spot_img
Friday, June 14, 2024
Homeነፃ አስተያየትጣት በመጠቋቆም ችግራችንን መፍታት አንችልም (ከጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ)

ጣት በመጠቋቆም ችግራችንን መፍታት አንችልም (ከጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ)

ከጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ፤
ታህሳስ 22 ቀን 2013 ዓ.ም

“ ተስፋ መቁረጥ ቀላል ነው፤ ጣት መጠቆም ደግሞ የበለጠ ቀላል ነው” ዛክ ቴይለር።

ከላይ የተጠቀምኩትን ጥቅስ የተናገሩት፤ የቀድሞው የሲንሰናቴ ባንግልስ የኳስ ቡድን አሰልጣኝ የነበሩት ዛክ ቴይለር ናቸው። አሰልጣኙ ይህንን የተናገሩት፤ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር፤ በታህሳስ 1 2019፣ ቡድናቸው፤ የኒውዪርክ ጄት የተባለውን ቡድን በጠንካራ ፉክክር ካሸነፈ በኋላ ነው። ያሸነፍነው፤ ጣት ባለመጠቋቆማችን እና ተስፋ በላመቁረጥ እንደ አንድ ቡድን በመንቀሳቀሳችን ነው ሲሉ፤ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ተናግረዋል።

ሃገራችን ውስጥ ያለው ሁኔታ እጅግ ከባድ እና በንጹሃን ዜጎቻችን የሚፈጸመው ጭፍጨፋ፤ ቃላት የማይገኝለት ዘግናኝ መሆኑን ለማስረዳት መሞከር ለቀባሪው ማርዳት ይሆናል። ይህንን ከባድ እና የዜጎቻችንን ሕይወት እየቀጠፈ የሚገኘውን አረመኔ ድርጊት ግን ጣት በመጠቋቆም እና በመግለጫ ጋጋታ፤ እንዲሁም፤ ለፖለቲካ ትርፍ ሲባል በሚደረገ አላስፈላጊ መወራጨት፤ ልንቆጣጠረውም ሆነ ልናሸንፈውም አንችልም። በዜጎቻችን ላይ የሚደረገውን ዘር ተኮር ጥቃት፤ መንግሥት ብቻውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊፈታው ይችላል ብሎ ማሰብም፤ የችግሩን ውስብስብነት እና የሃገራችንን ጠላቶች፤ ሃገርን የማተራመስ ቁርጠኝነት ካለመገንዘብ የሚመጣ እሳቤ ነው። ሁሉም በየፊናው፤ መፍትሄ ብሎ የሚገልፀው፤ መፍትሔ የሚሆን ሳይሆን፤ መንግሥት ላይ ጣቱን በመጠቆም፤ በዚህ የፖለቲካ ጡዘት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት በማሰብ ነው። “የመንግሥት ተቀዳሚ ሃላፊነቱ፤ የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ ነው” እየተባለ የሚነገረን ነገር ከመደጋጋሙ የተነሳ፤ በጣም ስልችቷል። የመንግሥት ተቀዳሚ ሃላፊነት የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ ነው ማለት፤ መንግሥት ሁሌም ወንጀል ከመፈጸሙ በፊት፤ እርምጃ የመውሰድ አቅም አለው፤ ወይም ደግሞ ሁሉንም ወንጀል በአስፈላጊ ፍጥነት መከላከል ይችላል ማለት አይደለም። ማንም ሃገር፤ ወንጀልን ከመፈጸሙ በፊት ቀድሞ ሙሉ ለሙሉ ያስቆመ ሃገር እስካሁን የለም። ምንም እንኳን በተለያዩ ሃገሮች፤ መንግሥታት፤ የተለያዩ አሰቃቂ ሊሆኑ የሚችሉ ወንጀሎችን፤ ቀድመው በማወቅ እና የመከላከል እርምጃ በመውሰድ ጥቃት በማስቆም፤ የንጹሃንን ሕይወት ቢታደጉም፤ እነዚህ የወንጀል መከላከል ድርጊቶች ግን ብዙውን ጊዜ ይፋ ስለማይሆኑ፤ ሕዝቡ አያውቃቸውም።

