spot_img
Thursday, November 30, 2023
Homeነፃ አስተያየትየጠቅላዩ ችግር የሃገር ችግር (በዮርዳኖስ ሃይለማርያም )

የጠቅላዩ ችግር የሃገር ችግር (በዮርዳኖስ ሃይለማርያም )

advertisement

በዮርዳኖስ ሃይለማርያም 
yordimassa@yahoo.com
ጥቅምት 25 ፣ 2013 ዓ ም

ቶሮንቶ ካናዳ

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ከበፊትም ጀምሮ ጣጣ የበዛበትና በተለያዩ ጊዜያት ችግሮች አንዴ ብቅ አንዴ ዝም በማለት ለጊዜውም ቢሆን እየተዳፈነ የመጣ የፖለቲካ ምህዳር ነው። ያለፉት ስርዓታት መቼም በግልፅ የመብት ጥያቄን ያነሳ እየደፈጠጡና ጥያቄ ለማቅረብ የሚፈልጉትንም በቀጥታ በመጉዳት ወይም እንዲሸማቀቁ በማድረግ ቢያንስ ባህሪያቸውን ቀድመው በግልፅ አሳውቀው ተፈርተው ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን በጉልበት እየገዙ ለመቆየት ችለው ነበር። ከሚያዚያ ወር 2010 ዓ/ም ጀምሮ የተፈጠረው ግን እጅጉን ግራ የሚያጋባና ለዳኝነት የማይመች ሆኖ ሃገራችን ሲያመሳቅልና ችግሮቿን ሲያወሳስን ቆይቶ ይባስ ብሎ ሃገራችን አሁን ላለበት አስፈሪ ደረጃ መድረሱ ያሳዝናል። 

በሚያዚያ ወር 2010 ዓ/ም ዶክተር ዓቢይ አሕመድ የተባሉ የኢህአዴግ ባለስልጣንና ዋና የስለላ መረቡ ባለሙያ እንዲሁ በተለያዩ ደረጃዎች ሃላፊና የመረቡ ምክትል ሃላፊ ሆነው የሰሩ በአንድ ወቅትም የስለላ መረቡ ዋና ዳይሬክተር የነበሩ ሰው ከነበሩበት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትርነት ደረጃ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ሃገሪቱን ከገባችበት አደገኛ ሁኔታ መርተው ወደተሻለ ሁኔታ ይለውጧታል ተብለው በራሱ በኢህአዴግ መመረጣቸው ተሰማ። እሳቸው አንደበተ ርቱእ ሰው በመሆናቸው ኢትዮጵያዊነትን፣ ዲሞክራሲን፣ ሰብአዊ መብትን ባጠቃላይ መልካም መፃኢ ዘመንን በማስመልከት እጅግ በተዋቡ ቃላት በፓርላማው ፊት ቀርበው ሲናገሩ ሃገራዊ ስሜትና ብሄራዊ አንድነት ርቆት የነበረው ኢትዮጵያዊ ሁሉ በደስታ ተሞላ፣ በተለያዩ ሃገራት በተለይም በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ በመዘዋወር ከፕረዚደንት ኦባማ የመጀመሪያ የምርጫ ዘመን ባልተናነሰ መልኩ እንደ ተወዳጅ ፊልም አክተር ከፍተኛ አቀባበልና ሙገሳ፣ እግራቸውን እስከ መሳም የሄደ የፍቅር አገላለፅ ተደረገላቸው። በዳያስፖራ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ሁሉ ባገሩ ከፍተኛ ተስፋ አሳደረ። አንዳንዱም ተቻኩለው የነበራቸውን ስራ ጥለውና ቤታቸውን ሸጠው ወዳለሟት “ዲሞክራሲያዊትና የበለፀገች ኢትዮጵያ” ጉዟቸውን አቀኑ፡ የኝህ ሰው ንግግር ዕውነት መስሏቸው። 

ይሁን እንጂ እኝህ ጠቅላይ ሚኒስትር ከአንደበተኝነት የዘለለ ተግባራዊ ውጤት ማሳየት ስላልቻሉ ባገራችን በተለያዩ ቦታዎች በርካታ ሁከቶች መቀስቀስ ጀመሩ። በመጀመሪያዎቹ አንድ መቶ ቀናት ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኤርትራ መሪ ጋር እርቅ በመፈፀም በሁለቱ ሃገራት መካከል ሰላም ወረደ ተብሎ ተዘመረ፣ ተዘፈነ፣ ጉሮ ወሸባም ተባለ። ያኔ የዲፕሎማሲ፣ የፖለትካና የሃገር ለሃገር ግንኙነት ባለሙያዎች በጠቅላይ ሚኒስትሩና በኤርትራው መሪ በዓረብ ሃገራት አማላጅነት እየተፈረሙ የነበሩ ስምምነቶች ግልፅነት ይጎድላቸዋል የሚል ከባድ ትችት ቢሰነዘርም ያ ከዘር ጥላቻና ከተለያዩ ፖለቲካዊ ቀውስ ጋር አብሮ የኖረ ህዝብ እነዚህን ወሳኝ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የግልፅነት ችግርና የዲፕሎማሲ ስህተቶች ለማጤንና ለመረዳት ፍላጎት አልነበረውም።

ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ሁሉም ሰው በየዕለቱ ከሚያየውና ከሚሰማው ሁኔታ በመነሳት ክፉኛ መደናገጥ ጀመረ። መጠየቅም ጀመረ። ምክንያቱም ዕርቅ ተብሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓለም መድረክ እስከ ኖቬል ያስሸለመው ተግባር ኖቬሉን ሲሸለሙ እንኳን በቦታው አልነበረም። የተደረገው ዕርቅ የመሪዎቹን ስምምነት አጠናከረ እንጂ በህዝብና በህዝብ መካከል ያለውን ሰላማዊ ግንኙነት ማስቀጠል አልቻለም። በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል ለጊዜው ተከፍቶ የነበረው ድንበር ከአውሮፕላን በስተቀር ወደ ነበረበት ተመልሶ ተዘግቷል። ለጊዜው አሰራር ለማመቻቸት ነው የተዘጋው ቢባልም ይኸው ከተዘጋ ሁለት ዓመት አለፈው። በአውሮፕላንም ቢሆን እንደተባለው በመታወቂያና በቀላል መንገድ መገናኘት ቆሞ የኤርትራ መንግስት ከኢትዮጵያ የሚነሱ ነገሮችን ሁሉ በጥርጣሬ ስለሚመለከት በተለይም የትግራይ ተወላጆች ኤርትራ የሚገኙ ዘመዶቻቸውን ለመጠየቅ ወደ ኤርትራ ሲሄዱ የኤርትራ መንግስት ወታደሮች ሰላማዊውን ኢትዮጵያዊ እንደ ወንጀለኛ የመመርመር ስራ ተያያዙት። በዚህም ምክንያት በሁለቱም ሃገራት ተጀመረ የተባለው ሰላማዊ ግንኙነት የትም ሳይደርስ ጨነገፈ። 

