
በህይወት አበበ መኳንንት
ለማንኛዉም ችግር መፍትሔ ለማግኘት በመጀመሪያ ችግሩን ማወቅ እና እዉቅና መስጠት ያስፈልጋል። ሀገራችን የገባችበት ማጥ ቀላል አይደለም። የወደፊቱም እስካሁን ከሆነው የበለጠ አስጊ ነዉ። ህዝቦቿ ተጨንቀዋል አብዛኛዉም ግራ ተጋብቷል።ትላንት በሩቅ እንሰማ የነበረዉ መጥፎ ዜና ባንድም በሌላ በራችንን አንኳክቶ እየመጣ ነዉ። ታድያ ለዚህ ሁሉ ለደረሰ መከራ እና ስቃይ ሀላፊነት የሚወስደዉ ማነዉ? ለምንስ ዓላማ ነዉ? ብለን ብንጠይቅ መልሱ ጥያቄዉን እንደተረዳንበት መንገድ እና ለነገሮች ካለን አመለካከት በመነሳት የተለያየ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ፦ አንዳንድ ሰዎች ሀገሪቷ ታላቅ የለዉጥ ሂደት ላይ ናት ስለዚህ ይህ መንገጫገጭ የሚጠበቅ ነዉ ብለዉ ያምናሉ። ሃገሪቷ እየገጠማት ያለዉ ነገር የሂደቱ አካል ነዉ እንዲሁም በዚህ ሂደት ዉስጥ ጥቂቶች መስዋእት መክፈላቸዉ የማይቀር ነዉ ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ሀገሪቱ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታይ መልኩ ግፍ አና መከራ እያስተናገደች እንደሆነ እንዲሁም በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሀገርን ለመለወጥ ግፍ እና መከራን ማሳለፍ ተቀባይነት የለዉም ብለዉ ያምናሉ። ዜጎችም ለዚህ መሰዋእትነት መክፈል የለባችውም ብለዉ ይሞግታሉ። ሰለዚህ እነዚህ ሁለት ጽንፍ ከያዙ አስተሳሰቦች የሚገኘዉ የመፍትሄ ሀሳብ ለየቅል እንደሚሆን ግልጽ ነው። አሁን ሀገራችን ላይ እየሆነ ያለዉ ነገር ይህ ነው። ዜጎች ሀገራቸዉን ወደ ተሻለ መንገድ ለመለወጥ ሳይሆን በማንነታችዉ ብቻ መስዋእት እየሆኑ ነዉ። አርሰዉ፣ ዘርተው፣ አጭደዉ፣ ወቅተው፣ ከምረው ባሉበት እጃችው ዛሬ አስክሬን እየተሸከሙበት ነው። በርግጥ አስክሬን ለመሸከምም በህይወት መትረፍ ያስፈልጋል። ታድያ በየትኛው ስሌት ነዉ ይህ የለዉጥ ጉዞ የሚሆነዉ። ይህ በማንነቱ በቻ [አማራ በመሆኑ ብቻ] እየተጨፈጨፈ ያለዉ ማህበረሰብ ሀገሪቷን በታላቅ የለዉጥ ጎዳና ለማስኬድ ሲባል መስዋእት ለመሆን ፍቃዱን ሰጥቷል ወይ ብሎ መጠየቅ የእያንዳንዱ ኢትዮጲያዊ ገዴታ ነው። አዎ!! ፈቃዱን ሰጥቷል እንዳይባል ጠዋት ማታ በየአደባባዩ የድረሱለኝ ጥሪ እያቀረበ፣ መንግስት ከለላ ይሁነኝ እያለ እየተማጸነ ነው። በርግጥ የመንግስት ተቀዳሚ ሀላፊነትም የዜጎችን በህይወት የመኖር መብት ማስከበር ነው። ሌሎች መብቶች ከዛ በኋላ የሚተገበሩ ናቸዉ። በአሁኑ ሰአት ግን በህይወት የመኖር መብት ህልም የሆነባቸው በርካታ ሰዎች ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ መንግስት ለችግሩ እዉቅና ከመስጠት እና አፋጣኝ እርምጃ ከመዉሰድ ይልቅ ችግሩን ማቃለል ተያይዟል። በየጊዜዉ የምንሰማው የፕሮጀክት ምርቃት እና የመሰረተ ድንጋይ መጣል ወሬ ብቻ ነው። ፕሮጀክት መታቀዱም ሆነ መጀመሩ ክፋት ባልነበረዉ ነበር ነገር ግን እያንዳንዱ ኢትዮጲያዊ ከእነዚህ ፕሮጀክቶች ተጠቃሚ ለመሆን ዛሬን በህይወት መኖር አለበት። እነዚህ ፕሮጀክቶች ዛሬ ያጣናቸዉን ሰዎች አይመልሱልንም ወይም ነገ እንዳናጣቸው አያደርገንም። ታድያ አንድ የሀገር መሪ ይሄ ይጠፋዋል ብሎ ማሰብ ዘበት ነዉ። ማንኛዉም ሰው ዛሬ ተነስቶ የሀገር መሪ ልሁን ቢል የማይቻል እንደሆነ ብዙዎቻችን እንስማማለን። ምክንያቱም የአመራር እዉቀት እና ብቃት ያስፈልጋል። በርግጥ ይህ እድል ቢሰጣቸዉ ሀገሪቷን ቀጥ አድርገዉ የሚመሩ ጥቂት ሰዎች አይጠፉም። ታድያ ይህ እዉቀት አለኝ ብሎ ሀላፊነትን የተቀበለ ሰው በእሱ የስልጣን ዘመን ይህ ሁሉ ለመናገር የሚሰቀጥጥ ግፍ ሲፈጸም እንዴት ተቀብሎት ተመቻችቶ ይቀመጣል ብለን ስንጥይቅ ደግሞ የተወሰኑ ምክንያቶችን መዘርዘር እንችላለን። 1) ስልጣኑ የይስሙላ ነው ማለት ዋናው ሰልጣን ያለው የራሳቸዉን አላማ ለማሳካት አማራዎችን እየጨፈጨፉ ያሉ አካላት ጋር ነው። 2) መንግስት ወደ ስልጣን ሲመጣ ይዞት የመጣዉን ዓላማ ለማሳካት ሀገሪቷ ላይ እየሆነ ያለውን ቀዉስ እንደ መልካም አጋጣሚ በመዉሰድ ችግሩን ከመፍታት ይልቅ ችግሩን ማቃለል እና ሊሰጠዉ የሚገባዉን ትኩረት መንፈግ እንደ አቋም ወስዶታል። 3) በተለያዩ ክልሎች በተለይ በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ አማራዎችን ክልሉን ለቀዉ እንዲወጡ አለበለዚያ ገድሎ እና አፈናቅሎ መጨረስ ከመንግስት ድጋፍ ያገኘ ዓላማ ነው። 4) መንግስት ችግሩን የተረዳበት መንገድ እጅግ በጣም የተሳሳተ እና እየወሰደ ያለዉ እርምጃም በዛዉ ልክ የተሳሳተ ነው ወይም ባጭሩ የመምራት ችሎታዉ የወረደ ነዉ ማለት ነው።
አሁንም ከእነዚህ ምክንያቶች ተነስተን የምናመጣው መፍትሄ ወይም የምንይዘዉ አቋም የተለያየ ነዉ የሚሆነው። ለምሳሌ፦ ለምክንያት አንድ መፍትሄዉ ሰልጣን መልቀቅ ነው። ሀላፊነት ቦታን ይዞ ነገር ግን የዜጎችን ሞት ለማስቆም እንኳን ስልጣን ከሌለዉ ትክክለኛው እርምጃ ስልጣን መልቀቅ ነው። ካልሆነ የፕሮጀክት መክፈቻ ንግግር እያደረጉ እና ሪቫን እየቆረጡ ብቻ ሀገር መምራት አይቻልም። ለምክንያት ሁለት እና ሶስት ደግሞ ባለጊዜ መሆን ነገ ከተጠያቂነት አንደማያድን ማስተዋል ነው። ይህንን ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ የሰራዉ ፍግ ህወሃትን የት እንዳደረሰዉ ማየት በቂ ነው። ምንም ይሁን ምን ዘለዓለም የሚገዛ ሰዉ የለምና። ለምክንያት አራት ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ የያዘዉን የመደመር ፍልስፍና ቆም በሎ መፈተሽ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው። ሀገር እየመራ እስከሆነ ድረስ ለእያንዳንዱ ዜጋ ህገመንግስታዊ መብት መከብር ሀላፊነት አለበት። ይህ ካልሆነ ግን በተለያዩ ሀገራት እንዳየነው ሙሉ ሃላፊነት የሚወስድበት ጊዜ ይመጣል።
