spot_img
Sunday, May 28, 2023
Homeነፃ አስተያየትየወቅቱ የአማራና የኦሮሞ ልሂቃን የፖቲካ መስተጋብሮች ከኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነት አንጻር

የወቅቱ የአማራና የኦሮሞ ልሂቃን የፖቲካ መስተጋብሮች ከኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነት አንጻር

- Advertisement -
Amhara _ Oromo _ article

ዳምጠው ተሰማ
የካቲት 11 , 2013 ዓ. ም.


የወቅቱን ሁለቱን ህዝቦች ልሂቃን ፖለቲካዊ መስተጋብር ቀደም ካለው ታሪካዊ ዳራ ብጅር የተሻለ ይመስለኛል፡፡ በአማራን እና በኦሮሞ ማህበረሰብ መሃል የማይታረቅ የፖለቲካ ጸብ እንዲኖር የመፈለጉ እንቅስቃሴ ጣሊያን አድዋ ላይ በኢትዮጵያዊያን ህብረት ድል በተመታች ማግስት እንደዋነኛ የፖለቲካ መሳሪያ ተደርጎ እንደተዋሰደ እረዳለሁ፡፡የአድዋ ታሪካዊ ድል ጣሊያንን ያንበረከክንበት ብቻ አልነበረም፡፡ ይልቁንም ለመላው የአውሮፓ ቅኝ ገዚዎች መርዶ ነጋሪ፣ ለመላው ጥቁር ህዝብ የሞራል ጋሻን ያበረከተ ነበር፡፡ ድሉ አለም አቀፍ ይዘት እንዳለው ሁሉ በጥቁር ንጉስ እና በጥቋቁር ጀነራሎች የምትመራውን ኢትዮጵያን ለመበቀል አለም አቀፍ ተዋናዮች ቀጥተኛ እና ኢ-ቀጥተኛ ተሳታፊ ሊሆኑ ችለዋል፡፡ 

የሽንፈቱ እፍታ መምረር ያሰከራት ጣሊያን እንደመሆኗ እ.ኤ.አ. የ1896 ሽንፈቷልን ለመበቀል ስትዘጋጅ የኢትዮጵያን ብርቱ ክንድ ለመምታት ከግዙፍ ወታደራዊ ኃይል የበለጠ የውስጥ ክፍፍል መፍጠር ውጤታማ እንደሚያደር አስልታ ነበር የ1928ቱን ወረራ የፈጸመችው፡፡ ጣሪን በወረራው ዋዜም ሆነ በሂደቱ በኢትዮጵያዊን መካከል የእርስ በእርስ መጠራጠሮች እንዲነግሱ ፣ አንዱ በሌላው ላይ ሰይፍ እንዲመዝ፣ የአማራው ልሂቃን በሌላው ወንድሞቹ እንደጨቋኝ ገዥ እንዲታይ፣ ከአማራው ውጭ ያሉ ልሂቃኖች ስለሀገራቸው ያስመዘገቧቸውን አኩሪ ታሪኮችን እንዳይዘክሯቸውና በጥላቻ የኢትዮጰያን ኑባሬ አንዲክዱ በዲናር ተከፋዮች አማካኝነት ማስረጽ ችላ ነበር፡፡ ለጣሊያን ከፋፍሎ ማጥቃት ስልት አልመች ያሉ የኦሮሞና የሌሎች ብሄር ልሂቃን ግን ሰማዕታት ሆነዋል፡፡ በጥላቻ ትርክት የተማገረው ከፋፍሎ የመደቆስ ስልትና የኢትዮጵያዊን ህብረት የመናድ ሴራን ለ5 አመቱ የወረራ ዘመን እንድመሳሪያ መጠቀም ተችሏልም፡፡ እንኳን የዛን ዘመን የመሃል ሀገር ፖለቲካ አስኳል የሆነው የኦሮሞና የአማራ ልሂቃን የኮንሶን ህዝብ ከሌላው ነጥሎ ለማሰልፍ ተሞክረል፡፡

