spot_img
Wednesday, June 7, 2023
Homeነፃ አስተያየትገንፎ “እፍ እፍ” ሲሉሽ ሊውጡሽ ስለሆነ እውነት አይምሰልሽ!(ኃይለማርያ ደንቡ)

ገንፎ “እፍ እፍ” ሲሉሽ ሊውጡሽ ስለሆነ እውነት አይምሰልሽ!(ኃይለማርያ ደንቡ)

- Advertisement -

ኃይለማርያ ደንቡ
ሐምሌ 11 2013 ዓ.ም .

ለብዙ ዓመቶች ውጭ አገር በመኖሬና ከፈረንጆች ጋር አብሮ በመኖርና በመስራት ስለቆየሁ ጠባያቸውን በደንብ የተረዳሁ ይመስላል፡፡ አቤት ስልጣኔአቸው የሚደነቅ ነው፡፡ አቤት ተንኮላቸው የሚኮነን ነው እያባበሉና እያሳቁ ማረድ፡፡

ድሮ እኔ የምኖርበት ሰፈር በጣም የታወቁ አንድ ሽማግሌ ሰው ነበሩ፡፡ ሰፈር ውስጥ የተቸገረ ሰው ካገኙ ቶሎ ብለው በዚያ ቃላት መምረጥና ማሳመር በሚችል ምላሳቸው ሰውዬውን: “አይዞህ እኔ አለሁልህ እኔ ጋ ያለውን በግ ሸጠህ ጊዜያዊ ችግርህን ተወጣ” ይሉታል፡፡ ችግረኛው ለእውነትና ከልብ የመነጨ ሀሳብ መስሎት ደስ ብሎት በጉን ሸጦ ጊዜያዊ ችግሩን ይወጣል፡፡ ምንም የሌለው የነጣ ደሀ ከሆነ ግን  ከመጀመሪያውኑ አንድም ቃላት አይተነፍሱም፡፡ አይዞህ ተብሎ በግ የተሰጠው ደሀው ሰውዬ ቢያንስ ጊደር ወይንም ወይፈን እንዳለው “ለጋሹ ደጉ ሽማግሌ” ቀደም ብለው ጠንቅቀው ያውቃሉ እቅዳቸው ትንሽ  ሰጥቶ ብዙ መቀበል ነውና ሳይውል ሳያድር ምንም ሳይቸግራቸው ቸግሮኛልና ጊደርህን ወይንም ወይፈንክን ካልሰጠኸኝ ይሉታል፡፡ ይሉኝታ ያለው ደጉ ሕዝባችን እውነትም የተቸገሩ መስሎት ያለውን ጊደሩን ወይንም ወይፈኑን ይሰጣል፡፡ ከብዙ ጊዜ የድግግም ማታለል በኋላ ግን ሽማግሌው አታላይ መሆናቸው ታወቀባቸው፡፡ 

የእኛ የታዳጊ አገሮችና ያደጉ የከበርቴ አገሮች ግንኙነት ከዚህ ጋር ይመሳሰላል: እንዲያውም ይብሳል፡፡ 

ስልጣኔ በመሰረቱ ተፈጥሮን መቆጣጠር ነው፡፡ ይህ ሁሉም ሰው የሚመኘውና የሚፈልገው ጥሩ ነገር ነው፡፡ ይሁን እንጂ መጥፎ ጎኖችም አሉት ሰዎች ተፈጥሮን በመግራት ምርታማ ለመሆን የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ወደ ስልጣኔ የሚያሻግር ቢሆንም በተፃራሪው አሉታዊ ክስተቶችን ይዞ ይጓዛል፡፡ 

ምንም ነገር በጊዜና በቦታ የሚታይና የሚጨበጥ: በሂደቱ ላይ የሚንፀባረቁ ኩነቶች አሉ፡፡ የውስጥ ቅራኔ የፈጠራቸው ተቃራኒ ኩነቶች ናቸው፡፡ ተፈጥሮ የራሱ የሆነ ሕጎችና ሂደቶች አሉት፡፡ ሰው የሚሉት ፍጡር ብቻ ነው ይህንን የተፈጥሮ ሕጎችን የሚያዛባው፡፡ ይህም በመሆኑ ነው ተፈጥሮም በበኩሉ የራሱን ምላሽ የሚሰጠው፡፡ የአየር ብክለቶችና የኮሮና ቫይረስ የመሳሰሉት ክስተቶች ዕድገት የፈጠራቸው የስልጣኔ ቅራኔ ውጤቶች ናቸው ፡፡ያደጉ አገሮች የፈጠሯቸው ግን ለእኛም የተረፉ ችግሮች ናቸው፡፡ የሰለጠኑ አገሮች ባንድ በኩል እነሱ ያፈሩትን የቴክኖሎጂ ውጤቶችን እያፈኑ: በሌላ በኩል የእኛን የአፍሪቃ የተፈጥሮ ሀብቶችን በርካሽ ገዝተው ያንኑ እቃ ለእኛው መልሰው በውድ ዋጋ እየሸጡ በአንድ ፍታዊ በሆነ ዓለም ውስጥ አብረን እንኖራለን ይሉናል፡፡  

