
በጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ
ታኅሣስ 11 2013
ከላይ በርዕስ የተጠቀምኩትን፤ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሙት፤ የሞሶሊኒ አማችና የጣልያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የነበሩት ጅያኖ ጋላትሶ ቺያኖ “La victoria trova cento padri, e nessuno vuole riconoscere l’insuccesso.” ሲሉ ነበር የገለጹት። ይህ ብሂል እውነትነት እንዳለው በብዙ ሁኔታዎች የታየ ለመሆኑ በርካታ ማስረጃዎች አሉ። የሰው ልጅ በተፈጥሮው፤ ተሸናፊነትን ይጸየፋል። ተሸንፎ እንኳን “አሸንፍያለሁ” ብሎ መፎከር የተለመደ ነው። ብዙ ሳንርቅ ይህንን በሃገራችን እንኳ፤ ባለፉት 30 ዓመታት በተደጋጋሚ አይተናል። የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ ስዩም መስፍን፤ የኢትዮጵያን ሏአላዊነት፤ በአለም መድረክ ላይ ካስደፈሩ በኋላ፤ ዓይናቸውን በጨው አጥበው፤ የአልጀርሱ የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ድርድር በእኛ “አሸናፊነት” ተጠናቋል ብለው፤ ሕዝቡ በአደባባይ ሰልፍ ወጥቶ ደስታውን እንዲገልጽ አድርገውታል። ለሕዝብ የተነገረው ውሳኔ፤ ሃሰት መሆኑ ሲጋለጥ፤ የወቅቱ መንግስት ሕዝቡን ይቅርታ አልጠየቀም፤ በዋሾው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ላይ ምንም ዓይነት እርምጃ አልወስደም። ይህን የመሰለ ውርደት ተከናንበን፤ “በተከድኖ ይብሰል” እሳቤ አልፈነዋል።
የኤርትራ መንግሥት፤ የኢትዮ-ኤርትራ የወሰን ውዝግብ ገና በድርድር በነበረበት እና፤ የኤርትራ የድንበር ኮሚሽን አባላት፤ ለድርድር አዲስ አበባ በነበሩበት ስዓት ነበር፤ በወቅቱ፤ የኢትዮጵያ ግዛት የነበረውን ወሰን ጥሶ፤ ሰራዊቱን እና ታንኩን ይዞ፤ በሃገራችን ላይ ወረራ የፈፀመው። በዚህ ሻዕብያ በለኮሰው ጦርነት፤ አይቀጡ ቅጣት ቢቀጣም፤ ለሕዝቡም ለዓለምም “አሸንፍያለሁ” ሲል ነው እስካሁንም የሚዘግበው። አስገራሚው ነገር፤ ሻዕብያ አሸንፍያለሁ፤ የሚለው፤ ግዛቴ የሚላቸው መሬቶች፤ አሁንም በኢትዮጵያ ቁጥጥር ሥር ሆነው ነው። በሰሞነኛው የኢትዮጵያ መንግሥት የሕግ ማስከበር ሂደትም፤ ይህንኑ ድራማ ከወያኔ ስናደምጥ ነበር። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፤ መቀሌ አፋፍ ላይ ሆኖ፤ የወያኔ ባለሥልጣናት፤ አክሱምን እና ሁመራን አጥቅተን መልሰን ተቆጣጥረናል ሲሉ ፈገግ አሰኝተውናል።
