spot_img
Saturday, September 30, 2023
Homeአበይት ዜናየብሔር ልዩነታችን ላይ መሰረት ባደረገ ፖለቲካዊ የአስተዳደር ስርዓት የዜጎችን መሰረታዊ ሰብዓዊ መብቶች...

የብሔር ልዩነታችን ላይ መሰረት ባደረገ ፖለቲካዊ የአስተዳደር ስርዓት የዜጎችን መሰረታዊ ሰብዓዊ መብቶች ማረጋገጥ አይቻልም፡፡

advertisement
Solidarity Movement for new Ethiopia

ጋዜጣዊ መግለጫ
በፒዲ ኤ ፍ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

የብሔር ልዩነታችን ላይ መሰረት ባደረገ ፖለቲካዊ የአስተዳደር ስርዓት የዜጎችን መሰረታዊ ሰብዓዊ መብቶች ማረጋገጥ አይቻልም፡፡

በሀገራችን ኢትዮጵያ በንጹሃን ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለ አሰቃቂ ግድያ፣  የአካል  መጉደል ፣ ለዘመናት ከኖሩበት ስፍራ መፈናቀል እንዲሁም  ያፈሩትን ሃብትና ጥሪት በአንድ ጀንበር አጥተው ለተረጅነት መዳረግ በየጊዜው የሚያጋጥም የተለመደ አሳዛኝ ክስተት ሆኗል፡፡ ይህንን በዜጎች እየደረሰ ያለውን አሰቃቂ ግድያ፣  የአካል  መጉደል ፣ መፈናቀልና   ሃብትና ንብረታቸውን ማጣት እንዲቆም ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች ደግመው  ደጋግመው ቢያወግዙም በተቃራኒው ችግሩ ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ ይገኛል፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን ዕምነት ፤ ባህል፣ ስነልቦና ፣ ጋብቻ ፤ስራ ፤ጉርብትና ሌሎችም መስተጋብሮች ላንለያይ አስተሳስረውን ጠንካራ የአብሮነት ባህል የነበረን ህዝቦች ነን፡፡ ይህ የአብሮነት መስተጋብር በብዙ አጋጣሚዎች ፈተና  ላይ የወደቀ ቢሆንም  እስከዛሬዋ ቀን ድረስ አብረን እንድንጓዝ አድርጎናል፡፡

መሰረታዊ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ሳይሸራረፉ በማክበር የሁላችንም መኖሪያ የሆነችውን ሀገር አንድነት በማስጠበቅ ፤ በመንግስት አስተዳደር ስርዓት ውስጥ ብዝኃነታችንን የሚያስተናግዱ የተለያዩ ፖሊሲዎችንና የህግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት  ለጋራ ጥቅም በማዋል፤ እስከዛሬ የነበሩንን ጠንካራ ልምዶች ይበልጥ በማጠናከር  ከድክመቶቻችን እና ስህተቶቻችን በመማር ብሎም በማሻሻል በአብሮነት ሁሉም አሸናፊና ተጠቃሚ የሚሆንበት ስርዓት መዘርጋት ይቻላል ብለን እናምናለን፡፡

በእኛም ሀገር ይሁን በሌሎች ሀገራት ላይ  ለሚከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች  የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም በአሁኑ ጊዜ የቆየ አብሮ የመኖር እሴቶቻችንን በመፈታተን በሀገራችን እየተከሰቱ ለምንመለከታቸው ከፍተኛ የንጹሃን ህይወት መቀጠፍ ፣ መፈናቀልና የንብረት ውድመት የመብት ጥሰቶች ዋነኛው መንስዔ የሀሰት ትርክት የወለደው ብሔር ተኮር የጥላቻ ፖለቲካ  መሆኑ ጥርጥር የሌለው አሳዛኝ ሐቅ ነው፡፡

