spot_img
Tuesday, June 25, 2024
Homeነፃ አስተያየትወልቃይት ጠገዴ የትግራይ ወይስ የጎንደር? (ኤፍሬም ማዴቦ)

ወልቃይት ጠገዴ የትግራይ ወይስ የጎንደር? (ኤፍሬም ማዴቦ)

ኤፍሬም ማዴቦ ( emadebo@gmail.com )
ሐምሌ 8 , 2013 ዓ. .ም

“እኔ እስከማውቀው ድረስ ወልቃይት ጠገዴ በትግራይ አስተዳደር ዉስጥ ሆኖ አያውቅም!” – ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም የቀድሞ የትግራይ ጠ/ግዛት ገዢ

አሜሪካኖች የሚሉት ነገር ከትክክለኛ ምንጭ መገኘቱን ለማረጋገጥ . . . .  I heard it from the horse’s mouth ይላሉ። አሜሪካኖች እንዲህ የሚሉት ፈረስ አፍ አውጥቶ ተናግሯቸው አይደለም። ነገርን ከባለነገሩ ለመስማታቸው ማረጋገጫ ምሳሌያዊ አነጋገር ነው። 

የትግራይን ክልል የቆዳ ስፋት፣ አጎራባች ወረዳዎችና በተለይ በቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዘመን የነበረው የትግራይ ክልል ካርታ ምን እንደሚመስል ከራስ መንገሻ ስዩም የበለጠ ሊነግረን የሚችል አንድም ሰው የለም። ራስ መንገሻ ስዩም እሳቸው የትግራይ ገዢ በነበሩበት ዘመን የነበረውን ብቻ ሳይሆን ወደ ኋላም እስከ አያታቸው እስከ አጼ ዮሐንስ ድረስ ሄደው ስለ ትግራይ ብዙ ሊነግሩን የሚችሉ የፖለቲካና የታሪክ መዝገበ ቃላት ናቸው፣ የትግራይ ተወላጅ ናቸው፣ ደግሞም ትግራይን ለ14 አመታት አስተዳድረዋል። እኚህ ሰው ወልቃይት ጠገዴን አስመልክተው ከላይ የተቀመጠውን የምስክርነት ቃል የሰጡት የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ ፊዴሬሺን ምክር ቤት በቀረበበት ወቅት ከአሜሪካ ድምጽ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ነበር። ቃለ ምልልሱ በተለይ ወልቃይት ጠገዴ በትግራይ አስተዳደር ዉስጥ ሆኗ አታውቅም የሚለው የራስ መንገሻ ስዩም ምስክርነት፣ እውነት ሲነገር የማይወደውን የወያኔን አገዛዝና በአለም ዙሪያ ያሉትን ደጋፊዎቹን ክፉኛ አበሳጭቷል።

ወልቃይት ጠገዴ የጎንደር እንጂ የትግራይ አካል አለመሆኗን ለማረጋገጥ ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ ጎንደርንና ትግራይን ያስተዳደሩ ግለሰቦችን፣ የታሪክ አዋቂዎችን እና የጂኦግራፊ ጠበብቶችን መጠየቅ ነው የሚያዋጣን እንጂ ወልቃይት ጠገዴን ከጎንደር ቆርጦ አለአድራሻው ትግራይ ላይ መቀጠልና መሬት ላይ ያለውን የህዝብ አሰፋፈር እራስን በሚጠቅም መንገድ በመለወጥ የሚገኝ ነገር ቢኖር የጥያቄ መልስ ሳይሆን ቂም፣ ጥላቻ፣ እርስ በርስ መተላለቅና መራራቅ ብቻ ነው።  

የወልቃይት ጠገዴ የማንነት ጥያቄ በተነሳ ቁጥር አንዳንድ ግለሰቦች፣ ወገኖችና ቡድኖች፣ ወልቃይት ጠገዴ ትግራይ ዉስጥ ሆነች ጎንደር ሁለቱም ኢትዮጵያ ዉስጥ እስከሆኑ ድረስ ምን ያጨቃጭቃል ብለው ይጠይቃሉ። ጥያቄው “ኢትዮጵያ” እና “ኢትዮጵያዊነት” የሚል ቃል ስላለበት ትክክለኛ ጥያቄ ሊመስለን ይችላል። ግን ይህ ጥያቄ ከፍተኛ የአመለካከት፣ የግንዛቤና የመረዳት ችግር ያለበት የአንድ አቅጣጫ ጥያቄ ነው። ለመሆኑ ወልቃይት ጠገዴ ትግራይ ሆነች ጎንደር ኢትዮጵያ ዉስጥ እስከሆነች ድረስ ምንም ችግር ከሌለው ቀድሞውኑስ ለምንድነው ህወሓት ከጎንደር ቆርጦ አውጥቶ ከትግራይ ጋር የደባለቃት? ይህ ዛሬ “ወልቃይት ጠገዴ ዬትም ይሁን የት ምን ችግር አለበት“ የሚለው ጥያቄስ ለምን ያኔ ወልቃይት ተቆርጣ ስትወሰድ አልተነሳም? ደግሞስ ኢትዮጵያ ዉስጥ ቋንቋን መሰረት ያደረገ ፌዴራሊዝም ሲመሰረት የመጀመሪያ ቋንቋው አማርኛ የሆነውን የወልቃይትን ህዝብ ከአማራ ቆርጦ ትግራይ ላይ መቀጠል ለምን አስፈለገ? ህወሓት የኢትዮጵያን ህዝብ በቋንቋ ከፋፍሎ ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ከቋንቋው ጋር የተያያዘ የማንነት መታወቂያ ሲሰጠው ለምንድነው ወልቃይት ጠገዴ ብቻ አለታሪካዊ አድራሻው አዲስ አድራሻ የተሰጠው? ኢትዮጵያ በፌዴራል ስርዓት የምትተደዳር አገር ናት። እያንዳንዱ የፌዴራል ክልል የራሱ የሆነ መንግስት፣ ህገ መንግስትና ግዛት አለው። ይህ ማለት ደግሞ የትግራይ ክልል የራሱ ግዛት አለው፣ የአማራ ክልልም የራሱ ግዛት አለው። ስለዚህ ወልቃይት ከጎንደር ተቆርጦ ወደ ትግራይ ሲጨመር ከአማራ መንግስት ግዛትና አስተዳደር ወጥቶ ወደ ትግራይ መንግስትና አስተዳደር ዉስጥ ገባ ማለት ነው። ይህ ምንም ችግር የለውም የሚል ሰው ወይም ቡድን እሱ እራሱ ትልቅ ችግር አለበት። ህወሓት እራሱ በጻፈው ህገ መንግስት መሰረት ኢትዮጵያ ዉስጥ የሉዓላዊነት መሰረት ብሔር ብሔረሰቦች ናቸው። ይህ ሉዓላዊነት ደግሞ እስከመገንጠል ሊያደርሳቸው ይችላል። ለምሳሌ፣ የትግራይ ክልል ኢትዮጵያዊነት በቃኝ ካለ የመገንጠል ጥያቄ ማቅረብ ይችላል። ትግራይ ህገ መንግስታዊ መብቱን ተጠቅሞ ኢትዮጵያዊ አልሆንም ብሎ ከኢትዮጵያ ቢገነጠል በምን ሂሳብ ነው ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለው የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ከትግራይ ጋር አብሮ የሚገነጠለው?

