በደነቀ ተሰማ
ሐምሌ 25 2013 ዓ.ም .
መግቢያ
ቀደምት የኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲ አላማና ግብ መሰረት የሚያደርገው ቅቡልነቱ የተረጋገጠ ሃገር ግንባታና የግዛት አንድነት ማስጠበቅ ላይ ነው በሚለው ብዙ ጸሃፊዎች ይስማማሉ፡፡ ግንኙነቶች በወታደራዊና በዲፕሎማሲያዊ ትብብር ላይ የሚያተኩሩ ሆነው ከውጭ የሚገኘው ዲፕሎማሲያዊ እና ሁሉ አቀፍ ድጋፍ የስርዓቱን ኃይል የሚያጠናክሩም እንደነበሩ ይነገራል፡፡ የንጉሳዊያኑ እና የወታደራዊ መንግስት የውጭ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ የታሪክ ሂደቶች የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት ለድርድር እቅርበው አያውም፡፡ ማለትም እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ ዳር ድንበርን የማስጠበቅ፣ ዲፕሎማሲያዊ ቅቡልና ነጻ የፖለቲካ-ማህበረሰብ የመፍጠር ጉዳዮች ለድርድር የማይቀርቡ ሆነው ቆይተዋል፡፡
የድህረ-1983 ዓ.ም. የውጭ ፖሊሲና አተገባበር ከወታደራዊው ዘመን የተለየና በተለይ በአፈጻጸሙ፣ በተለዋዋጭነት ባህሪው በአመዛኙ ከጃንሆይ ዘመን የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡ የዚህ ጽሁፍ ትኩረት በድህረ-1983 ዓ.ም. በ1994 የጸደቀው የውጭ ጉዳዮችና የደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ የተሰኘው የውጭ ጉዳይንና ብሄራዊ ደህንነትን በአንድ ላይ ጠምሮ የያዘው የፖሊሲ ሰነድ ነው፡፡ ሰነዱ ኢትዮጵያ ከልማትና ዲሞክራሲ ከፍ ያለ ጉዳይ የላትም የሚል አይነት ነው፡፡ በአመዛኙ በደርግ ዘመን ይስተዋል የነበረውን የመከበብን አውድ ያለውን የፖሊሲ አተያይ ያስቀረም ነው፡፡ አለም አቀፍ አጋር ከማበጀት አንጻርም ተጣጣፊ፣ ተለዋዋጭ የሆነ እንዲሁም ከወታደራዊ ዘመን የስጋት ትንተና የተለየና ከውስጥ ወደውጭ (in ward looking policy approach) የሚመለከት የፖሊሲ አቅጣጫ ነው፡፡ የፖሊሲ መነሻ የተደረጉት ጉልህ ጉዳዮች ልማትና ዲሞክራሲ፣ ብሄራዊ ክብርና ኩራት እና ግሎባላይዜሽን ናቸው፡፡
በውጭ ግንኙነቱና ዲፕሎማሲ ልማትንና ዲሞክራሲ ለማሳካት እንዲሁም የውጭ ስጋቶችን ቀንሶ ለሀገሪቱ ሰላም ምቹ ሁኔታ መፍጠር አላማ ያለው የፖሊሲ ሰነድ ነው፡፡ ስድስት ፖሊሲውን ማስፈጸሚያ ስትራቴጂዎች የተቀመጡ ሲሆን እነዚህም በውስጥ ጉዳይ ላይ አበክሮ መስራት፣ ኢኮኖሚ ተኮር ስትራቴጂ፣ በተገቢ ትንተና ላይ ተመስርቶ እድሎችን አሟጦ መጠቀም፣ በተገቢ ትንተና ታግዞ ስጋቶችንና ለስጋት ተጋላጭነትን መቀነስ እና አስተማማኝ የመከላከያ ኃይል መገንባት የሚሉ ናቸው፡፡
