spot_img
Wednesday, June 12, 2024
Homeነፃ አስተያየትየኦነግ-ኦፌኮ የሽግግር መንግስት ጉዳይና የአቶ ሬድዋን ሁሴን አስደንጋጭ መልስ

የኦነግ-ኦፌኮ የሽግግር መንግስት ጉዳይና የአቶ ሬድዋን ሁሴን አስደንጋጭ መልስ

በ ዶ/ር ታምሩ ፈረደ
ሰኔ 28 2013 ዓ ም

በዶ/ር መራራ ጉዲና የሚመራው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረሥ (OFC) ና በአቶ ዳዉድ ኢብሳ የሚመራዉ OLF (ኦነግ) የኦሮሚያ ክልላዊ ብሄራዊ የሽግግር መንግስት  (Oromia Regional National Transitional Government (ORNTG)  እንደመሰረተና በአገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ የ FDRE Salvation Government (አገር አድን መንግስት ለማለት ይመስላል) የሚባል ደግሞ እንዲመሰረት ጥሪ አቅርበዋል። 

ቀደም ብሎ የ ኦፌኮ ና ኦነግ ሰዎች  እነ በቀለ ገርባ መቀሌ ድረስ ሂደው ከህወሃት ጋር ያደረጉትን ትብብር ለሚያዉቅና አሁንም ከአሸባሪዉ ህዉሃት ጋር ተባብሮ ኢትዮጵያን ለማፍረስ በዉስጥም በዉጭም ቀን ከሌት የሚሰሩት የኦነግና ኦፌኮ ሰዎችን መሰሪ ስራ ለሚከታተል ኢትዮጵያዊ ሁሉ ይህ የኦፌኮ ና ኦነግ መንግስት ምስረታ አመቺ ጊዜ ጠብቆ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚሰራው ስራ አዲስ ምዕራፍ መጀመሪያ መሆኑ ግልጽ ነው። 

የኦነግ ሰዎች ኦሮሚያ የሚሉትን አገር ለመመስረት ኢትዮጵያ መፍረስ እንዳለባት ደጋግመው በአደባባይ ነግረዉናል። በተግባር የኦነግ ተዋጊዎች መጤ ና ነፍጠኛ በሚሏቸው ኢትዮጵያዊያን ላይ ከአርባ ጉጉና በደኖ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ አሰቃቂ ዘር ማጥፋትና ጭፍጨፋ ሲያደርጉ እንደነበረ ለማንም ግልጽ ነው።

ሰኔ 26፤ 2013 (July 3rd)፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮነን ተግኝተው ንግግር ያደርጉበታል የተባለ በዙም ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ኢትዮጵያን በዉጩ ዲፕሎማሲ ስራ የሚረዱ በውጭ አለም በተለያየ አገር የሚኖሩ ትዉልደ ኢትዮጵያዊያን ተጋብዘው ነበር። ከ 600 በላይ ሰው በተከታተለው ስብሰባ ላይ አቶ ደመቀ በስራ ብዛት እንዳልተገኙ ተገልጾ፣ ንግግር ያደርጉት የክብር እንግዳ አቶ ሬድዋን ሁሴን ነበሩ። ብዙ አምባሳደሮችም ተገኝተው ነበር። ተሳታፊዎች ለአገራችን ኢትዮጵያ እጂግ ጠቃሚ የሆኑ ሃሳቦችን አቅርበዋል። ተገቢ ጥያቄዎችንም አንስተዋል። 

ከተጠየቁት ጥያቄዎች አንዱ በዶ/ር መራራ ጉዲና የሚመራው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረሥ (OFC) ና በአቶ ዳዉድ ኢብሳ የሚመራዉ OLF (ኦነግ) መንግስት መስረተናል ማለታቸውን መንግስት እንዴት ያየዋል የሚል ነበር።  ለዚህም አቶ ሬድዋን ሁሴን የመለሱት መልስ ብዙውን ተሰብሳቢ ያስደነገጠ ነበር። “ባልድራስም የሽግግር መንግስት አቋቁሟል። የሽግግር መንግስት አቋቁመናል ስላሉ ሁሉንም አናስርም” የሚል ነበር። 

