
ሺፈራዉ አበበ
ሚያዚያ 14, 2013 ዓ.ም.
አገራችን የምትገኝበት የሰላምና የደህንነት ሁኔታ አሳዛኝና አሳሳቢ ነዉ። ለዚህ መንስኤ በሆኑ ኃይሎች ላይ ይደረግ የነበረዉ ዉግዘት ዉጤት ባለማስገኘቱ፣ በአሁኑ ጊዜ ወቀሳዉ፣ ክሱና፣ ዉግዘቱ፣ ለተፈጠረዉ ችግር በቂ መልስ ሊሰጥ ባልቻለዉ ጠ/ሚ እና በሚመራዉ የፌዴራል መንግስት ላይ የሚያነጣጥር ሆኗል።
በአንድ መሪ ላይ ክስም ሆነ ወቀሳ መሰንዘሩ፣ እንኳን በቀውስ ወቅት በአዘቦቱም አይቀሬ ነዉ። ከወቀሳም ሆነ ከክስ በላይ የሆነ መሪ ኖሮ አያዉቅም፣ ለወደፊትም አይኖርም። ጠ/ሚ አብይ ይህን እውነት ምን ያህል እንደሚረዳው አላዉቅም፣ ለወቀሳና ለጠፋ ነገር ኃላፊነት ለመውሰድ ያለዉ ተነሳሽነት ግን አነስተኛ እንደሆነ ልብ ማለት ይቻላል።
የክስ ወይም የወቀሳ መኖር የመልካም ስራ መኖርን መዘንጋት ወይም መሰረዝ ተደርጎ መታሰብ የለበትም። ጠ/ሚ አብይ ባለፉት ሶስት አመታት ያከናወናቸዉ በርካታ መልካም ድርጊቶች እንዳሉ መካድ አይቻልም።
አንዳንዶቹ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ተጠናቀዉ ዉጤታቸዉ የታየ ሲሆን፣ ሌሎቹ ደግሞ በመልካም ሂደት
ዉስጥ እንዳሉ መመስከር ይቻላል። የተደረጉ አንዳንድ ተቋማዊለዉጦች፣ ኢኮኖሚዉን ለመደገፍና ለማሳደግ የተደረጉ ጥረቶች፣ ከኤርትራ ጋር የተደረገዉ ስምምነትና የተገነባዉ
ዝምድና፣ የአባይ ግድብ ግንባታ የማፋጠን ሂደት፣ የአረንጓዴዉ አሻራና ማራኪ የሆኑ ፓርኮች ግንባታ ሊጠቀሱ የሚችሉ የጠ/ሚሩ አመራርና የግል ክህሎቶች የታየባቸዉ ክንዉኖችና ዉጤቶች ናቸዉ።
ወቀሳና ክስ የተለያዩ ናቸዉ። አንድ ግለሰብ፣ መሪ ወይም አካል ሲወቀስ ስህተቱን እንዲያርምና ለወደፊቱ የተሻለ ነገር እንዲያደርግ ታስቦ ነዉ። በተቃራኒዉ ክስ፣ የተፈጸመን ስህተት ሆን ተብሎ እንደተፈጸመ አድርጎ በመዉሰድ የሚደረግ ዉግዘትና (የፐብሊክ)ፍርድ ጥሪ ነዉ።
እኔ እንደሚገባኝ እጅግ በርካታ ኢትዮጵያዉያን (እኔን ጨምሮ) የሰላምና ደህንነት ችግርን አስመልክቶ በጠ ሚሩ ወይም የፌዴራል መንግስቱ ላይ የሚያሰሙት ስሞታና ወቀሳ አላማዉ (ሰሚ ቢኖር) የንጹሃንን ህይወት ለመታደግ በቂ እንቅስቃሴ እንዲደረግ ለማሳሰብ እንጂ ጠ/ሚሩንም ሆነ የፌዴራል መንግስቱን በመወንጀል ከዚያ የሚገኝን የፖለቲካ ግብ ለማራመድ አይደለም።
በግሌ፣ ጠሚ አብይ ሆን ብሎ አገርን፣ ወገንን የሚጎዳ ነገር ማድረግ ወይም መፍቀድ ቀርቶ ያልማልም ብዬ አላምንም።
ከዚህ አንጻር በሰሞኑ በአንዳንድ የአማራ ክልል ከተሞች የተደረጉ ሰልፎች ላይ የተያዙና የተሰሙ አንዳንድ መፈክሮች ከንደት መግለጫነት ያለፈ የጠ/ሚሩን ማንነት ይገልጻሉ ብዬ አላምንም።
