ከኤፍሬም ማዴቦ
ነሃሴ 20 2013 ዓ ም
ኢትዮጵያ ባለፉት አንድ መቶ ሃምሳ አመታት ውስጥ ባህር ተሻግረው ከመጡ የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች፣ከተላላኪዎቻቸውና ከጎረቤት ተስፋፊዎች ጋር እልህ አስጨራሽ ጦርነቶች ተዋግታለች። በእነዚህ ፈታኝና አስቸጋሪ የጦርነት ዘመኖች የነበረው እያንዳንዱ ትውልድ አገራዊ ግዴታውን በጀግንነትና በታማኝነት በመወጣቱ የዛሬው ትውልድ “ቅኝ ገዢዎችን ያንበረከከች ብቸኛ የጥቁሮች አገር” የሚልና የሚያኮራ ስያሜ ያላት አገር ባለቤት ሊሆን ችሏል።
ኢትዮጵያዊያን ነጮችም ጥቁሮችም የሚመሰክሩት አኩሪ የአይነኬነት፣ የአይበገሬነትና የነጻነት ወዳድነት ታሪክ የኖረን ፈጣሪ ከሌላው ጥቁር ህዝብ የተለየን አድርጎ ስለፈጠረን ወይም እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ከሌሎች አገሮች ለይቶ ስለሚያያት አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝብ ብሔር፣ቋንቋና ሃይማኖት ሳይለያየው በአገሩና በነጻቱ ላይ የተቃጣበትን አደጋ መክቶና ጠላቶቹን አሳፍሮ መመለስ የቻለው፣ በረጂም ግዜ የአብሮ መኖር ታሪክ የዳበረና ከሌሎች አገሮች የተለየ ባህል፣ስነልቦናዊ ዘይቤ፣ እሴትና ማህበራዊ ወረት ስለነበረው ነው።
አገራችን ኢትዮጵያ ዛሬም ከፍተኛ የህልውና አደጋ ፊት ለፊቷ ላይ ተጋርጧል። ይህ አደጋ የአገር ውስጥ፣ የጎረቤትና የባህር ማዶ አጋሮቻቸው በአንድነት ይዘውብን የመጡት አደጋ ነው። ታዲያ ያ ለዘመናት ያስተባበረን ባህል፣ እሴትና ማህበራዊ ወረት የት ሄዶ ነው ዛሬ ጠላቶቻችን ሊያጠፉን ሲተባበሩ እኛ ላለመጥፋት መተባበር አቅቶን ጭራሽ አንዳንዶቻችን ከጠላት ጋር አብረን የቆምነው? ኢትዮጵያ በየዘመኑ ከጠላት ጋር ተሰልፈው የወጓት ባንዶች ነበሯት። እንዳሁኑ ዘመን በቡድን ተፈላልገውና ተጠራርተው “ኢትዮጵያ መፍረስ አለባት” የሚል መዝሙር እየዘመሩ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር እጅና ጓንት የሆኑ ባንዳዎች ግን ኖረውን አያውቁም።