በሃገራችንም ያለው ክስተት ከዚህ የተለየ አይደለም። ሕዝብ የማያውቃቸው፤ በርካታ የከሸፉ ጥቃቶች አሉ። ሆኖም፤ ሁሉንም ማክሸፍ ባለመቻሉ፤ ዜጎቻችን አሁንም የዘር ተኮር ጥቃቶች ስለባ እየሆኑ ነው። በርካታ ጥቃቶች እና ግድያዎች የተፈፀሙት በአማራው ሕዝባችን ላይ ቢሆንም፤ በሌሎች ዜጎቻችንም ላይ ቀላል የማይባሉ ጥቃቶች ተፈጽመዋል። የእነዚህ ጥቃቶች ዋና ዓላማ፤ አንዱን ብሔር በሌላው ላይ ለማነሳሳት እና፤ በሃገራችን ማብቂያ የማይኖረው፤ የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲኖር ለማድረግ ነው። ብዙ የፖለቲካ ድርጅቶች እና የማህበረሰብ አንቂዎች (አክቲቪስቶች) ይሄ ይጠፋቸዋል ብዬ ለማመን እቸገራለሁ። ጠላቶቻችን፤ የፖለቲካ ልዩነታችንን፤ እንዲሁም ደግሞ የፖለቲካ ባሕላችንን ጠንቀቀው ያውቃሉ። በተደጋጋሚ እንዳየነው፤ የሃገራችንን ሏአላዊነት፤ አደጋ ላይ የሚጥል፤ የውጭም ሆነ የውስጥ ሃይል ሲነሳ፤ ሁላችንም ባንሆን፤ አብዛኞቻችን፤ በአንድነት በመቆም፤ ሃገራችን ላይ ያፈጠጠውን አደጋ ለመከላከል ቅድሚያ እንሰጣለን። “የእናት ሆድ ዥንጉርጉር” እንዲሉ፤ ሃገራችን አደጋ ባጋጠማት ቁጥር፤ ሁሌም ከውስጥም ሆነ ከውጭ ጠላቶች ጎን የሚቆሙ እኩይ ዜጎች አሉን።

ዋናው እና ትልቁ ችግራችን፤ የሃገራችንን ሏአላዊነት የሚፈታተን አደጋ፤ ረገብ ሲል፤ እና ውስጣዊ ችግር ሲገጥመን፤ በአንድነት ቆመን ችግሩን ለመፍታት በታትሪነት ከመስራት ይልቅ፤ ለፖለቲካ ትርፍ የምንሩሯጥ፤ ትልቁን ሃገራዊ ሰዕል ዘንግተን፤ ከአፍንጫችን ርቀን የማናስብ፤ ለአጭር ጊዜ የፖለቲካ ትርፍ የምንወራጭ መሆናችን ነው። ሰሞኑን በተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች የሰማነው የመግለጫ ጋጋታ፤ መንግሥት ላይ ጣት ከመጠቆም ባለፈ የጠቆሙት ምንም የመፍትሔ ሃስብ የለም። ይህም፤ የፖለቲካ ድርጅቶቻችን በሃሳብ ድርቀት ደዌ የተበከሉ መሆናቸውን ያሳያል። አብን የተባለው የፖለቲካ ድርጅት፤ በአማራው ላይ የሚደረገው ጥቃት “አማራውን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት የታቀደ ፕሮጀክት ነው” ሲል ያወጣው መግለጫ ከነባራዊው የሃገራችን ሁኔታ ጋር የማይሄድ፤ አቅጣጫውን የሳተ የፖለቲካ ምርጫ ዘመቻ መሰል መግለጫ ነው። በዚህ ጊዜ በሃገራችን፤ በመጠኑም ቢሆን ተረጋግቶ ያለ ክልል የአማራ ክልል ሆኖ ሳለ እና፤ አብዛኛው አማራ፤ በክልሉ ሰላማዊ ኑሮውን እየኖረ ባለበት ሁኔታ፤ “አማራን ከምድረ ገጽ የማጥፋት እቅድ አለ” የሚል የፖለቲካ ድርጅት፤ ችግሩን ያላጤነ፤ መፍትሔም ለመጠቆም ያልተዘጋጀ ድርጅት መሆኑንም ያሳብቅበታል።