በታዳጊ አገሮችና ባደጉ አገሮች መካከል ያለው የሥራ ክፍፍል በአንድ ቀፎ ውስጥ ያለ የንብ ሕብር የሚያደርገው የስራ ክፍፍል አይነት ነው፡፡ በንብ ሕብር ውስጥ ያሉት ንጉስ ንግስት ሰራተኛ አንድ ቤት ውስጥ እየኖሩ ሁሉም የድርሻቸውን ሰርተው የድርሻቸውን እንደሚካፈሉ ሁሉ: ዓለምም በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ እየኖረ በየሕብረተሰብ ተከፍሎ እያንዳንዱ ሕብረተሰብ የድርሻውን ሰርቶ: የድርሻውን እኩል የሚካፈል ነው፡፡ ስለዚህም ዓለም ድሀና ሀብታም የማይለይ ወደ አንድ ስልጣኔ ማዕከል (Globalization) የሚጓዝ ነው ይሉናል፡፡ 

በዚህ በተዛባና በጥቅም በተከፋፈለ ዓለም እያንዳንዱ መንግስት ለራሱ ጥቅም ሲል የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡ ሁሉም ለራሱ ነውና: ታዳጊ አገሮችም በዋናነት አገራችን ኢትዮጵያም ሁኔታውን ተረድታ አሸንፋ መውጣት ነው የሚጠበቅባት፡፡ 

ወደ አነሳነው ነጥብ እንመለስና አሁን ባለንበት ዘመን በታዳጊ አገሮችና ባደጉ አገሮች መካከል ተባብሶ የመጣው ትግል ጥሬ እቃ አቅርቦት ላይ ነው፡፡ 

የተፈጥሮ ሐብቶች እንክብካቤ ካልተደረገላቸውና በጥንቃቄ ካልያዟቸው አላቂዎችና ጠፊዎች ናቸው፡፡ “አለው አለውና: አለው አለውና … “እንደሚባለው ያደጉ አገሮችም የተፈጥሮ ሀብታቸውን አሉት አሉትና አላቂና በሕይወትም ላይ ያልተጠበቁ የጤና እክሎችን ማምጣቱን ሲገነዘቡ ፊታቸውን ወደ አልተነካው የተፈጥሮ ሀብት የበለጠ ወዳለበት ታዳጊ አገሮች እንዲያዞሩ አድርጓቸዋል፡፡

ዘረፋው መልኩን ቀየረ እንጂ ድሮም የነበረ ነው፡፡ ድሮ ታዳጊ አገሮችን የቀኝ ግዛት በማድረግ ሲዘርፉ ነበር፡፡ ዛሬ ግን የኃይል አሰላለፍ በአለም ደረጃ ትንሽ በመቀየሩና የታዳጊ አገሮችም ተጠናክሮ መምጣት ዘረፋውን በዘዴ ማድረግ ሆኗል፡፡ እንደ ድሮው አገሮችን የቀኝ ግዛት በማድረግ በማስገደድና በማስፈራራት መውሰድ ሳይሆን እንደ ዘዴኛው ሽማግሌ በብልሀትና በዘዴ መውሰድ ሆኗል፡፡ 

ሰውየው መሪ ሲሆን የእኛ አገልጋይ ይሆናል ብለው ያሰቡት ሰው ገና አመራር ላይ ሳይወጣ ጀምሮ ያዘጋጁታል፡፡ ምናልባት ያ አገልጋይ ይሆናል ተብሎ የታጨው መሪ እነሱ በማይፈልጉት ሁኔታ መስመር ቀይሮ መሄድ ከጀመረ: የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር በቅድምያ በዚያው አገር የተንሸዋረሩ ምሁሮችን በመጠቀም በሕዝብ እንዲጠላ ካደረጉ በኃላ ከስልጣን እንዲባረር ያደርጉታል፡፡ አሊያም መፈንቅለ መንግስት ያዘጋጃሉ፡፡ ዛሬ በተጨባጭ እንደምናየው የታዳጊ አገር መሪዎችን ስልጣን ላይ አውጪም አውራጅም እነሱ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ዛሬ አገራችን ኢትዮጵያ ውስጥም ይህንን ደባ ለመፈፀም በመዘጋጀት ላይ ያሉ ይመስላል፡፡ 

