spot_img
Tuesday, June 25, 2024
Homeነፃ አስተያየትየአገር ወዳድነት ስሜት በጠፋበትና ክህደት በበዛበት አገር ጠንካራ ኢኮኖሚና ማህበረሰብ መገንባት አይቻልም፣...

የአገር ወዳድነት ስሜት በጠፋበትና ክህደት በበዛበት አገር ጠንካራ ኢኮኖሚና ማህበረሰብ መገንባት አይቻልም፣ ክፍል ሁለት!

ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር) _
ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)
መጋቢት 22፣ 2021

መግቢያ

ይህንን አርዕስት አስመልክቶ በመጀመሪያው ጽሁፌ ወደ መደምደሚያው ገደማ በተለይም በዕድሜ የገፉ ኢትዮጵያውያኖችን ሚና በሚመለከት አንዳንድ ነገሮችን ብዬ ነበር። አንዳንዶች እንደዚህ ዐይነቱን አጻጻፍ ከተስፋ መቁረጥና ከሃሳብ ተሟጦ ማለቅ ጋር ለማያያዝ ሞክረዋል። ይህ ዐይነቱ አተቻቸት ትክክል መስሎ ቢታይም ጸሀፊው ማንንም ተስፋ ለማስቆረጥ ብሎ አይጽፍም፤  ጽፎም አያውቅም። ከዚህም ባሻገር ጸሀፊው ከ20 ዓመታት በላይ ተስፋ ሳይቆርጥ ጊዜ በመውሰድና ከጊዜው ጋር ሊሄዱ የሚችሉ አርዕስቶችን በመመረጥ ከፍልስፍና እስከፖለቲካና፣ እንዲሁም ደግሞ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ሰፋፊ ጽሁፎችን ለአንባቢያን አቅርቧል። የተለያዩ ጽሁፎቹም በድረ-ገጹ ላይ የሚገባቸውን ቦታ በመያዝ ተቀምጠዋል። ወደፊትም ጤንነቱ እስከፈቀደለት ድረስ የሚችለውን ከማድረግ አይቆጠብም።

በዕድሜም ሆነ በሙያ የምንለያይ የአገራችን ሁኔታ ያሳስበናል የምንል ኢትዮጵያውያን በአለን አቅም ድምጻችንን ስንናሰማ ከአርባ ዓመታት በላይ አስቆጥረናል። ይሁንና ግን ይህን ያህል ዓመታት የፈጀና የብዙ ወጣት ኢትዮጵያውያንን ህይወት የቀጨፈና አገራችንንም ዛሬ የምትገኝበት ቦታ ላይ ያደረሳት ፖለቲካ የሚባለው የትግል ፈሊጥ ችግራችንን የሚፈታልን ከመሆን ይልቅ ያለውን ችግር የባሰ ውስብስብ በማድረግ በመሀከላችን ከፍተኛ አለመግባባትን ፈጥሯል። አንዳንዶቻችን ለአንድ ዓላማ ከመታገል ይልቅ ጎራ በመለየትና እንደጠላት በመተያየት ኃይላችንን ጭረሰናል፤ ሳናውቀውም የብዙ ሰዎችን ህይወት አበላሽተናል። እንደሚታወቀው ማንኛውም ሰው በዚህች ዓለም ላይ የሚኖረው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በህይወት እስካለ ድረስም ብዙ ነገሮችን ለመስራት ይፈልጋል። ያለንበትም ዘመን 21ኛው ክፍለ-ዘመን ነው። ይህም ማለት ዘመኑ በቴክኖሎጂና በሳይንስ የረቀቀ ቢሆንም በዚያው መጠንም ሀብትንና ኃይልን የሚጨርስ ነው። አብዛኛዎቻችን ይህን ሁኔታ ተረድተን ወይም አልተረዳን እንደሆን ለማወቅ በጣም አስቸጋሪ ነው። በሌላ አነጋገር፣ ማንኛውም ሰው ከፖለቲካ ባሻገር ሌላም ህይወት እንዳለው መረዳት ያስፈልጋል። የፖለቲካ ትርጉሙም የሰውን ልጅ ህይወት ማቃለል እንጂ ውስብስብ ለማድረግና በዘለዓለማዊ ጭንቀት ውስጥ እንዲኖር ማድረግ አይደለም።

ለማንኛውም በሳይንስ ዓለም ውስጥ የዩኒቨርሳል ህግ የሚባል ነገር አለ። ይህም ማለት አንድ  ሰው ትግል ብሎ- የፖለቲካን ትግል ብቻ የሚመለከት- ሲነሳ በጭንቅላቱ ውስጥ መቋጠር ያለባቸው ነገሮች አሉ። እነዚህን መሰረተ-ሃሳቦች በጭንቅላቱ ውስጥ የቋጠረ ከሆነ ኃይሉንም ሆነ ያለውን ሪሶርስስ በስነ-ስርዓት ለመጠቀም ይችላል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ጤንነቱንም አይጎዳም፤ ቤተሰብም ካለው የተወሰነውን ጊዜውን ከቤተሰቡ ጋር ያሳልፋል። ምን ለማለት ነው የምፈልገው?  አብዛኛዎቻችን በፖለቲካ ትግል ውስጥ ሰተት ብለን ስንገባ ብዙ ያላብላላናቸው ነገሮች አሉ። ይኸውም አንድ ሰው የፖለቲካ ትግል አካሂዳለሁ ወይም በፖለቲካ ትግል ውስጥ እሳተፋለሁ ብሎ ሲነሳ ፖለቲካ የሚባለው ነገር በአንድ አገር ውስጥ ከሚገኝ ህዝብ ጋር በቀጥታ የተያያዘ መሆኑን መገንዘብ አለበት። ፖለቲካም ከፍትህና ከነፃነት ጋር የተያያዘ እንደመሆኑ መጠን እነዚህ በራሳቸው ከፍተኛ ንቃተ-ህሊናን እንደሚጠይቁ ግልጽ የሆነ አመለካከት መኖር አለበት። ስለሆነም እነዚህን ነገሮች በአገራችን ውስጥ ካሉት ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር፣  ማለትም ከመንግስት የመኪና አወቃቀርና እንዴትስ እንደተዋቀረ፣ ከፖለቲካ ንቃተ-ህሊና መኖርና አለመኖር ጋር፣ በምድር ከሚታየው የኢኮኖሚና የማህበራዊ ሁኔታ ጋር፣ ድህነትና የስራ-አጥነት ካሉ እንደዚሁም ከእነዚህና እነዚህን ከመሳሰሉት ጋር ማያያዝ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። የፖለቲካ ትግል በመሰረቱ ከስልጣን ጋር ብቻ የተያያዘ ሳይሆን አንድን ህዝብ ንቃተ-ህሊናውን በማዳበር ሰው መሆኑን ተገንዝቦ ታሪክ እንዲሰራና ተስማምቶ እንዲኖር ለማድረግ ነው። ከዚህ ግንዛቤ ውጭ በፖለቲካ ስም የሚካሄድ ትግል የዩኒቨርሳል ህግን ይጥሳል። የሰውን ኃይል የሚጨርስና በአንድ አገር ውስጥ ያለን ሀብት የሚያባክን ይሆናል። በተለይም ጭቅጭቅ ወይም ንትርክ የበዛበትና በተሳሳተ ትረካ ላይ ተመስርቶ የሚካሄድ ፖለቲካ የመጨረሻ መጨረሻ ያሉትን ሁኔታዎች የባሰውኑ ውስብስብ ያደርጋቸዋል።

ባለፉት አርባ ዓመታት ፖለቲካ የሚባለውን ፈሊጥ ከሳይንስና ከፍልስፍና ጋር ከመያያዝ ይልቅ በስሜት ላይ ተመርኩዞ የተደረገው ትግል አላስፈላጊ ደም መፋሰስ ውስጥ ከቶናል። ከአርባ ዓመታት በኋላም አሁንም ቢሆን ከቂም በቀልና ከቅዠት ዓለም ውስጥ ያልተላቀቅን ጥቂቶች አይደለንም። በአብዮቱ ወቅትና ከዚያም በኋላ በአገራችን ምድር ለምን እጅግ አስቀያሚ ነገሮች ሊከሰቱ ቻሉ? ለምንስ በፖለቲካ ስም ደም መፋሰስ ውስጥ ተገባ? ብሎ አንዳችንም ወደ ኋላ በመሄድ ጥያቄን በጥይቄ እያነሳን ምክንያቶቻቸውን ለመፈለግ አልቻልንም፤ ፍላጎትም የለንም። ባጭሩ ከአርባ ዓመት በኋላ አብዛኛዎቻችን የአስተሳሰብ ለውጥ አላደረግንም። አሁንም ቢሆን ካለስልትና ፍልስፍናዊ መሰረተ በሌለውና ሳይንሰ-አልባ በሆነ መልክ ነው የምንታገለው። ተጨባጭ ሁኔታዎችን ለማንበብ የሚያስችል ሳይንሳዊ ዘዴ ማዳበር አልቻልንም። በምን ዐይነት ርዕዮተ-ዓለምም እንደምንመራ ግልጽ አይደለም። ከዚህ ዐይነቱ የተወሳሰበና የሚያደናግር ሁኔታ ስነሳ በመደምደሚያው ላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት ጭንቅላታችን ውስጥ የቋጠርነው ነገር ስላለ እሱን በማውጣትና በአዲስ በመተካት በአገራችን ምድር ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲሰፍንና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ ሊመሰረት የሚችል ኢኮኖሚ እንዲገነባ የሚያስችል የፖለቲካ ትግል ማካሄድ አንችልም። ፖለቲካም ከሳይንስ፣ ከፍልስፍና፣ ከሶስይሎጂ፣ ከስነ-ልቦና ሳይንስ፣ ከኢኮኖሚና እንዲሁም አንድ አገር እንደማህበረሰብ እንዲገነባና እንዲታይ ከሚያስችሉት ነገሮች ጋር የማይያያዝ ከሆነ ይህ ዐይነቱ ፖለቲካ የፖለቲካ ትግል ተብሎ ሊጠራ በፍጹም አይችልም። ስለሆነም በዚህ መልክ ለማቅረብ መሞከሬ እህቶቼንና ወንድሞቼን ተስፋ እንዳማስቆረጥ ባይታይብኝ ደስ ይለኛል። 

ያም ሆነ ይህ የአገር ወዳድነት ስሜትን አስፈላጊነት የግዴታ ዛሬ ካለው ተጨባጩ የአገራችንም ሆነ የዓለም አቀፍ የፖለቲካ ሁኔታ በመነሳት ነገሩን ማብራራት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። በተለይም አሁን ባለንበት በተወሳሰበ የዓለም ሁኔታ ውስጥ የየፊናችንን አስተዋጽዖ ማበርከት አለብን የምንል ከሆነ መሰረታዊ ጉዳዮችን ግልጽ ማድረግ ያለብን ይመስለኛል። መሰረታዊ ነገሮች ግልጽ ሲሆኑና የትግሉ ዓላማም ሲታወቅ ብቻ ነው ታሪካዊ ግዴታችንን መወጣት የምንችለው።

የአገር ወዳድነት ስሜት በምን መልክ ይገለጻል? አገርንስ መውደድ ማለት ምን ማለት ነው?

በመጀመሪያው ጽሁፌ በስሜት ላይና በንቃተ-ህሊና ላይ የተመሰረተውን በተለያየ መልክ የሚገለጸውን የአገር ወዳድነት ስሜት ልዩነት ለማሳየት ሞክሬአለሁ። ሁለቱም የአገር ወዳድነት ስሜት መግለጫዎች የግዴታ ከማቴሪያል ዕድገትና ከዕውቀት መዳበር ጋር የተያያዙ ሲሆን፣ በተለይም በንቃተ-ህሊና ላይ የተመሰረተው የአገር ወዳድነት ስሜት የግዴታ ሁለ-ገብ ባህርይ እንዳለውና በተናጠል በሚታዩ ነገሮች ላይ ብቻ ሊገለጽ እንደማይችል ነው። ይህንን ዐይነቱን ሁለ-ገብ አስተሳሰብ የግዴታ ጠጋ ብሎ መመልከት ያስፈልጋል። ምክንያቱም በተለይም ከ1950ዎቹ ዓመታት መጀመሪያዎች ጀምሮ በአገራችን ምድር የገባው አስኳላ ወይም ዘመናዊ በመባል የሚታወቀው ትምህርት በማሰብ-ኃይላችን ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ለማሳደር በመቻሉ ነው። በሌላ አነጋገር፣ በጊዜው የገባው ትምህርት እራሳችንን ወደ ውስጥ እንድንመለከት፣ የአንድን ነገርና የህብረተሰብአችንን ዕድገት ከታች ወደ ላይና ከሁሉም አቅጣጫ ከህብረተሰብ ታሪክና ከሎጂክ አንፃር ለመመርምር የሚያስችል ኃይል ሊያጎናጽፈን ባለመቻሉ ነው። የአስኳላን ትምህርት አስመልክቶ ሰሞኑን አዲስ አበባ በአንድ የቴሌቪዢን ጣቢያ አንድ በዕድሜያቸው ገፋ ያሉ የቲያትር ሰው ተጠይቀው አገራችን ዛሬ ላለችበት ውድቀት ተጠያቂው የአስኳላ ትምህርትና ከዚህ ጋር ተያይዞ የአገራችንን ዕውቀት በመናቃችን ወይም ደግሞ ኋላ-ቀር ነው በማለት በማጥላላታችን ነው የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል። ስለሆነም በጥያቄ መልክ ያስቀመጥኩትን አርዕስት ለመመለስ ከመሞከሬ በፊት በዚህ ዐይነቱ ባልተሟላ ወይንም ምክንያታዊ ባልሆነ መልክ የቀረበውን አባባል የግዴታ ምክንያታዊ በሆነ መልክ መተንተን የሚያስፈልግ ይመስለኛል።

በእኛ አገር ያለው ትልቁ ችግር ከውጭ የሚመጡ አስተሳሰቦችና ቴክኖሎጂዎች ሊያስከትሉ የሚችሉትን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ውጤቶች ሳንመረመር ዝም ብለን ተግባራዊ ለማድረግ መጣደፋችን ነው። ይህ ዐይነቱ ጥድፊያና ያስከተለውን አሉታዊ ውጤት ምክንያቱን ሳንመረምር በአጠቃላይ ከምዕራቡ ዓለም የመጣው ዘመናዊ በመባል የሚታወቀው ትምህርትና ከዚህ ጋር የተያያዘው ቴክኖሎጂ ናቸው ለውድቀታችን ምክንያቶች የሆኑት ብለን ነገሮችን በቅጡ ያላገናዘበ መደምደሚያ ላይ እንደርሳለን። ስለሆነም ከምዕራቡ ዓለም የሚመጣውን ነገር ሁሉ በጅምላ እንደመጥፎ ነገር አድርገን እንወስዳለን። እንደዚህ ዐይነቱን ብዙም ሳይብላላ የሚሰነዘር አስተያየት ሳዳምጥ በአጠቃላይ ዕውቀትና ዘመናዊነት በሚሉት ዙሪያ የቱን ያህል ከፍተኛ ክፍተት እንዳለ ነው መገንዘብ የቻልኩት። የአውሮፓውን የዕድገት ታሪክ ለተመለከተ ከግሪክ ስልጣኔ ጀምሮ ዕውቀትንና ዕድገትን በሚመለከት በምሁራኖች ዘንድ የጦፈ ክርክር ተካሂዷል። ዕውቀትና ዕድገት አንድ ላይ ተያይዘው የሚሄዱ እንጂ ተነጣጥለው እንደማይታዩ የግሪክንም ሆነ በኋላ ላይ ሬናሳንስ በመባል የሚታወቀውንና የኢንላይተንሜትን እንቅስቃሴ ለተከታተለ ሊረዳ ይችላል። በአውሮፓው የህብረተሰብ አገነባብ ታሪክ ውስጥ በማንኛውም ጊዜ ዕውቀት የሚባለው ነገር ሳይብላላ ዝም ብሎ ተግባራዊ የሆነበት ጊዜ በፍጹም አልነበረም። የተሃድሶ አብዮት ከተካሄደ ከ14ኛው ክፍለ-ዘመን በኋላም፣ በተለይም ካፒታሊዝም እያደገ ሲመጣ በተለያዩ ምሁራን ዘንድ ከመንግስት ጀምሮ እስከ ህገ-መንግስት ድረስ፣ ከኢኮኖሚ ቲዎሪና እስከ ትክክለኛው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ድረስ፣ የኋላ ኋላ ደግሞ ካፒታሊዝም እያደገ ሲመጣና  በአንድ አገር ውስጥ የህብረተሰብ አሰላለፍ እየተሰበጣጠረና በመደብ እየተካለለ መምጣት ከጀመረበት ከ19ኛው ክፍለ-ዘመን ጊዜ ጅምሮ በኢኮኖሚና በሶስዮሎጂ፣ የኋላ ኋላ ደግሞ በስነ-ልቦና ሳይንስ ላይ የጦፈ ክርክር ተካሄዷል። በተለይም በኢኮኖሚና በሶስዮሎጂ ዙሪያ የተደረገው ክርክር የሚያመረቃና፣ እስከ 19ኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ ይታመንበት የነበረውን የእነ አዳም ስሚዝን ቲዎሪ በአዲስ መልክ እንዲታይ የተደረገበትን ሁኔታ እንመለከታለን። በተለይም ማርክስና ኤንገልስ ያፈለቁት የኢኮኖሚና የሶስዮሎጂ ቲዎሪዎች የሚያረጋግጡት ሁኔታዎችን ትችታዊ በሆነ መልክ(Critical Thought) የሚመለከቱ አንዳንድ የተገለጸላቸው ምህራን ከኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ መሆን ጋር በየአገሮቻቸው ውስጥ የሚከሰቱ የሀብት ክፍፍልና፣ ከዚያ ጋር ተየያይዞ የሚፈጠረውን የማህበራዊና የስነ-ልቦና ቀውስ ዝም ብለው እንደማያዩና ጉዳዩን በጥልቀት በመመርመር አዳዲስ የኢኮኖሚና የሶስዮሎጂ ዕውቀቶችን ማዳበር እንደሚችሉ ነው። ስለሆነም በአውሮፓ የህብረተሰብና የኢኮኖሚ ዕድገት ታሪክ ውስጥ አንድ ዐይነት ቲዎሪና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ብቻ ሳይሆኑ ተግባራዊ የሆኑት በየጊዜው እንደ ኃይል አሰላለፍ ለውጥ የተለያዩ ፖሊሲዎች ተግባራዊ ለመሆን ችለዋል። ከትልቁ የኢኮኖሚ ቀውስ ከ1930 ዓ.ም በኋላ እንደ አሜሪካ የመሳሰሉት አገሮች በኬይንስ የፈለቀውን፣ የመንግስትን በኢኮኖሚ ውስጥ ጣልቃ-መግባትን አስፈላጊነት የሚያትተውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው ከሞላ ጎደል ተግባራዊ ያደረጉት። ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላም አብዛኛዎቹ የካፒታሊስት አገሮች በመንግስት የተደገፈ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረጋቸው ነው ኢኮኖሚያቸውን ማዳበር የቻሉትና ሳይንስና ቴክኖሎጂም በከፍተኛ ደረጃ ማደግ የቻሉት።  ከዚህ ዐይነቱ የምሁራዊ ዕድገትና ክርክር ስንነሳና ልዩ ልዩ ቲዎሪዎችንና ፖሊሲዎችን በምንመረምርበት ጊዜ ከአውሮፓ የመጣው የአስኳላ ትምህርትና የዘመናዊነት ፖሊሲ ነው እንደዚህ ዐይነቱ መቀመቅ ውስጥ ሊከተን የቻለው የሚለው አባባል በጣም አሳሳች ነው። ስህተቱና የታሪክ ወንጀሉ የእኛ ዝም ብሎ መቀበልና፣ ለመመርመርና ለማወዳደር በፍጹም አለመቻል ነው። ይህንን አስተያየት ትተን ወደ ሌላ፣ በተለይም ስልጣኔን ወይም ዘመናዊነትን በሚመለከት አንዳንድ መሰረተ-ሃሳቦችን ደግሞ እንመልከት።