አሁንም መንግስትም ሆነ ሌሎች የሚመለከታቸው የፖለቲካ ባለድርሻ አካላት በከፍተኛ የሃላፊነት ስሜት፣ ሀገራዊ ፍቅርና ቁርጠኝነት የአለም አቀፍ ሕግጋትን መሰረት ባደረገ መልኩ፤ ያለንበትን 21ኛውን ክ/ዘመን በሚመጥን በሰከነ ስሜት በቅንነት በመነጋገር፤ መሬት ላይ ያለውን ብዙኃኑን ምስኪን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመስል የፖለቲካ አስተዳደር ስርዓት ለመዘርጋት እስካልወሰኑ ድረስ በሁሉም የሀገራችን ወሰን ውስጥ ያሉ ዜጎቻችንን መሰረታዊ የሰብዓዊ መብቶች በዘላቂነት ማስከበር ከቶውንም አይቻልም፡፡ ሰብዓዊ መብቶች ባልተከበሩበት፤ የህግ የበላይነት ባልተረጋገጠበት፣ ሰላም ባልሰፈነበት ሁኔታ የሀገርን ዕድገትና ለውጥ ዕውን ለማድረግ ማሰብ እጅግ አዳጋች ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ እየተስተዋለ ያለው የጥላቻ፣ የመናናቅ፣ ልዩነትን መሰረት ያደረገ የብሔር ፖለቲካ፣ የጨቋኝ ተጨቋኝና የመጤ ሰፋሪ ትርክት ምንአልባትም ከእስካሁኑም ወደከፋ የግጭት አረንቋ ቢከተን ነው እንጂ የዜጎችን ሰው በመሆናቸው ብቻ እና በዜግነታቸው ማግኘት ያለባቸውን መብቶች ማስከበር  ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ችግሩን በፈጠርንበት አስተሳሰብ ፣ ችግሩን በፈጠሩት የፓለቲካና የታሪክ ስሁት ትርክቶችን  ሳናስተካከል መፍትሔ ማምጣትም ከባድ ነው፡፡

በሀገራችን በየትኛውም ዘመን እንደህዝብ ተለይቶ የደላው ወይ ሌላውን የጨቆነ የለም፡፡ ይህንንም የተለያዩ የመንግስት እና የፖለቲካ ድርጅቶች አመራሮች በተደጋጋሚ አስረግጠው የተናገሩት ዕውነታ ቢሆንም በተቃራኒው በተዛባ የታሪክ አረዳድ ሆን ብለውም ይሁን በስህተት የፖለቲካ አጀንዳ ባደረጉ አካላት ምክንያት የተነሳ ምንም የማያውቁ ንጹሀን ወገኖቻችን ደም እንደጎርፍ እየፈሰሰ ንብረታቸው እየወደመ ይገኛል፡፡ ይህም የሀገር ህልውናን አደጋ ላይ በመጣል ወደ ከፍተኛ ግጭት፤ ሞት፤ መፈናቀልና ስደት፤ ብሎም ለውጭ ኃይሎች ወረራና ጥቃት ሊያጋልጠን ይችላል፡፡ ከአባይ ግድብ ጋር በተገናኘም ሆነ በቀጠናችን ካለ የሽብርተኝነት እንቅስቃሴ ይህ የማይሆንበት ሁኔታ ይኖራል ብለን አንገምትም፡፡ ስለሆነም በቅርቡ በእርስ በርስ ግጭት ሕዝባቸውን ለስደትና ሞት ከዳረጉ ሀገራት በመማር ከምን ጊዜውም በላይ ሀገራዊ እና ሕዝባዊ አንድነታችንን ማጠናከር የሚገባን ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ መንግስት፣ ሕግና ስርዓት እያለ እንኳ በተገቢው መልኩ ማስቀረት ያልቻለውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት  በጦርነትና በስደት መካከል ደግሞ ምን ያህል የከፋ ሊሆን እንደሚችልና  ለውርደት እንደሚዳርገን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡

ይህ ፖለቲካው የወለደው የዜጎች ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት አይነቱን እየቀያየረ አንድ ጊዜ ሀይማኖትን ሌላም ጊዜ ብሔርን ወይንም አመለካከትንና አቋምን ሰበብ በማድረግ ይብዛም ይነስም ያልደረሰበትና ያልነካው የሕብረተሰብ ክፍል የለም ማለት ይቻላል፡፡  የችግሩ ምንጭም የቅርብ ሳይሆን አስርት አመታትን የቆየና አሁን እየባሰ የመጣ ነው፡፡