አገራችን ኢትዮጵያ በአለም ውስጥ ሃያ አመት በማይሞላ ግዜ ውስጥ ሁለት ስር ነቀል አብዮት ያካሄደች ብቸኛ አገር ናት። በ1966 ዓ.ም. ወታደራዊው ደርግ ሶሻሊዝምን እገነባለሁ በሚል የኢትዮጵያ ህዝብ የተሳሰረባቸውን የባህል፣ የሞራልና ማኅበራዊ እሴቶች አጠፋ። በ1983 ዓ.ም. የተካሄደው ሁለተኛው አብዮት ደግሞ ከመጀመሪያው አብዮት የተረፉ እሴቶች ተሟጠው እንዲጠፉ ከማድረጉ ባሻገር የኢትዮጵያን ሕዝብ ከታሪኩና “ኢትዮጵያዊ” ከሚባል ማንነቱ ጋር እንዲጣላ አደረገ። ለዚህ ነው በእነዚህ ሁለት አብዮቶች ውስጥ ተወልዶ ያደገውና ህወሓቶች በብሔር ፖለቲካ ጠምቀው ያሳደጉት የዛሬው ትውልድ በኢትዮጵያዊነቱ ሳይሆን በብሄር ማንነቱ ላይ፣ በአንድነቱ ላይ ሳይሆን በጥቃቅን ልዩነቶቹ ላይ የሚያተኩረው። ዛሬ በታሪካችን ለመጀመሪያ ግዜ ጎራ ለይተን እና በቡድን ተቧድነን ኢትዮጵያ “ትፈርሳለች” . . . . . “አትፈርስም” መባባል የጀመርነው ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ኢትዮጵያ ተነካች ሲባል የሚያስተባብሩን እና አንድ ላይ እንድንቆም የሚያደርጉን እሴቶችና ወረቶች በመላላታቸው አንዳንዶቹም በመጥፋታቸው ነው።
ኢትዮጵያ ዛሬ የምትገኝበት ሁኔታ እጅግ በጣም አሳሳቢ ሁኔታ ነው። ይህንን እንደ አገር በሁላችንም ላይ የተቃጣ አደጋ አንድ ላይ ሆነን መክተን እኛነታችንን ማስከበር ካልቻልን አማራጩ አገር አልባ መሆን ሊሆን ይችላል። ግን እንዴት ነው ይህንን በአንድነታችን ላይ የመጣ አደጋ መከላከል ያለብን? ምንድናቸው ያሉን አማራጮች? በጋራ መመከት ማለት ከዉስጥም ከውጭም ተጠራርተው የዘመቱብንን ጠላቶች ጦርነት ገጥመን ማሸነፍ ብቻ ነው፣ ወይስ ሌሎች አማራጮችም አሉ? ካሉን ምንድናቸው?
አገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት ሃምሳ አመታት ሦስት እጅግ በጣም የተለያዩ የመንግስት አይነቶችን አስተናግዳለች፣ ዛሬ አራተኛውን እያስተናገደች ነው። እያንዳንዱ አገዛዝ ከሱ በፊት ከነበረው አገዛዝ ተረክቦ ያባባሰውና እሱ እራሱ ፈጥሮ ለሚቀጥለው አገዛዝ ያስተላለፈው ችግር አለ። የዛሬዋ ኢትዮጵያ በየዘመኑ የተፈጠሩና ከዘመን ዘመን እየተሸጋገሩ የመጡ ችግሮች የተከመሩባት አገር ናት። ወታደራዊው ደርግ ሥልጣን ይዞ ብዙም ሳይቆይ ህብረተሰብአዊት ኢትዮጵያን እንዴት እገነባለሁ ለሚለው ጥያቄ ነው ትኩረት መስጠት የጀመረው እንጂ የወዲፊቷን ኢትዮጵያ እንዴትና ከነማን ጋር እንገንባ ለሚለው ጥያቄ ቦታም አልነበረውም። ደርግ አገር ውስጥ ከተለያዩ ባለድርሻዎች ጋር የገባውን ጦርነት በኃይል ከማሸነፍ ውጭ ሌላ አማራጭ አለ ብሎ የሚያምን መንግስት አልነበረም። .