በአጠቃላይ የስልጣኔን ታሪክ ስንመለከት እያንዳንዱ አገር ከሌላው አገር ጋር ግኑኝነት ሳያደርግ ወይም ዕውቀትን ሳይዋስ በፍጹም ያደገበት ዘመን የለም። ለምሳሌ አውሮፓውያን የሚኮሩበትን የግሪኩን ስልጣኔ ታሪክ ስንመለከት መነሻው ግብጽ ነበር። በተጨማሪም ከህንድና ከሱሜሪያ ወይም ባቢሎን የመጡት ዕውቀቶች ለግሪኩ ስልጣኔ መሰረት እንደጣሉ በበቂው በማስረጃ መልክ በተደገፈ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። ታላቁ አሌክሳንደር ግብጽን ከመውረሩና ስልጣኔውን ከማስፋፋቱ በፊት የግሪክ ታላላቅ ፈላስፋዎች፣ ፒታጎራስ፣ ፕላቶና ሶሎን በመባል የሚታወቀው መሪና ፈላስፋ ግብጽ አገር የፍልስፍናንና የአስትሮኖሚ ትምህርታቸውን በግብጽ ፈራዖኖችና ቀሳውስቶች አማካይነት እንደሰለጠኑ ግልጽ ነው። ይህንን በሚመለከት አንታይ ዲዮፕ የሚባለው የሴኔጋሉ የፊዚክስ፣ የአስትሮኖሚና የፍልስፍና አዋቂ ግብጽ ድረስ ዘልቆ በመሄድ ለማረጋገጥ ችሏል። አፍሪካም የአውሮፓው ስልጣኔ መሰረት እንደሆነችና፣ ፕላቶም ሆነ ሶክራተስ ብዙ ነገሮችን ቃል በቃል ከግብጽ ቀሳውስት እንደወሰዱና እንዳስፋፉት „አፍሪካ የአውሮፓው ስልጣኔ እናት“ (Africa the Mother of European Civilization) በሚለው መጽሀፉ በሚያሳምን መልክ ለማረጋገጥ ችሏል። ይህንን የሱን ታላቅ ስራ እስካሁን ድረስ በጥያቄ ውስጥ ያስቀመጠ ወይም ትክክል አይደለም ብሎ የተከራከረ የለም። የግብጽ ስልጣኔም የጥቁር አፍሪካውያን ስልጣኔና፣ የመጀመሪያዎቹ የግብጽ ፈራዖኖችም ከኢትዮጵያ እንደሄዱ ዴዎዶሮስ ክሮኖስ በመባል የሚታወቀው የሲሲሊያን ተወላጅና ከክርስቶስ ልደት በፊት በ91 ዓ.ም የተወለደው  የታሪክ ተመራማሪ ለማረጋገጥ ችሏል። ማርቲን በርናል የሚባለውም የታሪክ ተመራማሪም እንደዚሁ ጥቁር አቴና(Black Athena) ተብሎ በሚጠራው ግሩም መጽሀፉ ግሪክ የግብፅ ቅኝ-ግዛት እንደነበረችና፣ ግሪኮችም ብዙ ዕውቀቶችንና አምልኮዎችን ከግብፅ እንደወረሱ በምርምሩ ለማረጋገጥ ችሏል። በሌላ አነጋገር፣ የግሪክ ፍልስፍና፣ ሳይንስ፣ ማቲማቲክስ፣ የህንጻ አሰራር ቴክኒክና ሌሎች ሁለ-ገብ ዕውቀቶች በሙሉ ከተለያዩ አካባቢዎች በመምጣት በግሪክ ፈላስፋዎች ከሁኔታው ጋር በመቀናጀት ተጨምቀው የወጡና የዳበሩ ናቸው። ይህ ዐይነቱ ተጨምቆ የወጣና የዳበረ ዕውቀት ወደ ስምንት መቶ ዓመታት ያህል ከተዳፈነ በኋላ በ14ኛው ክፍለ-ዘመን በአረቦች አማካይነት ወደ አውሮፓ በመምጣት ለጣሊያኑ የተሃድሶ እንቅስቃሴ መሰረት ሊጥል ችሏል።

ያም ሆነ ይህ የግሪክ ስልጣኔንና የኋላ-ኋላ ደግሞ ሬናሳንስ በመባል የሚታወቀውን በጣሊያን ምድር ተግባራዊ የሆነውን ሁለ-ገብ ዕድገት ስንመለከት የሁለቱም መነሻ ወይም ዋናው መሰረት የንቃተ-ህሊና መዳበርና አዕምሮ ከተሳሳተ ወይም በክስተት ላይ ከተመሰረተ ዕውቀትና አምልኮአዊ አስተሳሰብ መላቀቅ በመቻሉ ነው። የተፈጥሮንና የኮስሞስን ህግ በመመርመርና በማጥናት በዚህ አማካይነት በምድር ላይ አነሰም በዛም ሰላም የሰፈነበትና አገዛዞችንም ሆነ ህዝብን ከኋላ-ቀር አስተሳሰብ በማላቀቅና የዕውቀት ባለቤት በማድረግ የሰውን ልጅ ኑሮ የሚያቃልል ቴክኖሎጂዎች መስራትና፣ የሰውም ልጅ ሊኖር የሚችልበትን ጥበባዊ ከተማዎችንና መንደሮችን መገንባት ነው። በሌላ አነጋገር፣ የግሪኩ ስልጣኔ የዳበረው የሰውን ልጅ፣ በተለይም በጦርነት መንፈስ የተያዙትንና ጦርነትን የሚጭሩትን የገዢ መደቦች ከአውሬ ባህርያቸው በማላቀቅ በአርቆ-አሳቢ መነፅር ታሪክን መስራት እንዲችሉና፣ የሚኖሩበትን አካባቢ ወደ ገነትነት እንዲለውጡ ለማድረግ ነው። ይህ ዐይነቱ የጭንቅላት እንቅስቃሴና ተግባራዊም የሆነው ሁለ-ገብ ዕድገት የመጀመሪያው የሰብአዊ እንቅስቃሴ(Humanism) በመባል ይታወቃል። በመሆኑም በፍልስፍና ላይ የተመሰረተው ዕውቀት የግሪክ ፈላስፋዎች ቢያዳብሩትና ቢያስፋፉትም ለግሪኮች ብቻ ተብሎ የተጻፈ እንዳልሆነ የፕላቶንንም ሆነ የአሪስቶተለስንና የሌሎችንም ፈላስፋዎችና ሳይንቲስቶች ስራዎች ላነበበ በደንብ ሊገነዘበው ይችላል። በሌላ አነጋገር፣ ዕውቀቱ ለሰው ልጅ ሁሉ የሚሆንና፣ እስካሁንም ድረስ ጊዚያዊነቱን ያጣ አይደለም። በሚገርም መልክ የሰው ልጅ በዚህች ምድር ላይ እስካለ ድረስ ሊጠቀምበት ይችላል ተብሎ የተጻፈ ይመስላል።

በጥያቄ መልክ የተቀመጠውን አርዕስት ጠጋ ብለን ስንመለከት በግሪክ ምድር በፍልስፍና ላይ የተመሰረተው ፖለቲካ የሚባለውና ለሰለጠነ አስተሳሰብ መሰረት የጣለው ፍልስፍና ዋናው መነሻ በጊዜው ከነበረው አስቸጋሪ ሁኔታ፣ የጦርነትና የውድመት፣ በሽታዎችና ድህነት መላቀቅ የሚቻለው በንቃተ-ህሊና ላይ የተመሰረተ የሰውን ልጅ መውደድ ወይም አገርን መውደድ ከሚለው ጥላ አስተሳሰብ ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው።  በግሪክ አገር ወይም ምድር ስልጣኔ ወይም ዘመናዊነት ከሰው ልጅ ዕድገትና የጭንቅላት ነፃነት መጎናፀፍ ውጭ ሊታሰብ በፍጹም አይችልም ነበር። አገርም እንደ አገር ሊጠራ የሚችለው የሰለጠነና ፍትሃዊነት ያለው መንግስት ሲቋቋምና ህዝቡም በስራ-ክፍፍል አማካይነት ሲያያዝና የተሟላ ነፃነት ሲኖረው ብቻ ነው። የፖለቲካ መሰረቱም ፍልስፍና ሲሆን፣ ከፍልስፍና ውጭ የሚካሄድ ፖለቲካ እንደ ፖለቲካ ሊጠራ በፍጹም አይችልም። በሌላ አነጋገር፣ በአንድ አገር ውስጥ ያለ አገዛዝ ወይም መንግስት በአገር ውስጥ የሚያካሂደው ፖለቲካ መሰረቱ ፍልስፍና መሆን አለበት። ፕላቶ እንደሚያስተምረን አንድ አገር አይ በፈላስፋዎች መመራት አለበት፣ አሊያም ደግሞ አገዛዞች በፈላስፋዎች መመከርና ቁጥጥርም እንዲደረግባቸው ያስፈልጋል ይላል። ምክንያቱም ፖለቲካ ከፍልስፍና ተነጥሎ በሚታይበትና መሪዎች ጭንቅላታቸው በሰብአዊነት መንፈስ ባልተቀረፀበት አገር የፈለጉትን ነገር በማድረግ አንድ ህዝብ በሰላም እንዳይኖርና የሰለጠነ ስራ እንዳይሰራ ስለሚያደርጉ ነው። ፍልስፍናዊ መሰረት የሌለው ፖለቲካ ደግሞ ለዘራፊዎችና ለጦርነት አፍላቂዎች አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል። ይህም የሚያመለክተው የግሪክ ፈላሳፋዎች ዘራፊ የሆነን አገዛዝና ጦርነትን አፍላቂ መንግስት እንደሚቃወሙ ነው። አልፈውም በመሄድ የአንድ አገር አገዛዝና መንግስት በኃይላቸው በመመካት ሌላውን ደከም ብሎ የሚገኝን አገር ወይም ጎረቤት መውረር እንደሌለባቸው ያስተምራሉ። ፍልስፍናንና ጥበብን በመዘንጋት በመባለግ ላይ የተመሰረተና ሌሎች አገሮችን በመውረር ታሪካቸውን ድምጥማጡን የሚያጠፋ ኃይል ኢምፔሪያሊስታዊ ወይም ወራሪ ኃይል ብለው ይጠሩታል። በሌላ አነጋገር፣ የግሪኮች የአገር ወዳድነት ስሜት ከስልጣኔ ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ መንግስታቸውም በኃይሉ የሚመካና ወራሪ መሆን እንደሌለበት በሚገባ ያስተምራሉ። ከዚህ ስንነሳ የእነሱ የአገር ወዳድነት ስሜት ከጠቅላላው የሰው ልጅ  ስልጣኔ ተነጥሎ የሚታይ አይደለም። 

ከዚህ አጭር ገለጻ ስንነሳ የአገር ወዳድነት ስሜት ከፍልስፋናና ከጥበብ፣ እንዲሁም በከፍተኛ ደረጃ ከንቃተ-ህሊና መዳበር ውጭ በፍጹም ሊታሰብ አይችልም። በግሪከ ፈላሳፋዎች በተለይም በፕላቶን ዕምነት በአንድ አገር ውስጥ እንደ ሰንሰለት የተያያዘ የውጣ ውረድ አገዛዝ መኖር ያለበት ቢሆንም፣ የግዴታ ግን ስልጣንን የሚቆጣጠረው ኃይል ህዝቡን ፍትሃዊነት ባለው መልክ ማስተዳደር መቻል አለበት። ፍትሃዊነት በሌለበት አገር ውስጥ ደግሞ ማህበራዊና ባህላዊ ቀውሶች ይፈጠራሉ። በሌላ ወገን ደግሞ ከውጭ የሚመጣንና በጉልበቱ የሚመካን ኃይል እጅህን ወደ ላይ አድርገህ ስጥ የሚል አስተሳሰብ አልነበራቸውም። ለማንኛውም የአገር ወዳድነት ስሜት በፍልስፍና ላይ ሲመሰረት የመጨረሻ መጨረሻ እያንዳንዱ ግለሰብ ነፃና የመፍጠር ኃይልም እንዳለው የሚያስተምር ነው። በሌላ አነጋገር፣ እያንዳንዱ ግለሰብ ከተተበተበበት ባህላዊ ወይም ኋላ-ቀር አስተሳሰቦች ከተላቀቀ የማሰብ ኃይሉ ይዳብራል፤ መፍጠርም ይችላል፤ እንደሰውም ይኖራል፤ ሰው መሆኑንም ስለሚገነዘብ ሌላውን እሱን የሚመስለውን አያጠቃም። እያንዳንዱን ግለሰብም የሚያገናኘውና የሚያስተሳስረው በህብረተሰቡ ውስጥ በሚያደርገው ተሳትፎና አስተዋፅዖ እንጂ የዚህ ሃይማኖት ተከታይ ወይም ከዚያኛው ጎሳ በመምጣቱ አይደለም። በተለይም ፕላቶ የጎሳ ወገናዊነትን ወይም ሶሊዳሪትን አጥብቆ ይቃወማል።