ንዴቱ ግን እንዲሁ የተፈጠረ አይደለም። የአማራ ባለስልጣኖችን የገደለ ወንጀለኛን ፎቶ ተሸክሞ
እስከመዞር ያደረሰን ንዴት ማጣጣል ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል ብዬ አምናለሁ። መንግስትም የሰልፍ አደራጆች ላይ ከማተኮር ይልቅ ቁጣዉ እዚያ ደረጃ እንዲደርስ ያደረገዉም ዋናዉን ምክንያት ማከም ያስፈልገዋል ብዬ አምናለሁ።
አንዳንዶች አገሪቱ አጣብቂኝ ዉስጥ ባለችበት በአሁኑ ወቅት ጠ ሚሩን መዉቀስ የፌዴራል መንግስቱን በማዳከም፣ የአገሪቱን አንድነትና ሰላም ለማይፈልጉ ሃይሎች እንደመርዳት ወይም ለአገሪቱ መበታተን እንደማገዝ ይቆጠራል ይላሉ። በጥቃቅኑ ጉዳይ ሁሉ መጮህና በፌዴራል መንግስቱ ላይ
ስሞታ መቆለል ያስፈልጋል ብዬ ባላምንም፣ የመሪንም ሆነ የመንግስትን ስህተቶች መጠቆም አንዱ የአገር ወዳዶች ግዴታ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል። ጠ/ሚሩ ላይ ወቀሳ ወይም ሂስ ስለቀረበ አገር የምትበታተን ከሆነ፣
ይችን አይነት አገር ተራራ የሚያህል ሙገሳም አያጸናትም። የአገሪቱን አንድነት ሊበትኑ የተነሱ
ኃይሎች ላይ መንግስት ጠንካራ እርምጃ ለምን አይወስድም የሚል ወቀሳ መንግስትን ወይም
ጠ/ሚሩን የሚያደክም ከሆነ እንግዲያስ ያ ጠ/ሚርም ሆነ የሚመራዉ መንግስት በስልጣን ላይ መቆየት የለበትም።
እንደእኔ እምነት ግን ጠ/ሚሩ፣ የሚመራዉ መንግስትም ሆነ አገራችን በወቀሳና በክስ በትችትና በሂስ ሊሰበሩ ይችሉ የሚል ስጋት የለኝም።
ዶ/ር አብይ ስልጣን ከያዘ ማግስት ጀምሮ የሚሰነዘሩ አብዛኛዎቹ ክሶችም ሆነ ወቀሳዎች የሚገናኙት ከአንድ ጉዳይ ጋር ነዉ፤ ይኸዉም በአገሪቱ ዉስጥ የቀጠለዉ የጸጥታ መታወክና ያስከተላቸዉ የሰዉና የንብረት ዉድመት ነዉ። ይህ ችግር ደግሞ ህወሃት-ወያኔ የተወልን ወይም የዉጭ ጠላቶች ቀመሙልን የቤት ስራ ብቻ ሳይሆን፣
ባለፉት ሶስት አመታት መደረግ የነበረባቸዉ ነገሮች ካለመደረጋቸዉ የተነሳ የቀጠሉ ችግሮች ናቸዉ።
ለዚህም ጠ/ሚሩ መወቀስም፣ ሃላፊነት መዉሰድም አለበት ብዬ አምናለሁ።
የኢትዮጵያ የሰላም ችግር ምንጩ፣ የአገሪቱ ህገ-መንግስት የፈጠረዉ የፖለቲካና የአስተዳደር ስርአት ነዉ። ሌሎች የሚደረደሩ ምክንያቶች ቢኖሩ አንድም ማደናገሪያ ናቸዉ፣ ሌላም ሚናቸዉ ዉስን ነዉ። መፍትሄዉ ግን በአጭርና በረጅም ጊዜ ተከፍሎ የሚደረግ መሆን ይኖርበታል። በረጅሙ ጊዜ (ከምርጫ በኋላ በሚኖሩ አመታት) ህገ-መንግስቱ መቀየር/መከለስ ለዘላቂ ሰላም በቸኛዉ አማራጭ ነዉ። ይህን ተልእኮ ጠ/ሚሩም ሆነ የሚመራዉ የብልጽግና ፓርቲ ይፈጽመዋል ብሎ መጠበቅ አይቻልም። በህገ-መንግስቱ ጉዳይ ላይ ያላቸዉ አቋም ከህወሃት-ኢህአድግ የተለዬ እንዳልሆነ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። ስለዚህ የህገ-መንግስት ለዉጥ ለማየት የሚፈልጉ ኢትዮጵያዉያን ምርጫቸዉን ከዚያ አንፃር ያደርጋሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