በአፈጻጸምም በርካታ አህጉር አቀፍና አለም አቀፍ ግንኙነቶች ተከናውነዋል፡፡ እንደቀድሞዎቹ ስርዓቶች ለፓን አፍሪካኒዝም ዝግመተ-ለውጥ የመርህና የአፈጻጸም ግብአቶችን በማበርከት፣ አፍሪካን በአለም አቀፍ መድረኮች በመወክል እንዲሁም ክልል አቀፍ የሆኑ የአፍሪካ የትብብር ማዕቀፎችን (በኢጋድ፣ በኮሜሳ) በመምራትና በመሳተፍ አይተኬ ሚና መጫወቷም የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው፡፡ ይህም በሰላምና ደህንነት ጥበቃ-በሰላም ማስከበር ውጤታማ ዘመቻዎችን በመፈጸም፣ በጸረ-ሽብር ዘመቻ፣ በአየር ንብርት ለውጥ ፎረሞች ተሳትፎና በአለም አቀፍ ድረጃ የአፍሪካዊያንን ጥቅም በማሳወቅና በመደራደር ወዘተ የሚገለጽ ይሆናል፡፡ በ2010 ዓ.ም. መረጃ መሰረት ለአፍሪካ ህብረት 6.8 ሚሊዮን ዶላር አመታዊ መዋጮ በማድረግ አለም አቀፍ ኃላፊነቷን እየተወጣች ትገኛለች፡፡ መዋጮውን በወጥነት ከሚከፍሉ 11 አገሮች አንዷ ስትሆን መዋጯቸውን ቀድመው ከሚከፍሉት 7 ሃገራት ተርታም ናት፡፡
በሌላ በኩል ፖሊሲው በግዛት አንድነት ዲስኩር፣ በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ፣ በጋራ እሴት ግንባታ፣ በሉኣላዊነትና ክልላዊ ውህደት/ፌደሬሽን፣ በወደብና የባህር በር ጉዳዮች፣ በዙሪያ መለስ አተያይ፣ ወዘተ እና በመሰል ጉዳዮች ላይ ውስንነቶች ያሉበት ነው፡፡ በ20 አመታት ውስጥ የተከሰቱ ወሳኝ ውጫዊና ውስጣዊ ኑባሬዎችን ያልተካተቱበት መሆኑ በክፍተትነት የሚወሰድ ነው፡፡ ከአፈጻጸም አንጻር ሲለካ የፖሊሲ ሰነዱ የሙያዊ ዲፕሎማሲን አስፈላጊነት የሚገልጽ ቢሆንም አተገባበሩ ውስንነቶች ያሉበት ነው፡፡ በአቅም ማነስ የተገለሉ ባለስልጣናትና አማጺያን ሳይቀሩ ዲፕሎማት የሆኑባት ሀገር ስለመሆኗ ብዙ ጥናታዊ ትችለቶች ቀርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ትችቶች ከአለም አቀፍ እና ከክልላዊ ሁኔታዎች አንጻር፡ የክለሳ አስፈላጊነት
በ1990ቹ አጋማሽ ጀምሮ በስራ ላይ ያለው ወይም በይፋ ያልተቀየረው የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳዮችና የደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ሳይለወጡ ወይም ባሉበት ቢተገበሩ ጥቅም ያላቸው አቅጣጫዎች/ መርሆች ያሉት ቢሆንም እንዲከለስ የሚያስገድዱ ነባርና ዘመን ወለድ ክፍተቶች ያሉበት ነው፡፡ እነዚህ ክፍተቶቹንና የክለሳ አስፈላጊነት ማጠንጠኛዎች አለም አቀፋዊ ሁኔታዎች፣ ክልላዊና ሀገራዊ የውጭ ፖሊሲ ምሰሶች ናቸው፡፡ በዚህ ጽሁፍ አለም አቀፋዊ እና ክልላዊ ሁኔታዎች ላይ ብቻ የተወሰኑ ሃሳቦች ብቻ ለውይይት ቀርበዋል፡፡
- አለም አቀፍ ሁኔታዎች
ከአለም አቀፍ ሁኔታ አንጻር የሚቀርበው ሃሳብ የአለም አቀፍ የኃይል ሚዛን መለዋወጥና የአዳዲስ መርሆች መምጣት፣ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ሲቀረጽ የግሎባላይዜሽን ጥቅምና ወሳኝነትን የተጋነነ ግምት መሰጠቱ፣ በፖሊሲው የተወሰኑ የአለም ክፍሎች የተዘነጉ መሆኑ እና ፖሊሲያችን የአውሮፓ ህብረት የቅርብ ጊዜ ለውጦችን የማያውቃቸው መሆኑ ላይ የሚያጠነጥን ነው፡፡
