
(በስለአባት ማናዬ)
የግብፅ እና የሱዳን ቤንዚንነት !
የዝሆኖቹ ርግጫ በአፍሪካ የእጅ አዙር ጦርነት እና የውክልና መዋጫወቻ ሜዳውን እያሰፋው ነው። አሁን በዓለም ላይ በከፍተኛ ደረጃ እጥረት እየታየበት ያለ ንጥረ ነገር አለ። ብረት እና የብረት ማዕድን ።አፍሪካ ደግም የዚህ ማዕድን ሃብታም ነች ባይባልም ያላትን አልተጠቀመችበትም። አሜሪካ እና ቻይና እጅግ የሚወዛገቡበት ጉዳይ ደግሞ የብረት ፖለቲካ ነው። በዚህ የሃያላኑ ርኩቻ የወደብ ፖለቲካ የጦር ሰፈር ግንባታ ጥድፊያ ፣የአንድ ቀበቶ አንድ መንገድ ፕሮጀክት ውዝግብ፣ የአፍሪካን የብረት ማዕድን የብረት ፖለቲካ ብንለው ይቅላል የመጠቅለል አካሄድ ነው። አመጣጣቸው ግን ይለያል የውጭ ጉዳይ ፖሊሱ ማስፈፀሚያ ስልታቸውም ይለያያል።አንድ ነገር ግን ስጋት አይሏል። የአፍሪካ በተለይ የአፍሪካ ቀንድ ዛሬም እንደ ትናንቱ የቀዝቃዛቅ ጦርነት የእጅ አዙር ጦርነት መፋለሚያ ሜዳ እንዳይሆን የሚለው። የዚህ ቀጣና መንግስታት እና ፖለቲከኞች እርስ በእርስ ከመሻኮት ወጥተው ታላቁን ካርታ ማንበብ የግድ የሚላቸው ሰዓት ላይ እንደሚገኙ ግን በአርግጥ ብዙዎች እየመከሩ ነው።
የቻይና አንድ ቀበቶ አንድ መንገድ መሰናክል የሚያጋጥመው ኢትዮጵያ ስትዳከም ነው!!
ይህ እሳቤ ከ2018 ጀምሮ በምዕራባዊያን እና በአሜሪካ ፖሊሲ አውጭዎች በኩል በስፋት ሲቀነቀን የከረመ አጀንዳ ነው። ከአሁን በፊት ግሎባል ሪሰርች ሴንተር እና ኒኤር ኢስት አውት ሉክ በስፋት ፅፈውብታል። ድረ ገፆቻቸውን ጎብኙ።
ከስድስት ወራት በፊት እየተለወጠ ባለው የአፍሪካ ቀንድ ጂኦ ፖለቲካ እንዴት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አስጠብቆ የሚጓዝ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ስትራቴጂ መንደፍ ይቻላል በሚል ደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የደህንነት ጥናት ኢንስቲቲዩት(ISS) የበይነ መረብ ውይይት አካሂዶ ነበር።በዚያ ውይይት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲው ዶክተር ዮናስ አሽኔ አንጋፋው ጡረተኛ ዲፕሎማት ዶክተር ተቀዳ ዓለሙ ተጋባዥ አቅራቢዎች ሆነው ተገኝተዋል። አምባሳደር ተቀዳ ዓለሙ ኢትዮጵያን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ በመሆን በርካታ ዓመታት ወክለዋታል አገልግለዋታል። እርሳቸው በዚያ ውይይት ላይ እንዳቀረቡት ኢትዮጵያ አሁናዊው የአፍሪካ ቀንድ የጂኦ ፖለቲካ ስንጥቃቶች ቅድሚያ መለየት አለባት ባይ ናቸው። የቀጣናው ውልቃቶችን ጥሩ ወጌሻ ሆኖ ለመውጣት መጀመሪያ የሃይል አሰላለፉን በሚገባ ማጥናት እና ለዚያ መግቻ መሳሪያ የሆኑ የዲፕልማሲ ስልቶችን መንደፍ ያሻል ምክረ ሀሳባቸው ነው።
ወቅታዊው የኢትዮጵያ አካሄድ ግን በብዙ የዘገየ በሚል ትችት አሳርፈውብታል። በተለይ ከአረቦች ጋር እያደረገችው ያለው ግንኙነት በእጅጉ ጠንቃቄ የሚሻ ጎዳይ ሆኖ አግኝተውታል። በተለይ በቀይ ባህር አካባቢ በግብፅ ፊታውራሪነት እየተተወረ ያለው የቀይ ባህር ፎረም ለኢትዮጵያ እጅግ ጊዜ የማይስጥ የቤት ስራ ሆኖ መጥቷል።ግብፅ ከትናት እስከ ዛሬ ድረስ ኢትዮጵያን ከቀይ ባር ጂኦ ፖለቲካ የማራቅ የሴራ ዲፕሎማሲዋን ስታከናውን ቆይታለች ዛሬም ገፍታበታለች።
ኢትዮጵያ ለዚህ ወሳኝ መፍትሄ መሻት ይገባታል። በተለይም በጎረቤት ሀገራት የወደብ ድርሻ እንዲኖራት የማድረግ የዲፕሎማሲ ጥረት ። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከኢትዮጵያ ፍላጎቶች ጋር ተቃርኖም ተዛምዶም ያለው ሆኖ መጥቷል። ተቀርኖው በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት አዝማሚያ እያሳየ ነው።ይህን አደገኛ አዝማሚያ መቀልበስ የሚቻለው ኢትዮጵያዊያን በውስጥም በውጭም ያሉት በመተባበር ለብሔራዊ አንደነታቸው ሲቆሙ ብቻ ነው ካልሆነ ዛሬም እንደ ትናንቱ በተቃርኖ መንገድ መንጎዳቸውን ከቀጠሉ አደጋው የከፋ ነው። አሜሪካ በምስራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያን ዋና የስትራቴጂ አጋሯ አድርጋ ከርማለች ፣አሁን አሁን በኬንያ ለመተካት የምታደርገው ጥረት ይስተዋላል።
የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችን ከማሻሻያ ጓዳ ሊወጣ ይገባል!!