ያም ሆነ ይህ፣ የህገ-መንግስት ማሻሻያ ዛሬ የሚደረገዉን የግፍ ግድያ ዉድመትና ዋይታ ለማስቆምና የአገሪቱን ህልዉና ከስጋት ለመታደግ አይደርስም። አሁን የሚያስፈልገዉ፣ መንግስት አሁን ባለዉ ህገመንግስት ጭምር የተደነገገዉን ሰላምን የማስከበር ሃላፊነቱ በአግባቡ ለመወጣት መቻሉ ነዉ። ስሞታና ወቀሳዉም ይህን ኃላፊነት መንግስት እየተወጣ አይደለም የሚል ነዉ።
1. በትግራይ ስላለዉ ጦርነት የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያዉቀዉ ጦርነቱ በሶስት ሳምንታት የተቋጨ መሆኑን ነበር። በቅርቡ ግን ያ ቀርቶ ጦርነቱ በስምንት ረድፍ እንደቀጠለ ጄ/ል ባጫ ደበሌ ገልጿል። ከሁሉም በላይ የትግራይ ወጣት ልብ መሸፈትና የተረፉ የህወሃት ተዋጊ ሃይሎችን ለመቀላቀል መፈለጉ የሰብአዊ ቀዉሱንና የወገን ስቃይ ያራዝመዋል፣ ከዉጭ ጫና ለመፍጠር ለሚያቆበቁቡ ኃይሎችም መልካም ሰበብ ይሆናል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የጠ/ሚሩ ወይም የመንግስት ክፍተት ጦርነቱ ስላለበት ሁኔታና በተለይም የትግራይ ህዝብ እያለፈበት ስላለዉ ችግር ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚሰጡት መግለጫ አለመኖሩ ነዉ። ጦርነቱ በትግራይ ህዝብና በሌላዉ ኢትዮጵያዊ መካከል የፈጠረዉን መራራቅ መካድ አይቻልም። ይህ መራራቅና መቃቃር ጊዜያዊ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ። ምንም ይሁን ምን፣ የትግራይ ህዝብ የኢትዮጵያ ህዝብ አካልና የነፍስ ክፋይ ስለሆነ፣ ያ ህዝብ ስለሚያልፍበት ሁኔታና ቀጣይ ምልከታዎች ለኢትዮጵያ ህዝብ ማስረዳት የጠ/ሚሩ ኃላፊነት ነዉ። ያን ሃላፊነት ግን በአግባቡ እየተወጣ ነዉ ማለት አይቻልም።
ከትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ የወልቃይትና የራያን እጣ ፋንታ ለመወሰን ለጊዜዉ መንግስት እየሄደበት ያለዉ አቅጣጫም ቀደም ሲል ህወሃት/ኢህአዲግ ያሰመረዉ አቅጣጫ ስለሆነ፣ ዉሎ አድሮ የሚፈነዳ ቦምብ እንደሆነ መገመት ቀላል ነዉ።
2. ከትግራይ ዉጭ በሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች ያለዉ የሰላምና የጸጥታ ሁኔታ እየተሻለዉ ሳይሆን
