spot_img
Friday, June 14, 2024
Homeነፃ አስተያየትየጠቅላይ ሚኒስትሩ አደንቋሪ ዝምታና መዘዙ

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አደንቋሪ ዝምታና መዘዙ

 ከጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ
ሃምሌ 22 ቀን 2013

ዶ/ር ዐብይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መጥተው፤ ለኢትዮጵያ ያላቸውን ራዕይ ካበሰሩና፤ ኢትዮጵያን ወደፊት የሚያራምዱ ፖሊሲ በመንደፋቸው፤ ፖሊሲያቸውን ከሚደግፉ ሰዎች አንዱ ነኝ። ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ስልተ ስርዓትን ለመገንባት የሚያስችል ተቋማትን በመገንባት እና፤ በተለይም፤ ትህነግ የሰለበውን ኢትዮጵያዊ ስነ ልቦና መልሶ በመጠገን በኩል ያሳዩት አመራር ለብዙ ኢትዮጵያውያን ምሳሌ የሚሆን ጥሩ መሰረት  ጥለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በትጋትና በቅንነት ለሃገር ከፍተኛ ሥራ እየሰሩ ቢሆንም፤ በርካታ ድክመቶችም ታይተውባቸዋል። ከነዚህ ድክመታቸው በዋናነት የሚገለፀው፤ ሃገር ውስጥ ቀውስ በገጠመ ቁጥር፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መገኘት በሚገባቸው የአመራር ቦታ አለመገኘታቸው ነው። 

የአንድ ሃገር መሪ፤ ከሚጠበቅበት ተግባር አንዱ፤ በሃገር ውስጥ ቀውስ ሲኖር፤ በአደባባይ ወጥቶ ሕዝቡን ማረጋጋት እና፤ የመንግስትን አቅጣጫና የሚወሰደው ቀጣይ እርምጃ ምን እንደሆነ ለሕዝብ በግልጽ ማሳወቅ ነው። በዚህ ረገድ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በግልጽ ያየንው፤ አደባብይ ወጥቶ ለሕዝብ ገለፃ ከማድረግ፤ ሕዝብን ከማበረታታና ከማጽናናት፤ እንዲሁም ቀጣዩ አቅጣጫ ምን እንደሆነ ከማብራራት ይልቅ፤ ከሕዝብ የሚደበቁ መሆናቸው ነው። በተለያዩ አካባቢዎች፤ በንጹሃን ዜጎች ላይ ጭፍጨፋ ሲፈፀም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ ሃገር መሪ፤ አደባባይ ወጥተው ለሕዝብ ገለፃ ከማድረግ እና ለሕዝብ ተስፋ ከመስጠት ይልቅ፤ ዝምታን በመምረጣቸው፤ በተደጋጋሚ ከመወቀሳቸውም በላይ፤ “ከጽንፈኞች ጋር አብረው ይሰራሉ” እስከሚል ክስ ድረስ ሲቀርባባቸው ቆይቷል። ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በፓርላማ፤ ወይም ፕሮጀክቶች ሲመሩ፤ ወይም አልፎ አልፎ በሚሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፤ በኋላም ደግሞ በጽሁፍ፤ በዜጎች ላይ የሚፈፀመውን ግድያ ይናገሩና ያውግዙ እንጂ፤ በቀጥታ በመገናኛ ብዙሃን ላይ ወጥተው “ሕዝብን ለማጽናናትና” ተስፋ ለመስጠት ጊዜ መድበው፤ ለሕዝብ ማብራርያ የሰጡበት ጊዜ ትዝ አይለኝም። 

