spot_img
Thursday, July 25, 2024
Homeነፃ አስተያየትአካባቢያዊ ማንነቶች፣ አማራነት እና ኢትዮጵዊነት አንድም ሶስትም ናቸው፡፡

አካባቢያዊ ማንነቶች፣ አማራነት እና ኢትዮጵዊነት አንድም ሶስትም ናቸው፡፡

አማራነት እና ኢትዮጵዊነት

ዳምጠው ተሰማ ደነቀ
ህዳር 8 2013 ዓ.ም.

የአማራን ህዝብ አንድነት የመናድ አቅም ያላቸው አሰላፎች በመሬት ላይ ሳስተዋል፡፡ ከወንዜነትና ከባህል ጋር የሚያያዙ ድርብርብ ማንነቶች ተፈጥሯዊ እና ጤናማ በመሆናቸው በአማራዊ አንድነታችን ውስጥ እንደጸጋ የሚወሰዱ ናቸው፡፡ አካባቢን ወይም ሌሎች ማህበራዊ እሴቶችን የማንነት መገለጫ አድርጎ የመውሰድ ልምድ፣ አጽናፋዊው አንድ አማራነትና የኢትዮጵያዊነት ማንነቶች የሚመጋገቡ ናቸው፡፡   

አንድ አማራ ከየት ነህ ሲባል ራሱን በሳይንቴነት፣ በቋራነት፣ በተጉለቴ፣ በመንዜነት፣ በወልቃይቴነት ወዘተ ሊገልጽ ይችላል፡፡ የተለመደም ነው፡፡ አሶሳ፣ ወልቂጤ ላይ ወይ ባሌጎባ ላይ የምናገኘውን አማራ ተመሳሳይ ጥያቄ ብናወርብለት ጎጃሜ ፣ ጎንደሬ ነኝ፣ ወሎዬ ነኝ… ወዘተ የሚሉ መልሶችን ሊሰጠን ይችላል፡፡ በአማራ ህዝብ ውስጥ እስካሁን ድረስ የሚስተዋል ወግ አጥባቂነት እና ለእርስት የተለየ ግምት የሚሰጥ በመሆኑ የእሱ ወይም የቤተሰቦቹ እትብት የተቀበረባትን መንደር ወይ አካባቢ የማንነቱ አካል አድርጎ በመውሰድ እንደመገለጫ አድርጎ እንዲጠቅስ ያደርገዋል፡፡ ይህ የማህበረሰባችን ከትውልድ አካባቢው ጋር ጥልቅ ትስስር እንደተግዳሮት የሚወሰድ አይደለም፡፡

ሃርር ላይ ያለ የትጉለት ወይም የጅሩ አማራ ቆጥቦ የሚከፍታትን ሱቁ ሸዋ ማርኬት ብሎ የሚሰይም በዘፈቀደ አይደለም፡፡ አንድን ሰፈር ወረዳ (ለምሳሌ ሀገሬ ወገራ፣ ሀገሯ መሬ ነው፣ ሀገሬ ሁመራ..) ጠርቶ ሀገረ እያለ ሲፎክር ሲሸልል የሰማነው አማራ የአማራነት ማንነቱን ከልቡ ስላልጣፈው ወይም ኢትዮጵያ ሀገሩ ሳትመስልው ቀርቶ እንዳይደለ የሚታወቅ ነው፡፡ ወገራ ወይም መሬ ለምትባለው መነሻው ያለውን ታማኝነት አጉልቶ ስለሚመለከት እና የሱ መነሻ የሆነችውን የአያት-አባቶቼ አሻራ የሚላት አካባቢ በታማኝነት ያለመጠበቅ/ያለመከበር የሀገሩን የኢትዮጵያ ሉአላዊ ማንነት ጎደሎ የሚያደርጎ መሆኑን ስለሚረዳ ነው፡፡ ይህ አይነት የማህረሰብ አተያይና ትስስር በአማራነት ላይ የተጋረጠ ተግዳሮት አድርጎ መመልከት ወደተሳሳታ ድምዳሚና ፍረጃ ይከታል፡፡ 