በሃገራችን ታሪክ በተደጋጋሚ እንዳየነው፤ ሁሉም የድል ተሻሚ የሆነ አባዜ አለበት። ከሁለት ዓመታት ተኩል በፊት ሕወሃትን ከሥልጣን ያፈናቀለው፤ “ጀግናው ቄሮ ነው” በሚል ትርከት፤ ህዝቡ ለ27 ዓመታት በተለያየ መንገድ ያደረገውን ትግል እና፤ ለዚህ ውጤት የበቃበትን መንገድ ለማኮሰስ ተሞክሯል። እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ማንም ይሁን ማን “የአንድ ዘር ጀግና የለውም” የሰው ልጅ ሁሉ የተፈጠረው በሰውነት ነው። አንዱ ዘር ከአንዱ ዘር የሚለየው የተለየ ችሎታም ሆነ ሥጦታ የለውም። በእርግጥ፤ ግለሰቦች በማንኛውም ማህበረሰብ ውስጥ ልዩ ተሰጦ ኖሯቸው ሊወለዱ ይችላሉ፤ በሚኖሩበት ማህበረሰብም፤ ተሰጧቸውን ሊያዳብሩ የሚችሉበት ምቹ አጋጣሚ ሊኖር ይችላል፤ ነገር ግን፤ ሁሉም አይሁዳዊ አልበርት አነስታይን፤ ሁሉም ሶርያዊ እስቲቭ ጃብ፤ ሁሉም አሜሪካዊ ቢል ጌት፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አበበ በቂላ ወይም ዶ/ር አክሊሉ ለማ አይደለም። ለጀርመን የአንደኛ እና የሁለተኛ አለም፤ ጦርነቶች ክፉኛ አወዳደቅ፤ “ጀርመናዊ ከማንም የሰው ልጅ የተለየ እና የበለጠ ነው፤ ማንንም ማሸነፍ ይችላል” በሚል የመከነ አስተሳሰብ በትዕቢት የተወጠረ ስለነበር ነው። እንዲህ ዓይነት ትእቢት ግን ለጀርመን እንዳልበጅ ታሪክ ያስተምረናል።
ሃያሏ አሜሪካ፤ በቬትናም እና በሶማሊያ የተጎናጸፈችው ሽንፈትም፤ ከዚህ ትዕቢት የመነጨ ነው። ሕዝብን እንረዳለን ብሎ ሶማሊያ የገባ ሰራዊት፤ በሃገሪቱ መሪ ጄነራል መሃመድ ፋራህ አዲድ ላይ ጦርነት በመክፈቱ፤ የአሜሪካ ሰራዊት፤ በሶማሊያ አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቷል። ይህ የሚያመለክተን፤ ጦርነቶች ፍትሃዊ ሲሆኑ፤ ጊዜው ቢረዝምም፤ ብዙውን ጊዜ የሚያሸንፈው ለፍትሕ የቆመ ሃይል መሆኑን ነው። ኢፍትሃዊ ጦርነቶች፤ ውጊያቸው በአሸናፊነት ቢጠናቀቅም እንኳን፤ በሰተመጨረሻ ጦርነቱን የማሸነፍ ዕድላቸው የመነመነ ነው። በጥቅምት 1928 ጣልያን ኢትዮጵያን ስትወር፤ ውጊያ አሸንፋ፤ ሃገራችንን ለአምስት አመታት ተቆጣጥራ ነበር፤ ውጊያውን ብታሸንፍም ግን፤ ጦርነቱን አላሸነፈችም። ከአምስት አመታት የአርበኞች መሪር ትግል በኋላ፤ ኢትዮጵያ እና አጋዥ ሃይሎቿ ጣልያንን ድል ማድረግ ችለዋል። ጣልያንን ካሸነፍን በኋላ ግን፤ ባንዳ እና አርበኛ በሚል ተከፋፍለን፤ ሃገራችንን ወደ ኋላ በጎተተ በርካታ የፖለቲካ ሴራዎች ተተብትበን አልፈናል።
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ በመቀሌ በሰራዊቱ መሃል ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፤ ከዚህ ድል በኋላ እርስ በእርስ እንዳንከፋፈል በአደራ አሳስበው ነበር። ይህ ድል “የከበደ ወይም የተሰማ አይደለም፤ የሁላችንም ድል ነው” ሲሉም አስረግጠው ተናግረዋል። ምድር ላይ ያለው እውነታ የሚጠቁመን ግን፤ ይህ መልዕክት ሙሉ ለሙሉ በውስጣችን ዘልቆ እንዳልገባ ነው። ብንቀበለውም ባንቀበለውም መሪሩ ሃቅ፤ ለዚህ ውጊያ በፍጥነት እና በብቃት መጠናቀቅ ምክንያቱ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀፎው እንደተነካ ንብ ከጫፍ እስከ ጫፍ በመነሳቱ ነው። የመከላከያው ሰራዊት፤ በአማራ ክልል ልዩ ሃይል እና ሚሊሽያ፤ በአፋር ክልል ልዩ ሃይል እና ፖሊስ ሰራዊት ቀጥተኛ ተሳትፎ፤ እንዲሁም፤ በሌሎች ክልሎች፤ የልዩ ሃይል አባላት እና ፖሊስ አባላት፤ ተሳትፎ፤ በአዲስ አበባ ፖሊስ እና የፌደራል ፖሊስ ተሳትፎ፤ እንዲሁም በመላው ሕዝባችን ደጀንነት ባይታገዝ ኖሮ፤ ዛሬ የምናጣጥመውን የውጊይ ድል፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ማጣጣም አንችልም ነበር።
