
ዳምጠው ተሰማ ደነቀ
ታህሳስ 5 , 2013 ዓ. ም.
የአማራ ክንፍ ብልጽና ፓርቲ እና አመራሮች እንዲሁም ከአዲስ አበባ በስተደቡብ ያሉ አንዳንድ ፖለቲከኞች ‘‘ሃቀኛ ፌደራሊዝም (Genuine federalism)’’ እንደሚያስፈልግና ይህም ለኢትዮጵያ ሀገረ-መንግስት ዋስትና እንደሆነ በአጽዖት ሲገልጹ ያስተዋለው ጋዜጠኛ የሺሳብ አበራ ሃሰብ እንድሰነዝር ይህን ጽሁፍ ለማሰናዳት ችያለሁ፡፡ እኔም መግለጫዎቹን ስመከላታቸው እኩልነትን፣ ዲሞክራሲና ብዝሃነትን የሚያከብር፣ ብልጽግን የሚያመጣ፣ መቻቻልንና አብሮነትን የሚያሰፍን የፌደራል አስተዳደር እንገንባ የሚል አውድ አላቸው፡፡ በዚህም መነሻነት በጉዳዩ ላይ መርህ ተኮር ምልከታዎቼን አስቀምጫለሁ፡፡
በጽንሰ-ሃሳብ ደረጃ ‘‘ሃቀኛ ፌደራሊዝም (Genuine federalism)’’ እና “ወስላታ (pseudo-federalism)’’ ፌደራሊዝም የሚባል ክፍልፋይ የተለመደ አይደም፡፡ የፌደራል ስርዓትን አተገባበር ለማመላከት ብያኔ ለመሰጠት ካልሆነ ሃቀኛ ፌደራሊዝም እና የውሸት ፌደራሊዝም የሚል የአስተዳር ዓይነትን የሚመለከት አስተምሮም የለም፡፡ በአመክንዮ ካየነውም አንድ አሃዳዊ ያልሆነ አስተዳደር በሳይንሳዊ መለኪያ ተመዝኖ የፌደራል ስርዓት መምሰል ካልቻለ “ሃቀኛ ያልሆነ የፌደራል አስተዳደር እየተከተልን ነው” የሚል ብያኔ መስጠት ሳይገባን የፌደራል አስተዳደር አልሰፈነም ማለቱ የተሻለ ነው፡፡
ፌደራሊዝም የሚለውን ጽንሰ-ሃሳብ ስናነሳ ስለሳይንሳዊ ባህሪያቱ እና ትግበራው (Art) ማውሳታችን የሚጠበቅ ነው፡፡ የፌደራሊዝም ሳይንስ ዘርፍ ያልተማከለ ዲሞኪራሲያዊ አስተዳደር መርሆች ላይ መመራመርን፣ ንድፈ-ሃሳብ ተኮር መማማርን፣ ዘመኑንና ሁኔታዎችን መጣኝ የአስተዳር ስልቶች ፈጠራን፤ የፖለቲካ-ኢኮኖሚ (በአብዛኛው ከፖለቲካ ውሳኔ ጥገኛ የሆነው የፊስካል ፌደራሊዝም ምሰሶዎች ላይ ያተኮረ) አስተዳደርን ማጥናትን፣ የጋራና የግል የስልጣን (shared and self-rules) ሚዛን ባህሪያት መተንተንን፣ የጎንዮሽና የሽቅብታ (Horizontal and vertical relationship) ግንኙነት ጤናማነት መርሆች ብያኔንና ዲስኩርን፣ የፌደራል ስርዓት የንጽጽር ጥናትን የሚመለከት ነው፡፡
ሳይንሱ አብረው ያልነበሩ አካልት ተጠረቃቅመው (coming together) መደመር እና ቀድሞ የነበረን አሃዳዊ የመዋቅር ግንኙነት አላልቶ በአብሮነት (holding together) የመኖርን ሂደቶች የሚመለከቱታሪካዊና ወቅታዊ ኩነቶችን የሚያጠና ነው፡፡
በተጨማሪም የማዕከላዊ መንግስቱንና የክልሎቹን የጋራና የተናጠል ስልጣኖች የአወቃቀር መሰረቶች እና የፌደራል ስርዓት አወቃቀር የመርህና የአፈጻጸም ውስንነቶች ወዘተ… ጽንሰ-ሃሳቦች የሚወሱበትም ነው፡፡ የትርጓሜ እና የጽንሰ-ሃሳብ አንጻራዊ ብያኔም በሳይንሱ ውስጥ የሚያልፍ ነው፡፡