እኛም እንደዜጋ የተለያየ አቋም ቢኖረንም አንድ የሚያደርገን ጉዳይ ግን በምንም አይነት መንገድ የዜጎች መሞት ምክንያታዊ ሊሆን አለመቻሉ ነው። ይህንን ደግሞ ከእስካሁኑ በተጠናከረ መልኩ ልንታገልለት የሚገባ ጉዳይ ነው። አሁንም ዜጎች በማንነታቸው ብቻ ስለሚደርስባችው ግፍ እና መከራ በአንድነት ቁመን ልንቃወም ይገባል። በእያንዳንዱ የስልጣን እርከን ላይ ያሉ የመንግስት ባለስልጣናት ሀላፊነታቸዉን እንዲወጡ ልንሞግታቸዉ እና ጫና ልናሳድርባቸው ይገባል። ሀገሪቷን ከገባችበት ቀዉስ ማዉጣት ግዴታቸው ነዉ። የተኛንም ከእንቅልፋችን ልንነቃ ይገባል። ነገ በቤታችን ሲመጣ መንቃታችን አይቀርም ነገር ግን ዛሬ ላይ ቀድመን መንቃታችን ነገ በቤታችን ላይ እንዳይመጣ ለማድረግ ያስችለናል።
እያንዳንዷ ነፍስ ዋጋ አላት!!!!
እንዲህ ዓይነት አደገኛ እና ጽንፈኛ አስተሳሰብ፤ ሃገርን በባሰ ሁኔታ ከማበጣበጥ በስተቀር መፍትሔ አይሆንም። እንደ ሕይወት አበበ መኮንን ያሉ ሰዎች “ሥልጣን ይለቀቅ” ብለው ከመጠየቅ ውጭ፤ ለዛ አማራጭ የሆነ ነገር አያቀርቡልንም። በኢትዮጵያ ሥልጣን መያዝ ያለበት ማን እንደሆነ የሚወስነው ሕዝብ ነው። ይህንንም በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ እናያለን። በተለያየ ግንባር፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፤ የየክልል ልዩ ሃይላት እና የፌደራል ፖሊስ አባላት፤ በየአካባቢው በአማራው ወገናችን ላይ ብቻ ሳይሆን፤ በሶማሌውም፤ በአፋሩም፤ በኦሮሞውም፤ በጉሙዙም፤ በትግራዩም፤ ወዘተ፤ ላይ የሚፈፀሙትን አሳዛኝ እና አሰቃቂ ግድያዎች፤ ለማስቆም የሕይወት ዋጋ እየከፈለ ነው። መንግሥት እጁን አጣጥፎ እንደተቀመጠ የሚነገረው ትርከት፤ የእነዚህን ውድ ዜጎች መስዋዕትነት የሚያራክስ ነው። በተለያዩ አካባቢዎች ግድያዎች ስላሉ፤ ሌላው ነገር በሙሉ ባለበት ይቁም የሚል አስተሳሰብ፤ በሃገር ውስጥ ሽብር የሚነዙትን፤ የዜጎቻችንን ወድ ሕይወት የሚቀጥፉትን አረመኔ ሃይሎች ዓላማ ማሳካት ማለት ነው። በእያንዳንዱ በሚመረቅ ኅንፃ፤ የኢትዮጵያውያንን ሕይወት የሚቀይር፤ ነፍስም የሚያድን፤ የሥራ እድል መፍጠር መሆኑን አለመረዳት፤ ከአፍንጫ አርቆ አለማሰብ እና፤ መሪነት ማለት ምን ማለት እንደሆነም አለመገንዘብ ነው። አሜሪካንን በሚያክል ሃያል ሃገር፤ በአንድ ወር ውስጥ 45 የብዙ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፍ ግድያ ተፈጽሟል፤ ያ መሆኑ ግን አሜሪካንን ደካማ አያደርገውም። ወ/ሮ (ወ/ት) ሕይወት፤ ሥልጣን ይለቀቅ ሲሉ፤ በእርግጠኝነት መናገር የምችለው፤ እራሳቸውን ለዚህ ሥልጣን እጩነት አያቀርቡም። ችግራችን እጅግ ውስብስብ ጠላቶቻችንም የተቀናጁ እና የተደራጁ ናቸው። መንግሥት ሥልጣን ላይ ለመቆየት አማራውን ያስጨፈጭፋል፤ የሚል ውኃ የማይቋጥር ትርከት ግን፤ ለማንም አይጠቅምም። በሰፊው መልስ እስክሰጥ በዚሁ ይቆይልኝ።
