spot_img
Thursday, July 25, 2024
Homeነፃ አስተያየትየሚሰማ ካለ (አንዳርጋቸው ጽጌ)

የሚሰማ ካለ (አንዳርጋቸው ጽጌ)

በ16 July 2021 ፎሪንፖሊሲ (foreignpolicy) የተሰኘው ታዋቂው የአሜሪካ መጽሄት በድረ ገጹ (foreignpolicy.com) ላይ አፍጋኒስታን እንዴት በአሜሪካ እንደተከዳች ያሰፈረው ጽሁፍ https://foreignpolicy.com/…/pakistan-united-states…/ ለኢትዮጵያ ጠቃሚ ትምህርት ይዟል። ጽሁፉ ብዙ ነገሮችን የነካካ ስለሆነ የማተኩረው በቀጥታ በሚያስገርም መልኩ ከኢትዮጵያን ሁኔታ ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ነጥቦች በሰፈሩበት የጹሁፉ ክፍል ላይ ብቻ ነው ። ይህንን ጹሁፍና በትናንትናው እለት (19/08/2021) የተባበበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊ የሆነው አንቶኒዮ ጉተሬዝ ኢትዮጵያን አስመልክቶ ከተናገረው https://youtu.be/RaiKk1dB-Po ጋር አቀናጅተን ካየነው ኢትዮጵያ በጥንቃቄ ካልተራመደች ችግር ላይ የምትወድቅ መሆኑን ይጠቁማሉ።

በቅድሚያ (foreignpolicy) ካወጣው ጽሁፍ እጀምራለሁ። እንግሊዝኛውን ለማንበብ ለፈለገ የመጨረሻዎቹን 4 አንቀጾች ማንበብ ይችላል።“

ዋሽንግተን፤ የአፍጋን መንግስት ከታሊባን ጋር የሰላም ድርድር እንዲያደርግ እጁን ጠመዘዘች። የአፍጋን መንግስት ግን ታሊባኖችና ዋናዎቹ ደጋፊዎቻቸው የሆኑት ፓኪስታኖች፣ ቃላቸውን የማይጠብቁና የማያከብሩ እንደሆኑ ከማንም በላይ እውቀቱ ነበረው።

የሰላም ድርድሩ ለዋሽንግተን አስፈላጊ ነበር። በድርድሩ ተስፋ የተደረገው፣ በድርድር የመጣ የስልጣን ሽግግር በሚል ልብወለድ የአሜሪካንን ሽንፈት ለመሸፈን ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ ለድርድር የሚቀርብ ምንም ነገር አልነበረም። የአፍጋን መንግስት ህገመንግስታዊ ለሆነ ህጋዊ አስተዳደር፣ ምርጫን ጨምሮ፣ የቆረጠ ሲሆን፣ ታሊባን ደግሞ ህገ መንግስቱን መናድ ብሎም ምርጫ እስላማዊ አይደለም የሚል አቋም የያዘ ነው። ታሊባኖች ሰላማዊ ድርድር የተባለውን የቀልድ ሂደት፣ ለድርጅታቸው ማገገሚያ፣ ሰራዊታቸውን በሚፈልጉት ቦታ ለማሰማሪያና መሳሪያቸውን በየቦታው ለመሸሸጊያ እየተጠቀሙ የአሜሪካን መውጣት ተጠባበቁ።