የወልቃይት ጠገዴን የማንነት ጥያቄ በተመለከተ የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ከልዑል ራስ መንገሻ ስዩም በተጨማሪ ዶ/ር ገላውዲዎስ አርአያ የሚባሉ ምሁርንም ለቃለ መጠይቅ አቅርቧቸው ነበር። የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ትግርኛ ፕርግራም እንዲህ ሲል ነበር ዶ/ር ገላውዲዎስ አርአያን የጠየቃቸው . . . . . .  “ወልቃይት ከጥንትም ጀምሮ የትግራይ ክልል አካል ሆኖ አያውቅም የሚሉ ወገኖች አሉ . . .አርሶስ ምን ይላሉ”?

“ወልቃይት ከጥንት ጀምሮ በትግራይ ስር አልነበረችም የሚለው አባባል የታሪክ መሰረት የለውም . . . . ስህተት ነው”  . . . . እንዲህ አይነት የማንነት ጥያቄ ሲነሳ ጥያቄው መመለስ ያለበት የታሪክ ሰነድን በመመርመር ነው”

ዶ/ር ገላውዲዎስ አርአያ የታሪክ ምሁር አይደሉም። ሆኖም የወልቃይት ጠገዴን ማንነት አስመልክቶ የአሜሪካ ድምጽ ላቀረበላቸው ጥያቄ የታሪክ ሰነዶችን አገላብጠው ወገናዊ ሳይሆን ምሁራዊ መልስ መስጠት የሚችሉ ናቸው። እሳቸው ግን “ዘር ከልጓም ይስባል” የሚሉት ብህል አሸንፏቸው ምሁርነታቸውን ክደው በታሪክ ያልተደገፈ ወገናዊ መልስ ሰጡ።ዶ/ር ገላውዲዎስ የአሜሪካ ድምጽ የጠየቃቸውን ጥያቄ ሲመልሱ “ወልቃይት በአጼ ዮሐንስ ዘመንና ከዚያም በፊት በታሪክ ከትግራይ ስር ነበረች ብለዋል። የሚያሳዝነው አባባላቸው አይደለም። ዘረኞቹ የህወሓት መሪዎችም ደደቢት በረሃ ከገቡበት ቀን ጀምሮ ወልቃይት የትግራይ ናት ብለዋል ዛሬም እያሉ ነው። አብዛኛዎቹ የህወሓት መሪዎች መሀይምም እብሪተኛም ናቸውና ወልቃይት የትግራይ ናት ሲሉ አባባሉ የሚመነጨው አንድም ከዕብሪት አንድም ከመሃይምነት ነው። ዶ/ር ገላውዲዎስ ግን በከፍተኛ ደረጃ የተማሩና ብዙ ያነበቡ ሰው ናቸው። በጣም የሚያሳዝነው እኚህ የተማሩና ያነበቡ ሰው የወልቃይት ጠገዴን የማንነት ጥያቄ የመለሱበት መንገድ እንደ መሃይሞቹ የህወሓት መሪዎች በዕብሪትና ባለማወቅ ላይ የተመሰረተ መሆኑ ነው። ዶ/ር ገላውዲዎስ እንደ ማንኛውም ምሁር ታሪክ ለመጥቀስ ሞክረዋል፣ ችግሩ እሳቸው የጠቀሱት የወልቃይት ታሪክ ያልተጻፈና ከብዙ የተጻፉ ታሪካዊ መረጃዎች ጋር የሚጋጭ የመላምት ታሪክ መሆኑ ነው። ለመሆኑ ዶ/ር ገላውዲዎስ መረመርኩ የሚሏቸው የታሪክ መረጃዎች ወልቃይት በአጼ ዮሐንስ ግዜ ዬት እንደነበረች ነው የሚናገሩት?

በጂኦግራፊ ምርምር ስራው የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነውና ብራስልስ ዩኒቨርሲቲ ዉስጥ የጆግራፊ አስተማሪ የነበረው ፕሮፌሰር ኤሊስ ሬክለስ በ1880 ዓም በጻፈው The Erath and its Inhabitants በሚለው መጽሐፉ ዉስጥ ደምቢያ፣ ጭልጋ፣ያንጣነገራ፣ ዳጎሳ፣ ቋራ፣በጌምድር፣ ጉና፣ሳይንት፣ ዋድላ፣ ደላንታ፣ ወገራ፣ስሜን፣ ጸለምት፣ አርማጭሆ፣ ጠገዴ፣ ዋልድባና ወልቃይት የአማራ ግዛቶች ናቸው ይላል። ጸለምት፣ጠገዴ፣ ዋልድባና ወልቃይት የአማራ ግዛት ናቸው ከተባለ ደግሞ የእነዚህ ቦታዎች የካርታ አድራሻ ትግራይ ሳይሆን ጎንደር ነው ማለት ነው። ፕሮፌሰር ሬክለስ ወልቃይ ጠገዴ በአጼ ዮሐንስ ዘመን የማን እንደነበረች በግልጽ አሳይቶናል። ካሁን በኋላ የሚቀረው ዕዳ የዶ/ር ገላውዲዎስ ነው። እኚህ ሰው እውነትም ምሁር ከሆኑ ይህንን የፕሮፌሰር ሬክለስን መረጃ ታሪክ ጠቅሰው ያስተባብሉ አለዚያም መሳሳታቸውን አምነው ይቅርታ ይጠይቁ።

ከአጼ ዮሐንስ በፊት ኢትዮጵያን ለ13 አመታት የመሩት አጼ ቴዎድሮስ ናቸው። በሳቸው ዘመንና ከሳቸውም በፊት የተጻፉ የታሪክ መረጃዎችስ ስለወልቃይት ጠገዴ ምን ይላሉ? ስለ ኢትዮጵያ ታሪክና ጂኦግራፊ ብዙ ከጻፉ አውሮፓውያን ዉስጥ ቅድሚያውን የሚይዙት እንግሊዞች ናቸው፣ በተለይ በአጼ ቴዎድሮስ ዘመን ንጉሱ ቤ/መንግስት ድረስ እየተመላለሱ ስለ ኢትዮጵያ ብዙ ጽፈዋል።ኤሲ ኩክ Routes in Aabysina በተባለውና በ1867 ዓም በጻፈው መጽሐፉ ዉስጥ የትግራይንና የአማራን ግዛቶች እንደሚከተለው በዝርዝር ያስቀምጣል-

የአማራ ግዛት

ስሜን፣ ወልቃይት፣ ዋልድባ፣ ጭልጋ፣ ወገራ፣ ቋራ፣ በለሳ፣ ፎገራ፣ ዳሞት፣ ጎጃም፣ በጌምድርና በሽሎ

የትግራይ ግዛት

መናገሻ ከተማው አድዋ የሆነው የትግራይ ግዛት ወሰኑ በምዕራብ በኩል ሽሬ፣ በደቡብ ምዕራብ ተምቤንና አዴት፣ በደቡብ ገር አልታ፣በደቡብ ምስራቅ ሀራማት፣ በምስራቅ አጋሜ በሰሜን የመረብና የበለሳ ወንዝ ናቸው። 