I). የአለም አቀፍ የሃይል ሚዛን መለዋወጥና የአዳዲስ መርሆች መምጣት፡ ከ1994 ዓ.ም. ወዲህ በአለም አቀፍ ደረጃ የስደተኛ ፖሊሲዎች ለውጥ (አውሮፓ ድንበር መዝጋትና የአሜሪካ ግንብ)፣ የአዳዲስ አለም አቀፍ ህጎች መጽደቅ (የአለም አቀፍ ወንጀለኞች ሰነድ ተግባራዊ መሆን፣ ወዘተ)፣ የአለም ፓርላማዎች ፎረም መርሆችና ትብብሮች መስፋት ተስተውሏል፡፡ በ1990ዎቹ የአሜሪካ ገናና ሆኖ መውጣትና የራሺ ሃያልነት መቀዛቀዝ የተስተዋለበት ሆኖ የአለም የኃይል ሚዛን በሁለቱ ጎራ (በምዕራብና ምስራቅ ጎራ ወይም በአሜሪካ እና በራሺያ ወገን በተሰለፉ የአለም ክፍሎች) የሚጠበቅ ነበር፡፡ የአለም አቀፍ የኃይል ሚዛንን የሚያስጠብቁ ሃያላን በብዛት መፈጠራቸውም (ቻይና፣ ህንድ፣ ራሺያ፣ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት…) ሌላው ጉልህ ጉዳይ ነው፡፡
በተጨማሪም የአፍሪካ ህብረት ጣልቃ ያለመግባት (non-interference) የሚለውን መርሁን ችላ ያለማለት (non-indifference) በሚል መቀየሩ፣ የአጀንዳ-2063 (አህጉር አቀፍ ጥቅል የእድገትና የትብብር ማጭቀፍ) መጽደቁ፣ የሰብአዊ ደህንነት ጉዳይ የተባበሩት መንግስታት አጀንዳ መሆኑ ወዘተን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያም ብትሆን በህገ-መንግስቱ አንቀጽ 86 ካስቀመጠቸው ጣልቃ ያለመግባ (non-interference) መርህ በተቃራኒ በሶማሊያ ከ5 አመት በላይ የረዘመ ዘመቻ አድርጋለች፡፡ ኤርትራም ሰሞኑን ወደኢትዮጵያ ጎራ ብላ ራሷን ከትህነግ ሮኬት ለመከላከል ያደረገችው ሙከራ ከጣል ገብነት መርህ ጋር አብሮ የሚታይ ክስተት ነው፡፡
II). የፖሊሲው የግሎባላይዜሽንን መስተጋብር በተጋነነ አግባብ መመልከቱ፡ የዛሬ 20 አመት አለማቀፋዊነት (globalization) በቁልፍ አጀንዳነት ጣሪያ የነካበት እንዲሁም የሊበራል ፍልስፍናን ገዢ ሃሳብ ሆኖ የወጣበት ወቅት ነበር፡፡ ለአብነት (The end of History and the last Man (1992)) በአሳማኝ አመክዮና በውብ ቋንቋ የተሰደረ መጽሀፍ በፖሊሲ አውጭዎች ላይ ተጽዕኖ አሳድሮ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲ ግሎባላይዜሽንና ከግሎባላይዜን ጋር ተዛዝሎ የሚመጣ አለም አቀፍ የሊብራል ግንኙነት ላይ ከተገቢው በላይ በመተማመን የተቀረጸ አይነት ነው፡፡ ከልማትና ዲሞክራሲ፣ ከብሄራዊ ክብርና ኩራት ጋር ከሦስቱ የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲ አንዱ ተደርጎ ነው የተገለጸው፡፡ ሀገራዊ አንድነት፣ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ፣ ሰብዓዊ ልማት ወዘተ የግሎባላይዜሽንን ያህል ክብደት አልተሰጠውም፡፡ ዛሬ ላይ አለም አፋዊነት ከመፋፋም ይልቅ የመቀልበስ አዝማሚ እያሳየ ነው፡፡ የአሜሪካ ከሜክሲኮ ድንበር በኩል የአትምጡብኝ ግንብ የመገንባት ውሳኔን፣ የእንግሊዚ ከአውሮፓ ህብረት መውጣትን፣ የአውሮፓ ሃገራት ከአረብና ከአፍሪካ ሃገራት የሰዎች ፍሰትን ለመቀነስ ያለመ የስደተኞች ፖሊሲ ማውጣትንና መተግበርን ለምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