ይህንን ሃገራዊ ድል፤ የአንድ ወገን ብቻ “ድል” አድርገው “የሚፎክሩ ሃይሎች፤ ውጊያው እንጂ ጦርነቱ ገና እንዳላበቃ አልተረዱም። ምንም እንኳን ሹማምንቶቻችን፤ “ጦርነቱ አብቅቷል” ቢሉንም፤ ጦርነቱ ተጀመረ እንጂ፤ አላበቃም በማለት፤ መራራውን እውነት እንዲያጤኑ፤ ደውሉን መደውል የግድ ይላል። ብዙዎቻችን ከሻዕቢያ እና ከሕወሃት ውድቀት ያልተማርነው ብዙ ነገር እንዳለ ድርጊቶቻችን ያሳብቃሉ። በተለይ ደግሞ ዛሬ፤ ሁሉም የሚድያ ባለቤት፤ ሁሉም የፖለቲካ ተንታኝ እና የወታደራዊ ስትራቴጂ ነዳፊ፤ ጦርነቱ፤ ልክ እንደ ምድሩ ጦርነት፤ በበይነ መረብ በሆነበት በዚሀ የሥልጣኔ ዘመን፤ ድል አብሳሪውን፤ አጀጋኙን፤ አሸማቃቂውንና፤ “ሊቀ ሊቃውንቱን”፤ እንደልቡ ሲፈነጭ ከልካይ በሌለበት በዚህ ወቅት፤ ውጊያውን እንጂ ጦርነቱን እንዳላሸነፍን ካለመገንዘብ የምናደርጋቸው ድርጊቶች፤ ከፊታችን የተደቀነውን የጦርነት አደጋ ከባድ፤ ችግሩንም እጅግ ውስብሰብ ያደርገዋል።
ከታሪካችን ያልተማርነው እና የዘነጋነው ነገር፤ የሻዕብያ መራሹ የሕወሃት እና አጋፋሪውቹ ቡድን፤ የወታደራዊውን መንግስት ከሥልጣን አስወግደው፤ ሃገራችንን ሲቆጣጠሩ፤ ወቅቱ ውጊያው ያበቃበት እንጂ፤ ጦርነቱ ያበቃበት ወቅት እንዳልነበረ ነው። እነዚህ ተዋጊ ሃይሎች፤ ከአማፂነት ወደ ሃገር አስተዳዳሪነት እራሳቸውን ሊቀይሩ ባለመቻላቸው እና፤ ውጊያውን እንጂ ጦርነቱን እንዳላሸነፉ ካለመግንዛባቸው፤ በርካታ ሃገር እና ትውልድ አጥፊ የሆኑ ከፍተኛ ስህተቶች ፈጽመዋል። እነዚህ ሃይሎች ያልተረዱት ነገር፤ ውጊያውን ያሸነፉት፤ ሕዝቡ ከወታደራዊው መንግስት ጎን ባለመቆሙ፤ በውጭ እና በውስጥም፤ በተለያዩ መንገዶች፤ በነበረው መንግስት ላይ አመጽ እና ጥቃት ይፈጸም ስለነበር ነው። ከዚህም በተጨማሪ፤ በወታደራዊው መንግስት ከፍተኛ ጥላቻን ያነገበው ሕዝብ፤ ስንቅ እየሰጠ፤ ቦታ እየመራ እና መረጃ እያቀበለ፤ ለአማጽያኑ ክፍተኛ ድጋፍ በመስጠቱ ነበር፤ ድል የተጎናጸፉት። ከዚህም አልፎ፤ ጦርነቱ አለም አቀፋዊ ይዘት ስለነበረው እና፤ አማጽያኑ በአሜሪካን የስለላ ድርጅት እና፤ በኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች እየታገዙ፤ ወደ 4 ኪሎ ቤተ መንግስት መግባታቸውን ዘነጉ። ከወታደራዊው መንግስት ጋርም የተደረግው ውጊያ 17 ዓመታትን የፈጀ፤ የብዙ ወጣቶችን ሕይወት የቀጠፈ እና በሚሊዮኖች ብር የሚገመት ንብረት ወድሞ መሆኑንም እረሱት። ጦርነቱን “የኬክ ጉዞ” የሚያስመስል ስዕል በመሳል፤ “ከእኛ በላይ ጀግና የለም” “250 ሺህ ጦር ያለውን እና በዘመናዊ ትጥቅ የታጀበን ሰራዊት አሸንፈናል”፤ ወዘተ በሚል ዲስኩር፤ “ጦርነትን መዋጋት ብቻ ሳይሆን፤ ጦርነትን መስራት እንችላለን” በሚል፤ ግብዝነት እና ትእቢት በመወጠራቸው፤ ውጊያውን እንጂ ጦርነቱን እንዳላሸነፉ በቅጡ ሳይረዱት ቀሩ።