እኝህ ስሜታዊና ግብታዊ የሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር መጀመሪያ ከኤርትራ ጋር ያለውን ትክክለኛ ውልና ግንኙነት ለኢትዮጵያ ህዝብ በምስጢር እንዲያዝበት አድርገው ሲያበቁ በቀይ ባህር ላይ የኢትዮጵያ ባህር ሃይል እናቋቁማለን እስከሚል የማይተገበር ቅዠት ለኢትዮጵያ ህዝብ ነግረዋል። ከዚህም ሌላ የህዝቡን ድህነትና ኋላ ቀርነት እንደ ፖለቲካ መጠቀሚያ በመውሰድ ያልፍልናል ብሎ እንዲጎመዥና በራሱ መንገድ የሚፍጨረጨረውን ሳይቀር የሚያስተጓጉሉ በርካታ የሌሉ የሃሰት ፕሮጀክቶችን በመዘርዘር ሃገራችን በአንድ ዓመት የበለፀገች ሃገር የምትሆን እስኪመስለን ድረስ አሞኝተውናል። ለምሳሌ በለጋሃር ፕሮጀክት ላይ የዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ መንግስት ራሱን የቻለ የከተማ ውስጥ ዘመናዊ ከተማ ይቆረቁራል ብለው ነበር። ያ ፕሮጀክት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንደሚጀመርና ሲጀመርም ለብዙ መቶ ሺዎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥር ተተንብዮ ሲያበቃ ዛሬ ሶስተኛ የስልጣን ዘመናቸው ላይ ቆመን ስናስበው ግን ፕሮጀክቱ የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል። የመንገድም ሲነሳ ከአዳማ አዋሽ አርባ፣ እንዲሁም ከአዋሽ አርባ ድሬዳዋና ከድሬዳዋ ደወሌ ሰፊና ባንዴ በርካታ መኪኖች ማስተናገድ የሚችል ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ የጠበቀ አስፋልት ማለትም ሃይወይ ይሰራል ብለው ነበር። እነዚህ ፕሮጀክቶች እንኳንስ ሊሰሩና አገልግሎት ሊሰጡ ባለው አንድ መንገድ ተመላልሰው ሰርተው ልጆቻቸውን ያሳድጉ የነብሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በተፈተረው የፀጥታ መደፍረስ ምክንያት በመንገዶቹ መጠቀም ይሚችሉበት ሁኔታ የለም። እነዚህን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሃሰት ተስፋዎች በምሳሌነት አቀረብኩ እንጂ እኝህ ጠቅላይ ሚኒስትር በደረሱበት ሁሉ ተሰብሳቢውን ሰው ለማስደሰት ብቻ በፍፁም ያልታቀዱና በህሊናቸው ያልነበሩ ነገሮችን በቅፅበት በመፈብረክ ሲያወሩና በጋሻ ጃግሬዎቻቸው በኩል እውነት እንዲመስሉ ሲያስወሩ ከርመዋል። የህዝብ ጉዳይ ላይም አንድ ጊዜ ወርቅ ነው ያሉትን ህዝብ በሌላ መድረክ ላይ ደግሞ የተለያዩ ቅፅል ስሞችን በመስጠት የቀን ጅብና ፀጉረ ልውጥ በማለት ከተለያዩ የሃገራችን ህዝቦች ጋር ለጠብ እንዲጋለጡ ሞክረዋል። አንዳንድ ክልሎች ላይ ደግሞ አንዱ ህዝብ በሌላኛው ህዝብ ላይ እንዲነሳ አሊያም መቃቃር እንዲሰማው ቁጥር ስፍር የሌላቸው መጥፎ የፖለቲካ መርዝ ሲዘሩ ነበር፡ አሁንም ይህንኑ ተግባራቸው በመፈፀም ላይ ይገኛሉ። ለምሳሌ ወደ ባሌ ሄደው ለህዝብ ንግግር ሲያደርጉ “ብልፅግና ፓርቲን ያቋቋምነው ለናንተ ለኦሮሞዎች ነው” ሲሉ ወደ ወሎ ሄደው ደግሞ የዛሬ መቶ ሰላሳና መቶ ሃምሳ ዓመታት የነበሩ አከባብያዊ ግጭቶችን የዚህ ትውልድ ዕዳ ለማድረግ ስለቦሩ ሜዳ ውጊያ ተርከዋል። በዚሁ ድርጊታቸው ሙስሊሙ ህብረተሰብ የዛሬ መቶ ሃምሳ ዓመት የነበረውን ትግርኛ ተናጋሪ ንጉስ ፈፀመው ስለተባለ በማስረጃ ያልተደገፈ ትረካ በማንሳት ሃይማኖታዊ የሆነ ቅራኔ እንዲፈጠር ሞክረዋል።  

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሄዱበት ሁሉ ለመድረኩ የሚመጥን ሳይሆን እዚያ መድረክ ላይ ያሉ ያልሰለጠኑና ያልተማሩ ህዝቦች ይፈልጉታል የሚሉትን ሃሰት በማዘጋጀት ተሰብሳቢውን አስጨብጭበው ስለመውጣት እንጂ በሃገሪቱ ስላለው ተጨባጭ ሁኔታ ከማንም ጋር ለመወያየት ዝግጁ ያልሆኑ በጣም ደካማና የመሪነት ባህሪይ ያልተላበሱ ሰው በመሆናቸው ሃገራችን ከነበረችበት የአፈና ስርዓት ወጣች ብለን ተስፋ ባደረግንበት ማግስት ከነበረው አፋኝ ስርዓት በባሰ ነፍሰ ገዳይና አሳሪ የሆነ ስርዓት በማስፈን ላይ ይገኛሉ። እሳቸው ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በፓርላሜንታዊም ይሁን በፕረዚደንታዊ ስርዓታት ላይ የሚታዩትን የጋራ አመራር (group leadership) በማጥፋት የአንድ ሰው መንግስትና ፓርቲ አቋቁመው ለሁሉም ክልሎች ትግራይን ሳይጨምር የራሳቸው ምስለኔ ልከው ከህዝብ አሰራርና ከዲሞክራሲ ባህሪይ ውጭ የሆነ ተግባር በመፈፀማቸው በህዝቡ ላይ የነበራቸው ተቀባይነት በከፍትኛ ፍጥነት ቡን ብሎ አሁን በጣም የተጠሉና የሚናገሩት የማይሰማላቸው መሪ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።