ውድ አቶ ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ ወይዘሮ በህይወት አበበ መኳንንት የጻፈችውን ጽሁፍ በደንብ የተረዳኸው አይመስለኝሞ። እህታችን በተቻለ መጠን ሚዛናዊ በሆነ መልክ ነው ዛሬ አገራችን ያለችበትን ሁኔታ ለማቅረብ የሞከረችው። ይህ ዐይነቱ አቀራረብ የሷ ብቻ ሳይሆን አብዛኛዎቻችን የምንጋራውና የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ ያስቀመጠ ነው።
ያለው ሀቅ ዶ/ር አቢይ ስልጣንን ከጨበጠ ጀምሮ በተለይም በአማራውና የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች በሆኑት ላይ አሰቃቂ ግድያ ተፈጽሟል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዘመዶቻችን ከኖሩበትና ሀብት ካፈሩበት አካባቢ እንዲፈናቀሉ ተደርገዋል። በቤነሻጉልና በምዕራብ ወለጋ፣ ሰሞኑን ደግሞ በሰሜን ሸዋ በአጣዬና በካራቆሬ፣ ከአንድ ዐመት በፊት ደግሞ በሻሸመኔ ኗሪ በሆነው የአማራውና በሌሎችም እህቶቻችንና ወንድሞቻችን ላይ የደረሰው አሰቃቂ ግድያና የንብረት ውድመት የተካሄደው በአቢይ የአገዛዝ ዘመን ነው። እንደዚህ ዐይነት አሰቃቂ ግድያ ሲፈጸምና ህዝብም ሲፈናቀል አቢይ አንዳቸውም ቦታ በመሄድ ዘመዶቻቸው የሞቱባችውንና የተጎዱትን አላጽናናም። እንዲያውም ይባስ ብሎ እኔ አልገደልኳቸውም እያለ ነው የሚያውራው። ሰሞኑን ደግሞ ይባስ ብሎ የተጎዳውን ህዝባችንን ሳያጽናና የፈራረሱ ቦታዎችን ሳይጎበኝ በአዲስ አበባ የሚኖሩ ሲሪያዎችን ነው የጎበኘው። ይህንን ጉድ የተመለከቱ ሰዎች የሰውየውን የጭንቅላት ሁኔታ እየተጠራጠሩ ናቸው። ማሰብ ይችላል ወይ ብለው እየጠየቁ ነው። ለማንኛውም በተለይም በአማራው ላይ የሚካሄደው ጭፍጨፋ በእነ ሺመልስ አብዲሳ የሚቀነባበርና ማዕከላዊ መንግስቱም እጁ እንዳለበት የሚያመላክቱ ሁኔታዎች አሉ። በተለይም በሰሜን ሸዋ የደረሰው እልቂትና ከተማን ማውደም በተደራጀ መልክ የተካሄደ ለመሆኑ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው።