የ1960ቹ የበዳይ ተበዳይ ትርክትና ፖለቲካዊ ተዋስዖ ርዕዮ-አለማዊ አዋዜ ይታከልበት አንጂ የወረራው ዘመን ከፋፍሎ የመግዘት ተቀጽላ ነው፡፡ይህውም በውጭ ተጻራሪ አካላት የሚታገዝና     በሃገሪቱ ከ65-70 በመቶ የሚሆነውን የሚሸፍኑትን የአማራንና የኦሮሞን ህዝቦች ከፋፍሎ ሀገሪቱን ማዳከምን ኢላማ ያደረገ ስምሪት ነበር፡፡

በወቅቱ የነበረው አምባገነናዊ አስተዳደር፣  የወቅቱ የጨቋኝ ተጨቋኝ የአተራረክ ዘይቤና የግራ ዘመሙ ፖለቲካዊ ቅኝት፣ የውጭና የውስጥ ተዋናዮች መብዛትና የኢትዮጵያን እንደ ቅርጫ ስጋ የመከፋፈል ሴራን እውን ለማድረግ የርዕዮ-አለምና የቁሳቁስ እስፖንሰርነት እንቅስቃሴዎች በጣሊያን የወረራ ዘመን ለተጀመረው አፍራሽ የባዕዳን የሴራ ድር-ማግ የሚያቀብሉ ኩነቶች ነበሩ፡፡ በዚህ የተነሳ የወቅቱን የመገንጠል ጥያቄዎችን ጤናማ የፖለቲካ ጥያቄ አድርጌ የምወስድ ነኝ፡፡ ምክንያቱም ከላይ የተጠቀሱት የሀገራዊ አንድነትን ማራኪ የማያደርጉ አስተሳሰቦችና ልዩ ልዩ ከኢትዮጵያ አንድነት በተቃራኒ የተሰለፉ ተሳታፊዎች የፖለቲካዊ አየሩን በተተቆጣጠሩበት ሁኔታ የአምባገነናዊ አስተዳደር ድቆሳ ሲታከልበት የተገንጣይነትና የአቢዮተኝነት ንቅናቄ የሚጠበቅ በመሆኑ ነው፡፡ ሆኖም የዚህ አይነት ወቅታዊ ሁኔታ ወይም አምባገነናዊ አገዛዝ አንዱን ብሄር ከሌላው በተለየ መልኩ የሚደቁስ እንዳልነበረ እሙን ነው፡፡ ቶሎ የመከፋት ደረጃችን ስለሚለያይ እና ለተመሳሳይ ችግር የተለያዩ መፍትሄዎች የማመንጭት ተፈጥራዊ ባህሪ ስላለን አንዱ መፈንቅለ መንገስትን እንደመፍትሄ ሲወስድ ሌላው ተገንጣይነትን ሊመርጭ ይችላል፡፡ 

በዚያን የሆያ-ሆዬና የአቢዮች ዘመን ከአንድ ወገን ማለትም ተራማጅ ነኝ ከሚለው አካል  በኩል የሚሰሙ ድምጾች አይለው በመቆየታቸው የወቅቱ የፖለቲካ ኃይሎች የጽሞና ጊዜ ወስደው በጋራ ራዕይ ላይ መምክርና አካታች መፍትሄ መዘየድ ሳይቻል ቀርቷል፡፡ በመሆኑም ከመተማመን ይልቅ የሚጋጩ ህልሞች የሚመስሉ ድምጸቶች ገነው በመውጣታቸው መፈራረጅና የተለያየ የታሪክ አተረጓጎም የጨዋታውን ሜዳ ተቆጣጠሮት ሳለ የኢህደሪ መንግስት መዳከምና መገርሰስ ለሁለተኛው መዋቅራዊ የከፋፍለህ ግዛ ምዕራፍ አቀብሎናል፡፡  

በድህረ-1983 ዓ.ም. ስርዓታዊ በሆነ አግባብ የጣሊያንን ሌጋሲ ወራሽ ቡድኖች የአማራንና የኦሮሞን ልሂቃን ግንኙነት በሳትና ጭድነት መስለው ለተግባራዊነቱ ባለመታከት ሰርተዋል፡፡        ከ1982 ዓ.ም. ጀምሮ ንጹሃን አማራዎች፣ ክርስቲያን ኦሮሞች አና ጉራጌዎችን ሰማዕት ያደረጉ ጭፍጨፋዎች ዋነኛ መነሻቸው የባዕዳን ሴራ ነው፡፡ የሴራው ተሸካሚዎች የድርድር ጠረጴዛን ማዘውተር ያለመድነው ሴራ የተሴረብን ኢትዮጵያዊን ነበርን፣ ነንም፡፡ ባለፉት 30 ሲደምር አመታት የልሂቃኑ ግንኙነት በህግና በፖለቲካ መርሆች ተጋርዶ ጤናማ ወይም በመተማመን ላይ የተመሰረተ መስተጋብር እንዳይኖር ሆኗል፡፡

