ከጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ
ሰኔ 23 ቀን 2013
“ሽማግሌዎች ጦርነትን ያውጃሉ፤ መዋጋት ያለበት እና የሚሞተው ግን ወጣቱ ነው”31ኛው የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ሐርበርት ሁቨር።
ከሶስት ሳምንታት ገደማ በፊት፤ ከባለቤቴ ጋር በሃገር ጉዳይ ስንወያይ፤ አንድ ያነሳሁት ሃሳብ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ተኩስ በማቆም፤ለትግራይ ሕዝብ ከኢትዮጵያ የመገንጠል ወይም፤ ከኢትዮጵያ ጋር የመቀጠል፤ የሕዝበ ውሣኔ እድል እንዲሰጥ የሚል ነበር። ይህንንም ነገር ከኮንግረስ ጄምስ ራስክን ቢሮ ጋር ውይይት ባደረግኩበት ወቅት አንስቼ ተውያይቼበታለሁ። ይህን ሃሳብ እንዳነሳ ያደረገኝ፤ በጦርነቱ መራዘም ምክንያት በትግራይ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ስቃይ እና፤ እያንዳንዱን ወንጀለኛ ለመያዝ በሚካሄደው ዘመቻ፤ በሰራዊቱ እና በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚደርሰው ሞት አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ ነው። ከራሱ ሌላ ለሕዝብ ደንታ የሌለው ሽብርተኛው የሕወሃት ቡድን፤ ለኢትዮጵያ ራስ ምታት ከሆነ ግማሽ ምዕተ ዓመት ሊቆጠር የቀረው ጊዜ ትንሽ ነው። ሕዝቡም የዚህ ፀረ ሕዝብ ሃይል የፕሮፖጋንዳ ሰለባ የሆነ በመሆኑ፤ ከፊሉም በፍርሃት በመሸበቡ፤ ሌላው ደግሞ፤ ልጆቹ፤ ወንድምና እህቶቹ፤ በመሆናቸው እና ከቀሪውም ጋር በሥጋና ጋብቻ ዝምድና እና በዘር የተጋመደ በመሆኑ፤ የፈለገ ዓይነት በደል ቢፈጽም፤ ሕዝቡ ሕወሃትን ከጉያው አውጥቶ ሊጥለው ስለማይፈልግ፤ ጦርነቱ፤ ከወያኔ ጋር ብቻ መሆኑ ቀርቶ ሕዝቡ ውስጥ ከተሰገሰገው ደጋፊ ሃይል ጋር ነበር። ይህ ማቆምያ የሌለው ጦርነት ውስጥ መቀጠል፤ ለማንም የማይበጅ መሆኑን በመገመት፤ እንዲሁም፤ አብዛኛው የትግራይ ሕዝብ፤ ለኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትና ለሃገሪቱ ሕግ ያለመገዛት ዝንባሌ ከማሳየቱም በላይ፤ በኢትዮጵያ መንግስት እና በተለይም በአማራው ሕዝብ ላይ፤ ጥላቻን እያጎለበተ በመምጣቱ፤ ትግራይ፤ እንደ ቀድሞው ከኢትዮጵያ ጋር፤ ለሕግ ተገዢ ሆኖ ለመቀጠል ወይም ላለመቀጠል ሕዝቡ እንዲወስን ቢደረግ ይበጃል ብዬ አምናለሁ።
በዚህ ጦርነት እና ከጦርነቱም በፊት፤ በትግራይ ሕዝብ ላይ በሕወሃት የተፈፀመውን በደል እና ግፍ፤ ቤቱ ይቁጠረው። አንድ ሊሰመርበት የሚገባው ነገር፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ግጭት ውስጥ የገባው ወዶ ሳይሆን ተገዶ ነው። ማንም ሃላፊነት የሚሰማው መንግሥት ሰራዊቱ ተጨፍጭፎበት ዝም ሊል የሚችልበት ምንም ምክንያት የለም። በዚህ ጦርነት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ተሸንፏል ያልኩበት አበይት ምክንያት፤ የትግራይን ሕዝብ ልብ ለማሸነፍ በቂ ሥራዎች ያልሰራ በመሆኑ ነው። ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እንድገለጽኩት፤ የዶ/ር ዐብይ አስተዳደር ትልቁ ድክመት፤ በአለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በሃገር ውስጥ፤ ምንም ዓይነት የሕዝብ ግንኙነት አቅም ያልገንባ መሆኑ ነው። በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ትግራይ ውስጥ በቂ የሆነ የማስተማርያም ሆነ የሕዝብን ልብ የማሸነፍያ ሥራዎች አለመሰራታቸው፤ የኢትዮጵያ መንግስት ትልቁ ሽንፈት ነው ብዬ አምናለሁ። ይህ ሠራዊቱ ተሸነፈ ከሚል ጋር እንዳይምታታ። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፤ ከ40 ዓመታት በላይ ለጦርነት ሲዘጋጅ የነበርን እና እስካፍንጫው የታጠቀውን፤ ከ200 ሺህ በላይ የሕወሃት ጦር ከሶስት ሳምንታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ፤ መድረሻ አሳጥቶት፤ ዋሻ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል። ከዚህም በላይ፤ ከዶ/ር ደብረጽዮን ጀምሮ ያሉ በርካታ አመራሩን፤ ከጥቅም ውጭ አድርጓል። ሕወሃት፤ መልሶ የኢትዮጵያን መንግሥትነት ሊጨብጥ የፈለገበትን ሕልም፤ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አምክኖታል። ሰራዊቱ “ተሸነፈ” በለው የሚቃዡ ካሉ፤ ቆም ብለው አሰብ ያድርጉ እና ወደ ቀልባቸው ይመለሱ። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ዛሬም በትግራይ ውስጥ አለ፤ “የአብይን ጦር፤ እግር እግሩን እየተከተልን፤ እያጠቃን ነው” የሚለው የጌታቸው ረዳ ቱልቱላ፤ ቱልቱላ ብቻ መሆኑን የሚያሳብቅ ነው።
ሕወሃት፤ አይቀጡ ቅጣት ከመቀጣቱም በላይ፤ ከ8 ወራት ገደማ በፊት የነበረው ወታደራዊ አቋም በላዩ ላይ ባልጠበቀው ቅጽበት ተደርምሶበታል። የሕወሃት ሕልም፤ ኢትዮጵያን መልሶ ተቆጣጥሮ፤ ሕዝቡን ለማሰቃየት እና የሃገሪቱን ሃብት ለመመዝበር ነበር፤ ይህ ሊሆን እንደማይችል፤ የሽንፈት “ጽዋውን” እያጣጣመ፤ እየጎመዘዘው ተግቶታል። ሕወሃት፤ ሕልሙ ትግራይን ብቻ የመቆጣጠር ቢሆን ኖሮ፤ ሕገ መንግሥቱን ተጠቅሞ፤ ሕዝበ ውሳኔ ይሰጥ፤ “የመገንጠል መብቴን” ላስከብር ባለ ነበር። በእብሪት ሕሊናው የተደፈነ በመሆኑ፤ የኢትዮጵያን ሰራዊት የማሸነፍ አቅም አለኝ በሚል እብሪት፤ ነው ጥቅምት 24 2013 በአረመኔ ሁኔታ የሰሜን እዝ ሰራዊትን በተኛበት የጨፈጨፈው። ሕወሃት “በጦርነት የማሸነፍ” ምንም አቅም ባይኖረውም፤ ያው በተካነው የውሸት ፕሮፖጋንዳው አሸንፍያለሁ ማለቱን ይቀጥላል። በገንዘብ የገዛቸው የዜና አውታሮች፤ ይህንን ሃሰት ማራገባቸው አይቀሬ ነው።