ነገሩን መስመር ለማሲያዝ፣ በተለይም በመሀከላችን ያለውን አለመግባባት መልክ ለመስጠት የአገር ወዳድነት ስሜት ከሁለ-ገብ ዕውቀት ውጭ በፍጹም ሊታይ አይችልም። ይህ ማለት ግን እያንዳንዱ ግለሰብ ሁሉንም ነገር አጠቃሎ ያውቃል ማለት አይደለም። ለማለት የሚፈለገው ለአገርና ለህዝብ ዕድገት የትኛው ዕውቀት ነው አስፈላጊውና ሃቀኛውን መንገድ ሊያሲዝ የሚችለው የሚለውን ለማስገንዘብ ብቻ ነው። ስለሆነም ስለ አገር ወዳድነት ስሜት መኖር በምናውራበት ጊዜ አየሩን፣ የምድሩን አቀማመጥና ወንዙንና ተራራውን ብቻ ሳይሆን፣ በተለይም በአንድ አገር ውስጥ የሚኖርን ህዝብ መውደድና ለጠቅላላው ህዝብ ጠበቃ መቆምን የሚመለከት ነው። ሳይታክቱም ለፍትሃዊነትና ለሰላም መታገል ነው። አንድ ህዝብ ከድህነትና ከለማኝነት ሊወጣ የሚችልበትን መንገድ ማሳየትና እራሱን እንዲችል ማድረግ ነው። በዚህም መሰረት ከውጭ የሚመጣን አሳሳችና ጥገኛ የሚያደርግን ዕውቀት መሰል ነገር ካለርህራሄ መዋጋት ነው። ምሁራዊ ኃይልን በማዳበር በሁሉም አቅጣጫ ምርምር በማድረግ ወጣቱን በማስተማር ተከታታይነት የሚኖረው ማህበረሰብና አገር እንዲመሰረት ያልተቋረጠ ትግል ማድረግ ነው። ስለሆነም የአገር ወዳድነት ስሜት የፖለቲካ ፍትሃዊነትን  እንዲኖር መታገል፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ዕድገት በጠንካራ መሰረት ላይ እንዲገነባ ማድረግ፣ በተቻለ መጠን በህዝቡ መሀከል ሊኖር የሚችለው የሀብትና የገቢ ክፍፍል መረኑን እንዳይለቅ፣ በአካባቢ ላይ የሚደርስን ግፍ መታገል፣ የሰው ልጅ ተፈጥሮን የሚፈልግ እንደመሆኑ መጠን ዕድገት የሚባለው ነገር የተፈጥሮን ሚዛን እንዳያናጋ መታገል፣ የሚሰሩት ህንጻዎችና ከተማዎች ሰዎች የሚኖሩባቸው የሚሆኑ፣ አገር መባለጊያ ሳይሆን ጤናማ እሴቶችና ባህል የሚዳብሩበት፣ በዚህ ዐይነት ህብረተሰብ ውስጥ ልዩ ልዩ ሃይማኖቶች ተቻችለው ሊኖሩ የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር ማለት ነው። ሃይማኖትም ሲባል የሰውን ልጅ በጭፍን ተከታይ የሚያደርገው ሳይሆን በተቻለ መጠን ፍልስፍናዊ አስተሳሰብና ሃይማኖት አንድ ላይ ሊዳብሩ የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው። በቄስ አውጊስቲኑስና በቄስ ቶማስ አኪና ዕምነትና ምርምር መሰረት በሃይማኖትና እነ ፕላቶ ባዳበሩት ፍልስፍና መሀከል ምንም ዐይነት ልዩነት የለም። ያለው ልዩነት ሃይማኖት በዕምነት ላይ የተመሰረተ ሲሆን፣ ፍልስፍና ግን ምርምርን፣ ጥያቄንና  ከዚህ በመነሳት አርቆ-አሳቢነትን(Rational Thinking) የሚያስቀድም ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በመጀመሪያው ጽሁፌ ላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት የዘመናዊነትንም ሆነ የዕውቀትን ግንዛቤ በሚመለከት በፍልስፍና ዓለም ውስጥ ሁለት ዐይነት አመለካከቶች እንዳሉና፣ ባለፉት ሁለት መቶ ዓመታት፣ በተለይም ባለፉት 70 ዓመታት ትክክልኛ ዕውቀትን ሳይሆን የተሳሳተን፣ እኩልነትን ሳይሆን ኢ-ፍትሃዊነትን የሚያስፋፋ ዕውቀት መሰል ነገር በዓለም አቀፍ ደረጃ በመስፋፋቱ አገዛዞች መረናቸውን እንዲለቁ ተደርገዋል። የያዙትን የጦር መሳሪያንና ሌሎች የጭቆና መሳሪያዎችን ተገን በማድረግ ከ90% በላይ የሚሆን በየአገሩ የሚኖርን ህዝብ የሚያዋክቡና መሪ ነን የሚሉ ግለሰቦች እንደልዩ ፍጡር የሚመለኩበትና የሚፈሩበት ሁኔታ ሊፈጠር ችሏል። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ተፍጥሮአዊ ተደርጎ በመወሰዱ ለጦርነትና ለመሰደድ ዋናው ምክንያት ሊሆን በቅቷል። በዚህም የተነሳ በየአንዳንዱ አገርና በአገራችንም ምድር ለሰው ልጅ የሚያመችና እያንዳንዱ ግለሰብ አገሩን እንዲወድ የሚያስችል ሁኔታ እንዳይፈጠር ለማድረግ ተችሏል።

ይህንን ትተን አብዛኛዎቻችን ኢትዮጵያ ውስጥ ብንወለድምና አገራችንንም እንወዳለን ብለን ብንምልና ብንገዘትም ሁላችንም ተመሳሳይ የሆነ የአገር ወዳድነት ስሜት ሊኖረን በፍጹም አይችልም። የተወለድንበት አካባቢና የቤተሰብ ሁኔታ፣ የሄድንበት ትምህርት ቤትና በትምህርት ዓለም ውስጥ የቀሰምነው ትምህርት፣ በስራ ዓለምም ከተሰማራን በኋላ የምንሰራበት አካባቢና ያሉን ጓደኞችና፣ እራሱ ኩባንያው ወይም መስሪያ ቤቱና ሌሎችም ነገሮች ለአገር ወዳድነት ስሜት መዳበርና አለመዳበር የራሳቸውን ተፅዕኖ ያሳድራሉ። ከዚህም ባሻገር በፖለቲካና በምሁራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፈንም ሆነ ያልተሳተፍን ከሆነ እነዚህ ሁለት ነገሮች በራሳቸው ለአገር ወዳድነት ስሜት መኖርና አለመኖር አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ። በተለይም ለአገር ወዳድነት ስሜትና ለሰፊው ህዝብ ጠበቃ መሆን አንድ ሰው ከወጣትነት ጊዜው ጀምሮ በፖለቲካና በምሁራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ያደረገው ተሳትፎ ወሳኝ ሚናን ይጫወታሉ። በሌላ አነጋገር፣ ከወጣትነት ጊዜው ጀምሮ በፖለቲካና በምሁራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፎ ያላደረገ የአገር ወዳድነት ስሜቱ በንቃተ-ህሊና ላይ የተመሰረተ ሳይሆን በስሜት ላይ ነው ማለት ነው። ከዚህ ስንነሳና በአውሮፓ ውስጥ የፍልስፍናና የሳይንስን ዕድገት፣ ከዚያም በኋላ የኢኮኖሚንና የማህበራዊ ጥያቄዎችን በማንሳት የፖለቲካ ስልጣንን የጨበጡ ኃይሎችንና ህዝቡም እንዲረዳው የተደረገውን መሻሻል ስንመለከት መሰረታዊ ለውጥ ሊመጣ የቻለው ከልጅነታቸው ጀምረው በጥሩ ዕውቀት በተኮተኮቱና የሰብአዊነትን አርማ አንግበው ለነፃነትና ለፍትሃዊነት በታገሉ ከ90% በላይ ከአሪስቶክራሲው መደብ በፈለቁ በተገለጸላቸው ምሁራኖች አማካይነት ነው። አብዛኛዎቹ ምሁራኖች የፈለቁበትን የወግ አጥባቂ መደብ አመለካከት በመጣል ነው ጭንቅላታቸውን በማንቀሳቀስ ለሁላችንም መሰረት የሆኑ ዕውቀቶችን ማፍለቅና ማዳበር የቻሉት። ለምሳሌ የፍሪድሪሽ ኢንገልስን የህይወት ታሪክ በምንመለከትበት ጊዜ አባቱ የጨርቃ ጨርቅና የጥጥ መፍተያ ፋብሪካዎች ባለቤት ሲሆን፣ በጊዜው ቩፐርታል የሚባል አንድ የጀርመን ከተማና ማንቼስተር ወደ ሶስት ሺህ ሰራተኞችን ቀጥሮ ያሰራ የነበረና በጣም ሀብታም የነበረ ሰው ነው። ከልጅነት ዕድሜው ጀምሮ በሰብአዊነት የሰለጠነው ፍሪድሪሽ ኢንግልስ በእሱና ፋብሪካው ውስጥ በልጅነታቸው ተቀጥረው ይሰሩ የነበሩ የለጋ ወጣት ልጆችን ሁኔታ በደንብ ይመለከታል። ቀስ በቀስም ሁኔታውን በመከታተልና በማጥናት ለመጀመሪያ ጊዜ ከአባቱ ጋር ግጭት ውስጥ ይገባል። ትችታዊ መጽሀፎችን በማንበብና በመከታተል ከአባቱ የተለየ አስተሳሰብን ያዳብራል። ወደ ሌላ ቦታም በመሄድና ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በመግባት በፍልስፍናም ሆነ በልዩ ልዩ ዕውቀቶች ጭንቅላቱን ያዳብርል። ከማርክስ ጋር በፈጠረውም ግኑኝነት የወዝ አደሩ ሁኔታ በእንግሊዝ አገር (The Condition of the Working Class in England)  የሚለውን የመጀመሪያውን ትችታዊ የሶስዮሎጂ መጽሀፍ ይጽፋል። የዕውቀት ጓደኛው ማርክስም ከሞተ በኋላ ዳሳ ካፒታልን በማጠናቀርና በማስተካከል እንዲታተም በማድረግ ለአንባቢያን ያቀረበ ታላቅ ምሁር ነው። 

ከዚህ ስንነሳ ሙሉ ጊዜያቸውንና ዕድሜያቸውን ለምርምርና ለጥናት ማዋል በቻሉ ምሁራን አማካይነት ነው የሳይንስንና የቴክኖሎጂን ዕድገት መቀዳጀት የተቻለው።  ወደ እኛ አገር ስንመጣ ግን ይህ ጉዳይ የተለመደ አይደለም። አንድ ወይም ሁለት ግለሰቦች ካልሆኑ በስተቀር ከላይኛው መደብ የፈለቀ በከፍተኛ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የተሳተፈ የለም። በተማሪው እንቅስቃሴ ጊዜ የተደረገውን ተሳትፎ ከምሁራዊ አንፃር መገመት በጣም አስቸጋሪ ነው።  ለማንኛውም የመደብ ጉዳይ የሚሉት ነገር በራሱ ለአገር ወዳድነት ስሜት መዳበርና አለመዳበር የራሱን ሚና ይጫወታል። በተለይም ከላይኛው የህብረተሰብ ክፍል ከወጣንና በጥሩ ዕውቀት ጭንቅላታችን እስካልተኮተኮተ ድረስ የአገር-ወዳድነት ስሜትና በጠቅላላው ህብረተሰብአዊ ዕድገትን በሚመለከት ያለን ንቃተ-ህሊና ዝቅ ሊል ይችላል። ይህ ዐይነቱ የአገር ወዳድነት ስሜት በዘመነ ኢምፔሪያሊዝም የእኛን አገር ብቻ ሳይሆን በተለይም የላቲንና የማዕከለኛውን አሜሪካ አገሮችና የሌሎችንም የአፍሪካ አገሮች የሚፈታተንና አገሮቻቸውንና ባህላቸውን በማፈራረስ ሰፊው ህዝብ በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲኖር የተደረገበትን ሁኔታ እንመለከታለን። ከላይኛው የህብረተሰብ ክፍል የሚወለዱ ለትምህርት በቀጥታ ወደ አሜሪካ የኤሊት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንዲሰለጥኑ ስለሚላኩ ትምህርታቸውን ጨርሰው በሚመጡበት ጊዜ የአገሮቻቸውንና የህዝቦቻቸውን ጥቅም የሚያስጠብቁ ሳይሆኑ የአሜሪካንና የተቀረውን የካፒታሊስት አገሮችን ጥቅም ነው የሚያስጠብቁት። ለሀብት ክምችት መዳበርና ለሰፊው ህዝብ የስራ-መስክ ሊከፍት የማይችል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ በአንድ በኩል ድህነትና የአመጸኝነት ተግባር እንዲስፋፉ ሲያደርጉ፣ በሌላ ወገን ደግሞ አገራቸው በዕዳ እንዲተበተብ በማድረግ ሀብት ወደ ውጭ እንዲሸሽ ያደርጋሉ። የአገራቸውም የጥሬ-ሀብት እንዲዘረፍ ሁሉንም ነገር ያመቻቻሉ። ከውጭ አገር ትላልቅ ኩባንያዎች ጋር የጥቅም ትስስር በማድረግ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ የአካባቢና የባህላዊ ቀውስ እንዲፈጠር ያደርጋሉ። ይህ ሁኔታ በአገራችንም በግልጽ የሚታይ ነው።

ስለሆነም ስለ አገር ወዳድነት ስሜት በምናወራበት ጊዜ አገር ወዳድነት በምን መልክ ሊገለጽ ይችላል? ብለን በምንመረምርበት ጊዜ ፅንሰ-ሃሳቡን ከብዙ አቅጣጫ መመለክት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። በተለይም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተጋለጥን(Exposed) ከሆነና የዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ለብዙ ዓመታት የሰራን ከሆነ ከአገራችን ጋር የማይጣጣም የአኗኗር ስልትና በሳይንስና በቴክኖሎጂ እንዲሁም በስራ-ክፍፍል ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ዕድገት ተግባራዊ እንዳይሆኑ እናደርጋለን። ለምሳሌ የካፒታሊስት አገሮችንም ሆነ ኋላ ላይ የተነሱትን እንደ ጃፓንና ቻይና፣ እንዲሁም የሌሎችንም አገሮች የኢኮኖሚና የህብረተሰብ ዕድገት ሁኔታ ስንመለከት በተለይም ጃፓንና አሁን ደግሞ ቻይና በኢኮኖሚ ለማደገና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመከበር የበቁት በተለይም ስልጣንን የጨበጡ ኃይሎች በምንም ዐይነት ለውጭ ኃይል የተጋለጡ ባለመሆናቸውና የመንግስት መኪናቸውንና የስለላ መዋቅሩን ለውጭ ኃይሎች ለሚሰልሉ ክፍት ባለማድረጋቸው ነው። በሚገርም ሁኔታ ከቻይናና ከኮሪያ የሚመጡ ተማሪዎችም ሆነ ሌሎች ቅድሚያ የሚሰጡት ለአገራቸው ዕድገት ብቻ ነው። መብለጥንና መሻሻልን የሚፈልጉ እንጂ የሚታለሉና የአገራቸውን ጥቅም አሳልፈው የሚሰጡ አይደሉም። ስለሆነም ከውጭ የመጣውን ዕውቀት ውስጥ ካለው ጋር በማቀናጀት ለዕድገት እንዲያመች በማድረግ ዛሬ እንደምናየው ሰፋ ያለና የዳበረ ኢኮኖሚ ለመገንባት ችለዋል።  ከዚህ ስንነሳ በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ለብዙ ዓመታት የሰሩ ባዳበሩት በተለይም የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ አመለካከት የአገር ወዳድነት ስሜታቸው የላላና የዕድገትን ጉዳይ በሚመለከት የተቆነፀለ አስተሳሰብ ነው ያላቸው ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። ምክንያቱም ቀላል ነው። ጭንቅላት በአንድ የተወሰነ ዕውቀት መሰል ነገርና የአሰራር ቴክኒክ ከሰለጠነ እነዚህ ነገሮች ጭንቅላት ውስጥ ይቀረፃሉ(programmed)። ከዚህ የአስተሳሰብና የአሰራር ቴክኒክ ውጭ የሚመጡ አስተሳሰቦች በሙሉ እንደ እንግዳ ነገር መታየት ይጀምራሉ። በዚህም ምክንያት የተነሳ ነው አብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገሮችና አገራችንም ጭምር ሰፋ ያለ የተለያየ ምሁራዊ ዕውቀት ባልተስፋፋባቸው አገሮች ከአንድ ቀውስ ወደ ሌላ በመግባት በኤክስፐርትነት ስም እዚህና እዚያ በሚሯሯጡና መንግስታትን በሚያማክሩ ተዋንያን የሚዳክሩት። ለምሳሌ የጋና ፕሬዚደንት ጆን ኩፉርና የላይቤሪያው ፕሬዚደንት ወይዘሮ ኤለን ጆንን ጉዳይ ስንመለከት  ሁለቱም የዓለም ባንክ ከፍተኛ ባለስልጣናት ነበሩ። ፔሪዚደንቶች ሆነው ሁለቱም ስምንትና አስራሁለት ዓመታት ቢያስተዳድሩም በአገራቸው ምድር ሁለ-ገብ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ አገሮቻቸውን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት ለማድረግ አልቻሉም፤ ህዝቦቻቸውንም ከድህነት ማላቀቅ አልቻሉም። ተግባራዊ ባደረጉት የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት የቀድሞው ሁኔታ እንዲጠናከር በማድረግ ሁለቱም አገሮች ከካካኦ ምርትና ለጎማ ከሚሆን ወተት ከሚያፈልቅ የዛፍ ተከላ መላቀቅ አልቻሉም። 

ባጭሩ አንድን አገር በአገር ወዳድነት ስሜት ለመገንባትና የጠነከረና የሚከበር ማህበረሰብ ለመገንባት ከተፈለገ እነዚህን ነገሮች በሙሉ መመርመር ያስፈልጋል። የመጨረሻ መጨረሻ ተከታታይነት የሚኖረው ማህበረሰብ መገንባት አለብን የምንል ከሆነ ሰፊውን ህዝብ የመንፈስ ጥንካሬ እንዲኖረው የሚያደርግ ዕውቀት እንዲገበይ ማድረግ አለብን። አንድ ህዝብ ማንነቱን ሲያውቅና ከብዙ አቅጣጫዎች መመልከት ሲችል ብቻ ነው በቀላሉ በውጭ ኃይሎች ሊታለል የማይችለው። በአገራችንና በተቀሩት የአፍሪካ አገሮች ያለው ትልቁ ችግር ይህ ነው። ስለዚህ ሰፊውን ህዝብ ማስተማርና ማንቃት፣ በተከታታይ ዕውቀቱን ሊያደስባቸው የሚችልባቸው ሁለ-ገብ ትምህርትና የሙያ ስልጠና የሚሰጥባቸው ተቋማት በየቦታው መዘርጋት እንዳለባቸው መታገሉ የአገር ወዳድነት ስሜት መለኪያ ነው።  