ወያኔ እና ሻዕብያ፤ የኢትዮጵያን መንግስት እና ሃገር፤ ለሁለት ከፍለው፤ ሕዝቡን መግዛት ከጀመሩባት ሰከንድ ጀምረው ጦርነት ላይ ነበሩ፤ ይህንን ግን በቅጡ አልተረዱትም። ያሸነፉትን ውጊያ፤ የሕዝብ ውጊያ መሆኑን እና፤ በተለያየ ቡድን ተሰልፎም ይሁን በተናጠል በሚችለው አቅም ሁሉ የታገለው እና የተዋደቀው ሁሉ የዚህ ድል ባለቤት መሆኑን ዘንግተው፤ ትግሉ ከአስከፊው ሥርዓት ጋር እንጂ ከሕዝቡ ጋር አለመሆኑን የተሸበቡበት የትዕቢት ሰንሰለት አላሳይ ብሏቸው፤ ሕዝቡን እንደማስተባበር፤ ለአንድ ሃገር ሏአላዊነት እንዲቆም ከማድረግ ይልቅ፤ “በከፋፍለህ ግዛ መርህ” የራሳቸውን ሥልጣን ለማራዘም እና የጥቂት አመራሮችን ዘመድ አዝማዶች በሃብት ለማደለብ፤ ወርቃማውን አጋጣሚ፤ ሳይጠቀሙበት ቀሩ። ሻዕቢያም፤ የኤርትራን ሕዝብ እረግጦ በመግዛት፤ “ጦርነቱን ያሸነፍነው እኛ ነን፤ ከእኛ በላይ ጀግና ለአሳር ነው” በሚል የወጠጤ ስሜት፤ እንደ አበደ የሰፈር ጎረምሳ፤ የአካባቢውን ሃገራት ሁሉ ይተናኮል ጀመር።
አወቅነውም፤ አላወቅነውም፤ ሕወሃት ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ፤ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ጦርነት ላይ ነበር። እኔ እንደሚገባኝ፤ ጦርነትን ሙሉ ለሙሉ አሸነፍን ልንል የምንችለው፤ የሕዝቡን ልብ ስናሸንፍ ብቻ ነው። የሕዝቡን ልብ ማሸነፍ የማይችል ማንኛውም ሃይል፤ በትንሹም ይሁን በትልቁ ሁሌም ከሕዝቡ ጋር በጦርነት ውስጥ ነው የሚቆየው። ሕወሃት በሥልጣን በቆየባቸው 27 ዓመታት፤ ሃገራችን፤ በተረጋጋ ሁኔታ የቆየችበት አንድም ወቅት አልነበረም። ተረጋግቷል ተብሎ በታሰበበት ወቅት ሁሉ እንኳን፤ የማይሰሙ፤ የማይታዩ “የዝምታ ጦርነቶች” ነበሩ። ሕወሃት ሃገሪቱን በዘር ከፋፍሎ ሁሉንም ነገር እኔ በጉልበት አደርጋለሁ ካለባት ሰከንድ ጀምሮ፤ የመላው ሕዝብ ልብ ሸፍቶ፤ ከሕወሃት ጋር ጦርነት ገጥሟል። ይህ ያላባራ ጦርነትም ነው ዛሬ ሕወሃትን ከመንግስትነት ተሸቀንጥሮ ወድቆ’ ወደ አማጺነት ጉድጓዱ እንዲመለስ ያደረገው እና በውጊያው የተሸነፈው። የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ይህንን ውጊያ በድል አጠናቋል። መሰረታዊ ጥያቄው ግን፤ ጦርነቱን አሸንፈናል ወይ ነው። የትግራይን ሕዝብ ልብ’ስ ሳናሸንፍ፤ ጦርነቱን ማሸነፍ እንችላለን ወይ? ለዚህስ የእያንዳንዳችን አስተዋጽኦ ምን መሆን አለበት? በውጊያው ድል ተኩራርተን፤ በአግላይነት ስሜት፤ እንዲሁም እኛና-እነሱ በሚል ብሽሽቅ እና ንትርክ፤ ሃገራችንን፤ ወደ የምንፈልገው ዘላቂ ሰላም ማስጓዝ እንችላለን ወይ? የአንዱን ዘር በማጀገን፤ የሌላውን ዘር በማንኳሰስ፤ “የድሉ አባት እኔ ነኝ” በሚል የግብዝነት አባዜስ፤ የግጭት አዙሪትን መስበር እንችላለን ወይ?
