spot_img
Sunday, May 28, 2023
Homeነፃ አስተያየትሕወሓት ካጫረው ደም-አፋሳሽ ጦርነት ምን ትምሕርት ተገኘ፣ ዘላቂ መፍትኄውስ?

ሕወሓት ካጫረው ደም-አፋሳሽ ጦርነት ምን ትምሕርት ተገኘ፣ ዘላቂ መፍትኄውስ?

- Advertisement -

የግል አስተያየት፣ አያል ሰው ደሴ (ዘብሔረ-ኢትዮጵያ)
ኅዳር ፲፯ ቀን ፪ ሽህ ፲፫ ዓ/ም

በዚች አጭር ጽሑፍ የሕወሓት አመራር በትግራይና በቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የፈጸመውን ግፍና ሰቆቃም ሆነ በደርግ ሥርዓት መወገድ ላይ የነበረውን ሚና ለመዘርዘር ሣይሆን አሁን ለምንገኝበት ደም-አፋሳሽ ሁኔታ የዳረገንን የቅርብ ምክንያትና አገራችንንና ሕዝባችንን ከቀጣይ መዘዘ-ብዙ ችግር ለመታደግ ቢወሰዱ የምላቸውን አሳቦች ለወገን ኢትዮጵያውያን ለማስተላለፍ መሆኑን ከወዲሁ በአክብሮት እገልጣለሁ።

ሕዝብ ለለውጥ ባደረገው መስዋዕት ያስከፈለ ትግል ዶ/ር ዐብይ አሕመድ መጋቢት ፳፬ ቀን ፪ ሽህ ፲ ዓ/ም ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሆኑ በኢሕአዴግ አገዛዝ ተስፋ የቆረጠውና በአገር ላይ ባንዣበበው አደገኛ ሁኔታ ለሥጋት የተዳረገው የኢትዮጵያ ሕዝብ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ደስታውንና ድጋፉን መለገሱ ይታወሳል። በአጭር ጊዜም የፖለቲካ እስረኞችን ከመፍታት ጀምሮ አደፋፋሪ የለውጥ እርምጃዎች ተወስደዋል። የለውጡ ሂደትና ምሪት እንዲለወጥ ከተፈለገው ገዥ ድርጅት /ፓርቲ/ ኢሕአዴግ መኻል በወጡ ወገኖች እጅ በመሆኑ ለውጥ እንዲመጣ የፈለገውና በተቃውሞ ጎራ ቆሞ የቆየውም ሆነ ከኢሕአዴግ ውጪ የነበረው ሠፊው ሕዝብ በለውጡ አጠቃላይ ምሪትና ሂደት ላይ ትርጉም ያለው ጫናና አስተዋጽዖ ለማድረግ ባለመቻሉ፣ ለውጡ በአዲሱ የኢሕአዴግ መሪዎች ፍላጎትና የፖለቲካ ፍልሥፍና እንዲካሄድ ግድ ሆኗል።

ኢትዮጵያን ለሃያ-ሰባት ዓመታት በገዛው ኢሕአዴግ ውስጥ እስከለውጡ ድረስ አውራ ሆኖ ሥልጣንን ሁሉ ሰብስቦ እንደፈለገው ሲገዛ በቆየውና በለውጡ ይዞታ፣ አካሄድና አደረጃጀት ላይ ቅሬታ ያደረበት የሕወሓት አመራር፣ በአገር አንድነትና በሕዝብ ሰላም ኪሣራም ቢሆን ለውጡን ለማደናቀፍና ያጣውን ሥልጣን መልሶ ለመያዝ ያልተጓዘበት መንገድ አልነበረም። በሕወሓት አመራርና በቀሩት የግንባሩ አባላት ዘንድ የተፈጠረው ልዩነት እየተካረረ ሄዶ እነሆ አገራችንን ለደም-አፋሳሽ ችግር ዳርጓል። ይኽ ችግር መመለሻ ወደሌለው አደገኛ ሁኔታ የገባው ግን በዓለም ላይ የብዙ ሰዎችን ሕይዎት እየቀሰፈ ያለውን የኮቪድ 19 ወረርሽ መከሰት ተከትሎ በተፈጠረው አሉታዊ ሁኔታ የአስቸኳይ-ጊዜ-አዋጅ በመታወጁና በ፪ ሽህ ፲፪ ዓ/ም ይካሄዳል የተባለው አገር-አቀፍ ምርጫ እንዲተላልፍ በሕዝብ ተወካዮች ምክር-ቤት የተወሰነውን ውሣኔ ትግራይን የሚገዛው ሕወሓት አልቀበልም በማለት የራሱን ምርጫ በማካሄዱ ነበር። እራሱን ከማዕከላዊ መንግሥት ባገለለው የሕወሓት አመራርና በአዲስ መልክ ብልጽግና ፓርቲ ሆኖ በቀጠለው የቀድሞ ኢሕአዴግ መኻል የነበረው ልዩነት ከጊዜ-ወደ-ጊዜ እየተካረረ በመሄዱ አገርን ለከፋ አደጋ ያጋልጣል በሚል ሕዝብን ስጋት ላይ መጣሉ ግልጥ ነበር። እየሰፋና እየተካረረ የሄደው ልዩነት በአገርና በሕዝብ ላይ ያጠላውን አደጋ የፊት-ለፊት ውይይት በማድረግ እንዲፈታ አባል የሆንኩበት ድርጅት የኢትዮጵያ ኅብረሕዝብ ብሔራዊ ንቅናቄ (ኅብረሕዝብ) ለብልጽግና ፓርቲና ለሕወሓት አመራሮች ግልጽ ደብዳቤ በመጻፍና በመግለጫዎች ጭምር ለፖለቲካ ድርጅቶች፣ ለሲቪክና የሙያ ማኅበራት፣ ለሐይማኖት አባቶችና ለአገር ሽማግሌዎች አሳስቦ ነበር።     

በመጨረሻም፣ ትግራይን የሚገዛው የሕወሓት እብሪተኛ አመራር በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ጦር ላይና በፌዴራል ፖሊስ አባላት ላይ ጥቅምት ፳፬ ቀን ፪ ሽህ ፲፫ ዓ/ም ጦርነት ከፍቶ ይሆናል ተብሎ የማይታሰብ እጅግ ነውረኛና አሣፋሪ የአገር ክኅደት ወንጀል በመፈጸሙ፣ በማዕከላዊ መንግሥትና በዚኽ ድርጅት መኻል የቆየውን ልዩነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የነበረውን አነስተኛ ዕድል ጨርሶ እንዲከስም አድርጓል። ይኽ አረመኔኣዊ ግድያ መሠረታዊ ወታደራዊ የመለዮ ሥነ-ምግባርና ሥነ-ሥርዓትን የጣሰ፣ በማይ-ካድራም ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት የጥቃት ዒላማ ሆነው በዘግናኝ ሁኔታ የተጨፈጨፉበት በመሆኑ ከጦር-ሜዳ ወንጀልና በሰው-ዘር-ፍጅት የሚያስጠይቅ ይሆናል። እነኝኽ የወንጀል ድርጊቶች ከዚያ በታች የሚታዩ አይሆኑም። 

