ተስፋዬ ደምመላሽ
ታህሳስ 22 2013 ዓ. ም.
አቅጣጫውን ጠብቆ የማያውቅና የታሰበለት ቦታ ደርሶ ዘላቂ ሰላም ሳያወርድ እንደወረርሽኝ በየጊዜው የሚያገረሸ የፖለቲካ “ለውጥ” አባዜ ኢትዮጵያን ከተጠናወታት ረጅም የአብዮትና የድህረ አብዮት ዘመን አልፏል። አንድ ትውልድ እያለፈ ሌላ እየተተካ ነው። ከጽንሱና ከአነሳሱ አገርን የለውጥ ባልቤት ከማድረግ ይልቅ የለውጥ ኢላማ ያደረገው ነባር የፖለቲካ ቅየራ እቅዶች ክትትል በተለይ ላለፉት ሦስት አስርተ አመታት ጎሣ አምላኩ የሆነ ነው።
የዛሬዎቹ (ተረኛ) ቅየራ አድራጊ ፈጣሪዎች የጎሣ አምልኮ ጣዖታቸውን ለመማጸን በየጊዜው በገፍ ሰው መሥዋዕት እያቀረቡለት ይገኛሉ። ለዚህ ነው የኢትዮጵያ ንጹሃን ዘጎች፣ በልዩ ኢላማነት ደግሞ አማሮች፣ በየክፍለ ሃገሩ በተደጋጋሚ በጅምላ በሚጨፈጨፉበት፣ እንደ አገር የለዉጥ ባለቤትነታችን ከመቸዉም ጊዜ ይበልጥ ባልተረጋገጠበትና ደህንነታችን በያቅጣጫው ለውጭ ባላጋራዎቻችን ጥቃት በተጋለጠበት ውስጣዊ ውጥረት ዉስጥ ያለነው።
በቅርቡ ሥልጣን የያዘው የሱዳን አምባገነናዊ አገዛዝ፣ እንደሚገመተው ከግብጹ ቢጤው ጋር በመመሳጠር የወሰደው ጠብ ጫሪ ወታደራዊ ጥቃትና የኢትዮጵያን መሬት ወረራ ያለንበት ዉጥረት አንዱ አማሚና አስቆጪ ማሳያ ነው። በኦሮሞና በቤንሻንጉል ጉሙዝ አካባቢዎች ዘረኛ አሸባሪዎች ምንም “መከላከያ” በሌላቸው ሰላማዊ የኢትዮጵያ ዜጎችና ቤተስቦች ላይ የሚያደርሷቸው አሰቃቂ የግድያ፣ የንብረት አውዳሚና የህዝብ አፈናቃይ ጥቃቶች ተጨማሪ አስከፊ ማሳያዎች ናቸው።
ላይ ላዩን ሲያዩዋቸው ጨርሶ ኢምክንያታዊ ከሆነ ጅምላ ሰው ጭፍጨፋ የሚያልፍ ትርጉም ወይም ቅጥና ይዘት የሌላቸው በመምሰል አገዛዛዊ አካላትን ግብረ አበሮቻቸው ያደረጉ የቤንሻንጉል ጉሙዝ መንጋዎች ጥቃቶችም ሳይቀሩ ሰፋ ባለ የለውጥ እቅዶች ክትትል ታሪካዊ አውድ የሚታዩ ናቸው። ኢትዮጵያ ለአስርተ አመታት ተይዛ ከቆየችበት ድህረ አብዮታዊ የዘር ፖለቲካ አባዜ አንጻር የሚስተዋሉ ናቸው። በትናንቱ ወያኔም ሆነ በዛሬው ኦነግ ገጽታቸው በጥልቅ የተዛባ፣ በመሠረቱ ከኢትዮጵያዊነት መንፈስ ጋር የተጣላ ፀረ አማራ “ለውጥ” አሳዳጅ ናቸው።
ይህም ማለት፣ ቃል በቃል ሰው በላ ከሆነ አረመኔያዊ ተግባር ይታቀባሉ ሊባሉ ከማይችሉና ንጹሃንን ጨፍጫፊ ከሆኑ ቡከን አሸባሪዎች ጀርባ ሳይቀር የአገር ወስጥም ዉጭም ሌሎች ዶላቾችና ዘዴኞች ጠፍተው አያውቁም። የአሸባሪዎቹን ኢሰብአዊ ጭካኔ ለራስቸው የፖለቲካ ጥቅም መከታተያ መሣሪያ የሚያደርጉ ዘዋሪ ኦነጋዊም ወያኔያዊም ወገኖች እጥረት አልነበረም፤ ዛሬም የለም።
ወያኔዎች እርግጥ ከመንግሥት ሥልጣን ተባረዋል፤ ሆኖም በአልሞት ባይ ተጋዳይ ርዝራዥ አሸባሪነት እና እንደለመዱት የውጭ ኃይሎች (የሱዳን፣ የግብጽ፣ የምዕራቡ) መጠቀሚያና ተጠቃሚ በመሆን ለመቀጠል አይሞክሩም ማለት አይቻልም። የትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያዊነት ምንጊዜም የሚካድ ወይም ጥያቄ ወስጥ የሚገባ አይደለም፤ ነገር ግን የወያኔ ፖለቲካ ከጽንሱና ሥር መሠረቱ በአማራ ጠልነት፣ በባንዳነትና አገር ከሃዲነት የተበከለ ነው።