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ክለሳ መደረግ ከጀመረ እነሆ ሶስት ዓመታት እየሞላው ነው።በዚህ እየተከለሰ ባለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሁለት ነገሮች አዲስ ሆነው እና ትኩረት ተሰጥቷቸው ብቅ ብለዋል። በረቂቅ ሰነዱ ላይ እናየሁት አሁን የወደብ ጉዳይ ከሸቀጥ ፖለቲካ ወጥቶ የደህንነት ጉዳይ ተደርጎ ተወስዷል።ይህ መልካም ጅማሮ ነው።የባህር ሃይል የማደራጀት ስራው ያው ወደ ተግባር ተገብቶ ተደራጅቷል። የወደብ ጉዳይ በባሌም በቦሌም ተብሎ አፋጣኝ ምላሽ ያሻዋል። በደረቅ መሬትም ለውጦ ቢሆን የአውሮፓ እና የላቲን አሜሪካ ሀገራትን ተሞክሮ መድገም ይበጃል።የሃያላኖቹን ርኩቻ በምስራቅ አፍሪካ ላይ የከፋ ቀውስ እንዳያደርስም የሃይል አሰላለፉን በመገንዘብ የራስን አዋጭ የዲፕሎማሲ መንገድ መምረጥ መልካም ነው። በተለይ ወደ አንዱ ወገን ብቻ ሙጭጭ ማለትም ተገቢ አይደለም። ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ያላት ተሰሚነትን በአፍቃዊ መንፈስ አሁንም ማጠናከር ይገባታል። በተለይ ምዕራባዊያን ይህን አካሄዷን ለማዳከም በየጊዜው እየሸረቡት ያለው ዳግማዊ የቅኝ ግዛት መንፈስም በጥሞና እየተከታተሉ ማምከኛ መፍትሄ መስጠት ያሻል ባይ ናቸው በአዲስ አበባ ዩነቨርሲቲ የአፍሪካ ጥናት ክፍል ተማራመሪው ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ። ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ ኢትዮጵያ የውጭ የደህንነት ስጋቶቿን ለመቀነስ ቅድሚያ የቤት ውስጥ ፖለቲካዋን መፈተኝ ይገባታል የሚል ምክረ ሀሳብ አላቸው። የሀገር ውስጥ ፖለቲካው መስከን ከተሳነው እና እዚህም እዚያም የልዩነት ሰበካዎች እየጎሉ የንፁሃን ሞት እና መፈናቀል ከተበራከተ ፤በሀገር ውስጥ የሚከፉ ሃይላት ቁጥራቸው ይበራከታል ። ያ ደግሞ ለውጭ ሃይላት የእጅ አዙር ጦርነት እንደ ለም መሬት ይሆንላቸዋል የሚል ስጋት አላቸው። ብሔራዊ ጥቅምን አደጋ ውስጥ የማይጥል የፖለቲካ አሰላለፍ ያስፈልጋል ነው የፕሮፌሰሩ ሙግት። ያለ ባለዚያ ግን ነገም እንደ ትናንቱ በድህነት አዙሪት በደህንነት ስጋት መንፈስ ውስጥ መራመዳችን አይቀሬ ነው ። ምስራቅ አፍሪካ ዛሬም እንደ ትናንቱ እየተገነባ የሚፈርስ እየፈረሰ የሚገነባ ቀጣና ከመሆን እንዲተርፍ ኢትዮጵያ የራሷን ጠጠር ማኖር አለባት።
ግብፅ እና ሱዳን ኢትትዮጵያን ለማዳከም የሸረቡት መንታ አሻጥር
ያልተቋጨው የውሃ እና የድንበር ፖለቲካ!!
የቅኝ ግዛት ዘመኑ የእንግሊዙ ሻለቃ የቀበረው ፈንጅ ዛሬም መምክን ተስኖታል፤የናስር ብሔርተኝነት፡የከዲቭ እስማኤል ፓሻ ሴራም ተጠናክሯል።ያልተቋጨው የውሃ እና የድንበር ፖለቲካ የካርታ ባለሙያዎች ከድንበር ክለላ ጋር በተያያዘ ሁለት ነጥቦችን ያነሳሉ። የመጀመሪያውመለየት(Deliminations)-ይሄምበስምምነት(Treaty)፣በጽሑፍ እንዲሁም በካርታ ፣በወረቀት ላይ የሰፈረ የደንበር መስመር ተብሎ ይገለጻል።ሁለተኛው ከለላ( Demarcation)- በመባል የሚታወቀው ነው።ከአፄ ምኒልክ እስከ ዛሬ ድረስ የተከናወነው እየተከናወነ ያለው ነገር የድንበር መለያ(Deliminations) የሚባለው እንጂ የድንበር ከለላ( Demarcation) አልተካሄደም።
የእንግሊዞ የጦር መኮንን ሻለቃ ጉዊን የቀበሩት ፈንጅ
ሻለቃ ጉዊን በ1903 በአውሮፓዊያኑ የራሳቸውን ፍላጎት ያስቀደመ የእንግሊዝ እና ሱዳንን ማለት ነው የድንበሩን ሁኔታ የሚገልፅ ካርታ አዘጋጅቶ አቀረበ። በዚህ ካርታ የኢትዮ -ሱዳን የድንበር ርዝመት 1600 ኪሎሜትር ሲሆን ፤ የድንበሩን ርዝማኔም በሁለት ክፍል ከፍሎ አስቀምጦታል።(አቶ ቹቹ አለባቸው -2011 ዓ/ም -ባህርዳር) አንደኛው ፡በሰሜን ምዕራብ የሰቲት(ራውያን) ወንዝን መነሻ በማድረግ ወደ ደቡብ በኩል የጓንግ ን ወንዝ ተፋሰስና ገላባትን ና መተማ ዮሐንስን የሚያዋስንው አሜራ ወንዝ ተፋሰስን ይዞ ሽንፋ(ማጠብያ) ወረዳ የሚገኝ የስኳር ተራራ( በእንግሊዞች ዳንግልሽ፣በሱዳኖች ጀበል ስኳር) እየተባለ የሚጠራው ከፍታ ተራራማ ቦታ ድረስ አንደኛው ክፍል በማለት አቅርቧል።