ወደ አሁናዊ ጉዳይ ስመጣ የአማራ ህዝብ በብዛት ይኖርባቸዋል ከሚባሉት ክልሎች ቀዳሚው ኦሮሚያ ነው፡፡ በአማራ ክልል የሚኖረውን የኦሮሞ ህዝብ ቁጥርምን ያህል በሌሎች ክልሎች አይገኝም፡፡ ዘርፈ ብዙ በሆነው መስተጋብርን ማለትም ጤናማ የማህበረ-ኢኮኖሚ ግንኙነቶችን በማከናወን ረገድ በሁለቱ ማህበረሰብ መካከል ብዙ ያልተነበበ ገጽ አለ፡፡ በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች ለአይንና ለጆሮ የሚቀፉ ማንነት ላይ ያነጣጠሩ ኢሰብአዊ ድርጊቶች እየተፈጸሙ ባሉበት ሁኔታ እንኳን በአመዛኙ በብዙ አካባቢዎች የሁለቱ ማህበረሰብ የማህበረ-ኢኮኖሚ መስተጋብር እና የባህል አንድነት በነበረብት ነው፡፡  

ለምን የኦሮ-አማራ ጥምረት ተቀዛቅዞ የተቃርኖ ድምጾች ገነኑ?

የፖለቲከኞች ስክነት ማጣትና ጸንፈኛ ሆኖ በመታየት ቅቡልነትን ለማሳደግ በሚጥሩ የሁለቱም ህዝብ ልሂቃኖች የጸነፉ የሚዲያና የአዳራሾች ውስጥ ንግግሮች ያለመገራት አዝማሚያ አለ፡፡ በለውጡ ማግስት በአዳራሽ ጭብጨባዎች የሰከሩ አንዳንድ የሁለቱም ህብች ፖለቲከኞች አለም ከአዳራሽ ውጭ እንደሌለች እስኪመስል ድረስ የጸነፉና ለትርጉም የተጋለጡ ንግግሮችን ሲያደርጉ ሃይ ባይ ጠፍቶ እንደነበር የሚታወቅ ነው። በኦሮሚያ የሚስተዋሉ ማንነት ተኮር ጥቃቶች ጭብጨባ በበዛባቸው ስብሰባዎች ‘‘ወሎ በደም አሮሞ ነው እና ወሊሶ ኦሮማይድ የሆነ አማራ ነው’’ ከሚሉ ፋይዳ ቢስ አገላለጾች ጋር ተደምረው የኦሮ-አማራ አሰላለፍ ለመቀጨጩ በምክንያትነት የሚጠቀሱ እንደሆኑ አምናለሁ። ሚዲያዎችም ያልተሞረዱ ሀሳቦችን እንደወረዱ በማሰራጨትና በሁለቱ ማህበረሰብ ልሂቃኖች መካከል ስንጥቆችን የማስፋ ዝንባሌ ያላቸውን ግለሰብችን በማቅረብ ብሽሽቅ የሚመስል ተግባር መፈጸማቸው የኦሮ-አማራ ጥምረት የአንድ ወቅት አጀነዳ ሆኖ እንዲቀር ሚናው የጎላ ነው።

አንዳንድ የለውጥ ኃይል አመራሮችና የኦሮሞ ፖሊቲከኞች አወዛጋቢ በሆነው የአዲስ አበባ የባለቤትነት ጉዳይ ላይ ዘፈቀዳዊ የዋጭ-ሰልቃጭ መግለጫዎችን መስጠት እና ከአማራም ሆነ  ከኦሮሞ ወገን የሆኑ አንቂዎች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የአኩራፊዋን የህወሀትን አጀንዳ በመቀበል በቁርሾ ላይ ቁርሾ የመደማመር ሚና ተጫውተዋል፡፡ የማህበራዊ ሚዲያ ልጓም ማጣት ነገሩን ከመስመር እንዲያልፍ አድርጎታል የሚልም እይታ አለኝ፡፡   

የአማራ እና ኦሮሞ ልሂቃን መጓተት እንዲረግብና በመተማመን ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ይኖር ዘንድ ምን ይደረግ ?