በዘር ፖለቲካ ቀውስ ፈጣሪነታቸው ወያኔዎችም ሆኑ ኦነጎች አገዛዛዊ ወይም ተቃዋሚ በሚባሉ ጎራዎች በቀላሉ የሚፈጁ አይደሉም። የአገዛዝ እና የተቃውሞ ወሰን ላይ እግራቸውን አንፈራጠው በሁለቱም ጎራ የሚንቀሳቀሱ ወገኖች ናቸው። በስግብግብ ጎሠኛ ሙስናም ይሁን በአድር ባይነት እንዳስፈለጋቸው ወይም እንደተመቻቸው ከአንዱ ጎራ ወደ ሌላው ገባ ወጣ ይላሉ። በወያኔያዊና ኦነጋዊ ዘረኛ ፖለቲካና አገዛዝ እንግዲህ የሚመስለውን የሆነ ነገር እምብዛም የለም።
በተለይ በኦሮሞና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ አካባቢዎች ‘ጸጥታ ጠባቂ’ መሰል አገዛዛዊ “ልዩ ኃይሎች” በተወካይ ነውጠኛ መንጋዎች አማካኝነት ወይም ራሳቸውን በራሳቸው ወክለው በአሸባሪነት ይንቀሳቀሳሉ። የፖለቲካ አስመሳይነቱ፣ ምስቅልቅሉና ውዝግቡ ሁሉ የበላይ ኃላፊና ተቆጣጣሪ ደግሞ “ፌደራል” ተብዬው ጠቅላላ የጎሣ አገዘዝ መዋቅር ነው። በአብይ አገዛዝ ተቋማት ዉስጥ ሽብር ተንኳሽና አቀናባሪ ሸፋጮች መረብ ዘርግተው ለወያኔዎች የደህንነት ሥራ የሚሠሩ ግለሰቦችና ቡድኖች እንደነበሩና ዛሬም እንዳሉ ሰሞኑን ተዘግቧል። ይሁን እንጂ፣ የአገዛዙ ሥርዓት ራሱን ችሎ ለውዝግቡ ተጠያቂ ነው። በቀጥታም ሆነ በዙሪያ፣ በአድራጊነትም ይሁን በአላድራጊነት፣ ወይም ደግሞ በእቅድም ባይሆን በውጤት ሥርዓቱ እንዳለ አሸባሪ ነው።
ይህን እውነታ ፍንትው አድርጎ የሚያሳየን ሌላ ነገርም አለ። ይኸውም፣ ዋኖቹ (ወይም ተረኞቹ) የሥርዓቱ አመራሮች በአገርም ሆነ “ክልል” በተባለ ግዛት አገዛዝ ሆነውም ወይም ተብለውም በማንነት ፖለቲካ ዙሪያ የሚያጠነጥን፣ ከአገር አንድነት መንፈስ ጋር መቆራቆስ የማያቆም ‘ተቃውሞ’ ከማድረግ ምንም ያህል አለመቦዘናቸው ነው። ማለትም፣ በዘረኝነት አስተሳሰብ ከተቃኘ ያለፈ ታሪክ ሞጋችነት አለመቆጠባቸው፣ ከተጎጅነት ስሜት ትርክት አቀንቃኝነት እምብዛም አለመራቃቸው፣ እንዲሁም ከቅሬታና ብሶት ዲስኩር ሱሰኝነት ራሳቸውን ነፃ አውጥተው የኢትዮጵያን ሉአላዊነትና አንድነት በሙሉ ልብ ለመቀብል አለመፈለጋቸው ወይም አለመቻላቸው ነው።
ወደ መሠረታዊው ጉዳይ ስንመጣ፣ በነፃነት፣ በዲሞክራሲ፣ በልማትና በብልጽግና ስም ኢትዮጵያ ውስጥ የሆኑ ያልሆኑ የፖለቲካ ለውጥ እቅዶች ይነሳሉ ይወድቃሉ፣ ይፈካሉ ይጨልማሉ። ለተወሰኑ አመታት በረው ይከሰከሳሉ። መከረኛውን ነገደ ብዙ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአስርተ አመታት ቀፍድደው የያዙት የአምባገነናዊነት፣ የዘርኝነት፣ የጭፍጨፋ፣ የውዝግብ እና የተንሰራፋ ድህነት መዋቅሮች ግን ወይ ፍንክች!