በ1983 ዓ.ም. ወደ ሥልጣን የመጣው ህወሓትም የሽግግር መንግስት ሲመሰርትም ሆነ የዛሬዋን ኢትዮጵያን ሲፈጥር ከሱ ፍላጎትና ፈቃድ ውጭ ምንም ነገር እንዲሆን አልፈቀደም። መንግስታት በተለዋወጡ ቁጥር ግን የኢትዮጵያ ህዝብ “ብሔራዊ እርቅ”፣ “ብሔራዊ መግባባት” ወይም “ሁሉን አቀፍ ድርድር” የሚልና በአቀራረቡ የሚለያይ በይዘት ግን ተመሳሳይ የሆነ ጥያቄ ከ1967 ዓ.ም. ጀምሮ ምኒልክ ቤተመንግስት የገቡ መሪዎችን ሁሉ ጠይቋል፣ ዛሬም እየጠየቀ ነው።
የዚህ ጽሁፍ ጸሐፊ የዛሬ ሁለት አመት ተደራድረን የጋራ አገር መፍጠር ካልቻልን አማራጩ ደም እየተፋሰስን መኖር ነዉ! (ecadforum.com) የሚል አንድ መጣጥፍ ለንባብ አብቅቶ ነበር። በዚህ መጣጣፍ ላይ ጸሐፊው ድርድርን አስመልክቶ “የኢትዮጵያ ህዝብ ከጠ/ሚ አቢይ አህመድ መንግስት በጉጉት ከሚጠብቃቸዉ ስራዎች ዉስጥ አንዱና ትልቁ “ማንነት” እና “ዜግነት” በሚል ጎራ ተለያይተው ሆድና ጀርባ የሆኑትን ሁለት ጎራዎች ወደ ድርድር ጠረቤዛ በማምጣት የወደፊቷን ኢትዮጵያ ቅርፅና ይዘት የሚወስኑ ትልልቅ ጥያቄዎችን እንዲመልሱ ማድረግ” አለበት የሚል የዉይይት ሃሳብ አቅርቦ ነበር። ይህ ጽሁፍ ለንባብ ከበቃ ከሁለት አመት በኋላ ዛሬም የብሔራዊ ድርድር ጥያቄ እየተጠየቀ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ለአገራዊ ድርድር ቦታ የሰጠ አንድም መንግስት ባለመኖሩና ጥያቄው ዘመናት በማስቆጠሩ እነማናቸው የሚደራደሩት፣ ማነው አደራዳሪው የሚለውና የድርድሩ ዋና ዋና ሃሳቦች ምንድናቸው የሚለው ጥያቄ ውስብስብ እየሆነ መጥቷል። ይህ የሚነግረን ግዜ በወሰድን ቁጥር ችግሮቻችንም ለችግሮቻችን መፍትሄ የምናገኝበትም መንገድ ይበልጥ ውስብስብ እየሆኑ እንደሚሄዱ ነው።
ህወሓቶች የጠ/ሚኒስትር አቢይ አህመድ መንግስት የድርድር ጠላት ነው እያሉ መክሰስ ከጀመሩ ቆይተዋል፣ ነገር ግን እነሱ እራሳቸው በ1983 አዲስ አበባ ሲገቡና ከገቡም በኋላም ለአመታት ከቀረበላቸው ጥያቄ አንዱ የብሔራዊ መግባባት ጉባኤ ይጠራ የሚል ነበር። ያኔ የነሱ መልስ ኢትዮጵያ ውስጥ የተጣላ ህዝብ የለም የሚል ነበር። ዛሬ ህወሓቶች በህዝብ ተጠልተው ከማዕከላዊው መንግስት እንዲባረሩ፣ እንደገና ጫካ እንዲገቡና ትግራይ የጦርነት አውድማ እንድትሆን ያደረገው ይህ “ኢትዮጵያ ውስጥ የተጣላ ህዝብ የለም” የሚለው የትዕቢተኞች መልስ ነው እንጂ ህወሓቶችማ ከሥልጣን ተባረው መቀሌ ከገቡ በኋላም ተደጋጋሚ የእንወያይ ጥሪ ቀርቦላቸው ነበር።