1). በምክክርና በድርድር መተማመኖችን በመፍጠር የጋራ ራዕይ መገንባት፡- ምክክር የማድረጉ ሂደት ሰባት ጊዜ ባይሳካ አንኳን ለስምንተኛ ወይም ከዛ በላ ለሆነ ጊዜ ተደጋግሞ ሊደርግ የግድ ነው፡፡ በድርድር ውጤት እስኪገኝ ድረስ ደክመኝ ተብሎ የሚተው እንዳይደለ የሁለቱም ማህበረሰብ ልሂቃን ሊያሰምሩበት የሚገባ ነው፡፡ አሁን ላይ የሚታየው የተቃርኖ ፖለቲካ እነሱ የጠሉትን እኛ እንወደዋለን እነሱ የወደዱትን እኛ እንጠላዋለን አይነት ነውና መስከን አለበት፡፡ የህግ መርህ ማሻሻያዎችም ሆነ አፍራሽና የተዛቡ የፖለቲካ ትርክት ለውጦችን አምጠን የምወልዳቸው ከድርድር ብቻ ነው የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡ በኦሮሚያ የሚኖረው የአማራ ህዝብ ደህንነት ጥበቃና የተመጣጣኝ ውክልና መብት እንዲሁም የኦሮሚፋ የቋንቋ የፌደራሉ መንግስት የስራ ቋንቋ ይሆን የሚል ጥያቄና በአዲስ አበባ ከተማ ላይ የሚስተዋለው ፖለቲካዊ ቋጠሮ የሚፈታው እየጋለ በሚረግብ እየበረደ በሚግል ውይይት ነው፡፡ በቀዳሚነት ግን የሰው ልጅ በህይወት የመኖር መብት የማስከበር ኃለፊነትን መወጣት ከኦሮሞ ልሂቃን ይጠበቃል፡፡ በዘላቂ ሰላም ላይ ከመውሳት በፊት በዚህኛው ጉዳይ ላይ ትኩር ማድረግ ያሻልም፡፡ይህን አይነት ኃላፊነት የመወጣት ቁርጠኝነት ጠረጴዛ ስቦ በድርድር ለጋራ ችግሮቻች የጋራ መፍትሄ ለማምጣት መደላድል ይፈጥራል፡፡  

2) የጋራ የሲቪክ ተቋማት ምስረታ:-የአንድ ችግር መፍትሄ አንድና ወጥ ሊሆን አይችልም። በመሆኑም አሁን ላይ በፖለቲካዊ ድርድር ያልተፈቱ ልሂቃን መራሽ ክፍተቶችን ተቋማዊ በሆነ አግባብ ማስተካከል ስለሚያስፈልግ በዋናነት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ላይ የሚያጠነጥኑ የባህል፣ የኢኮኖሚ፣ የስነጥበብ፣ የእስፖርት፣ የትምህርት በጎ አድራጎት ተቋማትን ማቋቋም ያስፈልጋል። የሚደራጀው የሁለቱ ህዝቦች ልሂቃንን ያቀፈ አደረጃጀት የአማራም ሆነ የኦሮሞ ማህበረሰብ በተለይ ወጣቱ መረጃን የማንጓለል፣ የማመዛዘን እና አመክኗዊ የሞራል ዳኘኝነት እየሰጠ ለሀገራዊ ሰላም ለመጠበቅ ታሪካዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ የማስተማርና የውትወታ ስራ የሚሰራ ይሆናል፡፡ ሚዲያዎች የሚያሰራጯቸው ትርክቶችና የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች ትልቁን ስዕል ከግምት ያስገቡ እንዲሆኑ በሙያ ጭምር ያግዛል። ከሁለቱ ህዝቦች  አብራክ የተወለዱ ልሂቃንም የቀጣይ የአብሮነት እጣፋንታን በሚያቃኑ ፍልስፍናዎች ፖለቲካችንን ለመቃኘት ለመተረክና እውነተኛ የአብሮነት ታሪኮች ለጋራ እሴት ግንባታ እንዲውሉ ሰብአዊ መደላድል እንደሚሆኑ የሚታመን በመሆኑ ድምጻቸው ከፍ ብሎ እንዲሰማ የማህበራት ሚና የጎላ ነው፡፡  በኢትዮጵያ የጋራ ራዕይ ላይ ብሎም በአማራና በኦሮሞ ህዝብ የሰርገኛ ጤፍነት ታሪክና ነባራዊ ሃቅነት ላይ የሚያጠነጥን ትርክትና አካዳሚያዊ ትንተናን ማቅረብ የሚችሉ የሁለቱ ህዝቦች ልሂቃን ድምጽ እንዲሰማ የሚያስችል በተለያዮ ዘርፎች ላይ ትኩረት የሚያደርጉ የሁለቱ ህዝቦች  ማህበራት በፌደሬሽን፣ በኮንፌደሬሽን በቅንጅትና በጥምረት በማስተሳሰር ለሚፈለገው ሰናይ አላማ ማዋልንም የሚቻልበት እድል አለ፡፡             