ኢትዮጵያ ይህን ውዝግብና መከራ ተለይቶት የማያውቅ አሳሪ የለውጥ እቅዶች ሰንሰለት በጣጥሳ ነፃ የምትወጣው በምን መንገድ ይሆን? በሌላ አባባል፣ በአገሪቱ ዘላቂ ሥርዓታዊ ለውጥ የሚመጣው እንዴት ነው? ለዘለቄታው አማራን ከጥፋት ለመታደግ፣ አያይዞም የመላ ኢትዮጵያዊያንን ደህንነትና ሰላም ለማረጋገጥ ለዚህ ብርቱ ጥያቄ መልስ መፈለግ ግድ ይላል።
እንደሚታወቀው፣ የሰንሰለቱ የመጀመሪያ ቀለበት የተማሪው ንቅናቄ ነበር፤ “ሥር ነቀል” የተባለው፣ ግን በእውነቱ ራሱን አገራዊ ሥር መሠረት የነሳው የተማሪዎች ንቅናቄ። በሆኑ ያልሆኑ የፖለቲካ ቅየራ እቅዶች ቅብብሎሽ ለአስረተ አመታት የቀጠለው አገር ቅፍደዳ በተማሪ አብዮተኞች እንደነገሩ ተጸንሶና ታቅዶ፣ እቅዱ በአገሪቱ አስተዋይ ምሁራንም ሆነ ተራማጅ በተባሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እምብዛም ሳይፈተሽ፣ በሃሳብ ሳይብላላ፣ ሳይጣራ፣ በአገራዊ አገባቡም ሳይመጠን ወይም ሳይስተካከል በጅምላ በደርግ ተሞጭልፎ ደም በደም “ተፈጻሚ” ሆነ።
ሆኖም፣ አፈጻጸሙ አስፈጻሚ አገዛዙ ራሱ ላይ ክፉኛ ውድቀትን አመጣ። ውድቀቱ ይባስ ብሎም ኢትዮጵያን አገራዊ መንግሥት አልባ አድርጎ አስቀረ። ለወያኔ ደመኛ ሥልጣን ያዢነትና ለከት የለሽ አገር በዝባዥነት መንገድ አሳምሮ ጠረገ፤ በር ወለል አድርጎ ከፈተ። ስግብግብ፣ ዋጮ ተኩላዎችን የበጎች ዘብ ቋሚዎችና ጠባቂዎች አደረገ። በኢትዮጵያ አገራዊና ፖለቲካዊ አካል ውስጥትሮጃን ፈረስ አስገባ፣ አጥቂና አፍራሽ ኃይል ከተተ።
ከዚያ በክፋት፣ በመሰሪነትና በድርጅታዊ ባንዳነት የተካኑ፣ የአገር ሃብት ዝርፊያ በቃኝ የማይሉ ወያኔዎች የመሰጠሩትም በገሃድ ያወጁትም አማራ ጠልና የአገር ጠንቅ የሆነ “ህገ መንግሥታዊ” እና “ፌደራላዊ” የተባለ ዘረኛ የፖለቲካ መዋቅር በጥድፊያ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ተጭኖ በሂደት ተደላደለ። በስም ይክሱ እንዲሉ፣ አንድ ራሱን ዲሞክራሲያዊ ስያሜ የሰጠ፣ ግን እውን ዲሞክራሲን ጨርሶ የማያውቅ ፈላጭ ቆራጭ የለውጥ እቅድ በሌላ ተተካ። ደም የተጠማ፣ ሲበዛ ነውጠኛ የነበረ የደርግ “ዲሞክራሲያዊ መአከላዊነት” አገር አመሳቃይና አሸባሪ በሆነ የሕወሐት “አብዮታዊ ዲሞክራሲ” ተደመሰሰ።
ነገሩ ግን አልሸሹም ዞር አሉ ነበር። በፖለቲካ ቅየራው ያ ሁሉ የኢትዮጵያዊያን ደም ፈሶና አጥንት ተከስክሶ፣ አገራዊ ሕይወታችን እንዳልነበረ ሆኖ፣ ያ ሁሉ ዋጋ ተከፍሎ፣ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ የኢትዮጵያን ምድር ሳይለቅ ይበልጥ ህዝብ ከፋፋይና አወዛጋቢ ግልብ ዘረኝነትን ተላብሶ እንዳለ ቀጠለ።