ጠ/ሚኒ ዶ/ር አብይን የሰላም ተሸላሚ አድርገው ሲያቀርቡት እነዚህ ፈረንጆች ምን አስበው ይሆን? ለኢትዮጵያ የደገሱላት የተንኮል ድግስ ምን ይሆን? ብዬ ከመጀመሪያውኑ ጥርጣሬ ውስጥ ገብቼ ነበር፡፡ “ሳያሽ የበላ ዝንጀሮ ሲሰል ያድራል” ነውና ተጠራጠርኩ፡፡ ከጥቅማቸው አንፃር ካልሆነ በስተቀር: ለኢትዮያ አንድም ቀን አስበው የማያውቁ ያደጉ የከበርቴ አገሮች: መሪያችንን ያለምክንያት አልነበረም እንደዚያ ሲያቆላምጡት የነበረው፡፡ የዓለም የሰላም መሪ፣ የአፍሪቃ ሰላም ፈጣሪ፣ ለኢትዮያ ብሔር ብሔረሰቦች ለእኩልነት የቆመ ታላቀ መሪ፣ የሰው ዘር በቅድሚያ የተገኘው ከዶክተር አብይ አገር ነው፣ እናም እኛና ዶ/ር አብይ አንድ ነን፣ እንዲያው ዶክተር አብይ ምን ያልተሸለመው፣ ስለ ዶክተር አብይ ምን ያልተወራ፣ እና ምን ያልተባለ ነገር አለ? ለካስ ዶክተር አብይን እንደ ገንፎ እፍ፣ እፍ ፣ እያሉ ሲያመቻቹት የነበረው ቀደም ሲል እንደ ጠረጠርኩት በሁለት አቢይ ጉዳዮች (በአባይና በሕወሃት ጥያቄዎች) ከእነሱ ጋር ስምምነት እንዲፈጠር ነበር፡፡ 

አባይ እኮ ትልቅ የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት ነው፡፡ አባይ እኮ ከቤንዚን ከናፍጣና ከሌሎች የማዕድን ሐብቶችም በልጦ የሚገኝ የተፈጥሮ ስጦታ ነው፡፡ ግድቡን ተግባራዊ ማድረግ ከተቻለ እኮ ተስማሚ የአየር ንብረታችንን ተጠቅመን እንኳን አፍሪቃን የመካከለኛ ምስራቅ አገሮችንም ጨምሮ መመገብ እንደምንችል  ያውቃሉ፡፡ አባይ በሚፈጥረው የውሀ ኢነርጂ ብቻ ምን መሆንና ምን ማድረግ እንደምንችልና እንደ አባይ ሙላት ጠላቶቻችንን ጠራርገን እንደምንወስድ ያውቃሉ፡፡ የፍራፍሬው፣ የአሳና የአዞ ሀብቱ፣ ተጨምሮ ኢትዮጵያ ወደፊት በአፍሪቃ አህጉር ምን ስፍራ እንደሚኖራት በቅጡ ያውቃሉ፡፡ ስለሚያውቁም ነው እነሱ የሚመሩት እንደ ዓለም ባንክ የመሳሰሉት የፋይናንስ ተቋሞች ለአባይ ግድብ የገንዘብ እጃቸውን ምንም የማይዘረጉት፡፡  ስለሚያውቁ ነው የሀይል አሰላለፍ ለእነሱ ወደሚያመቸው ወደ መካከለኛ ምስራቅ በኩል እንዲያጋድል አንዴ በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሌላ ጊዜ ደግም በአውሮፕያዊያኖች ሽምግልና እንዲያልቅ አስታራቂ ልሁን ባይ የሚሉት፡፡ 

“አለው አለውና: አለው አለውና…” ነው ያለው ዘፋኙ፡፡ አዎ ጠ/ሚኒስቴር ዶ/ር አብይም ቢሉት ቢሉት ከፈገግታውና ከቆንጆ ቁመናው በስተቀር በኢትዮያ አንድነትና ሉአላዊነት ላይ እንዳለፉት ትላልቅ የኢትዮጵያ መሪዎች: ለመጥቀስም ያህል: እንደ አፄ ዘራያዕቆብ፣ እንደ አፄ ቴዎድሮስ፣ እንደ አፄ ዩሐንስ፣ እንደ አፄ ሚኒልክ፣ እንደ አባባ ጃንሆይና፣ እንደ ጓድ መንግስቱ፣ የማይደራደር መሪ ሆኖ አግኝተውታል፡፡ 

ጠ/ሚኒስቴርዶ/ር አብይን በአባይ ጥያቄ አባብለው፣ አለስልሰው፣ እፍ እፍ ብለው፣ እንደ ገንፎ በቀላሉ አልዋጥ ሲላቸው፣ ሁለተኛውን አማራጭ ከሕወሃት ጋር ተደራደሩ የሚል ስልት መንደፍ ጀመሩ፡፡ እዚህም ለይ በመጀመሪያ ለስለስ በማለት ምክር መስጠት ጀመሩ፡፡ ምክር መስጠት ይቻላል ይፈቀዳል፡፡ ይህ አልሳካ ሲል ደግም ወደ ማስገደድና ተጽኖ ወደ መፍጠር መሻገር ጀመሩ፡፡ ይህ እጅ መጠምዘዝ በሰለጠነ ዓለም ውስጥ አይቻልም፤ አይፈቀድም፡፡ በዓለም አቀፍ ሕግ ወዳጃዊ መንግስቶቹም ሆኑ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ለአንድ አገር መንግስት ይበጃል የሚሉትን ሀሳቦችና ምክሮች መለገስ ይችላሉ፡፡ ከዚያ ባሻገር ግን እንዲህ አላደረግክምና እንዲህ አድርግ፡፡ እንዲህ ካላደረግክ እንዲህ እናደርግሀለን ማለት አይችሉም፡፡ ይህ ዛቻ ነው፤ ይህ ማስፈራራት ነው፤ ይህ ጣልቃ ገብነት ነው፡፡ 