3).የቅዱስ ውሸትና የሪኮንስትራክሽን ስርጸት፡- እንደኢትዮጵያ ያለን ታላቅ ሃገር /ሪፐብሊክ/ “በቅዱስ ውሸት (Noble Lie)” እውን ይሆናል በሚለው የአፍላጦስ (የፕሌቶ) ንድፈ ሃሳብን የተቃኘ የሃገረ መንግስት ግንባታን እውን ማድረግ የጋራ ራዕይን እንድንወራረስ ፋይዳ አለው፡፡ፕሌቶ በግሪክ ማህበረሰብ የፖለቲካ ስርዓት ስኬታማነት የሚበጅ ክቡር ውሸት አስፈላጊ ነው፤ ለሪፐብሊኩ ጽኑ መሰረት ይሆናል የሚለው ተዋስዖው በየትኛውም አለም የፖለቲካ ተዋስዖ ገዢ ሃሳብ ነው፡፡፡፡ፕሌቶ ዘ-ሪፐብሊክ በተሰኘው ስራው የከበረ/ የተፈቀደ/ ውሸት ምንነት ሲያብራራ “ትርፍ ጊዜያችንን በታሪክ ነጋሪነት እናሳልፍ፣ የምንናገረው ታሪክ የነገ ጀግኖቻችንን የሚያሰተምር ይሆናል” በማለት ይጀምራል፡፡ “ወጣቶች በዚህ ቀረጻ ውስጥ የሚያለፉ ናቸው፤ በቅድሚያ ሙዚቃ ከዚያ የጂምናስቲክ ትምህርት የሚሰጥ ሲሆን ሙዚቃ ስነ-ጸሁፍንም ያካትታል፡፡ ለወጣቶች የምናስተምራቸው ልብ ወለድ ታሪክ ሙሉ በሙሉ ከእውነት የራቀ አይሆንም፡፡ ይህን አይነት ትምህርት የጀምናስቲክ መማሪያ እድሜ ደረጃ ላይ ሲደርሱ የሚሰጥ አይደለም፡፡ በትምህርታዊ ቀረጻው ህጻናት የሚነገራቸው ታሪክ በማንኛውም ሰው በየአጋጣሚው የሚተረክ መሆን የለበትም፣ “ሳንሱር ያስፈልገዋል”[1]፡፡ “በስነ-ጽሁፍ ለወጣቶች ትምህርት ስናስተላልፍ ትርጉም አልባ እውነቶች አይነገሩም፤ ውሸቶችም የተመጠኑና ሳንሱር የተደረጉ ይሆናሉ”፡፡የፕሌቶ ክቡር ውሸት (Noble Lie) በሪፐብሊኩ (ሪፐብሊክ የሚለውን ሃገራዊ ስርዓት ብለን እንውሰደው) መልካም ግብን ለመምታት ታልሞ ሲዋሽ ነው፡፡