በመጨረሻ ይህ የአብዮተኛ ገዢ ፓርቲዎች የለውጥ እቅዶች ቅብብሎሽ አሁን ያለውን ከቀን ወደ ቀን ለዘብተኝነትና ፋሺስታዊ ጽንፈኝነት የሚፈራረቁበትን የአገዛዝ ዑደት ወይም ዙር አተረፈ። ይህ ዛሬ ያልንበት አምባገነናዊ የለውጥ ዙር የነባሩን ዘረኛ ሥርዓት ሦስት ምሰሶዎች፣ ማለትም “ህገ መንግሥታዊነቱን”፣ “ፈደራላዊነቱን” እና “ክልላዊነቱን” ደግሞ በማረጋገጥ ቀጣይ ለማድረግ እየጣረ ያለ ነው።
በጅምሩ የጠ/ሚንስትር አብይ አሕመድአመራር እርግጥ ሥርዓቱ ዳርቻዎች ላይ ጥቂት እርምቶችና መሻሻሎች አድርጓል። ሰሞኑን በትግራይ መሽጎ የነበረውን ሞገደኛ የትግራይ ገዢ ፓርቲ በተቀላጠፈ የጦር ዘመቻ ቀላል የማይባል ከሥልጣን የማስወገድ ዉጤትም አስገኝቷል።
ሆኖም፣ የዘር አገዛዙ መዋቅራዊ ምሰሶዎች፣ በተለይ ህገ መንግሥታዊ፣ ክልላዊ እና ፌደራላዊ ተብዬ ቋሚ አካላቱ፣ በጠ/ሚንስትሩ ይሁንታና ደጋፊ ተሟጋችነት በመሠረቱ እንዳሉ አሉ። በነዚህ ተቋማዊ አካላት ቀጥታም ሆነ ተዘዋዋሪ ተባባሪነት የሚደረጉ በተለይ አማራን ለጥፋት ኢላማ ያደረጉ የአሸባሪ ስብስቦችና መንጋዎች ጅምላ ጭፍጨፋዎች ተባዝተውና ተባብሰው ቀጥለዋል።
በተጨማሪ፣ ሁሉ ነገር፣ የአገሪቱ መዲና አዲስ አበባ ሳይቀር፣ “የኛ” የብቻችን ነው ባይ፣ ጥቅሞቻቸውን ከአፍንጫቸው ጫፍ ምንም ያህል አርቀው ማየት የማይችሉ ኦነጋዊያን የራሳቸውን ስግብግብ ፈላጭ ቆራጭ የበላይነት የጎሣ አገዛዙ ላይ እየጫኑበት መሆኑ ግልጽ ነው። ጥረታቸው ግን ከአገዛዙ ጠቅላላ መዋቅርና ርዕዮታዊ ይዘት ጋር ዋና መስተጻርር የለውም። እንዲያውም፣ ኦነጋዊያን የጎሣ ብሔርረኞች መዋቅሩን በተረኝነት ሙጥኝ ብለው ቀጣይነቱን የሚደግፉና የሚያረጋግጡ ናቸው። በውጤት፣ ‘የጎሣ ህገ መንግሥት፣ ክልላዊነንትና ፌደራላዊነት ወይም ሞት’ እያሉ ነው።
ከአገዛዙ መዋቅር የወጣው የአብይ አመራር ቃል በቃል ያለውን ቢል እንግዲህ ነባሩን የዘር አገዛዝ ሥርዓት በመሠረቱ እስቀጣይ ነው። ይህ እስከሆነ ድረስ፣ አብይ የሚወስዳቸው ድህረ ጦርነት ሁኔታዎችን በድፍኑ “የማረጋጋት” እርምጃዎች አገዛዙን ራሱንም ሆነ ኢትዮጵያን በለውጥ ጎዳና ሩቅ አይወስዱም። የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚሻውን ነፃ አገራዊ ዜግነትን ያማከለ አዲስ ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት ምሥረታ መዕራፍ አይከፍቱም።