ሃገር ቀውስ በገጠማት ጊዜ፤ አንድ የሃገር መሪ፤ ሕዝብን ለማጽናናት እና ለማበረታታ ከሚያደርገው ገለፃ በላይ፤ የሕዝብን ልብ የሚያረጋጋና፤ ለሕዝብ ተስፋ የሚሰጥ ነገር የለም። ፈረንጆቹ የሃገራቸውን መሪዎች፤ አንዱ ሥራቸው (comforter-in-chief) መሆን ነው ይላሉ፤ በግርድፉ “አጽናኚ መሪ” ለማለት ነው። የሃገር መሪዎች፤ አጽናኚ መሪ የሚሆኑበት ምክንያት፤ ሃገር ቀውስ በገጠማት ጊዜ፤ ሕዝቡ ከመንግስት  ግልጽ አቅጣጫ የሚጠብቅ በመሆኑ ነው። የሃገር መሪ አደባባይ ወጥቶ፤ በመገናኛ ብዙሃን ለሕዝቡ፤ ያለውን ወቅታዊ ጭብጥ፤ መንግሥት ለመውሰድ የተዘጋጀው እርምጃ ምን እንደሆነ፤ ቀውሱ እንደሚያልፍ እና ለውጥ እንደሚመጣ፤ መንግሥት ቀውሱን ለመፍታት የሚመድባቸው የሰው እና የገንዘብ ሃይል ምን እንደሚመስል፤ የማስረዳት ሃላፊነት አለባቸው። ይህ ግን በተደጋጋሚ፤ በዶ/ር ዐብይ አስተዳደር ተዘንግቱላ፤ የተፈጠረው ክፍተትም ብዙ መላ ምቶችን ያስተናገደ በመሆኑ፤ ለፖለቲካው አለመረጋጋትም እንደ አንድ ምክንያት ይጠቀሳል።  

በአንድ ወቅት ዶ/ር ዐብይ ሲናገሩ፤ እሳቸው ባለፈ ችግር ላይ ከማተኮር ይልቅ የወደፊት ዕድልና ተስፋ ላይ ማተኮር እንደሚፈልጉ ገልፀዋል። ለሳቸው ግልጽ መሆን ያለበት ግን፤ ይህ የግል ጉዳያቸው ሣይሆን፤ የሃገር ጉዳይ መሆኑ ነው። በግል ሕይወታቸው፤ የፈለጉትን መርህ መከተል ይችላሉ፤ በሃገር ጉዳይ ግን፤ የሃገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ ይኖርባቸዋል። በብሔራዊ ችግር ጊዜ፤ የሕዝብን ስነ ልቦና በበቂ ሁኔታ ማረጋጋት የሚችለው የሃገር መሪ ነው። በተለይ አሁን በማህበራዊ ሚድያዎች፤ እና እራሳቸውን ጋዜጠኛ ብለው በመደቡ አውታሮች በሚነዙ ያልተጣሩ ወሬዎች፤ ሕዝብ በቀላሉ እንደሚረባበሽ ግልጽ ነው። በዚህም ምክንያት የፌደራል መንግሥቱ፤ ቶሎ ቶሎ ለሕዝብ መረጃዎችን መስጠትና፤ ቀወስ ባጋጠመም ቁጥር፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፍጥነት፤ ለሕዝብ መግለጫ መስጠት ይኖርባቸዋል። 

በጣም አሳዛኙና አስገራሚው፤ በተለይ፤ በጥቅምት 24 ቀን 2013 ሕወሃት በሃገር ላይ ጥቃት ከፈፀመ በኋላ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፓርላማ ውጭ እና ፕሮጄክት በሚያስመርቁበት ጊዜ ከተናገሩት ውጭ፤ ለሕዝብ ጊዜ መድበው መግለጫ የሰጡት አንዴ ብቻ ነው። ከዚህም አልፎ፤ የፌደራል መንግሥቱ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት ከሚሰጠው መደበኛ ጋዜጣዊ መግለጫ በስተቀር፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ምንም ዓይነት መደበኛ ጋዜጣዊ መግለጫ የማይሰጥ መሆኑ፤ አስገራሚ ብቻ ሳይሆን፤ ሃገሪቱን የሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ድኩማን አስመስሏታል። ለነገሩ፤ የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽ/ቤት የሕዝብ ግንኙነት ከፍል ቢኖረውም፤ ይህ ጽ/ቤት በምን ሥራ ላይ እንደተጠመደ ለማንም ግልጽ አይመስለኝም። 