ወጣቶችን በማስተማር የወደፊቱ ትውልድ ለሃገሩ የቀና/የተሞረድ/ እንዲሆን የሚዋሹ/የሚደበቁ/ ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው በሆነ አጋጣሚ ውሸት ጠቃሚና የማይወገዝ መሆኑን “የፕሌቶ ዘ-ሪፐብሊክ” ተዋስዖ (discourse) ያስረዳል፡፡ ይህም ከችግር ለመዳን የሚያስችል የሰዎችን ስነ-ልቦና ለመገንባት ነው፡፡ ኢትዮጵያ የተከበሩም የተዋረዱም ውሸቶች ባለቤት ናት፡፡ በማህበረሰቡ ውስጥ ስር የሰደደ የክቡር ውሸት ስነ-ልቦና ሰርጾ ይገኛል፡፡ በተግባር የተፈተነ በጎ አስተዋጽዖ አለው፡፡ በአካዳሚዊ ፍልስፍ አይታገዝ እንጂ በኢትዮጵያም ክብር ውሸት ያለና የነበረ ነው፡፡ በትህትና የታነጹ አባቶች “ዋሽቶ ማስታረቅ” የሚል የቆየ አስተሳሰብ አላቸው፡፡ ይህ አስተሳሰብ በየትኛውም የሃገሪቱ አካባቢ የሰረጸ በተግባርም እየተፈተነ አወንታዊ ውጤት ማሰገኘቱን ከሊቅ እስከ ደቂቅ የምናውቀው ነው፡፡ አንዳንድ ሙያዎችም ሰራተኛው የሚያውቀውን ሃቅ እንዳይናገር ወይም እንዲደብቅ ያዛሉ፡፡ በቃ አንድ ሰው አይኑ ያየውንና ጆሮው የሰማውን በአጠቃላይ በስሜት ህዋሳቶቹ ታግዞ መገንዘብ የቻለውን እውነታ እንዲገልጽ ሲጠየቅ ያለመናገር መዋሸት ነው፡፡ ምክንያቱም ያለመዋሸት አውነቱን ማሳወቅ ነውና፡፡ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ የኦሮሞና የአማራን ህዝብ የዘር ግንድ አንድነት ወይም ከአንድ ምንጭ መቀዳትን የሚመለከት አውድ ያለው መጽሃፍ ለቅዱስ ውሸት

የቀረቡ ይዘቶች አንዳሉት ከግል ግምገማዬ መረዳት ችያለሁ፡፡ ወጣቶች የቡርቃ ዝምታ የተሰኘን ምርጥ ነገር ግን ጥላቻን ጠማቂ ልብ-ወለድ አንደእውነተኛ ታሪክ አድረገው እንዲረዱት የሚሹ ልሂቃን ባሉበት ዘመን የፕሮፌሰር ፍቅሬ ጅማሮ እጅግ የሚደነቅ አድርጌ ነው የምወስደው፡፡ በተቃራኒው የሃገሪቱን ታሪካዊ ልዕልናና የህዝቦችን ሃገራዊ የጋራ ራዕይ በሚፈታተን መልኩ ተከሽነው በእውነት እየተዋዙ የሚቀርቡ ስርዓታዊ ውሸቶች አሉ፡፡ እነዚህ በፕሌቶ እይታ የተዋረደ ውሸት (Bad lie) የሪፐብሊኮን ልዕልና የሚንዱና የዲኮንስታራክሽን ማስፈጸሚ አተራረኮች ናቸው፡፡ የተቀደሰ ውሽትን መርሆችና ሪኮንስተራክሽን እሳቤዎች ለመተግበር ምህዳሩ ዝግ አይደለም፡፡ ከኦሮሞም ሆነ ከአማራው ወገን ያሉ ልሂቃን  ከኢትዮጵያ ሃገረ መንግስት እሳቤ በተቃርኖ የተቃኘውን የኦሮሞን ጻነት ግንባር (ኦነግ) ጉምቱ መሪ አቶ ሌንጮ ባቲ የአሁኒቷ ኢትዮጵያን በመፍጠር ሂደት የኦሮሞን ህዝብ ድርሻ ተገቢ ክብር ሰጥተነው በአብሮነት መቀጠልና የሀገሪቱ ችግር ስርዓት ወለድ እንጂ ብሄር መራሽ አይደለም የሚል እሳቤን ሲሰብኩ አይተነናል፡፡[1] ይህ ብቻ አይደለም፣ ቀደም ሲል ኢትዮጵያን አስበንበት ዲኮንስትራክት አድርገናት ነበር፣ አሁን ላይ ግን ሪኮንስትራክት ማድረጉን መርጠናል በሚል ያቀረቡትን ንግግር አድምጫለሁ፡፡ ኦሮሞን ከኢትዮጵያ ገንጠሎ ሪፐብሊክ መመስረት ከሚል ፖለቲካዊ ንቅናቄ ወደ ኢትዮጵያዊ አብሮነት እና የአማራ ጨቆና የሚልን ትርክት በመተው ስርዓት ወለድ ነበር ችግራችን ወሰደሚል ፖለቲካዊ ችግር መንስዔ-ትንተና የተደረገ ሽግገር ነው፡፡ ይህን የአቶ ሌንጮን የሃሳብ እጥፋት በቀላል የሚታይ ለውጥ አድርገን ከወሰድነው እይታችን አቅላይ ተደርጎ የሚፈረጅ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ከፍም ዝቅም የማይል አቋም የሚያራምዱ በእኔ አቅም የማይተረክ የገዘፈ ታሪክ ያላቸው ከኦሮሞ አብራክ የወጡ ዋርካዎች የሪኮንስትራክሽንና “በቅዱስ ውሸት ቅኝቶችን መሬት ለማስረገጥ በቂ መምህራኖች ናቸው፡፡