ከነዚህ አይነት አተያዮች ውጭ ሃቀኛ ፌደራሊዝም እና የውሸት ፌደራሊዝም የሚባል የጽንሰ ሃሳብ ክፍልፋይ የተለመደ አይደለም፤የውሸት ወይም ወስላታ ፌደራሊዝም የሚል ያልተማከለ አስተዳር ብያኔም ከአፈጻጸም ጋር የሚገናኝ ነው፡፡ የፌደራሊዝም አተገባበር ከመርሆች ተፋልሶ ሲገኝ የውሸት ወይም ወስላታ አሊያም ሃቀኛ ያልሆነ የሚል ተለምዷዊ ስያሚ ሊሰጠው ይችል ይሆናል፡፡ ይህም ችግር ሲኖር ለችግሩ መጣኝ የዳቦ ስም ሰጥቶ ወደ መፍትሄው ለመመልክት የሚደረግ ጥረት አካል ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡
የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ተንተርሰን ጉዳዩን ብንመለከተው ‘‘ሃቀኛ ፌደራሊዝም (Genuine federalism)’’ የሚለው አገላጽ የፖለቲከኞች እና የፖለቲካ ድርጅቶች መግለጫዎች እዝማች ሆኗል፡፡ እንደ እውነቱ ተቋማዊ አሰራር ከነገሰ፣ የመንግስታቱ የጋራ ስልጣን ከራስ ገዝነት ጋር ከተጣጣመ፣ የህዝቦች የጋራ ራዕይ እውን ከሆነ፣ ዲሞክራሲና እኩልነት ከሰፈነ ወዘተ ፌደራል ስርዓቱ ሃቀኛም ተብሎ ቢገለጽ ችግር አይኖረውም፡፡ የአንድ ሃገር የፌደራል ስርዓት አተገባበር ከፌደራሊዝም አስተምሮ መርሆች አንጻር ትንታኔ ሊሰጥበት አመርቂ ከሆነም ሀቀኛ ፌደራሊዝም ተብሎ ቢጠራ የሚከለክል አስተምሮም የለም፡፡ እንደኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ “የተገንጣይነትን አራማጅ ቡድኖችንና” “የአሃዳዊያንን” ፍላጎት በማጣጣም ጤማና ሀገረ-መንግስት ቀጣይነት ማረጋገጫ መኖሩም “የፌደራል አወቃቀር” ትግበራ ማሳያ ተደርጎ ሊቀርብ ይችል ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓት አተገባበር ታሪክን መመልከቱ ሀቀኛ ፌደራሊዝም (አገላለጹ ተለምዷዊ ተደርጎ ቢወሰድግን የተሻለ ነው) የሚለውን የሰሞነኛ ጩኸት አውድ ለመረዳት የሚያመች ይመስለኛል፡፡ እኤኣ በ1955 ኤርትራን ከኢትዮጰያ ጋር ያዋደደ ፌደራላዊ አስተዳደር የታወጀ ቢሆንም በተግባር መለኪያ ግን ለይስሙላ የነበረ ሲሆን ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ በመላው ሀገሪቱ የፖለቲካ ጨዋታ ህግ እንዲሆን የተደረገው የፌደራል ስርዓት የህዳጣንን አምባነንነትን ማስቀጠያ- የከፋፍለህ ግዛ ማስፈጸሚያ መሆኑ የአደባባይ ሀቅ ነው፡፡ በተለይ የበርካታ ክርክሮቻችን መነሻ የሆነው የድህረ-1983 ዓ.ም. የፌደራላዊ አስተዳደር ትግበራችን የመጤና ነባር ብያኔ፣ የበዳይ-ተበዳይ ትርክት እና ያልተቀደሰ ውሸት (bad lie) ማስፈጸሚያ ነበር፡፡