በ2020 የተሞከረው የሰላም ድርድር የትም የማያደርስ ሲሆን አሜሪካ የአፍጋን መንግስት ወደ ሰላማዊ ድርድር ካልተመለሰ 2 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር እርዳታዋን እንደምታቆም አስፈራራች። ከዛም አልፋ የአፍጋን መንግስት 5000 አክራሪ የታሊባን እስረኞችን እንዲፈታ አስገደደች። በምትኩ በመቶዎች የሚቆጠሩ በታሊባኖች እጅ የነበሩ የአፍጋን መንግስት ሰራተኞች እንዲለቀቁ አስደረገች። የተፈቱት ታሊባኖች ዛሬ በታሊባን አማካኝነት የሚካሂደውን ጥቃት የሚመሩ ሆነዋል። ጋሃኒ (የአፍጋኒስታን ፕሬዚደንት) የ2019 ፕሬዚደንታዊ ምርጫ እንዲያስተላልፍ አሜሪካ ጫና ፈጠረች። አሜሪካ ይህን ጫና ለማድረግ የመረጠችበት ምክንያት፣ መንግስት ፈርሶ፣ ታሊባንን ባካተተ የሽግግር መንግስት መተካቱን ታሊባን ለሰላማዊ ድርድር በቅደመ ሁኔታነት በማስቀመጡ ነበር። ጋሃኒ ይህን የአሜሪካ ሃሳብ ፈጽሞ አልተቀበለውም።

በ1990 አሜሪካ አፍጋኒስታንን ለፓኪስታን ጥላ እንደወጣች ዛሬም ጥላ እየወጣች ነው። የትናንቱን ስህተት ዛሬም እየደገመች ነው። …………… ታሊባንም እንደገና አፍጋኒስታንን የዘመናችን የአለም ሸብርተኞች መናኸሪያ ሲያደርጋት ዋሽንግተን ከራሷ ውጭ ሌላ ማንም መወንጀል አትችልም።”ይህ ከዚህ በላይ በግርድፉ የተተረጎመ ጽሁፍ አፍጋኒስታን እና ታሊባን የሚለውን ቃል እያወጣን ኢትዮጵያና ወያኔ የሚሉትን ቃላት እየተካን ብንመለከተው ተመሳሳይነቱ የሚገርም ነው። አሜሪካ አፍጋኒስታን ውስጥ መንግስትን ከታሊባን ጋር እንዲደራደር፣ ምርጫ እንዳይደረግ፣ ማስፈራራት እና ማእቀብ ስታደርግ የቆየችው ሽንፈት ተከናንባ፣ ተዋርዳ እንዳትወጣ ወይም 20 አመት ሙሉ በርካታ ወታደሮቿን፣ ገንዘቧን ሰውታ መቋጫ ያጣውን የአፍጋን ችግር ጫንቃዋ መሸከም ከማይችልበት ደረጃ ደርሶ እንጂ ለአፍጋኒሳትን ህዝብ አስባ እንዳልሆነ ግልጽ ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥም አሜሪካ፤ “የኢትዮጵያ መንግስት ለሰላም ይደራደር፣ ወያኔና ሌሎች ህገመንግስታዊ ስርአቱን በአመጽ ለመናድ እንደወያኔ የተሰለፉ ጽንፈኞችን ያካተተ ጊዜያዊ መንግስት ይቋቋም፣ ምርጫ እንዳታደርጉ፣ የምንለውን ካልሰማችሁ የኢኮኖሚና ሌሎች ማእቀብ እጥልባችኋለሁ” ስትል ከርማለች። የጣለችውም ማእቀብ አለ። በኢትዮጵያም ጉዳይ አሜሪካ ይህን ያህል የወያኔ ጠበቃ የሆነችው ከራሷ ጥቅም አኳያ ያሰላችው ነገር ስላለ ነው። ዝርዝሩ ውስጥ አልገባም። ሆኖም አፍጋኒስታን ላይ የሆነውን ስናይ አሜሪካ የኢትዮጵያንስ ጉዳይ በደንብ አስልታዋለች ወይ የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። አዎን ከአፍጋኒስታን ወጥታለች የፈለገችውም ይህንኑ ነው። አፍጋኒስታንን ግን ለማን ነው ጥላ የወጣችው?

