spot_img
Tuesday, October 3, 2023
Homeነፃ አስተያየት“ያልነቃው አንቂ” በሕዝባችን ደም መነገድ ያቁም! ክፍል አንድ

“ያልነቃው አንቂ” በሕዝባችን ደም መነገድ ያቁም! ክፍል አንድ

advertisement

ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ 
ሚያዚያ 16 ቀን 2013

ከሁሉ አስቀድሜ፤ በተለያዩ አካባቢዎች፤ በወኖቻችን ላይ የተፈፀመው እና እየተፈፀመ ባለው ጭፍጨፋ የተሰማኝን ልብ የሚሰብር ጥልቅ ሃዘን እገልፃለሁ። ቸሩ እግዚአብሔር ነፍሳቸውን በአፀደ ገነት ያኑር። ቤተሰብን ወዳጅ ዘመድን፤ እንዲሁም መላው ሕዝባችንን፤ እግዚአብሄር ያጽናና።

ሽብርተኝነት የሕሊና ጦርነት ነው። አሸባሪዎች፤ ፍርሃት፣ አለመረጋጋት፣ እንዲሁም በማህበረሰባችን ክፍፍል በመፍጠር ሊቆጣጠሩን እና ባሕሪያችንን እንድንቀይር ለማድረግ ይሞክራሉ።ፓትሪክ ኬነዲ

እንደ አውሮፓ አቆጣጠር፤ በታኅሳስ 2008፣ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት፤ ዳግማዊ ጆርጅ ቡሽ፤ ኢራቅን በጎበኙበት ወቅት፤ በኢራቃውያን፤ ከፍተኛ ፀረ አሜሪካ እና ጆርጅ ቡሽ የተቃውሞ ሰልፍ ተድርጎ፤ነበር። በዚህ ሰልፍ የተገረሙ ጋዜጠኞች፤ ጆርጅ ቡሽን እንዲህ ሲሉ ጠየቋቸው። “ኢራቅን ከሳዳም ሁሴን አገዛዝ ነፃ አውጥተው፤ ሕዝቡ ደስተኛ መሆን ሲገባው፤ በእርሶ እና በመንግስቶ ላይ የተቃውሞ ሰልፍ በማድረጉ ምን ተሰማዎ የሚል። የእሳቸውም መልስ ያልተጠበቀ እና አስገራሚ ነበር። ሲመልሱም እንዲህ አሉ። “ይህንን የተቃውሞ ሰልፍ በዓይኔ ለማየት በመቻሌ በጣም ነው ደስ ያለኝ፤ እኛ እኮ የኢራቅን ሕዝብ ነፃ ያወጣነው፤ ሕዝቡ በነፃነት፤ በአደባባይ ወጥቶ ስሜቱን እንዲገልጽ ነው፤ ይህ ለሰራነው ሥራ ጥሩ ምስክርነት ነው።”

ይህ የጆርጅ ቡሽ መልስ፤ በተለይ ለዶ/ር ዐብይ መንግሥት ደጋፊዎች፤ ከፍተኛ መልእክት አለው። ሰሞኑን በአማራ ክልል በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ፤ በርካታ የዶ/ር ዐብይ ደጋፊዎች፤ ቅሬታቸውን ሲገልፁ አስተውያለሁ። ምንም እንኳን በአማራው ወገናችን ላይ በሽብርተኞች የሚደርሰውን ጥቃት ለማውገዝ እና መንግሥት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ ለመጠየቅ የተዘጋጀ ሰልፍ ቢሆንም፤ አንዳንድ ጽንፈኛ ግለስቦች እና የፖለቲካ ስብስቦች፤ የሰልፉን ዓላማ ለማስቀየር እና በየከተሞች ነውጥ ለመፍጠር ያልተሳካ ሙከራ ማድረጋቸው ሊኮነነ ቢገባውም፤ ሰልፉ፤ ሃገራችን፤ ባለፉት ጥቂት አመታት በመጣው ለውጥ ምን ያክል እንደተራመደች የሚያሳይ ነው። ከጥቂት ዓመታት በፊት እንዲህ ዓይነት ሰልፎች፤ ሰላማዊ ሰዎች ሳይገደሉ ወይም ሳይታሰሩና ሳይጎዱ ይጠናቀቃል ብሎ ማሰብ የማይቻል ነበር። ብዙዎቻችንም፤ ባለችን አቅም ለዓመታት የጮኽነው እና በርካቶች መስዋዕትነት የከፈሉት፤ የሕዝቡ ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲጠበቁ በመሆኑ፤ በተለይ የፀጥታ ዘርፉ ያሳየው፤ ዲስፕሊን ሊመሰግን እና ሊበረታታ ይገባዋል። መልመድ ያለብን፤ የተለዩ እና ተቃዋሚ ሃሳቦችን በስርአት ማስተናገድን ነው። በሃሳብ ስለተለያየን፤ በጠላትነት መተያየት አለብን ማለት አይደለም። በሃሳብ ልዩነቶቻችን ተከባብረን፤ስንደማመጥ እና ለሃገር በትጋት ስንሰራ ነው ሃገራችንን መለወጥ፤ የዲሞክራሲያዊ ሥርዐት መሰረት ልንጥል የምንችለው።  