እነዚህ እና መሰል ጥያቄዎች መመርመር እና መመልሰም ይኖርባቸዋል። ዛሬ የምናያቸው ነገሮች የሚጠቁሙን ከሕወሃት አወዳደቅ ተምረን፤ የአስተሳሰብ አቅጣጫችንን አለመለወጣችንን ነው። ትላንት፤ አማራውን ወጣት፤ የግንቦት 7 ወይም የቅንጅት አባል እያለ ሲያሳድድ ከነበረው ጽንፈኛው የወያኔ ሃይል ከመማር እና፤ በማንነት ላይ የሚደረግን ጥቃት በጽኑ ከመታገል ይልቅ፤ ትግሬ ሁሉ ወያኔ ነው ወደ የሚል የጽንፈኛ ሃይሎች ትርከት እየተሸጋገርን መሆናችን ሁላችንንም ሊያሳስበን ይገባል። በዚህ አካሄድ ከቀጠልን፤ ጦርነቱ ማብቅያ አይኖረውም። በወያኔ ስርዓት፤ “በየጥንቸል ጉድጓዳቸው ተደብቀው” የነበሩ፤ ዛሬ ግን ለውጡ በፈጠረው አጋጣሚ፤ ቀና ብለው በጫሩት ጽሁፍ፤ በተቸራቸው ጭብጨባ ሰክረው፤ “ከእኛ በላይ ኢትዮጵያዊ ለአሳር ነው” የሚሉን “አዲሶቹ ጋዜጠኛ አክቲቪስቶች” እንዲሁም እራሳቸውን ጉምቱ ፖለቲከኛ አድርገው የሚገምቱ ጽንፈኞች፤ ጦርነቱ ሲጀመርና የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሽያ፤ በሕወሃት ጦርነት ጥቃት ተፈጽሞበት ወደ ጦርነቱ ሲገባ፤ “ዐብይ አሕመድ አማራውን ከፊት አሰልፎ ሊያስጨፈጭፈው ነው፤ የአማራው ልዩ ሃይል ለማን ብሎ ነው ጦርነት ውስጥ የሚገባው” በሚል ትርከት፤ የአየር ሞገዱን፤ የማህበራዊ ሚድያውን እና የጋዜጣ አምዶችን አጣበው ነበር።
እነዚህ ሰዎች፤ ሕወሃት ለዓመታት በሸበባችው ፍርሃት ውስጥ፤ የራሳቸው የሕሊና እስረኞች ሆነው፤ በምናባቸው ይታያቸው የነበረው “የሕወሃት አሸናፊነት” ስለነበር፤ በአማራው ሕዝብ ላይ ለመነገድና የፖለቲካ ትርፍ ለማጋበስ፤ ብዕራቸውን አሹለው የሚጠብቁት፤ እነሱ “የዐብይ አሕመድ ሽንፈት የሚሉትን” የሃገር ሽንፈትን ለመዘገብ ቋምጠው ነበር። የአማራው ተቆርቋሪ በመምስል፤ መሰረተ ቢስ ዕይታቸውንም፤ የፍርሃታቸው መሸሸጊያ አድርገውት ቆይተዋል። ሆኖም፤ ሕወሃት አይቀጡ ቅጣት ሲቀጣ፤ የመጀመሪያዎቹ “የድሉ ፊታውራሪ በመሆን”፤ “ድል አድራጊው የአማራ ኃይል ከድል ሲመለስ አፈ ሙዙን በብአዴን ላይ ያዙር” ሲሉ የመርዝ ኪኒናቸውን ሲነሰንሱ ለማየት በቅተናል።
ይኽው ጽንፈኛ ሃይል ነው፤ “የሃገር ልጅ፤ የማር እጅ” በሚል መሪ ቃል፤ ሕዝቡን አስተባብሮ፤ ለትግራይ ክልል እርዳታ ለማሰባሰብ የተነሳውን የኪነ ጥበብ ባለሙያዎቻችንን ጥሪ፤ ለማደናቀፍ ተግቶ የሰራው። ኦሮምያ ክልል፤ ቤኒሻንጉል እና ሶማልያ ክልል አማራው ሲፈናቀል እና ሲገደል፤ “የኪነ ጥበብ ባለሙያዎቹ የት ነበሩና ነው፤ ዛሬ ማይካድራ ላይ አማራን ጨፍጭፈው ወደ ሱዳን ለተሰደዱ ሰዎች እርዳታ የሚያሰባስበው” በሚል የፈጠራ ትርከት፤ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን ስልክ ደውሎ እና በማህበራዊ ሚድያ ዘመቻ በማሸማቀቅ፤ የእርዳታ ማሰባሰቡ በጎ ተግባር ላይ፤ አሳዛኝ ተጽእኖ ፈጥረዋል። ጽንፈኛው ሃይል በሕዝብ ስም ለመነገድ፤ በሕዝብ ስቃይ ለማትረፍ ሲከጅል ይህ አዲስ አይደለም። በ1990ዎቹ (እንደ አውሮፓ አቆጣጠር)፤ ይህንን ክሰተት አይተነው ነበር። ጽንፈኛው ሃይል፤ አቧራውን አራግፎ፤ ከተደበቀበት ሥርቻ ማንነቱ ላይ ጭምብል ለጥፎ “ከኔ በላይ ተቆርቋሪ ለእሳር” በሚል ግብዝነት ብቅ ቢልም፤ ሥራው ማንነቱን ፍንትው አድርጎ ያሳይበታል። ይህ “ትግሬ ጠል” ሃይል፤ ሌላው ቀርቶ በሰሜን አሜሪካ እንኳ ኢትዮጵያውያንን በማሸማቀቅ፤ ሬስቶራንት ውስጥ ትግርኛ እንዳይዘፈን፤ “ሌላው ኢትዮጵያዊ” ከትግርኛ ተናጋሪው ጋር እንዳይገበያይ፤ እንዲሁም ትግሬ እና ሕወሃት/ሻዕብያ አንድ ናቸው በሚል ትርከት፤ በአንድነት ሥም እየነገደ ሕዝባችንን የከፋፈለ ሃይል ነበር። ይህን ሃይል አደብ ግዛ የሚለው በመጥፋቱ፤ “እራሱን በኢትዮያዊ ማንነት ማማ ላይ ሰቅያለሁ” ብሎ፤ ለሌላው ዜግነትን በመስፈር፤ ለዓመታት “የሚፈራ ሃይልም” ሆኖ ቆይቶ ነበር። በወቅቱ በደቡብ ኢትዮጵያ በተከሰተው ርሃብ፤ የኪነ ጥበበ ጠበብቶቹ፤ ጋሽ ደበበ እሸቱ እና ጥላሁን ገሰሰ ወደ ዋሽንግተን ዲሲ መጥተው፤ በወቅቱ ከነበረው የኢትዮጵያውያን የሰሜን አሜሪካ የሙዚቀኞች ማህበር ጋር በመተባበር፤ በጠኔ ለተጎዳው ሕዝባችን እርዳታ ለማሰባሰብ ሲሞክር፤ “እርዳታውን ማሰባሰብ ወያኔን መርዳት ነው” በሚል በያዘው ጽንፈኛ እና አደገኛ አቋምም፤ እንቅፋት ሆኖ ነበር። ሆኖም፤ ይህንን ጽንፈኛ ሃይል ለመሞገት ተቁቁም የነበረው የሕብረት ሬድዮ፤ በግንባር ቀደምትነት በመሰለፍ፤ ጽንፈኛውን ሃይል በመምገት እና፤ በኢትዮያ አንድነት ሰም የለበሰውን መርዛም ጭምብል በአደባባይ አስውልቆ፤ ከነበረብት ማማ ላይ ስለጣለው፤ የኪነት ባለሙያዎቹ፤ የእርዳታ ማሰባሰብ ግብራቸውን ማከናወን ችለዋል። በትግርኛ ተናጋሪው ላይ የነበረው አደገኛ ከፋፋይ ዘመቻም አከርካሪውን ሊመታ ችሏል።
የዋሽንግተኑ ጽንፈኛ ሃይል፤ እኩይ ገቢሩ ለዓመታት የቆየው፤ በሃሳቡ የማይሰማሙ ሰዎች ዝም በማለታቸው እንጂ፤ በጽንፈኛው ሃይል አቅም እና ጉልበት አልነበረም። ዛሬም፤ “የሃገር ልጅ የማር እጅ” በሚለው እቅድ ላይ የተጀመረው የጽንፈኞች ዘመቻ ዓላማው የከፋፋይነት እና፤ እነሱን የሚመስሉ ሰዎች ሃገርን ካልተቆጣጠሩ፤ ሃገራችንን ለማዳከም የያዙት ውጥን መሆኑ፤ ለሁሉም ግልጽ ሊሆን ይገባል። የኪነ ጥበብ ባለሙያዎቹን፤ በአማራው ላይ መፈናቀል እና ግድያ ሲፈፀም ለምን እርዳታ አልለገሳችሁም ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። ይህን የሚጠይቁ ሰዎች ደግሞ እራሳቸውንም የት ነበርን፤ አሁንስ የት አለን ብለው ሊጠይቁ ይገባል። ትላንት አልተደረገም እና ዛሬ ለምን ይደረጋል የሚል አስተሳሰብ ግን ከቀጨጨ አእምሮ የመነጨ፤ እኩይ አላማ ያነገበ ለመሆኑ፤ አጠያያቂ አይደለም። እነዚህ እኩይ ሃይሎች፤ ትግራይን መልሶ መገንባት እና የትግራይን ሕዝብ መልሶ ማቋቋም፤ የጦርነቱ አካል መሆኑን ነው። እነዚህ ሃይሎች በሚደሰኩሯቸው ዲስኩሮች እና በሚለጥፏቸው ጽሁፎች መረዳት እንደሚቻለው፤ ዛሬ ከሌላው የተለየ አድርገው “የሚያጀግኑትን የአማራ ልዩ ሃይልና ሚሊሽያ” ለራሳቸው እኩይ አላማ ሊጋልቡት እያዘጋጁት እንደሂነ ነው። ትላንት ሕወሃት፤ በአጃቢዎቹ እና በአጫፋሪዎቹ አጨብጫቢነት እና ድጋፍ፤ የፌደራል መንግሥቱን፤ እንደ-አቅመ ቢስነት በመሳል፤ “ከእኔ በላይ ጀግና ለአሳር ነው ሲለን የነበረው። ይህን በሚሳኤል እና በሮኬት፤ እንዲሁም በተለያዩ ዘመናዊ መሳርያ የታጠቀን፤ በርካታ የሰው ሃይል ያሰለፍን ሃይል፤ ማንም ባልጠበቀው ፍጥነት፤ የፌደራል መንግሥቱ በሰጠው አመራር፤ በውጊያ አሸንፎታል።
የአማራ ክልልን ልዩ ሃይልና ሚሊሽያ፤ ከሌላው የተለየ ጀግና አድርገው የሚስሉልን ሃይሎች፤ “የፌደራል መንግስቱ ቤኒሻንጉል ክልል ሕግ ማስከበር ካልቻለ፤ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ሕግ ማስከበር ይችላል” በሚል የከበሮ ድለቃ፤በአማራ ክልል መንግስት ላይ በሚፈጥሩት ተጽዕኖ፤ እነሆ የአማራ ክልል የፖሊስ ኮሚሽነሩ ምንም ሕጋዊ መሰረት የሌለው፤ አደገኛ የሆነ ጥያቄ ለፌደራል መንግስት ማቅረባቸውን ሪፖርተር የተሰኘው ጋዜጣ ዘግቦት አይተን ለመገረም በቅተናል። ትላንት ጄነራል አሳምነው ጽጌን የፈጠራ ጽንፈኛ ሃይል፤ ዛሬም ሌላ አሳምነው ጽጌ ለመፍጠር እንዳልተዘጋጀ እርግጠኞች መሆን አንችልም። ለፌደራል መንግስቱ፤ እና ለኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል አስቸጋሪ የሆነ ክስተት፤ እንዴት ነው፤ ለአማራ ክልል ልዩ ኃይል ሊቀልለት የሚችለው? ገራሚው ነገር፤ ትላንት፤ የአማራው ልዩ ሃይል እና ሚሊሻው ከሕወሃት ጋር መዋጋት የለበትም ያሉን ሰዎች ናቸው፤ ዛሬ፤ ይህ ሃይል ቤኒሻንጉል ገብቶ ይዋጋ የሚሉን።
