spot_img
Sunday, September 24, 2023
Homeነፃ አስተያየትበማያስፈልግ ውሸት፤ ብሔራዊ ቅሌት! ( ከጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ)

በማያስፈልግ ውሸት፤ ብሔራዊ ቅሌት! ( ከጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ)

advertisement
Tibebe Samuel _  ብሔራዊ ቅሌት

 ከጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ
ሚያዚያ 8 ቀን 2013

“ሐሰትና ስንቅ፤ እያደረ ያልቅ” ሃገራዊ ብሂል።

በርካታ ጥናቶች እንደሚያስረዱት፤ በተለያዩ ሃገራት ያሉ መንግሥታት፤ ሕዝባቸውን በተደጋጋሚ ስለሚዋሹት፤ ሕዝብ በመንግሥት ላይ እምነት አጥቷል። በሃገራችንም፤ ከዚህ የተለየ አይደለም። በተለይ ከደርግ የአገዛዝ ዘመን ጀምሮ፤ ሕዝብ በመንግሥት ላይ እምነት ከማጣቱ የተነሳ፤ ሕዝቡን በተለያዩ መንግስታዊ እቅዶች (ፕሮጀክቶች) ላይ ለማሳተፍ የተደረጉ ጥረቶች ከሽፈዋል። በዘመን ሕወሃትም፤ ከደርግ ጊዜ በባሰ እና፤ መንግሥት “የረቀቀ” በሚመስለው ውሸቱ፤ ሕዝቡ በመንግሥት ላይ ምንም ዓይነት እምነት እንዳይኖረው አድርጎታል። የመንግሥት ባለሥልጣናት ዛሬም ድረስ ያለተረዱት ነገር፤ ሕዝብ የማያውቀው ነገር የለም። የሚያውቀውን ሕዝብ መዋሸት ግን ለምን ያስፈልጋል?

ሕወሃት ከሥልጣን ማማው ላይ ሲወረወር፤ አንዱ ተስፋችን፤ እውነት የሚነግረን መሪ ይኖረናል የሚል ነበር። ዶ/ር ዐብይም ወደ ሥልጣን ሲመጡ፤ ከተናገሩት እና ቀልቤን ከሳበው አንዱ ነገር፤ “ሁሌም እውነቱን እነግራችኋለሁ” ማለታቸው ነበር። ከሁለት ዓመታት ገደማ በፊት ለሕትመት በበቃችው “ሕዝቡ፤ ከመሪዎቹ እውነት እንዲነገረው ይጠብቃል” በሚል ርዕስ በፃፍኩት ጽሁፍ፤ አንዳንዴ፤ እውነቱን መናገር መሪር ሊሆን ይችላል፤ ዋጋም ሊያስከፍል ይችል ይሆናል። ግን ውሸት ተነግሮ፤ ውሸትነቱ ቆይቶም ሲጋለጥ፤ የበለጠ መሪር፤ ይሆናል፤ የበለጠም ዋጋ ያስከፍላል። ብዬ ነበር። ዛሬ፤ በማያስፈልግ ውሸት፤ እነሆ ሃገራችን፤ በዲፕሎማሲው መድረክ ላይ ከፍተኛ ዋጋ የምትከፍልበት ወቅት ላይ ተገኝተናል። 

የሕወሃት መራሹ ቡድን፤ በትግራይ በተመደበው የሰሜን ዕዝ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት ላይ አሳዛኝና ዘግናኝ ጥቃት በመፈፀሙ፤ የፌደራል መንግሥቱ፤ በትግራይ ክልል በወሰደው ሕግን የማስከበር ዘመቻ፤ የኤርትራ ወታደሮች በዚህ ዘመቻ መሳተፋቸውን አስመልክቶ ለተነሳው ጥያቄ፤ የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥታት፤ የሰጡት ምላሽ፤ የኤርትራ ወታደሮች፤ በዚህ ዘመቻ አለመሳተፋቸውን ነበር። አንዳንዶቻችንም፤ በምንችለው መንገድ እውነቱን ለመረዳት ባደረግነው የግል ጥረት፤ በተለያየ የሃላፊነት ቦታ ላይ ካሉ የኤርትራም ሆነ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት በእርግጠኝነት የተነገረን፤ የኤርትራ ወታደሮች፤ በዚህ ዘመቻ እንድልተሳተፉ ነበር። ይህንንም መረጃ በመቀበል ነበር፤ ይህ ፀሃፍ፤ ለአሜሪካው ኮንግረስ የብላክ ኮከስ ሊቀመንበር ለሆኑት፤ ለኦሃዮ ስቴት የህዝብ ምክር ቤት ተወካይዋ ወ/ሮ ጆይስ ቤቲ፤ እንዲሁም ለሜሪላንዱ የሕዝብ እንደራሴ ቤንጃሚን ካርድን፤ እና ሌሎች ተቋማት፤ የኢትዮጵያ የፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል እየወሰደ ባለው ሕግ የማስከበር እርምጃ፤ የኤርትራ ወታደሮች አልተሳተፉም በማለት፤ ለኢትዮጵያ ድጋፋቸውን እንዲሰጡ የጠየቀው። 