በአጼ ቴዎድሮስ ዘመን ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጸለምትና ዋልድባ ጎንደር ዉስጥ እንጂ ትግራይ ዉስጥ እንዳልነበሩ የታሪክ ምስክርነታቸውን የሰጡን እንግሊዛዊው ኮሎኔል ኤሲ ኩክ ናቸው። እነዚህ ቦታዎች በአጼ ዮሐንስ ዘመንም ጎንደር ዉስጥ እንጂ የትግራይ ዉስጥ አይደሉም ያሉት ደግሞ የቤልጂጉ ፕሮፌሰር ኤሊስ ሬክለስ ናቸው። ከሁለቱ ነገስታትና ከሁለቱ የታሪክ ምስክሮች (ፕሮፌሰር ሬክለስና ኮሎኔል ኩክ) በፊት የነበሩ የታሪክ ማስረጃዎችም ምንም በማያወላዳ መልኩ ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጸለምትና ዋልድባ የጎንደር ግዛቶች መሆናቸውን ነው የሚናገሩት።

ከአጼ ኢዮአስ ህልፈት እስከ አጼ ቴዎድሮስ ድረስ በነበረው ዘመን ኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግስት አልነበራትም። በአገራችን በኢትዮጵያ ይህ ዘመን “ዘመነ መሳፍንት” በመባል ይታወቃል። በዚህ ኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግስት ባልነበራትና ጉልበተኛ ያሰኘውን በሚያደርግበት ዘመንም ቢሆን ወልቃይት ጠገዴ የአማራ ግዛት መሆኗን በወቅቱ ኢትዮጵያን ጎብኝቶ የነበረው የስኮትላንዱ ተወላጅ ጀምስ ብሩስ በማያሻማ ቋንቋ ተናግሯል። ጀምስ ብሩስ ስለ ትግራይና አማራ ድንበር እንዲህ ብሎ ነበር የጻፈው . . . . Tekeze is the Natural boundary between Tigre and Amhara” ተከዜ የትግሬና የአማራ የተፈጥሮ ድንበር ነው”  ጀምስ ብሩስ የተወልን መረጃ እጅግ በጣም አሳማኝ መረጃ ነው፣ ምክንያቱም ጀምስ ብሩስ የትኛው መስፍን የትኛውን ግዛት ያስተዳድር እንደነበረና የእያንዳንዱ መስፍን ግዛት የት ድረስ እንደነበረ በዝርዝር የሚያውቅና የጻፈም ሰው ነው።

ዶ/ር ገላውዴዎስ ወልቃይት ጠገዴ የትግራይ ክልል አካል ነው ለሚለው አባባላቸው እንደ ዋነኛ ማስረጃ የጠቀሱት በ1630 ዓም የፓርቱጋሉ ተወላጅ አማኑኤል በሬዳ Tractatus tres historico- geographici በሚል አርዕስት የጻፈውን መጽሐፍ ነው። ይህንን መጽሐፍ ሪቻርድ ፓንክረስት A Seventeenth Century Historical Account of Tigray, Ethiopia በሚል አርዕስት ከፖርቱጋል ቋንቋ ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ ተርጉመውታል። ዶ/ር ገላውዴዎስ ይህንን መጽሐፍ ከዬት ወዴት እንዳነበቡት እሳቸው ብቻ ናቸው የሚያውቁት . . . .  መጽሀፉ በተጻፈበት ቋንቋ በፖርቱጋልም ሆነ በተተረጎመበት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ወልቃይት ጠገዴ የትግራይ አካል ናት የሚል አንድም ቦታ የለም። እንዲያውም መጽሐፉ በዶክተር ደረጃ ለተማሩት ለዶ/ር ገላውዴዎስ ቀርቶ አንድ ቀንብቻ ፊደል ለቆጠረ አንባቢም ግልጽ በሆነ መንገድ የሚናገረው በምዕራብ በኩል የትግራይ ወሰን የተከዜ ወንዝ እንደሆነ ነው።

ዘመነ መሳፍንትን ትተን በታሪክ ወደኋላ ስንሄድ ከምናገኛቸው ታዋቂ የኢትዮጵያ ነገስታት ዉስጥ አንዱ አጼ ዘርዓ ያዕቆብ ናቸው። እኚህ ሰው ኢትዮጵያን ለ37 አመታት መርተዋል። ፈላስፋና ሊቅ እንደነበሩ የሚነገርላቸው አጼ ዘርዓ ያዕቆብ ብዙ መጽሐፍት ጽፈዋል እንዲጻፍም አድርገዋል። በሳቸው ዘመን ከተጻፉት መጽሐፍት ዉስጥ አንዱ በአክሱም ንቡረ ዕድ የተጻፈው “ዜና አክሱም” የተባለው መጽሐፍ ነው። ሐይማኖትና ታሪክን አጣምሮ የያዘው ዜና አክሱም በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረችው ኢትዮጵያ ምን ትመስል እንደነበረ በዝርዝር ያተተ መጽሐፍ ነው። ይህ መጽሐፍ የኢትዮጵያን ታሪከ፣ ወሰን፣ የየክፍለ አገሩን ድንበርና በተለይ የዛሬዋ ትግራይን በወቅቱ ምን ትመስል እንደነበር በካርታ አስደግፎ ይዘረዝራል። ይህም በኢትዮጵያዊ ጸሐፊ የተጻፈ መጽሐፍ የሚነግረን በአጼ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመን ወልቃይት፣ ጸለምትና ጠገዴ የአማራ እንጂ የትግራይ እንዳልሆኑ ነው።

አቶ ዮሐንስ መኮንን የተባሉ ኢትዮጵያዊ የታሪክ ጸሐፊ. . .   Ethiopia: the land, its people, History and Culture በሚለው መጽሐፋቸው በአጼ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመነ መንግስት የነበረውንና በዜና አክሱም መጽሐፍ ዉስጥ የቀረበውን የትግራይ ካርታ እንደሚከተለው በዝርዝር ያቀርቡታል – 

ዜና አክሱም  . . .  አክሱምን ያማከለና በዘልማድ የተሳለውን የትግራይ ካርታ የሚያሳይ መጽሐፍ ነው። በዚህ ካርታ ዉስጥ አክሱምን የከበቡት የትግራይ ግዛቶች ተምቤን፣ሽሬ፣ ሰራዬ፣ ሐማሴን፣ ቡር፣ ሳማ፣አጋሜ፣ አምባ ሰናይት፣ ገር አልታ፣ እንደርታ፣ ሳሀርትና አበርገሌ ናቸው። ጆን ሾርት የተባሉ እንግሊዛዊ ጸሐፊ በ2003 ዓም በጻፉት The World through Maps: A History of Cartogrphy በሚለው መጽሐፋቸው በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረው የትግራይ ካርታ በ“ዜና አክሱም” መጽሐፍ ዉስጥ ከተጠቀሱት የትግራይ ግዛቶች ውጭ ወልቃይትን፣ ጸለምትንና ጠገዴን እንደማያጠቃልል በግልጽ ተናግረዋል።