በዚህ መልክ አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ እስካልተከፈተ ድረስ ደግሞ የአብይ አገዛዝ የሚያራምደው ባመዛኙ ቴክኖክራታዊ የሆነ የልማትና ብልጽግና እቅድ በተለመደው አገር አተራማሽ የፖለቲካ ቅየራ ጨዋታ ውስጥ ብቸኛ ወይም ዋና “ተፎካካሪ” እና (እንደሚጠበቀው) “አሸናፊ” ከመሆን ያለፈ የመሠረታዊ ለውጥ አመራር ሚና መጫወት አያስችለውም። አገዛዙ ለአስርተ አመታት ኢትዮጵያን ጠፍኖ ይዞ የቆዬው የነውጠኛ አመራር ሰንሰለት የመጨረሻው ቀለበት ሆኖ ለተወሰነ ጊዜ ከመቆየት አያሳልፈውም። ማለትም፣ በተለመደው መንገድ ሌላ ለውጥ ፈጣሪ ነኝ ባይ ወገን ተንስቶ ያለውን አገዛዝ በመተካት ራሱን የነባሩ ሰንሰለት ተጨማሪ ቀለበት እስካላደረገ ድረስ።
እንግዲህ ላለፈው ግማሽ መእተ አመት የሚጠጋ ዘመን ኢትዮጵያን በየጊዜው እያገረሸ ማስቸገር ያላቋረጠው የለውጥ ውጥረት ባጭሩ እንድሚከተለው ተጠቃሎ ሊገለጽ ይችላል። ለሆኑ የመንግሥት፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ ኑሮና የባህል ችግሮች መፍትሔዎች ያመጣል የተባለ የሆነ ፖለቲካዊ/አገዛዛዊ “ቅየራ” ሳይውል ሳያድር ራሱ የችግር ምንጭ ይሆናል፤ በውጥረት ላይ ዉጥረት የጨመራል። መፍትሔ ተብዬው ራሱ በተደራቢ ችግርነት ገኖ፣ ተባብሶ፣ ወደ ሌላ የፖለቲካ “ቅየራ” ዑደት ይመራል። ያ የቅየራ ዙር ደግሞ በተራው መልሶ የራሱን አባዜ፣ የራሱን ጣጠኛ ዝባዝንኬ ያፈልቃል።
ኢትዮጵያ ለረጅም አብዮታዊና ድህረ አብዮታዊ ዘመን ስታዘግምበት የቆየችው ዘላቂ አቅጣጫም ሆነ መዳረሻ የሌለው የለውጥ መንገድ እንግዲህ መውጫ ቢስ ዙሪያ ጥምጥም ሆኖ እናየዋለን። ከዚህ መጥፎ፣ አገር አሰናካይ አዙሪት ወጥተን ለመላው የኢትዮጵያ ዜጎች የጋራ ዘላቂ ደህንነት፣ ሰላም፣ ነፃነትና ልማት የሚበጅ እውን፣ መዋቅራዊ ሽግግርና ለውጥ የምናመጣው እንዴት ይሆን?
የሰሞኑ ጦርነት ድል የሥርዓታዊ ለውጥ ዕድል ፈጥሯል?
ይኸውና እንግዲህ እንደ አገር የድህረ አብዮት ታሪካችንን አስቸጋሪ፣ ጠመዝማዛ የፖለቲካ ፈለግ በመከተል ደፋ ቀና ብለን፣ ብዙ ዋጋ ከፍለንና ዉጣ ውረድ አልፈን ዛሬም አቅጣጫውም ሆነ መዳረሻው ያልተረጋገጠ የለውጥ እቅዶችና መተከካት ሁኔታ ላይ እንገኛለን። በፈረንጆች እንደሚባለው፣ ‘ይበልጥ ነገሮች ሲለወጡ፣ ይበልጥ ያውነታቸው ቀጣይ ይሆናል’።
ሆኖም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ታሪክ ዉስጥ እዚህ ግቡ የማይባሉ፣ አንሰው አገር አሳናሽ የሆኑ ጎጠኛ ወያኔዎችን ከትግራይ ገዢነት እንደ ሙጄሌ ነቅሎ የጣለው የቅርቡ የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ድል ያልታሰበ የመዋቅራዊ ሽግግር ገድ ወይም አጋጣሚ አስገኝቷል ወይ? ለአስርተ አመታት ስናዘግምበት ከቆየነውን በጎ ማብቂያ ከሌለው ጠባብ የፖለቲካ ቅየራ እግር መንገድ አውጥቶ ሰፊ የሥርዓታዊ ለውጥ ጎዳና የሚያስይዘን ዕድል ፈጥሯል ማለት ይቻላል?