የአፍጋኒስታን ህዝብ ታሊባንን እንደሚያውቀው ሁሉ ኢትዮጵያውያንም ወያኔን በደንብ ያውቁታል። ወያኔ ለሰላም ለእርቅ፣ የህግ የበላይነት ለሰፈነበት ህገመንግስታዊ ስርአት ተገዥ የማይሆን አሸባሪና ዘራፊ ቡድን ነው። የኢትዮጵያ መንግስት በአሜሪካ መንግስት ማስፈራሪያ ወይም ተጽእኖ የአፍጋን መንግስት የሰራውን ስራ በትንሹም ቢሆን ሰርቶ ውጤቱን አይተነዋል።

አሜሪካ “የኤርትራ መንግስት ወታደሮች ይውጡ” አለች። ይህን የማለት መብት የሌላትም ቢሆን እንዲወጡ ተደረገ። “የሰብአዊ እርዳታ ለትግራይ ህዝብ እንዲደርስ ሰላማዊ ሁኔታ በትግራይ መኖር አለበት” አለች፤ የኢትዮጵያ መንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ አደረገ። እንዲያውም በትግራይ ውስጥ የሚከፋፈለው የእርዳታ እህል በወያኔ በጎ ፈቃድ እንዲሆን ትግራይን ለቆ ወጣ። ወጤቱ ግን ሰላም አላመጣም፤ ረሃብን፣ ሞትን፣ መፈናቀልን አላስቆመም። ወያኔ ፋታ ባገኘ ቁጥር ለበለጠ ግጭት ራሱን ማስታጠቅ፣ ማደራጀት ነው የቀጠለው። የአሜሪካኖችን ጫና ፈርተን ለወያኔ መንገድ በለቀቅን ቁጥር አፍጋኒስታን ውስጥ እንደሆነው፣ ኢትዮጵያ በአክራሪ፣ ዘረኛ ሽብረተኞች እጅ የምትወድቅበትን፣ እነዚህ ሃይሎች እንደዛቱት ምድራዊ ሲኦል የምትሆንበትን ሁኔታ ከመፍጠር ውጭ የምንፈይደው ነገር እንደማይኖር ገሃድ ሆኗል።

ከዚህ ጋር አያይዞ የትናንቱን የተባበሩት መንግስታት ጸሃፊ ንግግር ማንሳት አስፈላጊ ነው። የተባበሩት መንግስታት የሚባል ነገር በዋንኛነት የአሜሪካ ፍላጎት ማስፈጸሚያ መሆኑን ማወቅ ይኖርብናል። የጸጥታው ምክር ቤት አባላት አሜሪካ እንዳሻት እንዳትፈነጭ የሚያደርግ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ቢኖራቸውም የተባበሩት መንግስታት መስሪያ ቤትና በየጊዜው የመጡ ጸሃፊዎች የአሜሪካ ጉዳይ አስፈጻሚዎች መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም። ያለ አሜሪካ ቡራኬም የተባበሩት መንግስታት ጸሃፊዎች እንደማይሾሙ መታወቅ አለበት። አሜሪካ የተባበሩት መንግስታትን ውሳኔ እየጣሰች ብዙ አለም አቀፍ ወንጀሎችን ስትፈጽም አንድም ቀን የተባበሩት መንግስታት ጸሃፊዎች በአደባባይ ወጥተው አውግዘዋት አያውቁም። ከጸጥታው ምክር ቤት ሙሉ ውሳኔ ውጭ አፍጋኒስታንን እና ኢራቅን ስትወር የተባበሩት መንግስታት ጸሃፊዎች እንደ ኮፊ አናን አይነቶቹ ለህገ ወጥ ድርጊቷ ተባባሪ እንጂ ተቃዋሚ አልነበሩም። ዛሬም ከዚህ የተለየ ነገር የለም። የትናንቱ የአንቶኒዮ ጉተሬዝ ንግግርም ከአሜሪካ መንግስት ባለስልጣናት ንግግር የተለየ ያልሆነው ለዚህ ነው። የተናጠል የተኩስ ማቆም እርምጃ የወሰደውን የኢትዮጵያ መንግስት ተኩስ ካላቆመው ሽብርተኛ አካል በኩል አስቀምጦ ተኩስ አቁሙ ብሏል። መንግስት በአሸባሪነት ከፈረጀው ወያኔ ጋር ተደራደሩ ብሏል። ጭራሹንም መንግስት በአሸባሪነት የፈረጀውን፣ የሃገር መከላከያ ሃይልንና ሰራዊት እንዲወድም መመሪያ ከሰጠው፣ በማይካድራ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲፈጸም፣ የአማራና የአፋር ህዝብ እንዲገደል፣ እንዲዘረፍ፣ እንዲፈናቀል፤ ማለቂያ የሌለውን መከራ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እንዲዘንብ አመራር ከሚሰጠው ከደብረ ጽዩን ጋር የተባበሩት መንግስታት ጸሃፊ ረዳቶች በስልክ እንደተነጋገሩ አንቶኒዮ ጉትሬዝ ያለምንም መሸፋፈን ነግሮናል።

