራ ዲሲፕሊን እንዲመራ በማድረግ፣ የአገር ሏአላዊነትን እንዲያስቀድም በማድረግ፣ ቢያንስ ለሁለት ዓመታት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ፣ ለመከላከያዉ የአገር አንድነትና ሰላምን እንዲያስጠብቅ ልዩ ትዕዛዝ በመስጠት፣
- የጎሳ ጥላቻ የፈጠረውን ህገመንግስትና የጎሳ አከላለል ማፍረስ፣
- የጎሳ ፖለቲካንና አደረጃጀት በአስቸኳይ አዋጅ ማገድ፣ በጎሳ ፖለቲካና በወያኔ ተጠምቀው ያደጉት የጎሳ ፖለቲካ መሪዎች፣ የብልፅግና መሪዎችን ጭምር፣ ሁሉንም ከሃላፊነታቸው በማንሳት እንደችሎታቸዉ ወደሲቪል ስራ እንዲገቡ በማድረግ፣ አገሪቱን፣ ከፖለቲካ ድርጅት አባልነት ነጻ በሆኑና ወደፊት የፖለቲካ ስልጣን ለመያዝ በማይፈልጉ፣ ከተለያየ ዘርፍ በተዉጣጡ ባለሙያዎችና (Council of Technocrats ) የሽማግሌዎች መማክርት ማስተዳደር፣ በየደረጃው ባለሙያዎች የአመራር ስራዉን እንዲሰሩ ማድረግ፣
- ኢትዮጵያዊያንን በጎሳቸው ወይንም በሃይማኖት ላይ በማተኮር ጉዳት የሚያደርሱ፣ የህዝብን ሰርቶ የመኖርና የመንቀሳቀስ መብት በሚጋፉ ላይ የመጨረሻውን ቅጣት መስጠት፣
- በሁለት ወይንም ሶስት ዓመታት ዉስጥ ምርጫ እንደሚደረግ ለህዝቡ ቃል መግባትና ዝግጅት ማድረግ፣
- ህዉሃት ይህን ጥሪ እንዲቀበል አዋጅ ማወጅ፣ ለትግራይ ህዝብ ጥሪ ማቅረብ፣ ህዉሃት ጥሪውን ካልተቀበለ ጦሩ በህዉሃት መሪዎች ላይ እርምጃ እንዲወስድ ትዕዛዝ መስጠት፣
- ህዝቡ ለራሱ ህይዎትና ለአገሩ ሲል ይህን ጥሪ በመቀበል በትዕግስት ከመንግስት ጋር እንዲተባበርና አገሩንና ራሱን እንዲጠብቅ፣ በልማቱ ስራ እንዲሳተፍ ጥሪ ማቅረብ፣
- የሃይማኖት ድርጅቶችና የሲቪል ድርጅቶች፣ ለሰላምና አገር አንድነት ጥበቃ የበኩላቸዉን አስተዋጾ እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረብ።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
ለሀገራችን ደህንነት ችግር የሆኑብንን ማጥፋት