በአንድ በኩል፣ ለሁለት አመታት ያህል በትግራይ መሸጎ የቆየውን የወያኔ ፈላጭ ቆራጭ ገዢ ወገንን ፍንቀላ የተከተለው አሁን ኢትዮጵያ የምትገኝበት የፖለቲካ ቅየራ ዙር ለነባሩ ጠቅላላ ጎሠኛ የአገዛዝ ሥርዓት መሠረታዊ ለውጥ ዋስትና አለመሆኑን እንረዳለን። የጦርነቱ ራሱ ዉጤት መቃናት ለዚህ አይነት ለውጥ ዋስትና የሌለው ለመሆኑ የተለያዩ ማስረጃዎች መዘርዘር ይቻላል። ግን በጥቅሉ ዋናው ምክንያት ጦርነቱ “ህገ መንግሥታዊ” እና “ፌደራላዊ” በመባል የጎሣ ክልሎች ቁጥር “ድምር” ከመሆን ያላለፈው ነባር “አገራዊ” የአገዛዝ ሥርዓት እንዳለ ራሱን በሥልጣን ላይ ለመጠበቅ ሊዋጋው የተገደደ ጦርነት መሆኑ ነው።
በይበልጥ ትኩረት ለመናገር፣ ጦርነቱ የትግራይ ዘረኛ ገዢ ፓርቲ ከአገር አቀፉ ዘር ተኮር የአገዛዝ ውቅር በከሃዲነት በማፈንገጥ አገዛዙ ላይ ላደረሰው ተንኮለኛ፣ አሸባሪ ጥቃት ምላሽ የተደረገ መጠነኛ “ህግ የማስከበር” ውጊያ ነበር። ከዚህ በተረፈ የሥርዓታዊ ለውጥ ወይም ሽግግር እቅድ አልነበረውም፤ ዛሬም የለውም።
ስለዚህ የጦርነቱ አሸናፊ የሆነው የአብይ አገዛዝ በራሱ ዘዴኛነትና ተነሳሽነት ያለውን የኃይል መዋቅር ጠጋኝና ጠባቂ የመሆን አዝማሚያ ቀልብሶ ነባሩን ጎሠኛ ሥርዓት ከሥር መሠረቱ ይቀይራል ተብሎ አይጠበቅም። አገዛዙ ከአብይ ራሱ ተለዋዋጭ፣ ሁሉን ነገር አዋቂና አድራጊ ፈጣሪ መሰል ግለሰባዊ አመራር ባሻገር የመዋቅራዊ ሽግግር መሪነት ዝንባሌ ወይም ፈቃደኝነት አያሳይም። ፈቃደኝነት ቢኖረውም እንኳን ለዚህ አይነት ሽግግር ተገቢ አቅጣጫና ቁጥጥር ሰጪ ራዕያዊና ስልታዊ መምሪያ ወይም ስነ ሥርዓት ያካተተ ነው ልንል አንችልም።
ብልጽግና የተባለው ፓርቲ ራሱም እንዲሁ ከጎሠኛ ብሔረኝነት ባሻገር በምር ታሳቢ ሊሆን የሚችል ርዕዮታዊ ይዘትም ሆነ ተክለ ድርጅታዊነት ወይም ቁመና አለው የሚባል አይደለም። በመሠረቱ ከአብይ ግለሰባዊ አመራር ተቀጣይነት የዘለቀ ወይም ከሆኑ ያልሆኑ አሸባሪ ዶላቾች ተዘዋሪነት ያለፈ ፖለቲካዊ ህላዌ ወይም አድራጊ ፈጣሪነት ምንም ያህል የለውም።
በሌላ በኩል ግን እንደ አገር ያለንበት የድህረ ጦርነት ሁኔታ ለመሠረታዊ ፖለቲካ ቅየራ የተመቻቸ፣ ወይም ሊመቻች የሚችል፣ ነው። ለዚህ ሦስት የተዛመዱ ምክንያቶች ባጭሩ መጥቀስ ይቻላል። መጀመሪይ ነገር፣ ለአገር አንድነት፣ ደህንነትና ልማት የሚበጅ ዘላቂ ለውጥ ዋና እንቅፋት ሆኖ ለሰላሳ አመት ያህል የአገር ሃብት ሲበዘብዝ የቆየውን ዘረኛ፣ ፀረ አማራ ሥርዓት ያቋቋመው የወያኔ ፓርቲ ከምንግሥት ኃይልና ሥልጣን ጨርሶ ተባሯል። ይህ ትልቅ ግልግል ነው። የሥርዓታዊ ለውጥ አንድ ትልቅ እንቅፋት ተወግዷል፣ ምንም እንኳን ኢትዮጵያዊነትን ተቀናቃኝ የሆነ የጎሣ ብሔርተኝነት የአገሪቱን ፖለቲካ ምህዳር አካቶ አለመልቀቁ ባይካድም።