በዓለም አቀፍ ግንኙነት እነዚህ ሁሉ በፍፁም የተከለከሉ ናቸው፡፡ ጣልቃገብነት በአለም አቀፍ ሕግ በፍጹም የተከለከለ ነው፡፡ የተባበሩተ መንግስታት ድርጅት በቻርተሩ ካስቀመጣቸው ዋና ዋና መርሆዎች አንዱ፤ ማንም አገር በሌላው ሉዓላዊ አገረመንግስት የውስጥና የውጭ ስራዎች ጣልቃ መግባት እንደሌለበት ነው የሚደነግገው፡፡ እስኪ መርሆዎቹን እንዳሉ ላስቀምጣቸው፡፡ 

According to the United Nations Charter, it is prohibited to intervene “in matters, Which Are Essentially within the domestic Jurisdiction of any State”.

According to the 1970 Declaration, Principles of non-interference constitutes a prohibition of direct or indirect intervention for any reasons “in the internal or external affairs of any other State “in accordance with that declaration the sub-stance of that principle includes the following:

  1. A prohibition of armed intervention or all other forms of interference or attempted threat against the personality of the state or against its political, economic and cultural elements;
  2. A prohibition of economic, political or any other measures whose aim is to coerce another state in order to obtain from it the subordination of the exercise of its sovereign rights and to secure from it advantages of any kind;
  3. A prohibition measures designed to organize, assist foment, or permit subversive, terrorist or armed activates directed towards the violent other throw of the regime of another state;
  4. A prohibition of interference in civil strife in another state;
  5. A prohibition of the use of force to deprive peoples of their national identity;
  6. The right of every state to choose its political, economic, social and cultural systems without interference from other state. 

ታድያ እነዚህን የዓለም አቀፍ ሕጎችና መተዳደሪያ ደንቦችን ሳያውቋቸው ቀርቶ ይሆን? የለም በቅጡ ያውቋቸዋል፡፡ የሚታገሉት ለእኛ ሳይሆን ለራሳቸው ጥቅም ስለሆነ የዓለም አቀፍ ሕጉን ለእነሱ በሚያመች ሁኔታ ቢተረጉሙት አይደንቅም፡፡ ሕወሀትና የኤርትራው ኢፒኤልኤፍ ፀረ ኢምፔሪያሊዝም የነበረውን ደርግ ለመጣል ኢምፔሪያዝም ያቀነባበራቸው ድርጅቶች ነበሩ፡፡ አላማቸው ኢትዮጵያን ማዳከም ነበረና ኤርትራን ከኢትዮጵያ አስገንጥሎ ኢትዮጵያን ወደብ አልባ አድርጎ ባድመንም ማስነጠቅ ነበርና ተሳክቷል፡፡ አሁን ደግሞ ይህም አልበቃ ብሎ የቀረውን ያልተሳካውን ለማሳካት ዶር አብይን እፍ እፍ ማለት ጀመሩ፡፡  

ሕወሀት ያከተመ ያለቀለት ድርጅት ነው፡፡ ግን ፖለቲካው እከክልኝ ልከክልህ ነበርና ውለታ ለዋለላቸው የቀድሞ የሕወሀት መንግስት ውለታ መመለስ አለባቸውና መንግስት ሽብርተኛ ብሎ በሕግ ከፈረደበት ድርጅት ጋር ታረቁ ይሉናል፡፡ 

ምንም ይበሉ ምን፣ያም ሆነ ይህ፣በኢትዮጵያ ሉአላዊነት ላይ መደራደር አንችልም፡፡ የምዕራቦች ፉከራ የኢኮኖሚ እቀባ ከመጣል አያልፍም፡፡ አሜሪካ ማዕቀብ ጥላለች፡፡ የአውሮጳ ሕብረትም ይከተላል፡፡ እኛ በቅጡ ከተደራጀን እንወጣዋለን፡፡ አያስፈራም አገር በራሱ የተፈጥሮ ሐብትና በራሱ ሕዝብ የስራ ጥረት እንጂ በብድርና በእርዳታ አይቀየርም ስልጣን ላይ ባስቀመጡት አሻንጉሊት መንግስት ሰጠን አበደርን እያሉ በተዘዋዋሪ መንገድ ገንዘቡ ተመልሶ ወደ እነሱ ካዝና ሲገባ እንጂ እርዳታውና ብድራቸው አገር ሲያለማ አይተን አናውቅም፡፡ 

አሁን ያለው መንግስት አሁን እንደጀመረው ለኢትዮጵያ ሉአላዊነት አንድነት ክብርና ብልጽግና ቆርጦ ከተነሳ ልድገመውና ማዕቀቡን መወጣት ይቻላል፡፡ በቅጡ ከተደራጀን እንኳን የእነሱ የኢኮኖሚ ጫና፣ ጦርነትም ቢከፍቱብን እንደልማዳቸው ተዋርደው በመጡበት ይመለሳሉ፡፡ ቬትናም አዋርዳ አባራቸዋለች፡፡ አፍጋኒስታን አዋርዳ አባራቸዋለች፡፡ ኩባም እንደዚሁ አዋርዳቸዋለች፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ የቀድሞ ታሪኳን መልሳ ለመድገም ምንም የሚያግዳት ነገር የለም፡፡ ኢትዮጵያ የጀግኖች ተምሳሌት ናት፡፡ ኢትዮጵያ የነፃነት ምልክት አገር ናት፡፡ ግን ዓለም ይወቅ፣ አፍሪቃዊያኖች ይወቁ፣ አዲሱ ኢምፔሪያሊዝም ኢትዮጵያን ሊወርና ሊያስወርር እየመከረ መሆኑን፡፡ 