ይህ ጦርነት ከተጀመረ ጀምሮም፤ በፌደራል መንግሥቱ በኩል የሚታየው ግልጽነት የጎደለው አካሄድ እና አንዳንዴም ዓይን ያፈጠጠ ውሸት ሃገራችንን ብዙ ዋጋ እያስከፈላት ይገኛል። በርካታ ውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና በሃገር ውስጥም ያሉ ዜጎች የፌደራል መንግሥቱ አካሄዱን ግልጽ ያድርግ ብለው ቢወተውቱም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “አደንቋሪ ዝምታቸውን” ቀጥለውበታል። ይህ ፍፁም ግራ የሚያጋባ ነው። በተለይም፤ የመከላከያ ሰራዊቱ፤ ከትግራይ የወጣበት ምክንያት እና አወጣጡ፤ አሁን ድረስ የተድበሰበስና፤ አሁንም በተለያዩ አካባቢዎች፤ መከላከያው የሚያደርገው ማፈግፈግ፤ ምንም ትርጉም የማይሰጥ ከመሆኑም በላይ፤ በብዙዎች ዘንድ ጥርጣሬን እየፈጠረ፤ ጥያቄንም እያጫረ መጥቷል። የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት፤ በፖለቲካዊ ውሳኔ፤ እጅና እግሩን የፊጢኝ በመታሰሩ፤ ሚናውን የክልል ልዩ ሃይላት እየተኩት ይገኛሉ። ይህ ለምን ሆነ? ምንም እንኳን የፌድራል መንግስቱ “የተናጠል የተኩስ አቋም አውጃለሁ” ሲል፤ አንዱ ለሕዝብ የገለፀው ነገር፤ “ሕወሃት ትንኮሳውን ከቀጠለ፤ እርምጃ እውሰዳለሁ” የሚል ቢሆንም፤ ሕወሃት በተለያዩ አካባቢዎች፤ ከትንኮሳ አልፎ፤ በህዝብ ላይ ግድያ በንብረትም ላይም ውድመት ሲፈጽም፤ የመከላከያው እንዲያጠቃ ትዕዛዝ ለምን እንደማይሰጠው ግልጽ አይደለም። እንደምንሰማው፤ በተለያዩ አካባቢዎች፤ በመከላከያው ማፈግፈግ፤ ወጣቱ እየተቆጣ አካባቢውን ለመከላከል እራሱ እየዘመተ ይገኛል። ይህ እጅግ አሳሳቢ ነው። የፌደራል መንግስቱስ የት ገባ የሚል ጥያቄንም የሚያጭር ነው። 

የበርካታ ሃገራት መሪዎች፤ ሃገራቸው ቀውስ ሲያጋጥማት፤ በፍጥነት ለሕዝብ መገለጫ ይሰጣሉ። በቅርቡ፤ በጀርመን፤ በቱርክ፤ በቻይናና በኦስትሪያ፤ ከፍተኛ የጎርፍ መጠልቅለቅ በመከሰቱ፤ በሰው እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። በሃገራቱም ላይ ከፍተኛ ቀውስ ፈጥሯል። የእነዚህ ሃገራት መሪዎች ያንፀባረቁት የጋራ ባህሪ፤ እና የመሪነት ሚና፤ በፍጥነት ወጥተው ለሕዝብ መግለጫ መስጠት ብቻ ሳይሆን፤ በጎርፍ የተጎዱ አካባቢዎችን በመጎብኘት ሕዝቡን ማረጋጋት እና አካባቢውን መልሰው በመገንባት፤ ሕዝቡ ወደ ነበረበት ቀደምት ሕይወቱ እንደሚመለስ ቃል በመግባት ለሕዝቡ ተስፋ የሰጡበት ሁኔታ ነው። እኛ ሃገር ይህ የሆነው፤ በመጀመሪያዎቹ የዶ/ር ዐብይ አስተዳደር ወቅት፤ በተለይም በሰኔ 16ቱ የመስቀል አደባባይ የቦምብ ጥቃት የተጎዱ ሰዎችን ዶ/ር ዐብይ በሆስፒታል የጎበኙበት ጊዜ ነው። እኚያ ዶ/ር ዐብይ፤ አሁን የት ገቡ?