በመሆኑም ግሎባላይዜሽን የውጭ ጉዳይ መሰረት አድርጎ ከመጠቀስ ይልቅ አለም አቀፍ ሁኔታዎች ከግምት ያስገባ ብሄራዊ ጥቅም የማስጠበቅ የውጭ ጉዳይ ሂደት አንደሚኖር ማመላከት ብቻ በቂ ነው፡፡ ፖሊሲ ላይ ሁሉ ነገር በዝርዝር አይቀመጥም የሚለው እሳቤም መረሳት አይኖርበትም፡፡
III). በፖሊሲው የተወሰኑ የአለም ክፍሎችን መዘንጋቱ/አንዱን ጠቅሶ ሌላውን መዘንጋቱ፡ በፖሊሲው ላይ ወሳኝ የሆኑ የኤዢያ፣ የላቲን አሜሪካ፣ ወዘተ ሀገራት አልተጠቀሱም፡፡ በአለም አቀፍ መድረኮች ከኢትዮጵያ ጥቅም አንጻር ውሳኔ የሚያሳልፉበት አጀንዳ ስላለ ፖሊሲው በጥቅል ወይም በተናጠል ሊገልጻቸው ሲገባ ተስተዋል፡፡ ለምሳሌ ከኤዤያ ቻይና፣ ጃፓን፣ ህንድ ብቻ ናቸው በሰነዱ የተገለጹት፡፡ እንደ ደቡብ ኮሪያ ያሉ ብርቱ የኢትዮጵያ አጋሮች ኢዥያ በሚለው ርዕስ ስር እንኳን ሊጠቀሱ ሲገባ ተትተዋል፡፡ የሚፈጥረውን ጥሩ ገጽ ከግምት በማስገባት በሚገኙበት የኢዢያ ክልል እንኳን ጠቅሶ (የአረቢያን ፔንሱላ… በተገለጸበት አግባብ መካከለያው፣ ሰሜን ምስራቅ ኤዢያ በሚል) የግንኙነት አቅጣጫ ማስቀመጥ ሲገባ አልተደረገም፡፡ እዚህ ላይ እያንዳንዱ ሃገር በፖሊሲ ሰነዱ ይዘርዘር የሚል ሃሳብ እያንጸባረቅሁ አይደለም፡፡ የኔ ትኩረት ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም አንጻር የተጽኖ ድርሻ ያላቸውን የአለም ሀገራት ሳይዘነጉ በጥቅል እንኳን ዲፕሎማሲያዊ በሆነ ገለጻ ሊካተቱ ይገባል የሚል ነው፡፡
IV). በአውሮፓ ህብረት ዙሪያ ያሉ አዳዲስ መስተጋብሮች፡ የአውሮፓ ህብረትን እንደ አንድ አሃድ (unit) አድረጎ የሚቆጥረውና የግንኙነት አቅጣጫ ያስቀመጠው የወቅቱ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የእንግሊዝን ከህብረቱ ውጭ የመሆን ጉዳይና አውሮፓዊያን ሃገራት በአለም አቀፋዊነት መርህ በተቃራኒ የፋይናንስና የሰው ሃይል ፍሰት ሂደትን የሚገቱ ፖሊሲዎች በተናጠል እያወጡ መሆኑን ከግምት ያስገባ አይደለም፡፡ በተግባርና በመርህ አንደ አንድ አሃድ ላለመሆናቸው ስደተኞችን በተመለከተ የተለያየ ውሳኔ ማሳለፋቸው፣ አለም አቀፍ ድጋፍን በተናጠል የሚያደርጉ መሆናቸው፣ የመገበያ ገንዘብን በተመለከተ ወደ-የሀገራቱ ገንዘብ ማዘንበላቸው ወዘተማሳያዎች ናቸው፡፡ እንደእግሊዝ ከህብረቱ መነጠል አይነት አንዳንድ ጉዳዮች የቅርብ ጊዜ ክስተቶች ስለሆኑ ያለማሻሻያ አካል ሊሆኑ የሚችሉበት አግባብ ጠባብ ነው፡፡
V). አለም አቀፍ የሰላም ማስከበር የስለጠና ተቋምን የሚመለከት አቅጣጫ
የሰላም ማስከበርን አለም አቀፋዊ ስምሪት እና ተቋማዊ አሰራር በተመለከተ ኢትዮጵያ የአለም አቀፍ ሰላም ሲደፈርስ ፈጥኖ ደራሽ መሆኗና የአመርቂ ውጤት ታሪኳ ከመገለጹ ውጭ የሰላም ማስከበር ተቋማዊ እንቅስቃሴን የሚመለከት የፖለሲ አቅጣጫ የለም፡፡ የ1994ቱ ሰነድ ጸድቆ ስራ ላይ ከዋለ ከዘጠኝ አመት በኋላ በ2003 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ስልጠና ማዕከል ተቋም ተገንብቷል፡፡ እዚህ ላይ ፖሊሲው የማያውው አዲስ የተቋም ኑባሬ አለ የሚለው ነው ፍሬ ነገሩ፡፡ ጉዳዩ አለም አቀፋዊነት ስላለውና በመርህ መመራት ስላለበት የዚህን አዲስ ተቋም ስርዓትና ተልኮ በፖሊሲ መካትት ስላለበት ክፍተቱን ለመሙላት የማሻሻያ ሃሳብ የሚጠበቅ ነው ማለት ነው ፡፡