ዋናው ችግር፤ “የእናት ሆድ ዥንጉርጉር ነው እንዲሉ” ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቅን አሳቢ ባለመሆኑ እና ከሕዝብና ከሃገር ጥቅም ይልቅ፤ የራሳቸውን እና የጥቂት ስብስቦችን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚተጉ በሚከተሉትም አደገኛ አቅጣጫ፤ ሃገር እና ሕዝብ የሚጎዱ በመሆናቸው፤ መንገዳችን ላይ ብዙ ጋሬጣ ይኖራል። እንደ ሁልጊዜውም ግን፤ በበጎ ዓላማ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎችን የሚጠልፉ እና ለራሳቸው እኩይ ዓላማ ለማዋል የሚፈልጉ ሃይሎች በመኖራቸው፤ ለሃገራችን የዲሞክራሲ ባሕል እድገት ፈተና መሆናቸው አይቀርም። እነዚህን ሃይሎች ደግሞ በምንችለው አቅም ሁሉ ልንሞግታቸው እና በሕዝባችን ደም መነገዱን አቁሙ ልንላቸው ይገባል። በተለይም፤ ለሕዝብ ቆመናል የሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ለሃገራችን አለን የሚሉትን ፍኖተ ካርታ በግልጽ በማቅረብ፤ በሰላማዊ መንገድ የሚፈልጉትን ለማሳካት መሞክር አለባቸው እንጂ፤ የሕዝብን ብሶት በመንጠቅ፤ ለእኩይ የፖለቲካ አላማቸው መሳካት ነውጥ ሲፈጥሩ እና ነውጥ ለመፍጠር ሲሞክሩ፤ ማንም ሃገሩን የሚወድ ዜጋ በዝምታ ሊያልፋቸው አይገባም። እነዚህ ሃይሎች፤ ሊመከሩ፤ ሊገሰፁ እና እርምት እንዲያደርጉ ግፊት መደርግ ይኖርበታል። ከዚህ ቀደም ተደጋግሞ እንደተገለፀው፤ ሕዝቡ ባልመረጣቸው “ገዥዎች” ተረግጦ የሚገዛበት ጊዜ አብቅቷል። ለዚህም ነው መጪው ምርጫ፤ ለሃገራችን የወደፊት እርምጃ  ወሳኝነት የሚኖረው።  