ዛሬ ኢትዮጵያ ከምንጊዜውም በላይ፤ የፌደራል መንግስቱ በአጠቅላይ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ፤ በትግራይ ክልል ቀውስ ላይ በማተኮር አመራር የሚሰጡበት እና ከሕዝብ ጋር ግልጽ ውይይት የሚያደርጉበት ጊዜ መሆን አለበት። ይህ ሁሉ ሰው ቀፎው እንደ ተነካ ንብ ከጫፍ እስከ ጫፍ ተነስቶ፤ ለዓመታት ታይቶ በማይታወቅ ኢትዮጵያዊ ወኔ ወደ ጦር ግንባር በሚዘምተበት ጊዜ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አደንቋሪ ዝምታ የት ገቡ የሚያሰኝ ብቻ ሳይሆን፤ ለብዙዊች አስገራሚ ሆኗል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬም 2% የማይሞላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚጠቀመው የማህበራዊ ገፆቻቸው መልዕክት በማስተላለፍ ተጠምደዋል፤ የሚያስተላለፉት መልዕክት ግን፤ ለሃገሩ ምንም ትርጉም እንደሌለውና አብዛኛው ኢትዮጵያዊ እንደማያየው የሚነግራቸው ሰው እንዴት አጡ? አንዳንድ ከመንግሥት ጋር ቅርበት ያላቸውን ሰዎች፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የዝምታ  ችግር ምን እንደሆነ ስጠይቅ የሚሰጠኝ መልስ፤ “ዐብይ፤ ብቃት በሌላቸው አማካሪዎች ተከበዋል፤ እሳቸው ጋር መድረስ አይቻልም” የሚል ነው። በእርግጥ ይህ ብቃት ያለው አማካሪ የሚጠይቅ ነው ወይ? ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብዙ ያነበቡ እና የሚያነቡ መሆኑም ይነገራል፤ ታድያ፤ በቀውስ ወቅት፤ የሳቸው የመሪነት ሚና ወሳኝ እንደሆነ እንዴት ሊጠፋቸው ይችላል? 

እውነት ለመናገር፤ በዚህ ወሳኝ ጦርነት፤ ሃገሪቱ በፌደራል ደረጃ መሪ አልባ ናት ማለት ይቻላል። የፌደራል መንግስቱን ሚና የአማራ ክልል መስተዳደር ተረክቦታል። ስለጦርነቱ፤ ዕለታዊ መግለጫ እንኳን የሚሰጠው የአማራ ክልል መስተዳድር የኮምኒኬሽን ቢሮ ነው፤ ለምን? ይህ ጦርነት እኮ የአማራ ክልል እና የሕወሃት ጦርነት አይደለም፤ በኢትዮጵያ እና በሕወሃት መሃከል እንጂ። ታድያ የፌደራል መንግሥቱ ዝምታን ለምን መረጠ? ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጠላት ታግተው የተያዙ ይመስል፤ ልምን ዝምታውን መረጡ? በዚህ የሃገር ቀውስ ወቅት፤ ሕዝቡን ካላበረታቱ፤ የጦርነቱን አቅጣጫ ለሕዝብ ካላሳወቁ፤ በሕዝብ ላይ የሚፈጠረው የስነ ልቦና ጫና የሚያስከትለው አደጋ አልታያቸውም ወይ? እነዚህ እና መሰል ጥያቄዎች መልስ ማግኘት አለባቸው። 

የጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አደንቋሪ ዝምታም፤ በአለም የሕዝብ ግንኙነት መድረክ ላይ ሃገራችን፤ “ሽንፈት” እንዲያጋጥማት አድርጓል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እራሳቸው ቢያንስ በሁለት ወር አንዴ፤ የዓለም አቀፍ መገናኛ አውታሮችን በመጥራት፤ የጦርነቱን አካሄድ እና ፤ የዓለም አቀፍ ሕብረተሰቡም ሆነ የምዕራቡን የዜና አውታራት ቅጥፈት ማጋለጥ ይችሉ ነበር። ስለዜና አውታራቱም ሆነ የምዕራባውያን ቅጥፈት፤ እሳቸው ቢናገሩት፤ በዓለም ደረጃ መነጋገሪያ የሚሆን፤ የኢትዮጵያንም አቋም ሙሉ ለሙሉ የሚያብራራ በሆነ። ይህ ግን አልሆነም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያን ድምጽ ሊያሰሙ የሚችሉበትን ትልቁን የድምጽ ማጉልያ (megaphone) ይዘው ለምን አደንቋሪውን ዝምታ መረጡ? ለምንስ ሜዳውን ለትህነግ ሙሉ በሙሉ ለቀቁ? የቦዘኔ ባሕሪ ያለው ጌታቸው ረዳ የድምጽ ማጉያውን በደንብ እየተጠቀመበት በመሆኑ ነው፤ የዜና አውታሮች፤ የሕወሃትን ውሸት ብቻ የሚዘግቡት፤ እኛ በሜዳው ላይ ሳንገኝ፤ የዜና አውታራቱን ብቻ መውቀስም ተገቢ ላይሆን ይችላል።   