 በሀገራችን ይህ ሁሉ ቢሆንም እንደ ሕዝብ የሚገድልና እንደሕዝብ  የሚያፈናቅል አላየንም፡፡ ለዚህም ጥቃት በሚደርስባቸው አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች ተጠቂዎችን ለማዳን፤ ለማሸሽ እና ለመደበቅ ያደረጉት ወገናዊና ሞራላዊ መልካም ስራ ማስረጃ ነው፡፡

የፖለቲካው በቅንነት በመተማመን እና በአንድ ሀገራዊ ስሜት አለመመራት ሁሉንም የሀገሪቱ ዜጎች በየትኛውም ስፍራ በእኩል ዓይን በማየት ለሰብዓዊ እና የዜግነት መብቶቻቸውን በሚያከብር እና በሚያስከብር መልኩ ባለመመራቱ የተነሳ ችግሩን ከማቅለል ይልቅ በማወሳሰብ ፡-

  • እጅግ ብዙ ንፁሐን ወገኖቻችን ሕፃናትን፡ ነፍሰጡሮችን፡ አቅመ ደካሞችን ጨምሮ ያለአግባብ በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወታቸው እንዲያልፍ ሆኗል
  • የሀገሪቱን የቀድሞ ኤታ ማዦር ሹም ጨምሮ የክልል ከፍተኛ አመራሮችን አጥተናል
  • ኢማሞችን እና ቀሳውስትን ጨምሮ የቤተ እምነት አገልጋዮችን ውድ ሕይወት አጥተናል
  • በዩንቨርሲቲዎቻችን ለትምህርት የሄዱ ብዙ  ወጣቶችን ትርጉም በሌለው ምክንያት ተቀጥፈውብናል
  • ለትምህር የሄዱ ሴት ተማሪዎችና የጤና ረዳት ሰራተኞች ታግተው ለስቃይ ተዳርገዋል
  • በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች መሰረታዊ አቅርቦቶች ለምሳሌ እንደ ትራንስፖርት፤ መንገድ መዘጋት፤  ምግብ፤ ባንክ፤ ቴሌኮሚኒኬሽን አገልግሎት፣ መድሀኒት ወዘተ አቅርቦት በተደጋጋሚ ረዘም ላሉ ጊዜያት በመቆራረጥ ሰላማዊ ዜጎች ለከፍተኛ ችግር እንዲዳረጉ ሆኗል፡፡
  • ግምቱ ከፍተኛ የሆነ የሀገር እና የህዝብ ንብረትና ሀብት እንዲወድም ሆኗል
  • ከዚህ ሁሉ በላይ በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ የደረሰው ጥቃት ችግራችን የደረሰበትን የአሳሳቢነት ደረጃ ፍንትው አድርጎ የሚያሰይ ነው፡፡ ለዚህ ጥቃት ዋንኛ መንስኤ ከሀገርና ከሰው ይልቅ ብሔርን ያስቀደመ የማንነት ፖለቲካ ውጤት ሁኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ዳግም እንደማይፈጠርስ ምን ማስተማመኛ አለን? ከብሄር፤ ከኃይማኖትና ከፖለቲካ ነጻ የሆነውን የመከላከያ ሰራዊት  ከውስጡ የወጡ የራሱ ወገኖች ያጠቁት የብሔር ፖለቲካው ውጤት ነው፡፡ ይህም በቶሎ በታላቅ መስዋዕትነት በቁጥጥር ባይውል ኖሮ የሀገራችንን ሉዓላዊነትን የሚገዳደርና ከዚህ የከፋ ቀውስ የሚያስከትል እንደነበረ መረዳት አያዳግትም፡፡

ችግሩ ላይ ብቻ ሳይሆን የችግሩ መንስዔ ላይ አተኩረን ለመስራት እና ለማስተካከል ከዚህ በላይ ምን ምክንያትና ምቹ ጊዜ እየጠበቅን ነው?  ምንስ እስኪፈጠር ነው ለውሳኔ የምንዘገየው?