በሃገራችን ያሉ የተቃዋሚ/ተፎካካሪ ፖለቲካ ድርጅቶች፤ ሕዝብን ማገልገል የሚጀምሩት፤ ቤተ መንግሥት ሲገቡ ብቻ ለምን እንደሚመስላቸው በጣም ግራ ያጋባል። ለተፈናቀለው ሕዝብ መንግሥት አልደረሰም፤ ተጎጂዎችን መንግሥት አልረዳም፤ በሚል የመግለጫ ጋጋታ ከሚያደነቁሩን፤ ተባብረው፤ ሕዝቡን አስተባብረው፤ ለተፈናቃዩ እና ለተጎጂው ሕዝባችን የሚችሉትን ሁሉ ቢያደርጉ፤ ከአደንቋሪው መግለጫ ይልቅ፤ የተስፋ ሰጪነት ምሳሌነታቸው በተደጋጋሚ ሊነገር የሚችል፤ ጥዑመ ዜማ ያለው መለከት በሆነ ነበር። በተደጋጋሚ የሚነገረው፤ “ዐብይ ከሥልጣን ይልቀቅ፤ መንግሥት ሃገር መምራት ስላልቻለ’ ሥልጣኑን ያስረክብ” የሚሉ መወራጨቶች፤ የትም እንደማያደርሱ እየታወቀ፤ ለሕዝብ ተቆርቋሪ ለመመስለ የሚነዙ ባዶ ጩኸቶች ናቸው። በተደጋጋሚ እንደተገለጸው፤ ከአሁን በኋላ ማንም የፖለቲካ ሃይል፤ የመንግሥት ሥልጣን ባለቤት የሚሆነው፤ በሕዝብ ፍላጎት እና ምርጫ ብቻ ነው። ስለዚህም፤ በግርግር ወደ ሥልጣን እንመጣለን ብለው የሚጎመጁ ሃይሎች እርማቸውን አውጥተው፤ ለቀጣዩ ምርጫ እራሳቸውን ያዘጋጁ። ያ እስኪሆን ድረስ ግን፤ ለሕዝብ የቆሙ የሕዝብ አጋሮች መሆናቸውን በተግባር ሊያስመሰክሩ ይገባል። ሃገር ለመምራት አቅም እንዳላቸው ለማሳየት፤ ከመንጠራራት በፊት፤ አንድ የፖለቲካ ድርጅት የመምራት አቅም እንዳላቸው፤ ለተቸገረው ሕዝባችን በመድረስ በተግባር ያሳዩን።

የኢትዮጵያ የውስጥ እና የውጭ ጠላቶች ተቀናጅተው በተለያየ አውድ የከፈቱት ጦርነት፤ ከማንም ድርጅት እና ግለሰብ ስልጣን በላይ አሳሳቢ ነው። ሃገራችን የገጠማት ፈተና፤ የሕልውና ፈተና ነው። ይህንን ለመገንዘብ፤ የአለም አቀፍ የዜና አውታሮችን ዘገባ ማየት ብቻ በቂ ነው። በዚህ በቀውጢ ጊዜ ከጎናችን የቆሙት ጥቂት የጎረቤት ሃገራት ናቸው። በኦሮምያ፤ በቤኒሻንጉል፤ አሁን ደግሞ በአፋር እና በሶማሊያ የምናያቸው ጥቃቶች፤ ያለዕቅድ እና ሳይታሰብባቸው የሚደረጉ ጥቃቶች አይደሉም። ዓላማውም፤ የመከላከያውን እና የፀጥታውን ሃይል በመሰበጣጠር፤ ሕዝባችን እርስ በእርሱ እንዲገዳደል፤ የተደገሰ ድግስ ነው። ይህ ደግሞ በፕሮፖጋንዳው ታግዞ፤ በአለም አቀፍ ተቋማት በተሰገሰጉ ጠላቶቻችን አማካኝነት፤ በሃገራችን ላይ እየፈጠረ ያለው ተጽእኖ ችግራችንን የበለጠ የተወሳሰበ አድርጎታል።

በተደጋጋሚ ከታሪካችን ያልተማርነው ነገር፤ መንግሥትን የችግሮች ሁሉ መፍትሔ አድርገን ማየታችን ነው። መንግሥት ውጤታማ ሥራ ሊሰራ የሚችለው፤ ሕዝብ ሲተባበር ነው። ሰዎችን ወይም ድርጅቶችን ከሥልጣን በማንሳት ብቻ የሚመጣ መፍትሔ የለም።  ይህንን አሁንም ከታሪካችን አልተማርንም፤ “ዐብይ ከሥልጣን ይልቀቅ” የሚሉን ሰዎች፤ ከዛስ በኋላ ተብለው ቢጠየቁ፤ የሚሰጡት መልስ የላቸውም። ችግሩ የጋራ፤ የተወሳሰበ፤ አህጉራዊ እና አለም አቀፋዊ ይዘት እንዳለው ያልተረዱ ሰዎች፤ እንዴት ነው መፍትሔ ሊያመጡ የሚችሉት? ያጋጠማን ችግር፤ በየትም ሃገር ታይቶ የሚታወቅ አይመስለኝም። በተደጋጋሚ ጽሁፎቼ ለማሳየት እንደሞከርኩት፤ ዶ/ር ዐብይ አሕመድ፤ ከስር መሰረቱ በተበላሸ መዋቅር ውስጥ ነው ሲሰሩ የቆዩት። ሃገራችን የነበረችበትን አደጋ ቆም ብለን እናስብ። ሕወሃት፤ ወደ መቀሌ ባይሸሽ ኖሮ፤ እጅግ የከፋ ጥፋቶችን አድርሶ፤ ከዚህ በበለጠ የማንወጣበት ትርምስ ውስጥ ሊከተን ይችል ነበር። ይህ ሳይሆን የቀረበት ምክንያት በሰው ሊገለጽ የማይችል ተዓመር ነው። ወታደሩን፤ ፖሊሱን፤ መላውን የፀጥታ መዋቀር፤ ኢኮኖሚውን እና ቢሮክራሲውን የተቆጣጠረ የፖለቲካ ሃይል፤ አንድ ጥይት ሳይተኮስ፤ ከስር መሰረቱ ማፍረክረክ፤ ተዓምር ነው ተብሎ ብቻ ነው ሊገለጽ የሚችለው።