በመሆኑም አገሬን እወዳለሁ ብለን በምናወራበት ጊዜ የግዴታ የፅንሰ-ሃሳቡን ምንነት በሚገባ መመርመር ያስፈልጋል። በተለይም ኢንፎርሜሽን በተንዛዛበትና ዕውነቱን ከሃሰት ለመለየት በሚያስቸግርበትና፣ ብልጭልጭ ነገሮች የሰውን አዕምሮ በቀላሉ በሚያሳስቱበት ዘመን የነገሮችን ምንነት ለመለያየትና ለመመርመር የሚያስችል ዕውቀት እስከሌለን ድረስ በቀላሉ ልንታለል እንችላለን። በቀላሉም አገር አፍራሽና ህዝብን በታታኝ ነገሮችን ተግባራዊ በማድረግ ታሪክንና ባህልን ለማውደም እንችላለን። ከዚህ ስንነሳ እነፕላቶ ደጋግመው የሚያነሱት ሀቀኛውን ከተሳሳተው ዕውቀት የመለየቱ ጉዳይ የነገሩንም ምንነት ለመረዳትና በቀላሉ ላለመታለል ይረዳናል። እነፕላቶ ብቻ ሳይሆኑ ካንትና ሄገልም እንደዚሁ ስለ ዕውቀት ምንነትና እንዴትስ እንደሚደርስበት በሰፊውና በሚያመረቃ መንገድ ተንትነዋል። ይህም ማለት አንድን ነገር በቅጡ መመልከት፣ የተመለከቱትን በሚገባ መረዳትና በአርቆ-ማየት መነጽር መመርመር፣ እነዚህ ሶስት የጭንቅላት ክንዋኔዎች ሲጣመሩ ብቻ ትክክለኛውን ዕውቀት የሚያስጨብጡ መሆናቸውን ያስተምሩናል። በተጨማሪም አንድ ነገር ብቻውን ተነጥሎ የሚታይ ሳይሆን፣ አንዱ በሌላው ላይ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችልና፣ አንድ ነገር እንዳለ ሊቆይ እንደማይችል ወይም ሊለወጥ እንደማይችል አድርጎ መቀበል እንደሌለብን ያስተምሩናል። ለምሳሌ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የተማርናቸው እንደኢኮኖሚክስ የመሳሰሉ ትምህርቶች ኢኮኖሚክስን ከፖለቲካና ከሶስዮሎጂ ነጥለን እንድናይ ነው የተደረገው። ሴቴረስ ፓሪቡስ(Ceteris Paribus) የሚሉት አነጋገር አለ። ይህም ማለት ሌሎች ነገሮች ሁሉ እንዳሉ ወይም ሳይለወጡ በአንድ ነገር ላይ ብቻ የሚካሄድ ለውጥ አጠቃላይ ለውጥን ያመጣል ብለው ያስተምራሉ። በሌላ አነጋገር የፖለቲካና ሌሎች የተቋማት ለውጥ እንዲሁም የመንፈስ ተሃድሶ ሳይደረግ በኢኮኖሚ ፖሊሲ ላይ የሚካሄድ ለውጥ አጠቃላይ ለውጥን ሊያመጣ ይችላል። ይህ ዐይነቱ ዕምነት በዓለም አቀፍ ተቋማት እንደ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ደርጅትና የዓለም ባንክ በመሳስሉትና፣ እንዲሁም በተለያዩ የዕርዳታ ሰጭ ድርጅቶች የሚሰበክ አስተሳሰብ ነው። ፖሊሲውም ፖዘቲቭ ሳይንስ በመባል ሲታወቅ፣ አንድ ሁኔታ እንዴት መለወጥ ወይም መምሰል እንዳለበት የሚነግረን ሳይሆን ያለውን ሁኔታ በገበያ ኢኮኖሚ መነጽር ብቻ በመመልከት ለመተንተን የሚሞክር ነው። ይሁንና ከላይ እንዳልኩት ፖሊሲው በአንድ አገር ውስጥ ለዕድገትና ለህብረተሰብአዊ ለውጥ መሰናክል የሆኑ ፖለቲካዊ፣ መንግስታዊ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ግኑኝነቶችንና የተለመዱ የአሰራር ቴክኒኮችን ለመመርመር የሚቃጣና ሰፋ ያለ ሀተታ ለመስጠት የሚችል አይደለም። ስለሆነም ስለህብረተሰብ በምናወራበት ወይም በምናትትበት ጊዜ ነገሮች በሙሉ የተያያዙና አንደኛው በሌላኛው ላይ የራሱን ተፅዕኖ ማድረግ እንደሚችል መገንዘብ በጣም አስፈላጊ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ማንኛውም ዕውቀት በተግባር የሚታይና የሚጨበጥ፣ እንዲሁም ለአንድ አገር ህዝብ ጠቃሚ መሆኑና አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። 

በአገራችን ምሁሮች መሀከል ያለው ትልቁ ችግር!

ሳላውቀው በፖለቲካ ዓለም ውስጥ ስተት ብዬ ከገባሁ ሰላሳ ዓመታት በሚያስቆጥር ዘመን ውስጥ በእኛ ምሁራን ዘንድ የአገራችንን ዕድገት በሚመለከት የመረቃ ክርክርና ጥናት አልተካሄደም ብል የምሳሳት አይመስለኝም። በአንዳንድ ምሁራን ዘንድ አንዳንድ መሰረተ-ሃሳቦች ቢነሱም፣ ለምሳሌ በክቡር የክብር ዶክተር ከበደ ሚካኤል „ጃፓን እንዴት ሰለጠነች“ የሚለውንና፣ በደጃዝማች ተክለሃዋርያት የተጻፈውን እንደ አርአያ ከመሳሰሉት መጽሀፎች በስተቀር በእነዚህ ላይ በመመርኮዝ ሰፋ ያለ ጥናት በማድረግ መሰረተ-ሃሳቡን ሊያሰፋፋ የሞከረ ምሁር እስካሁን ድረስ በፍጹም አላየሁም። ይህንና የአገራችንንም የህብረተሰብ አወቃቀርና ዕድገት በሚመለከት የሚያመረቃና አንድ ዐይነት ለዕድገት የሚያመች ሃሳብ ለመዳበር ባለመቻሉ ሁላችንንም ሊያገናኘን የሚችል የአስተሳሰብ አንድነት(Unity of Thought) ማዳበር አልቻልንም። በተለይም ደግሞ የአንድን ህብረተሰብ አካሄድና አንድ ህብረተሰብ በምን ዐይነት መልክ መቀረጽ አለበት በሚሉት መሰረተ-ሃሳቦች ላይ ጥናትና ክርክር እስካልተካሄደ ድረስ የተወሰነውን የምሁር ኃይል ሊያግባባና ያንን መሰረት በማድረግ ወደፊት ለመጓዝ የሚችል ህብረተሰብአዊ ዕቅድ ማውጣት አይቻልም። ይህ ዐይነት ሁኔታ በሌለበት አገር ደግሞ ጠቅላላውን ህዝብ የሚያስጨብጥና እንደመመሪያ ሊሆነው የሚያስችል መሰረተ-ሃሳብ ማስፋፋት አይቻልም። ስለሆነም አገዛዙም ሆነ ህዝቡ በዘፈቀደ የሚኖሩ እንጂ ዓላማ ያላቸውና በስነ-ምግባር በመመራት ለተከታታዩ ትውልድ የሚሆን መሰረት ለመጣል የማይቻልበት ሁኔታ ይፈጠራል ማለት ነው። በተለይም ደግሞ የህዝብ ቁጥር እየበዛና በዚያው መጠንም ፍላጎቶች ሲጨምሩ ነገሮች መፍትሄ ከማግኘት ይልቅ እየተወሳሰቡ በመምጣት በተለይም ደግሞ መንግስታዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች ይፈጠራሉ። ስለዚህም በአንድ አገር ውስጥ የሚፈጠሩና እየተስፋፉ የሚሄዱ አጠቃላይ ቀውሶች አገዛዙ በየጊዜው ብቃትነት ባለው ሁኔታ ስለማይዋቀርና፣ ከዚህም ባሻገር ሰፋ ያለና ከሁሉም አቅጣጫ መመርመር የሚችል ምሁራዊ ኃይል ለመፈጠር በማይችልበት ወይንም ደግሞ ተደጋጋሚና አሰልቺ በሆኑ የአሰራር ቴክኒኮች መጠቀም እንደ ባህል በሚወሰድበት አገር ውስጥ በግልጽ የሚታዩ ችግሮችንና ምክንያቶቻቸውን ለመመርመርና መፍትሄም ለመፈለግም ሆነ ለማቅረብ በጣም አስቸጋሪ ይሆናል።

ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት በተለይም በአውሮፓ ምድር ውስጥ መሰረታዊ ለውጥ ሊመጣ የቻለው ስልጣንን በጨበጡ ኃይሎች አማካይነት ሳይሆን ሁሉም ዕውቀቶች ከፖለቲካ ስልጣን ውጭ የዳበሩ ናቸው። ይሁንና ግን በጊዜው የነበሩ የፍጹም ሞናርኪዎች አገዛዞች ሳያውቁት የኋላ ኋላ የእነሱን ስልጣን የሚቀናቀንና ለሁለ-ገብ ዕውቀት የሚያመቹ ዩኒቨርሲቲዎችን በመክፈት ለምርምር አመቺ ሁኔታን ይፈጥራሉ። በትላልቅ ዩኒቭርሲቲዎች ውስጥ የተማሩት ታላላቅ ፈላስፋዎች ምርምራቸውን ጥልቀት በመስጠት ከፍልስፍና አልፈው ጠቅላላውን አንድን ህዝብና አገር በሚመለከቱ ነገሮች ላይ ሰፋ ያለ ምርምር ያደርጋሉ። ቀስ በቀስም አያሌ ደቀ-መዝሙሮችን በማፍራት በመንግስት ላይ ግፊት በማድረግ ጥገናዊ ለውጦች እንዲደረጉ ይወተውታሉ። ከዚህ ባሻገር በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች መሀከል ይደረግ የነበረው ውድድር አንዳንድ ሞናርኪዎችን ጭንቅላታቸውን እንዲከፍቱ ስላስገደዳቸው ወደ ውስጥ ያተኮረ የኢኮኖሚና የህብረተሰብ ግንባታ ክንውን ያካሂዳሉ። ይህ ዐይነቱ መሰረታዊ ለውጥ ሰፋ ያለና በተለያዩ አቅጣጫዎች ለሚመለከትና በኢንዱስትሪ ተከላ ላይ ለሚሰማራ የከበርቴ መደብ አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል። የኢኮኖሚ መስኩም እየሰፋ ሲመጣ የተገለጸለት መደብ የተሻለ የፖለቲካና ቢሮክራሲያዊ አወቃቀር መኖር እንዳለበት ግፊት ማድረግ ይጀምራል። በዚህ መልክ ህብረተሰቡ ከባህላዊ አመለካከት በመላቀቅ እራሱን የሚችል ህብረተሰብአዊ ኃይል እየሆነ ይመጣል።

ወደእኛ አገር ስንመጣ በምሁሮቻችን ዘንድ ያለው አመለካከት በጣም የጠበበና ለዕድገት በማያመቹ ነገሮች ላይ መረባረብ ነው። ሌላው ደግሞ በፖለቲካ ውስጥ በመሳተፍ ፖለቲካን ከሌሎች ነገሮች ነጥሎ በማየት ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ እንዳይዳብር በሩን ሁሉ ይዘጋል። ቡድናዊ ስሜትም በማዳበር አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳ ያደርጋል። ከሚቀድመኝ ይልቅ ልቅደመው በማለት ተንኮል በመሸረብ አይ ስም ያጠፋል፣ አሊያም ደግሞ በአንዳች ዐይነት ዘዴ ህይወቱ እንዲጠፋ ያደርጋል። ይህ ዐይነቱ ሂደት የግዴታ ለአክራሪነትና ድርጅትን ወደ ርዕዮተ-ዓለምነት በመለወጥ የአንድን አገር ዕድል ከአንድ ድርጅት ጋር ብቻ ማያያዝ ይጀመራል። ማምለክ የተጀመረበትን ድርጅት የተቃወመ ወይም የተሻለ አስተሳሰብ የሰነዘረ እንደጠላት በመታየት ማሳደድ ይጀመራል። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ የተማሪው እንቅስቃሴና አብዮቱ በዚህ ዐይነቱ ጠባብ አስተሳሰብና ምሁራዊ ብስለት አለመኖር ነው ሊሰናከሉና በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ወጣቶች ህይወታቸውን እንዲሰዉ ለመደረግ የበቃው። 99% የሚሆነው ይኸኛውን ወይም ያኛውን ድርጅት ይደግፍ ወይም ይከተል የነበረው ወጣት ህይወቱን የሰዋው በማያውቀው ነገርና ድርጅቶቹን በማምለኩ ብቻ  ነበር።

ያለፈው አልፏል፤ ያለፈውን ሰላሳና አርባ ዐመታት በፖለቲካ ዙሪያ የተደረገውን ትግል ስንመለከት ምሁራዊና ሳይንሳዊ ብስለት የጎደለው ነበር ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። ምሁራዊ ብስለት የጎደለው ትግል ደግሞ ውጤቱ ምን እንደሆነ ለማየት በቅተናል። ምክንያቱም በሳይንስና በፍልፍስፍና የተኮተኮተና የዳበረ ጭንቅላት በምንም ዐይነት አረመኔያዊ ስለማይሆን ነው። ለተወሰነ ዓላማ  እታገላለሁ፣ ህዝቤን ከድህነት ማላቀቅ አለብኝ ብሎ የሚነሳ ድርጅት ሌላውን ተመሳሳይ ዓላማ ያለውን ድርጅትም ሆነ እንቅስቃሴ  የትግሉ አጋር በማድረግ  ምኞቱ እንዲሳካ ያደርጋል እንጂ ተቀናቃኜ ነው በማለት ሊያጠፋው አይቃጣም። ባለፊት 27 ዓመታት ደግሞ  ከየት ብቅ እንደሚሉ አይታወቁም አንዳንዶች በአንድ ጊዜ ይነሱና የአገርና የህዝብ ጠበቃ መሆን ይጀምራሉ። እነዚህም እንደድሮዎቹ የሚመለክባቸው ይሆናሉ። ብዙ ገንዘብም በመሰብሰብ አንዳንዶቹ የራሳቸውን ኑሮ ያደላድላሉ። ለምሳሌ የግንቦት ሰባት የሚባለውን እንቅስቃሴ ስንመለከት በምሁራዊና በሳይንስ፣ እንዲሁም ደግሞ በፍልስፍና ዙሪያ ምንም ዐይነት ጥናት ያላካሄደና ደቀ-መዝሙሮችን ለማፍራት ያልቻለ ነው። ለምሁራዊ ውይይትም ሆነ ክርክር ዝግጁ የሆነ ድርጅት አልነበረም። ዝም ብላችሁ በጭፍን ተከተሉኝ የሚል ፊዩዳላዊ ባህርይ የነበረው ድርጅት ነበር። እንደተከታተልነው ወያኔን በመጥላት ላይ ብቻ ያተኮረው ትግልና ቅስቀሳ ኃይልንና ሀብትን ያባከነ ለመሆን በቅቷል። ድርጅቱ በግልጽ ይህንን ርዕዮተ-ዓለም ነው የምከተለው ብሎ ሲያስተምርና ስልጣን ላይ ቢወጣ እንዴት አድርጎ የአገራችንን የተወሳሰበውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ቀውስ ሊፈታ እንደሚችል ያስተማረው ነገር አልነበረም። ድርጅት ብለን ከጠራነው የአንድ ወይም የሁለት ሰው ኩባንያ የሚመስል እንጂ የቀረ ቢቀር ምሁራዊ ጹሁፎች የሚወጡበት አንድ ድረ-ገጽ ያልነበረውና፣ በየጊዜውም የሚታተሙ መጽሄትም ሆነ ጋዜጣ የሌለው ድርጅት ነበር። ድርጅቱን የሚመሩት ግለሰቦች ንቃተ-ህሊናቸው ከፍ ያለ ቢሆን ኖሮ በብዛት በሰበሰቡት ገንዘብ አገር ቤት ውስጥ አዲስ ወጣት ትውልድ በፍልስፍና፣ በፖለቲካ፣ በስልጣኔ፣ በሳይንስና በሌሎች ለሁለ-ገብ ዕድገት በሚያመቹ ነገሮች የሚሰለጥንበት ተቋም መክፈት በቻሉ ነበር።  እኔ እስከማውቀው ድረስ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ነኝ የሚል በየሳምንቱ የሚታተም ጋዜጣና በየወሩ የሚወጣ መጽሄት ሊኖረው ይገባል። በተለይም በአውሮፓ ውስጥ ይደረግ ከነበረው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ይህንን ነበር የምንመለከተው። ይህንን ትተን ግንቦት ሰባትንም ሆነ ሌሎች በፖለቲካ ስም የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችን ሁኔታ ስንመረምር ርዕዮተ-ዓለማቸው ምን እንደሆነና ለምንስ ዐይነት ህብረተሰብ እንደሚታገሉ በፍጹም የሚታወቅ ነገር የለም። ቀኝ ይሁኑ ግራ፣ ኮሙኒስቶች ይሁኑ ፋሺሽቶች፣ ሊበራሎች ይሁኑ ኮንሰርቫቲቦች…ወዘተ. ምንም የሚታወቅ ነገር የለም። የሚደግፏቸውም ግለሰቦች በጭፍን የሚከተሏቸው እንጂ በሚጠየቁበት ጊዜ አጥጋቢ መልስ ለመስጠት የማይችሉና ፖለቲካ የሚባለውን ግዙፍ ፅንሰ-ሃሳብ በደንብ ያልተረዱ መሆናቸውን ነው መገንዘብ የሚቻለው። በአንዳንዶች ዕምነት የአገራችንና የህዝባችን ዕድል በአንድ ግለሰብ ትከሻ ላይ ሊወድቅ የሚችል ሲሆን፣ አንድ ግለሰብ በአንድ ጊዜ ሁሉንም ነገር ሊሰራና ሊሆንም እንደሚችል አድርገው ነው የሚገምቱት። የስራ-ክፍፍልና ተከታታይነት ያለው ድርጅታዊ እንቅስቃሴ ለአንድ አገር ዕድገትና ለፖለቲካ ባህል መዳበር አስፈላጊ መሆናቸውን በፍጹም የተረዱ አልነበሩም፤ አይደሉምም።