በአማራው ወገናችን ላይ እየደረስ ያለው አስከፊ ጭፍጨፋ፤ ሊያስቆጣ የሚገባው ሁላችንንም ነው። ይህ ጥቃት፤ ሃገር ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ነው። ይህንን አሳዛኝ እና አረመኔያዊ ክስተት ደግሞ ለአለጥቂት ጽንፈኛ ኃይሎች የፖለቲካ ትርፍ መጠቀሚያ ለማድረግ መሞከር፤ እና በሕዝቡ ደም መነገድ፤ እራሱን የቻለ ወንጀል ነው። ሃገራቸን አሁን የደርሰችበት ቦታ ላይ የደረሰቸው በርካታ ፈተናዎችን አልፋ እና ለዚህም ከፍተኛ የሕይወት መስዋዕትነት ተከፍሎ ነው። የግጭት አዙሪቱን በመስበር፤ በሃሳብ ፍጭት፤ ሥልጣን በሰላም የሚሸጋገርበትን ጥርጊያ መንገድ ማዘጋጀት፤ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን፤ የሁሉም ዜጋ ሃላፊነት ነው። ይህቺ ሃገር የሁላችን እንጂ፤ የአንድ ሰው ወይም የአንድ ፓርቲ አይደለችም። ኢትዮጵያ በርካታ ጥሩ አጋጣሚዎችን አግኝታ አልተጠቀምንባቸውም። ብዙውን ጊዜም ሃገራችን የቆመችባቸውን መንታ መንገዶች በማየት፤ የሥልጣን ጥመኞች እና ጽንፈኛ ሃይሎች፤ በተደጋጋሚ ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ መርተዋታል። ዛሬም፤ በአማራ ክልል ተደርጎ የነበርውን ሰላማዊ ሰልፍ ለመጥለፍ ብቅ ያሉት ጽንፈኛ ሃይሎች፤ ከዚህ የተለየ ዓላማ የላቸውም። እንደ ትላንትናዎቹ መሰሎቻቸው፤ታሪክን በማጣመመ፤ ያለፍንባቸውን ፈተናዎች በማሳነስ እና የአሁኑን በማጋነን፤ ለሃገር በቅንነት እና በትጋት የሚሰሩ ብርቅዬ ዜጎችን፤ መሃል መንገድ ላይ ጠልፈው መና በማስቀረት፤ እነሱ በአቋራጫ ወደ ሥልጣን ለመምጣት ያለሙበት እኩይ ሕልም ነበር።

እነዚህ ጽንፈኛ ሃይሎች፤ በነውጥ ወደ መንበረ ሥልጣን ለመምጣት ሲሞክሩ የመጀመሪያቸው አይደለም የመጨረሻቸውም አይሆንም። በተደጋጋሚ፤ ባልተገራ አንደበታቸው በሚለቁት የመግለጫ ጋጋት፤ በርካታ ትንኮሳዎችን ሲያካሄዱም አይተናል። በየትም ሃገር መንግሥት በዝምታ ሊታለፉ የማይችሉ ተንኳሽ መግለጫዎችን፤ መንግሥት በትዕግስት ሲያልፈው አይተናል። የትኛውም፤ ሃገርን ለመምራት እችላለሁ ብሎ በፖለቲካ መድረክ የሚሳተፍ የፖለቲካ ድርጅት፤ የአሜሪካንን ፕሬዝዳንት ወይም የየትኛውነም አውሮፓ ውስጥ ያለ ሃገር መሪ፤ ያለምንም መረጃ፤ መሪው ከሽብርተኞች ጋር ተመሳጥሮ ይሰራል ብሎ ቢወነጅል፤ በዝምታ አይታለፍም። ዛሬ ሃገራችን ካለችበት አደገኛ የፖለቲካ ድባብ አንፃር ግን፤ እነዚህ የፖለቲካ ሃይሎች ላይ፤ መንግሥት እርምጃ ቢወስድ፤ ሊፈጠር የሚችለውን የፖለቲካ ቀውስ ማሰብ አያዳግትም። የእነሱም ተስፋ፤ በሚፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ እና ግርግር፤ ወደ ሥልጣን ለመምጣት ነው። የእነዚህ ሃይሎች ትንኮሳ ነውጥ ቢፈጥር፤ እየተካሄደ ካለው የሽብርተኞች ጥቃት ጋር ተደምሮ፤ ሊያስከትል የሚችለውን ደም መፋሰስ መገመት አያዳግትም። እንደውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው ጨዋና ታላቅ ሕዝብ በመሆኑ እንጂ፤ እንደ ጠላቶቻችን ትጋት እና ፍላጎት የእልቂት ድግስ ቢሆን ኖሮ፤ ኢትዮጵያ ቀዳማዊት የመን በሆነች ነበር።