የመተግበሪያ ህጉቹ እና አፈጻጸሙ የሃገርን ቀጣይነት ከማረጋግጥ ይልቅ ለፓርቲ ህልው ማበብ የሚያደላም ነበር፡፡ እንዲሁም በጋራ ስልጣን እና ራስን የማስተዳደር ስልጣን ዘፈቀዳዊ በሆነ አግባብ በአውራ ፓርቲ ፍላጎት የሚሰጡና የሚነጠቁ መሆናቸው የፈደራል ስርዓቱ ቅቡልነት እንዳይቸረው የሚያደርገግ መሆኑ መገመት አይከብድም፡፡ ይህም የትላንት ታሪኩ የጠለሸ ለነገ ተስፋ የሚጣልበት ስለማይሆን፡፡ ማንኛውም የስሜት ሃዋሳት ያሉት ሰው ቢሚገነዘበው ደረጃ ባፉት 30 ዓመታት የከፋ ዜጎች ሰቆቃ ነበር፡፡ጥቂት መቶዎች ብሄረሰብ ነን በሚል በቡድን መብት ጠገግ ስር ከተሰለፉ የሚሊዮኖችን መብት የመዳጥ እና የሚሊዮኖችን እጣ ፈንታ እንዳሻቸው የመወሰን እድል የተቸሩበትም ሁኔታ አለ፡፡ ይህ እየሆ ባለበት ወቅት የብሄር ብሄረሰቦች ዋስትና የሆነ የፌደራሊዝም እየተከለተልን ነው ከሚል መንግስታዊ ዲስኩር ውጭ የመስማት እድል አልነበረም፡፡ በለሆሳስ መከራን የሚያበዛ ስርዓት የሚመሰገንባት አንቆቅልጽ የሆነች ሃገር ከማለት ውጭ የሰላ ትችት አቅርቦ የማሰማት እድል የለም፡፡
በመሆኑም ፌደራላዊ አወቃወርና መርሆቹ ለኢትዮጵያ ይበጃሉ ብለው የሚያምኑ ካላት ባለፉት ሶስት አስርት አመታት የነበረው የፌደራል ስርዓት ስሪት ኢ-ዲሞክራሲያዊ ሃቀኛ ያልነበረ ነው የሚል ድምዳሜ ስለሚኖራቸው ነገ ላይ `ሃቀኛ ፌደራሊዝም ይኑረን የሚል ጥሪ ሊያቀርቡ እንደተገደዱ እገምታለሁ፡፡ ሀቀኛ ፌደራሊዝም የሚለውን ሀረግ አዘውትረው ይግለጹት አንጂ በፌደራሊዝም ስም የተበላሸ የትላንት ግንኙነታችን እንዳይደገም እና ቀደም ሲል የነበረው የይስሙላ ፌደራሊዝም ያስከተለው ቁርሾ እንዲታረም “የተሟል፣ ትክክለኛ፣ ጤናማ ፌደራሊዝም ወዘተ… እንሻለን የሚል ሃሳብ ሊሰነዝሩም ይችላሉ፡፡
በማያሻማና አካታች በሆኑ የህግ ድንጋጌዎች የተቃኘ የማህበረሰብንና የክልሎችን ጤናማ ግንኙነት የሚያጎለብት፣ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብን ቀጣይነት የሚያረጋግጥ፣ በብዝሃነት ውስጥ የጋራ ራዕይና እሴቶችን የሚፈጥር ዲሞክራሲዊ ፌደራሊዝም እውን ማድረግ “ሃቀኛ” ወይም “የውሸት ፌደራሊዝም” የሚሉ አተገባበር አመላካች ብያኔዎች አጀንዳ የመሆን እድል አይኖራቸውም በሚለው ላይ የጋራ አረዳድ ቢኖር ጥሩ ነው፡፡
በመጨረሻም “ሃቀኛ ፌደራሊዝም ነው ሀገሪቱን የሚታደጋት የሚለው ገለጻ” የትላንቱን ዝንፈት የሚያመላክት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ይህንም ከአውድ አንጻር ከተረዳነው “የቡድንና የግለሰብ መብቶች ተጣጥመው ያለመስተናገድ፣ የጋራ ራዕን ሚንዱ መርሆችና አፈጻተሞች መስተዋላቸው፣ በአግላይነት ላይ የተመሰረተ የአስተዳር ስርዓት መኖሩ፣ የከፋፍለህ ግዛ ሴራዎች መፈጸማቸው ወዘተ…ከፌደራል ስርዓት መርሆች ፍጹማዊ ተቃርኖ ያላቸው በመሆኑ ከትላንት ግድፈቶቻችን ተምረን የሁላችን የሆነች ዲሞክራሲያዊ ፌደራላዊት ሀገር ትኑረን” እንደማላት ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡
___
ዳምጠው ተሰማ ደነቀ በደብረብርሃን ዮኒቨርሲቲ የዓለምዓቀፍ ግንኙነት ያስተምራሉ
ከአዘጋጁ : በዚህ ድረ ገጽ በነጻ አስተያየት አድም ላይ ጥሁፍ ለማሳተም ከፈለጉ በሚከተው ኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com