ይኽ በሕወሓት ጽንፈኛ አመራር የተወሰደ አስነዋሪ እርምጃ ተራ ጤና-ቢስ ድርጊት ሣይሆን፣ ማንም ሉዓላዊ አገር ሊቀበለው የማይችልና በምንም መንገድ ሊታለፍ የማይገባን ቀይ-መሥምር የጣሰ ፀያፍ ተግባር እንኳን ኢትዮጵያችን ለባዕዳን የጥቃት አደጋ ተጋላጭ በሆነችበትና የዜጎቿን አንድነት አጥብቃ በምትሻበት ቀርቶ በማንኛውም ጊዜ ቢሆን በአገር ኅልውና ላይ የተፈጸመ ከፍተኛ የክኅደት ወንጀል በመሆኑ፣ ልዩነቱ በገዥው ፓርቲና በሕወሓት መኻል ከመሆን እንዲያልፍና በኢትዮጵያ ሕዝብና በሕወሓት መኻል እንዲሆን አድርጎታል። ለዚኽ የወንጀል ድርጊት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ትዕዛዝ አግባብነት ያለው ምላሽ እንዲወሰድ ግድ ሆኗል። በዚኽ ድርጅት ግብዝ መሪዎች የሥልጣን ጥም ምክንያት በተለኮሰ ጦርነት እነሆ የዜጎች ክቡር ሕይዎት እንዲጠፋና የአገርና የሕዝብ ንብረትንም ለውድመት እንዲዳረግ ሆኗል። በሕወሓት መዋቅር በታቀፉ ኃይሎች ማይ ካድራ በኖሩ ከስድስት-መቶ እስከ ስምንት-መቶ (ቁጥራቸው ከዚያ በላይ በብዙ ሊጨምር ይችላል ተብሎ የሚገመት) ሰላማዊ ዜጎች ላይ ማንነትን መሠረት ያደረገ ዘግናኝ የዘር ጭፍጨፋ መካሄዱ ተዘግቧል። በየቀኑም የጅምላ መቃብሮችና የተጣሉ የዜጎች አስከሬኖች የመገኘታቸው መርዶ በየቀኑ እየተሰማ ነው።       

ማንኛውም ጦርነት አስከፊ መሆኑና ክቡር በሆነው የሰው ሕይዎትና በንብረት ላይ እንዲሁ በአሃዝ ከሚገለጠው በላይ በዋጋ የማይገመት ጉዳት እንደሚያደርስ የታወቀ ነው። በጦር ሜዳ በሚደረግ ፍልሚያ በግንባር የሚገኝ ድል፣ በተቀናቃኙ ቁጥጥር ሥር ያሉ ቦታዎችን በማስለቀቅና የበላይነትን ማረጋገጥ ቢቻልም፣ የግድ ለጦርነቱ መንስዔ የሆነውን መሠረታዊ ችግር ላይፈታ እንደሚችል መረዳት ያስፈልጋል። አነስተኛም ይሁን ከባድ፣ በተከላካይነትም ይሁን በአጥቂነት በሚደረግ ፍልሚያ የሚሠለፍ ኃይል ጦርነቱን በአቸናፊነት ለመወጣት የሚጠይቀውንና የሚያስከፍለውን ዋጋ፣ የጦርቱን ዓላማና ግብ ከወዲሁ ጠንቅቆ ማወቅና በድኅረ-ጦርነቱ እንዲገኝ የተፈለገው ፖለቲካዊ ልዕለ-ግብ በትክክል የታወቀና ሙሉ ዝግጅት የተደረገበት ሊሆን ይገባል። ትልቁና ፈታኙ ይኽ ምዕራፍ ይሆናል። ይዋል-ይደር እንጂ የሕወሓት አመራር በጦር-ሜዳው ፍልሚያ ሲቸነፍ ለችግራችን መፍትኄ ተገኘ ማለት አይሆንም። በመሆኑም፣ አገራችንን ለዚኽ ደም-አፋሣሽ ችግር የዳረገውን መሠረታዊና ዋነኛ ምክንያት በቅጡና በድፍረት መረዳትና ወደ ሌላ ኅልውና-ተፈታታኝ የቀውስ አዙሪት እንዳንገባ ከወዲሁ ዘለቄታዊነት ያለው መፍትኄ ሊፈለግ ይገባል።

በአገር-ወዳድና ዴሞክራት ኃይሎች የቆየን ሁሉ ሕወሓት-መሩ ኢሕአደግ ሥልጣን ከመያዙ በፊትም ሆነ በኋላ አበክረን ስናሳስብ የነበረውና የታገልነው ይኽ አሁን ሕወሓትና መሰሎቹ የሚከተሉት የፖለቲካ-ቅኝትና የአደረጃጀት-ዘይቤ፣ በተለይም እንደ-አገራችን የምጣኔ-ሃብት አቅም ደካማ በሆነበት፣ ዴሞክራሲያዊ ባኅልና ሥርዓት ባልዳበረበት፣ የሕዝብ ቁጥር በእጅጉ እየጨመረ ባለበት፣ የባዕዳን መተናኮል ያልተለየውና የኅብረተሰብ ስብጥር የበዛበት አገር ውሎ-አድሮ አንድነትን ሣይሆን መበተንን፣ የጋራ እድገትንና ብልጽግናን ሣይሆን ሕዝብን ለትርምስ የሚዳርግ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያችንን ለውድቀትና ለባሰ የችግር አዙሪት እንዳይዳርግ፣ ትኩረታችንና አቅማችንን በማስተባበር ማንኛውንም አድልዖ ለሚያስወግድና በሁሉም ረገድ የዜጎችን እኩልነትና ማኅበራዊ ፍትኅን ለሚያረጋግጥ፣ ሁሉንም እኩል አትራፊና ተጠቃሚ ለሚያደርግ፣ ሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነቱን ለሚያስከብር ርቱዓዊ የፖለቲካ ሥርዓት እውን እንዲሆን ነበር።

ይኽ የሕግ ማስከበር የጦር-ሜዳ ፍልሚያ ይዋል-ይደር እንጂ በማዕከላዊ መንግሥት የበላይነት እንደሚጠናቀቅ ብዙ ላያከራክር ይችላል። ስህተትን የማረም ልማድ የሌለው እብሪተኛ የሕወሓት አመራር አብዛኛውም ይሁን የተወሰኑት በተለያዩ መንገዶች በሽምቅ ውጊያ ጭምር የንዝንዝ-ጦርነት እስከማድረግ ሊሞክሩና ከባዕዳን ድጋፍን በመሻትና በመተባበርም ቢሆን ሰላም ለማደፍረስና የተወሰነ ጉዳት ለማድረስ ይችሉ ይሆናል። ይኽ ከዋናው ጦርነት ቀጥሎ ለተወሰነ ጊዜ የሚገጥም ችግር ሊሆን እንደሚችል መገመት ቢቻልም፣ ሕግና ፀጥታን ከማስከበሩና ከማረጋጋቱ ጥረት ጎን-ለጎን መንግሥት ለሕዝብ አስፈላጊ የሆኑ የፍጆታ አቅርቦቶችንና አገልግሎቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ የሚቻለውን ርብርብ ማድረጉ የዚኽን ምዕራፍ ዕድሜ የመወሰን አቅም ይኖረዋል።