ኢትዮጵያን ወክሎ የዓለም አቀፍ ግንኙነቱን የሚያካሄደው ፌዴራላዊ መንግስት እንጂ ክልላዊ መንግስቶች አይደሉም፣ የማዕከላዊ መንግስት ሳያውቅና ሳይፈቀድ ማናቸውም መንግስቶቹም ሆኑ የአለም አቀፍ ድርጅቶቸ ከክልል መንግስቶች ጋር ቀጥታ ግንኙነት መፍጠርና ማንኛውንም አይነት እንቅስቃሴዎች ማካሄድ አይችሉም፡፡ የሚሰጡት ዕርዳታ ካለም በፌዴራ መንግስት በኩል ብቻ ነው መካሄድ ያለበት፡፡ እርዳታው በምን መልኩ የፖለቲካ ትርፍ ማግኛና የስለላ ቁማር መጫወቻ መድረክ ሊሆን አይችልም፡፡ 

የፌዴራል መንግስት ሳያውቅ የሚደረጉ ማንኛውንም አይነት እንቅስቃሴዎች የጣልቃ ገብ እንቅስቃሴዎች ናቸው፡፡ የዓለም አቀፍ ሕግን የሚጻረሩ እንቅስቃሴዎች ናቸውና በጥብቅ የሚወገዙ ናቸው፡፡ 

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስትና በአሸባሪው የወያኔ ትግራይ ክልላዊ መንግስት መካከል የተፈጠረው ግጭት ውስጣዊ ግጭት ነው፡፡ ይሄ የኢትዮጵያ መንግስት የውስጥ ጥያቄ ነው፡፡ ምንም አለም አቀፍ ይዘት የለውም፡፡ በመሆኑም ማናቸውም መንግስታት ሆኑ የአለም አቀፍ ድርጅቶች አያገባቸውም፣ አያሳስባቸውም፡፡ የኢትዮያ መንግስት ችግሩን በሚመስለውና በሚፈልገው ሁኔታ መፍታት ይችላል፡፡ 

ጠ/ሚኒስቴር ዶ/ር አብይ በአፍሪቃ አህጉር የጀመሩትን የሰላም ጥሪ በሚያስተዳድሩት ትግራይ ክልልም እንዲተገበር ደግመው ደጋግመው የሰላም ደወል ደውለዋል፡፡ አሸባሪው የወያኔ ትግራይ ክልላዊ መንግስት (ሕወሀት) ተንኮል እንጂ ፍቅር የማይገባው ድርጅት በመሆኑ የዶ/ር አብይን የመደመር ፍልስፍናን፣ ማለትም ቅራኔዎችን አርግቦ፣ አብሮ በጋራ በፍቅር፣ በሰላምና በዴሞክራሲ፣ የመኖርና የመስራት ፍልስፍናን እንዲቀበሉ አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአንድ ስፍራ ወደ ሌላ ስፍራ ለስራ፣ ለጦርነት፣ድርቅና ረሀብ ሲያጠቃውም እንዲሁ፣ ሌላ ቦታ ሰፍሮ የኖረና የሚኖር ህዝብ ነው፡፡ ይህ ህዝብ በሰፈረበት እና በኖረበት አካባቢ ካሉ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ተጋብቶ እና ተዋልዶ አንድ ሆኖ የኖረ ህዝብ በመሆኑ በፍፁም ሊለያይ የማይችል፣ የትግራይ ህዝብ ለዚህ ለኢትዮጵያዊ አንድነቱ ቅድሚያውን የሚይዝ ብሔር መሆኑን ጠ/ሚኒስቴር ዶክትር አብይ መደመር በሚለው መፀሕፋቸው አብራርተዋል፡፡ 

ጠ/ሚኒስቴር ዶክትር አብይ በእየፖለቲካ መድረኩም የኢትዮጵያ ሕዝብ እርስ በእርሱ የሚዳመር እንጂ በፍፁም በብሄር የሚለያይና የሚቀናነስ ሕዝብ እንዳልሆነም በቅጡ ተናግረዋል፡፡ ግን ምን ያደርጋል፣ ሕዝብን ከሕዝብ፣ ብሄርን ከብሄር፣ ሲያጋጭ የኖረ ሕወሀት ግን የመደመር ፍልስፍናን በመናቅ ይባስ ብሎ እንዲያውም እንደገና ወደ አመራር ካልተመለስኩ ብሎ በኢትዮጵያ ሰራዊት ላይ ድንገተኛ ጥቃት እና ጦርነት ከፈተ፡፡ ስለዚህ በሕወሀት ላይ የሚደረገው የአፀፋ ምት ትክክለኛ እርምጃ ነው፡፡ ለግማሽ ምዕተ ዓመት ያህል አሸባሪ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በድርጊቱ ሽብርተኛ ስለሆነ ሽብርተኛ ድርጅት መባሉም ትክክል ነው፡፡