እሳቸው ወደ ስልጣን ሲመጡ ማንም ሰው ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ ለእስርም ሆነ ለሌላ ነገር አይጋለጥም ብለው ነበር። ከሁሉም በላይ ደግሞ አጣርተን ማሰር እንጂ አስረን አናጣራም ብለው እንደነበር ይታወሳል። ይህ ባልይ ብጥቂት ጊዜ ውስጥ ግን ስድስት ሺ የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑና የሳቸውን መንግስት ይቃወማሉ ተብለው የተጠረጠሩ ዜጎች በጦር ማሰልጠኛው አፍነው በማስቀመጥ የዲሞክራሲና የፍትህ ጠላት መሆናቸው በግልፅ አሳይተውናል። በተለይ በዚህ ዓመት ደግሞ በርካታ የየብሄሩና የየፓርቲው ወሳኝ ሰዎች ወደ እስር ቤት እንዲወርዱ ተደርጓል። ለምሳሌ ታዋቂው የሰብአዊ መብት ተሟጋችና ፖለቲከኛ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ልቦለድ በመሰለና ከሱ ባህሪያት ጋር ፍፁም ግንኙነት በሌለው ርዕስ ተከሶ በፍትህ ማጣት እስር ቤት ውስጥ እንዲሰቃይ አድርገውታል። የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አመራሮች እነ ጃዋር መሐመድና በቀለ ገርባ በግልፅ ባልተቀመጠ ክስ በየእስርቤቱ እንዲታጎሩ ተደርገዋል። ታዋውና በሳሉ የፖለቲካ ሰው አቶ ልደቱ አያሌው በማይመለከተው ጉዳይ ተከሶ እስር ቤት ከገባ በኋላ ፍርድ ቤት ሶስት ጊዜ በዋስትና እንዲለቀቅ ቢያዝም ፖሊስ የፖአልቲካ ውሳኔ ነው በሚል አልፈታም በማለት የፍርድ ቤት ትዕዛዝን አልፈፅምም ብሏል። ይህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለሚፈልጉት እንጂ ለፍርድ ቤት አልታዘዝም የሚል ፖሊስ ስልጣኑን ይዞ መቀጠል አይችልም ነበር። ማንኛውም ሰው ፍርድ ቤት ይፈታ ብሎት ካልተፈታ ዶክተር ዓቢይ እየገነቡት ያለ መንግስት ከፋሽት መንግስታት አስተሳሰብ የራቀ አይደለም ማለት ነው። 

እኝህ ግብዝና ሁሌ እኔ ብቻ አዋቂ የሚል መንፈስ የተጠናወታቸው ጠቅላይ ሚኒስት ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ስለራሳቸው ምስል ግንባታ በተለያዩ ማስ ሚዲያዎች ብዙ ከመስራት ያለፈ ሃገርንና ህዝብን ሊያረጋጋና የህግ የበላይነት ሊያረጋግጥ የሚያስችል የመንግስት መዋቅር መዘርጋት አልቻሉም። ይህ የሆነውም መንግስትን ለመምራት የሚያስችል ብቃትና ዝግጅት ያልብ=ነበራቸው ከመሆናቸውም በላይ አሁንም ቢሆን ጠይቀው ለመረዳትና ለመማር ዝግጁ ባለመሆናቸው ችግሩ እየተባባሰ እንጂ እየተሻሻለ ሊሄድ አልቻለም። እሳቸው ኢትዮጵያ የምትባለው ሰፊና የአንድ መቶ አስራ አራት ሚሊዮን ሃገር አዲስ አበባ ብቻ ስለምትመስላቸው በቤተ መንግስታቸው ታዋቂና ሃብታም ሰዎችን ሰብስበው እራት በማብላትና እራሳቸውን እንደ ባለፀጋ በመቁጠር ብሉልኝ ጠጡልኝ ስላሉ ብቻ የሀገሪቱ ውስብስብ ችግር የሚፈታ ይመስላቸዋል። በርካታ ያልተመለሱ የህዝብ ጥያቄዎች ለመስማት ምንም ፍላጎት የሌላቸው መሪ ኮሽ ባለ ቁጥር የአመራር ድክመት መሆኑን ሳይሆን አንድ የሆነ ቡድን ያስከተለው ችግር መስሎ እንዲታይ የሃሰት ፕሮፓጋንዳና ዶክመታሪ ሲያሰሩ ጊዜያቸውን በማባከን ላይ ይውላሉ። 