አሁንም ቢሆን ሕወሓትን እንደ-ድርጅትም ሆነ አመራሩን በተናጠል ከፖለቲካ ጨዋታው ማስወጣት ቢቻልም እንኳ የዚኽን የአንድ አገር ዜጎችን ደም ያፋሰሰ ችግር መሠረታዊ መንስዔ ከሥሩ ማስወገድ እንዳልሆነ በቅጡ መረዳት ያስፈልጋል። ለዚኽ አሣዛኝ ችግር የዳረገን ዋነኛ ምክንያት ከድርጅቱ ከሕወሓትም ሆነ ተልዕኮ-ፈጻሚና አስፊጻሚ ከሆኑት ከመሪዎቹ ባኅሪ ብቻ ጠበብና ቀለል ተደርጎ ሣይሆን ድርጅቱ ከቆመበት የፖለቲካ ፍልሥፍናና መርኆ አኳያ ሊታይ ይገባል። ችግሩ ከዚያ አኳያ ተመዝኖ ከወዲሁ ዘለቄታዊነት ያለው መፍትኄ ካልተሰጠ ምናልባት የቀውሱ ተዋናዮች ማንነትና ቦታው ሊለያይ ካልሆነ በስተቀር የእርስ-በርስ ደም መፋሰሱና የመከራ አዙሪቱን ማስወገድ እና ውድ አገራችን ኢትዮጵያ እንደ-አገር፣ ሕዝቧም እንደ-ሉዓላዊና ነፃ ሕዝብ ዜጎቿ ሁለንተናዊ መብቶቻቸው ተከብረውና ከድህነት አዙሪት ተላቅቀው እንዲኖሩ ማድረግ የማይሆን ምኞት ይሆናል። ማንኛውም ችግርና መከራ በቅጡ ከተያዘ በውስጡ ይዞት የሚመጣ በጎ ነገር ስላለ፣ ያለፈ ታሪኩ ብቻ ሣይሆን መፃዒ-ዕድሉ እንደማይነጣጠልና እንደተሣሰረ የአንዲት አገር ማኅበረሰብ ከዚኽ አጥፊ ክስተት በቂ ትምሕርት ልንቀስም ይገባል። ኢትዮጵያን የምታክል ታሪካዊት አገርና የተከበረ ሕዝቧ እውነተኛ ማንነታቸውንና ዘመኑን ወደሚመጥን የከፍታ ደረጃ ለመውሰድ፣ የመከራ አዙሪትን በማስወገድ ለመሠረታዊ ችግሮቻችን ዘለቄታዊነት ያለው መፍትኄ ማስገኘት፣ አገራዊ-አንድነትን ማረጋገጥ፣ ሰላምንና መረጋጋትን ማስፈን፣ የሕግ-የበላይነትን ማስከበር፣ የፍትኅና የእኩልነት ሥርዓትን እውን ማድረግ ያስፈልጋል። ለዚኽም የሚከትሉትን እርምጃዎች መውስዱ አስፈላጊና ድፍረቱም ሊኖረን ይገባል በሚል እነሆ አሳቤን በአክብሮት አቀርባለሁ።

፩ኛ. አገራዊ ሰላምና መረጋጋት፡-

ሰላምና መረጋጋትን ማረጋገጥ የቅድሚያ-ቅድሚያ ተሰጥቶት በሁሉም የአገራችን ክፍሎች ተግባራዊ መደረግ ይኖርበታል። ይኽ ለቀጣይ እርምጃዎች እንደ ቅድመ-ሁኔታ የሚታይ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። በተለይ በትግራይና በሌሎች የአገራችን ክፍሎች ያሉ ሰላማዊ ዜጎች በማንነታችው ምክንያት ከሚኖሩበት ማፈናቀል ጀምሮ ክቡር ሕይዎታቸውን በጭካኔ እያጡ ባሉባቸው ሁሉ ተግባራዊ ሊደረግና ወንጀለኞችን ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ ያስፈልጋል። ከዚኽ አኳያ የትግራይን ሕዝብ ከአርባ ዓመታት በላይ አፍኖ በያዘውና በአገር-መከላከያ ሠራዊት ላይ ጦርነት በከፈተው የሕወሓት አመራር ላይ እየተካሄደ ያለው ዘመቻ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ተጓዳኝ ጉዳት እንዳይደርስ ሆኖ ሲጠናቀቅ፣ ሰላምና መረጋጋት ተረጋግጦ ሕዝብ ያለ-ስጋት መኖርና በየእርከኑ የሚመሩትን በነፃ ምርጫ እስከሚሰይም ድረስ በጊዚያዊነት መተዳደር ያለበት አሁን እንደተነገረው ከማዕከላዊ መንግሥት በሚሾሙ የብልጽግና ፓርቲ ተወካዮች መሆኑ ችግር ስለሚፈጥር ያ ባይሆን ይመረጣል። ከዚያ ይልቅ ሁኔታው ከጦርነት ማግስት የሚደረግ ፈታኝ የማርረጋጋት ሂደትን የሚጠይቅ ስለሚሆን፣ የትግራይ ሕዝብ እንደ ሁኔታው ከሦስት እስከ ስድስት ወራት ለሚቆይ ጊዜ ቢተዳደር የተሻለ የሚሆነው በመከላከያ ሠራዊት የበላይ ጠባቂነት፣ ከአገር-ደኅንነትና ከፌዴራል ፖሊስ ተወካዮችና ሕዝቡ ከአገር-ሽማግሌዎች ጀምሮ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን መርጦ በሚሰይማቸው የጋራ ጊዚያዊ አካል አማካይነት ቢሆን ይመረጣል። ይኽን ማድረግ አስፈላጊ የሚሆነው አንድም በረጅም-ጊዜ ሥር-ሰዶ የቆየውን የሕወሓት አፋኝ የጥርነፋ መዋቅር ጠንቅቆ የሚያውቀው ሕዝብ አመኔታ ኖሮት በፍላጎቱ ከፖለቲካ ድርጅት ሙሉ ቁጥጥር ነፃ የሆኑ አስፈላጊ ማኅበራዊና አስተዳደራዊ መዋቅሮችን ለማቋቋም የተሻለ ዕድልን ስለሚፈጥርለት፣ ሁለተኛ ይኽ አስቸጋሪ የሽግግር ጊዜ ከማዕከላዊ መንግሥት በሚሾሙ ወገኖች ቢደረግ ገና ከሕወሓት አመራር አፍራሽና አሉታዊ ቅስቀሳ ያላገገመው ሕዝብ በጥርጣሬ እንዲመለከትና የግድ ባልመረጣቸው የገዥው ፓርቲ ተሿሚዎች ሥር እንዲሆን የተፈረደበት አድርጎ እንዲቆጥርና እስካሁን ለአፈና ከዳረገው የሕወሓት መዋቅር ለይቶ ለማየት ሊያስቸግረው ስለሚችል፣ ከዚያ ሰቆቃ-ከወለደው ሥነ-ልቦናም ለመላቀቅ የተወሰነ ጊዜና ፋታ ስለሚያስፈልገው ነፃነት አይሰማውም። ከላይ በተጠቀሰው መልክ ቢሆን ግን የብልጽግናም ሆነ፣ የአረና እንዲሁም ሌሎች አቅም ያላቸው አገር-አቀፍ ድርጅቶች መደበኛ ድርጅታዊ ሥራዎቻቸውን በሰላም ማካሄድ ያስችላቸዋል። ሕዝብም የተለያዩ አማራጭ አሳቦችን የመስማት ዕድል ያገኛል። ከዚኽ በተጨማሪና ሊዘነጋ የማይገባው ጉዳይ የማረጋጋትና ሰላምን የማስፈን ሂደቱ የብልጽግና ፓርቲን የሕወሓት ወራሽ አድርጎ በማዕከላዊ መንግሥት መሰየሙ በተለይም ጥያቄ የተነሣባቸውና ብዙ መስዋዕትነት የተከፈለባቸው አካባቢዎችን በተመለከተ የሚኖረው አደገኛ ውጥረት ፋታ ሳይገኝ ለከፋ ደም-አፋሳሽ ሁኔታ ሊዳርግ መቻሉ አይቀሬ ስለሚሆን፣ ከላይ በተጠቀሰው አማራጭ በጊዚያዊነት እንዲመራ ማድረጉ ነገሮችን በእርጋታና በሰከነ ሁኔታ ለማየት ዕድል ይሰጣል፣ አስፈላጊም ይሆናል። 