የሕወሃት ሁኔታ፤ የሳዳም ሁሴንን ሁኔታም የሚያስታውሰኝ ዓይነት ነው። ሳዳም፤ በእብሪት ተወጥረው፤ አሜሪካንን “አሸንፋለሁ” በሚል ግብዝ ስሜት፤ አደባባይ ላይ ሽጉጣቸውን እየመዘዙ ሲፎክሩ፤ በአካባቢው ተፀኖ ፈጣሪ እና የሚፈሩም ነበሩ። እብሪታቸው ግን፤ ከዚያ ከሚፈሩበት አውድ አስወጥቶ፤ ለስቅላት ዳረጋቸው። ሕወሃትም፤ በተወሰነ ደረጃ፤ ለኢትዮጵያ ስጋት ፈጣሪ ሆኖ፤ ተጽዕኖ የመፍጠር ከፍተኛ አቅም ነበረው። ያንን አቅም ግን በዚህ ጦርነት አጥቷል። በትዕቢቱ እና በሕገ ወጥነቱ ከቀጠለ፤ ግን፤ ሞት ወይም፤ በድጋሚ ከመቀሌ ተሰዶ ወደ አይጥ ጉድጓድ ውስጥ የመመለስ ዕጣ እንደሚጠብቃቸው አመራሮቹ ያውቃሉ። በእኔ ግምት፤ ለእውነት ለትግራይ ሕዝብ የሚቆረቆሩ ተጋሩም፤ ሕወሃት የጦርነት ጉሰማውን አቁሞ፤ በክልሉ መሰረተ ልማት እንዲገነባ እና የፖለቲካ ሥልጣን ሞኖፖሊውንም እንዲተው፤ ይወተውታሉ የሚል እምነት አለኝ። ሕወሃት፤ የነበረውን “የጦርነት አቅም” አይተነዋል። ያ አቅሙ ነው፤ ወደ ጉድጓድ ያስፈረጠጠው። ዩኒፎርሙን አውልቆ “መዋጋት” ሲጀምር ግን፤ የ6 ዓመት ኅፃናትን ሳይቀር፤ ኅፃናትን እና አዛውንቶችን ከለላ አድርጎ (human shield) ነው ዕድሜውን ያረዘመው። ይህንን ያዩ እርዳታ ሰጪዎች እንኳን፤ ለኅፃናቱ ምንም ተቆርቋሪነት አላሳዩም።
ተወደደም ተጠላም፤ ጭብጡ፤ ሕወሃት በዚህ ግጭት ክፉኛ ተመትቷል። ሁልጊዜም፤ ሃላፊነት የሚሰማው መንግሥት፤ ለሃገር እና ለወገን የሚበጅ ፖሊሲዎችን መንደፍ አለበት። ሽንፈቱን ለመሸፈን እያጣጣረ ከሚፎክር ሽብርተኛ ጋር ንትርክ ውስጥ መግባት የለበትም። መንግሥት ልበ ሰፊ መሆን እና የሃገርን ጥቅምና ጉዳት ማመዛዘን ይገባዋል። ሕወሃት፤ ሕዝቡን ወደ አላስፈላጊ ጦርነት በመክተቱ፤ መሰረተ ልማት በማውደሙ፤ በንፁሃን ዜጎች ላይ የፈፀመው ግድያና በኅፃናት እና በአዛውንቶች መሃል መደበቁም ሽንፈቱን ያሳብቅበታል። የኢትዮጵያ መንግሥት፤ በተለይ በምእራቡ ዓለም እና፤ የሃሰት ትርከት በሚዘግቡ የዜና አውታሮች ከፍተኛ ጫና ውስጥ በመግባቱ እና፤ በተለይም በዓረብ ኢምሪት አግባቢነት፤ የተናጠል ተኩስ ማቆም ውሣኔ ላይ የደረሰው፤ ሠራዊቱ ከመቀሌ ከመውጣቱ ከሳምንት በፊት ነው። ሰራዊቱ ሲወጣ ከጀርባ እንዳይመታ በማሰብ፤ እንዲሁም እርዳታ ሰጪዎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ያለበትን ሃላፊነት ለመወጣት፤ በታላቅ ሚስጥር፤ ለተወሰኑ የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ባለሥልጣናት፤ ውሳኔውን ቢያሳወቅምና ሰራዊቱ እስኪወጣ በሚስጥር እንዲይዙት ቢነግራቸውም፤ ከሕወሃት ጋር እጅና ጓንት ሆነው የሚሰሩ “የእርዳታ ድርጅት” ባለሥልጣናት፤ ለሕወሃት አክቲቪስቶች ሚስጥሩን ማውጣታቸውን መረጃዎች ጠቁመዋል። ለዚህም ነው፤ የሕወሃት አክቲቪስቶች፤ የኢትዮጵያ ሰራዊት ለቅቆ ከመውጣቱ ከጥቂት ቀናት በፊት “የኢትዮጵያ ሰራዊት እየተሸነፈ ነው፤ መቀሌን ከጥቂት ቀናት በኋላ እንቆጣጠራልን፤ በማለት፤ በማህበራዊ ሚድያ፤ ፕሮፖጋንዳቸውን ለመንዛት የቻሉት።
የኢትዮጵያ ሰራዊት ከትግራይ ከተሞች መውጣት ለምን አስገራሚ ይሆናል፤ የአሜሪካን መንግስት እንድገለፀው ኢትዮጲያ እዚህ ውሣኔ ላይ የደረሰችው በዓረብ ኢምሬት ሽምግልና ነው። ከጦርነት አካባቢ ለቆ መውጣት ደግሞ በኢትዮጵያ አልተጀመረም። አሜሪካ ከአፍጋኒስታን እየለቀቀ ያለው፤ ከኢራቅ የለቀቀው፤ ከሶማሊያ የለቀቀው ተሸንፎ አይደለም፤ በእነዚህ ሃገራት መቆየቱ፤ ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝን በመሆኑ ነው። ለኢትዮጵያም እንደዛው።
እኔ በግሌ፤ ውሳኔው ለኢትዮጵያ ጠቃሚ ነው ባይ ነኝ። ይህን ሁኔታም ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ጋር ስናነፃረው፤ የውሳኔው ትክክለኛነት ግልጽ ይሆናል ብዬ አምናለሁ። የኢትዮጵያ ሰራዊት፤ የሻዕብያን ሰራዊት ባድሜ እና ፆረና ላይ ክፉኛ መትቶ፤ ወደ አሥመራ ለመገስገስ በተዘጋጀበት ሰዓት፤ አቶ መለስ ዜናዊ፤ ሰራዊቱ ወደ ፊት እንዳይገሰግስ፤ ሆኖም፤ ከድንበር ወደ ውስጥ አልፎ የተወሰነ የኤርትራ መሬት ላይ ሰክዩሪቲ ባፈር ዞን (security bufferzone) እንዲመሰረት ወሰኑ። ይህ ተገቢና ትክክለኛ ውሳኔ ግን እንደ ሰዬ አብርሃ ባሉና በሌሎች ከፍተኛ የጦር አመራሮች፤ ተቀባይነት ባለማግኘቱ፤ በሕወሃት ውስጥ ክፍፍልን ፈጠረ። በዛን ወቅት፤ የአቶ መለስ ዜናዊን ትክክለኛ ውሳኔ በመደገፍ አቡጊዳ በተባለ ድህረ ገጽ ባስነበብኩት ጽሁፍ አንድ ጥያቄ ጠይቄ ነበር። “የኢትዮጵያ ሰራዊት አሥመራን ተቆጣጠረ፤ ከዛስ? የሚል። አሁንም መሰራታዊው ጥያቄ፤ የኢትዮጵያ ሰራዊት እስከ መቼ ትግራይ ሊቆይ ይችላል? በተለይም ደግሞ በተለያዩ አግልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ውስጥ ገብቶ ለመስራት፤ ከሕዝብ ፈቃደኛነት ባለመኖሩና፤ ሃላፊነት የተሰጣቸው የፖሊስ ሹማምንት፤ መሳሪያ እየያዙ ወደ ሕወሃት በመሄዳቸው፤ እንደዚሁም፤ በተለያዩ የመንግስት አገልግሎት ውስጥ ስራቸውን የሚሰሩ የትግራይ ጊዝያዊ መንግሥት ባለሥልጣናት፤ በአሸባሪው ቡድን ግድያ እየተፈፀመባቸው፤ የኢትዮጵያ ሠራዊት እንዴት ትግራይ ውስጥ ሊቆይ ይችላል? በነገሬ ላይ አሁንም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፤ በትግራይ ክልል (security bufferzone) መስርቶ፤ ለሚመጣ ማንኛውም ጥቃት አፀፋውን ለመመለስ ዝግጁ ሆኖ እየጠበቀ ነው።
ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት፤ የመንግስት ሽንፈት፤ የትግራይን ሕዝብ ለማሸነፍ አለመስራቱ ነው። መንግሥት፤ የትግራይን ሕዝብ ልብ ለማሸነፍ ሰርቷቸዋል የሚባል ነገር ያለ አይመስለኝም። ሚድያውን እንኳን በተገቢ አልተጠቀመበትም። እንደውም፤ የትግራይ ሕዝብ በዓይኑ የሚያየወን የኤርትራን ጦር፤ ትግራይ ውስጥ አልገባም ሲል፤ የትግራይ ሕዝብ እንዴት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ እምነት ይኖረዋል? ከሕዝብ ግንኙነት ከፍተኛ ድክመት ጀምሮ፤ ግልጽነት የጎደለው የመንግሥት አካሄድ፤ እስካሁንም ድረስ፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እራሳቸው፤ በዝርዝር፤ ስለግጭቱም ሂደት ሆነ፤ ስለኢትዮጵያ ሰራዊት ከትግራይ ከተሞች አወጣጥ አለማብራራታቸው፤ የመንግሥትን ከፍተኛ ድክመት ያጋለጠ ነው። እንደ እኔ እምነት፤ መንግሥት፤ ለትግራይ አካባቢም ሆነ፤ ለተቀረው በተለያየ ግጭት ለተጎዳው ኅብረተሰብ፤ በዘመቻ መልክ እርዳታ ማሰባሰብ እና፤ እርዳታውንም በተቻለ ፍጥነት ማድረስ ነበረበት፤ ይህንንም ባለማድረጉ፤ በሕወሃት ኢትዮጵያዊ ስነ ልቦናውን የተሰለበውን የትግራይ ሕዝብ ልብ ለማሸነፍ አልቻለም።