VI). የባህር ሃይል ጉዳይ
የባህር ኃይል የባህር በር ካላት ሀገር ጠረፍ እስከ 12 ናወቲል ማየልስ በሚደርስ የራሷ በሆነ የውሃ ክፍል ላይና በአለም አቀፍ ውሃዎች ላይ እንስቃሴ ሊያደርግ የሚችል ነው፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳዮችና የብሄራዊ ደህንነት ፖሊሲ ስትራቴጂ ካስቀመጣቸው ስድስት (6) ቁልፍ ጉዳዮች አንዱ አስተማማኝ የመከላከያ ሃይል ግንባታ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ የምድር ሃይልና አየር ኃይልን ታሳቢ ያደረገ የፖሊሲ አቅጣጫ ነው የተቀመጠው፡፡ በዚህ ረገድ ፖሊሲው ጎደሎ ነው የሚለውን መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ የባህር ኃይልን ጉዳይ (አስፈላጊነት) የዘነጋ፡፡ ከ2010 ዓም ወዲህ የተጀመረው የባህር ኃይል የማም እርምጃ አዲስ ኑባሬ ስለሆነ የፖሊሲ ማዕቀፉ የማያውቀ ነው፡፡
በሌላ በኩል የሰላምና ደህንነት ፖሊሲው ከውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ተነጥሎ የሚዘጋጅ ከሆነም ባህር ኃይልን የሚመለከት የፖሊሲ አቅጣጫ መካተቱ የግድ ስለሚሆን አሁን ላይ ያለው የፖሊሲ ሰነድ የጎደለውን መሙያ ክለሳ ያስፈልገዋል የሚለው ሊሰመርበት ይገባል፡፡
VII). የሳይበር ደህንነት ጉዳይ
በአንድ ሀገር የውጭ ጉዳዮች ፖሊሲ የብሄራዊ ጥቅም ትንተና የሳይበር ቴክኖሎጂና ጥቃት ተገቢው ትኩረት ካልተሰጠው የፖሊሲ ክፍተት ስለሚኖር የብሄራዊ ጥቅንም አሟልቶ ለማስጠበው ችግር ሊገጥም ይችላል፡፡ የሃገሪቱ የደህንነትና የመረጃ መስሪያ ቤቶች የሳይበር ቴክኖሎጂን ለማዘመን ተቋማትን የማደራጀት ጅማሮ ያሳዩ ቢሆን ከወቅቱ የአለም የቴክኖሎጂ እድገቶች ጋር ለማጣጣም ቀጣይነት ያለው ምርምር እና የማዳቀል ስራ፣ ቁልፍ ጉዳይ ተደርጎ በፖሊሲው የተተነተነ እቅጣጫ ከማስቀመጥ አንጻር ክፍተት አለ፡፡ በተጨማሪም የሳይበር ጥቃቶችንና ዲፕሎማሲዊ አንድምታቸውን ከመዳሰስ አኳያም ውስንነት አለ፡፡
2. ከልላዊ ሁኔታ
በክልላዊ ሁኔታ ፍተሻችን የባህር በርና የወደብ አገልግሎት የአተያይ ውስንነትን፣ የውሃ ፖለቲካ ሁኔታን፣ ክልላዊ ፌደሬሽን፣ ኮንፌደሬሽን…ታሳቢነትን፣ በአፍሪካ ቀንድ የአዲስ ሀገር መፈጠርን፣ በፖሊሲው ላይ ከተገለጸው በተቃራኒ የሆነው የኢትዮ-ኤርትራ የግንኙነትን፣ በሶማሊያ የተከሰቱ ለውጦችን፣ የባህረ ሰላጤውና የቀይ ባህር አካባቢዎች አለም አቀፍ የስበት ማዕከል መሆናቸውን የሚመለከቱ ሃሳቦች ይነሳሉ፡፡
- የባህር በርና የወደብ አገልግሎት ጉዳዮች የአተያይ ውስንነት
የባህር በርና የወደብ አገልግሎት የማግኘት መብትን እና እድሎችን አሟጦ በመጠቀም ረገድ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሰነዱና አፈጻጸሙ ውስንነቶች ያሉበት ሲሆን ይህም በብዙ መልኩ ሊገለጽ ይችላል፡፡ ዋነኛው ግን በአተያያ ቁንጽልነት የሚገለጽ ነው፡፡