ይህንን እብሪተኛ የሕወሀት ድርጅት ለመቅጣት ፌዴራላዊ መንግስት ከፈለገ ብቻውን፣ አሊያም ከሚፈልጋቸው ወዳጅ መንግስቶች ጋር መተባበር ይችላል፡፡ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለማስከበርም ሆነ የኢኮኖሚ እድገቱን ለማፋጠን ይበጀኛል ከሚላቸው ከመረጣቸው መንግስታት ጋር የብዙ ዓመት ውሎችን መፈራረምም መብቱ ነው፡፡ መንግስት ቀዳማዊ የዓለም አቀፍ ግንኙነት አቀናባሪና እሱን የሚበልጥ ከመንግስት በላይ የሆነ ሌላ ልዩ ሃይል የለምና በሁሉም ነገር ወሳኝ አካል ነው፡፡  

የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግስት ይህንን ሽብርተኛ ድርጅት ለማጥፋት ከኤርትራ መንግስት ጋር መተባበሩ ሙሉ መብቱ ነው የኢትዮጵያ መንግስት የኤርትራ ወታደሮች ወደ ኢትዮያ መግባታቸውና አለመግባታቸው ለማንም መግለጫ የመስጠት ግዴታ የለበትም፡፡ ለመግባታቸው ወይንም ይግቡ አይግቡ ለማለትምውል መፈረም አይጠበቅበትም የሁለቱ መንግስቶች ምስጢራዊ ይሁን ይፋዊ ስምምነት መኖሩ ነገሩን በሙሉ ሕጋዊ ያደርገዋል፡፡

የኤርትራ መንግስት ይህንን ሽብርተኛ የሕወሀት ክልላዊ ሽብርተኛ ድርጅት በመቅጣትም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን ለማሸመድመድ በሚደረገው ሩጫ ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም ኢትዮጵያን ለመርዳት የሚያደርገው ቆራጥነትና መስዋዕትነት እጅግ ያስመሰግነዋል፡፡  

የዓለም አቀፍ ኢምፔሪያሊዝም ኢትዮጵያን ለማዳከም ኤርትራን ከኢትዮጵያ ገንጥሎ ሁለት ደካማ መንግስቶችን ፈጥሮ የኃይል ሚዛኑ ወደ መሀከለኛ ምስራቅ እንዲያጋድል የማድረጉንና ዛሬም ይህንን አቅዶ ለመተግበር በሚሯሯጥበት ወቅት “የተለያዩ ሕዝቦች” እንደገና የአንድነት መንፈስ ማሳየታቸውን አይወደውም በፍጹም አይፈልገውም፡፡ ለዚህም ነው የኢትዮጵያ መንግስት የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ ይውጡልኝ ሳይል የኤርትራ ወታደሮች በነዋሪው ሕዝብ ላይ በደል ፈፅመዋል ሳይል እነሱ የሽብርተኛው  ሕወሀት አፈቀላጤ በመሆን ለትግራይ ሕዝብ ያሰቡ በማስመሰል የኤትራት ወታደሮች በፍጥነት ይውጡ የሚሉት ለዚህ ነው፡፡ የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ የመውጣትና አለመውጣት ጉዳይ መወሰን የሚችለው የኢትጵያ መንግስት ብቻ ነው፡፡  ከዚህ አልፎ የኢትዮጵያ መንግስት ሚያከናውናቸው የውስጥና የውጭ ስራዎች ውስጥ ገብቶ ትዕዛዝ ለማስተላፍ የሚሞክሩ ኃይሎች ሁሉ የዓለም አቀፍ ሕግን የሚጥሱ ጣልቃገቦች ናቸው፡፡  

ከሁሉም በላይ የሚገርመው ደግሞ ፌዴራላዊ መንግስት በክልል መንግስት ለይ ሕግን ለማስከበር የሚወስደው ርምጃ በሁለት ሉዓላዊ መንግስቶች ለምሳሌ በኢትዮጵያና በሱዳን መንግስቶች መካከል የሚደረግ ጦርነት በማስመሰል ተደራደሩ ለእርቅ ቅረቡ ይላሉ፡፡ የክልሎችም ዳር ድንበርና ወሰን እነሱ የከለሉት ይመስል የአማራው ልዩ ሀይል የያዘውን የትግራይን ግዛት ለቆ መውጣት አለበት ይላሉ፡፡ 