ነገሩን ለማሳጠር ከእንደዚህ ዐይነት እጅግ ወደ ኋላ ከቀረ ፊዩዳላዊ አስተሳሰብ መላቀቅና ጭንቅላትን ብሩህ በሚያደርግ ዕውቀት ማነፅ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ኢማኑኤል ካንት የሚባለው ታላቁ የጀርመን ፈላስፋ ለማሰብና የራስህን ግንዛቤ ለመስጠት ጭንቅላትህን ተጠቀም ወይም ድፈር(Sapere Aude) እንደሚለው መጠየቅንና መከራከን መድፈርና መልመድ ያስፈልጋል። አንዱ የሆነውን ያልሆነውን ሲናገር ማዳመጥና እንደበግ እየተንጋጉ መውጣት ለዲሞክራሲና ለኢኮኖሚ ዕድገት  የሚደረገውን ትግል ያደናቅፋል። የአንድ አገር ህዝብ በዝንተ-ዓለም በድህነት እንዲማቅቅ ያደርጋል። ማንኛውም ስለአገርና ህዝብ ጉዳይ የሚሰጥ ሀተታ ትችታዊ በሆነ መነፅር መመርመር አለበት። አንድ ሰው የሚናገረው ነገር ህዝብን ሊያሰባስብ የሚችል መሆኑና አለመሆኑን፣ በሳይንስና በቴኮኖሎጂ ላይ ለተመሰረተ ሁለ-ገብ የአገር ግንባታ ይጠቅም አይጠቅም እንደሆነ አነጋገሩን በሚገባ ማጥናት ያስፈልጋል። ይህ ሲሆን ብቻ ነው የአገር ወዳድነት ስሜትን መወጣት የሚቻለው። ከዚህ ውጭ የሚደረግ ትግልና አንድን ግለሰብ ማምለክ የመጨረሻ መጨረሻ የአገራችንን ሁኔታ ውስብስብ ያደርገዋል። ስለዚህም ምን ማድረግ እችላለሁ? ትክክለኛውንስ ዕውቀት እንዴት መገብየት እችላለሁ? የትግሉስ ዓላማ ምንድ ነው? እያሉ የግዴታ በየጊዜው ጥያቄዎችን ማንሳትና ማጥናት፣ እንዲሁም በጋራ መወያየት ተገቢ ነው። ኃይልን በሚጨርሱ ነገሮች ላይ ጊዜን አለማባከንና ኃይልን የግዴታ መሰብሰብ ለትግል ያመቻል። ለዚህ ደግሞ የግዴታ ጭንቅላትን ሰብሰብ የሚያደርጉ ዘመናዊ ቴክኒኮችን፣ እንደዮጋና ሜዲቴሽን(Meditation) የመሳሰሉትን በየቀኑ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህ ዐይነቱ የጭንቅላት ጂምናስቲክ በሁሉም አቅጣጫ እንድናስብ የሚረዳን ብቻ ሳይሆን ኃይላችንንም በማያስፈልጉ ነገሮች ላይ እንዳናውልና ከንትርክም እንድንቆጠብ ይረዳናል። ፈላስፋው ሶክረተስ እንደሚያስተምረን፣ አንድ ሰው ሰውነቱ ፈታ ፈታ እንዲል በየቀኑ ጂምናስቲክም መስራት እንዳለበት ሁሉ፣ እንደዚሁም ጭንቅላትም ጂምናስቲክ ያስፈልገዋል ይላል። ይህ ብቻ ሳይሆን በተለይም በፖለቲካ ውስጥ እሳተፋለሁ የሚልና የሚሳተፍም ግለሰብ በየጊዜው የስነ-ልቦና ወይም የህሊና ምርመራ ማድረግ አለበት። ይህንን በሚመለከት ስንቶቻችን በየሁለት ዓመቱ ወደ ሃኪም ቤት ለምርመራ እንደምንሄድ የሚታወቅ ነገር የለም። ብዙ ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት የችኮነት ባህርይ ያላቸው፣ የሚክዱ ወይም ደግሞ አንድ ሰው ሲገደል ምንም ዐይነት ርህራሄ የማያሳዩና፣ ከአረጀ የአሰራር ቴክኒክ አልላቀቅም ብለው ህብረተሰብአዊ ትርምስ እንዲፈጠር የሚያደርጉ…ወዘተ. … ወዘተ. እነዚህ ዐይነት ሰዎች የስነ-ልቦና ወይም የህሊና መረበሽ እንዳለባቸው ነው። አንድ ሰው ለድርድርና ለዕርቅ ዝግጁ ካልሆነ፣ በሃሳብ ዙሪያ ክርክር ለማድረግ ፈቃደኛ ካልሆነ፣ ከተለዋዋጭ ሁኔታዎች ጋር እራሱን የማያቀናጅ ከሆነ፣ ጭንቅላቱን ለአዳዲስ አስተሳሰቦች ክፍት ካላደረገ፣ ራሱን መጠየቅ ካልቻለ…ወዘተ. …ወዘተ.   እንደዚህ ዐይነት ሰው በተጨባጭ ሲታይ የስነ-ልቦና ችግር አለበት። ከሃምሳ ዓመታት በላይ የፈጀ ትርምስና መፈናቀል፣ እንዲሁም ደግሞ በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ወጣቶች መሞት፣ ይህ ሁሉ ነገር የደረሰው ካለምክንያት አይደለም። ስለዚህም በተለይም በፖለቲካ ዓለም ውስጥ እሳተፋለሁ የሚልና ለስልጣን የሚታገል ሰው ወይም ድርጅት በየጊዜው የስነ-ልቦና ወይም የህሊና ሃኪም ጋ መሄድ አለበት። ይህ ባለመሆኑ ነው በአብዛኛው የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩ አገሮችና በአገራችንም ጭምር እንደዚህ ዐይነት አረመኔያዊ ተግባር ሲፈጸምና ያን የመሰለ ቆንጆ አገር ድምጥማጡ ሲጠፋ በዚያው የሚገፋበት።

ከአጠቃላዩ ሁኔታ ስንነሳ የአገር ወዳድነት ስሜት የሚለካው በእድሜ መግፋትና አለመግፋት ሳይሆን በጠራ ርዕይና ፍልስፍና አማካይነት ብቻ ነው። አንድ ሰው በእድሜ ገፋም አልገፋም አንድን ሃሳብ የሙጥኝ ብሎ ከያዘና ለሌላ ሃሳብ ክፍት እስካልሆነ ድረስና የተሻለ ሃሳብም ለመቀበል ዝግጁ ካልሆነ በእድሜ ገፋም አልገፋም እንደዚህ ዐይነቱ ግለሰብ አገር ወዳድነት ምን እንደሆነና፣ አንድስ አገር በምን መልክ እንደማህበረሰብ ሊደራጅ እንደሚችል የገባው አይደለም ማለት ነው። ስለሆነም እንደዚህ ዐይነቱን ሃሳብ ስሰነዝር በግምት ሳይሆን ከተመለከትኩትና ከሚጻፉት ነገሮች በመነሳት ብቻ ነው ለመጻፍ የተገደድኩት። በሌላ ወገን ደግሞ አንድ የማይካድ ነገር አለ። እድሜያችን እየገፋ በሄደ ቁጥር አዳዲስ ነገሮችን የመቀበል ፍላጎታችንና አቅማችንም እየደከመ ይመጣል። አንዳንድ በፍስልፍናና በሳይንስ የተዋቀረ ጭንቅላት ያላቸውና ዕድሜያቸውን በሙሉ ለፖለቲካ ለውጥ የሚታገሉ ሰዎች እስካልሆኑ ድረስ አልፎ አልፎ ስለፖለቲካ የምንጽፍ ሰዎች እድሜያችን እየገፋ በሄደ ቁጥር የመሰላቸትና በየጊዜው የሚለዋወጡ ሁኔታዎችንም የመረዳቱ ኃይላችን ቀስ በቀስ እየተሟጠጠ መምጣቱ የማይቀር ጉዳይ ነው። በተለይም አሁን ባለንበት በተንዛዛ የኢንፎርሜሽንና የቴክኖሎጂ ዘመን በየሰዓቱ የሚወረወሩትን ኢንፎርሜሽኖች በሙሉ ጭንቅላት ውስጥ በማስገባት ለማብላላት አቅምም ሆነ ኃይል ላይኖረን ይችላል። ስለሆነም ነገሩን በዚህ መልክ ብቻ መረዳቱ ከአለመግባባት ሊያድነን ይችላል።

    ለመሆኑ በዛሬው ወቅት በአገራችን ምድር  ያለው አገዛዝ አገር ወዳድ ወይስ የአገር ጠላት?

አንድ ስልጣንን የጨበጠ ኃይል፣ አገዛዝ ወይም መንግስት  ነው የሚያሰኘው አንድ የሚመራበት የፖለቲካ ፍልስፍና ሲኖረው ብቻ ነው። ትክክለኛ የሆነ የፖለቲካ ፍልስፍና ደግሞ በተግባር ዚመነዘር፣ ፖለቲካዊ ፍትሃዊነትን፣ የኢኮኖሚ ፍትሃዊነትን፣ የማህበራዊ ፍትሃዊነትን የሚያመጣ በመሆን የሚገለጽ ነው። ከዚህም በላይ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱትን መመሪያዎች ተግባራዊ ለማድረግ በህብረተሰብ ውስጥ ያሉት ቅራኔዎች እንዲቀንሱ የተቻለውን ሁሉ ነገር ማድረግ መቻል አለበት። ለራሱ ስልጣን ሲልም  የከፋፍለህ ግዛው ፖለቲካ በመከተል ጥርጣሬን መፍጠር የለበትም። ስለሆነም አንድ አገዛዝ የጠራ የፖለቲካ ፍልስፍና ካለው ቅድሚያ የሚሰጠው ወደ ውስጥ ሰላምን ማስፈንና ማንኛውም ዜጋ ትንሽ ሆነ ትልቅ ሳይፈራና ሳይተባ ሊንቀሳቀስበትና ሊኖርበት የሚችልበትን ሁኔታ መፍጠር ነው። አንድ አገዛዝም የበሰለና የሰለጠነ ነው የሚያሰኘው በተለይም በጎሳና በሃይማኖት ተሳበው የሚፈጠሩ ቅራኔዎች ገደባቸውን እንዳይለቁ በአፋጣኝ ፖለቲካዊ እርምጃዎችን በመውሰድ መረጋጋትን መፍጠር ከቻለ ነው። በዚህ መንፈስ የሚካሄድ ፖለቲካ በህዝብ ዘንድ መረጋጋትን በመፍጠር ለስራና ለፈጠራ ያለውን ፍላጎት ከፍ ያደርግለታል። በሌላ ወገን ግን በአገራቻንም ሆነ በተቀሩት የአፍሪካ አገሮች ስልጣንን በጨበጡና ለመጨበጥ በሚታገሉ ኃይሎች ተግባራዊ የሚሆነውን ፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ስንመረመር ያሉትን ቅራኔዎችና የኢኮኖሚ ቀውስ የሚያሰፉና ችግሩንም ውስብስብ የሚያደርጉ ናቸው። ሁኔታዉን በጥብቅ ለመመረመረ ሰው እነዚህ ዐይነት አገዛዞች ፖለቲካ የሚባለውን ግዙፍ ጽንሰ-ሃሳብ የሚገነዘቡ አይደሉም። በአንድ አገር ውስጥም እንዴት ህብረተሰብአዊ ሀብት እንደሚፈጠርና ድህነትም እንደሚወገድ የሚያውቁት ነገር የለም። ልዩ ልዩ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች እንዳሉና፣ የትኛውስ ለሁለ-ገብ ዕድገት እንደሚያመች የሚረዱ አይደሉም። ብቻ በዓለም አቀፍ ተቋማትና በአማካሪ ኩባንያዎች በመመከር የባሰውን ድህነት እንዲፈለፈልና የፖለቲካና የማህበራዊ ቀውስም እንዲከሰት ያደርጋሉ።

ወደ እኛ አገርም ስንመጣ በዶ/ር አቢይ አህመድ የሚመራው አገዛዝ የሶስት ዓመት ያህል ዕድሜ ቢያስቆጥርም ከፖለቲካ እስከ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ቀውስ ድረስ በግልጽ የሚታዩና ህዝብን ከፍተኛ ችግር ውስጥ የከተቱን ነገሮች ለመፍታት ያልቻለ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ የፖለቲካውን ሁኔታ እንመልከት። ህውሃት ወይም ወያኔ የሚባለው በውጭ ኃይሎች የሚደገፈውና የእነሱን ጥቅም ሲያስጠብቅ የነበረው የማፊያ አገዛዝ ከስልጣን ላይ ከተወገደ በኋላ ህዝባችን ይጠብቅ የነበረው ሰላምንና መረጋጋትን ነበር፤ ከዚህም በላይ ማንነቱን የሚገልጽበትንና እንደየሙያው ማህበር ወይም ድርጅት በመመስረት በጋርዮሽ መብቱን የሚያስጠብቅበትን ሁኔታ መፍጠር ነበር። ይህ ከመሆኑ ይልቅ የህውሃትን ቦታ የያዙትና አጉል ትረካ የሚያወሩት የዘንድሮው ባለተረኞች ተራው ደግሞ የእኛ ነው በማለት ማካሄድ የጀመሩት ፖለቲካ አገርን ማተራመስ ነው። በተለይም በአማራው ብሄረሰብና በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች ላይ የሚደርሰው ጥቃት የዛሬዎቹ ፖለቲከኞቻቸን የሚያረጋግጡት ፖለቲካ የሚባለው ግዙፍ ፅንሰ-ሃሳብ እንዳልገባቸው ነው። በዚህ መልክ የሚካሄደው ፍስልፍና ወይም ሳይንሰ-አልባ ፖለቲካ ባለፉት ሶስት ዓመታት ለብዙ ሺሆች እህቶቻችንና ወንድሞቻችን መገደልና መፈናቀል ምክንያት ሆኗል። በግልጽ እንደሚታየው ይህ ዐይነቱ ግድያና ህዝብን ማፈናቀል ሆን ተብሎ የሚሰራና የመጨረሻ መጨረሻ ሁሉንም ዜጋ መቀመቅ ውስጥ በመክተት ኢትዮጵያ የምትባል አገር እንደ አገርና እንደማህበረሰብ እንዳትኖር ለማድረግ የሚችል ነው። በሌላ አነጋገር፣ በእንደዚህ ዐይነቱ እጅና እግር የሌለው ፖለቲካ እራሱ የኦሮሞ ብሄረሰብ የሚባለውንም ተጠቃሚ የሚያደርገው ሳይሆን የሚጎዳውና ወደ ባርነት የሚለውጠው ነው። እንደዚህ ዐይነቱ አንድን ብሄረሰብ ብቻ እጠቅማለሁ ብሎ ተግባራዊ የሚሆን ፖለቲካ ለማህበራዊና ለኢኮኖሚ፣ እንዲሁም ለባህል ዕድገት ከፍተኛ እንቅፋት ይሆናል። አንድ ህዝብ ሲቀላቀልና ሲዋሃድ፣ እንዲሁም ደግሞ በአንዳች ዐይነት ፍልስፍና ሲመራ ብቻ ነው ጠቅላላውን ህዝብ የሚጠቅም ዕድገት ሊመጣ የሚችለው። የዛሬዎቹ ፖለቲከኞቻችን ወያኔ ከተከተለው የግድያና የዝርፊያ ፖለቲካ በቂ ትምህርት የቀሰሙ አይመስልም። ዝርፊያና ግድያ የመጨረሻ መጨረሻ እንደሚያስጠይቅ የተገነዘቡ አይመስልም። አንድ ሰው ወይም ድርጅት በዝርፊያና በግድያ ሳይሆን የመንፈስ ደስታን መጎናጸፍ የሚችለው በታታሪነትና በፈጠራ ስራ ብቻ መሆኑን የገባቸው አይመስልም።