ሁለተኛው ክፍል ከስኳር ተራራ(ከዳግልሽ ወይም ጀበል ስኳር) አጠገብ ቲሃ ወንዝን መነሻ አድርጎ ወደ ደቡብ በማቅናት ከነብስ ገበያ፣በሱዳኖች አጠራር(ጀበል ሀልዋ) ተራራ እግርጌ በሚገኘው ሽ ሽንፋ ወንዝና ነጥብበመያዝ እስከ ጋምቤላ አኮቦ ድረስ ሚያመለክተው ነበር። እነዚህ የእንግሊዙ ሻለቃ ካርታዎች የኢትዮዽያን ብሔራዊ ጥቅም የሚቃረን የባዕዳን ተልዕኮ የሚያስፍፅም የተቀበረ ፈንጅ ሆኖ ዛሬም ድረስ ጎረቤታሞቹን እየረበሸ ነው።
ኢትዮዽያን የዘነጋው የአስዋን ትልቅ ግድብ
በናስር አገዛዝ ዘመን ለውጥ ያለው ተግባር ተብሎ የሚጠቀሰው የናይል ፖሊሲ ና የአስዋን ግድብ ግንባታ ነው። በጥቅምት 1951 የተቋቋመው የግብፅ አገዛዝ ከእንግሊዞች ጋር በመሆን የጣና ግድብን በተመለከተ አዲስ ስምምነት ለማድረግ ሞክሯል። በመስክረም 1952 ወደ ስልጣን ከመጣ ሁለት ወራት በኋላ ወጣት መኮንኖች ታሪካዊ የተባለ ሽግግር አድርገዋል። በቀደመው አገዛዝ ውድቅ የተደረገውን እቅድ በማርቅቅ የአስዋን ግድብ እንዲገነባ አድርግዋል። ግድቡ የግብፃዊያን ማንነት ማብሰሪያ ተደርጎ ተወስዷል።
ግድቡን ተከትሎ የሚፈጥረውን ኋይቅ ካይር ተቆጣጥራዋለች። አዲሱ አገዛዝ (የናይል ሸለቆ ትብብር) የመመስርት እቅዱን ውድቅ በማድረግ በ1953 ከእንግሊዞች ጋር አካባቢውን የማፅዳት ስምምነት ተፈራረመዋል። ፕሮጀክቱ በገንዝብ የመደገፍ ሂደቱ ከምዕራባዊያን ጋር ያጋጫቸው ሲሆን ለግብፅ እና ሩስያ ግንኙነት መንገድ ከፍቷል። ቆየት ብሎ በ1956 ከእንግሊዝ ፣ፈረንሳይ፣እና እስራኤል ጋር ጦርነት ገጥመዋል።ጦርነቱ የፖለቲካ ድልን ያስገኘላቸው ሲሆን ቀጣናዊ የናስር ኩራት ከመፈጠሩ በላይ የፓን አረቢዝም ድል ተደርጎ ተወስዷል።መሬት ላይ እየሰሩ በዲፕሎማሲው መፍጠን ይጠይቃል!
የውሃውን እሳት በውሃ የማጥፋት ስትራቴጂ
በዓለም ላይ ከ286 በላይ ወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ይገኛሉ። በእነዚህ ወንዞች በርካታ ሀገራት የላይኛው እና የታችኛው ተፋሰስ አባል ሆነው እየተጠቀሙባቸው ይገኛሉ። ብዙ ጊዜ በላይኛው ተፋሰስ አባል ሀገራት ግድብ እና ሌሎች የልማት ስራዎች ሲጀመሩ የታችኞች ተፋሰስ አባል ሀገራት እሮሮ እና እየዬ ዲፕሎማሲያዊ ጩኸታቸውን ያሰማሉ። ሁል ጊዜም መፍትሔ የሚሆነው ግን የተጀመረው ግድብ በድል ሲጠናቀቅ እና ውሃው መፍሰሱን ሲቀጥል ነው። ኢትዮጵያስ ?ኢትዮጵያው ከእነዚያ እንደ አንድ ናት ።
የታላቁ ህዳሴ የህዳሴ ግድብን በፍጥነት ማጠናቀቅ አዲሱን የግብፅ ቅኝ ግዛት መንፈስ ለዘለቄታው መስበር ነው። ጥቅሙም ለኢትዮጵያዊያን ብቻ አይደለም። ለሌሎች አፍሪካዊያን ወንድሞቻችን ጭምር እንጂ። ለምን?የአድዋ ድል ለመላው ጥቁር ህዝቦች እና አፍሪካዊያን ወንድሞቻችን አይቻል የሚመልሰለውን የቅኝ ግዛት ቀንበር መስበሪያ ርዕዮት ዓለም ነበር ፓን ኢትዮጵያኒዝም ወደ በኋላ ላይ ፓን አፍሪካኒዝም የተሸጋገረው።አሁንም የህዳሴው ግድብ ከተጠናቀቀ በሁሉም የናይል ተፋሰስ አባል ሀገራት ግብፅን እንዴር ተቋቁመን እንችላለን ለሚለው የዘመን ግርጃ መቀልበሻ ጥቁር ማቅ ማውለቂያ ሞዴል ነው። ግድቡ ለአፍሪካዊያን ሌላም የምጣኔ ሀብት ሞዴል ይዞ የሚመጣ ነው!!እስካሁን በአፍሪካ ግዙፍ ግድቦች በራስ ሀብት ያለ ማንም የውጭ እርዳታ የተገነባ የለም። የህዳሴው ግድብ ሲጠናቀቅ ይህን የክፍለ ዘመን ግርዶሽ የሚገልጥ ነው። የታላቁ የህዳሴ ግድብ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የአድዋ ድል ብስራት የፓን ኢትዮጵያኒዝም ርዕዮት ዓለም ግማድ ነው!!