ለምሳሌ በኢትዮጵያ ከባባድ የሆኑ በርካታ ችግሮች ቢኖሩም ዋናዋናዎቹን መጥቀስ ካስፈለገ ግን ስራ አጥነት፣ ድህነት፣ የዜጎች በሰላም ወጥቶ መመለስ፣ የከፋ ድህነት፣ የኢኮኖሚ ውድቀት እንድሁም የህብረተሰብ አመለከኣከት ብልሽት ብናነሳ ለጊዜው በቂ ናቸው። እነዚህ በከፍተኛ ሁኔታ ፈጠው የሚታዩባት ሃገር እኝህ ጠቅላይ ሚኒስትር ከአዋቂዎች ጋር ተመካክረው ፍኖተ ካርታ ሳይቀርፁ ዝም ብለው በነሲብ ለመምራት መሞከራቸው ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባ ከተማ ፓርክ አሰርተው ሃብታሞችና ቱሪስቶች እንዲወዱላቸው በማሰብ ያ የፈጠጠ ሃገራዊ ችግር ወደ ጎን በመተው አንድ ፕሮጀክት መሪና ካቦዎች ከጉልበት ሰራተኞች ጋር በመሆን ሊሰሩት የሚገባ ተራ ስራ እሳቸው ቆመው ሲያሰሩና ሲያወሩ ይውላሉ። 

ስለ ዕውነት የትኛውንም ከተማ ማሳመር በጣም ተገቢና ደስ የሚል ተግባር ነው። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ዶክተር ዓቢይ ጊዜያቸውንና የሃገርን ሃብት እያባከኑ የሚውሉበት ያሉ የአዲስ አበባ ፓርክ ስራ በየክልሉ በዘሩ ምክንያት ለሚጨፈጨፈው ኢትዮጵያዊ ኢምንት ብቻ ሳይሆን እንደ ቀልድ መታየት ያለበት ያላዋቂ ተግባር ነው።

በተለይ ደግሞ የዜጎችን በሰላም ወጥቶ የመግባት መብት ከማንኛውም ዘመን በባሰ ሁኔታ በዚህ ጊዜ አዳጋች ሆኗል፣ በርካታ ሰዎች በዘራቸውና በሃይማኖታቸው ምክንያት ሲዘረፉ፣ ሲደበደቡና ሲገደሉ እሳቸው ሃብታሞች ሄደው ስለሚዝናኑበት የእንጦጦ ፓርክ እንደ ትልቅ ስራ በመተረክ ህዝቡን ሊያሞኙት ይሞክራሉ። ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው ሸገር ፓርክ ብለው ያሰሩትን መናፈሻ ሲያስመርቁ ወታደራዊ ማርሽና የኮማንዶ ትርኢት በቴሌቪዥን ቀጥታ ስርጭት እንዲተላለፍ ማድረጋቸው ነው። በሳቸው ደካማ አመራርና የፖለቲካ ሴራ ምክንያት አሁን ኢትዮጵያ ልተበታተን ጫፍ ደርሳለች። በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሃሰት ሪፖርት እንዲሁም በግላቸው በሚያሰማሩዋቸው አደገኛ የፖለቲካ ሃሳብ የሚያራምዱ ዘረኛ ሰዎች ሳቢያ ብዙ ዜጎች በዘር ግጭት ውስጥ ደማቸው በመፍሰስ ላይ ይገኛል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህዝቡ ላይ ተከማችተው መልስ የሚሹ በርካታ ጥያቄዎች እንዳይነሱ ከሚጠቀሙባቸው ስትራቴጂዎች ሁለቱን ብንወስድ አንዱ መልካም ስራ ሳይሰራ የተሰራ የሚያስመስል ዜናና የሃሰት ፕሮጀክቶች በመንገር በከንቱ ተስፋ ጊዜ ይገዛሉ። ሁለተኛው ደግሞ በፓርክ ምረቃና በበዓል ስም ወጠምሻ ኮማንዶዎች፣ ስናይፐር የታጠቁ ወታደሮችና ከፍተኛ የከባድ መሳሪያ ትርኢት በማከናወን በፊት በህዝቡ ላይ የነበረውን ፍርሃት እንዲቀሰቀስ መሞከር ነው። ከዚህ ጎን ለጎንም በህዝቡ ላይ በየቀኑ አዳዲስ አስጨናቂ ዜናዎችና አጀንዳዎች በመፍጠር ህዝቡ መሰረታዊ የሆኑ ጥያቄዎችን እንዳያነሳ ማለያየት ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ከየትኛውም ስርዓት በባሰ በዚህ ጠቅላይ ሚኒስትር ዘመን በዘር ተከፋፍሎ እርስ በርስ ለመጋጨት የተቃረበበት ዘመን ላይ ነው። አሁን ሁሉም ሰው በግድ ስለ ዘሩ እንዲያስብ ተደርጓል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በፈጠሩት ችግር ሰላማዊ ሰዎች በገጀራ ታርደዋል። ህፃናት ካለ ወላጅ ቀርተዋል፣ ሴቶች ተደፍረዋል፣ ቤቶች ተቃጥለዋል። ዛሬም ቢሆን ይህ ችግር እየተባባሰ እንጂ እየታረመ አይደለም። 