ከነባራዊ ሁኔታዎችና መሬት ላይ ካለው እውነት ጋር ተገናዝበው በየዘመኑ በተለያዩ ጸሐፊዎች የተጻፉትን የታሪክ መረጃዎች ትተን ወያኔና ደጋፊዎቹ በሚወዱትና በቋንቋ ላይ ተመስርቶ በጣሊያን ፋሺስቶች የተሳለውን የኢትዮጰያ ካርታ ስንመለክት አሁንም ወልቃይት፣ ጸለምትና ጠገዴ በትግራይ ዉስጥ ሳይሆን ጎንደር ዉስጥ ነው ያሉት። ጣሊያኖች በ1928 ዓም አዲስ አበባን ከተቆጣጠሩ በኋላ በቋንቋ ላይ ተመስርተው የሳሉት ካርታ በግልጽ እንደሚያሳየው ወልቃይት፣ ጸለምትና ጠገዴ ዉስጥ የሚኖረው ህዝብ የሚናገረው ቋንቋ አማርኛ ስለሆነ የተጠቃለለውም በአማራ ግዛት ዉስጥ ነው። 

በሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ ታሪክና ፖለቲካ ላይ ሰፋ ያለ ጥናትና ምርምር ካካሄዱ ምሁራን አንዱ ፕሮፌሰር ክርስቶፎር ክላፓም ናቸው። እኚህ ሰው ኢትዮጵያን እንደ ቤታቸው ጓዳ ያውቋታል ቢባል አባባሉ ከእውነት የራቀ አይደለም። ፕሮፌሰር ክላፓም Transformation and Continutiy in Revolutionary Ethiopia በሚል አርዕስት በ1988 ዓም በጻፉት መጽሐፍ ዉስጥ ትግራይንና ወልቃይት ጠገዴን አስመልክተው እንዲህ ነበር ያሉት . . . . .  የተፈጥሮ ድንበር በሆነው በተክዜ ወንዝ ከትግራይ የተለየው የወልቃይት ጠገዴ አካባቢ ጎንደር ዉስጥ እንጂ አንድም ግዜ በትግራይ ክልል ስር ሆኖ አያውቅም።

የወልቃይት ጠገዴን ማንነት አስመልክቶ ከ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ እስከ 1988 ዓም ድረስ የተጻፉትን የታሪክ መረጃዎች የጻፉት ኢትዮጵያዊያን፣ ጣሊያኖች፣ቤልጂጎች፣ እንግሊዞች፣ ፖርቱጋሎችና የፈረንሳይ የታሪክ ጸሐፊዎች ናቸው። እነዚህ የታሪክ ጸሀፊዎች በግዜ፣ በቦታና በዜግነት የተለያዩ ናቸውና እርስ በርስ አይተዋወቁም፣ የወልቃይት ጠገዴን ማንነት በተመለከት የሰጡት ምስክርነት ግን ተመሳሳይ ነው። በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረውን የኢትዮጵያ ታሪክ ከጻፉት ከአክሱሙ ንቡረ ዕድ ጀምሮ በ1988 ዓም የዘመናዊቷን ኢትዮጵያን ታሪክና ፖለቲካ እስከጻፉት እስከ ፕሮፌሰር ክላፓም ደረስ የነበሩት ጸሀፊዎች አንድም ግዜ  ወልቃይት፣ ጸለምትና ጠገዴ የትግራይ ክልል አካል ናቸው አላሉም። ሁሉም ቁልጭ ባለ ቋንቋ የጻፉት ወልቃይት ጠገዴና ጸለምት የጎንደር ወይም የአማራ አካል መሆናቸውን ነው። 

ዛሬ የወልቃይት፣ የጠገዴና የጸለምት ህዝብ ማንነቱ በጠመንጃ ሃይል ተቀምቶና አዲስ ማንነት ተሰጥቶት የመከራ ኑሮ እየኖረ ነው። ህወሓት ተከዜን ተሻግሮ ወልቃይት ጠገዴን ከትግራይ ጋር የቀላቀለው ወልቃይት ጠገዴ የትግራይ አካል ነበርች በሚል እምነት ሳይሆን “ታላቋ ትግራይ” ሰፊ የእርሻ መሬትና አለም አቀፍ ድንበር ሊኖራት ይገባል በሚል እምነት ነው።

የህወሓት መሪዎች ልብ ዉስጥ ጸረ አማራና ጸረ ኢትዮጵያ መርገም የተጸነሰው እነ መለስ ዜናዊና ስብሐት ነጋ ደደቢት በረሃ ሳይገቡ ገና ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ እያሉ ነው። እነዚህን የጥላቻ አባቶች በረሃ እንዲገቡ ያደረጋቸው እነሱ እንደሚሉት ኢትዮጵያ ዉስጥ በንጉሱና በደርግ ዘመን የነበረው የህዝብ መብትና ነጻነት መረገጥ ሳይሆን አማራን አሳንሰው ታላቋን ትግራይን ለመመስረት ይዘው የተነሱት እኩይ አላማ ነው። በእርግጥም የህወሓት ዘረኛ መሪዎች አይን ተከዜን ተሻግሮ ወልቃይት ጠገዴ ላይ ያረፈው ዘረኞቹ ደደቢት በረሃ ገብተው ሳምንት ሳይሞላቸው ነው። ለምሳሌ፣ እንደ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ1972 ዓም የህወሓት ጦር ተከዜን ተሻግሮ ወልቃይት ጠገዴን በወረራ መያዙንና ወረራውን ከተቃወመው ከአካባቢው ህዝብና ከኢህአፓ ሰራዊት ጋር ሽሬላና ቆላ መዘጋ አካባቢ ከፍተኛ ጦርነት መካሄዱን የሚያሳዩ ብዙ መረጃዎች አሉ። 