የባህር በር አተያያ፡ የባህር በር የንግድ አንቅስቃሴ ከማድረግ ባለፈ የሃይልና የስትራቲጂካዊ ተፈላጊነት መለኪያም ነው፡፡ በባህር በር ረገድ የኢትጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የቋሚ ጠላት ብያኔና አተያይ በመታጠሩ የወደብ አማራጭን አጥብቦ የሚመለከት ነው፡፡ በፖሊሲው ዘላለማዊ አጋርነትና ወዳጅነትን ሳይሆን ሁኔታና ብሄራዊ ጥቅመን ያገናዘበ ጥቅል ገለጻ መቀመጥ ሲገባው የባህር በር አገልግሎት/ የወደብ አቅርቦት አማራጫችን የሆነችውን ኤርትራ ተፈጥሯዊና ዘላቂ ጠላት ተደርጋ መበየኗ እና በአንድ ወገን ላይ ጥገኝነትን በሚያስከትል አግባብ የተቃኘ ነው፡፡
ይህም በአንጻራዊነት በአነስተኛ ወጭ አገልግሎት የሚስገኙ አማራጮች እንዳይታዩ ያደረገ ነው፡፡ ለምሳሌ የኬንያ ወደብ (ሞምባሳ) ከጂቡቲ ወደብ ጋር ሲነጻጸር ለሞያሌ፣ ለምስራቀቅ አርሲና አካባቢው በ317.1 ኪሎ ሜትር ይቀርባል፡፡ የሶማሊ ላንድ (Berbera) ወደብ ከጂቡቲ አንጸር እስጂግጂጋ ድረስ ላሉ አካባቢዎች 163.4 ኪሜ የሚቀርብ ሲሆን ለጎዴና አካባቢዋ ደግሞ 249.6 ኪ.ሜ ቀረቤታ አለው፡፡ በመሆኑም በዲፕሎማሲ ዘላለማዊ ጠላት ባለመኖሩ እነዚህ እንዲሁም የሱዳንና የኤርትራ ወደቦችም ለሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች የውጭ ንግድ እንቅስቃሴ በአማራጭ የሚታዩ መሆናቸውን በውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ማመላከት አይከፋም ነበር፡፡
- የአባይ ውሃ ፖሊቲካ በአፍሪካዊ መድረክ እልባት እንዲያገኝ ያለመተኮሩ
የአባይ ውሃን አጠቃቀም በተመለከተ በግብጽ ኢትዮጵያ መካከል ያልተቋጨ ተግዳሮት መኖሩ ከ1959 አግላይ የሁለትዮሽ ውል እና ከአረብ ሃገራት ጣልቃ ገብነት፣ የግብጽ የውጭ ድጋፍ የማስከልክል ወጥ አቋምና የኢትዮጵያን ሰላም በማናጋት የውሃ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የማምከን እንቅስቃሴ በስፋት የተተነተነ ቢሆንም መፍትሄውን በማመላከት በኩል ውስንነት፡፡ በፖሊሲው ክልላዊ ተቋማትንና ከመጠቀም አንጻር፣ የተፋሰሱን ሃገራት ባለጉዳይ ከማድረግና በርካታ ባለድርሻዎችን ከመጋበዝና የአፍሪካ ህብረትን የጉዳዩ ባለቤት ከማድረግ አንጻር ትኩረት ያንሳል፡፡ በአፈጻጸም ከአፍሪካ ወንድም ሀገራትን ድጋፍ እንዲገኝ በማድረግ በሚል የተገተጸችን ሃሳብ ቦርቀቅ አድርጎ በመተርጎም አህጉራዊ ዲፕሎማሲ የመስራት አማራጭን ችላ የማላት አዝማሚያ ነው ያለው፡፡
በአተገባበርም የ10 አመታት ሂደትን አልፎ እኤኣ በ2010 የተፈረመው (ኡጋንዳ፣ ታንዜኒያ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ኢትዮጵያ) የፈረሙትን የኮኦፐራቲቭ ፍሬም-ዎርክ ስምምነት ጅማሮ ማስቀጠል ወይም ፈራሚ ሀገራት የዲፕሎማሲ ጉልበት ማድረግም አልተቻለም፡፡ እኤአ በ2019 ወደ አሜሪካ ተኪዶ ለዲፕሎማሲዊ ቀውስ የተዳረግነው በአፍሪካዊ መፍትሄ ላይ አበክሮ ዲፕሎማሲ መስራት የሚያስችል ፖሊሲ አቅጣጫ ባለመቀመጡ እንደሆነ አስረጂ ሳይንሳዊ ትንተና ማቅረብ አይገድም፡፡
- ፖሊሲው ክልላዊ ፌደሬሽን፣ ኮንፌደሬሽን…ተሳቢ ያለማድረጉ