አዝናለሁ እጅግ በጣም አዝናለሁ፡፡ ርህሩሁና ጀግናው የትግራይ ሕዝብ ለዚህ አገር አጥፊና ኢትዮጵያን ያለ ወደብ ላስቀረው እብሪተኛ የሕወሀት ድርጅት ተገዥ ሆኖ መቅረቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ሕወሀት የዘረፈውን ገንዘብ በውጭ አገር ባንክ ተቀምጦ ዛሬ ፈረንጆች ከሚዘርፉት ለትግራይ ክልል ለልማት ውሉ ሕዝቡ የልማት ተጠቃሚ ሆኖ ዛሬ ለዚህ ድርጅት ተቆርቋሪ ቢሆኑ አይደንቅም ነበር፡፡ ግን የትግራይ ሰፊው ሕዝብ በጦርነት ከመማገድ በስተቀር ያተረፈው ነገር የለም፡፡ ያም ሆኖ ግን አሁን ኢትዮጵያን ክፉኛ ያጠቃው የብሄረተኝነት ጉንፋን የትግራይ ብሔረሰብንም ክፉኛ አጥቅቶታል፡፡ ትሁትና ጨዋው የትግራይ ሕዝብ ከዚህ ጉንፋን መላቀቅ አለበት፡፡

ነገሮቹ ብዙ ውስብስብ ናቸው፡፡ ያም ሆኖ ሕግ ለማስከበር በሚወስደው እርምጃ አመራሩና ሕዝቡን መለየትና ሕዝቡ ጉዳት እንዳይደርስበት መንግስት ትልቅ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ማሳሰቡ ተገቢ ነው እላለሁ፡፡ ቀሪው የኢትዮያ ሕዝብም አቅሙ በሚፈቅደው መሰረት ይህ ሕዝብ እንዳይቸገር ማድረግ ያለበትን ሁሉ መፈፀም ይጠበቅበታል፡፡ እንዲያውም ለዚህ ዓላማ ብቻ የቆመ ድጋፎቹን የሚያቀነባብር አንድ ተቋም ቢቋቋም ተገቢ ይሆናል እላለሁ፡፡  

በትንሹም ቢሆን ካለይ እንዳብራራሁት አገራችን ኢትዮጵያ አስቸጋሪ በሆነ የሽግግር ጉዞ ውስጥ ትገኛለች፡፡   ሽግግሩ የተሳካ እንዲሆን የጠ/ሚኒስቴር የመደመር ፍልስፍና የሚደገፍ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ማንኛውም የሽግግር ሕብረተሰብ ጠንካራ እጅ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ዶር አብይም ጠንካራ እጅ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ከውጭ ጠላቶቻችን ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ላይ የሚያብሩ የውስጥ ጠላቶቻችን ዝም ብለው የሚታዩ አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያ በሕግ የምትተዳደር አገር መሆን አለባት፡፡ አገር በሕግ ይተዳደራል፡፡ ሕግ ግን ያለ ሀይል አይሰራም፡፡ ሕግ ያለ ሀይል ቀለም የጨረሰ ወረቀት ነው፡፡ 

ማንኛውም የሚፈለገው ለውጥ በሰዎች የትብብር ጥረቶች ነው የሚካሄደው፡፡ የጠ/ሚኒስቴር ዶ/ር አብይ የመደመር ፍልስፍና ፍልስፍናውን በተቀበሉና እውቀት ባላቸው ሰዎቸ መካሄድ ይኖርበታል፡፡ የፖለቲካ ስልጣኑ አገርና ሕዝብ እኩል በሚያስተዳድሩና የብሄረሰቦችን እኩልነት በተግባር በሚተገብሩ ምሁሮች እጅ መግባት አለበት፡፡  ጠላቶቻችን ያልነበሩን ችግሮች እንደነበሩ ሲያደርጉ፣የነበሩ ችግሮችን ደግሞ ሲያጎሉና ሲያገዝፉ እናያቸዋለን፡፡ አፍሪቃን በብሄር ጦርነት ማግደውትና አቃቂመውት ወደ ሰላም መመለስ አልቻለም፡፡  በተለያዩ ዘዴዎች እንደ ሌሎች አገሮች ለመበታተን ሞክረው ያልተሳካላቸው ሀገርና ህዝብ ቢኖር አገራችን ኢትዮጵያ ብቻ ነበረች፡፡  ዛሬ ግን የተሳካላቸው ይመስላል፡፡ በቀይ ባሕር በኩል ይገቡ የነበሩ የኢትዮጵያ ወራሪ ጠላቶችን በግንባር ቀደም አዋርዶ ይልካቸው የነበረው የአማራና የትግራይ ሕዝብ ዛሬ እርስ በርስ እንዲጋደሉ አድርጓቸዋል፡፡  በፍቅር ተጋብቶና ተዋልዶ አብሮ የኖረ የአማራና የኦሮሞ ሕዝብም እያደባደቡት ነው፡፡  እንደ እነ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ (አባ መላ) የመሳሰሉ ብልህና ጀግና በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ቅንጣት ያህል ጥርጣሬ ያልነበራቸው መሪዎች ያፈራ ትልቁ የኦረሞ ብሄረሰብ ዛሬ አገር ተወራለች ከጠላት ጋር ተዋደቅ፣ በጠላት ላይ ዝመት ከማለት ይልቅ በአማራ ብሄረሰብ ለይ ዝመት የሚሉ ጽንፈኞችን አፍርቷል፡፡ እና በዚህም ጠላቶቻችን የተሳካላቸው ይመስላል፡፡ 