ይህ አንደኛው ሲሆን፣  አጠቃላዩን የፖለቲካ ፍልስፍና ትተን ፖለቲካውን በርዕዮተ-ዓለም መነጽር በምንመረምበት ጊዜ የዶ/ር አቢይም ሆነ የአገዛዙ የፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለም ግራ ይሁን ቀኝ፣ ኮሙኒስት ይሁን ፋሺስት ወይም ሌላ ዐይነት ርዕዮተ-ዓለም ይኑረው አይኑረው በግልጽ አይታወቅም።  ምንም ዐይነት ርዕዮተ-ዓለም ሳይጨብጥና እንደዕምነት ሳያራምድ በደፈናው ፖለቲካ እያለ በጭፍኑ የሚጓዝ ኃይል ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ በመሰለው የፖለቲካ ርዕይ በደንብ ባልተብላላበት አገር አደገኛ ሁኔታን ሊፈጥር ይችላል። በተለይም አንድ ግለሰብ በሚመለክበትና ዕውነተኛ ግለሰባዊ ነፃነት ባልዳበረበት አገር ምንም ዐይነት የፖለቲካ ዕውቀት ሳይኖራቸው ዶክተሩን የሚያመልኩና በጭፍን የሚነዱ ግለሰቦች ወደ ግብግብ ሊያመሩ ይችላሉ።  ግልጽነት የሌለበትና ዕውቀት ያልተሰፋፋበት ሁኔታ ደግሞ ለአክራሪዎችና ለፋሺስቶች መድረክ በመክፈት ዲሞክራሲያዊና ተራማጅ አስተሳሰብ ያላቸው ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች ክትትል ሊደረግባቸው ይችላል።    

ከዚህ ስንነሳ ዘመናዊ የሚመስሉትና ወጣቱ መሪያችን ዶ/ር አቢይ አህመድ የሚያካሂዱት ፖለቲካ ይበልጥ ሽወዳ የተሞላበትና ጠቅላላውን ህብረተሰብ የሚያተራምስና የውጭ ኃይሎችን ለወረራ የሚጋብዝ ነው። እንደሚታወቀው አንድ አገር እራሷን ከውጭ ወረራና ጥቃት ለመከላከል እንድትችል ጠቅላላው ህዝብ ኃይሉን መሰብሰብ አለበት። አንደኛው ጎሳ ወይም ሃይማኖት በሌላው ላይ መነሳት የለበትም። ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የአንድ አገር ዜጋ ሆነው በመተያየት አገራቸውን መገንባትና ከውጭ የሚመጣባቸውን ጠላትም በጋራ ለመከላከል የሚችሉ መሆን አለባቸው። የዚህን መሰረታዊ ጉዳይ አስፈላጊነት ስንመረምር ዶ/ር አቢይ የሚከተሉት ፖለቲካ ከውስጥ መፍረካከስን የሚያስከትል እንጂ ጥንካሬን የሚያመጣ አይደለም። በጥብቅ እንደምንከታተለው አገራችን ከሩቅም ሆነ ከጎረቤት አገሮች ጠላቶች አሏት። ሱዳን፣ ግብጽና ሶማሊያ ስትራቴጂያዊ ጠላቶቻችን ናቸው። ባለፉት ሃምሳ ዓመታት አገራችን ስትጠቃ የነበረው እነዚህ አገሮች የውስጥ ጠላቶቻችንን በማስታጠቅና እዚያው እንዲኖሩ በማድረግ ነው። ምንም ዐይነት ብሄራዊ ዓላማ ሳይኖራቸው ስልጣን ላይ ለመውጣት ብቻ ይታገሉ የነበሩ የተለያዩ የኢትዮጵያዊነትን ስም ያነገቡ ድርጅቶችና የብሄረሰብ ነፃ አውጭ ድርጅቶች በሱዳንና በግብጽ የሚደገፉ ነበሩ። ዛሬም አገራችን በጭንቀት ውስጥ ያለቸው ግብጽና ሱዳን በሚያደርጉት ያልተቀደሰ ትብብርና አገራችን በዘለዓለማዊ ትርምስ ውስጥ ወድቃ ህዝባችን ኃይሉን በማስተባበር ኢኮኖሚያዊና ህብረተሰብአዊ ግንባታ እንዳያደርግ ነው። በተለይም ከአንዳንድ የአገራችን ባለስልጣናት የሚሰማው፣ የሱዳን ህዝብና መሪዎቹ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ማድረግ አይፈልጉም የሚለው አባባል እጅግ አደገኛ የሆነና አላዋቂነትን የሚያረጋግጥ ነው። በእርግጥ የሱዳን ህዝብ ጦርነትን አይፈልግም። በታሪክ ውስጥ በማንኛውም አገር አንድ ህዝብ በራሱ ተነሳስቶ ጦርነትን ያካሄደበት ወቅት የለም። ጦርነት ሁልጊዜ የሚካሄደው በጉልበታቸው በሚመኩና ስግብግብነትን ከስልጣን ጋር ባዋሃዱ አገዛዞች ወይም መንግስታት አማካይነት ብቻ ነው። እንደሚታወቀው ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ሱዳንንም ሆነ ግብጽን የሚገዙ ገዢዎች በአስተሳሰባቸው ኋላ የቀሩና ህዝቦቻቸውን ረግጠው የሚገዙ ናቸው። እነዚህ አገዛዞች ንጹህ በንጹህ በሚሊታሪ ኃይል የሚያምኑና የራሳቸውን ዲሞክራሲያዊና ተራማጅ ኃይሎችን የሚያሳድዱና ወደ እስርቤት የሚከቱ ናቸው። ስለሆነም ሱዳንም ሆነ ግብጽ የዘለዓለም ራስ ምታቶቻችን ናቸው። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ ወደ ውስጥ መካሄድ ያለበት ፖለቲካ ህዝባችን በፍርሃት እንዲዋጥ የሚያደርግና መጤ ጎሳ እየተባለ ማንነቱ የሚገፈፍበት መሆን የለበትም። በዚህ ዐይነቱ ፖለቲካም ብሄራዊ-ነፃነታችንን በፍጹም ማስከበር አይቻልም። አንድ አገር ብሄራዊ-ነፃነቷን ልታስከብር የምትችለው ጠቅላላው ህዝብ እንደ አንድ ዜጋ ሲታይና ስልጣንን የጨበጡም ኃይሎች የህዝቡ አገልጋይ መሆናቸውን አምነው ሲቀበሉ ብቻ ነው። ማንኛውንም ከውጭ የሚመጣ ጥቃትም ሆነ ተንኮል ጠንቅቀው የሚጠባበቁና ህዝቡን የሚያስተምሩና የሚያነቁ፣ እንዲሁም በግልጽም የሚናገሩ መሆን አለባቸው። የውጭ ጠላቶችን ስልታቸውን ለመከታተል የሚያስችሉና ምርምር የሚደርጉባቸው በመንግስት የተደገፉ የዓለም ፖለቲካንና ግኑኝነትን ሁኔታ ለማጥናትና ለመመራመር የሚያስችሉ ሳይንሳዊ ተቋማት መገንባት አለባቸው። 

በተለይም ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ያለ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያለው አገር፣ በጣም ለም መሬትና ቆንጆ ህዝብና የሚያማምሩ ባህሎች ያለበት አገር የሚፈልገው ቆንጆ ፖለቲካን ነው። ባጭሩ መንፈስን የሚያረጋጋና ለፈጠራና ለውስጣዊ ጥንካሬ የሚያመች ፖለቲካ ነው መካሄድ ያለበት። በሌላ ወገን ደግሞ ችግሩ ከአገዛዙ ያልተፈጠረ በማስመሰል ውድ ወጣቱ ጠቅላይ ሚኒስተራችን አንዳንድ ቦታዎችን ሲጎበኙ የሚነግሩን „እኛ ኢትዮጵያውያኖች ኃይላችንን ብንሰበስብና ባንሻኮት ይህንን የታመቀ ሀብታችንን ልንጠቀምበት እንችላለን“ እያሉን ነው። እዚያው በዚያው ደግሞ በተለይም በቤኔሻጉልና በኦሮምያ ክልል በአማራው ወገናችን ላይ እጅግ የሚሰቀንን ግፍ ሲደርስ ምንም ነገር እንዳልተደረገ ሲስቁና ሲዝናኑ፣ እንዲያም ሲል „ለጥሩ ስራቸው“  ሽልማት ሲሰጣቸውና፣ እሳቸውም ተዝናንተው ሲቀበሉ እናያለን። ከዚህም ባሻገር አንዳንድ የኦሮምያ ቦታዎች በመሄድ ኦሮሞዎችን ብቻ ሰብስበው በኦሮምኛ ንግግር ሲያደርጉ እዚያ የሚናገሩት መደመር ከሚለው መጽሀፋቸው ጋር የሚቃረንና፣ የኦሮሞን ብሄረሰብ ልዩ እንደሆነና፣ ብቻውንም ግዛት እንደነበረውና ከውጭ የመጣበትን ጠላት ሁሉ ተከላክሎ እንደመለሰ ነው የሚነግሯቸው። ለማንኛውም እንደጀርመን በመሳሰሉ ዲሞክራሲያዊ የሆኑና በህግ የበላይነት በሚተዳደሩ አገሮች ቢሆን ኖሮ እንኳን እንደዚህ ዐይነት ወንጀል ተሰርቶ አንድ ፖለቲከኛ ኃላፊነቱን በሚገባ የማይወጣ ከሆነና ጉቦ ከበላና ከተነቃበት አንድ ቀን ስልጣን ላይ የመቆየት ዕድል የለውም። ወደ እኛ አገር ስንመጣ ግን አንድ ፖለቲከኛ ነኝ ባይ ሰው በገደለ ወይም ባስገደለ፣ ወይም ደግሞ ሰው ሲገደል ዝም ብሎ የሚያይ ከሆነ፣ አሊያም ደግሞ አንዱን ጋዜጠኝ በመታ ቁጥር እንዲያውም ይባስ ብሎ ሹመት ይሰጠዋል። 

ያም ሆነ ይህ እንደዚህ ዐይነት ሙጎሳና ሽልማት የሚያረጋግጠው እራሳቸው ሽልማት ሰጭዎችም የቱን ያህል ጭንቅላታቸው እንደደነዘዘና በምድር ላይ ያለውን ነገር ማየት እንደማይችሉ ነው። ይህ ዐይነቱ በጭንቅላቱ የቆመ አመለካከት በአንዳንድ ምሁራንም ሲንፀባረቅ ይታያል። ሰሞኑኑ በአንድ በታወቁ የአገራችን ፈላስፋና እንደዚሁም ደግሞ በአንድ በታወቁ የስነ-ጽሁፍ አስተማሪና ተመራማሪ  የዶ/ር አቢይን የመደመር መጽሀፍ ሰባተኛውን ዕትም አስመልክቶ ለታዳሚዎች ቀርበው የሰጡት ገለጻ እጅግ አሳፋሪና አሳዛኝም ነው። መጽሀፉን ያስተዋወቁት ፈላስፋው እንደሚነግሩን ከሆነ የዶ/ር አቢይ የመደመር መጽሀፍ ከሄገል፣ ፊኖሚኖሎጂ ኦፍ ዘ ስፒሪት ከሚለው መጽሀፍ ጋር የሚመሳሰል ሲሆን፣ የዶ/ር አቢይም ጥረት ልክ እንደ ሄገል  ፍጹማዊ ዕውቀትንና ሀቀኝነትን መፈለግ ነው ይሉናል። የስነ-ጽሁፉ ተመራማሪና መጽሀፉን የተቹት ምሁር ደግሞ፣ መጽሀፉን ሲያነቡ ያገኙት የአገርን መሪ ሳይሆን ደራሲን ነው የሚሉን። የእነዚህ ምሁራን ገለጻ በፍጹም ተጨባጩን የአገራችንን ሁኔታና ራሳቸው ዶ/ር አቢይም የሚከተሉትን ፖለቲካ የሚያንፃብርቅ አይደለም። እንደዚህ ዐይነት የኑሮ ውድነት ባለበት፣ ህዝብ በግፍ በሚገደልበትና በሚፈናቀልበት ሁኔታ ውስጥ በመደመር ስም የተጻፈን መጽሀፍ ማስተዋወቅ ህዝብንና አገርን እንደመናቅ ይቆጠራል። በተጨማሪም ይህ ዐይነቱ ገለጻቸው የሚያረጋግጠው ሁለቱም ምሁራን የፖለቲካ ብስለት የሌላቸውና፣ ንቃተ-ህሊናቸውም በጣም ዝቅ ያለ መሆኑን ነው።  በተለይም አንድ የፍልስፍና ምሁር በፍልስፍና መነፅር ከፖለቲካ አንስቶ እስከ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ነገሮች ድረስና ለጦርነትም ምክንያቶች የሆኑትን ነገሮችን በሙሉ የመመልከት ኃይል ይኖረዋል። እዚህ ያለሁበት አገርና አሜሪካ በታወቁ ፈላስፋዎች፣ የሶስዮሎጂና የኢኮኖሚ ምሁራን፣ እንዲሁም በአንዳንድ ሁለ-ገብ ዕውቀት ባላቸው ምሁራን የሚጻፉ መጽሀፎችን ሳነብ አንድን ህብረተሰብና የዓለምን የፖለቲካ ሁኔታ የመመልከት ኃይላቸው የቱን ያህል ከፍ ያለ እንደሆነ ነው። አመለካከታቸውና ወገናዊነታቸው አገራዊ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊም እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። ይሁንና የፍልስፍናና የስነ-ጽሁፍ ተመራማሪዎቻችን ባለፉት ሶስት ዓመታት በዶ/ር አቢይ የአገዛዝ ዘመን በአገራችን ምድር ምንም ግፍ ያልተፈጸመና የማይፈጸም ይመስል መጽሀፉን ማስተዋወቃቸውና በዚህ መልክ ጠቅላይ ሚኒስተሩን መካባቸው የሚያስተዛዝባቸው ነው። መጽሀፉም የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ፣ ከፖለቲካ አንስቶ እሰከ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ቀውስ ድረስ፣ እንደዚሁም ሌሎች የህብረተሰብአዊና ባህላዊ ውድቀትን አስመልክቶ ምክንያቶችን የሚዘረዝርና መፍትሄዎችንም የሚጠቁም መጽሀፍ ሳይሆን የደራሲውን የህይወት ታሪክ ያካተተ ከሳይንስ  አቀራረብ በጣም የራቀ ነው።፡ 

ለማንኛውም የዶ/ር አቢይ ፖለቲካ በፍልስፍና መነጽር ሲመረመር አገራችንና ህዝባችንን ያረጋጋና የሚያረጋጋ አይደለም። ጉዳዩ በሳቸው ላይ ብቻ የሚሳበብ ሳይሆን በጠቅላላው አገሪቱን እመራዋለሁ በሚለው በፖለቲካ ኤሊቱ ላይም ነው። ከዚህም በላይ የአገዛዙን ፖለቲካ የሚቆጣጠር ብቃትነት ያለው የህዝብ ተወካይ ምክር ቤት አለመኖሩን ነው የፖለቲካው ሁኔታ የሚያረጋግጠው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ የፖለቲካውን፣ የኢኮኖሚውን፣ የማህበራዊውንና የአካባቢውን ቀውሶች የሚከታተልና በማጥናት ሊሻሻሉ የሚችሉበትን መንገድ የሚጠቁም የሲቪል ማህበረሰብም ስለሌለ አገዛዙ በዘፈቀድ አገርንና ህዝብን የሚጎዱ ፖሊሲዎች ተግባራዊ ሊያደርግ ይችላል። በተጨባጭም የሚታየው ይህ ነው። በአጠቀላይ ሁኔታውን ስንመለከት ሁሉም በፍርሃት የተዋጠና በዘመነ ፊዩዳሊዝም ያለ ይመስል የዶክተሩን ዐይን ቁልጭ ቁልጭ እያለ የሚያይ እንጂ በድፍረት አንገቱን ቀና በማድረግ በተጨባጭ የሚታየውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ በማመልከትና በመቃወም አማራጭ መፍትሄ የሚጠቁም የተገለጸለት ኃይል  የለም። ዛሬ አገራችን ላለችበት ሁኔታ እራሱ ተቃዋሚ ነኝ የሚለውም ድርጅት ወይም ኃይል ተጠያቂ ነው። አንድ ድርጅት ወይም ፓርቲ ተቃዋሚ ነው የሚያሰኘው ከአገዛዙ የተሻለ ሀተታና አማራጭ የመፍትሄ መንገድ ሲያቀርብ ብቻ ነው። በቂ ጥናትና ምርምር ሳያደርግ በጭፍኑ ተቃዋሚ ነኝ የሚል ድርጅት በተጨባጭ ሲታይ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት መዳበርና ለኢኮኖሚ ዕድገት አዎንታዊ አስተዋፅዖ ሊያበረክት አይችልም። 