ቢያንስ ለአንድ ዓመት ያክል፤ ዶ/ር ዐብይ ከሕወሃት እይታ ውጭ ምንም መስራት አይችሉም ነበር፤ በወታደሩ፤ በፖሊሱ እና በፀጥታ መዋቅር ውስጥ መሰረታዊ ለውጥ የተደረገው በአንድ ዓመት ተኩል ውስጥ ነው። በብዙ ባለሙያዎች ግምት፤ እንዲህ ዓይነት ሥር ነቀል ለውጥ እና መሻሻል ቢያንስ ወደ አስር ዓመት ገደማ ይፈጃል። ይህ በምንም ዓይነት መመዘኛ ቢመዘን፤ የዶ/ር ዐብይ ትልቅ የስኬት ሥራ እና ሃገራችንን ከከባድ አደጋ የታደገ ተግዳሮት ለመሆኑ አያጠራጥርም።

ዶ/ር ዐብይ፤ ተቋማትን በመገንባት ያሳዩት ብቃት እና፤ ሃገራችንን ከነበረችበት የገደል አፋፍ ፈቀቅ እንድትል የተጫወቱት የመሪነት ሚና የሚደነቅ እና ማንንም ኢትዮጵያዊ ሊያኮራ የሚገባ ነው። ካዳበረነው የግጭት የፖለቲካ ባሕልም እንድንወጣም ብዙ ሞክረዋል፤ ጥረዋል፤ የለመድነው የእርስ በእርስ መጠላለፍ ግን ጥረታቸውን አላሳካም። ወደድንም ጠላንም፤ በሃገራችን እየተካሄደ ያለው ለውጥ ነው። ለውጥ ሲኖር ሁልጊዜም የሚከፋው ሃይል፤ ለውጡን ለማደናቀፍ ተግቶ ይሰራል። የንጹሃንንም ሕይወት ይቀጥፋል። በኢራቅ፤ አፍጋኒስታን፤ ሊብያ እና ሌሎች በርካታ ሀገሮች ያየነው ይህንኑ ነው። የእኛን ለየት የሚያደርገው ግን፤ ሕዝባችን ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው ታጋሽ እና ጨዋ ሕዝብ መሆኑ ነው። በሱኒ ሙስሊሞች ላይ የሚደረገውን የጅምላ ጥቃት፤ የአሜሪካ እና የኢራቅ መንግስታት ሊያቆሙት አልቻሉም፤ በታሊባን አፍጋኒስታን ውስጥ በንፁሃን ዜጎች ላይ የሚደረግውን ጥቃት የአሜሪካ እና የአፍጋኒስታን መንግስታት ሊያቆሙት አልቻሉም፤ ሌሎች ምሳሌዎችን ማንሳት ይቻላል። እነዚህ ጥቃቶች ያልቆሙት፤ የአሜሪካ መንግስት ደካማ በመሆኑ አይደለም። እነዚህ ሃይሎች፤ ልክ በሃገራችን እንዳሉ ጽንፈኛ ሃይሎች ውጊያቸው የሽምቅ ውጊያ በመሆኑ ነው። ጦርነቱ መደበኛ ጦርነት አይደለም፤ ለዚህም ነው፤ ጠላቶቻችንን በቀላሉ በማወቅ፤ እርምጃ ለመውሰድ የሚከብደው።