ከሦስቱ ዲ ዎች ወደ አራቱ ዲ ዎች እየተቀየረ ያለው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እና ምስራቅ አፍሪካ
የአሜሪካ የአፍሪካ ፖሊሲ ሶስቱ ዲዎች (3Ds)
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ይከተሉት የነበረው የአፍሪካ ፖሊሲ ለአሁናዊው የፕሬዚዳንት ትራምፕ የአፍሪካ ስትራቴጂ ኑባሬ ምክንያት የሆነ ይመስላል። የነጩ ቤተ መንግስት ሰዎች የአፍሪካን ከሽብርተኝነት አኳያ በሶስት ይከፍላቸዋል። ለእነዚህ ሶስት አዝማሚያዎች እና ፍረጃዎችም የራሳቸውን ሶስት ፖሊሲዎች ይተገብራሉ በእነርሱ አጠራር ሶስቱ ዲዎች (3Ds.diplomacy,defense ,dvelopmemnt)። ጎረቤት ሀገር ሱዳን እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ ፈቃጅ ሀገር/enabler states/መዝገብ ውስጥ ከተዋት ነበረ። በዚህ መስገብ ወስጥ ያሉ ሀገራት ለሽብርተኞች በገዛ ፍቃዳቸውከለላ እና ድጋፍ ያደረጋሉ ተብሎ የሚታሙ ናቸው። የደህንነት መረጃ የሚያቀብሉ መሳርያ እና ቴክኖሎጂ የሚሸጡ ተደርገው ይወሰዳሉ በእርግጥ ካርቱም ምን አይነት ቴክኖሎጂ ልትሸጥ ነው?
አንደ እነዚህ አይነት ሀገራትን ለመግታት አሜሪካ የአለም አቀፍ ዲፕሎማሲን ግፊቶችን ወይም ወታደራዊ ሃይሏን ለመጠቀም ትችላለች/2DS defense and diplomacy/,በዚህ ፖሊሲ ሱዳን በ1998 የአሜሪካን ጡጫ ከቀመሰች በሗላ ቢላደንን ማባረሯን ልብ ይሏል ። ለአሜሪካ ከፈቃጅ ሀገራት ይልቅ ራስ ምታት የሆኑት ቸልተኛ ሀገራት/slacker states/ናቸው። እነዚህ ሀገራት የላላ ህግ ያላቸው ወይም የህግ ማስከበር አቅማቸው ደካማ የሆኑ ናቸው ።ሽብርተኞች የጦር መሳርያ እንደ ፈለጋቸው ያዘዋውራሉ ልምምድ ያደርጋሉ የሽብር ጥቃት ይነድፋሉ። የአሜሪካ በእነዚህ ሀገራት ያሉ ጠንካራ ጎረቤት ሀገራትን ትጠቀማለች /Anchor states/ትላቸዋለች። ለእነዚህ ወሳኝ ሀገራት ደግሞ አንዱን ዲ ትጠቀማለች ልማት /development/ለኢትይዽያም ከጆርጅ ቡሽ እና ቢል ኪሊንተን ጀምሮ ይህ መስመር እንደ ተከፈተ ነው።
አሁናዊው የምስራቅ አፍሪካ ጂኦ ፖለቲካ በእርግጥ ከዚህ መንፈስ ነፃ ነውን?
ወቅታዊው ባይደን እና ብሊንክ መራሹ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ምሰሶዎች
አራት ስትራቴጂካዊ (ስልታዊ) ምሰሶዎች
1 የመከላከያ ዲፕሎማሲ እና ድተረንስ (deterrence) (“የነቃ ዲፕሎማሲ እና የወታደራዊ ድብልቆችን በመጠቀም ከቁጥጥር ውጭ ከመውጣታቸው በፊት ቀውሶችን ለመከላከል ወይም እነሱን ለመያዝ የሚፈልግ የውጭ ፖሊሲ”) ነው ፡፡2-ንግድ እና ቴክኖሎጂ ነው (“ጠበኛ ከሆነው የመንግስት ካፒታሊዝም (aggressive state capitalism ) ከስራአት ዉጭ ዓለማቀፋዊ የንግድ ዉደድሮች የሚሰርቱን ሃይሎች መከለከል።”)3-ከአጋሮች እና ተቋማት ጋር ተባብሮ ዓለም አቀፋዊ የንግድ መረብ መፍጠር (“አሜሪካ የአውሮፓ አጋሮች እና የእስያ አጋሮችዋ ጋር ” የቻይናን ቤልት እና ሮድ” (ብለት Belt and Road) ስልት ማክሸፍ) ፡፡4-ስደተኞች እና ተፈናቃዮች (“የተባበሩት ምዕራብ ዲሞክራቲክ መንግስታት ብዙ ስደተኞችን እና ተፈነቃዮች ለመቋቋም እየታገሉ ስለሆነ ፣ አሜሪካ የስደትን መንስኤዎች እና መዘዞችን መፍታት አለባት”)
የ ኩሽነር አደገኛው የዓባይ ውሃ ፖለቲካ አዝማሚያ
በአረብ እስራኤል የሰላም አደራዳሪነት ላለፉት አራት ዓመታት የሰሩት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ልጅ ባል ጃሬድ ኩሽነር አደገኛ እቅድ ይዘው ነበር።የልጅ ኩሸነር የምጣኔ ሀብት እቅድ ግብፅ በዓባይ ( ናይል) ወንዝን ተከትላ እያከናወነቻቸው ያሉ የልማት ፕሮጀክቶችን መደገፍን ያካተተ ነበር።የኩሽነር እቅድየግብፅ፣እስራኤል፣ ፍልስጤም፣ዮርዳኖስን እና ሌሎች ጎረቤት ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ውህደት ያለው ነው።ከፕሬዚዳንት ቡሽ አስተዳደር ጀምሮ የመካከለኛው ምስራቅ ሰላምን ለመደገፍ በሚል በአሜሪካ መንግስት ድጋፍ ሲተገበር የቆየውንና የእስራኤልን ምርት በግብዓትነት ተጠቅመው ወደ አሜሪካ ገበያ ከቀረጥ ነፃ የሚላኩ ሸቀጦችን የሚያመርቱ የግብፅ ኢንዱስትሪያል ዞኖችን ማስፋፋትና አጠናክሮ ማስቀጠልን አካቶ የያዘ ነው።በአሁኑ ሰዓት በግብፅ ውስጥ በዚህ ድጋፍ የሚንቀሳቀሱ 17 የኢንዱስትሪ ዞኖች ሲኖሩ ከ96 በመቶ በላይ የሚሆኑት ምርቶች በናይል(ዓባይ) ወንዝ ላይ በተመሰረቱ የመስኖ እርሻዎች ላይ ጥገኛ የሆኑ የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶች ላይ ያተኮሩ ናቸው። የከሸፈው እንበለው አሁን እና ዕቅድ ላይ ፍልስጤምም ተጠቃሚ ትሆናለች ተብሎ የታሰበው በዚህ ቀጣናዊ የልማት ትስስር ነበር።