በተለይም፤ ሕወሃት የኢትዮጵያ ሰራዊት ላይ ጦርነት ከፍቶ አይቀጡ ቅጣት ከተቀጣ በሁላ፤ በሃገራችን በተለያዩ አካባቢዎች፤ በተለይም በአማራው ወገናችን ላይ የሚደረግው ጥቃት ጠንክሮ ቀጥሏል። ይህንንም ለመመከት፤ መንግሥት የሚቻለውን ጥረት እያደረገ እና፤ የፖሊስ እና መከላከያ አባላትም የሕይወት ዋጋ እየከፈሉ ይገኛሉ። ይህ መሬት ላይ ያለው ሃቅ ነው። ይህንን መስዋዕትነት ፋይዳ ለማሳጣት፤ ጽንፈኝ አሃይሎች፤ መንግሥት እጁን አጣጥፎ እንደተቀመጠ የሚሰብኩት ስብከት እና  ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ በተደጋጋሚ የምንሰማው፤ እራሳቸው ባልነቁ ግን “አንቂ ነን” በሚሉ ጽንፈኛ ኃይሎች የሚሰበከው የሃሰት ስብከት፤ ‘ኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነት ፈተና አጋጥሟት አያውቅም’ የሚል ነው። ከዛም አልፎ፤ የሃገሪቱ መሪ ሳይቀሩ፤ ከሽብርተኞች ጋር ተመሳጥረዋል የሚል የሃሰት ክስ ይሰነዝራሉ። “ኦሮሞው አማራውን ከምድር ላይ ለማጥፋት” ፍላጎት እንዳለው አድርግወም ይደሰኩራሉ። ይህ ሃስት መሁኑ ሳይገባቸው ቀርቶ ግን አይደለም። ዓላማቸው፤ በዚህ በሃዘን እና ቁጣ ስሜት ውስጥ ያለውን ሕዝብ ስሜት “በመኮርኮር” ሕዝብን በሕዝብ ላይ በማነሳሳት፤ በመንግሥት ላይ እምነት እንዲያጣ እና እነሱም ወደ የሚናፍቁት ስልጣን በግርግር ለመምጣት ነው።

ታሪካችን የሚያስተምረን ግን፤ ሃገራችን ከዚህ ጊዜ የባሰ ሞት፤ መፈናቀል እና ውድመትን አልፋለች። በ1970 እና በ1980ዎቹ፤ በወያኔ እና ሻዕብያ፤ እንዲሁም ጠፍጠፍው በፈጠሯቸው ድርጅቶች፤ በርካታ ዘር ተኮር ግድያዎችን አስተናግዳለች። ያኔ እንደዛሬው የማህበራዊ ሚድያ ስላልነበረ፤ ፍጅቱ እንደአሁኑ ገኖ አልተነገረለትም። በ1990ዎቹም በአማራው ወገናችን ላይ፤ በአርባጉጉ፤ በበደኖ፤ በአርሲ፤ በሃረር፤ ወዘተ ከፍተኛ ጭፍጨፋዎች ተፈጽመዋል። በዘመነ ወያኔም፤ በአማራው፤ በጋምቤላው፤ በኦሮሞው፤ ወላይታው፤ አፋር፤ ሶማሌና ሌሎች ወገኖቻችንም ላይ ከፍተኛ ጭፍጨፋ ተካሂዷል።  በቀይ ሽብር እና በነጭ ሽብር እንኳን ከ500 ሺህ በላይ ወገኖቻችንን አጥተናል። የግጭት አዙሪት በፈጠረው ጠኔም በሚሊዮን የሚቆጠር ወገናችን በረሃብ ተሰቃይቶ ሞቷል፤ ከቀዬውም በሚሊዮን የሚቆጠር ተፈናቅሏል። ለእነዚህ የእርስ በእርስ ግጭቶቻችን እና የሕይወት እና ንብረት ውድመት፤ ዋና አቀናባሪው፤ የሃገራችን ታሪካዊ ጠላቶች የሆኑ ሃገራት ይሁኑ እንጂ፤ የእነሱን ዓላማ ለማስፈፀም የውድመቱ ተባባሪ የሆኑ የራሳችን ወገኖች ናቸው።