እኝህ ታሪካዊ አጋጣሚ በተሳሳተ ወንበር ላይ ያስቀመጣቸው ጠቅላይ ሚኒስትር በፊት በደህንነትና ስለላ መረብ ሃላፊነት ሲሰሩ ፀረ ኢትዮጵያ ሲዋጉና ሲያደራጁ ለነበሩት ለኤርትራው ፕረዚደንት ሃገራዊ ምስጢር አሳልፈው ይሰጡ እንደነበር በማስረጃ ተነግሯል። አሁንም ቢሆን ከንደዚህ ዓይነቱ ሃገራዊ ክህደት ወጥተዋል ለማለት የሚያስችል ምንም ተጨባጭ ተግባራዊ ምላሽ የለም። በቅርቡ ኢትዮጵያ ተበታትና ማየት ከሚፈልጉት የኤርትራ ፕረዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር የባልና የሚስት ያህል ከፕሮቶኮል ህግ ባፈነገጠ መልኩ እየተሻሹና እየተቃቀፉ በፊት የነበረው መንግስት የሰራቸውን ፕሮጀክቶች አብረው ሲመርቁ ይታያሉ። በሻሸመኔ፣ በአሳሳ፣ በአርሲ ነገሌ፣ በባሌ ሮቤና በበርካታ የኦሮሚያ ወረዳዎች ቁጥር ስፍር የሌላቸው ሰዎች በግፍ ሲጨፈጨፉ ባከባቢው ለነበሩት የመከላከያና የፖሊስ ሃይላት እንዳይተኩሱና ማንንም እንዳያስሩ መመሪያ ማስተለልፋቸውን ስንሰማ የዚህ ሰው ዓላማ ኢትዮጵያን ማፈራረስ እንዳይሆን ያጠራጥራል።

እኝህ ጠቅላይ ሚኒስትር በአንድ በኩል ስለሃገራዊ ደህንነት ሲሰብኩ በሌላ በኩል ደግሞ ሃገራዊ ደህንነት የህዝብ ደህንነት ከማስከበር ጋር ግንኙነት የሌለው ይመስል ሰዎች ሲገደሉ አንድ ቀን ቀደም ብለው በማይረባ ምክንያት ካገር ይወጣሉ ወይም ደግሞ ሌላ ፕሮጀክት ላይ ሲያወሩ ይውላሉ። በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሲጨፈጨፉ እሳቸው ለአንድ ሴኮንድም በቲሌቪዥን ቀርበው የሃዘን መግለጫ ሲያሰሙና ባንዲራ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ሲያዙ አይታዩም። ለሳቸው ኢትዮጵያ ማለት ስልጣናቸው ብቻ እንደሆነ አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ ግልፅ እየሆነለት መጥቷል።

ክፍል ሁለት

እኛ ኢትዮጵያውያን ላለፉት ሶስት ሺ ዘመናት ከሰማንያ በላይ ብሄርና ብሄረሰቦች ይህችን ሃገር ሃገራችን ብለን፣ እንዲሁም በተለያዩ የሃይማኖትና የዕምነት ተቋማት እንደየዕምነታችን ተከባብረን በኖርባት ምድር ላይ ካባቶቻችንና ካለፉት መሪዎች በውርስነት የተቀበልናቸው በርካታ መልክምና አንዳንድ ቁርሾዎች መኖራቸው አይካድም። ካለፈው ታሪካችን ተምረን ብዙ ተአምራት የምንሰራበትና ከመጥፎ ታሪኮቻችን ደግሞ ትምህርት ወስደን እነዚህን መጥፎ ቅርሶች ወደ መልካም በመቀየር ከሰው በታች ሆነን እንድታይ እያደረገን ያለውን ድህነት ታሪክ ሆኖ እንዲቀርና በዓለም መድረክ ላይ ቀና ብለን እንድንቆም የሚያስችል ተግባር በመፈፀም ፈንታ ሊፈቱ የማይችሉና መልስ የሌላቸው ጥያቄዎች ላይ እራሳችንን በማድከም፣ ታሪክን እንደ አንድ መማሪያ ሃሳብ ሳይሆን እንደ ኑሮአችን በመውሰድ የመልካም ታሪክ ሃገር እያልን ያቆየናትን ሃገር በመጥፎ ታሪክ ተክተን ሃገሪቱን ለማሻሻል ሳይሆን ሁላችንም በየፊናችን አኩራፊና ነቃፊ ብቻ ሆነ ሃገራችንን ወደ መጨረሻ እርከን እየገፋት እንገኛለን። 