ህወሓት አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ በሂደት ኢትዮጵያን በዘጠኝ ክልሎች ሲከፋፍል ሰሜን ኢትዮጵያ ዉስጥ በንጉሱ ዘመን ጠ/ግዛት በደርግ ዘመን ደግሞ ክፍለ ሐገር በመባል ይጠሩ የነበሩትን በጌምድርን፣ ጎጃምን፣ ወሎንና ሰሜን ሸዋን አማራ ክልል፣ ትግራይን ደግሞ እራሷን ችላ ትግራይ ክልል ብሎ በመከፋፈል ክልሎቹ የየራሳቸውን የክልል መንግስት እንዲመሰርቱ አድርጓል። ወያኔ እንዲህ አይነቱን በዘርና በቋንቋ የታጠረ የጎሳ ፌዴራሊዝም ከመፍጠሩ በፊት አንድ ኢትዮጵያዊ ያዋጣኛል ብሎ ካሰበ ከየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ ወደየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ ሄዶ የመኖር መብቱ የተከበረ ነበር። ለምሳሌ፣ ሌላውን ትተን ዛሬ ወያኔ በጠመንጃ አስገድዶ ከጎንደር ቆረጦ ትግራይ ላይ የቀጠለውን የወልቃይት ጠገዴን አካባቢ ብንመለከት ይህ አካባቢ የ1966ቱ አብዮት ፈንድቶ አካባቢው ለሶስት አስርተ አመታት የጦርነት ቀጣና ከመሆኑ በፊት የሚታረስ መሬትና የሚቆረስ ዳቦ የሌላቸው የትግራይ ገበሬዎች ተከዜን ተሻግረው በእርሻ ስራ ይተዳደሩበት የነበረ አካባቢ ነው። ሁመራን ጨምሮ የወልቃይት ጠገዴ አካባቢ በአለም ገበያ ከፍተኛ ዋጋ ያለውን የሰሊጥ ምርት በብዛት የሚያመርት አካባቢ በመሆኑ፣ ወልቃይት ጠገዴ ተከዜን ተሻግረው የሚመጡ አያሌ የትግራይ ተወላጆች ከጎንደሬዎች ጋር ትልቅ ማህበረሰብ ፈጥረው አማርኛም ትግርኛም እየተናገሩ በሰላምና በፍቅር የሚኖሩበት አካባቢ ነበር። የሚገርመው እነዚህ ከትግራይ የመጡ የወልቃይት ጠገዴ ነዋሪዎች ወልቃይት ጠገዴ ዉስጥ ቁጥራችን በዝቷልና ወልቃይት የትግራይ መሆን አለባት የሚል ዕብድትና ውስልትና አንድም ቀን ልባቸው ዉስጥ አድሮ አያውቅም። የወልቃይት ጠገዴ ህዝብም ቢሆን እጁን ዘርግቶ ከተቀበላቸው የትግራይ ወንድሞቹ ጋር ቋንቋቸውን እየተጋራ አብሯቸው ኖረ እንጂ እንደዛሬዎቹ የህወሓት ቡችሎች ከክልላችን ውጡልን የሚል እብደት ዉስጥ አልገባም።

የህወሓት መሪዎች ወልቃይት ጠገዴ የጎንደር እንጂ የትግራይ አካል አለመሆኗን በሚገባ ያውቃሉ። “ታላቋ ትግራይ” ያለ ወልቃይት ጠገዴ ታላቅ ተብላ መጠራት እንደማትችልም ያውቃሉ። ለዚህ ይመስላል ህወሓት ትግራይን ሙሉ ለሙሉ ከመቆጣጠሩ ከዘጠኝ አመት በፊት ተከዜን ተሻግሮ ወልቃይት ጠገዴን በወረራ የያዘው። ወልቃይት ጠገዴና አካባቢዋ የህወሓት መሪዎች ራዳር ዉስጥ የገቡት እነዚህ ወንጀለኖች “ታላቋ ትግራይ” የሚል ህልም ከታያቸው ቀን ጀምሮ ነው። በእርግጥም እንደነሱ ህልም ከሆነ ብዙም የተሳሳቱ አይመስልም – ትግራይን ትልቅ ለማድረግ ትግራይ የሌላት ነገር ከሌላ ቦታ ተፈልጎ መጥቶ ትግራይ ላይ መቀጠል ነበረበት። ለዚህ ደግሞ ከወልቃይት ጠገዴ የተሻለ ቦታ የለም። ለምን ይሆን? 

በየካቲት ወር 1970 ዓም የህወሓት ጦር “ትግራይ ለትግሬዎች” የሚል የዕብሪተኞች መፈክር አንግቦ አሲምባ ላይ ሰፍሮ በነበረው የወገኖቹ ሰራዊት (የኢህአፓ ሰራዊት) ላይ ድንገተኛ ጥቃት ሰንዝሮ በሁለቱም በኩል ብዙ ኢትዮጵያውያን መሞታቸውና መቁሰላቸው ዛሬም ድረስ የሚያንገበግበን አስቀያሚ የታሪክ ጠባሳ ነው። ለመሆኑ ህወሓት “ትግራይ ለትግሬዎች” ብሎ ብዙ የትግራይ ተወላጆች በመሪነትና በተዋጊነት የሚገኙበትን የኢህአፓን ጦር ከአሲምባ ካልወጣህ ብሎ ሲወጋ ለምን ይሆን የራሱ ጦር ተከዜን ተሻግሮ ወልቃይት ጠገዴን በወረራ የያዘው? ህወሓቶች “ትግራይ ለትግሬዎች” ካሉ ለምንድነው ጎንደር የጎንደሮች እንድትሆን ያልፈለጉት? ዘረኞቹ መለስ ዜናዊና ስብሐት ነጋ ኢትዮጵያዊነትን አፈራርሰው “ታላቋን ትግራይ” ለመፍጠር በረሃ ሲገቡ ለምንድነው ከዚያው ከትግራይ መሬት የበቀሉት እነ ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይና ዘሩ ክሸን ታላቋን ኢትዮጵያ ለመፍጠር ከደርግ ፋሺስቶች ጋር ሲፋለሙ ህይወታቸው ያለፈው?

የ1966ቱ አብዮት ከመፈንዳቱ በፊትና ከፈነዳም በኋላ ተማሪው ወደ ዕድገት በህብረት የዕውቀትና የስራ ዘመቻ እንዲዘምት ከመደረጉ በፊት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ የለውጥ ማዕከልና የአዳዲስ ሀሳቦች መፍለቂያ ምንጭ ነበረች። ጥላሁን ግዛውን፣ ዋለልኝ መኮንንን፣ ጌታቸው አቦማን፣ ዶ/ር እሼቱ ጮሌንና ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማሪያምን የመሳሰሉ አያሌ የመብትና የነጻነት መብራቶችን ያፈራው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እነ መለስ ዜናዊን፣ስዩም መስፍንን እና ስብሐት ነጋን የመሳሰሉ የጨለማ ኃይሎችንም አፍርቷል። እነዚህ የጨለማ ኃይሎች ናቸው ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ ወልቃይት ጠገዴን ጨምሮ በአራቱም ማዕዘኖች የምናየውን የወንድማማቾች መከፋፈልና የርስ በርስ መተላለቅ ችግሮች የመሰረት ድንጋይ ያኖሩት።

የህወሓት መሪዎች የታላቋን ትግራይ ህልም ማለም የጀመሩት በረሃ ሳይገቡ ገና ተማሪዎች እያሉ ነው። ይህንን ህልማቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ደደቢት በረሃ ገብተው የታላቋን ትግራይ ካርታ መሬት ላይ ስለው ሲመለከቱ ከኢትዮጵያ ውጭ የትግራይ ታላቅነት አልታይ አላቸው። ሆኖም እነዚህ የደደቢት ደደቦች በህልማቸው ያዩዋትን ታላቋ ትግራይ በውናቸው ማየት እስከቻሉ ድረስ አላማቸው የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው ነበርና፣ ትግራይን በቀዶ ጥገና ትልቅ ለማድረግ ቆርጠው ተነሱ። ታላቋ ትግራይ የባህር በር፣ ከጎረቤት ጋር በተለይ ከሱዳን ጋር የሚያገናኝ ድንበር ያስፈልጋታል፣ ታላቋ ትግራይ ለረጂም ግዜ የሚታረስ ለምለምና ሰፊ መሬት ያስፈልጋታል። ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ከትውልድ ስፍራው ከደደቢት በረሃ አዲስ አበባ እስኪገባ ድረስ ከፍተኛ የሻዕቢያ ዕርዳታና ድጋፍ ያገኘ ቢሆንም “ታላቋ ትግራይ” ወይም የትግራይ ሪፓብሊክ በሚለው አላማው ግን ህወሓትና ሻዕቢያ ተስማምተው አያውቁም። ደርግ በጦርነት ተሸንፎ እየተፍረከረከ ሲመጣ ህወሓት የ“ታላቋ ትግራይ” አላማውን በይደር አስቀምጦ “ኢህአዴግ” በሚባል ፈረስ ተጭኖ ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር ቢበቃም የሻዕቢያና የህወሓት በታላቋ ትግራይ ምስረታ አለመስማማት በአንድ ወቅት ወያኔ “ሻዕቢያ የትግል አጋራችን ነው እንጂ ሞግዚታችን አይደለም” እስከማለት የደረሰበት ግዜ እንደነበር አይዘነጋም።