ስለዚህ በእኔ እምነት፤ በዚህ ጦርነት፤ የትግራይ ሕዝብ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል፤ ሕወሃትም በማያዳግም ምት ተሸንፏል፤ የኢትዮጵያ መንግሥትም የሕዝቡን ልብ ለማሸነፍ ባለመቻሉ ተሸንፏል። ወጣም ወረደ፤ አሁን የደረስንበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። ጥያቄው ዘላቂው መፍትሔ ምንድነው፤ የሚል ነው። በዚህ ፀሃፍ እምነት፤ ይህ ጦርነት ያሳየን ነገር፤ አብዛኛው የትግራይ ሕዝብ ኢትዮጵያዊ ስነ-ልቦናው፤ በሕወሃት እንደተሰለበ እና፤ የትግራዋይነት ስነ ልቦና እንደተላበሰ ነው። ሕወሃት፤ የትግራይን ሕዝብ ኢትዮጵያዊ ስነ-ልቦና ለመስለብ ከ40 ዓመታት በላይ ሰርቷል። በተቀረው ኢትዮጵያም፤ ኢትዮጵያዊነት ስነ ልቦናን ለመስለብ፤ የመንግስትን መዋቀር እና ባጀት ተጠቅሞ በሰፊው ሰርቶበታል። ኢትዮጵያዊ ስሜት ሕዝብ ከሌለው አብዛኛው ሕዝብ ጋር፤ የኢትዮጵያን መንግሥትና ሕግ መንግስቴና ሕጌ ብሎ ከማይቀበል ሕዝብ ጋር፤ እንደ አንድ ሃገር እንዴት አብሮ መቀጠል ይቻላል? እንደ እኔ እምነት፤ የአዲሱ ፓርላማ የመጀመርያ ሥራ፤ ትግራይ እራሱን የቻለ አገር እንዲሆን፤ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው። ብዙዎች በዚህ ሃሳብ ደስተኛ እንደማይሆኑ እርግጠኛ ነኝ። በአንድ ስብሰባ ላይ፤ ሁለት ምሁራኖች ያንፀባረቁት ሃሳብ ለዚህ አመላካች ነው። አንዱ ተናጋሪ “We can’t leave our Tigryan brothers and sisters behind” ሲሉ፤ ሌላኛው ደግሞ፤ “የትግራይን ሕዝብ እንዴት ነው ለጌታቸው ረዳ ዓይነት ወሮ በላ ትተን የምንሄደው” ሲሉ ጠይቀዋል። አልፈልግም ያለን ሕዝብ፤ እንፈልገሃለን ብለን ሙጭጭ ብንል፤ ውጤቱ የኤርትራ ዓይነት ነው የሚሆነው። በፊት፤ የኢትዮጵያ “አስቸጋሪ ልጅ” ኤርትራ ነበረች፤ ዛሬ ጥሩ ጎረቤት ሆናለች። ዛሬ ደግሞ የኢትዮጵያ “አስቸጋሪ ልጅ” ትግራይ ሆናለች። እየተናተርክን እና እየትገዳደልን እንኖራለን፤ ወይስ ተለያይተን ሁላችንም በሰላም እንኖራለን።
ኢትዮጵያ ብዙ ፈተናዎች ይጠብቃታል፤ የኢትዮጵያዊነት ስነልቦናው የተሰለበ፤ ብዙ ዜጋ አለን። ይህንን ዜጋችንን መግራት እና፤ ለሥልጣን ጥመኞች እና ሃገርን ለሚያተራምሱ ኃይሎች የተመቸ እንዳይሆን በትጋት መስራት አለብን። የአዲሱ ትውልድ እድለኛ ነው። ስለሃገሩ የሚደክም እና ሃገሩን ከፍ ለማድረግ ተግቶ የሚሰራ መሪ አላት። እንደዚህ ፀሃፍ እምነት፤ እስካሁን ድረስ ዶ/ር ዐብይ ከሰሯቸው ብዙ ስራዎች፤ በከፍተኛነት የማስቀምጠው፤ ከሶስት አመት ተኩል በላይ፤ ኢትዮጵያዊ ስነ ልቦናን ለመገንባት የሰሩት ክፍተኛ ሥራ ነው። ይህንንም፤ ኢትዮጵያን የምንል ሁላ፤ በትጋት ልንሰራበት ይገባል።
ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን ቸሩ እግዚአብሔር ይባርክ። ለትግራይ ሕዝብ እና ለተቀረው መላ የኢትዮጵያ ሕዝ ሰላሙን እመኛለሁ።
___
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com