በየትም ሃገር ሕግን የማስከበር ሃላፊነት የሚወድቀው በመንግስት ላይ ቢሆንም፤ መንግሥት ወንጀልን ሙሉ ለሙሉ ያስቆመበት ሃገር የለም። በተለይ በመንግስት የሽግግር ወቅት፤ ብዙ ዓማጽያን፤ በንጹሃን ዜጎች ላይ ጥቃት እንደሚፈጽሙ ከታሪክ እንማራለን። ሃያሏ አሜሪካ፤ ኢራቅ ውስጥ መንግስት ከመሰረተች እና በሺህ የሚቆጠሩ ወታደሮችዋን፤ በኢራቅ ቋሚ ካደረገች በኋላ እንኳን ይኸው እሰከዛሬ ድረስ በሱኒ ሙስሊሞች ላይ የሚደረግው የጅምላ ግድያ እንደቀጠለ ነው። ይህ አሜሪካና 49 አጋዥ ሃገራቱ፤ ከ10 ዓመታት በላይ ሊቆጣጠሩት ያልቻሉት ክስተት ነው። መገንዘብ የሚገባን፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ተግቶ የሚሰራ ሃይል አለ። ይህ ሃይል በሚችለው አጋጣሚ ሁል ንጹሃን ዜጎቻችንን በመግደል፤ መንግሥት ሕግ ለማስከበር እንደማይችል ሊያረጋግጥ የሚፈልግ ሃይል ነው። ከዚህም አልፎ፤ እርስ በእርስ እንድንገዳደል የሞት ድግስ ደግሶልናል። ማንነት ላይ ያነጣጠረ የጅምላ ግድያዎችን ለማስቆም የምንችለው፤ መንግስት ከሚወስደው ሕግን ይማስከበር እርምጃ በተጨማሪ፤ በአንድ ላይ ቆመን፤ የሕዝቡን ልብም ማሸነፍ ስንችል ብቻ ነው። የሃገሬ አቅጣጫ “እኔ በምፈልገው መንገድ” ብቻ ካልሄደ በሚል ድንክዬ አስተሳሰብ እና እኔን የሚመስል ሰው ብቻ ሃገሪቱን ካልተቆጣጠረ በሚል ስሜት እንቅፋት ለመፍጠር ከሚተጋ ሃይል ጋር ከተባበርን፤ “ከፌደራል መንግስቱ የበለጠ ጉልበት ያለኝ እኔ ነኝ” የሚል ክልል ከፈጠርን መቼም ቢሆን ጦርነቱን አናሸንፍም።
“ንፁሕ ኢትዮጵያዊ”፤ “ቆሻሻ ኢትዮጵያዊ” በሚል እሳቤ እንኳን ከድህነት አረንቋ ልንወጣ ቀርቶ፤ አንድ እርምጃ እንኳን መራመድ አንችልም። ለሃገር ተግቶ የሚሰራ ኢትዮጵያዊ እንዳለ ሁሉ፤ ሃገር ለማጥፋት ተግቶ የሚሰራ ኢትዮጵያዊም አለ። ይህ ደግሞ በዘር እና በሃይማኖት የተወሰነ አይደለም። አማራ ስለሆንክ ሃገር አፍቃሪ፤ ትግሬ ስለሆንክ “ባንዳ” የሚለው ጽንፈኛ አመለካከት አብሮ አያኖርንም። ሰው ማንነቱን መርጦ አይወለድም። ከኢትዮጵያዊነትም በላይ፤ ሁላችንም የሰው ልጆች ነን፤ እንደ ግለሰብ እንጂ፤ እንደ ብሔር አናስብም። ትላንት ጦርነቱን የተቃወሙ ሰዎች፤ ዛሬ የድሉ ባቡር ላይ ቀድመው ተሳፍረዋል፤ እነሱን እሰየው ልንል ይገባል። ነገር ግን፤ ውግያውን ያሸነፍነው፤ በመላው ኢትዮጵያዊ ተሳትፎ እንጂ በአንድ ብሔር እንዳልሆነም ደግመን ልናስታውሳቸው ግድ ይላል። ይህ ውጊያ የወንድማማች ብቻ ሳይሆን፤ የአባት እና የልጅ ውጊያም ነበር። የ42 ዓመቱ የአማራ አባት፤ ከ21 ዓመቱ የትግራይ ልዩ ሃይል ልጃቸው ጋር የተዋጉበት አሳዛኝ ጦርነት ነው።
ውጊያውን አሸንፈናል፤ ጦርነቱ ግን አላበቃም። ጦርነቱን ለማሸነፍ፤ የትግራይን ሕዝብ ልብ ማሸነፍ ወሳኝ ነው። የትግራይ ሕዝብ፤ ሕዝባችን ነው ስንል ወሬ ብቻ መሆን የለበትም፤ በተግባርም ማሳየት አለብን። በትግራይ ክልልም ሆነ በተለያየ የሃገራችን ክፍል ለተፈናቀለው ሕዝብ እርዳታ ያሰፈልጋል፤ ይህ በመንግስት ብቻ የሚቻል አይደለም። ሕዝባችን ከጥግ እስከ ጥግ መንቀሳቀስ አለበት። በራስ አነሳሽነት ማድረግ የምንችላቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ካቴድራል የ8ኛ ክፍል ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ፤ በራስ አነሳሽነት በየትምህርት ቤቱ እየሄድን ልብስና ጫማ ሰብስበናል። ከሶማልያ ጦርነት በኋላ፤ በጦርነቱ የተፈናቀለን ሕዝባችንን ለማገዝ በተደረገው ዘመቻ፤ በራስ አነሳሽነት፤ እርዳታዎችን ለማሰባስብ ከአዲስ አበባ እስከ ካራማራ በመኪና ተጉዘን እርዳታ አሰባስበናል። ይህ ሕዝባችን ከጥግ እስከጥግ የተንቀሳቀሰበት ዘመቻ እጅግ ስኬታማ ነበር። በወሎ ረሃብ ወቅት፤ ጳውሎስ ኞኞ ባቁቋሙት የጋዜጠኞች