፪ኛ. መሠረታዊ አገራዊ ችግሮችን በተመለከተ፡

አገራችንን ለዚኽ ዓይነት ደም-አፋሳሽና አገርና ሕዝብን ለከፋ የችግር አዙሪት የሚዳርግ ሁኔታ መሠረታዊ መንስዔውን እና መፍትኄውን የሚያጠና ልዩ አካል /ኮሚሲዮን/ መሰየምና ጥናቱን በሦስት-ወር ጊዜ ውስጥ እንዲያቀርብ ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል። የችግር መሠረታዊ መንስዔና ምክንያት በቀና መንፈሥና በዝርዝር ሳይጠናና ሳይታወቅ ተዋናዮች ላይ ብቻ ማነጣጠርና እነሱ ከሌሉ ችግሩ እንደሚወገድ ማሰብ እርቀት አይወስድም። ወጀብ በበዛበት ቦታ የሚገኝ የበሰበሰና የተበከለ ቤትን ላዩ ላይ ቀለም ቀብቶ አዲስ ቤት ሠራሁ ብሎ እራስን ከማታለል የተለየ አይሆንም።

፫ኛ. ሕወሓትን በተመለከተ፡

ይኽንን ነጥብ ሳነሣ ሥፍር-ቁጥር የሌላቸው የትግራይ ወጣቶች ለፍትኅና ለእኩልነት ሲሉ ክቡር ሕይዎታቸውን ያጡና አካለ-ጎደሎ ሆነው አሁን በሕይዎት የሚገኙ ወገኖቸን ሳስብ ልቤ እየቆሰለና እያዘንኩ ነው። ይሁንናም፣ እነሱም ቢሆኑ ትግላቸው አገራቸውን ለመውጋትና ለውጭ ጠላት እንድትጋለጥ ለማድረግ ባለመሆኑ፣ የከፈሉት መስዋዕትነት በትግራይ ሕዝብ ስምና ኪሣራ ጥቂት አውራዎችና ቤተሰቦቻቸው ቅጥ-ያጣ ሃብታም እንዲሆኑ እና አልፎም በአገር ላይ የአገር-ክኅደት ወንጀል እንዲፈጽሙና ሰላማዊ ኢትዮጵያዊ ወገኖቻቸው ላይ የጅምላ ጭፍጭፋ እንዲያካሂዱ እንዳልነበር እንደሚያውቁ ስለምረዳ፣ በእብሪተኛ የሕወሓት አመራር የክኅደትና ሌሎች ፀረ-ሕዝብ ወንጀሎች እንደሚያዝኑ፣ ከድርጅቱ በላይ ሕዎታቸውን የሰጡላትን አገራቸው ኢትዮጵያን እንደሚወዱ ስለማምን፣ ይኽ አቋም በምንም ዓይነት በእነሱ ላይ የተቃጣ አለመሆኑንና ምክንያቱንም ይረዱልኛል ብየ ተስፋ አደርጋለሁ። የሕወሓት ጽንፈኛ አመራር በተደጋጋሚ የፈጸሟቸው የወንጀል ድርጊቶች ጀርመን የናዚ ፓርቲን፣ ኢራቅም የባዝ ፓርቲን፣ ወዘተ… ሕገ-ወጥ እንዲሆኑ ከተደረጉበት ያነሰ አስጠያቂነት የላቸውም።  

ስለሆነም፣ የሕወሓት ጽንፈኛ አመራር እንደ-ባዕድ ወራሪ ጠላት በራሱ የአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጦርነት አውጆ በአባላት ላይ አሰቃቂ ግድያ እና የመሣሪያ ዝርፊያ በማካሄድ ከፍተኛ የአገር-ክኅደት ወንጀል በመፈጸሙ እና ቢያንስ ማይ ካድራ ላይ ሰላማዊ ዜጎችን በማንነታችው ምክንያት ዘግናኝ የጅምላ ዘር ማጥፋትና የጦርነት ወንጀል በመፈጸሙ፣ ሕውሓት እንደ ድርጅት ለሕዝብ መብት እንደቆመ መደበኛ ድርጅትና በአገር የፖለቲካ ሕይዎት ውስጥ ሊጫዎት የሚገባውን ሚና ይቅርታ በሌለው የራሱ ተደጋጋሚ የወንጀል ድርጊት ምክንያት እንደ አሸባሪ የአገርና የሕዝብ ጠላት ተደርጎ ሊፈረጅና ሕጋዊ እውቅና ሊነፈገው ይገባል።

የአገር መከላከያ ሠራዊት ውስጥ በማንኛውም የእርከን ደረጃ ላይ የነበሩና በዚኽ የአገር-ክኅደት ወንጀል ተሣታፊ የሆኑት ጉዳያቸው በወታደራዊ ፍርድ-ቤት ሊታይ ይገባል። ከእነሱ መኻል በሙስና የተዘፈቁት ግን ጉዳያቸው በመደበኛው ፍርድ-ቤት ጭምር ሊታይ ይችላል።

ለአመራሩ የግል ምቾት የዋለው የድርጅቱ ንብረት ሊወረስና በቂ ጥናት ተደርጎ በሚቋቋም አትራፊ ድርጅት አማካይነት የትግራይን ሠፊ ሕዝብ፣ በተለይም በተረጋገጠ ሁኔታ በከፍተኛ የወንጀል ተግባር ላይ ያልተሠማሩ የቀድሞ ታጋዮችንና በትግሉ ወቅት ሕይዎታቸውን ያጡ ቤተሰቦችን በቀጥታ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል።