ኢትዮጵያ አንድነቷ ተረጋግጦ፣ ሰላምና መረገጋት ሰፍኖ የህዝቧን ቁሳዊና መንፈሳዊ ፍላጎት ማርካት የምትችለው በአንድ በኩል ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት ሲኖራት ነው፣ በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት ምን አይነት ቅርጽ መያዝ አለበት? ምን አይነት የዲሞክራሲ፣የፖለቲካ፣ የህግ፣ የኤኮኖሚና ማህበራዊ ተቋሞች ያስፈልጉናል የሚሉ ትልልቅ አገራዊ ጥያቄዎችን ኢትዮጵያዊያን ቁጭ ብለው ተደራድረው በጋራ ሲመልሱ ብቻ ነው። እነዚህ ትልልቅ ጥያቄዎች በነገስታቱ ዘመን በንጉሶች፣ በደርግ ዘመን በደርግና በኢሠፓ፣ በኢህአዴግ ዘመን ደግሞ በህወሓት ፊትአውራሪዎች ነበር የተመለሱት። የጥቂቶችን ወይም የአንድን ወገን ውሳኔ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደማይቀበለውና ዘለቄታዊነት እንደማይኖረው ያለፈው ግማሽ ምዕተ አመት ታሪካችን በግልጽ አሳይቶናል።
ኢትዮጵያ ዉስጥ ሁሉን አቀፍ ድርድር መኖር አለበት ብሎ የዚህ ጽሁፍ ጸሃፊ በነጋ በጠባ የሚወተውተው ትግራይ ውስጥ የተፈጠረውን ችግር በዉይይት ለመፍታት ብቻ አይደለም፣የትግራይ ችግር ተባብሶ ሌሎች “ትግራዮች” እንዳይፈጠሩም ነው። ድርድር መኖር አለበት የምንለው እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በግለሰብ ደረጃም በቡድንም መብቱና ነጻነቱ ተከብሮ በእኩልነት መኖር የሚችለውና፣ የነጻነታችን እና የእኩልነታችን መከበር የሚረጋገጠው ምን አይነት ዲሞክራሲያዊ፣ፖለቲካዊ፣ኤኦኖሚያዊና ማህበራዊ ተቋሞች ሲኖሩን ነው የሚለውን ትልቅ አገራዊ ጥያቄ በጋራ መመለስ እንድንችል ነው።
የትግራይ ህዝብ በተለይ የትግራይ ልህቃን እንዴትና ለምን እዚህ መአት ዉስጥ ገባን? እንዴትስ ነው የምንወጣው? ብሎ እራሱን መጠየቅ ያለበት ግዜ አሁን ነው። የትግራይ መጀመሪያም መጨረሻም ህወሓት ነው የሚል የተሳሳተ አቋም ይዞ አገርና ንብረት ሲወድምና በረጂም ዘመን የአብሮ መኖር ታሪካችን ላይ አስቀያሚ ጠባሳ ሲፈጠር ቁጭ ብሎ መመልከት ለትግራይም ባጠቃላይ ለኢትዮጵያም አይበጅም። ከአሁን በኋላ የህወሓት የሥልጣን ዘመን እንዲረዝም የትግራይ ወጣት ህይወት ማጠር የለበትም። ትግራይ ህወሓት ከመኖሩ ከብዙ ሺ አመታት በፊት ነበረች፣ ለወደፊትም ህወሓት የሌለባት ትግራይ ትኖራለች። “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” ባዩ ህወሓት ለትግራይ ህዝብም ለተቀረው ኢትዮጵያዊም የማይበጅ ፀረ ህዝብና ፀረ አገር ድርጅት ነው። የትግራይ ህዝብ በሚኖርበት አካባቢ እራሱን በራሱ ለማስተዳደርና፣ በማዕከል የፖለቲካ ሥልጣንን ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወገኖቹ ጋር ተጋርቶ ኢትዮጵያን በጋራ ለማስተዳደር የህወሓት መኖር አያስፈልገዉም።