ከላይ ከሉት የአካባቢ መጠሪያዎችን ተጠቅሞ ማንነትን መግለጽ ከአማራነት ጋር ተቃርኗዊ ግንኙነት የለውም፡፡ በመሰረታዊነት የሰው ልጅ የሙያ፣ የእምነት፣ የቋንቋ፣ የብሄር ወዘተ ማንነቶች አንዳሉት እና በሚያስፈልጉበት ቦታ መገለጫ አድርጎ ቢጠራችው እንደነውር ሊወሰድ አይገባም፡፡ የእስልምና ወይም የክርትና እምነት የምከተል አማራ፣ ቋንቋዬ ኦሮምኛ የሆነ አማራ ወይም አካባቢ ተኮር ማንነት ያለኝ (ለአብነት ጎጃሜነትን፣ይፋቴነትን፣ ማርቆሴ… በመጥቅስ) አማራ ነኝ በሚል ራስን መግለጽ ይቻላል፡፡ ማንነት ድርብርብ ነው የሚለውንም ጽንሰ ሃሳብ ልናሰምርበት ይገባል፡፡ በጥቅሉ አማራነት ከአካባቢያዊ እሳቤ፣ ከቦታና ከሌሎች ማንነቶች ጋር ተቃርኖ አለው ለማለት የሚያበቃን መነሻ የለም ማለት ነው፡፡ 

አንዳንዴ በወንዝ ልጅነት የመተዋወቅ ነገር ከአማራት እትብት በጠነከረ አግባብ የስበት ምንጭ ሆኖ ለመደራጀት መነሻ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ሃይማኖታዊ መስመርም በተመሰሳይ መልኩ ጠባቅ ስብስብን የሚፈጥር ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ አይነቱ የግንኙነት መሰረት የሆኑ የእኛነት መገለጫዎች በአማራዊ ማንነት የመሰባሰብ ሂደቶች ላይ ምንም አይነት ጫና አያመጣም የሚል ብያኔ መስጠት አይቻልም፡፡ ይህም የወካይነትን መርህ በመዳጥ/በአግላይነት የአካባቢያዊን፣ የጾታን፣ የእምነትን እና ወዘተ መስመር በመታከክ የፖለቲካውንና የኢኮኖሚውን ጉልበት የመቆጣጠር ዝንባሌና ተግባር ከተስተዋለ ብቻ ነው ሁኔታው በአሉታዊነት ለመመልት የሚቻለን፡፡ከልምድ እንደተረዳነው  ግለሰቦች የሌብነት ድር ለመዘርጋት የሚሞክሯቸው ወንዝ ተኮር አሰላለፎችም በተግዳሮትነት ሊፈረጁ የሚችሉ ናቸው፡፡ እነዚህኞቹ ለጊዜው የከፋ ቀውስ የሚያከትሉ ባይሆኑም  በአማራ ብሄርተኝነት ውስት የጸነፈ ጉጉት ያላቸውን ወጣቶች ሞራል የሚጎዱ ናቸው፡፡  

ሆኖም በህግ ሰውነት ባላቸው ድርጅቶች እና በመንግስት ስርዓት ውስጥ የሚስተዋሉ አንዳንድ አድሎ-ነክ ጉድለቶችን ከጎጠኝነት ጋር የማላከክ ዝንባሌ ካለ አፍራሽ ነው፡፡ የችግር ትንተናችን መዋቅራዊ በሆኑ ማህበራዊ እሴቶች፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስርዓቶች እና በግራንድ ፕሮጀክቶች ላይ ብቻ ማተኮር ይኖርበታል፡፡ 

ከላይ ያለው ሃሳብ እዳለ ሆኖ በአማራነት ቅኘት ውጭ ባሉ ማህበራዊና አካባቢያዊ ነክ የመቀራረብና የመደራጀት ሁኔታዎች ከአማራነት ግማድ በጠነከረ አግባብ ትስስር መፍጠራቸው ጤነኛ የማህበራዊ መስተጋብር በመሆኑ ላይ መጠራጠር አይኖርብንም፡፡ ይህ አይነት ሁኔታ ተፈጥሯዊ የማህበረሰብ እድገት ሂደት አካል መሆኑን እና የረጅም ጊዜ ስርጸትና የማህበራዊ ቀረጻ ውጤት መሆኑን መረዳት ያሻል፡፡ ይህ በአወንታዊነት መረዳታችን ደግም ፖዘቲቭ ኢነርጂ በማመንጨት የአካባቢያዊ፣ የእምነት ወዘተ ማንነቶች እንደጸጋ ተቆጥረው በአመዛኙ ወጥ በሆነው አማራነት ስር በመሰባሰብ ሂደት ላይ ጫና በማይፈጥሩበት አግባብ እየተስተናገዱ በአማራነት ውስጥ ያሉ አብረቅራቂ ማንነቶች ሆነው እንዲቀጥሉ ማድርግ እንችላለን፡፡ ጠቃሚ ከሆኑ እንዲያብቡ ይደረጋልም፡፡ የኢትዮጵያዊነት ውቅርም የእነዚህ ድርብርብ ማንነቶች ድምር ነው፡፡ አማራነትና ብሄርተኝነቱ የትኛውንም ህዝብ እና ማህበራዊ ማንነት በጠላት የማይፈርጅ ከመሆኑም በላይ በሀገሩቱ ያሉ የሌሎች ማህበረሰቦች የቋንቋ፣ የእምነት፣ መልከዓ-ምድር ወለድ ልዩ ልዩ ማንነቶችን እና ወግን አንደብሄራዊ ጌጥ የሚቆጥር በመሆኑ ለጤናማ ሀገረ-መንግስት ምስረታችን ፈር ተላሚ ነው፡፡   