አንዳንዴ መንግስት የወጣበትን ህዝብ ይመስላል ሲባል ዕውነት አይመስለኝም ነበር ወይም ከነማሻሻያው ልቀበለው የሚል ዕምነት ነብረኝ። አሁን ሳየው ግን ነገሩን ደግሜ ደጋግሜ እንዳጤነው እገደዳለሁ። ባሁኑ ሰኦእት በሃገራችን የፈጠጡ የሰላምና የፍትህ፣ የኢኮኖሚ፣ የዜጎች በሰላም ወጥቶ በሰላም መመለስ መብቶች ወዘተ ከባባድ ህገመንግስታዊ ጥያቄዎች ፈጠው የሚታዩበት ልዩ ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን። ይሁን እንጂ መንግስት እነዚህን አንገብጋቢ የፖለቲካ፣ የማህበራዊና የኢኮኖሚ ጥያቄዎችን ለራሱ በሚመቸው መንገድ ብቻ በመተርጎም ለራሱ የፖአልቲካ ፍጆታነት ሲያውላቸው ማየት እጅጉን የሚያሳዝን ቢሆንም በሃገራችን ውስጥ ያለ ዕውነታ ነው። 

አሁን ሃገራችንን እየመሩ ያሉ ልሳናቸውን እንጂ ህሊናቸውን ባግባቡ ያልገሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ስልጣን በመጡ በመጀመሪያዎቹ ወራት “ካሁን በኋላ ወደፊት እንጂ ወደኋላ ማየት የለም፣ ትናንት ለትናንት መተው አለበት። ያለፉት በደሎችን ሁሉ ይቅር ብለን ሁላችንም ኢትዮጵያውያን እጅ ለእጅ ተያይዘን ወደ ብልፅግና ከፍታ እንወጣለን። ወዘተ ” ሲሉ ህዝቡ እንደ አንድ መሪ ሳይሆን ከፈጣሪ መልእክተኛ ወይም ነቢይ ጋር እስከ ማነፃፀር የሄደ ከፍተኛ ድጋፍና ተቀባይነት አስገኝቶላቸው ነበር። ይሁን እንጂ ቃላቸው ከቃል በላይ ሳይሆን ቅርቶ በተለይም ህወሓትን ያጠቁ እየመሰላቸው የትግራይ ህዝብ ላይ ከፍተኛ የሆነ የስነ ልቦናና የኢኮኖሚ ጦርነት አወጁበት፣ በየአከባቢው በብሄራቸው ምክንያትየሚታረዱ አማሮች፣ ትግራዮችና ሌሎች ብሄረሰቦችንም እንዳልተበደሉ በተለያዩ መንገዶች ድምፃቸው ወደ ዓለም ህብረተሰብ እንዳይደርስ የራሳቸው ሚዲያዎችን በማደራጀትና በመክፈል፣ የሃሰት ፕሮፓጋንዳ በማስነዛትና የሰዎችን ዕልቂት እንደ አንድ ተራ ክስተት በማቅረብ በሃገርና በወገን ላይ ይህ ነው የማይባል ኪሳራ አድርሰዋል። 

በተልይም ደግሞ የራሱን ዜጎች በየምድረበዳውና በየባህሩ እየጠፋ እንዲቀር ያደረገና ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ስልጣን ላይ በጉልበት ተቀምጦ የተቃወመውን በመግደልና በማጥፋት የሚታወቀው ፋሺስቱ የኤርትራ ፕረዚደንት እንደ ዋነኛ አማካሪውና ወዳጅ አድርጎ መንቀሳቀሱ ይህ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢያንስ ስለኢትዮጵያ ደንታ የሌለው እንዲሁም በተገኘ መንገድ ሁሉ የፈሰሰ ደም ፈሶ የሱ ስልጣን ማስቀጠል የሚሻ መሆኑን በህዝቡ ዘንድ እየታወቀ መጥቷል። ሃገራችን ኢትዮጵያ ካልተበታተነች በስተቀር ኤርትራ ሰላም አታገንም እንደፈለግነውም ኢትዮጵያን መበዝበዝ አንችልም ብለው የሚያምኑና በፅናት የሚታገሉ ጠላት እንደ አንድ አማካሪና መሪ አድርጎ መቀበል በራሱ የሚናገረው ከባድ የሆነ ምስጢር አለ። ከዚያም በላይ እኝህ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰዎች በግፍ ተገደሉ ሲባሉ አስከሬንን በብሄር በመከፋፈል ከዚህ ብሄር ይህንን ያህል ሰው ሞተ ከማለት በስተቀር እነዚህ ንፁሃን ዜጎች በሳቸው አመራር ልፍስፍስነት አሊያም ለዜጎች ጥበቃ ለማድረግ ካለመፈለጋቸው የተነሳ መሞታቸውን እንኳ ለማሰብ አይፈልጉም። 