በጣም የሚገርመው እና፤ በተለይም በዓለም አቀፍ መድረክ፤ ሃገራችንን ተዓማኒነት ያሳጣው፤ ከተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሃፊ፤ የኤርትራ ወታደሮች፤ ትግራይ ክልል ስለመግባታቸው፤ የኢትዮጵያን መንግሥት ለጠየቁት ጥያቄ፤ ዶ/ር አብይ፤ ሽምጥጥ አድርገው መካዳቸው ነው። ይህ ግን ፍፁም አስፈላጊ ያልሆነ ውሸት ነበር። ኢትዮጵያ፤ የፈለገችውን ሃገር በመጋበዝ፤ በሕግ የማሰከበር ዘመቻው ተባባሪ ማድረግ ትችላለች። ይህንን የሚከለክል ምንም ዓይነት አለም አቀፍ ሕግ የለም። ይህ ፀሃፍ በተደጋጋሚ እንደገለፀው፤ ሃያሏ አሜሪካ፤ ኢራቅን እና አፍጋኒስታንን የወረረችው፤ ከሌሎች 49 ሃገራት ጋር በመተባበር ነው። የሶሪያው መንግስት፤ በራሺያ እየታገዘ ነው፤ ከተቃዋሚዎቹ ጋር ጦርነት የሚያካሄደው። የመን ውስጥ የሳውዲ አረብያ እና የአረብ ኢምሬት እጅ አለበት። ሌላው ቀርቶ፤ በ1970ዎች በሶማሊያ መንግስት በተደረገብን ወረራ፤ ለድል የበቃነው፤ በሶቪየት ወታደራዊ መኮንኖች አማካሪነት፤ እንዲሁም በየመን እና በኪዩባ ወታደሮች ቀጥተኛ የጦርነት ተሳትፎ ነው። ታድያ፤ የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ የኤርትራ መንግስት፤ በትግራይ ስላለው ዘመቻ በአለም መድረክ ላይ ምን አስዋሻቸው?  

በርካታ ኢትዮጵያውያን፤ በተለያየ መድረክ ላይ፤ የኤርትራና የኢትዮጵያ መንግሥታት የሰጡትን የተሳሳተ መረጃ እንደ እውነት በመቀበል፤ የኤርትራ ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ አልገቡም ሲሉ ተከራክረዋል። ዛሬም እየተከራከሩ ነው። “የዘፈን ዳርዳሩ እስክስታ ነው እንዲሉ” የኢርትራ ወታደሮች፤ በትግራይ ክልል መኖራቸው፤ መረጃዎች ሲወጡ፤ የኢትዮጵያ ወታደራዊ እና ሲቪል ባለስልጣናት፤ የሃሰት ሙዚቃቸውን በመቀየር፤ የሰሜን ዕዝ በሕወሃት ሲመታ፤ ድንበር ላይ በተፈጠረ ክፍተት፤ ‘የኤርትራ ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ገብተዋል፤ የሚል አሳሳች ከበሮ መደለቅ ጀመሩ። በዚህም ወቅት፤ አንዳንዶቻችን፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ግልጽ የሆነ ነገር ለሕዝብ እንዲያሳውቅ ጠይቀን ነበር። ይህ ግን አልሆነም። ይህ ጽሁፍ እስከተፃፈበት ድረስ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት፤ የኤርትራ ወታደሮች፤ ለምን ወደ ኢትዮጵያ ዘልቀው እንደገቡ፤ ምን ያክል ወታደሮች እንደገቡ፤ ተሳትፏቸው ምን ያክል እንደሆነ፤ ለሕዝብ ይፋ ያደረግው ነገር የለም። ለምን? 

ለመሆኑ፤ ዛሬ ከማንም በላይ፤ የትግራይ ሕዝብ፤ የኤርትራ ወታደሮች፤ በክልሉ እንደሚንቀሳቀሱ እያየ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፤ “የኤርትራ ወታደሮች ትግራይ ውስጥ የሉም” እያሉ ሲዋሹ እየሰማቸው፤ በሌላው ነገር እንዴት ሊያምናቸው ይችላል? የትግራይ ሕዝብ፤ በፌደራል መንግስቱ እና በተቀረው ኢትዮጵያዊ ላይ እምነት መጣል በሚያስፈልገው በዚህ አሳቻ ወቅት፤ ዓይኑን ያፈጠጠ ውሸት ስንዋሸው፤ ምን ይሰማው ይሆን? የሕዝቡንስ ልብ እንዴት ማሸነፍ ይቻላል? 