ይህ ዐይነቱ ከውስጥ አገሪቱን ፍርክርኳን የሚያወጣ ፖለቲካ እየተካሄደ ባለበት ወቅት አይ ወያኔን መልሶ ስልጣን ላይ ለማውጣት አሊያም ደግሞ አገዛዙን በቀጥታ የኢምፔሪያሊስት ኃይሎች አጎብዳጅ ለማድረግ የሚደረገው ግፊት ሁላችንንም ግራ አጋብቶናል። የወያኔ ግልገሎች የዲጂታል ውጊያ ጀምረዋል፣ የአሜሪካንና  የአውሮፓን መንግስታት ከጎናቸው ማሰለፍና ድልን መቀዳጀት ችለዋል በማለት እዚህ አውሮፓ ውስጥ የዙም ኮንፍረንስ በማድረግ ተሳታፊው ነገሩን ፈታ ፈታ እያደረገ ሊናገር የማይችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ችሏል። በሌላ ወገን ደግሞ ከውጭ የሚመጣውን ጫና ለመቋቋም እዚህና እዚያ የሚሯሯጠውን ቅንም ሆነ አድር ባይ ኢትዮጵያዊ ልቡን በመግዛትና በአገዛዙ ዙሪያ በማሰለፍ የሽወዳ ፖለቲካ በመካሄድ ላይ እንዳለ እንመለከታለን። ከዲፕሎማሲ ጫና ጋር ተያይዞ የዕርዳታው መቀነስ ወይም መቋረጥ አብዛኛዎቹን የዙም ኮንፈረንስ ተሳታፊዎችንና የዶ/ር አቢይ ደጋፊ የሆኑትን በጣም አሳስቧቸዋል። ዕርዳታ ከተቋረጠብን ምን ልንሆን ነው? በማለት ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ወድቀዋል። የህዝባችንም የመኖርና ያለመኖር ዕድል ከዕርዳታ ጋር እንደተያያዘ የሚቆጥሩ በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያኖች እንዳሉ ይታወቃል። ይሁንና ግን እነዚህ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን ያልገባቸው አንድ ነገር አለ። በመጀመሪያ ደረጃ፣ በጣም የተሳካላቸውና በቴክኖሎጂ መጥቀው የሄዱ አገሮች ካለ ዕርዳታና ብድር ነው  ኢኮኖሚያቸውን መገንባትና ከድህነት መላቀቅ የቻሉት። በሁለተኛ ደረጃ፣ ባለፉት 60 ዓመታት፣ በተለይም ደግሞ ባለፈው 27 ዓመት የህውሃት አገዛዝ ዘመን በዕርዳታና በብድር ስም ወደ አገራችን በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ገብቷል። በብዙ ሺህ ቶን የሚቆጠርም ስንዴና፣ እንደዚሁም ሌላም ምግብ ወደ አገራችን ገብቷል። ይሁንና ይህ ሁሉ ዕርዳታ ወደ አገራችን መጥቶ አሁንም ቢሆን ህዝባችንና አገራችን ከድህነትና ከጥገኝነት በፍጹም አልተላቀቁም። የባሰ ደሀና ለማኝ አደረጉን እንጂ። ታዲያ ይህንን ከመመርመርና ከማጥናት ይልቅ ለምን ይህ ሁሉ ጩኸት እንደሚደረግ አይገባኝም። በዚህ ዐይነቱ ጩኸትም የአገር ወዳድነት ስሜትን ማሳየት አይቻልም። እንደዚህ ዐይነቱ ጩኸት አዘናጊና በራሳችን ላይ እንዳንተማመን የሚያደርገን ነው።

ለማንኛውም፣ ማንኛውም የዓለም አቀፍ ፖለቲካ ይገባኛል የሚል ሰው ማንሳት ያለበት ጥያቄዎች አሉ። ይህ ሁኔታ እንዴት ሊፈጠር ቻለ? በምንስ ምክንያት ነው የአውሮፓና የአሜሪካን መንግስታት እንደዚህ ዐይነቱን ዐይን ያወጣ ጫና የሚያደርጉብን? በማለት የጠለቀ ጥናትና ውይይት በማድረግ መልስ ማግኘት መጣር አለበት። በእኔ ዕምነት የአሜሪካንንም ሆነ የአውሮፓን መንግስታትና የአውሮፓውን ህብረት በማሳመን ወዳጆቻችን ለማድረግ በፍጹም አይቻልም። የእነሱ የፖለቲካ ጨዋታ የበላይነት(Dominance) ፖለቲካና፣ እንደ እኛ የመሳሰሉ አገሮችን እንደ አሽከርና ተላላኪ አድርጎ ማስቀረት ነው። እኛ የምንልህንና የምናዝህን ስማ ነው የሚሉን። ለዝንተ-ዓለም ፍራፍሬ በማፍራትና የጥሬ-ሀብት በማውጣት እኛን መግበን ነው የሚሉት። ባጭሩ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚና ጠንካራ ማሀበረሰብ መገንባት የለብህም ነው የሚሉን።  የሚያካሂዱትም ጦርነት ግልጽ ነው። አገሮችን ማዋከብና የህዝብን ስነ-ልቦና መረበሽ ነው። የአንድን አገር ስልጣኔና ታሪክ ማፈራረስ ነው። አገሮችን በሙሉ በግሎባል ካፒታሊዝም ቁጥጥር ስር በማድረግ ታዛዥና ተበዝባዥ እንዲሆኑ  ማድረግ ነው። በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የሚመራው ግሎባል ካፒታሊዝም ታሪክና ባህል ምን እንደሆኑ የሚያውቅ አይደለም። ፍልስፍናው ሀብትን ማካበትና ጥሬ-ሀብቶችንብ መቆጣጠር ብቻ  ነው። ስለሆነም የፖለቲካ ብስለት የሌላቸውን ጎጠኞችንና ከሃዲዎችን በመርዳት ጦርነት ከፍተውብናል። ከዚህ ባሻገር የአውሮፓውም ሆነ የአሜሪካ መንግስታት፣ እንዲሁም ደግሞ የአውሮፓው ህብረት የመሳሰሉት ተቋማት በራሳቸው በየመንግስታቱ በተቋቋሙትና በሚደጎሙት ቲንክ ታንክ ድርጅቶች የሚመከሩ ናቸው። ለምሳሌ የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስለኢትዮጵያም ሆነ ስለተቀሩት የሶስተኛው ዓለም አገሮች መረጃዎችንና ዕውቀት መሰል ነገሮችን የሚያገኘው የሳይንስና የፖለቲካ ተቋም ወይም አካዴሚ(Foundation for Science and Politics) ከሚባለው የተሳሳተ መረጃዎችን ከሚያቀርብ ድርጅት ነው። ከዚህም በላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተሩም ሆነ እራሱ መንግስት በስለላ ድርጅቱ የሚመከሩ ናቸው። እነዚህ ተቋማት ደግሞ በየአገሩ አለመረጋጋት እንዲፈጠር የሚያደርጉና በዚህ ዐይነት እርኩስ ተግባር የሰለጠኑ ነው የሚመስለው። በተጨማሪም ጋዜጠኞችም እንደዚሁ የተሳሳተ መረጃዎችን በማቅረብ መንግስታትን የሚያሳስቱ ናቸው። አሜሪካንም እንደዚሁ ነው። የቲንክ ታንክ ድርጅቶችና እንደ ሲኤንኤንና ቢቢሲ የመሳሰሉት ናቸው የተሳሰቱ መረጃዎችን በማቅረብ የስነ-ልቦና ጦርነት የሚያካሂዱብን። ይህም ማለት ግን እራሳቸው መንግስታት ከዚህ የተለየ ፖለቲካ ያካሂዳሉ ማለት አይደለም። የአሜሪካና የአውሮፓ መንግስታት የትላልቅ ኩባንያዎችን ጥቅም የሚያስጠብቁ ስለሆነ ይህንን ዐይነቱን የተሳሳተ መረጃ ይፈልጋሉ። ይህ በእንደዚህ እያለ የወያኔ አገዛዝ ባለፉት 27 ዓመታት ከእነዚህ ዐይነት ቲንክታንክ ድርጅቶችና ሜዲያዎች ጋር የእጅና ጓንት ሆኖ በመስራት አጋሩ ሊያደርጋቸው በቅቷል። ወደ ኢትዮጵያም በሚመጡበት ጊዜ ከፍተኛ ወጪ በመመደብ ሁሉንም ነገር ያደርግላቸው እንደነበር ይታወቃል። ስለሆነም የአውሮፓም ሆነ የአሜሪካ መንግስታት ለምን ጫና እንደሚያደርጉብንና የስነ-ልቦና ጦርነት እንደከፈቱብን ለሁላችንም ግልጽ መሆን ነበረበት።

ከዚህ በተጨማሪ የአሜሪካንም ሆነ የአውሮፓ መንግስታትና የዓለም አቀፍ ተቋማት የሚባሉት 27 ዓመታት ያህል ከወያኔ ጎን በመቆምና ማንኛውንም ዕርዳታ በማድረግ በአገራችን ምድር ፈሺስታዊ አገዛዝ እንዲሰፍንና ህዝባችንም ፍዳውን እንዲያይ አድርገዋል። ወያኔ ያካሂድ በነበረው ዘረፋ ተባባሪ በመሆን ሀብታችንን ዘርፈዋል። በኢኮኖሚ ፖሊሲያቸው አማካይነት በዕዳ እንድንተበተብ አድርገውናል። የአገራችን የንግድ ሚዛን በከፍተኛ ደረጃ እንዲናጋ ለማድረግ በቅተዋል። በዚያው መጠንም ባልተስተካከለና ዕውነተኛ የህዝብ ሀብት በማይፈጥር የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ድህነተና የባህል ውድመት እንዲመጣብን አድርገዋል። ባጭሩ እነዚህ የውጭ ኃይሎች ልክ እንደ ወያኔ መከሰስና በዓለም ፍርድ ቤት ፊት መቅረብ የነበረባቸው ናቸው።  ስልጠነናል፣ ዲሞክራቶች ነን፣ ወደ ውስጥም የህግ የበላይነት አለን በሚሉ የአሜሪካና የአውሮፓ መንግስታት አማካይነት ነው  እኛ ብቻ ሳንሆን አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ህዝቦችም ፋሺስት በመሰሉ አገዛዞች የሚሰቃዩት። ከዚሁ ሁኔታ ስንነሳ ይህንን ጉዳይ በግልጽ መወያየት ያስፈልጋል። በዚህ ላይ ግልጽነት ከሌለና መወያየትም እስካልተቻለ ድረስ ስለአገር ወዳድነት ማውራት አይቻልም። አንድ ሰው አገር ወዳድ መሆኑ የሚታወቀው በእንደዚህ ዐይነቱ መሰረታዊ ነገሮች ላይ ግልጽና የማያወላዳ አቋም ሲኖረው ብቻ ነው። ለማንኛውም ለዚህ መልሱ ልክ ቻይናዎች እንዳደረጉት ኃይልን ሰብስብ አድርጎ ወደ ውስጥ ያተኮረ የአገር ግንባታ ፖሊሲ ማካሄድ ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ ፖለቲካው ከሽወዳና ከራስ ጥቅምና ፍላጎት ባሻገር መታየት አለበት። ፖለቲካው ህዝባዊና ሁሉንም ኃይሎች በማካተት ለስራ የሚጋብዝ መሆን አለበት። ከፋፋይና ኃይልን በታኝ መሆን የለበትም። በመንግስት መኪና ውስጥ ተሰግስገው በህዝባችንና በአገራችን ላይ ጦርነት ያወጁብን ኃይሎች በቁጥጥር ስር መዋል አለባቸው። ይህ ዐይነቱ ጦርነት ልዩ ልዩ መልኮችን ያየዘና ህዝባችንን ፍዳውን እያሳየው ነው። በቀማኞችና በገዳዮች ብዛት የተነሳ በአዲስ አበባም ሆነ በተቀሩት የየክልሉ ከተማዎች ውስጥ ህዝቡ እንደልቡ ሊንቀሳቀስ የማይችልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ፖሊሶች ራሳቸው ለወንጀል ስራዎች ተባባሪዎች ነው የሚመስሉት። በሌላ ወገን ደግሞ ሰሞኑን የፌዴራል ፖሊስ ቃል አቀባይ ለጋዜጠኞች በሰጠው ሰፋ ያለ ገለጻ ከየክልሉ የፖሊስ ኃይሎች ጋር ተባብሮ „በየአካባቢው ፍጹም ሰላም እንዲሰፍንና ህዝባችንም እርግጠኝነት እንዲሰማው“ በትጋት እንደሚሰራ ነው። ይሁንና ግን የፖሊስ ቃል አቀባዩ ገለፃ ከዕውነት የራቀ ነው።  ተጨባጩን የአዲስ አበባንም ሆነ የተቀሩትን ከተማዎች የፀጥታ ሁኔታ የሚያንፀባርቅ አይደለም። በፌዴራል ፖሊሱ ቃል አቀባይ እንደዚህ ዐይነት ስለሳምና መረጋጋት ገለጻ ከተሰጠ በኋላ በመንግስት መዋቅር የሚደገፍና ትላልቅ መሳሪያዎችን የታጠቀ ኦነግ ሸኔ የሚባል አሸባሪ ቡድን አጣዬ በሚባለው በሰሜን ሸዋ ውስጥ ባለ ከተማ ጦርነት ከፍቶ የብዙ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል። ብዙ ሰዎችም እንደ ቆሰሉና ንብረትም እንደወደመ ከቦታው የሚመጡ መረጃዎች ያረጋግጣሉ። የኦነግ ሸኔን በከፍተኛ መሳሪያ ታጥቆ ተራውን ሰው መግደልና አንዳንድ ቦታዎችን መቆጣጠር አስመልክቶ የኦነግ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት ኦቦ ቀጀላ መርዳሳ ለአሃዱ ሬዲዮ በሰጡት የቃለ-መጠይቅ ምልልስ መሰረት አሸባሪው ቡድን በመንግስት መዋቅር የተደራጀና በገንዘብና በመሳሪያ እንደሚደገፍ ነው። ከኦነግ ምክትል ሊቀመንበሩ ከአቶ ቀጀላ መርዳሳ የተሰጠውን መልስ ስናዳምጥ የጠቅላይ ሚኒሰተራችንን የዶ/ር አቢይ አህመድንና የኦሮምያ ክልል ፕሬዚደንት የሆነውን የአቶ ሺመልስ አብዲሳን ሚና እንድንጠይቅ እንገደዳለን። ፖለቲካቸውም በምንም ዐይነት በፍልስፍናም ሆነ በሳይንስ የሚደገፍ እንዳልሆነ መገንዘብ ይቻላል። ኢ-ምሁራዊና ኢ-ሳይንሳዊ የሆነ ፖለቲካ  መሆኑን ማወቅ አለባቸው። የዶክተር ዲግሪ ከጨበጠና በፍስልፍና ትምህርት ከተመረቀ  ሰው ደግሞ እንደዚህ ዐይነት ፀረ-ህዝብና ፀረ-ሳይንስ ፖለቲካ አይጠበቅም። ለማንኛውም አቶ ቀጀላ መርዳሳ የሰጡትን መልስ ላዳመጠና የፊታቸውን ገጽታ በደንብ ላነበበ ሰውየው እንደማይዋሹ ነው። እዚህ ላይ መንግስት የሚባለውን ወደ 115 ሚሊዮን የሚጠጋውን ህዝባችንን የሚያስተዳድረውንና የኦሮምያ ክልልን አስተዳዳሪዎች የምንጠይቃቸው በዚህ ዐይነት የሽወዳና የተንኮል ፖለቲካቸው ምን ለማድረግ እንደሚፈልጉና? ምንስ ለማግኘት እንደሚመኙ ነው? ይህ ዐይነቱ አካሄድ የፖለቲካ ስልታቸው ከሆነ ፖለቲካ ሳይሆን በተደራጀ መልክ ወንጀል እንደሚፈጽሙና አገራችንንም እንድትፈራርስ ወይም በዘለዓለማዊ ጦርነት ውስጥ እንድትወድቅ እንደሚሰሩ ማወቅ አለባቸው። በዚህ ዐይነቱ የተወላገደ ፖለቲካቸው የሚጠቅሙት የኦሮሞን ብሄረሰብ ሳይሆን ኢምፔሪያሊስት ኃይሎችን፣ ግብጽንና ሱዳንን፣ እንዲሁም ደግሞ እንደነሳውዲ አረቢያ የመሳሰሉትን የወንጀሎች መንግስታትን ነው። ይህንን ጉዳይ ጠቅላላው የኢትዮጵያ ህዝብ በጥብቅ በመከታተል እንዲገታ ማድረግ መቻል አለበት። ካለበለዚያ ኢትዮጵያ የምትባለው አገር እንደ አገርና ህዝባችንም እንደማህበረሰብ ሊኖር እንደማይችል ማንኛውም ቅን ኢትዮጵያዊ እንዲገነዘበው ያስፈልጋል።  