በተጨማሪም አንዳንድ ጠቃሚ ያሆኑ የወንዜያዊም ሆኑ ሌላ አይነት እሴቶች የአማራን ህዝብ በማዘመን ሂደት ውስጥ ፈተና ስለሚገጠማቸው የብሄርተኝነቱን ማበብ እና የሀገረ መንግስቱን ጥንካሬ የመቃረን አቅም አይኖራቸውም፡፡ የዘመኑ የሙያ ማህበራትና የቢዝነስ አክሲዮኖች መስፋፋት፣ ከላይ ለተጠቀሱት ማንነቶች ገፊ ያልሆነ አማራዊ ስርጸት፣ የሰዎች ከቦታ ቦታ መዘዋውር እና የባህል መወራስ ሲኖር በርካታ የትላንት ንዑስ የማንነት መገለጫዎች እየሳሱ አማራነት ሊያብብ ይችላል፡፡ በጥቅሻ የሚናበቡ በአማራነት ለዛ የተቃኙ አደረጃጀቶች ስለሚበረክቱ የአማራ ህዝብ ለሀገረ-ኢትዮጵያን ሁለንተናው ልህቀት ምሰሶ የመሆን ድርሻውን በምግባር የመወጣት እድሉ ይሰፋል፡፡      

እናም የትኛውንም ማንነትና እሱን ተመርኩዞ የተቃኘ አሰላለፍን የምንመለከትበትን መነጽር አካታች አድርገን፣ ሆደ-ሰፊነትን እያበዛን እና የተለያዩ ችግር መሳይ ማህበራዊ አሰላለፎች ወደ እድል እየቀየርን የአማራን ህዝብ ማህበራዊ አንድነት የምናጠናክር እንድንሆን ይጠበቃል፡፡ ይህን በምግባር ሆነን የምገኘው አይናችንና ልባችን ከትልቁ ስዕል ላይ ላፍታም የማይርቅ ከሆነ ብቻ ነው፡፡  

ከአሁን በፊት እንደተግዳሮት ሲወሰድ የሚስተዋለው ጎጣዊ እና የአምቻ-ጋብቻ መቧደን መሰረታዊ መነሻው ጥቅምና ጥቅም ብቻ መሆኑን በመገንዘብ መፍትሄውም በልኩ የሚሰፋ ነው የሚሆነው፡፡ የተጋነነ የችግር ትንተና አንዳይደረግ እና እሱንም ተከትሎ ከችግሩ በላይ የተለጠጠ የመፍትሄ እርምጃ እንዳይወሰድ ጥንቃቄ ያሻል፡፡ በአንዳንዶች የሚስተዋለው ከአማራነት ውጭ የሚስተዋሉ አንዳችም አይነት ማንነቶችን ያለማቀበል (Ambitious nationalism) አዝማሚያ ከአማራ ህዝብ የድርብርብ ማንነት ስሪት አንጻር ከተመዘነ በአግላይነት የሚፈረጅ ነው፤ ጤናማም አይደለም፡፡      

በመጨረሻም በሚከተለው ሃሳብ ላይ ድርብ መስመሮችን አጋድሜ ሃሳቤን እቋጫለሁ፡፡ አካባቢን ወይም ሌሎች ማህበራዊ እሴቶችን የማንነት መገለጫ አድርጎ የመውሰድ ልምድ፣ አጽናፋዊው የአማራ ህዝብ አንድነትን የማጠናከር ሂደት እና ኢትዮጵያዊ ማነትን የመላበስ ሁኔታ የሚመጋገቡ ናቸው፡፡ ተመጋጋቢነት አንድም ሶስትም የመሆናቸው ሚስጥር እዳለ ሆኖ አንደየአውዱ እና እንደየፈርጃቸው ነጣጠሎ በመመልከት በመካከላቸው ምንም አይነት ተቃርኖ ያለመኖሩን መረዳትም ተገቢ ነው፡፡ 

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

1 COMMENT

  1. አንድም ሶስትም ስትል እማይሆን ነገር ለማለት ነው ? አንድ እንዴት ሦስት እንደሚሆን አስረዳን እስኪ ?

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here