ኢትዮጵያ ውስጥ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው አገራዊ ድርድር በክልሎች መካከል የሚደረግ ድርድር ነው የሚል ግምት የለኝም፣ሆኖም የወደፊቷ ኢትዮጵያ ምን መምሰል አለባት የሚል ትልቅ ውሳኔ ሲወሰን በውሳኔው ውስጥ የትግራይ ህዝብ ጥቅምና ፍላጎት መወከል አለበት የሚል ፅኑ እምነት አለኝ። ትልቁ ጥያቄ ይህ ጥቅምና ፍላጎት በማን ይወከላል የሚለው ጥያቄ ነው። አገር ውስጥና ከአገር ውጭ የሚኖሩ የትግራይ ልህቃን፣የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምሁራን፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መሪዎች ትግራይ ውስጥ የተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ እንዴት መብረድ አለበት የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ከፌዴራሉ መንግስት ጋር ውይይት መጀመር አለባቸው። በሌላ በኩል ደግሞ ትግራይን ጨምሮ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት የምታስተናግድ የተረጋጋችና በኤኮኖሚ የዳበረች ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እንዴት ነው የምንፈጥረው በሚለው ትልቅ አገራዊ ውይይት ዉስጥ ድህረ-ህወሓት ትግራይ እንዴት ትወከላለች፣ ማንስ ይወክላታል የሚለውን ጥያቄ መመለስ ይኖርባቸዋል።
ኢትዮጵያ 80 ብሔር ብሔረሰቦች እንዳሏት ይነገራል። እነዚህ ብሔር ብሔረሰቦች በሰፈሩበት የቦታ ስፋት፣ባላቸው የህዝብ ብዛት፣ ቋንቋና ባህል እንደሚለያዩ ሁሉ የወደፊቷ ኢትዮጵያ ምን መምሰል አለባት የሚለውን ጥያቄ የሚመልሱበትም መንገድ ይለያያል። አንዳንዶቹ እራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር ያላቸው ፍላጎት በጣም ከፍተኛ ነው (Territorial Autonomy)፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በግዛት ላይ ያልተመሰረተ ራስ ገዝ አስተዳደር ይፈልጋሉ (Non Territorial Autonomy)። አንዳንዶቹ በህግ አስፈጻሚውም በህግ አውጭም አካል ውስጥ ተመጣጣኝ የሆነ ሥልጣን ሊኖረን ይገባል የሚል እምነት አላቸው፣አንዳንዶቹ ደግሞ ባህላቸው፣ ቋንቋቸውና ታሪካቸው እስከተከበረ ድረስ ውክልናን ከዜግነት ውጭ አይመለከቱም። አብዛኛዎቹ ብሔር ብሔረሰቦች እራሳቸውን ከኢትዮጵያ ውጭ አይመለከቱም፣ የመገንጠል አላማን የሚያራምዱ አንዳንድ በጣት የሚቆጠሩ ብሔር ብሔረሰቦች (በተለይ የብሔር ልህቃን) አሉ።