የተባበሩት መንግስታት ጸሃፊ አንድ ሃገር በህጋዊ መንገድ በአሸባሪነት ከፈረጀችው ግለሰብ ጋር የመነጋገር መብት አለው ወይ? ለመሆኑ ይህ ሽብርተኛ በአሜሪካ ወይም በሌሎች ትልልቅ ሃገሮች የተፈረጀ ቢሆን ኖሮ ጸሃፊው ይህን ያደርግ ነበር ወይ? የኢትዮጵያ መንግስት ለዚህ የንቀት ድርጊቱ ምን ምላሽ ይሰጠው ይሆን? አንቶኒዮ ጉተሬዝ የአሜሪካ መንግስት ቡራኬ ሳይኖረው በንግግር ሆነ በድርጊት ይህን ያደርግ ነበር ወይ? ለእንዲህ አይነቱ አደገኛ የሆነ የአሜሪካና የተባበሩት መንግስታት መስሪያ ቤት ሴራና ጫና የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ምላሹ ምን መሆን አለበት?

ምላሻችንን አፍጋኒስታን ውስጥ በአሜሪካ መሪነት በህዝቡ ላይ እየደረሰ ካለው ጉዳት ልናገኘው ይገባል። ምላሻችንን ባለፉት ሰላሳ አመታት የወያኔን እኩይ ባህሪያት ከተረዳንበት የራሳችን ተመክሮ የሚመነጭ መሆን አለበት። ወያኔን በማስታመም፣ የሚመጣ ሰላም፣ መረጋጋት፣ ለልማት የሚገኝ ፋታ እንደሌለ አውቆ ትግሉ የፈለገውን መስዋእትነት የሚያስከፍልም ቢሆን የሚከፈለውን ከፍሎ ወያኔን ከመቅበር ውጭ አማራጭ የለውም። የወጭ መንግስታት ችግራችሁ ዞሮዞሮ የፖለቲካ መፍትሄ የሚጠይቅ ነው በሚሉት እንስማማለን። ይህ መፍትሄ ግን ወንጀለኛውን አሸባሪና ዘራፊ ወያኔን ያካተተ ከቶውን እንደማይሆን የሃገራችን መሪዎች ለሚመለከተው ሁሉ በማያሻማ ቃላት መንገር ይገባቸዋል። ህዝብም ቢሆን በተለያዩ ምክንያቶች በምንም መመዘኛ ለሃገርና ለህዝብ ጠቀሜታ ለማያመጣ ከወያኔ ጋር ለሚደረግ ድርድር በራሳቸው ተነሳሽነትም ይሁን በውጭ ጣልቃ ገብነት እራሳቸውን የሚያዘጋጁ ሃገራዊ ሃይሎችን ነቅቶ መጠበቅ ይኖርበታል። ከወያኔ ጋር የሚደረግ ማንኛውም ድርድር በኢትዮጵያ ህዝብና በሃገሪቱ ከፍተኛ ኪሳራ የሚጠናቀቅ መሆኑን እስካሁን ያልተረዳ ካለ፣ በጨዋ ቋንቋ “ሆን ብሎ ያንቀላፋ” ብቻ ነው።

አንዳርጋቸው ጽጌ
_
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com    

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here