በተለዩ ጊዜያ በሃገራችን ከተራ አርሶ አደር ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የመንግስት ባልስልጣናት በተለያዩ ጊዜያት ሲገደሉ መንግስት ዜጎቹን በሰላም የማኖር አቅሙ የመከነና መጣልን ተብሎ የተዘመረለት የዶክተር ዓቢይ ለውጥም መጨንገፉ በግልፅ ታይቷል። ከዚህ በኋላ ሌላ ተአምር መጥቶይህንን የበሰበሰና የወደቀ ስርዓት ያነሳዋልየሚል ተስፋ ባይንርም እንኳ አሁንም ሃገሪቱ ሙሉ በሙሉ ከመበታተኗ በፊት ዶክተሩ ተፀፅተው ሃገሪቱን ብቃት ላላቸው ሽማግሌዎችና የሽግግር መንግስት ማስረከብ ቢችሉ ቢያንስ ላለፈ ይቅርታ የሌለው ጥፋታቸው ማካካሻ ሆኖ ያገለግላል። ሃገራችን በየትኛውም ዘመኗ እንደ ዶክተር ዓቢይ ያለ ግብዝና በሃሰት ላይ ሃሰት እየተናገረ የሚመራ መሪ አጋጥሟት አያውቅ። ዶክተር ዓቢይ በመቶዎች የሚቆተሩ የማይፈፀሙ ውሸቶችን ለህዝቡ በመንገር ለጊዜው ሲያደናግሩት ቢቆዩም አሁን ግን ሁሉም ነገር ኮለል ብሎ የታየበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። 

በሃገራችን እኮ የተራው ሰው ይቅርና የአንድ ክልል ፕረዚደንት፣ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግና ፕረዚደንቱ አማካሪ እንዲሁ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙን ጨምሮ ሌላ ትልቅ ጀነራል በአንድ ፀሃይ በጥይት ተደብድበው ተገለዋል። ቀደም ሲልም የህዳሴ ግድብ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ በጥራራ ፀሃይ በከተማ መሃል በጥይት ተገለዋል። በቅርቡ ደግሞ አንድ ታላቅ የኦሮሚኛ ዘፋኝ በጥይት ተገድሏል። ይህንን ተከትሎም 239 ንፁሃን ዜጎች በኦሮሚያ በጎራዴ እየታረዱ ተገለዋል። አሁንም ይህ ግድያ አላቆመም። ዶክተሩ ግን እነዚህን በመፍታትና በማጣራት ፈንታ ፓርክ በማስመረቅና ጠላዋ እንዳማረላት ኮማሪ በማይረባ ጉዳይ ሽርጉድ ሲሉ ሃገራችንን ወደ ገደል እየገፉብን ይገኛሉ። አማሮች በማንነታቸው ተጋሩ በዘራቸው ሲታረዱ እኝ ሰውዬ ወደ ሌላ ሃገር የሃዘን መግለጫ ሲልኩ ይታያሉ፣ በቅርቡ የአፋር ህዝብ በጎርፍ ሲጥለቀለቅ እሳቸው ወደ ሱዳን የሃዘን መግለጫ ሲልኩ ነበር። ሰዎች በማንነታቸውና በሃይማኖታቸው ክርስቲያን ተብለው ሲታረዱ ዶክተር ዓቢይ ስለመናፈሻና ሃብታሞች የት ሊዝናኑ እንደሚችሉ ሲያወሩ ይታያሉ። ይህ አንድ ህፃን ሊያደርገው የማይገባ ድርጊት የአንድ መቶ አስራ አራት ሚልዮን ሃገርን የሚመራ ሰው ባህሪይ ነው ቢባል አሳፋሪ ነው። ደግነቱ ይህ በአማርኛ ተፃፈ እንጂ የዓለም መሳቂያ ባደረገን ነበር። 

……….ይቀጥላል

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here