ለአገራችን ኢትዮጵያ አንድነት ሲባል አሁን ከአጋጠማት ፈተናና በዉጭ አገራት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚደርገዉን የተቀናበረ ተጽዕኖ ለመቋቋም ሲባል፣ በሁሉም ነገር ባንስማማ እንኳ መንግስትን መደገፍና መስዋዕትነት እየከፈለ ካለዉ ጀግናው የኢትዮዮጵያ ጦር ጎን መቆም ተገቢ ነው። ያም ሆኖ ግን የመንግስትን ድክመት መጠቆምና ስህተቱን እንዳይደግም ማሳሰብ ተገቢ ነው። ጭፍን ድጋፍና አድናቆት ለመንግስትም ለአገራችንም ጎጂ ነው።

አሁን ለደረስንበት የተመስቃቀለ የአገራችን ሁኔታ፣ ችግሩን የዶ/ር አቢይ መንግስት ባይፈጥረውም፣ የአስተዳደራቸው ዳተኝነትና የዲፕሎማቶቻቸዉ ችሎታ ወይንም ተነሳሺነት ማነስ ግን ዋና ችግር ነበር። ይህም ሊሻሻል ይገባል። 

አሁንም  የኢትዮጵያን አካል ለመገንጠል ለዓመታት የታገለንና እጁ በንጹሃን ደም የጨቀየ ኦነግን፣ አዲስ አበባን ኗሪዎቿ ያስተዳድሯት ብሎ ከተነሳ፣ ለአመታት ወያኔን በመታገል እድሜዉን በእስር ቤት በጨረሰው እስክንድር ነጋ የተመሰረተው ባልድራስ ጋር ማወዳደር ትልቅ ስህተት ብቻ ሳይሆን የዶ/ር አቢይን መንግስትን አካሄድና አቋም ጥያቄ ዉስጥ ያስገባል።  ባልድራስ መንግስት ሳይሆን ህጋዊ ፓርቲ ነው። የባልድራሶችም ትግል በሰላምና በፍርድ ቤት ነው። ጃዋር መሃመድ ቄሮን ገጀራና ሜጫ አስይዞ የአዲስ አበባ የጋራ ቤቶች ለመዉረር ሲሞክር፣ ሃይ የሚለው የመንግስት አካል በመጥፋቱ እስክንድር ነጋ  የአዲስ አበባን ህዝብ መብት ለማስጠበቅ ሲል ተገዶ ባልድራስን መስርቷል። ለዚህም በአደባባይ ምን እንደተዛተበትና ለእስር እንደበቃ እናስታዉሳለን። እስክንድር ነጋ የሰላም ታጋይ ምሳሌ ነው።

የኦፌኮው መሪ ዶ/ር መራራም በቅርቡ ቤቲ ከምትባል ጋር ባደርጉት ቃለ ምልልስ፣ ከኦነግ ጋር ከሃያ አመታት በላይ በጋራ እንደሰሩ በግልጽ ነግርዉናል።  አሁን ነገሮች ይበልጥ ግልጽ ሆነዋል። ኢትዮጵያ የመፍረስ አደጋ በየአቅጣጫዉ ተደቅኖባታል። 

አሁንም የዶ/ር አቢይ ዳተኝነት ወደከፋ አደጋ እያመራን ነው። ጃዋር መሃመድም በኢትዮጵያ ሁለት መንግስት አንዳለ በአደባባይ ሲናገር እርምጃ ሳይወሰድበት በመቅረቱ ብዙ ጥፋት አድርሷል። የአቶ ሬድዋን ሁሴን አቋም የዶ/ር አቢይ መንግሥት አቋምን ያንጸባርቃል ተብሎ ይታመናል። ካልሆነም መንግስት ትክክል ነው የሚለዉ የተለየ አቋም ካለዉ በአስቸኳይ ለህዝብ መግለጽ ይኖርበታል።   

መንግስት አቁቁመናል በሚሉት ኦፌኮ ና ኦነግ ላይ የዶ/ር አቢይ አመራር አስቸኳይ ህጋዊ እርምጃ ካልወሰደ በዳተኝነቱ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ለሚደርሰው ጥፋት ሁሉ ከተጠያቂነት አያመልጥም። አሸባሪዎቹ ህዉሃት ና ኦነግ አሁን ደግሞ ኦፌኮ ተጨምሮ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ አደጋ ደቅነዋል። የኢትዮጵያ ህዝብም እየመጣበት ያለዉን የተቀናበረ አደጋ ተገንዝቦ ሊዘጋጅ ይገባል። 

ኢትዮጵያ በአንድነቷ ጸንታ ለዘላለም ትኑር!
__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here