ዓባይን መሰረት ያደረገ የምጣኔ ሀብት ትስስር። ከዚህ አኳያ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ድጋሚ ተመርጠው ቢሆን ኖሮ በእስራኤል ፍልስጤም የክፍለ ዘመኑ ስምምነት ውስጥ በምጣኔ ሀብት ዕቅዳቸው ውስጥ ግብፅ ከአሁን በፊት በቅኝ ግዛት ዘመን የፈረመቻቸውን የናይል ወንዝ ውሎች እውቅና ለመስጠት አስራ አንደኛው ሰዓት ላይ ነበሩ። አንደንዴ እድል ፊቱን ያዙርልህ ይባላል እና ትራምፕ ተሸነፉ ፤ቢያሸንፉ ኖሮ ከባድ የምጣኔ ሀብት ጫና ይደርስብን ነበር። ፍልስጤማዊያንን በሰሜን ሲናይ የማስፈር ዕቅድ በናይል ወንዝ ላይ ከባድ ተፅዕኖ የሚፈጥር አደገኛ አዝማሚያ ነው።ኢትዮጵያ ይህን የግብፅ እና እስራኤል አካሄድ ሁሌም ንስር ሆና መከታተል ይገባታል። የፍልስጤማዊያን የፖለቲካ ጥያቄ መፍትሔ ለማሰገኘት በተደረጉ ጥረቶች የናይል ወንዝን እንደ መሳሪያ ጥቅም ላይ ለማዋል በተለያየ ጊዚያት ሙከራዎች መደረጋቸውን ታሪክ ያስረዳናል።በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፍልስጤም የእርዳታ ስራዎች ኤጀንሲ(UNRWA) በጋዛ ሰርጥ የሚገኙ ፍልስጤማዊያን የነበረባቸውን የውሃ ችግር እልባት ለመስጠት የናይልን ወንዝ ጠልፎ መጠቀም አዋጭ እንደነበር በ1955 ባደረገው ጥናት ሪፖርት አውጥቷል።በተጨማሪም የናይል ወንዝን ጠልፎ የግብፅ የሰሜን ሲናይ ግዛትን በማልማት ና ከጋዛ ሰርጥ ጋር በማጣመር ፍልስጤማዊያንን አገር እንዲመሰርቱበት ወይም ደግሞ በስደተኝነት ማዕቀፍ እንዲሰፍሩበት የማድረግ እቅድ በግብፅ፣በእስራኤል፣ የአሜሪካ እና የባህረ ሰላጤው ሀገራት መሪዎች ደረጃ ለረዥም ጊዜ ሲመክሩ እና ሲዘክሩባቸው የከረሙ ትልቅ አጀንዳዎች ናቸው።ለአብነት ያህል የቀድሞው የግብፅ ፕሬዚዳንት አንዋር ሳዳት በ1970ዎች መጨረሻ ላይ እስራኤል ባደረጉት ጉብኝት፣የቀድሞው የግብፅ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ በ1980ዎች ከእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በነበረው ውይይት፣በቅርብ በጊዜም የቀድሞው የግብፅ ፕሬዚዳንት ሞሀመድ ሙርሲ በ2013 ከፍልስጤሙ መሪ ሙሃመድ አባስ ጋር ባደረጉት ውይይት ፍልስጤማዊያንን በሰሜን ሲናይ የማስፈር አጀንዳ ተመክሮባቸው ነበር።በእስራኤል በኩልም ብዙ ጊዜ ከኔጌቭ ለግብፅ መሬት ቆርሶ በመስጠት በአፀፋው ግብፅ በሰሜን ሲናይ በናይል ውሃ ከሚለማው ቦታ ለፍልስጤሞች በመስጠት እንዲሰፍሩ ደጋግማ ጠይቃለች።ሌላ ጊዜም የናይል ወንዝን ጠልፎ ወደ እስራኤል በማሻገር ወደ እስራኤል ብሔራዊ የውሃ ማከማቻ (NATIONAL WATER CARRIER )የማስገባት ዕቅድ ወጥቶም ነበር። አል ሲሲ በዓባይ ፖለቲካ ከኢትዮጵያ ጋር በአለም አቀፍ አሸማጋይነት መደራደር (ከአፍሪካ ማስወጣት) አጥብቀው ይሻሉ።ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ 2019 የአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀመንበር ነበሩ። ያኔ ባነሷቸው እና አፍሪካን ወክለው በተገኙባቸው መድረኮች ሁሉ ስለ ህዳሴ ግድብ አንዳች ነገር ትንፍሽ አላሉም። ለምን በአለም መድረክ ቢያነሱት እና ጉዳዩን ለመወያያ አጀንዳ ቢያቀርቡት ከአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 መርህ ጋር ይጣረስባቸዋል እና ። ምክንያቱም በአጀንዳ 2063 የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ መፍታት የሚል ነው እና።አል ሲሲ ጉዳዩን ከአፍሪካ ይልቅ ወደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት የወሰዱት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዳግም ይመረጣሉ በሚል ያልተጨበጠ ተስፋ እና የቀድሞው ምክትል ፕሬዚዳንት ዲሞክራቱ ጆ ባይደን መመረጥ እድላቸው አናሳ ነው በሚል ነበር።ግን ያል ተጠበቀው ሆነ ።አሁን አል ሲሲ ከፍተኛ ጫና በመፍጠር ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከነጩ ቤተ መንግስት ሳይወጡ አስገዳጅ ስምምነት እንዲፈረም ይፈልጋሉ።አል ሲሲ ትራምፕ ከወጡ የአረብ ጉዳይ ደላላነትም ያከተመ በመሆኑ የሞት ሽረት ተጋድሎ እያደረጉ ነው።
ወቅታዊው የግብፅ እና ሱዳን አሳሳች ጉዞ ምንን ያመለክታል?
የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማቶች እና ፖለቲከኞች ፡
ወታደራዊ መለዮለባሾች ገና ድርድሩ ሳይጀመር የተቃርኖ ጉዞ ጀምረው ነበር።እነዚህ ሀገራት ከአሁን በፊትም ሆነ ሰሞኑን እየተከተሉት ያለው መንገድ ድርድሩን አሰልች በማድረግ ከአፍሪካ ህብረት የድርድር መድረክ ለመውጣት ነው።ነገር ግን ካይሮም ሆነች ካርቱም በቀጥታ የአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት አያስፈልግም አይሉም።ምክንያቱም አህጉራዊ ተቋም ነው እና በርካታ ሀገራት እና ድርጅቶች የአፍሪካን አደራዳሪነት ስለሚቀበሉት፤በቀጥታ ቢወጡ ከባድ ጫና ይፈጠርባቸዋል።
ከዚህ አኳያ የካይሮ አሳሳች እና አደናጋሪ ዲፕሎማቶች የመረጡት አካሄድ ፡ድርድሩን አንዴ የሚጀመር ሌላ ጊዜ የሚቋርጥ፣አንድ ጊዜ ግብፅ በመቃረን ሌላ ጊዜ ሱዳን ተመሳሳይ መንገድ እንድትከተል በማድረግ ኢትዮዽያም ተበሳጭታ ከድርድሩ እንድትወጣ ማድረግ ነው።ከዚያ መልሰው ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይወስዱታል፡ጎን ለጎን ደግሞ የኢትዮዽያን ወዳጆች ሳይቀር ይኸው የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ህብረት ብላችሁ መስራቿ እንኳን አታምንበትም በማለት ስሟን ያጥላላሉ።
ምን ይደረግ??
አሁንም ቅድሚያ የውስጥ ጉዳያችን ከሴራ ፖለቲካ መንጣት ይገባዋል። ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ የሚቻለው የውስጥ አንድነት ሲጠናከር ብቻ ነው። አለባለዚያ እዚህም እዚያም የፖለቲካ ንትርክ፣የዜጎች መገደል እና መፈናቀል ቀጣይነት የሚኖረው ከሆነ ፡ ዙሪያችንን እንደ ጆፌ አሞራ ለከበቡን ጥላቶቻችን ተጋላጭንታችን እየሰፋ ይመጣል። ካይሮ የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጉዳይን እንዴት አድርጋ እንደተጠቀመችበት ማየት ብቻ በቂ ነው።የካርቱም ሰዎች አሁን መንታ መንገድ ላይ ናቸው።በአንድ በኩል የሱዳን ህዝብ እና ሲቪል አመራሮቹ ወዳጅነትን እና መርህን መሰረት ማድረግ ይሻሉ፡በሌላ በኩል ባለመለዮ ለባሾች ዳግም ከካይሮ ጋር ተጎዳኝተው የሸርተቴ መንገድ ጀምርዋል።
በቅርቡ ደግሞ ዳርፍር እና ከደቡብ ኮርዶፋ አማፅያን ጋር የተፈራረሙትን የሰላም ስምምነት ገቢር ለማድርግ የነበረው ካቢኔ ተበትኖ አዲስ ስለሚዋቀር ይህም በእጅጉ ያሳስባቸዋል።ለፈርዖኖቹ ግን እነዚህ የካርቱም የፖለቲካ ውልቃቶች እጅግ ጠቃሚ ናቸው።እንዳሻቸው ከሌሎች አረብ ነጋዴዎች ጋር ሆነው እንዲተውሩ አስችሏቸዋል።ወደ ኋላ ተመልሰን 1958ትን የአውሮፓዊያኑ ማለቴ ነው ታሪክ ማጥናት ያስፈልጋል።ያኔ ሱዳን የተሻለ መንግስት እና ለኢትዮዽያም የተሻለ እይታ የነበረው አስተዳደር ነበረ።ግብፆች በፍጥነት መፈንቅለ መንግስት እንዲካሄድ አድርገው ጀኔራል አቡድን አምጥተው ነው ታህሳስ 1959 ዳግማዊውን የቅኝ ግዛት ዘመን የናይል ወንዝ ስምምነት የተፈራረሙት።
ከዚህ አኳያ ለራሳችን መፍትሄው እኛው ራሳችን ነን፡የደህንነት እና የፀጥታ ተቋሞቻችንን ይበልጥ ማጠናከር፡እያንዳንዱ ዜጋ የሀገሩ ዘብ ጠባቂ መሆን፣የመንግስት ሹማምንት እና ፖለቲከኞችም የእርስ በእርስ የፖለቲካ እንካ ስላንትያ ከመወራወር ይልቅ ህዝብን በሚያቀራርብ አጀንዳ ላይ ማተኮር ይገባቸዋል። የግድቡን ግንባታ አሁንም በነቃ ጥንቃቄ ማፋጠን ያስፈልጋል። ቀጣዩ ክረምት እጅግ ወሳኝ ነው። የውሃ ሙሌቱ በተሳካ ሁኔታ ከተካሄደ ካርቱም ምን አልባትም ከፔንዱለማዉ ዠዋዥዌዋ ትውጣ ይሆናል።ብሔራዊ ጥቅማችንን በዘላቂነት ለማስከበር እጅግ ታሪካዊ ጊዜ ላይ እንገኛለን ። ዲፕሎማሲን ከማጠናከር ጎን ለጎን አሁንም ወደ ውስጣችን እንመልከት።
በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት የሚካሄድውን ድርድር ግን በፍፁም አሰልች ቢሆንም የግብጽ እና ሱዳንን አጭበርባሪነት እስከ ወዲያኛው ድረስ ለአፍሪካዊያን ወንድሞቻችን ለማሳየት መቀጠል ይኖርብናል።
ብሔራዊ ጥቅም ሲባል????