አሳዛኙ ነገር፤ የኢትዮጵያ መንግስት በዜጎች ላይ የሚፈፀመውን ጥቃት ለማስቆም እየሰራ አይደለም የሚሉ ሃይሎች ከማንም የበለጠ ይጮኻሉ። እውነቱን በመበረዝም መርዛቸውን ይረጫሉ። እነዚህ ሰዎች በየትኛው ዩኒቨርስ ውስጥ እንደሚኖሩ ግልጽ አይደለም። ጃል ማሮ የተባለ አረመኔ የተገደለው፤ የሰላም ችቦ ትተክሎለት አይደለም። በተለያየ አቅጣጫ በሃገራችን እና በሕዝባችን ላይ በተከፈተው የሽምቅ ውጊያ የፌደራል እና የክልል የፀጥታ ሃይላት፤ በየቀኑ የሕይወት ዋጋ እየከፈሉ ነው። በቅርቡ እንኳን 32 የፌደራል ፖሊስ አባላት በዚሁ የሕግ የማስከበር ሥራ ላይ እንዳሉ ተገድለዋል። በምን ዓየነት ሕሊና ነው፤ ሶፋ ላይ ተቀምጦ፤ በኮምፕዩተሩ በሚከትብ፤ የፌስቡክ አርበኛ የእነዚህ ጀግኖች ሕይወት መላገጫ የሚሆነው?  ከእሳቱ ርቀው፤ የሃሰት ትርከት የሚያሰራጩ የአስተሳሰብ ድንክየዎች፤ ጣት ከመጠቆም በስተቀር ለሀገራችን፤ ያበረከቱት በጎ አስተዋጽኦ ምንድነው? አዲስ አበባ ተቀምጦ፤ በጥሬ ስጋ የሚጫወት እና በውስኪ የሚራጭ የዘመኑ ፖለቲከኛስ፤ ለተጎጂው ህዝባችን፤ አንድ ጠርሙስ ወኃ ማቀበል ተስኖት፤ በምን ሞራል ነው፤ መንግሥትንም ሆነ ሌላውን ለመውቀስ እና ለማውገዝ የሚችለው?

ቆም ብለን እናስብ፤ ጠላቶቻችን የሚፈልጉት ጣት እየተጠቋቆምን፤ እንድንዳከም እና እርስ በእርስ እንድንጋደል ነው። ለዚህም ነው፤ በዓለማችን ታላላቅ የተባሉት የዜና አውታሮች፤ ምንም ነገር ሳያዩ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የእርስ በእርስ ጦርነት ተጦጡፏል እያሉ የሚያስነብቡን። የፖለቲካ ሹክቻው የትም አይሄድብንም፤ መሻኮትም የምንችለው፤ የምንሻኮትባት ሃገር ስትኖረን ነው። ውጊያው አብቅቷል፤ ጦርነቱ ግን እንደቀጠለ ነው። ይህንን ያልተገነዘብን ከሆነ፤ በተደጋጋሚ የንጹሃን ዜጎቻችን ሕይወት ገና እንደሚቀጠፍ ያልተገንዘብን እና ያንን ለመመከት ያልተዘጋጀን መሆናችንን ያሳብቅብናል። ለንፁሃን ዜጎች መቀጠፍ ጥፋቱ የመንግስት አይደለም፤ ኢትዮጵያን ለማጥፋት በወሰኑ ሃይሎች የሚፈጸም ጥፋት እንጂ። አጥፊውን በሚገባ ካላወቀን፤ ጥፋቱን ለመመከት አንችልም። ዐብይ አሕመድን፤ በተለያየ ምክንያት የሚጠሉት አሉ፤ ይህ መብታቸው ነው። በእርግጠኝነት መናገር የምችለው፤ ዐብይ አሕመድ በኢትዮጵያ ሕልውና ላይ የማይደራደሩ፤ ለዛም ሕይወታቸውንና የቤተሰባቸውን ሕይወት አደጋ ላይ ጥለው የታገሉ እና እየታገሉ ያሉ ቁርጠኛ መሪ በመሆናቸው፤ ከሚጠሏቸው ጥቂት ዜጎች የበለጠ፤ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚደግፋቸው እና የሚመካባቸው ብርቅዬ የሃገር አለኝታ ናቸው። ለዚህም ነው፤ ኢትዮጵያን የምንወድ ሁሉ፤ ጣት ከመጠቋቆም ይልቅ፤ ጉልበታችንን፤ እውቀታችንን እና ሃብታችንን አስተባብረን፤ በቁርጠኝነት ልንደግፋቸውና ሃገራችን ከተቃጣባት ከባድ አደጋ ልንታደጋት የሚገባው።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ፤   

ከኢትዮጵያ ውጭ ለምትኖሩ፤ መልካም 2021 ይሁንልን።        

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here