የህወሓት መሪዎች ታላቋን ትግራይ ከባህር ጋር የማገናኘት ህልማቸው እራሱ ህልም መሆኑን ቢረዱም፣ የትግራይን ሪፓብሊክ ከሱዳን ጋር ማገናኘትና የሚታረስ ለምለም መሬት ከጎንደር ቆርጠው ትግራይ ላይ መቀጠል ግን ለግዜውም ቢሆን በነሱ አቅም መደረግ የሚችል ጉዳይ መሆኑን በሚገባ የተገነዘቡ ይመስላል። ለዚህም ነው እግራቸው ደደቢት በረሃን በረገጠ ልክ በአምስተኛው አመታቸው ተከዜን ተሻግረው ወልቃይት ጠገዴንና ጸለምትን በወረራ የያዙት። ከወሎ ላስታ የሚነሳው የተከዜ ወንዝ፣ ጎንደርና ትግራይን፣ በጎንደር በኩል ደግሞ ኢትዮጵያንና ኤርትራን የሚያዋስን ትልቅ ወንዝ ነው። የትግራይ ገበሬ ስራ ፍለጋ ወደ ጎንደር ማለትም ወደ ወልቃይት ጠገዴ መምጣት ከፈለገ ተከዜን ተሻግሮ አስፈሪውን የተከዜ ሸለቆ ማቋረጥ አለበት። ይህንን አድካሚ ጉዞ ተጉዘው ከጎንደር ሰው ጋር ተቀላቅለው የጸለምትን ማህበረሰብ መስረተው እየነገዱና እርሻ እያረሱ ሰላማዊ ኑሮ የሚኖሩ ብዙ የትግራይ ተወላጆች አሉ። እነዚህ ትግራዋዮች አማርኛም ትግርኛም እየተናገሩ ከወገናቸው ከጎንደር ማህበረሰብ ጋር አብረው ከመኖር ውጭ ወልቃይት ጠገዴ የኛ ነው ብለው አያውቁም። ወልቃይት ጠገዴ የትግራይ ነው የሚለው አጉል የባለቤትነት ጥያቄ የተነሳው እነ መለስ ዜናዊና ስብሐት ነጋ “ታላቋ ትግራይ” የሚለውን የሞኝ ህልም ካለሙ በኋላ ነው። ይህ ወልቃይት ጠገዴ የትግራይ አካል ነው የሚለው የባለቤትነት ጥያቄ የትግራይ ህዝብ ጥያቄ ሳይሆን የዘመናዊቷም ሆነ የጥንታዊቷ ኢትዮጵያ መሰረት የሆነቸውን ትግራይን ከኢትዮጵያ ነጥለው የትግራይ ሪፓብሊክ ለመመስረት ያቀዱ ጥቂት ከሀዲዎችና የባንዳ ልጆች የጠነሰሱት አኩይ ጥያቄ ነው።

የህወሓት መሪዎች በ1972 ዓም ወልቃይት ጠገዴን በወረራ ከያዙ በኋላ ወልቃይት ጠገዴንና እስከ ሁመራ ድረስ ያለውን ሰፊ መሬት እስከ ወዲያኛው የትግራይ አካል ያደርጉልናል ብለው ያሰቧቸውን ሶስት ዋና ዋና እርምጃዎች ወስደዋል። የመጀመሪያውን እርምጃ የወሰዱት ጫካ ዉስጥ እያሉ ሲሆን ሁለተኛውንና ሶስተኛውን እርምጃ የወሰዱት ከጫካ ወጥተው የመንግስት ስልጣን ከጨበጡ በኋላ ነው። ከላይ ከፍ ሲል እንደተጠቀሰው የትግራይ ገበሬ ህወሓት የሚባል ድርጅት ከመፈጠሩ ከብዙ አመታት በፊት ተከዜን ተሻግሮ ወልቃይት ዉስጥ ከአማራ ወንድሞቹ ጋር አብሮ በሰላም ይኖር ነበር። የህወሓቶች አላማ ግን ሰላም ሳይሆን ጦርነት፣ አብሮ መኖር ሳይሆን መነጣጠል ስለሆነ የኋላ ኋላ ይበጀናል ብለው ላሰቡት “ህዝበ ውሳኔ” እንዲመቻቸው ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የትግራይ ገበሬ በገፍ እያመጡ ወልቃይት ዉስጥ ማስፈር ጀመሩ። በ1983 ዓም ደርግን አሸንፈው ስልጣን ከጨበጡ በኋላ ደግሞ ወልቃይት ጠገዴ የትግራይ ክልል አካል ነው ብሎ አዲስ ካርታ ሳሉ። ይህ ሁሉ አልበቃ ብሎቸው ከ30ሺ በላይ መሳሪያ ለታጠቁ የቀድሞ ተዋጊዎቻቸው ሰፋፊ መሬት እየሰጡ ወልቃይት ዉስጥ እንዲሰፍሩ አደረጉ። እነዚህ ቀፍትያ፣ ጸለምትና ዳንሻ አካባቢ ወያኔ ያሰፈራቸው ተዋጊዎች ናቸው ዛሬ ወልቃይት ጠገዴ የትግራይ እንጂ የጎንደር አይደለም እያሉ አካባቢው የጦርነት ቀጣና እንዲሆን ያደረጉት። አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ እንዲሉ ዛሬ በማዕከል የህወሓት መሪዎች፣ በክልል ደግሞ የትግራይ መንግስት መሪዎች የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ አልቆለታል ብለው እየነገሩን ነው። እነዚህ ዕብሪተኞች የጨበጡት ጠመንጃ ልባቸውን አሳብጦት ነው እንጂ የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይማ ተጀመረ እንጂ አላለቀም። 