ያም ሆነ ይህ በአማራ ብሔረሰብ ላይ የሚደርሱት ጥቃቶችና ማንኛውም አይነት ተጽዕኖዎች በአፋጣኝ መቆም አለባቸው፡፡ በብሄር ብሄረሰቦቸ መካከል ያሉት ልዩነቶች በውይይትና በዲሞክራሲያዊ መንገድ የሚፈቱ እንጂ በፍፁም እርስ በእርሰ የሚያጋድሉና አንዱ በአንዱ ላይ ተነሳ የሚያሰኙ አይደሉም፡፡ ዛሬ በአማራ ብሔሬሴብ ላይ እየደረሰ ያለው ጥፋት ዲሞክራት የሆነ ኃይል ሁሉ ድርጊቱን መቃወምና በጋራ ታግሎ ችግሩን ማቆም መቻል አለበት፡፡ ይሁን እነጂ ዛሬ አገራችን እንዲህ ውጥረት ላይ ባለችበት ጊዜ የማይተኙ ጠላቶችዋ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እርስ በርስ እየተናበቡ ባሉበት፣ የውስጥ ፅንፈኛ ሀይሎችም ከእነዚሁ ጠላቶች ጋር ሆነው አብረው እየወጉን ባሉበት፣  ለአማራ ብሄረሰብ ቆመናል በማለት አሁን የሚደረገውን ዲሞክራሲያዊ የሆነ የሽግግር ጉዞን የሚቃወሙ ሀይሎች አውቀውም ይሁን ሳያውቁ  ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ተሰልፈዋል፡፡ “አንገት የተፈጠረው አዙሮ ለማየት ነው” ይባላልና የፖለቲካ አቋማቸውን አዙረው የሚመለከቱበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ 

የ360 ሚዲያ ተሰላፊዎቸ ለዚህ ቅድሚያውን ቦታ ይይዛሉ፡፡ አቶ ኤርሚያስ አንተን መሳዮች እንጂ ምሁሮችን አታሳምንም፡፡ “ተኩላ እንደ አንበሳ እጮህ ብላ ተተረተረች” ይባል የለም?

የኢትዮጵያ ከዝቅተኛ ስርዓተማህበር ወደ ከፍተኛ ስርዓተማህበር በመሸጋገር ለይ ትገኛለች፡፡ ይህ የሕብረተሰብ አስቸጋሪ ሽግግር ወቅት 300፣ 500 እና 600 ዓመታት ሊፈጅ ይችላል: የላይ መዋቅሩ የተስተካከለና በኢኮኖሚው ላይ መደመራዊ ስኬቶች የሚያመጣ ከሆነ፣ ምሁሩ እድገት የሚጎትተው ጎጣዊ የሆነ ብሄራዊ አስተሳሰቡን አሽቀንጥሮ ጥሎ፣ በአገር ደረጃ ማሰብ ከጀመረና፣ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ከተጣደፈ፣ የሽግግር ጉዛውሊቀንስ ይችላል፡፡ በዚህ ሕብረተሰብ ውስጥ ያሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ነባራዊ ስለሆኑ፣ በሂደት እንጂ በፖለቲካ አዋጅና፣ ብዙዎች እንደሚያስቡት የመንግስት ለውጥ በማድረግ ብቻ የሚፈቱ አይደሉም፡፡ 

አገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት የተወሳሰቡ ችግሮች የብሄረሰብ ችግሮችንም ጨምሮ ጠ/ሚኒስቴር ዶር አብይ የፈጠራቸው ችግሮች አይደሉም፡፡ የኖሩ የነበሩ፣ ያሉና የሚኖሩ፣ ችግሮች ናቸው፡፡ በእነዚህ ችግሮች አፈታትና መፍትሄ አሰጣጥ ላይ ከጠ/ሚኒስቴር ዶር አብይ ጋር ላንስማማ እንችላለን፡፡ ግን እነዚህን ችግሮች በጋራ እንወያይና እንፍታ ከማለት ይልቅ ጠ/ሚኒስቴር አልፈታቸውምና ከጠላት ጋር ተባብረን ኢትዮጵያን እናፈርሳለን፤ ጠ/ሚኒስቴር ዶር አብይን ከስልጣን እናወርዳለን፤ ማለት የፖለቲካን “ሀሁ” አለማወቅ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ምሁር ልማዱ ነው፡፡ የተደራጀና ስልጣን ሊረከብ የሚችል ድርጅት በሌለበት ሁኔታ የመጣውን መንግስት ሁሉ ውረድ ውረድ ማለት፣ ስርዓት አልበኝነት ብዙ ጊዜ የእሱ መለያ ተግባር ሆኗል፡፡ መቼ ነው እንደዚህ አይነት ብልሽቶች ከኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ የሚጠፉት? አሁን የምርጫው ሂደት ተጠናቋል፣ ከአሁን ጀምሮ ተስፋዬ የሰላምና እርቅ ሂደቶችን ማየት ነው፡፡ አገር አቀፍ አገርን የማዳን የሰላምና የዕርቅ ጥሪ እንዲደረግም የሁልጊዜ ምኞቴ ነው፡፡ 

አመሰግናለሁ::

ኃይለማርያ ደንቡ – Hailemariam Denbu (International Law Practicioner)

Email: berekefet@gmail.com

__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
12,879FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here