“እውነት ትቀጥን እንደሁ እንጂ አትሰበረም” ይባላል። በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መንግስታት ከአምስት ወራት ክህደት እና ድብብቆሽ በኋላ፤ የኤርትራ መንግስት የተባበሩት መንግሥታት ተወካይ፤ ሰሞኑን ለተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት በፃፉት ጽሁፍ፤ እውነቱን አፍርጠውታል። በዚህ ደብዳቤያቸውም ላይ፤ የኤርትራ ወታደሮች፤ በኢትዮጵያ ውስጥ መግባታቸውን አምነዋል። ሆኖም፤ የኤርትራ ወታደሮች፤ በትግራይ ፈጽመዋል ስለተባለው ዘግናኝ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሙሉ በሙሉ ክደዋል። ትላንት የካዱትን ዛሬ ሲያምኑ እያየን፤ ዛሬ የሚክዱትንስ፤ እውነት ላለመሆኑ እንዴት ልናምናቸው እንችላለን?

በተለይ በዚህ የፌደራል መንግሥቱ፤ በትግራይ የሕግ ማስከበር ሂደት፤ መንግሥት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ፤ በሕዝብ ግንኙነት በኩል ያሳየው ድክመት ከፍተኛና አሳፋሪ በመሆኑ፤ እንደዚህ ፀሃፍ ዓይነት ደቂቅ ዜጎች፤ ይህንን ክፍተት ለመሙላት፤ በተለያየ መድረክ ብዙ ተሟግተዋል ዛሬም እየተሟገቱ ይገኛሉ። ዜጎች፤ “የሃገራቸው አምባሳደር” በመሆን፤ በሚያደርጉት ሙግት ግን፤ ሙግታቸው በሃስት መረጃ የተደገፈ ከሆነ፤ ዛሬ ብቻ ሳይሆን፤ ወደፊትም ተአማኒነት ስለማይኖራቸው ድካማቸው ከንቱ ሆኖ ይቀራል። ትላንት “ባለማወቅ የዋሸናቸውን” ሰዎች፤ ዛሬ እንዴት ትብብራቸውን ልንጠይቅ እንችላለን? 

የኢትዮጵያ መንግሥት፤ መዋሸት በማያስፈልገው ሃገራዊ ጉዳይ ላይ በመዋሸት፤ በዓለም መድረክ ላይ፤ ውርደት አከናንቦናል። በጉዳዩ፤ በቀጥታ ተጎጂ የሆነውን፤ በተለይ የትግራይን ሕዝብ፤ በአጠቃላይም፤ የኢትዮያን ሕዝብ እምነት አጥቷል ለማለት ያስደፍራል። ሕዝቡ በመንግሥት ላይ እምነቱ እንዲጎለብት እና፤ ያለምንም ማመንታት፤ የተለያዩ መንግሥታዊ እቅዶች ላይ እንዲሳተፍ ለማድረግ፤ መንግሥት፤ ግልጽ በሆነ እና በማያሻማ ሁኔታ፤ በዚህ የሕግ ማስከበር ዘመቻ፤ የኤርትራ ወታደሮች እንዴት ወደ ትግራይ ሊገቡ እንደቻሉ፤ የተሰጣቸው ሚና ምን እንደነበር፤ ምን ያክል ወታደሮች እንደገቡ፤ አሁን ምን ያክል የኤርትራ ወታደሮች እንዳሉ፤ እንዲሁም መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ለምን ለሕዝቡም ሆነ ለዓለም አቀፍ ሕብረተሰብ እውነቱን እንዳልተናገረ፤ ማብራርያ መስጠት ይኖርበታል። 

ከመንግሥት በተጨማሪ፤ በዚህ ጉዳይ ተወቃሽ ሊሆኑ የሚገባቸው “የኢትዮጵያ የሃገር ውስጥ ጋዜጠኞች” ናቸው። በአንድም ወቅት፤ የኤርትራ ወታደሮችን አስመልክቶ፤ ጥልቅ ምርመራ እና መረጃ የያዘ ዘገባ አልሰሩም፤ በተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናት ጋዜጣዊ መግለጫ በሚሰጥበት ጊዜ፤ የኤርትራ ወታደሮችን አስመልክቶ፤ ጠበቅ ያለ ጥያቄ አቅርበው አያውቁም፤ ይህ ለምን ሆነ? ጋዜጠኞች፤ እንደ ባለሙያ፤ ሙያቸውን አክብረው፤ ሳያዳሉና ያለፍርሃት፤ እውነት ብቻ ሊዘግቡ ይገባል። ይህ ሲሆን፤ መንግስትም ጥንቃቄ ያደርጋል፤ እኛም ከእንደዚህ ዓይነት ብሔራዊ ውርደት እንተርፋለን። 

ቸሩ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን ይባርክ!    

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
13,682FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

1 COMMENT

  1. Worqu Belayneh Might is what thugs understand and practice; deal with them likewise. “Human Rights, Rule of Law, etc” do not work in the context of unruly people. Practice Mengistu Hailemariam’ style of ‘justice’ by eliminating the thugs on the sport and without mercy. BRing Worqu Belayneh to justice he is waging war on all non-amhara !

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here