የሙዚቃ ቡድን፤ ወደ 159ሺህ ብር ለተረጂዎች ተሰብስቧል። ይህ ጋዜጠኞች በግል ተነሳሽነት ያደረጉት ነበር። ዛሬ እንደ አሸን የፈሉ “ጋዜጠኞቻችን” እንኳን በራሳቸው አነሳሽነት እርዳታ ሊያሰባስቡ ይቅርና፤ እርዳታ ለማሰባሰብ በበጎ እሳቤ ተነሳስተው የተጠራሩ የኪነት ባለሙያዎቻችንን ለማሸማቀቅ የሄዱበት መንገድ አሳፋሪ እና በሁላችንም ሊወገዝ የሚገባው ነው። ውጊያውን ስላሸነፍን፤ ሁላችንም “የድል አባቶች” በመሆን፤ “ለድሉ አንሻማ” በድሉም አንኩራራ፤ ጦርነቱ ገና አላበቃም። ጦርነቱን ለማሸነፍ ተግተን እንስራ። ከታሪካችን እንማር፤ በማንነት ላይ የሚያነጣጥር ማንኛውም ጥቃት ይቁም።
እግዜብሔር ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን ይባርክ።
There are some crucial actions that need to be taken as soon as possible, the genocide in Metekel/Benshangul areas. It is beyond comprehension why this situation has not been taken with utmost urgency by the government. How insensitive have we become about the death of innocent people. The article argues that during a transition period, it is well known that many extremists kill innocent people. But, this is genocide happening on innocent people just because they belong to a certain ethnic group, this is very serious and it needs to be addressed immediately. There is no justification for it.
Issues like handling of refugees in Tigray, and taking care of people that are internally displayed all over the country should also be priorities.
However, winning the heart and minds of Tigrayans will be a process that will happen through time. It is also a process that goes in both directions, do not forget that Ethiopians are still suffering from the bad deeds committed by TPLF.
It is true, all Ethiopians should come together, they should refuse to be divided by ethnicity, that is the only way they can build a peaceful and prosperous country.
This is a good start, to get rid of TPLF which has been the source of all the evils that happened to our country. TPLF may be destroyed, but the system that it has implemented for more than 25 years is still alive. If we do not make any changes to that, we are doomed to fail.
This is a well thought article. All Ethiopians should read this and understand the battel may be over, but the war is still on going. Wining the heart of the people is paramount for lasting peace. I thank the author for his insight.