ሰላማዊ ክልላዊ ትብብርና ፌደሬሽን ኢትዮጵያዊያን በአፍሪካ ቀንድ ብሎም በአፍሪካ የተሻሉ ተጽዕኖ ፈጣሪና ተጠቃሚ የማድረግ እድል ይኖረዋል፡፡ ወደብ አልባነት ኢትዮጵያ በክልሉ ሃያል የምሆን እድሏን ከሚገቱ ቁልፍ ጉዳዮች አንዱ መሆኑን የተለያዩ አካዳሚዊ ምርምሮች አረጋግጠዋል፡፡ ይህን ክፍተት በመሙላት ኢትዮጵያዊንን ተጠቃሚ የሚደርግ ወይም አንደአጠቃላይ የቀጠናውን ህዝብ የሚያበለጽግ የትብብር ማዕቀቀፍን የሚያሳይ ፖሊሲ አስፈላጊነት ቢኖረውም የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዘንግቶታል፡፡ በመሆኑም በማሻሻያ ክልላዊ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ የውህደት ወይም ፌደሬሽን አቅጣጫዎች እንዲካተቱ ይጠበቃል፡፡
- በአፍሪካ ቀንድ ክልል የአዲስ ሀገር መፈጠር
ሉአላዊት ሀገር ደቡብ ሱዳን አዲስ አክልላዊ ክስተት ናት፡፡ ከአዲሷ ጎረቤት ሀገር ጋር ግንኙነት መፍጠር አይቀሬና ተፈጥሯዊ በመሆኑ በተግባር እየተከናወነ ነው፡፡ ሆኖም በጨበጣና ያለመርህ የሚደረግ ግንኙነት ለተቋማዊ አሰራር ስለማያመች ብሎም አሉታዊ ውጥቶችም ስለሚኖሩት የግንኙነቱን አቅጣጫዎች በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ማዕቀፍ ወስጥ ማካተተት ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሰነድ ደቡብ ሱዳንን ጎረቤት ሃገር በሚለው ገለጻው ያውቃታል ካላልን በስተቀር በህጋዊ ስያሜዋ አያውቃትምና ከስሟ ጀምሩ ያሉ ዲፕሎማሲዊ ረቂቅ ጉዳዮች መካተት ይኖርባቸዋል፡፡
- የኢትዮ-ኤርትራ የግንኙነት በስራ ላይ ካለው ፖሊሲ ያለው ተቃርኖ
ኤርትራ፡ ከ1994 ዓ.ም. ጀምሮ በስራ ላይ የቆየው የውጭ ፖሊሲ ሰነድ ክፍል ሁለት 1.2 ላይ ኤርትራንና ስልጣን ላይ ያለውን መንግስት አይረቤና ለኢትዮጵያ ሰላም፣ ዲሞክራሲና ልማት ጠንቅ አድርጎ ተንትኗቸዋል፡፡ ዛሬ ላይ የባላንጣነት ግንኙነቱ ተቀይሯል፡፡ ጠላት ተደርገው የተፈረጁት ኤርትራም ሆነች ገዢው ፓርቲ አሉ፡፡ በመሆኑም ፖሊሲ ይህን አዲስና የትብብር ግንኙነት የማያውቀው ከመሆኑም በላይ በተግባር ካለው ግንኙነት የሚቃረኑ የግንኙነት ብያቤዎችን፣ ትንተናዎችንና አቅጣጫዎን ያስቀመጠ ነው፡፡
- በሶማሊያ ያለው የጸታና ሀገረ-መንግስት ሁኔታ መለወጥ
በኢትዮጵያ የፖሊሲ አተያይ ሶማሊያ እየፈረሰች ያለች ሀገር በመሆኗ አሉታዊና አወንታዊ ጫናዋ እንዲሁ ወደቦቿን ለኢትዮጵያ አማራጭ የውጭ የንግድ መስመሮች የመሆን እድላቸው የመነመነ ተደርጎ ነው የተወሰደው፡፡ ሌላው ቀርቶ ፖሊሲው በወጣ በአምስተኛው አመት ላይ የሶማሊያ አሸባሪ ቡድኖች የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም ስጋቶች ናቸው ከሚለው የመንግስት አቋም የሚቃረን አውድ ያለው ነው፡፡