ኢትዮጵያ ዉስጥ እያንዳንዱ ቡድን የሚፈልገውን ህገ መንግስታዊ ዲዛይን የማግኘት አቅሙ በራሱ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ቡድኖች ፍላጎትና የድርድር አቅም ላይም የተመሰረተ ነው፣ ደግሞም እያንዳንዱ ቡድን የሚፈልገውን ለማግኘት የሚከተለው መንገድ ወይም ሂደት አንዱ ቡድን በሌላው ላይ ተጽዕኖ የማድረግ አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ ይወስናል። በዚህ የተነሳ አንዳንዶቹ ቡድኖች ሁሉን አቀፍ ድርድር፣ አንዳንዶቹ ብሄራዊ መግባባት፣አንዳንዶቹ ህገ መንግስታዊ ጉባኤን አንዳንዶቹ ደግም የሽግግር ግዜ ፍትህን እንደ አማራጭ ይወስዳሉ። ለአንዳንድ ቡድኖች ህገ መንግስቱን የሚያረቀው አካል ጥንቅር እጅግ በጣም አስፈላጊ ሲሆን፣ ለአንዳዶች ደግም ህገ መንግስቱ የሚረቅበትና ረቂቁ የሚጸድቅበት ሂደት ከምንም ነገር በላይ አስፈላጊ ነው።
ህገ መንግስታዊ ድርድሮች በሚካሄዱባቸው አገሮች ውስጥ ትልቅ ክርክር የሚካሄደው መንግስት ምን አይነት ባህሪይ ሊኖረው ይገባል የሚለው ጥያቄ ላይ ነው። አንዳንድ ወገኖች ግን በመጀመሪያ መንግስት ዲሞክራሲያዊ መሆን የለበትም ወይ ብለው ይሞግታሉ። የኢትዮጵያ መንግስት ዲሞክራሲያዊ መሆን አለበት በሚለው ሃሳብ ላይ የማይስማማ ኢትዮጵያዊ የለም። ሆኖም ግን ኢትዮጵያ ብዙና የተለያዩ ብሄር ብሔረሰቦችና ያንኑ ያክል የተለያዩ ፖለቲካና ማህበራዊ ፍላጎቶች የሚገኙባት አገር ስለሆነች እነዚህን የተለያዩ ፍላጎቶች የሚወክሉ ወገኖች ዲሞክራሲ ያስፈልገናል በሚለው ጥቅል ሃሳብ ላይ ቢስማሙም፣ ምን አይነት ዲሞክራሲ ነው የሚያስፈልገን በሚለው ጥያቄ ላይ ግን በጣም ይለያያሉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ ሁሉን አቀፍ ድርድር ያስፈልጋል የሚባለውም እንዲህ አይነት አለመስማማቶችን ለማስወገድ ነው።
ኢትዮጵያ ዉስጥ በዲሞክራሲ ስም አብዛኛው ሊጨፈልቀን ይችላል፣ሃይማኖታችን፣ ባህላችንና ታሪካችን ላይከበር ይችላል ወይም እውቅና አይኖረንም የሚል ስጋት ያላቸው አያሌ አናሳ ቡድኖች አሉ። በእርግጥም በህግና በተቋሞች እንዲገዛ ተደርጎ በስምምነት ዲዛይን ያልተደረገ ዲሞክራሲ የአብዛኛውን ጥቅም ብቻ እያስከበረ አናሳውን ሊረሳ ይችላል። ይህ ስጋት የረጂም ግዜ የርስ በርስ ግጭትና የጦር አበጋዞች ባሉባቸው አገሮች ውስጥ እውነተኛ ስጋት ነው። አገራችን ኢትዮጵያ ደግሞ የረጂም ግዜ የርስ በርስ ግጭትም የጦር አበጋዞችም ያሉባት አገር ናት።
ኢትዮጵያ የብሔር አክራሪነት፣የፖለቲካ አለመረጋጋት፣የሥልጣን ፉክክርና አንዳንዴ የሚጋጭ ፍላጎት (Conficting Interest) ያላቸው የፖለቲካ ልህቃን ያለባት አገር በመሆኗ በትላልቅ አገራዊ ጥያቄዎች ላይ ተደራድረን ዉሳኔ ላይ ለመድረስ ብዙ ግዜ ሊወስድብን እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም። በተለይ ድርድሩ በተለያዩ ምዕራፎች ዉስጥ የሚያልፍ ከሆነና እያንዳንዱ ምዕራፍ የራሱ የሆኑ ሃሳቦችና ዉሳኔዎች ሲኖሩት ድርድር ረጂም ግዜ ይወስዳል። ለምሳሌ፣ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሽግግር ግዜ ፍትህ ነው የሚያስፈልገን? በቀጥታ ሁሉን አቀፍ አገራዊ ድርድር ውስጥ መግባት ነው ያለብን ወይስ በብሄራዊ መግባባት ውስጥ አልፈን ነው ወደ ሁሉን አቀፍ አገራዊ ድርድር መሄድ ያለብን? ህገ መንግስታዊ ጉባኤ ማካሄድ አለብን ወይስ እንደየአስፈላጊነታቸው በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ ሁሉ ማለፍ አለብን? እነዚህን ጥያቄዎች መመለስና –
- ጥያቄዎቹን ማን ይመልሳል
- በድርድሩ ላይ እነማን ይሳተፋሉ
- ተሳታፊዎቹን ማን ይመርጣቸዋል
- ተሳታፊዎች በምን መመዘኛ ይመረጣሉ
- በድርድሩ ውስጥ የሚወሰኑ ዋና ዋና ሃሳቦች ምንድናቸው
- ውሳኔዎች በምን አይነት መንገድ ነው የሚወሰኑት
- ድርድሩን የሚገዙ ህጎች እና ደንቦች እንዴትና በማን ይረቃሉ
- ድርድሩን የሚመራው ማነው
- የድርድሩ ቦታ የት ነው
የሚሉ ጥያቄዎችን ለመመለስ እንደ ኢትዮጵያ አይነቱ ለዘመናት የተጨቃጨና ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት ባህል የሌለው ልህቅ ባለበት አገር ውስጥ ብዙ ግዜ ሊወስድ ይችላል። ዋናው ድርድድር የሚጀምረው እነዚህ ውሳኔዎች ሁሉ ከተወሰኑ በኋላ ስለሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገው የፖለቲካ ድርድር ብዙ ግዜ ይወስዳል፣ደሞም ከባድና አስቸጋሪ ነው።
በቅርቡ ከጠ/ሚ አቢይ አህመድ ጽ/ቤት አገራዊ ድርድርን አስመልክቶ የተሰማው ዜና እጅግ በጣም የሚያበረታታ ዜና ነው። ይህ ድርድር ከፍተኛ ቅድመ ዝግጅት የሚፈልግ ድርድር ስለሆነ መንግስትን ጨምሮ ድርድሩን የሚያዘጋጁ አካላት ሁሉ ከዚህ ቀደም በብሄራዊ ደረጃ ተሰይመው የውኃ ሽታ ሆነው ከቀሩት የድንበር ኮሚቴና የሰላምና ዕርቅ ኮሚቴ ከተባሉ ሁለት ፕሮጀክቶች ትልቅ ትምህርት መቅሰም ይኖርባቸዋል። ይህ ድርድር ማዕከላዊው መንግስት ትግራይ ውስጥ ከህወሓት የጥፋት ኃይሎች ጋር የገባውን ጦርነት እንዲቆም ከማድረግ ጀምሮ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከአንድ መቶ አመታት በፊት ተጀምሮ በእንጥልጥል የቀረዉን የአገረ መንግስት ግንባታ ሂደት የሚያጠናቅቁና ኢትዮጵያን እንደ አገር በሚያቆሙ ፖለቲካዊና ዲሞክራሲያዊ ተቋሞች ላይ አገራዊ ስምምነት የሚፈጠርበት ድርድር መሆን አለበት። የድርድሩ ውጤት ባለቤት የኢትዮጵያ ህዝብ ስለሆነ የድርድሩ ሂደትና በድርድሩ ወቅት የሚወስኑት ውሳኔዎች ይዘት ለኢትዮጵያ ህዝብ በተከታታይ መገለጽ አለበት። ይህ እንዲሆን የኔም የአያሌ ኢትዮጵያዊያንም ምኞት ነውና ፍጻሜውን አምላክ ያሳምርልን!
ሰበር ዜና ደብተራ ሀብታሙና ኤርሚያስ ተደባደቡ ማለቴ በቃላት ሲናኮቱ ነበር ጦር ሳይማዘዙ አይቀርም ብዬ ነው፥
፥ሞት ለነፍጠኛ ልሂቃን ሁሉ ና በሙሉ ነፃነት ለማራ መሪ በማጣት የታመመ ሕዝብ