እነዚሁ አካላት በልብ ወለድ የተቃኘ የተቃርኖ ፖለቲካን ከማስተካከልና እውነትኛ ታሪኮችንም ለትውልዱ በተለያየ መንገድ እንዲያስተምሩ እድሎችን ማቻቸት የሁሉም የሀገር ጉዳይ ያገባኛል የሚል አካል ኃላፊነት ነው፡፡ 

ማጠቃለያ

ችግሮቻችን ዘርፈ ብዙና በሶስተኛ ወገብ ማቀጣጠያ የሚጨመርባቸው በመሆናቸው ባለመሰልቸት ምክክሮችን ማድረግ፣ የጋራ ራዕይንና ግብን ማሳካት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ማተኮር የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ሌላውና ዋናው አንኳር ጉዳይ በየትኛውም አካባቢ በተለይ ኦሮሚያ የሰው ልጅ በህይወት የመኖር መብት የማስጠበቅና በማንነት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን የማስቆም ቁርጠኝነት በማምጣት በስሜት ህዋሳቶች የሚዳሰስ ውጤት ማስመዝገብ ነው፡፡ በሌላ በኩል በረጅሙ የታሪክ ጉዟችን ከቅኝ ገዚዎች የወረስነውና በመተማም ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ እንዳይኖረን ዋነኛ መሰናክል ተደርጎ የሚወሰደውን የታሪክ አተራረክና አረዳዳችንን በሰከነ ፖለቲካዊ ውይይት ፈር የማስያዝ የቤት ስራ ማጠናቀቅም የግድ ነው፡፡

የኦሮ-አማራ የማህበረ-ፖለቲካ ጥምረት መጀመር በራሱ እና ጥምረቱ የፈጠረው ጉልበት የምንጊዜም የኢትዮጵያዊያን የጋራ እሴት ጠንቅ የሆነውን ትህነግን መገርሰሱ ሁለት አንኳር ነጥቦችን የሚያስገነዝበን ነው። አንደኛ እኤአ ከ1896 ጀምሮ ሲለፉበት የነበረው በኦሮሞንና በአማራ ልሂቃን ተቃርኗዊ ግንኙነትን ዘላለማዊ የማድረግ ሴራ እንደጉም በኖ የሚጠፋ መሆኑን ማሳያ ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ የሁለቱ ህዝብ ልሂቃኖች አንጻራዊ ትብብር በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ አህጉሩ ደረጃ ግዙፍ ኃይል መሆኑን አስረጂ ነው። በመሆኑም የኦሮ-አማራን የአጭር ጊዜ መልካም ውጤቶች ለነገ ጉዟችን የታሪክ ስንቅ ቢደረጉ ተመራጭ ነው፡፡  

[1]“Then the first thing will be to establish a censorship of the writers of fiction, and let the censors receive any tale of fiction which is good, and reject the bad; and we will desire mothers and nurses to tell their children the authorized ones only. Let them fashion the mind with such tales, even more fondly than they mould the body with their hands; but most of those which are now in use must be discarded” (Plato, 1999:53).

[2] https://www.youtube.com/watch?v=v3Urpnr64Zo ላይ የቀረበውን የአቶ ሌንጮ ባቲን ንግግር ያዳምጡ፡፡

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
12,856FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here