ያም ሆነ ይህ መንግስትና አንድ አገዛዝ ግዴታቸውና ኃላፊነታቸው በአገር ወስጥ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግና ማንኛውም ዜጋ ካለፍርሃት የሚኖርበትን አመቺ ሁኔታ መፍጠር ነው። አንድ ጠቅላይ ሚኒስተርም ሆነ ጠቅላላው አገዛዝ ስልጣንን የያዙት ህዝብንና አገርን ለማገልገል ነው። በሌላ ወገን ደግሞ የህዝብን ሰላም የሚነሱና አገር እንድተፈራርስ ማንኛውንም ተንኮል የሚፈጽሙም ሆነ የሚያቀነባብሩ ጽንፈኛ ኃይሎችን እየተከታተሉ በቁጥጥር ስር ማዋል የአገዛዙ ዋና ተግባር ነው። ጠቅላይ ሚኒስተሩም ሆነ ሌሎች ስልጣንን የጨበጡት ለመታየትና ለመከበር ሳይሆን በህገ-መንግስቱ መሰረት ህዝብን ለማገልገል ስልጣን ላይ የተቀመጡት። ይህም ማለት አገራችን በጠንካራ መሰረት ላይ እንድትገነባ በማድረግ ህዝባችን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት እንዲሆን ማድረግ ነው። ህዝባችን ከድህነትና ከረሃብ ተላቆ የተከበረች ኢትዮጵያ እንድተገነባ ማድረግ የመንግስት ታሪካዊ ግዴታና ኃላፊነት ነው። ይሁንና የአቢይ መንግስት ስልጣንን ከጨበጠ ጀምሮ አገራችንና ህዝባችን እፎይታን አግኝተው አያውቁም። አልፎ አልፎ የወያኔ እጅ ቢኖርበትም ስልጣንን የተቆጣጠረው ከኦሮሞ ብሄረሰብ የተውጣጣው ኃይል የማናለኝበት ስሜት በመሰማት ህዝባችንን ፍዳውን እያሳጠው ነው፡፟፡ የኦሮሞ ጽንፈኞች ድርጊት በገሃድ የሚታይና አብዛኛውም ህዝብ በስቃይ የሚኖርበት ስለሆነ ይህንን ሃቅ አሌ ማለት አይቻልም። በመሰረቱ የህዝባችን ስቃይና የአገራችን መፈራረስ የሚያሳስብህ በሆነ ነበር። ጽሁፎችህን አለፍ አለፍ አድርጌ እንዳነበብኩት ከሆነ አንተ የምትነሳው ከአንድ ግለሰብ ሁኔታ እንጂ ከጠቅላላው ህዝባችን የኑሮ ሁኔታና አገራችን ካለችበት ሁኔታ አይደለም። በአጻጻፍህ አንድን ግለሰብ የማምለክ ዝንባሌ ይታይብሃል። እንደሚመስለኝ በሃይቴክ በተትረፈረፈ የካፒታሊስት ዓለም ውስጥ ነው የምትኖረው። ሳይንስና ቴክኖሎጂ ደግሞ እዚህ ዐይነቱ የዕድገት ደረጃ ላይ ለመድረስ የቻሉት ኋላ-ቀርና ዲስፖታዊ አገዛዝን በመቃወምና አሽቀንጥረው በመጣል ነው። ግለሰብአዊ ነፃነትንና ዲሞክራሲ በተግባር ሊታዩ የቻሉትና እኛም ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ያስፈልገናል ብለን የምንታገለው የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት ለመሆነ ነው። አቢይና ተከታዮቹ የሚሰሩትን የማያውቁና የሳይንስንና የቴክኖሎጂን ዕድገት የሚቀናቀኑ ናቸው።
በአጭሩ እህታችንን ካለአግባብ የወነጀልካትና የምታስተጋቢው የጽንፈኛ አመለካከትን ነው የሚለው ዛሬ በአገራችን ምድር ስልጣንን የጨበጠውን ኃይልና ተከታዮችን የሚመለከት እንጂ ወይዘሮ በህይወት አበበ መኳንንትን አይደለም። ስለዚህ ውድ እህታችንን ካለአግባብ ነው የሰደብካት። የግዴታ ይቅርታ መጠየቅ አለበህ። ውድ እህቴም ሳትፈሪና ሳትቸሪ በዚ ዐይነቱ ሚዛናዊ አጻጻፍሽ ቀጥይበት። በተረፈ ጊዜ ካለሽ ይህንን ድረ-ገጽ ተመልከቺልኝ። http://www.fekadubekele.com n የድረ-ገጹ አድራሻ።
ዶ/ር ፈቃዱ በቀለ