
ከኢትዮጵያ ኅብረሕዝብ ብሔራዊ ንቅናቄ (ኅብረሕዝብ-ኢትዮጵያ) የተሰጠ የአቋም መግለጫ፤
ኅዳር ፳፫ ቀን ፪ ሽህ ፲፫ ዓ/ም
ምንም እንኳ ሕወሓት ለሃያ-ሰባት ዓመታት ኢትዮጵያን በበላይነት ሲመራ ከቆየ በኋላ በሕዝብ ትግል
የነበረውን ሥልጣን ካጣ ጀምሮ ከማዕከላዊ መንግሥት ጋር ያለው ግንኙነት ከጊዜ-ወደ-ጊዜ እየሻከረ
መሄዱና ልዩነቱንም በሰላማዊ መንገድ በውይይት ለመፍታት የማይቻልባቸው ምልክቶች እንደነበሩ
ቢታወቅም፣ ከጥቅምት ፳፬ ቀን ፪ ሽህ ፲፫ ዓ/ም ጀምሮ በአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን-ዕዝ ጦርና
በትግራይ በሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ ላይ የፈጸመው አሳፋሪ የክኅደት ወንጀል ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የነበረውን ተስፋ ጨርሶ እንዳከሰመውና ማዕከላዊ መንግሥትም የአጸፋ እርምጃ ለመውሰድ እንዲገደድ አድርጓል።
ይኽ በሕወሓት ጽንፈኛ አመራር የተወሰደ አስነዋሪ እርምጃ ተራ ወንጀል ሣይሆን፣ ማንም ሉዓላዊ
አገር ሊቀበለው የማይችልና በምንም መንገድ ሊታለፍ የማይገባን ቀይ-መሥምር የጣሰ ፀያፍ ድርጊት፣
እንኳን ኢትዮጵያችን ለባዕዳን የጥቃት አደጋ ተጋላጭ በሆነችበትና የዜጎቿን አንድነት አጥብቃ በምትሻበት ቀርቶ በማንኛውም ጊዜ ቢሆን በአገር ኅልውና ላይ የተፈጸመ ከፍተኛ የክኅደት ወንጀል በመሆኑ፣ ልዩነቱ በገዥው ፓርቲና በሕወሓት መኻል ከመሆን እንዲያልፍና በኢትዮጵያ ሕዝብና በሕወሓት መኻል እንዲሆን አድርጎታል።