ይህንን ትተን አንድ አገዛዝ አገር ወዳድ መሆኑና አለመሆኑ የሚረጋገጠው ተግባራዊ በሚያደርገው የኢኮኖሚ ፖሊሲም አማካይነት ነው። እንደሚታወቀው ኢኮኖሚ ለአንድ አገር ወሳኝና የአንድን ህዝብ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ የሚወስን ነው። ስለሆነም በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባለ አገር አንድ መንግስት ተግባራዊ  ሊያደርግ የሚገባው የኢኮኖሚ ፖሊሲ  ድህነትን መቅረፍና፣ በዚህ አማካይነት ወደሚቀጥለው እርምጃ ማለፍ ነው። ድህነት ቀስ በቀስ ሊቀረፍ የሚችለው ደግሞ በመጀመሪያ ደረጃ ቅድሚያ የሚሰጣቸው እንደመሰረታዊ ፍላጎቶች(Basic Needs) የመሳሰሉት ሲፈቱ ብቻ ነው። አገር ወዳድ ነኝ የሚል መንግስትም በመጀመሪያ ደረጃ በእነዚህ ነገሮች ላይ ነው መረባረብ ያለበት። አንድ ሰው ሲበላ፣ ንጹህ ውሃ ሲያገኝ፣ መጠለያ ሲኖረው፣ ህክምና ሲያገኝና እራሱን እንዲያውቅ የመሰረታዊ ትምህርት ዕድል ካገኘ ሰው መሆኑን ይገነዘባል። የማሰብ ኃይሉም ይዳብራል። አገሩንም ለመገንባት በቆራጥነት ይነሳል። ስለሆነም እንዲዚህ ዐይነቱ መሰረታዊ ጉዳይ ሊቀረፍና መልክ ሊይዝ የሚችለው በሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ፖሊሲና የህብረተሰብ ግንባታ አማካይነት እንጂ በተናጠል በሚካሄድ፣ ጥቂቶችን በሚያስደስትና በሚጠቅም፣ አብዛኛውን ህዝብ ደግሞ በሚያገል ፖሊሲ አማካይነት አይደለም። ቢያንስ ከኋላ መያዝ አለብን ብለው የተነሱ አገሮችን የኢኮኖሚ ፖሊሲና የዕድገት ታሪክ ሁኔታ፣ ከጀፓን እስከ ራሺያ፣ ከደቡብ ኮሪያና እስከ ቻይናና ሲንጋፖር ድረስ ተግባራዊ የሆኑትን የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ስንመለከት ወደ ውስጥ ያተኮረና ድህነትን በመቅረፍ ላይ ነው ከፍተኛ ርብርቦሽ ያደረጉት። ስለሆነም እነዚህ አገሮች የውጭ ኤክስፐርቶችን ምክር ሳይሰሙ በራሳቸው በመመካት፣ ከልምድና ከስህተት በመማር ነው ዛሬ የደረሱበት ደረጃ ላይ ለመድረስ የቻሉት።

አጠቃላዩን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ወይም ማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ በመባል የሚታወቀውን ስንመለከት የዶ/ር አቢይ አገዛዝ ኢኮኖሚ ማለት ምን ማለት እንደሆነ የገባው አይመስልም። በተለይም አዲስ ኃይል ስልጣን ላይ በሚወጣበት ጊዜ ህዝብ የሚጠብቀው አንድ ነገር አለ። ይኸውም ከፖለቲካው በተጨማሪም የኢኮኖሚ ፖሊሲውም ሊሻሻል ይችላል፣ አዲሱ አገዛዝ ድህነትን ለመቅረፍና የመጨረሻ መጨረሻም ድህነትን በማስወገድ ሰፋ ያለ ለሰፊው ህዝብ የስራ መስክ ሊከፍት የሚችል ሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሊከተል ይችላል የሚል ግምት ይኖረዋል። ስለሆነም እንደዚህ ዐይነቱ አገዛዝ አዲስ ፖሊሲ ከመንደፉ በፊት የአገሪቱን ጠቅላላ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ሁኔታ ሁለ-ገብ በሆነ መልክ በማጥናትና ለድህነትና ለኋላ-ቀርነት ምክንያት የሆኑትን ነገሮች በመመርመር አዲስና ግልጽ የሆነ፣ በእርግጥም አገሪቱንና ህዝቡን ከድህነት ሊያላቅቃቸው የሚያስችል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው ተግባራዊ ማድረግ የሚገባው። ይሁንና ግን የዶ/ር አቢይ አገዛዝ ይህንን ከማድረግ ይልቅ ዛሬም እንደትላንትናው የኒዎ-ሊበራል የነፃ ገበያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው መከተል የጀመረው። ይባስ ብሎ ግሽበትን የሚያስከትልና ድህነትን የሚያሰፋና የሚያጠናክር ፖሊሲ ነው  ተግባራዊ የሚያደርገው። ለጊዜው የህዝቡን ሆድ በማይሞሉ በቀጥታ ከኢኮኖሚ ግንባታ ጋር ግኑኝነት በሌላቸው፣ ይሁንና ግን ከረጅም ጊዜ አንፃር በሚያስፈልጉ መናፈሻዎች በመስራት ላይ ነው ያተኮረው። አሁን ደግሞ የተያዘው ጉድ ቱሪስቶችን ለመሳብ በሚል „ገበታ ለሀገር“ በሚል ግራ የተጋባና ቁንጽል ስራ ሀብትን እዚያ ላይ ማባከን ነው። ከዚህም በላይ ወጣቱ የስራ መስክ እንዲከፍት እየተባለ የሚሰጠው የስታርት-አፕ ስልጠና በመሰረቱ በአገሪቱ ውስጥ የተንሰራፋውን የወጣቱን የስራ-አጥነት ሁኔታ በምንም ዐይነት ሊቀርፍ የሚችል አይደለም። በየቦታው የዕድ-ጥበብ ሙያ መስኮችን በማስፋፋትና ወጣቱን የቴክኖሎጂ ባለቤት ሊያደረገውና በቀጥታም ከህዝቡ ጋር የተያያዘና የህዝቡን ችግር በሚቀርፍ የቴክኖሎጂ ምርት፣ ለምሳሌ ብረታ ብረትን ማቅለጥና ብሎኖችንና ለሳኒቴሽን የሚሆኑ ቧንባዎችንና፣ እንዲሁም ለቤት ስራ የሚያገለግሉ የህንፃ መሳሪያዎችንና፣ ሌሎች ተመሳሳይ ነገሮችንና ለቤት ግልጋሎት መጠቀሚያ የሚሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ከመስራት ይልቅ ባላስፈላጊና አንገብጋቢ ባልሆኑ ነገሮች ላይ ነው ሀብት የሚፈሰው። ይህ ዐይነቱ ሂደት ደግሞ ድህነትን ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ የሚቀርፍ ሳይሆን የድህነቱን ዘመን የሚያራዝም ነው። 

ከግሽበት መናር ጋር የተያያዘውንም ፖሊሲም ስንመለከት በመሰረቱ የድሮው ብር በአዲሱ ሲተካ አጠቃላይ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለውጥ አልተደረገም። አሁንም እንደድሮው የኢትዮጵያ ብር ከዶላር ጋር ሲወዳደር በየጊዜው ዝቅ እንዲል የሚደረግ ከሆነ አዲስ ብር ተለወጠ አልተለወጠ የሚያመጣው ፋይዳ የለም። ከዚህም ባሻገር ለዋጋ ግሽበት መናር  ምክንያቶች ሊሆኑ የሚችሉ የግልጋሎት መስጫ የኢኮኖሚ መስኮች መስፋፋት፣ ለምሳሌ በየቦታው ትላልቅ ሆቴል ቤቶችን መስራት የግዴታ ለዋጋ መናር በቂ ምክንያቶች ናቸው። ምክንያቱም እነዚህ ዐይነት የግልጋሎት መስጫዎች ሀብትን ከሰፊው ህዝብ ስለሚጋሩ ነው። መደረግ የነበረበትና ያለበትም ምርትንና ምርታማነትን በሁሉም መስክ ማስፋፋት ነው። የትናንሽና የማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች በየቦታው የሚተከሉበትን ሁኔታ በማመቻቸት ለህዝቡ ፍጆታ የሚያገለግሉ ምርቶችን ማምረት በተገባ ነበር።  እንደሚታወቀው የግልጋሎት መስኩ የሚመካው በምርት ክንውንና በምርታማነት ላይ ብቻ ነው። በእርሻም ሆነ፣ በትናንሽና በማዕከለኛ የኢንዱስትሪ መስክ ላይ ርብርቦሽ ካልተደረገና በጭፍኑ የግልጋሎት መስኩ ብቻ እንዲስፋፋ ከተደረገ የተዛባ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። የዶ/ር አቢይ አገዛዝና ፖሊሲ አውጭዎች እነዚህ አስፈላጊ ነገሮች በሙሉ የታያቸው አይመስልም። በተለይም የአገር ውስጥ ገበያ እንዴት እንደሚዋቀርና በየቦታው በተቋማት የተደገፉ የኢኮኖሚ ግንባታዎች መካሄድ እንዳለባቸው የተረዱና ከሌሎችም አገሮች ልምድ ለመቅሰም የሚፈልጉ አይደሉም። ከዚህም ባሻገር የየክልሉ አስተዳዳሪዎችና የከተማዎች ከንቲባዎች በየአካባቢያቸው ኢኮኖሚያዊና የንግድ እንቅስቃሴ፣  በልዩ ልዩ መልክ የሚገለጽ የባህል እንቅስቃሴና በተቋማት የሚደገፍ፣ ለምሳሌ የቤተ-መጻህፍትና የቲአትር ቤቶችና የሙዚየሞች መቋቋም… ወዘተ. ወዘተ. የመሳሰሉትን አስፈላጊነት የተረዱና የሚረዱም አይደሉም። በአጠቃላይ የአገራችንን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሁኔታ ስንመለከት አገሪቱን የባህል አገር ከማድረግ ይልቅ የብልግና ኢንዱስትሪ በማስፋፋት ከፍተኛ የሆነ የስነ-ልቦናና የባህል ቀውስ በማምጣት ለአሁኑም ሆነ ለመጭው ትውልድ አስቸጋሪ ሁኔታ እንዲፈጠር የሚያደርግ አካሄድ ነው። የዛሬዎቹ ፖለቲከኞቻችን በዚህም መስክ ከወያኔ አገዛዝ የተሻለ ማሰብ እንደማይችሉ ነው ያረጋገጡት።

የዚህ ሁሉ ችግር ምክንያቱ  ምንድነው? እንደሚታወቀው ዶ/ር አቢይና ሌሎችም በአገዛዙ ውስጥ የተካተቱት ግለሰቦች ከውጭ ወይም ከውስጥ ሆነው ወያኔ 27 ዓመታት ያህል ሲሰራ የነበረውን ወንጀል በመቃወም የታገሉና አማራጭ ፖሊሲዎችን ያቀረቡ አልነበሩም። ከአቶ ሙስጠፌና ከእሳቸው ጋር ከሚሰሩት አንዳንድ ባለስልጣናት በስተቀር በፌዴራልም ሆነ በየክልሉ የተቀመጡት ባለስልጣናት 27 ዓመት ያህል ከወያኔ ጋር በመሆን አይ እሱ ሲፈጽም የነበረውን ወንጀል አብረው ፈጽመዋል፤ አሊያም ደግሞ ፖለቲካውና ፖሊሲው ትክክል ነው በማለት ዝምብለው የሚመለከቱ ነበሩ። ይህም ማለት በዚህ ዐይነቱ የፖለቲካ ክንዋኔ ውስጥ ያደጉና ከደማቸው ጋር ያዋሃዱ ናቸው። ስለሆነም ከእንደዚህ ዐይነት ፖለቲከኞች ነን ባዮች ሰላምና መረጋጋትን መጠበቅ አይቻልም። ህዝባችንን ከድህነት ሊያላቅቀው የሚችል ሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ፖሊስ ተግባራዊ ያደርጋሉ ብሎ ማመንም አይቻልም። እንደዚህ ዐይነቱ አገዛዝ አገራችንን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት በማድረግ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ውስጥ ተገቢውን ቦታ እንድትይዝ ለማድረግ ይችላል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው።

በእንደዚህ ዐይነት መንግስታዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ለምትገኝ አገር ዋናው መፍትሄ አዲስ ዐይነት መንግስታዊ መዋቅርና የፖለቲካ አስተዳደር መዘርጋት ነው። ለዚህ ደግሞ አዲስ ብቃትነት ያለውና አመራርን ለመውሰድ የሚችል የኤሊት ኃይል መኮትኮት ያስፈልጋል። እንደዚህ ዐይነቱ ኤሊት የፖለቲካ ስልጣንን ከመቀዳጅቱና በተለያዩ የአድሚኒስትሬሽን ቦታዎች ኃላፊነትን ከመቀበሉ በፊት ቢያንስ አምስት ዓመት ያህል በልዩ የኤሊት ትምህርትቤት በፍልስፍና፣ በፖለቲካ፣ በሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ትምህርት፣ በስነ-ጥበብ፣ በሳይንስ፣ በኢንጂነሪግና በከተማ ልማትና አርኪቴክቸር መስልጠን አለበት። ይህ ዐይነቱ ልዩ ኤሊት ከሁሉም ብሄረሰቦች የተውጣጡ ወጣቶችን የሚያቅፍና የሚሰለጥን ሲሆን፣ ተመሳሳይ ተቋማትም በየክልሉ ወይም በየክፍላተ-ሀገራቱ ከተሞች መቋቋም አለባቸው። በዚህ መልክ የሚሰለጥነው አዲስ አመራር መንፈሳዊና የሰውነት ብቃት ይኑረው አይኑረው በየጊዜው ልዩ ዐይነት ምርመራ ይደረግለታል። ከውጭ ኃይሎችም ጋር ምንም ዐይነት ግኑኝነት አይኖረውም። የሚሰለጥነውም በአገሪቱ ውስጥና እዚያው የሚቀርና ዕውቀቱንም ማሻሻል ካለበት ተጨማሪ ኮርሶች በየጊዜው እንዲወሰድ ይደረጋል። በእኔ እምነት በአገራችን ያለውን የፖለቲካና የመንግስት ቀውስ በዚህ ዐይነቱ የረጅም ጊዜ ስትራቴጂ ብቻ ነው መፍታት የሚቻለው። በምርጫና ፓርቲዎችን በመለዋወጥ አገሪቱ የገባችበትን ሁለ-ገብ ቀውስ(Structural Crises) መፍታት በፍጹም አይቻልም። በዛሬውም የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ምርጫ ማድረግና በምርጫ መሳተፍ ያለውን ሁኔታና አገርን አፍራሽ ፖለቲካ ዕውቅና መስጠት ነው። ስለሆነም ስትራቴጂያዊ በሆነ መልክስ የሚያስብ ኃይል ወይም ድርጅት ሁሉ ገንዘቡንና ኃይሉን በሚቀጥለው ምርጫ ላያ ባያጠፋ ይሻላል። ለዘላቂ ሰላምና ተከታታይነት ለሚኖረው ዕድገትና ማህበረሰብ በአዲስ መንፈስ መታገል አለበት።

ለማንኛውም በአንድ አገር ውስጥ ያለ አገዛዝ የአገር ወዳድነት ስሜትነቱ የሚለካው በጠቅላላው ተግባራዊ በሚያደርገው ፖለቲካዊ፣ የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ፖሊሲ፣ እንዲሁም የአካባቢ ፖሊስ እርምጃዎች አማካይነት ነው። ህዝብን ከመሰብሰብና ከማጠናከር ይልቅ የሚበታትን ከሆነ፣ ድህነትን ከሚያስወግድ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ይልቅ ያለውን የሚያጠናክርና የሚያሰፋ ከሆነ፣ ከውስጥ ገበያ መስፋፋትና መዳበር ይልቅ ዶላር ለመቃረም ሲባል በውጭ መስኩ ላይ ብቻ ርብርቦሽ የሚደረግ ከሆነ ይህ ዐይነቱ ፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጠቅላላውን ማህበረሰብ ያናጋል። መንግስቱም ሆነ አገዛዙ የአገር ወዳድነት ስሜት የሌላቸው ብቻ ሳይሆኑ የኢኮኖሚንና የህብረተሰብን፣ እንዲሁም የተፈጥሮን ህግ ያልተረዱና ለመረዳት የማይፈልጉ መሆናቸው የሚያረጋግጡ ይሆናሉ። ስለሆነም የዛሬው የዶ/ር አቢይ አገዛዝና በጠቅላላው በአገሪቱ ምድር በክልል ደረጃ ስልጣን ላይ የተቀመጡት ኃይሎች በሙሉ አገርና ማህበረሰብ፣ እንዲሁም ደግሞ ሰው ማለት ምን ማለት እንደሆነ ያልገባቸው ናቸው ማለት ይቻላል። አገርና ህዝብ የራስን ፍላጎት ማሟያ ሳይሆኑ፣ አገር ታሪክ የሚሰራበት፣ ህዝብን በሙሉ ኃይሉ  እንዲነሳ በማድረግ ታሪክን ሰሪ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ ማመቻቸት ነው። የሰው ልጅም ነፃነት ሊገለጽ የሚችለው በስራና በፈጠራ እንዲሁም ጠንካራ ኢኮኖሚና ማህበረሰብ ሲገነባ ብቻ ነው። ስለሆነም  ለአንድ አገርና ማህበረሰብ ጥንካሬና ተከታታይነትም መኖር የመንግስት አወቃቀርና መንግስት የሚከተለው ፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ወሳኝ ሚናን ይጫወታሉ። መልካም ግንዛቤ!!

fekadubekele@gmx.de

www.fekadubekele.com    

ማሳሳቢያ.: ከታች የሚታየውን The Process of Democratization የሚለውን ሲጫኑት ቅርጹ ይበተናል። በተጨማሪም ይህን የመሰለ ተከታትይነት የሚኖረው ጥናት እንዲቀርብ የሚፈልግ ሰወም ሆነ ድርጅት ድረ-ገጼ ላይ ዶኔት የሚለውን በመጫን አስፈላጊውን ዕርዳታ ማድረግ ይችላል። 

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here