እየባሰበት እንደመጣ ከጠ/ሚሩ ዉጭ ሁሉም ልብ የሚለዉ ይመስለኛል። ባለፉት ስድስት ወራት
እንኳ በምእራብና ምስራቅ ወለጋ፣ በመተከል፣
በቻግኒ፣ በጉራ ፈርዳ፣ አሁን ሰሞኑን ደግሞ በአጣየና አጎራባች ከተሞች የተፈጸሙት ግድያዎች፣
የንብረት ዉድመቶች፣ መፈናቀሎችና የንጹህ ኢትዮጵያዉያን ስቃዮች በእዉነት
የደህንነትና የጦር ሃይል ያለዉ መንግስት በሚኖርበት አገር ይፈጠራል ብሎ ለመገመት ይቻላል።
ሁሉም ቦታዎች ሊባል በሚችል መልኩ የተፈጠረዉ እልቂት የመጀመሪያ ጊዜ አለመሆኑን
ልብ ስንል ደግሞ በመንግስት ላይ የሚደረገዉን ወቀሳና ሂስ ይበልጥ አግባብ ያለዉ ያደርገዋል።
3. ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ከጎጃምና ወለጋ በተወሰደ መሬት ህወሃት-ወያኔ የፈጠረዉ ክልል ነዉ። በዚህ ክልል የሚገደሉት የአማራ፣ የአገዉና የሺናሻ ማህበረሰቦች በቁጥር አናሳ አይደሉም። ገዳዮቹ ወጡበት ከሚባለዉ የጉሙዝ ብሄረሰብ ጋር ሲወዳደር የአማራዉ ቁጥር ከፍተኛ ነዉ። ግድያ አድራጊዎቹ በቁጥር የበዙት ላይ መጠነ ሰፊ ጭፍጨፋና ማፈናቀል የሚያደርጉት የክልሉ መስተዳድር በግልጽም ሆነ በድብቅ በሚያደርገዉ ድጋፍ እንደሆነ ብዙ ማስረጃ ቀርቧል። ወቀሳዉ የፌዴራል መንግስቱ አስቸኳይ እርምጃ በመዉሰድ ተጠቂዎችን ከተቀነባበረ ግድያ ሊታደጋቸዉ አልቻለም የሚል ነዉ። አግባብም ያለዉ ወቀሳ ነዉ። የመንግስት ዳተኝነት ሰዎች በቀልን በእጃቸዉ ዉስጥ እንዲያስገቡ በማድረግ በቅርቡ በቻግኒ የታየዉ አይነት ጸያፍ የደቦ ፍርድ እንዲታይ ያደርጋል።
4. በኦሮሚያ ለሶስት አመታት የዘለቀዉ የኦሮሞ ብሄረተኞች ተግዳሮት የጠ/ሚሩ የአመራር ድክመት ዋናዉ መገለጫ ነዉ ማለት ይቻላል። የዛሬ አንድ አመት ግድም በሻሸመኔ፣ በዝዋይ፣ በጅማ፣ በአሩሲ ነገሌና ሌሎች ቦታዎች በተመሳሳይ ወቅት የደረሰዉ መጠነ ሰፊ ግድያ፣
የሰዉ ጉዳትና የንብረት መዉደም በታሪክ ሊረሳ የሚችል አይደለም። ታዲያ ያን ያዬ መሪና መንግስት፣
ሰሞኑን በአጣዬ ከተማ ላይ ከወረደዉ ጥፋት እጁን እንደጲላጦስ አጥቦ ወንጀሉን ሁሉ ኦነግ-ሸኔ ላይ ሊጭን ይቻለዋል? የኦሮሞ ብሄረተኝነት ስትራቴጂ የአማራዉን ማህበረሰብ በብሶት እንዲነሳ በማድረግ የፌደራል መንግስትን አቅም
ማሽመድመድ ነዉ። የዚህ ስትራቴጂ ግብ ምንም ይሁን ምን፣ በመጨረሻዉ ይሳካም፣ አይሳካም፣
በአሁኑ ወቅት ስትራቴጂዉ እየሰራ እንደሆነ እንኳን የአገሪቱ መሪ የሩቅ ተመልካችም ልብ ሊለዉ
የሚችል ገሃድ እዉነት ነዉ። ከዚህ አደጋ አንጻር ጠ/ሚሩ የሚሰጠዉ አመራር ዘገምተኛና ደካማ
መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የተገላቢጦሽ የጠ/ሚሩ የዛሬ ማስጠንቀቂያ ያነጣጠረዉ
በንጹሃን ሞት ተቆጭተዉ የእሱንና የመንግስትን ድክመት ለመግለጽ ሰልፍ የወጡ ወጣቶች ላይ ነዉ።
የኦሮሚያ ብሄረተኝነትን አፍራሽ ተልእኮ ልዩ የሚያደርገዉ፣ ጠ/ሚሩ የፈለቀበት የኦሮሚያ ብልጽግናና የኦሮሚያ መስተዳድር ባለስልጣኖች ጭምር የተነከሩበት መሆኑ ነዉ። ከዚህ አንጻር የሚነሳዉ ጥያቄ፣ ጠ/ሚሩ እነዚህን በስሩ ያደሩ ከፍተኛና ምንዝር ባለስልጣኖች ልክ ለማስገባት አቅም አለዉ ወይስ በተቃራኒዉ በእነሱ ፈቃድ ስር የሚመላለስ የምስል መሪ ነዉ የሚለዉ ነዉ። የስልጣን ሚዛኑ ምንም ይሁን ምን፣ እንደአገር መሪ፣ ጠ/ሚሩ ያሉት አማራጮች ግን እየጠበቡ ሄደዉ አሁን የቀሩት ሁለት ብቻ ናቸዉ። እነሱም አንድም የኢትዮጵያን አንድነት ከሁሉም በላይ በማስቀደም፣ ያለዉን ሃይል አስተባብሮ የኦሮሞ ብሄረተኝነትን በማያሻማ መንገድ ልክ እንዲኖረዉ ማድረግ፤ አልያም በስልጣኑ ስር ያለች አገር በኦሮሞ ብሄረተኞች ታምሳ ወደእርስ በርስ ጦርነት ስትሄድ መመልከትና የታሪክ ተወቃሽ መሆን ነዉ።
ሃይለማርያም ደሳለኝ የወያኔን ትእዛዝ ለስድስት አመታት ሲፈጽም ኖሮ በመጨረሻዉ ግን መስመሩን ከለዉጥ ፈላጊዎች ጋር እንዳደረገ ይነገርለታል። ጠ/ሚ አብይ ከሃይለማርያም የተሻለ የአመራር ልቦና እና ሰፊ የሚባል የማህበረሰብ ድጋፍ ያለዉ መሪ ስለሆነ ሃይለማርያም ካደረገዉ የተሻለ እንጂ ያነሰ እንዲያደርግ አይጠበቅበትም።
ለዉጡ የመጣዉ በወጣቶች ደም ነዉ። በኢህአድግ ዉስጥ ሆነዉ ለዉጡን የመሩት ሰዎች፣ ጠ/ሚሩን ጨምሮ፣ ነፍሳችን ለአደጋ ተጋልጣ ነበር ቢሉምና ምናልባትም ይህ አባባል እዉነትነት
ቢኖረዉም እንኳ፣ ከመካከላቸዉ አንዳቸዉም የህይወት መጥፋት ቀርቶ የአንድ ሌሊት እስር ሳያዩ አሁን
ለያዙት ስልጣን እንደበቁ ሊያስታዉሱ ይገባል። ታዲያ የብዙ ወጣቶች ደም ፈሶ፣ የብዙዎች አካል ጎድሎ፣
ብዙዎች በእስር ማቀዉ፣ የተረፉት ተሰደዉ የመጣዉን ለዉጥ የተረከቡት ሰዎች፣ ዳግም የወጣትም ሆነ የአረጋዊ፣ የወንድም ሆነ የሴቶች ደም እንዳይፈስ
ቃል ገብተዉ ስለሆነ፣ ቢዘገይም ቃላቸዉን ያስታዉሱ ዘንድ፣ ለጠፋዉ የሰዉ ህይወት፣
ለወደመዉ ንብረት፣ ለባከነዉ ጊዜ የሚያካክስ ስራ በፍጥነት እንዲሰሩ፣
ጥሪዉ ከምንጊዜዉ ጎልቶ ከሁሉም አቅጣጫ እየተደረገ ነዉ። ይህን ለማድረግ ቢንቀሳቀሱ አብዛኛዉ ኢትዮጵያዊ ከጎናቸዉ ይሰለፋል። ይህን ባያደርጉ ግን ትናንትና ዛሬ ንጹሃንን ያጠፋ የብሄርተኝነት ጋኔን ነገ እነሱንም አይምራቸዉም።