ይኽ እርምጃ የሕወሓትን ቀንደኛ የአመራር አባላት በሠሩት ወንጀል እንዲጠየቁ የሚያደርግና ድርጅታዊ ኅልውናን የሚመለከት እንጅ በድርጅቱ ውስጥ የታገሉትንና መስዋዕትነት የከፈሉትን እንዲሁም ቤተሰቦቻቸው ያላቸውን ሙሉ የዜግነት መብትም ሆነ ማግኘት የሚገባቸውን ተዛማች የሆኑ ሕጋዊ ጥቅማ-ጥቅም የሚነካ አይሆንም። 

፬ኛ. አገራዊ (ብሔራዊ) የእርቅና የሰላም ጉዳይ፡

ለአገራችን ውስብስብ ችግሮች ዘለቄታዊነት ያለው ሰላማዊ መፍትኄን ለማስገኘትና ወደ-ዴሞክራሲያዊ-ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ግንባታ የሰከነ ሽግግር ማድረግ ይቻል ዘንድ አገር-አቀፍ የሰላምና እርቅ ጉባዔ ማካሄድ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ዴሞክራትና አገር-ወዳድ ኃይሎችና መልካም-አሳቢ ግለሰቦች ከሦስት-አሥር-ዓመታት በላይ ለዘለቀ ጊዜ ያለመታከት ሲወተውቱ እንደቆዩ ይታወቃል። በሕዝብ ግፊት ከኢሕአዴግ መኻል በወጡ በዶ/ር ዐብይና በአጋሮቻቸው የተመራው ለውጥ ሲከሰትም አባል የሆንኩበት ድርጅት ኅብረሕዝብ ለውጡ ሕዝብ የታገለለትንና መስዋዕት የከፈለለት መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ጥያቄ ዳግም እንዳይቀለበስና እውን እንዲሆን ይኽን የአገራዊ (ብሔራዊ) የእርቅና የሰላም ጉባዔ እና ቅድሚያ ሊሰጣችው የሚገቡ ሌሎች አንገብጋቢ ጉዳዮችን በጽሑፍ ማቅረቡ ይታወቃል። አሁንም ቢሆን ወደ-ምርጫ ከመኬዱ በፊት ይኽ እውን ሊደረግ ይገባል።

፭ኛ. የክልል ልዩኃይልን በተመለከተ፡

በ ‘ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች’ ስም በአገራችን ላይ የተጫነውና በዜጎች መኻል ልዩነትን መሠረቱና መርኆው ያደረገ ከፋፋይ የፖለቲካ ሥሪት በሕዝባችን የጋራ ኢትዮጵያዊ የወል እሴቶችና ማንነት ላይ የዘመተ፣ በተፈጥሮው ወደ-ውስጡ ብቻ የሚያይና ሌላውን ወገኑን እንደ-ባዕድ እንዲመለከት የሚያደርግ በመሆኑ፣ ወደ አንድነት ሣይሆን አገራችንና ሕዝባችንን  ወደ ከፋ የቀውስ አዙሪት ውስጥ የሚያስገባ አደገኛ፣ መዘዘ-ብዙ እና ጠንቀኛ መሆኑን ከአርባ ዓመታት በላይ የተሟገትንበትና ሕወሓት ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ደግሞ ጎጅነቱን በተግባር ያየነው ጉዳይ ነው። ይኽ ጦሠኛ የፖለቲካ ሥሪት በተለይም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሕዝባችን ላይ ያስከተላቸውን ዘግናኝ የወንጀል ድርጊቶች ተመልክተናል። ‘በደንባራ በቅሎ ደወልም ታክሎ’ እንዲሉ፣ ይኽ ከፋፋይ የፖለቲካ ሥሪት ለብቻው በአንዲት-አገር ዜጎች መኻልና በአገር ላይ የሚያስከትለው ጦስ ሣያንስ፣ እነሆ ‘ልዩ-ኃይል’ የሚባል ከአገር መከላከያ ሠራዊት የሚገዳደር ታጣቂ ክፍል እንዲታጀብና እንዲጎለብት ሆኗል። በአገራችን በየአካቢው የሚገኝ መለስተኛ ኢ-መደበኛ አደረጃጀት ያለው ታጣቂ ኃይል ድሮም እንደነበር ይታወቃል። በንጉሡ ዘመን ቀደም-ሲል ‘ነጭ-ለባሽ’ የሚባልና በኋላ በአገር ደርጃ የተሻለ አደረጃጀት ይዞ ‘ብሔራዊ-ጦር (ሕዝባዊ-ወራዊት}’ የሚባል ታጣቂ ኃይል ነበር። የዚኽ ታጣቂ ኃይል የግሉን የነፍስ-ወክፍ የቃታ-ጠመንጃ የታጠቀና ከመደበኛ ፖሊስ ጋር በመተባበርም ይሁን ለብቻው በአካባቢው የሚገኝ ቀማኛና ሽፍታን በማደን ለፍርድ የማቅረብ፣ የውጭ ጠላት ሲኖርና ክተት ሲታወጅ ደግሞ የሚዘምት የአርሶ-አደር ጦር ነበር። ይኸ ኃይል በደርግ ጊዜ ሥልጠናና ትጥቅ እየተሰጠው ከመደበኛው እግረኛ ሠራዊት ጋር በመዝበት ለአገሩና ለሕዝብ ከፍተኛ ተጋድሎ አድርጓል። የዚያ ሕዝባዊ ጦርና የአሁኑ ልዩ-ኃይል በሚባለው ታጣቂ መካከል ያለው መሠረታዊ ልዩነት የትጥቅ ብቻ ሣይሆን መሠረታዊ አደረጃጀቱና ዓላማው ነው። የብሔራዊው (የሕዝባዊው) ጦር ተኣማኒነትና ተጠሪነት ለአንዲት አገሩ ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ ብቻ ነው። የአሁኑ የክልል ልዩ-ኃይል ቀጥታ ተጠያቂነትና ተኣማኒነት ግን ለክልሉ ሕገ-መንግሥት ነው።  

በአገራችን ላይ ያለው ልዩነትን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ርዕዮትና አደረጃጀት ያለው አሉታዊ ተጽዕኖ በክልል በተዋቀረውና ተኣማኒነቱ ለክልል በሆነው ታጣቂ ኃይል ላይ ብቻ ሣይሆን በጽንሰ-አሳብ ደረጃ ተኣማኒነቱ ለአገሪቱ ሕገ-መንግሥት በሆነው የአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ እንደሆነ በሰሜን-ዕዝ ሠራዊት ውስጥ በጄኔራል ማዕረግ በጦሩ ላይ የአመራር ኃላፊነት ከነበራቸው ጀምሮ እስከ ወታደር ባሉ እርከኖች የነበሩ የሕወሓት አባላት ለአገራቸው ለኢትዮጵያ በመሃላ የገቡትን የተኣማኒነት ቃል ሽረው ለክልላቸው ቅድሚያ በመስጠት በራሣቸው የጦር ጓደኞች ላይ ዘግናኝ ጭፍጨፋ በማካሄድ ጭምር ታሪክ ይቅር የማይለው ከፍተኛ የአገር-ክኅደት ወንጀል ሊፈጽሙ ችለዋል። አሁን በሚደረገው ፍልሚያም በጡረታ የተገለሉት ሣይቀሩ ከድርጅታቸው ጎን ተሠልፈው የአገራቸው መከላከያ ኃይል ላይ በመዝመት ተቀዳሚ ተኣማኒነታቸው የት ላይና ለማን እንደሆነ እይታየ ነው። ቀደም-ሲልም፣ ከማል ገልቹ ከጦሩ ከድቶ ወደ ኤርትራ ሲሄድ በቀሩት ላይ ጭፍጨፋ ለማካሄድ ሁኔታው ባይመቸው ወይም ስላልፈለገ ሊሆን ቢችልም፣ ያስከዳቸው ወታደሮች ግን ‘የኔ’ የሚላቸውን ኦሮሞዎች ብቻ መርጦ ነበር። ያም ማለት በአንድ አገር ሠራዊት አባላት መኻል ቋንቋን መሠረት ያደረገና በማንኛውም ጊዜ ጎራን የለየ ጎሠኛ መዋቅር ተዘርግቷል ማለት ነው። (በወቅቱ አገራችን ምን ያኽል አደጋ ላይ እየወደቀች እንደሆነ ከቀድሞ የሠራዊት አባላት ጓደኞቸ ጋር አውስተን አዘናችንንና ስጋታችንን በቁጭት ተጋርተናል።)