የድህረ ጦርነቱ ሁኔታ ለሥርዓታዊ ለውጥ ምቹነት ሁለተኛውና ተዛማጁ ምክንያት በኢትዮጵያ ለሚገኙ የሕወሐት ተለጣጣፊ ሆነው ለተፈጠሩና ከሞላ ጎደል እሱኑ አገልጋይ በመሆን ባምሳሉ ለተባዙ ሌሎች፣ በተለይ ኦሮሞና አማራ ፓርቲዎች፣ ዋና አሽከርካሪያቸውና ዘዋሪያቸው የነበረው የወያኔ ፓርቲ የደረሰበት አይወድቁ ውድቀት ያለውን እንድምታ የሚመለከት ነው።
የሕወሐት የዘረ ፖለቲካ እቅድ ለዘለቄታው አለመሳካት እቅዱ በጥልቅ የተሳሳተና የማያዛልቅ የነበረ መሆኑን ግልጽ የሚያደርግ ብቻ አይደለም። በቅጥያ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ምህዳር ያጥለቀለቁት የሆኑ ያልሆኑ የማንነት ፖለቲካ እቅዶች በሙሉ የሚጋሩትን መሠረታዊ እንከናማነትም የሚያሳይ ነው።
የወያኔዎች ውድቀት እንግዲህ ለትግራይ ብቻ ሳይሆን በአገር አቀፍ ደረጃ ቢያንስ በእምቁ የመዋቅራዊ ለውጥ በር ከፋች ነው። ይህ እውነት ነው፣ ምንም እንኳን እምቁን በጎ ክፍተት በእውን መጠቀሙ ለሥርዓታዊ ለውጥ ደጋፊዎች ራሱን የቻለ ከባድ የግጥሚያ ጥሪ ቢሆንም።
ወያኔዎች ወደ ሰላሳ አመታት ለሚጠጋ ዘመን የኢትዮጵያን ፖለቲካና ምጣኔ ሃብት በበላይነት መቆጣጠር ችለው ነበር። ለከት በሌለው ጎሠኛ ሙስና የተበከለ አገር ቁጥጥራቸውንና ብዝበዛቸውን ቀጣይ ማድረግ ሲሳናቸው ደግሞ አኩርፈው ወደ ተነሱበት የጎሣ ክልላቸው ፈርጥጠው ራሳቸውን ጥግ ያዥ አደርጉ። ባለ በሌለ የጦር መሣሪያ እስክ አፍንጫው በመታጠቅ ትግራይ ወስጥ መሽገው ጥቂት ጊዜ መቆየት ቻሉ። ሆኖም ውሎ አድሮ ከሚገባቸው ዉድቅት ማምለጥ አልቻሉም።
ነገዳዊ ማንነቶችን ተሻጋሪና አስተባባሪ ኢትዮጵያዊ አንድነትን የሚጻረሩ ጎጠኞችን እጣ ፈንታ በሚመለከት የሕወሐት የፖለቲካ ውድቀት የሚሰጠው አንድ ዋና አስተምህሮ አለ። ይኸውም፣ ከኢትዮጵያ አንድነት መንፈስ ጋር የሚጣላ ማንኛውም የጎሣ ብሔርተኝነት ራሱ ላይ ትልቅ ሞራላዊ፣ ምሁራዊና ፖለቲካዊ ኪሳራ አድራሽ መሆኑ ነው። መጨረሻው አያምርም፤ አወዳደቁ የከፋ ይሆናል። ዘፈኑ እንደሚለው፣ “…ዛሬ አዲስ አይደለም፣ በለኮሰው እሳት[ኢትዮጵያን] የነካ…ሲቃጠል”።
የወያኔ ፓርቲ ትግራይን “ነፃ” አወጣለሁ ብሎ ተደራጅቶ ለአስርተ አመታት የተከታተለው ኢሰብአዊ፣ አማራ ጠል የፖለቲካ እቀድ ያልተሳካ የኦነግ ሸኔው ወይም የቤንሻንጉል ጉሙዙ ጨርሶ ስብእና የሌለው ንጹሃን አማሮችን ሴት ወንድ፣ ህፃን ጎልማሳ፣ ወጣት አረጋዊ ሳይል በጅምላ ጨፍጫፊ ምናምንቴ የሸብርተኝት ‘መርሃ ግብር’ ይሳካል ወይም ይዘልቃል ተብሎ ጭራሽ አይጠበቅም። ውሎ አድሮ የህ እኩይ የሽብርተኝነት ገቢርም ከተገቢው መጨረሻ አያመልጥም።