በማዕከል እነ አባይ ጸሐዬና ስብሐት ነጋ፣ በክልል ደግሞ እነ አባይ ወልዱን የመሳሰሉ ዘረኛና ዕብሪተኛ የህወሓት ሰዎች የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ ያለቀለት ጉዳይ ነው ብለው የሚነግሩን አለምክንያት አይደለም። በአንድ በኩል ዛሬ በክልልም በማዕከልም የፖለቲካ ስልጣንን የሚቆጣጠሩት ህወሓቶች ስለሆኑ እነሱ በጎንደርና በትግራይ መካከል ያሰመሩትን የውሸት ድንበር የሚነካ ማንም ሰው ያለ አይመስላቸውም። በሌላ በኩል ደግሞ የህወሓት መሪዎች ከቅርብ ግዜ ወዲህ የጀመሩት  . . . . . የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ በ”ህዝበ ውሳኔ” (Referendum) ይወሰናል የሚሉት ፈሊጥ አላቸው። ወያኔዎች ይህንን የሚሉት አለምክንያት አይደለም። ባለፉት አርባ አመታት በተለይ ወልቃይት ጠገዴን በወረራ ከያዙበት ከ1972 ዓም ጀምረው ወልቃይት ጠገዴ ዉስጥ መሬት ላይ ያለውን የህዝብ አሰፋፈር እኛን በሚጠቅም መንገድ ቀይረናል ብለው ስለምያምኑ ነው። መቼም እንደነመለስ ዜናዊና እንደነ ስብሐት ነጋ አስተሳሰብ ትግርኛ የሚናገር ሰው የሚኖርበት ቦታ ሁሉ የትግራይ ክልል አካል ቢሆን ኖሮ ደቡባዊ ኤርትራም እስከ ሐማሴን ድረስ የትግራይ ክልል አካል መሆን ነበረበት – ወይም አፋን ኦሮሞ የሚናገረው የኬንያ ክፍልና አፋርኛ የሚናገረው የጂቡቲ ክፍል በሙሉ የኢትዮጵያ አካል መሆን ነበረበት። 

ሰሜን ኢትዮጵያ ዛሬም እንደቀድሞው የጦርነት ደመና አንዣቦባታል፣  ዛሬ ጎንደር ዉስጥ ወያኔ ወልዶ ወያኔ ያሳደገቸው የቅማንትና የወልቃይት ጠገዴ የማንነት ጥያቄዎች ተቃቅፎና ተደጋግፎ የኖረን አንድ ህዝብ ቅማንትና አማራ፣ አማራና ትግራይ እያሰኘ ወደ ጦርነት እያመራ ነው። ጦርነት የሰለቸው የወልቃይት ጠገዴና የአካባቢው ህዝብ የአገር ሽማግሌዎችን መርጦ አዲስ አበባ ድረስ በመላክ አቤቱታውን ጉዳዩ ለሚመለከተው ለፌዴሬሺን ምክር ቤት አሰምቷል። የሰላም ቋንቋ የማይገባውና በሰላማዊ መንገድ ለሚደረጉ ምንም አይነት እንቅስቃሴዎች ቦታ የማይሰጠው ወያኔ ግን ህዝባዊ አቤቱታውን ተቀብሎ መፍትሄ እንደ መፈለግ ከአቤቱታ አቅራቢዎች ዉስጥ አንዳንዶቹን እየመረጠ ማሰር ጀመረ። በነገራችን ላይ የወልቃይት ጠገዴና የአካባቢው ህዝብ መርጦ አዲስ አበባ ከላካቸው የአገር ሽማግሌዎች ዉስጥ አንዳንዶቹ ዛሬም ድረስ ዬት እንደደረሱ አይታወቅም። ኢትዮጵያ ዉስጥ በየትኛውም ደረጃ የሚነሱ የማንነት ጥያቄዎችንና በብሄር ብሄረሰቦች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን ተመልክቶ ውሳኔ የሚሰጠው የፌዴሬሺን ምከር ቤት ነው። የወልቃይት ጠገዴና የአካባቢው ህዝብም የአገር ሽማግሌዎች መርጦ አዲስ አበባ ድረስ የላከው የፌዴሬሺን ምክር ቤቱ ማንነቱን በተመለከተ የደረሰበትን በደል ተመልክቶ ፍትሃዊ ውሳኔ እንዲሰጠው ነበር። ሆኖም ነገሩ አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይነቃም ነውና የፌዴሬሺን ምክር ቤቱ እሱ እራሱ ተመልክቶ ውሳኔ መስጠት የሚገባውን ጉዳይ የትግራይ ክልል መንግስት ይመልከተው በማለት ችግርን ለችግር ፈጣሪው እንዲተላለፍ አድርጓል። የህወሓት መሪዎች በፍትህ መቀለድ ልማዳቸው ስለሆነ ነው እንጂ የወልቃይት ጠገዴ ጥያቄ የሁለት ክልሎች ጥያቄ በመሆኑ እዚያው ፊዲሬሺን ምክር ቤት ዉስጥ ውሳኔ ማግኘት ነበረበት እንጂ በምንም አይነት ወደ ትግራይ ክልል መመራት አልነበረበትም። ደግሞም ይህንን ወያኔ ለረጂም ግዜ አስቦበት የሰራውን ስራ የፌዴሬሺኑ ምክር ቤት አየው የትግራይ ክልል መንግስት አየው በሁለቱም ቦታዎች ውሳኔ ሰጪዎቹ ያው የህወሓት ሰዎች ናቸውና ውሳኔው ለውጥ አይኖረውም።

ኢትዮጵያ በለውጥ ማዕበል በምትናጥበት ወቅት ወልቃይት ጠገዴ ዉስጥ በተለይ ዳንሻ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ወልቃይት ጠገዴ የጎንደር አካል ነው የሚሉና የለም ወልቃይት ጠገዴ የትግራይ አካል ነው የሚሉ የተለያዩ ኃይሎች ህዝባዊ ስብሰባዎችንና ሰላማዊ ሰልፎችን አካሂደው ነበር። እነዚህ ሁለት ሰልፎች አግሩ አዲስ አበባን ከረገጠ ጀምሮ የምናውቀውን የወያኔን ማንነት እንድናረጋግጥ አድርገውናል። ህወሓት እራሱ የጻፈውን ህገ መንግስት አክብረው በሰላማዊ መንገድ “ማንነታችን ይከበር” ብለው መሰብሰብ የሞከሩ ኃይሎች መሰብሰብ አትችሉም ተብለው በጠመንጃ ኃይል እንዲበተኑ ሲደረግ በአንጻሩ ወልቃይት ጠገዴ የትግራይ አካል ነው ብለው ነገር ግን ህግ መንግስቱን በመጣስ የጦር መሳሪያ አንግበው የተሰበሰቡ ኃይሎች ግን የፖሊስ ጥበቃ ሲደረግላቸው ታይቷል። ዳንሻ ዉስጥ የወልቃይት ጠገዴን ትግራይነት ደግፈው የወጡ “ሰላማዊ ሰለፈኞች” ያነገቡትን ጠመንጃ ላይና ታች ከፍና ዝቅ እያደረጉ እየዘለሉ ሲጨፍሩ የፌዴራል ፖሊስና የአካባቢው ሚሊሺያ ጥበቃ አድርጎላቸዋል። በወቅቱ ኦሮሚያ ዉስጥ በግልፅ እንዳየነው ከመሬታችን አታፈናቅሉን ብለው ባዶ እጃቸውን የተቃውሞ ሰልፍ ያደረጉ ወጣቶች ግንባር ግንባራቸውን በአልሞ ተኳሽ ጥይት እየተመቱ ረግፈዋል። የኦሮሚያ ክልል መንግስት ፕሬዚዳንት ተብዬው ሙክታር ከድር እነዚህን ባዶ እጃቸውን የተቃውሞ ሰልፍ ሲያደርጉ የረገፉትን ወጣቶች ነው እርምጃ የተወሰደባቸው በጸጥታ ኃይሎች ላይ ሲተኩሱ ነው ብሎ የከሰሳቸው። መቼም የወያኔ ነገር ሁሌም የተገላቢጦሽ ነው። ህገ መንግስቱን አክብረው በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞ ያቀረቡ ኃይሎችን ግንባር ግንባራቸውን በጥይት እየመታ ይገድላል። የራሱን ህገ መንግስት በሚጻረር መልኩ የጦር ሜዳ መሳሪያ አንግበው ሰላማዊ ሰልፍ ለሚያካሄዱ ኃይሎች ደግሞ የፖሊስ ጥበቃ ያደርጋል።