ይኽ መቸም ቢሆን በአንድ አገር የሠራዊት ተቋም ውስጥ ሊኖር የማይገባው አሣፋሪና እጅግ አደገኛ ሁኔታ ነው። ይኽ ሁኔታ በሠራዊቱ ውስጥ ሊኖር የሚገባውን መሠረታዊ የሆነና ጨርሶ ጥያቄ ውስጥ የማይገባ ፊጹም የመተማመን ይዞታ (Esprit de corps) በእጅጉ የሸረሸረ በመሆኑ ከፍተኛ ትኩረትና አስቸኳይ መፍትኄ ሊሰጠው ይገባል። እንደ-ቀድሞ ሠራዊት አባልነቴ እንደዚኽ እጅግ አሣፋሪና ልብ-ሰባሪ ሁኔታ ገጥሞኝ አያውቅም። ሠራዊት ከማንምና ከማንም በላይ ያልተከፋፈለ ተኣማኒነቱ ለአገርና ለሕዝብ የሆነ የአገር የወል ማንነት መገለጫ የመጨረሻ አይነኬ ጎራ ነው። ይኽ ይዞታ የሚንጸባረቅበት ሠራዊት ያለው ሕዝብ አገር አለኝ ማለት አይችልም። ለአገሬ በእጅጉ አዘንኩ።

በአገራችን እንዲሠፍን የተፈቀደለት የፖለቲካ ሥርዓት በመከላከያ ሠራዊታችን ሣይቀር በመንግሥታዊ መዋቅሮች ውስጥ ምን-ያኽል ሰርጾ እንደገባና ያም በአገርና በሕዝብ አንድነትና ደኅንነት ላይ የሚኖረው አደገኛ ተጽዕኖ በተገቢ ሊጤንና እንደ-አገር ከእነዚኽ በተግባር ከታዩ ኩኔቶች በቂ ትምሕርት ሊቀሰም ይገባል። አገርንና መንግሥትን ወክለው በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ዜጎች ሣይቀሩ በሚያሣፍር መልኩ ታማኝነታቸውን ከአገራቸው አስበልጠው ለጎሣቸው ሲሰጡ እያየን ነው። ምንም-እንኳ በአሁኑ ጊዜ የሕወሓትን ያኽል በመሣሪያ ኃይል የተጠናከረ ክልል ባይኖርም፣ የክልል አስተዳደር አደረጃጀቱም ይኸንኑ በአብዛኛው ማንነትንና ቋንቋን መሠረት ባደረገ መሥፈርት የተዋቀረና ታማኝነቱ ለክልሉ በሆነ የታጠቀ ኃይል የታጀበ በመሆኑ፣ በክልል አመራሮችና በማዕከላዊ መንግሥት መኻል የሚፈጠር አለመግባባት እንዲሁ በሰላማዊ መንገድ ይፈታል ብሎ ማሰብ እንደማያዋጣና በሠራዊቱ ውስጥ ባሉ አባላት ዘንድ ሊያሳድር የሚችለውን አሉታዊ የሥነ-ልቦና-ጫና-ለወለደው አለመተማመን እንደሚዳርግ፣ ለውጭ ጣልቃ-ገብነት በር እንደሚከፍትና ያም ምን ያኽል አገርን ለአደጋ ሊያጋልጥ እንደሚችል በጥሞና ማስተዋሉ ተገቢ ይሆናል።

ታላቂቱንና ታሪካዊቷን ኢትዮጵያ ለዚኽ አሣፋሪ የእርስ-በርስ አለመተማመን የዳረገንን ይኽን መዘዘ-ብዙ ጎሠኛና ጎጠኛ አስተሳሰብ ያሠፈነ የፖለቲካ ቅኝት ከሰንኮፉ መንቀልና ቢያንስ ዓመታትን ባልፈጀ ሂደት ከዋና የአደረጃጀት ዘይቤነት ማስወገድ ያስፈልጋል። በቅድሚያ ግን ማንኛውም ክልል በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 52 ቁጥር 2 (ሰ) እንደተፈቀደው ከሕግ አስከባሪ ፖሊስ ውጭ ታጣቂ ኃይል በዚኽ ደረጃ የሚያስፈልግበት ምክንያትም ሆነ ሕጋዊ መሠረት ስለማይኖር አፋጣኝ መፍትኄ ሊፈለግለት ይገባል። ሌላው ቢቀር፣ እስካሁን እንደሚታየው የክልል አወቃቀር ከተፈጠረ ጀምሮ ሁሉንም ክልሎች የሚያስተዳድሩት ተመሣሣይ የገዥው ፓርቲ አባል ወይም ተባባሪ የሆኑ ድርጅቶች ብቻ ስለሆኑ፣ ሌሎች ድርጅቶች የመወዳደር ዕድል ቢኖራቸውም እንኳ ቀጣሪና አባራሪ ሆኖ የቆየውና ከሞላ-ጎደል ሁሉንም አስተዳደራዊ-መዋቅሮች የሚቆጣጠረው ገዢ ድርጅት በሥልጣን ላይ ለመቆየት ሲል በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ይኽን ታጣቂ ኃይል ጫና ለማሳደርና ለአፈና ሊጠቀምበት ስለሚችል፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚኖረው አሉታዊ አስተጋብዖ በቀላሉ የሚገመት አይሆንም።

ስለሆነም፣ አገራዊ ምርጫ ከመደረጉ በፊት ይኽንን የክልል ልዩ-ኃይል የሚባል ታጣቂ ክፍል ቁጥሩንና የትጥቁን (የመሣሪያውን) ዓይነት በሕግ ከመገደብ ጀምሮ የተወሰኑትን አነስ-ያለ ቁጥር ያለው ፈጥኖ-ደራሽ ክፍል በማቋቋምና በዚያ ውስጥ እንዲያገለግሉ በማድረግ፣ የተወሰኑትን ወደ-ክልሉ ፖሊስ በማዛወር፣ ፍላጎትና ብቃት ያላቸውን በአዲስ መልክ በቂ ሥልጠና (በተለይም ረዘም ያለ በአገራዊ ሥነ-ልቦና ሊታነጹ የሚችሉበት ትምሕርት እየተሰጣቸው) የአገር መከላከያ ሠራዊትን እንዲቀላቀሉ፣ የቀሩትን ከክልላቸው ውጭ በሚገኙ የሥራ መስኮች እንዲሠማሩ በማድረግ ደረጃ-በደረጃ ማፍረስ ያስፈልጋል እላለሁ። ለተሟላ መፍትኄ ግን ልዩ የጥናት አካል ቢሰይም መልካም ይመስለኛል።     