በመጨረሻ፦ ጠ/ሚሩ በተለያዩ ጊዜያት በሰላምና ጸጥታ የማስከበር ሂደት ዉስጥ ስለሚሞቱና ስለሚቆስሉ የመከላከያና ደህንነት ሃይሎች (የክልል ልዩ ሃይሎችን ጨምሮ) ሲናገር ተሰምቷል፣ አግባብም ነዉ። እስካሁን ሃዘንን መግለጽ ቀርቶ አፉን ሞልቶ ሲናገር ተሰምቶ የማያዉቀዉ በግፈኛ ብሄረተኞች ያለአበሳቸዉ፣ በማያዉቁት ፖለቲካ እንደከብት እየታጎሩ ወይም እንደአዉሬ እየታደኑ ስለሚገደሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ኢትዮጵያዉያን ነዉ። ለዚህም ነዉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጠ/ሚሩ ርህራሄ ወይም አዘኔታ የተለየዉ መሪ ነዉ የሚል ትችት የሚሰነዘረዉ። አንድ የአገር መሪ በስልጣን እስካለ ድረስ ራሱን እንደአገር አባት አድርጎ ማየትና በታላቅ ደስታም ሆነ በታላቅ ሃዘን ወቅት የህዝቡን ስሜት መጋራት፣ መግለጽ የስራ ድርሻዉ እንደሆነ መረዳት አለበት። ታዲያ ብልጽግናዉ ለማን ነዉ? ህልሙና ከፍታዉ ለማን ነዉ? ለአፍሪካ? ለስታቲስቲክስ? ለዝና? ረጋ ብሎ ሊያስብ ይገባዋል።
ጠ/ሚ አብይ የሚሰማዉ መካሪ ካለ፣ ቢዘገይም፣ የመምከሪያዉ ወቅት አሁን ነዉ። በአገሪቱ ዉስጥ እየባሰ ስለመጣዉ የሰላምና የደህንነት ቀዉስና የመዉጫ መንገድ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ለኢትዮጵያ ህዝብ ማብራሪያ መስጠት አለበት። እግረ-መንገዱንም እስካሁን በእሱ ስልጣን ስር ለደረሰዉ ግድያ፣ ዉድመትና ሰቆቃ ይቅርታ መጠየቅ፣ ለተጎዱ ቤተሰቦች ሃዘኑን መግለጽና፤ የተፈናቀሉና ንብረታቸዉ ለወደመባቸዉ ወገኖች መንግስት ህዝቡን አሰተባብሮ ስለሚያደርገዉ እርዳታ መናገር አለበት።
ህዝብ አንድን መሪ የሚያከብረዉ መሪዉ ህዝቡን ሲያከብር ነዉ። ህዝቡን ከስጋት ለማረጋጋት የማይሞክር ጠ/ሚ እንዴት ነዉ የህዝብን ከበሬታ የሚያገኘዉ? ለተጎዱ ቤተሰቦች የማስተዛዘኛ መልእክት ለማስተላለፍ የሚቸገር መሪ እንዴት ነዉ የዚያ ህዝብ ልብ ሊይዝ የሚችለዉ? የጠ/ሚሩ ዝምታ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ከዘገየ ግን ንቄት ተደርጎ ነዉ የሚወሰደዉ። ያ ከሆነ ደግሞ፣ የናቀ መልሶ መናቁን ዉሎ ሳይድር እያየነዉ ነዉ። የዛሬ ሶስት አመት የጠ/ሚሩ ፎቶ የታተተመበት ቲ-ሸርት እንደብርቅ ይለብስ የነበረ ወጣት ዛሬ በአደባባይ የተሰቀለ ፎቶዉን ቀዳዶ ሲጥል እያየን ነዉ።
እግዚአብሄር ቸር ያስመክር!
__
በወቅታዊ ጉዳዮችም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ጽሁፍዎን በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት በሚከተለው አድራሻ ይላኩልን : info@borkena.com