የህወሓት ህልም መነሻው “ታላቋ ትግራይ”  መድረሻው ደግሞ “የትግራይ ሪፑብሊክ” ነው። ይህ ህልም በ1972 ዓም በተግባር መተርጎም ሲጀምር የመጀምሪያዋ ሰለባ ወልቃይት ጠገዴ ነበረች። እርግጠኛ ነኝ የወልቃይት ጠገዴ የማንነት ጥያቄ መልስ የሚያገኘው የአካባቢውን ህዝብ ታሪካዊ ማንነት ደፍጥጦ ወያኔ በቀዶ ጥገና በሳለው ካርታ ላይ ተመስርቶ ከሆነ የህወሓት መጥፊያ የሚጀምረው ከወልቃይት ጠገዴ ይሆናል። ወያኔ በጉልበት ትግራይ ካልሆንክ እያለ የሚጨቀጭቀው የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ማንነቴን የማውቀው እኔ ነኝ ብሎና በማንነቱ ተደራጅቶ በህጋዊ መንገድ ማንነቴን አክብሩልኝ እያለ ነው። አንድም ቀን የህዝብን ጥያቄ በተገቢው መንገድ መልሰው የማያውቁት የህወሓት መሪዎች እኔ አማራ እንጂ ትግራይ አይደለሁም ብሎ ጥያቄ ላቀረበ ህዝብ ጥያቄህን የሚመልሰው የትግራይ ክልል መንግስት ነው የሚል ቧልትና ሸፍጥ የተቀላቀለበት መልስ ሰጥተውታል። የህወሓት መሪዎች የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ጥያቄ የሚመለከተው ወልቃይት ጠገዴንና ትግራይን ብቻ ነው ብለው አስበው ከሆነ እጅግ በጣም ተሳስተዋል። የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ጥያቄ የአማራ፣ የወላይታ፣ የሶማሌ፡ የአፋር፣ የሲዳማ . . ወዘተ ባጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ ነው። ስለዚህ የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ በጠመንጃ ተገድዶ አለማንነቱ ሌላ ማንነት ሲሰጠው ቆሞ የሚመለከት ኢትዮጵያዊ የለም።

ዕብሪተኞቹ የወያኔ መሪዎችና የጭፍን አላማ ተከታይ ምሁሮቻቸው በምናባቸው ስለው ያስቀመጡት የታላቋ ትግራይ ካርታ ዛሬ ከተደበቀበት ወጥቶ በየቦታው እየታየ ነው። ህወሓቶች ሃያ አምስት አመት ሙሉ እንዳሰኛቸው እየረገጡ ሲገዙን ዝም ስላልናቸው የታላቋ ትግራይ ካርታ ብቻ ሳይሆን ልባቸውም ከሚገባው በላይ አብጦ ትልቅ ሆኗል። በደቡብ ምዕራብ ወልቃይት ጠገዴን ጠቅልሎ ትግራይን ከሱዳን ጋር ያገናኘው የታላቋ ትግራይ ካርታ ታች ታቹን እንደ ሐርግ እየተመዘዘ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና ከዚያም አልፎ ጋምቤላን በርቀት እየተመለከተ ነው። ይህ የኛ ዝምታ በረዘመና የህወሓቶች ልብ ባበጠ ቁጥር እያደገ የሚሄደው የታላቋ ትግራይ ካርታ መቆሚያም ያለው አይመስልም። ወያኔና ያዩት አሻንጉሊት ሁሉ የነሱ የሚመስላቸው ህጻናት አንድ ናቸው። ህጻናት ወላጆቻቸው ቤት ዉስጥ ካልገሯቸው መዋዕለ ህጻናት ሲሄዱ ችግር መፍጠራቸው አይቀርም። የወያኔም ነገር እንደዚሁ ነው። ወንዝና ድንግል መሬት ባየ ቁጥር የምትታየው ታላቋ ትግራይ ብቻ ናት። የኢትዮጵያ ህዝብ ይህንን መቆሚያ የሌለው ዕብደት በግዜ ህክምና ካልፈለገለት ሁላችንም ጨርቃችንን ጥለን የምናብድበት ቀን ሩቅ አይደለም። ወልቃይት ጠገዴን በወረራ ይዞ በጠመንጃ እያስገደደ የነዋሪውን ማንነት ሲቀይር ዝም ብለን የተመለከትነው ወያኔ ዛሬ የልብ ልብ ተሰምቶት በቤኒሻንጉል በኩል ወደ ጋምቤላ እያመራ ነው። ይህንን ክረምት በመጣ ቁጥር እየሞላ በጎርፍ የሚያስቸግረንን ወንዝ ገድበን ማቆም ያለብን ከባህር ጋር ከመቀላቀሉ በፊት ነው እንጂ ባህሩን ከተቀላቀለማ ወንዝ መሆኑ ቀርቶ እሱ እራሱ ባህር ይሆናል  . . . . . ባህር ደግሞ ሰፊ ነውና አይገደብም። 

ይህ ፅሁፍ የተጻፈው በፈረንጆቹ ዘመን አቆጣጠር በ2016 ዓ.ም. አሥመራ በነበርኩበት ግዜ ነው፣ ጽሁፉ በወቅቱ በትንሳኤ ሬዲዮ ቀርቧል፣ በ2017 ዓ.ም. ሜልቦርን እና ብርስበርን ላይ በተደረገው የአርበኞች ግንቦት 7 ህዝባዊ ስብሰባ ላይም ቀርቧል። 

__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

2 COMMENTS

  1. ይህ ሰው በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋ የመጻፍ ትልቅ ተሰጥኦም ልምድም ያለው ሰው ነው፡ ከ15 አመት በፊት ብሎገር ሳለ ጀምሮ ተከታትየዋለሁ። እንግሊዝኛን እንደፈረንጆቹ ከሚጽፉ በጣም ጥቂት ኢትዮጵያዊያን ውስጥ አንዱ ነው፣ በአማራኛም ሲጽፍ የደቡብ ሰው አይመስልም። ምነው እነዚያን ብርሃኑና አንዳርጋቸው የሚባሉ ፖለቲከኞች ትቶ ብጽፍ- አማራ ጠል እየተባለ የሚሰደበው ኤፍሬም ስለወልቃይት የጻፈውን ሰዳቢዎቹ አስበውም የሚያውቁ አይመስለኝም- ትልቅ ኢትዮጵያዊ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here