፮ኛ. የሕዝብ ቆጠራ፡

በኮቪድ ፲፱ አደገኛ ወረርሽኝ ምክንያት በ፪ ሽህ ፲፪ ዓ/ም ሊካሄድ የነበረው አገራዊ-ምርጫ መተላለፉና ያም ሕገ-መንግሥታዊ-ቀውስና ውዝግብ ማስከተሉ ይታወሳል። ውዝግቡን እንተወውና ምርጫው መተላለፉ እውነተኛ ነፃ፣ ፍትኅዊ፣ ርቱዓዊና ዴሞክራሲያ ምርጫ ለማድረግ መሟላት ያለባቸው የቅድመ-ሁኔታ መብቶችና አስፈላጊ መዋቅራዊ አደረጃጀቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ፣ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ድርጅቶችም በምርጫ-ቦርድ የሚጠየቁትን ለማጠናቀቅና በበቂ ለመዘጋጀት ያልታሰበ መልካም አጋጣሚን ፈጥሯል። አገራዊ-ምርጫ ከመደረጉ በፊት መሟላት ካለባቸው ዓይነታ ጉዳዮች ውስጥ በአገር-አቀፍ ደረጃ ተኣማኒነት ያለው የቤትና የሕዝብ ቆጠራ ሊደረግ ይገባል። በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 103 (5) እንደተጠቀሰው የምርጫ ክልሎች አከላለል የሚወሰነው የሕዝብ ቆጠራውን ውጤት መሠረት አድርጎ ስለሆነ፣ በአንቀጽ 54 (3) የሕዝብ ቁጥር የተወካዮችን ቁጥር ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ መሆን ስላለበት፣ ከምርጫ በፊት መደረግ ከነበረበት ሦስት ዓመታት ያለፈው የቤትና የሕዝብ ቆጠራ ተግባራዊ መሆን ይኖርበታል። የሕዝባችንን ቁጥርም ከደፈናዊ ግምት ባለፈ በትክክል ማወቁ ለበጀት አመዳደብና ለሌሎች አስተዳደራዊ ጉዳዮች አስፈላጊ ይሆናል።

፯ኛ. የሕገመንግሥት ጉዳይ፡-

በአገርና በሕዝብ ዕጣ-ፈንታ ላይ ወሣኝነት ያለውን አንገብጋቢ የሕገ-መንግሥት ጉዳይ በተመለከተ በሚደረግ ክርክር በተለይ ባለፉት ሠላሣ ዓመታት በማዕከላዊ መንግሥትም ይሁን በየክልሉ ሥልጣን ላይ በቆዩ ድርጅቶችና የፖለቲካ አቀንቃኞቻቸው (ካሬዎቻቸው) እንዲሁም እንደ ሕወሓትና መሰሎቹ በማንነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ቅኝትና የአደረጃጀት ዘይቤን በሚከተሉ ድርጅቶች በኩል የሚሰማው አሳብ ግትርነት የሚንፀባረቅበት ሆኖ ይገኛል። ምንም ዓይነት ምክንያት ሊደረደር ቢችል አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ-መንግሥት “ችግር የለውም፣ አይነካ”፣ አልፎም “ችግር እንኳ ቢኖር አተገባበር ላይ ነው” የሚለው ደፈናዊ ሙግት ከሌላ ሣይሆን በራሣችን አገርና ሕዝብ ላይ ያስከተለውን ጦስ የዘነጋ፣ አሳማኝነት የሌለውና ኃላፊነት የጎደለው ሆኖ አየዋለሁ። በምልዓተ-ሕዝቡ ኪሣራ በዚኽ ሕገ-መንግሥት ተጠቃሚ የሆኑ ክፍሎች እንዲነካ ስለማይፈልጉ ነው ሊባል ይችላል። ያ እውነታ እንደሚኖረው አምናለሁ። ምክንያቱ ግን ያ ብቻ አይመስለኝም። ከሚያቀርቧቸው መከራከሪያዎች ውስጥ አንደኛው ‘ሕገ-መንግሥቱን መንካት አገር ያፈርሳል’ የሚለው የተዛባ አስተሳሰብ ነው። ይኸን መሟገቻ የሚያቀርቡ ወገኖች የሳቱት ቁም-ነገር ይኽችን ከ፬ሽህ፪፻፶፬ ዓመተ-ዓለም /4254 AD/ ጀምሮ መንግሥታዊ አስተዳደር ያላት፣ በዜጎቿ ደምና አጥንት የቆመችና በልጆቿ የተባበረ ትግል ነፃነቷንና ሉዓላዊነቷን አስከብራ የቆየች ጥንታዊትና ታሪካዊት አገር ይኽ ሠላሣ ዓመት ያልሞላውና ዴሞክራሲያዊ ባልሆነ መንገድ የተወሰኑ ቡድኖችን ጥቅም ለማስከበር ሲባል በሕዝብ ላይ የተጫነ ሕገ-መንግሥት የፈጠራትና ሙቀት ሲነካው እንደሚፈረካከስ በሙጫ የተጣበቀ የገል ሥባሪ አድርገው መቁጠራቸው የሙግቱን ግልብነትና ግብዝነት የሚያሣይ ነው። ሕገ-መንግሥት እንደ ሙሴ ጽላት ከመለኮት የተሰጠና እንዴ ከተጻፈ የማይነካ ሣይሆን በየጊዜው ሊለዋወጡ የሚችሉ የኅብረተሰብ ፍላጎቶችን እንደየሁኔታው ሊያሟላ የሚችልና አግባባዊ በሆነና ሥርዓትን በተከተለ መልክ አስፈላጊ የሆኑ ለውጦች ሊደረጉበት የሚችል ሕይዎት ያለው፣ የሚገዛበት ሕዝብ አስፍላጊ ሆኖ ሲያገኘውም ጨርሶ የሚቀየር የመተዳደሪያ ሰነድ ነው። ስለሆነም፣ ባለፉት ሠላሣ ዓመታትና በተለይም ያለፉት ሦስት ዓመታት በሕዝባችንና በአገራችን ላይ ለተከሰቱ ችግሮች ይኽ ሕገ-መንግሥት ያለውን አስተዋጽዖ ረጋ ብሎ ከልብ መመርመርና እንዳለ ይዞ መቀጠሉ የሚያስከትለውን ጦስ ማጤኑ አስፈላጊ ይሆናል። ሰላምን የሚያደፈርሰው፣ ሕዝብን ለእልቂት የሚጋብዝና አገርን የሚያፈርሰው ይኽን ማድረጉ ሣይሆን፣ እንዲሁ በጭፍን “አይነካም፣ በዚኽ አንደራደርም” የሚለው ደረቅ ሙግትና ይኽንኑ ጠንቀኛ ሕገ-መንግሥት ይዞ መጓዝ ይሆናል። ይኽቺ አገር ከዚኽ ሕገ-መንግሥት በፊትም ነበረች፣ ወደፊትም ትኖራለች። ለአገራችን አንድነት፣ ለሕዝባችን አስተማማኝ ሰላምና እድገት የተሻለውና ተመራጭ የሚሆነው ግን ይኽን ጉዳይ ከምርጫ በፊት መልክ ማስያዝ ይሆናል።