በየቀኑ ክቡር የሰው ነፍስ በአሰቃቂ ሁኔታ እየተቀጠፈ እያለ የሞተው ወይም ገዳይ  ከኛ ነው ከነሱ ነው እያሉ የፖለቲካ ቁማር ከመጫወት ሁላችንንም እንደሀገር  ከሰውነት ከፍታ ያወረደንን የጥላቻ ፖለቲካ በመመካከርና በማሻሻል የተሻለ ስርዓትን ለትውልድ እናቆይ፡፡

ለፌደራልና ለክልል መንግስታት አመራሮች

ልዩነታችን ላይ መሰረት ባደረገ የፖለቲካ አስተዳደር ስርዓት የዜጎችን መሰረታዊ የሰብዓዊ መብቶች ማረጋገጥ አይቻልም፡፡

የፖለቲካ ባለድርሻ አካላት በከፍተኛ ታሪካዊ ሀገራዊ ስሜት በመሞላት በቁርጠኝነት የአለም አቀፍ ሕግጋትን መሰረት ባደረገ፤ ያለንበትን 21ኛውን ክ/ዘመን በሚመጥን በሰከነ ስሜትና በቅንነት በመነጋገር፤ መሬት ላይ ያለውን በደምና በእምነት ተሳስሮ በሀዘንም  በደስታ አብሮ የሚኖረውን ብዙኃኑን ምስኪን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመስል የፖለቲካ አስተዳደር ስርዓት ለመዘርጋት እስካልወሰናችሁ ድረስ በሁሉም የሀገራችን ወሰን ውስጥ ያሉ ዜጎቻችንን መሰረታዊ የሰብዓዊ መብቶች በዘላቂነት ማስከበር ከቶውንም አትችሉም፡፡ ሰብዓዊ መብቶች፤ ሰላምና ህግ ባልተከበረበት ሁኔታ ደግሞ ዕድገትንና ለውጥን ማሰብ እጅግ አዳጋች ነው፡፡ ይህ አካሔድ ደግሞ ለናንተም አይጠቅምም፡፡ ከእስካሁኑ ተግዳሮት በጊዜ ትምህር መውሰድ መልካም ነው፡፡ ችግሩን ለመፍታት እንደሚታሰበውም ቀላል እንዳልሆነ ብንረዳም እንደሚፈራውም ከባድ እንዳልሆነ እናምናለን፡፡ ከባድ ቢሆንም ደግሞ የእውነትን የአንድነትን የእኩልነትን ሰብዓዊ መብቶች የሚከበሩበትን፤ ለትውልድ ጥላቻን ሳይሆን ፍቅርን የምናወርስበትን መንገድን መርጠን የሚጠይቀውን መስዋዕትነት መክፈል የተሻለ ነው፡፡ ተቋማትም እስኪገነቡም ቢሆን የሰው ልጆች ወጥተው መግባት ዜጎች በህይወት የመኖር መብት አላቸው፡፡ መንግስት የዜጎቹን ደህንነት ከማረጋገጥ የቀደመ ምን አይነት አጀንዳ ሊኖረው ፈጽሞ አይገባም፡፡

በመሆኑም

  1. መንግስት ችግሩን ከምንጩ ለአንዴና ለመጨረሻ ለማድረቅ ቁርጠኛ ውሳኔ በመወሰን ጊዜ ባለመስጠት ውይይትና ምክክር ከላይ እስከታች እንዲጀመር እስከዚያውም በከፍተኛ ርብርብ ህግ የማስከበር ስራውን እንዲያስፈፅም እንጠይቃለን
  • እስከዛሬም ድረስ በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች የተፈጠሩትን ዘግናኝ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ገለልተኛ ወገን እንዲያጣራ በማድረግ አጥፊዎችና ተባባሪዎች እንደ ተሳትፎዋቸው መጠን ከፍተኛውን ቅጣት እንዲያገኙ ተጎጂዎችም ተመጣጣኝ ካሳ እንዲያገኙ እንዲደረግ እንጠይቃለን
  • እስከዛሬም ድረስ በተፈጠሩ ችግሮች ምክንያት ከሚኖሩበት አካባቢ የተፈናቀሉ ዜጎች ተገቢው ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደነበሩበት እንዲመለሱና መደበኛ ኑሯቸውን እንዲጀምሩ በመንግስት ያለተገደበ ድጋፍ እንዲደረግላቸው  እንጠይቃለን

ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ

እስከዛሬ ድረስ በፖለቲካው ምክንያት በተፈጠሩ ችግሮች ብዙ ዋጋ እየከፈለ እና መሰረታዊ ሰብዓዊ መብቱን እየተገፈፈ ያለው ንጹህ የሆነው እና አብሮ በሰላም እየኖረ ያለው በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች የሚኖረው ህዝባችን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ያለንን አብሮነት አሁንም በማጠናከር እንደሕዝብም እንደግለሰብም አብረን በመቆም ለልጆቻችን የተሻለች ሀገር እናቆይ፡፡ ከጥላቻና ከብሄር ወይም ከማናቸውም የማንነት ልዩነት በመውጣት ለፖለቲካ ቁማር የማንመች እንሁን፡፡ ካለበለዚያ ከእስካሁኑ በባሰ የመጨረሻ ተጎጂዎች እኛው ነን፡፡

ምንም እንኳን የተለያየ አመለካከት ቢኖረንም በሰው ልጆች ሰብዓዊ መብቶች እና በሀገር አንድነት ጉዳይ የማንደራደር እንሁን፡፡ ሁላችንንም ስደተኞች ረሀብተኞችና ጠፊዎች ያደርገናል እንጂ ሀገር ለአንድ ብሄር፤ ለአንድ ክልል ፤ለአንድ ቡድን ወይ ለአንድ ፓርቲ ብቻ ተለይታ አትፈርስም፡፡ ለተወሰነ ባለስልጣን ወይ አክቲቪስት ፈርሳ ለሌሎቻችን አትቆምም፡፡

  ከሰሜን እስከደቡብ ከምስራቅ እስከምዕራብ አብረን ስንቆም ችግሮቻችን ከኛ በታች ይሆናሉ፡፡ ጥላቻና መጋደል በህግም ፊት ወንጀል በሞራልም ነውር በእምነቶቻችንም ኃጥያት ነውና በሰከነ መንፈስ ሰብዓዊነትን በማስቀደም ሀገራችንን በማስከበር በብዝኃነት መኖር እንደለመድነው ቃልኪዳናችንን እናድስ፡፡

ውስጣዊ አንድነታችን  በተዳከመ ቁጥር የውጭ ጠላቶቻችን ይደፍሩናል ያጠቁናል የዚያን ጊዜ ብሔር መርጠው አይወጉንም፤ ሁላችንንም ጨለማ ይወርሰናል፡፡ ምርጫው በእጃችን ነውና ሳይዘገይብን በይቅርታ መንፈስ እንነሳ፡፡ ሰው መሆናችን ትልቁ አንድነታችን መሆኑን እናስተውል፡፡የነበሩንን እና ያሉንን መልካም አብሮ የመኖር እሴቶች በማጠናከር ችግሮቻችንን በዕርጋታ እየፈታን እንጓዝ፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በማንም ይፈጠሩ፤ ማንም ተጎጂ ይሁን ሰው ነውና ወገን ነውና በአንድነት በማውገዝ በአንድነት ፍትህን በመጠየቅ ለሚለያዩን የማንመች እንሁን፡፡ ለልጆቻችን ፍቅርን ተስፋን መከባበርንና የስራ ባህልንና ማውረስ አለብን፡፡

እናቶች አባቶች ወጣቶች ሴቶች የሀይማኖት አባቶች ምሁራን የጥበብ ሰዎች የሚድያ አካላት በአጠቃላይ ሁላችሁ ኢትዮጵያውያን በሀገር ውስጥም ይሁን በውጭ ያላችሁ በሙሉ ይህን ከባድ ጊዜ ተያይዘን እንድናልፈው የበኩላችንን አስተዋጽዖ እንድናደርግና የዜጎች ሰብአዊ መብቶች ሳይሸራረፉ የሚከበሩበት፡  በህግና በስርዓት ብቻ ፍትህ የሚጠየቅበትና የሚገኝበት ማንኛውም አካል ከዜጎችና ከሀገር ደህንነት በታች የሚሆንበት መዋቅራዊ የስርዓት መሻሻል እንዲመጣ  በሰላማዊ መንገድ አብረን  ጥሪያችንን እንድናሰማ ስንል በታላቅ አክብሮት እንማፀናችኋለን፡፡

ቅድሚያ ለሰብዓዊነት!

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ

ታህሳስ 22 / 2013

            አዲስ አበባ / ኢትዮጵያ

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
13,705FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here