በመጨረሻ፣ ዛሬ ያለንበት ውዝግብ ያልተለየውና የኢትዮጵያ ደህንነት ያልተረጋገጠበት ድህረ ጦርነት ሁኔታ ለሥርዓታዊ ለውጥ ታሳቢነትና ተፈጻሚነት ምቹ የሆነበት ሦስተኛ ምክንያትም መጠቆም ይቻላል። የኸውም፣ ከአራት አስርተ አመታት በላይ የፈጀ፣ መዳረሻ የሌለው፣ የተተካኪ ፖለቲካ እቅዶች ገጭ ገጭ ጉዞ ያደከመው አእምሯችን ለዚህ አይነት አዲስ አስተሳሰብ በአድካሚው ጉዞ ራሱ ተዘጋጅቷል። የጉዞው አታካችነትና አገር አመሳቃይነት ዛሬ በተለመደው መንገድ ስለ ብሔራዊ ጉዳዮቻችን ማሰብ አቁመን “ራሳችንን” ከጎሠኝነት የተለየና የተሻለ የአገር ጉዳዮች አስተሳሰብ አቅጣጫ እንድናስይዝ የሚያበረታታን ነው።
ወቅታዊው ሁኔታ ራሱ አዲስ የፖለቲካ አስተሳሰብ ይጋብዛል፤ ማለትም፣ ለአገር ተቆርቋሪ ወገኖች ግብዣውን የምንቀበል ከሆንን፣ በምር አሳቢነት ትንሽ ጀግነን፣ ከሚመቸን የተለመደ የፖለቲካ ቋንቋና ዲስኩር ክልል ወጣ ብለን። የአገር ጉዳዮችንና ችግሮችን በአነጋገር ዘይቤነት ብቻ በተለመዱና ምንም ያህል ጽንሳዊ ፍሬ ነገርም ሆነ በጎ አገራዊ አገባብ በሌላቸው ረቂቅ ርዕዮታዊ ፈርጆችና ቃላት (ለምሳሌ፣ “ዲሞክራሲ” እና “የራስን ዕድል በራስ መወሰን”) ቀደም ቀደም ብልን ለመቃኘት ከመሞክር እንድንቆጠብ ወቅቱ በር ከፍቶልናል። ጊዜው አገራችንን ለረቂቅ የፖለቲካ ሃሳቦች “ለማመቻቸት” መሞከሩን ትተን ሃሳቦቹን የጥልቅ ታሪክ ባለቤት ከሆነው አገራዊ ህልውናችን ጋር ለማጣጣም በጽናት እንድንነሳና እንድንቆም የሚገፋፋን ነው።
እርግጥ አሁን እንደ አገር ያለንበት ሁኔታ ህልውናችን ያልተረጋገጠበት አስጊና ወጣሪ ነው። ግን ውጥረቱ አወንታዊ ተጽዕኖ እንዳለውም አንዘንጋ። ያልተረጋገጠው አኳኋናችን አእምሯችንን ይበልጥ ከፍተን ብሔራዊ ጉዳዮቻችንን ባልተለመደ ተጨባጭ አቀራረብ በቀጥታ ከሥር መሠረታቸው ለመረዳትና አገራችንን ለመላ ዜጎቿ ደህንነት፣ ሰላም፣ ነፃነትና መዳበር በሚበጅ መልክ መልሰን ለማቅናት የሚረዱን ዕድሎችም ፈጥሯል።
እነዚህ ዕድሎች በግብታዊ መንገድ ተከሳች የሆኑ ወይም በቀላሉና በቀጥታ ልንጠቀምባቸው የምንችል ገዶች አይደሉም። አጠቃቀማቸው ዘላቂ ስልታዊ አስተውሎ፣ ትንተና እና ልማት የሚጠይቅ ነው። ይህን ታሳቢ በማድረግ በተከታይ አጭር ጽሑፍ የሥርዓታዊ ለውጥ ዕድል አፈጣጠርና አጠቃቀም ላይ ያተኮረ መለስተኛ ወይይት አቀርባለሁ።
tesfayedemmellash@gmail.com