በዚኽ ረገድ አንዳንድ ወገኖች የሚሻሻልም ካለ ከምርጫ በኋላ በሚሰየመው አዲስ የተወካዮች ምክር–ቤት ይታያል የሚል አሳብ ሲሰነዝሩ ይሰማል። ለእነዚኽ ወገኖቸ ያለኝ ጥያቄ፤ ለዚኽ ሕገ-መንግሥት የመፈተሽ እንኳ ዕድል ሣይሰጥና ቢያንስ አስፈላጊ የሆኑ መሻሻያዎች ሣይደረጉ በሚደረግ ምርጫ የተሰየሙ የተወካዮች ምክር-ቤት አባላት በምን አሳማኝ ምክንያትና በምን አስገዳጅ ሁኔታ ነው የተወከሉበትንና ለዚያ ወንበር ያበቃቸውን ሕገ-መንግሥት እንዲሻሻል የሚፈልጉት? ያኔ ማድረግ ይችላሉ ተብሎ ከታሰበስ አሁን ያለው ምክር-ቤት ለምን ተግባራዊ ማድረግ ተሣነው ወይም አልፈለገም? የሚል ነው። አሁን ያለው የተወካዮች ምክር-ቤት አባል ያላደረገውን በተመሣሣይ ሁኔታ የሚመረጠው ያደርገዋል ብሎ ማሰብ ላም አለኝ በሰማይ አጉል ምኞት ይሆናል። ሕገ-መንግሥት እኮ በአጭሩ ዜጎች ለሚያስተዳድሯቸው ኃላፊዎች ሥልጣናቸውን ገድበው የሚሰጡበትና እነሱም ግዴታቸውን ወድደው የሚወስኑበት ሰነድ ነው። በአመጽ ሣይሆን ሕግን ተከትሎና በሰላማዊ መንገድ የሕገ-መንግሥት ጥያቄን ማንሳት ደግሞ የዴሞክራሲ መብት ነው። አይነካ የሚሉ ወገኖች ምን እንደሚያስፈራቸው ግልጥ አይደለም። አገርና የአገር ጉዳይ የጋራ እንጅ ለተወሰኑ ክፍሎች ብቻ ተወስኖ የተሰጠ አይደለም። ጥያቄ ማንሣት ሊፈራ ሣይሆን ሊደፋፈር ይገባል። የሕገ-መንግሥት ባለቤት ደግሞ ምልዓተ-ሕዝቡ ነው። እስኪ በሕዝብ ፊት ግልጥ ውይይት ይደረግና ለውሣኔ-ሕዝብ ይቅረብና ይታይ።  

ዴሞክራሲና ፍትኅን ከፈለግን ዴሞክራሲያዊ ሕገ-መንግሥት እንዲኖር የግድ ይላል። ስለሆነም ጥያቄው የሚነሳው አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር፣ የአገር አንድነት ለአደጋ እንዳይጋለጥና ተስፋ ላለው አዲስ ዴሞክራሲያዊ-ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት እውን መሆን አስፈላጊ በመሆኑ ነው። ስለሆነም፣ የሕገ-መንግሥት ጉዳይ አንድም ምርጫ ከመደረጉ በፊት እንዲታይ፣ ካልሆነም ቀጣዩ ምርጫ ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚቆይ መደበኛ ተወካዮች የሚመረጡበት ሣይሆን የሕገ-መንግሥት ሸንጎ የሚሰየምበት ቢሆን የተጀመረው ለውጥ ሂደቱን የተሳካና ታሪካዊ ውጤት እንዲኖረው ያደርጋል የሚል እምነት አለኝ። ሕዝባችን ዘለቄታዊነት ለሚኖረው ዴሞክራሲያዊ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ባለቤት እንዲሆንና አገራችንን የሚገባት ከፍታ ላይ እንድትደርስ ይኽን ለማድርግ ድፍረቱና ቁርጠኝነቱ ሊኖረን ይገባል። ተስፋም አደርጋለሁ።

፰ኛ. የዜጎችን መፈናቀልና ጭፍጨፋዎችን በተመለከተ፡

ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ የተፈጸሙ የሕዝብ መፈናቀሎችንና ዘግናኝ ጭፍጨፋዎችን፣ እንዲሁም በሰሜን ዕዝ ሠራዊት ላይ የተደረገውን እንዲሁም አሁን የተከሰተውን ደም-አፋሳሽ ጦርነት ተከትሎ በማይ ካድራና በአካባቢው ሰላማዊ ዜጎች ላይ በሕወሓት ሥር በሚንቀሳቀሱ ቡድኖች የተፈጸመውን ማንነትን መሠረት ያደረገ የጅምላ ጭፍጨፋን በተመለከተ ዝርዝር ጥናትና ምርመራ የሚያደርግ ገለልተኛ ልዩ አጣሪ አካል (ኮሚሲዮን) እንዲሰየምና ውጤቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር-ቤት ሊቅርብና ሕዝብ በይፋ እንዲያውቀው ሊደረግ ይገባል። የምርምሩ ዘገባም የሕግ-አስከባሪው ከደረሰበት ጋር ተዳምሮ ወንጅለኞች ከያሉበት ታድነው ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ ያስፈልጋል።

“የሞተውም ባልሽ ገዳዩ ወንድምሽ፣ አዘንሽ ቅጥ አጣ፣ ከቤትሽ አልወጣ” እንደተባለው፣ በአንድ አገር ዜጎች መኻል የሚደረግን የመሰለ አስከፊ ጦርነት የለም። በምንም ምክንያት ይሁን በምን፣ ኢትዮጵያችን ወንድም-ወንድሙን፣ ወገን ወገኑን የሚገድልባት አገር እንዳትሆን ጥረት ማድረግ አለብን። አሁን የተከሰተው ደም-አፋሳሽ ችግር ሁላችንም ቆም ብለን ልናስብ፣ ትምሕርት ሊሆነንና የመጨረሻው እንዲሆን ጠንክርን ልንሠራ ይገባል። በጥቂቶች እብሪት ምክንያት በዚኽ ጦርነት ያጣነው፣ የምናጣውም በጋራ ቆሞ የውጭ ወራሪን ሊመክትና ለሕዝብ አለኝታ፣ ለአገርም መከታ የሚሆንን የራሣችንን ወገን መሆኑን መርሳት አይኖርብንም። እያንዳንዱ የጠፋ ሕይዎት ትቶት የሄደ በሃዘን ልቡ የተሰበረ ቤተሰብ እንዳለም አንርሳ።

እግዚአብሔር አገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክና ይጠብቅልን!!

ድል ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት!!  

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
12,858FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here