በእርግጥ ለፈረንሳዮች እኚህ ሰው ታላቅ ጀግና ናቸው። ጀኔራል ደጎል ለፓሪስ ያልሆኑላት የለም ። ደራሲም ወታደርም መሪም አዋጊ ጀኔራልም ሆነው አገልግለዋታል። ቻርለስ ደጎል ስለ ብሄራዊ ጥቅም በሕይወታቸው ማምሻ አካባቢ ሲናገሩ ያስቅደሙት በአውሮፓዊያኑ ሰኔ 18 ቀን 1940 ለንደን ውስጥ ቢቢሲ ራዲዮ 4 ላይ ቀርበው ያደረጉትን ታሪካዊ ንግግር ነው።ያ ታሪካዊ ንግግራቸው የሚያተኩረው በወቅቱ ሂትለር መራሽ መስፋፋቱ ፓሪስ ዘልቆ በፈረንሳይ የሂትለር አሻንጉሊት መንግስት መመስረቱን ተከትሎ ነው።ፓሪስ አልተንበረከከችም!!!!!!
ያኔ ይላሉ ጀኔራል ደጎል እጅግ የተበሳጨሁት ለሀገሬ ሰዎች ከሂትለር በፊት ያደረኩትን የማንቂያ ደዎል ሳስብ ነው። ቀድሜ ለሀገሬ ሰዎች የማዚኖ አጥር ድንጋይ ነው የሚል ጭብጥ ያለው መጽሐፍ ደርሼ አሰራጭቼ ነበር።የሀገሬ ህዝብ ግን ልብ ብሎ አላነበበውም።የመጽሐፉ ቁም ነገር ሲፈተሽ ፈረንሳይ ጀርመን እና ሌሎች ሀገራት ድጋሚ ጥቃት እንዳይፈፅሙ በሚል ድንበሯን በረዥም የድንጋይ አጥር ከልላ ነበር። የማዚኖ አጥር የሚባለው።
ታላቁ ደራሲ እና የጦር መኮንን ጀኔራል ቻርለስ ደጎል ግን የማዚኖ አጥር ድንጋይ ነው ።ፈረንሳይ ዘመናዊ ጦር መገንባት አለባት፡ዘመናዊ ታንኮች ሊፈበረኩ ይግባል ነበር ጉትጎታው።ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ማግስት ፓሪሶች ለእኚህ ጀኔራል ጆሮ ነፍገዋቸው ነበር።እርሳቸውም ፓሪስ ስትጠራኝ እመለሳለሁ ብለው ወደ ሚወዱት የድርሰት ስራ ተመለሱ ፓሪስን የኋሊት ትተዋት ወደ ገጠራማው አካባቢ ተጓዙ።
ሂትለር ስልጣን ሲጨብጥ ደግም መስፋፋቱን ሲጀምር ቻርለስ እንዳሉት የማዚኖ አጥር ድንጋይ ሆኖ በሂትለር ዘመናዊ ታንክ በደቂቃዎች ውስጥ ተደርምሶ ፈረንሳይ በሂትለር ብረት መዳፍ ስር ወደቀች።አሁን ፓሪስ የገፋችውን ጀኔራል መልሳለ ጠራች ጀኔራል ቻርልስ ደጎል የት አደለ ስትል ድምፃን ከፍ አድርጋ ተጣራች፡ጀኔራሉም ፓሪስ ስትጠራኝ እመጣለሁ አይል ያሉት ከተፍ አሉ ፡ፓሪስ ሳይህን ለንደን ።
የመረጃውን ጦርነት ቀድመው ከፈቱት ፡ቢቢሲ ላይ ቀርበው ፓሪስ አልተንበረከከችም ፡የሂትለር አሻንጉለቲ መንግስት ሳይሆን እኛ ነን የፓሪስ የቁርጥ ቀን ልጆች መሪዎች አሉ።ይህን ንግግራቸው እና ድርጊታቸውን በረዥሙ ካስታወሱ በኋላ ለብሄራዊ ጥቅም ዘብ መቆም ማለት ሀገር አደጋ ውስጥ በገባች ጊዜ እንጂ በሰላም ጊዜ አርበኛ መሆን አይደለም ይላሉ።
ሀገር በአራቱም አቅጣጫዎች ከውስጥም ከውጭም ስጋት ከተጋረጠባት እነዚያን መንታ ስጋቶች ለማክሸፍ በሞራል ከፍታ የተግባር ሰው መሆን ነው ይላሉ።እኔም ያደረግኩት ይህን ወርቃማ እድል ነው ባይ ናቸው።አይ ታላቁ ደጎል ወርቃማ እድል አሉት አይደል።ለቻርልስ ደጎል ብሄራዊ ጥቅም ማለት
ሀገር ክንደ ፈጣማ እንድትሆን በሁሉም ዘርፍ መትጋት፡በአስችጋሪ ጊዜ ሲጠሩ አቤት ወደዬት ማለት፡
ጥላትን ፊት ለፊት በጦር በጎራዴ ብቻ ሳይሆን በመረጃ ጦርነትም መፋለም፡ከሁለም በላይ ግን ሀገሬ አልተንበረከከችም ብሎ የሞራል ከፍታን አንስቶ ለሰንደቅ ዓላማዋ መፋለም ቀዳሚው ነው ብለዋል።
ከዝነኞቹ የአሜሪካ የፖሊሲ ጉዳይ የጥናት ማዕከላት መካከል አንዱ የሆነው ሁቨር ኢንስቲቲዩት ትልቁ አዳራሽ በታላላቅ እንግዶች እና በጀማሪ ዲፕሎማቶች ፣በአለም አቀፍ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ ትምህርት ተከታታዮች እና መምህራን እንዲሁም የዋሽንግተን ባለስልጣናት ታድመውበታል።
ጊዜው ሰኔ 14 2000 ዓመት ምህረት በአውሮፓዊያኑ ነበር።የቴክሳሱ ሀገረ ገዥ በዚያ አዳራሽ የመገኘታቸው ሁኔታ ታላላቅ ባለስልጣናትን ለታናሹ ቡሽ የምርጫ ቅሰቀሳ ድጋፍ የሚያደርግ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አቅጣጫዎች ላይ ሀሳብ እንዲሰጡ ይጋብዛሉ የሚል ጭምጭምታ ተሰምቶ ነበር።
የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሊቁ ሄነሪ ኪሲንጀር እና የያኔው ሹም ኮሊን ፖል ከሁለት አንዳቸው ወደ ሆቨር አዳራሽ ወደ መድረክ ይወጣሉ በሚል እተጠበቀ ነበር። የሆነው ግን ተቃራኒው ነው ። ኒዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ሁነቱን ባሰፈረበት አምድ ላይ እንዳብራራው ያኔ 45 ዓመት የሞላቸው የስታንፎርድ ዩኒቨርሲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰሯ ኮንዶሊዛ ራይስ ነበሩ የተጋበዙት።የኮንዶሊዛ ራስ የንግግር አጀንዳ ደግሞ ለብሄራዊ ጥቅም መታገል(Promoting national interest ) የሚል ነበር።ለስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሯ ራይስ የንግግር መክፈቻ ቃላት በእርግጥ ከድህረ ሶቬት ህብረት ማግስት ምን በብሄራዊ ጥቅማች ላይ አደጋ የሚደቅኑ እነማን ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ጥያቄ የሚያጭሩ ነበሩ።
ለኮንዶሊዛ ራይስ ብሄራዊ ጥቅምን ለማስከበር ከመትጋት በፊት ብሄራዊ አጀንዳ መቅረፅ እና ብሄራዊ ትልም ማስመር ይቀድማል። እነዚህን ሁነቶች በግልፅ የሚረዳ ዜጋ ደግሞ ለእነዚህ መሳካት ሌት ከቀን ከልዩነት ይልቅ በትብብር ለሀገሩ ጥቅም ይዋደቃል ነው ነገሩ።መረጃ፣ቴክኖሎጂ እና እውቀት እና ጥበብን ማዳበር ደግሞ ለብሄራዊ ጥቅም መከበር ትልቅ መወጣጫ መሰላሎች ናቸው። የምጣኔ ሀብት የእድገት ምሰሶዎችን በግልፅ አስቀምጦ አካታች መተግበሪያ ስልቶችን ማንበር ሌላኛው ወሳኝ ምዕራፍ ነው። የፖሊሲ ጉዳዮች መጀመሪያ መረቀቅ ያለባቸው በባለስልጣናት አልያም በካቢኔዎች ሳይሆን በሀሳብ አፍላቂዎች ፣ለሀገር ጥቅም ሟች በሆኑ የቁርጥ ቀን ልጆች መሆን አለበት ነው ምክረ ሀሳባቸው። ኮንዶሊዛ ራይስ ያኔ ያሰሙት ንግግር ብሪታንያ ሰኔ 23 ቀን 2016 ከአውሮፓ ህብረት የመነጠል ውሳኔ ማግስት ዘ ኢኮኖሚስት ላተመው አንድ ርዕሰ ጉዳይ መነሻ ሆነዋል።
የሀገር ብሄራዊ ጥቅም አደጋ ውስጥ የሚገባው ስልጣን በጓደኝነት ወይም ሹሞክራሲን መሰረት ሲያደርግ (the elite that failed .the economist 2016) ነው ይላል። አፍቃሪ ሪፐብሊካኗ እመቤት ኮንዶሊዛ ራይስ እንደሚሉት አምስት ነጥቦች ላይ ቅድሚያ ትኩረት ማድርግ ብሔራዊ ጥቅምን ለማሰጥበቅ እጅግ ወሳኝ የመሪዎች ሚና ነው።ዜጎች ደግሞ ለተቀመጡ ግቦች መሳካት የራሳቸውን ጠጠር ይጥላሉ። ቀዳሚው ወታደራዊ አቅምን ማፈርጠም እና የደህንነት ተቋማት ብቃትን ማሳደግ ፣የምጣኔ ሀብት እድገትን አፋጣኝ ፖሊሲ ማውጣት እና መተግበር፣ወዳጅ እና አጋር ሀገራትን ማብዛት እና ግንኙነትን በመርህ ላይ ማጠናከር ፣የምንጊዜ ጥላትን አካሄድ ማጤን እና በየጊዜው ፈጣን አፀፋ መውሰድ፣ብሄራዊ ጥቅምን የሚገዳደሩ መንግስታት ወደ በትረ ስልጣን ሲመጡም ከወደጅ ሀገራት ጋር በመሆን የፖሊሲያቸውን አንካሳነት በዓለም አደባባይ መሞገት የሚሉ ናቸው።
ኢትዮጵያም ዛሬ ላይ ፓሪስ ስትጠራኝ እመጣለሁ ብለው ፡ፓሪስ አልተንበረከከችም እንዳሉት ታላቁ ደራሲ ፡መሪ ፡የጦር መኮንን ደጎል አይነት በሁሉም ዘርፎች የቁርጥ ቀን ልጆቿን ትሻለች::
ማስታወሻ ፤በስለአባት ማናዬ ( የዓባይ ፖለቲካ እና የባዕዳን ተልዕኮ እና የዓረብ መንግሥታት ስውር እጅ በዓባይ ላይ መጽሐፍት ደራሲ
__
በወቅታዊ ጉዳዮችም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ጽሁፍዎን በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት በሚከተለው አድራሻ ይላኩልን : info@borkena.com