በወቅቱ የነበረው የሁኔታ ግምገማ በሶማሊያ ያለውን መልካም አድል ለመጠቀም ተግዳሮት መኖሩን የሚያሳይ ከሆነ እንኳ የሶማሊያ አወንታዊ አስተዋጽዖ እምበዛም ነው ከሚባል ይልቅ ወደፊት የኢንቨስትመንትና የገበያ አማራጫችን መሆን ትችላለች የሚል አመላካች አቅጣጫ መኖር ነበረበት፡፡ በመሆኑም አሁን ላይ ሁኔታዎች ሲለወጡ ሶማሊያን የሚገልጽ የፖሊሲ አቅጣጫ ክፍተት ገጥሟል ማለት ነው፡፡ በፖሊሲው በአወንታዊም ሆነ አሉታዊ ተጽኖዋ አናሳ ነው የተባለቸው ሶማሊያ በ1998 ዓ.ም. አደገኛ እና የኢትዮጵያ የሳለም ጠንቅ ተብላ በእስውላማዊ ፍርድ-ቤቶች ህብረት፣ በአልሻባብና በአል-ኢትሃድ ቅሪቶች ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ተደርጓል፡፡ ከዚህ አንጻር ፖሊሲው እኳን የዛሬውን የሶማሊያን ሁኔታ ቀርቶ የትላንቱን ከሶማሊ በኩል የሚኖር ስጋትና መልካም እድል በአግባቡ የሚገልጽ አይደለም ወደሚለው ድምዳሜ ይመራናል፡፡
- የባህረ ሰላጤው፣ የቀይ ባህር አካባቢዎች የስበት ማዕከል መሆናቸው
በርካታ የአላም ሃያል ሀገራትና አንዳንድ የአረብ ሃገራት በተጠቀሰው ክልል የወታደራዊ ማዘዣዎችና የኢኮኖሚ መሰረተ ልማቶች የመገንባት እቅስቃሴዎቸው ከዛሬ 20 አመቱ በእጂጉ የተለየና የተዋናይ መጠኑም የበዛ ሆኗል፡፡ ከዚህ ክስትት አንጻር በስራ ላይ ያለው ፖሊሲ የእይታ ወስንነቶች ያሉበት ስለሆነ በአካባቢው እየተስፋፋ ያለውን አለም አቀፍ መስተጋብር ወደ እድል ቀይሮ ተጠቃሚ መሆን የሚቻልበት የፖሊሲ አቅጣጫ ያስፈልጋል፡፡ የዚህን አካባቢ ሁኔታን በተመለከተ ከውጭ ወደውስጥ በማየትና መስተጋብሩን ወደ-እድል በመቀየር ላይ ያተኮረ የፖሊሲ አቅጣጫ ክፍተትን በአግባቡ በመረዳት ክለሳ ያስፈልጋል፡፡
ማጠቃለያ
ፖሊሲው ከላይ የተጠቀሱትን አለም አቀፍና ክልላዊ ለውጦችንና የተዘነጉ ጉዳዮችን አካቶ ተቋማዊ የአሰራር ስርዓት ለማስፈን ያስችል ዘንድ ማሻሻያ/ክለሳ ያስፈልገዋል፡፡ ከአዳዲስ የአለም አቀፍ ህግጋትና መርሆች፣ ከአሰላለፍና ከአጋርነት ለውጦች አንጻር የሚቃኝ ይሆናል፡፡ ዲሞክራሲና ልማት፣ ኢኮኖሚ ተኮር ዲፕሎማሲ የመሳሰሉ ጎዳዮች በነበሩበት ሊቀጥሉ የሚችሉና ወቅቱን የሚመጥኑ ናቸው፡፡ ፖሊሲው ከብሄራዊ ክብርና ኩራት አኳያ ያስቀመጣቸው ትንታናዊ እይታዎች ደግም በውስን ክለሳ ተጠግነው የሚቀጥሉ ናቸው፡፡ ከውስጥ ወደውጭ የሆነው የወቅቱ የፖሊሰ አተያይ በሁለተኛው (ከውጭ ወደውጥ የማየት ስልትን አካቶ) የአተያይ አይነት ሚዛኑ ከተጠበቀለት መቀጠል የሚችል ነው፡፡ በክልላዊ ሁኔታ አንጻር በባህር በርና በወደብ አገልግሎት የአተያይ፣ ክልላዊ ፌደሬሽን፣ ኮንፌደሬሽን…ተሳቢ በማድረግ ረገድ፣ በአፍሪካ ቀንድ የአዲስ ሀገርና ክሰተቶች መፈጠርን የሚመለከት፣ የኢትዮ-ኤርትራ የግንኙነት ለውጥን ያገነዘበ፣ የባህረ ሰላጤውና የቀይ ባህር አካባቢዎች አለም አቀፍ የትኩረት መሆናቸውን በሚመለከት ሊመጡ የሚገቡ አቅጣጫዎች ዙሪያ የክለሳ አስፈላጊነትን ይስተዋላል፡፡ በመጨረሻም የማሻሻያ እንቅስቃሴዎችም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስተርና ከስትራቴጂክ የፖሊሲ ጥናት ተቋም በተጨማሪ ልምድ ያላቸውን የፓርላማ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ አመራሮችን፣ የዲፕሎማሲና የፖሊሲ ጥናት ሙያተኞችን፣ የወታደራዊ መንግስት ዘመን የተመረጡ ዲፕሎማቶችን ያሳተፈ ቢሆን ይመረጣል፡፡
__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com