የአብዛኛው ሰው ግምት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዝምታን የመረጡት፤ በመእራባውያን ተጸኖ ነው ይላሉ፤ ለዚህ ምንም ዓይነት ጭብጥ ባይኖርም፤ ተገቢ መላ ምት ነው። የፈለገ ዓይነት የምእራባውያን ተጽእኖ ቢፈጠር ግን፤ ሕዝቡ ከተባበረ፤ ወገቡን ጠበቅ አድርጎ ያልፈዋል። በምዕራባውያን በኩል ያልሰማነው እና በኢትዮጵያ ወታደራዊ እርምጃ ላይ ለመውሰድ ያቀዱት እርምጃም ካለ ይነገረን። እኛን የቸገረን፤ የጠቅላይ ሚኒስሩ ዝምታ፤ እንዲሁም የፌደራል መንግስቱ፤ መገኘት በሚገባው ቦታው አለመገኘት ነው። ሕዝብ የማወቅ መብት አለው። ሕዝብን ለተወሰነ ጊዜ ዋሽቶ ጊዜ መግዛት ይቻላላ፤ እውነቱ ግን ይወጣል፤ ይህንንም “የኢርትራ ወታደሮች አልገቡም” በሚለ አላስፈላጊ ውሸት አይተነዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩና ፌደራል መንግሥቱ አሁን እየሄዱበት ባለው አቅጣጫ ከቀጠሉ፤ ሃገሪቱ ለበለጠ ቀውስ ትዳረጋለች የሚል ሥጋት አለኝ። ጠቅላይ ሚኒስትሩን ነቅንቆ፤ ከተኙበት “ጥልቅ እንቅልፍ” የሚቀሰቅሳቸው ሰው ያስፈልጋል። ሃገራችን፤ በቂ ወኔ፤ በቂ የሰው ሃይል፤ በቂ ትጥቅና ስንቅ አላት። ሊሞቱላት የተዘጋጁ ወጣቶች ወደ ጦር ሜዳው እየተመሙ ነው። የፌደራል መንግሥቱ “የተቅለሰለሰ” አቋም እና ግልጽነት የጎደለው አካሄድ፤ እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስትሩ አደንቋሪ ዝምታ፤ በሕዝቡ ውስጥ ብዙ ጥያቄን እያጫረ እና፤ በስነ ልቦናውም ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ የፌደራል መንግስቱ አመራር መስጠት፤ ወይም ገለል ብለው አመራሩን ለክልል መስተዳደሮች መተው አለባቸው። ተወደደም ተጠላም፤ የፌደራል መንግስቱ አመራር ሰጠም አልሰጠም፤ ሕዝቡ ሃገሩን ይከላከላል፤ ኢትዮጵያንም ከማንኛውም አጥፊ ሃይል ይታደጋል። ይህ ለወዳጅም ለጠላትም ግልጽ መሆን አለበት። በዚህ አጋጣሚ መጠየቅ የምፈልገው፤ ሃገሪቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አላት ወይ የሚለውን እና፤ ይህ ምክር ቤት ስለጦርነቱ አካሄድ መሰረታዊ ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የማይጠይቅበት ምክንያት ምንድነው የሚለውን ነው። 

                            እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን ይባርክ፤

__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

1 COMMENT

  1. በሚገረም አገላለፅ ነው እውነታውን ያሰቀመጠከው ግን አንድ የረሳሀው ነገር ጠቅላይ ሚንሰትሩ አፈፈ ቅቤ መሆኑን እን የእሱ ሰልጣን እሰከተጠበቀ ድረስ አይመለከተውም አንድ ያለገባው ነገረ ግን እየገዘገዙት አንደሆነ በቅጡ አለተረዳም እያደረገ ያለው ሀገሪቶን እሱ ድሬም ባደረጋት መለስ ነው እየነዳት ያለው ያደሞ ምን ያህል እርቀት ያሰኬዳል የምናየው ነው ለማንኛውም እንደዜህ አየነተ ሀሳቦቸ በጣም ጠቃሜ ሰለሆነ keep it up thanks

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here