ዛሬም ሃገራችን ያጋጠማት ፈተና፤ ላለፉት 50 ዓመታት እየተንከባለለ የመጣ እንጂ፤ ዐብይ አሕመድ የፈጠሩት፤ ፈተና አይደለም። ዛሬ ያጋጠመን ፈተናም ካለፉት ፈተናዎቻችን አይበልጥም። ልዩነቱ ግን፤ ዛሬ ተናጋሪው፤ ብዙ ነው፤ በወገኖቻችን ደም ለመነገድ እና ሳንቲም ለማትረፍ ያኮኮበው ሃይል ብዙ ነው፤ በዚህም ምክንያት ብዙው ነገር ገኖ እና ተቀናብሮ የሚቀርብ በመሆኑ፤ ፈተናውን ከዚህ በፊት ከነበረው የከፋ አስመስሎታል። በአማራው ሕዝባችንም ሆነ በሌላው ኢትዮጵያዊ ወገናችን ላይ የሚደርስ ጥቃትን መከላከል የመንግሥት ሃላፊነት ነው። ይህ ማለት ግን፤ መንግሥት ሁል ጊዜ በፍጠነት እና በአጭር ጊዜ የሽብርተኞችን ጥቃት ማስቆም ይችላል ማለት አይደለም። በአለማችን፤ የሽብር ጥቃትን በመከላከል ድንቅ የሚባሉ እንደ እስራኤል ዓይነት ሃገር እንኳን፤ እስራኤላውያንን ሙሉ ለሙሉ ከሽብረተኞች ጥቃት ለመታደግ አልቻለችም። በናይጄሪያና በኬንያም ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃቶች ተፈጽመዋል፤ እየተፈጸሙም ነው። ናይጄሪያ፤ ከ1960ዎቹ ጀምሮ እስካሁንድረስ ከሽብርተኞች ጋር እየተፋለመች ነው። ሽብርተኝነትን በማጥናት ከፍተኛ ሙያ ያላቸው ሰዎች፤ ሽብርተኝነትን መዋጋት ምን ያክል አስቸጋሪ መሆኑን ደጋግመው ገልፀዋል። ይህ ችግር ለኢትዮጵያም ከባድ ፈተና መሆኑ እና የሁላችንንም የተቀናጀ ትግል እንደሚጠይቅ ልንገነዘብ ይገባል።

አንድ መታወቅ ያለበት ነገር፤ ዛሬ በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለው ተጋድሎ ከሽብርተኞች ጋር ነው። እነዚህ ሽብርተኞች፤ በግል እና በቡድን የሚንቀሳቀሱ፤ በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚኖሩ፤ አንዳንዴም በሥልጣን ላይ ባሉ ጽንፈኞች የሚታገዙ ናቸው። እነዚህን ሰዎች ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመለየት እና ማንነታቸውን ለማወቅ አይቻልም። ለሽብርተኞች መረጃ በማቀበል የሚያግዙ መንግሥት ውስጥ የተሰገሰጉ ሃይሎችም ይኖራሉ፤ እነዚህንም በአጭር ጊዜ እና በፍጥነት ለመለየት አዳጋች ነው። ብዙዎች በሥልጣን ላይ ያሉት፤ እና በየምክር ቤቱ የተሰገሰጉት፤ በቂ ችሎታ የሌላቸው፤ ለገዢው ፓርቲ “ታማኝ” በመሆናቸው ብቻ፤ በሥልጣን ላይ የተቀመጡ ናቸው። እነዚህን ሰዎች፤ ከማይመጥናቸው ሥልጣን ላይ ለማንሳት፤ ምርጫው አስፈላጊ እና ወሳኝ ነው። በ2007 (2015 እንደ አውሮፓ አቆጣጠር) በተጭበረበረ ምርጫ ሥልጣን የያዙትን የፖለቲካ ኃይሎች፤ ተዓማኒነት ባለው ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ስንቀይራቸው ነው፤ ሃገራችን፤ በተረጋጋ ሁኔታ፤ ወደፊት መራመድ የምትችለው። በሕዝብ ያልተመረጠን የፖለቲካ ኃይል፤ በሕዝብ ባልተመረጠ የፖለቲካ ኃይል መተካት፤ “ታጥቦ ጭቃ ከመሆን” ባለፈ፤ ምንም ፋይዳ አይኖረውም።   

ክፍል ሁለት ይቀጥላል።

___
በወቅታዊ ጉዳዮችም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ጽሁፍዎን በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት በሚከተለው አድራሻ ይላኩልን : info@borkena.com

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
13,723FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here