spot_img
Saturday, July 13, 2024
Homeነፃ አስተያየትአሜሪካ ኢትዮጵያን ካደች፣ መአቀብም ጣለች፣ እኛስ ምን እናድርግ

አሜሪካ ኢትዮጵያን ካደች፣ መአቀብም ጣለች፣ እኛስ ምን እናድርግ

ሰማነህ ታ. ጀመረ
ኦታዋ፤ ካናዳ
ተባባሪና አርታዒ: አቶ ንጉሴ ዓዳሙ
ቤሪ፤ ኦንታሪዎ፤ ካናዳ
መስከረም 10, 2014 ዓ.ም.

ዛሬ መስከረም 11 ቀን 2014 ዓ.ም. አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ለመወሰን የፈለገችውን ወስናለች። ኢትዮጵያን ለማንበርከክና የርሷ ተገዥ የሆነ የቡችላ መንግስት ለመፍጠር ብዙ ለፍታለች፤ ኢትዮጵያን በበቂ አስፈራርታለች። 

ሁሉም መንገድ ሲዘጋባት ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ መአቀብ አሽመድምዳ ቢቻል መንግስት መገልበጥ ባይቻላት የተበጣጠሰች ሃገር ለማድረግ ተግታ ሰርታለች። በዩጎዝላቢያ፣ በሊቢያ፣ በሱዳን፤ በኢራክ ስላደረገችው በኢትዮጵያም የማታደርግበት አመክንዮ አይኖርም። ለኢትዮጵያዊያን ይህ ስናስበው የነበር እንጂ በዱብዳ የመጣብን አይደለም። 

የሚገርመው የባይደን አስተዳደር የኢትዮጵያን ሕዝብ እና መንግስት ሊያሞኙና ሊያዘናጉ የሄዱበት መንገድ ነው። በኢትዮጵያ ዓዲስ ዓመት ዋዜማ ባይደን ለኢትዮጵያዊያንና ለኤርትራዊያን የመልካም አዲስ ዓመት ምኞታቸውን “እንቁጣጣሽ” ሲሉ የገለጡበት የአዛኝ ቅቤ አንጓች መልእክታቸው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በዚሁ እለት የተከበሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ጳጳሳትንና ካህናትን ያነጋገሩብት የሽንገላ አቀባበላቸው ነው። ይህ ድርጊታቸው በግልፅ ለሰው ያላቸውን ንቀት ቁልጭ አርጎ አሳይቶናል። ምክንያቱም ይህን ባሉበት ምላሳቸው ሃያራት ስዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ላይ የኢኮኖሚ መአቀብ መጣላቸውን አብስረዋል። የነርሱ እንቁጣጣሽ መሆኑ ነው።  

በተጨማሪ አፍጋሃኒስታን ላይ ተዋርዳ ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ ተቃውሞ የበዛበት የባይደን አስተዳደር የፖለቲካ ጫና አቅጣጫ ማስቀየር እንደፈለገ፣ ለዚህ ኢትዮጵያ አዲስ የጦርነት አቅጫ መፍጠር ነበረባት። ለአሜሪካ የኢትዮጵያ ሕዝብ መሞት፤ መስቃየት፤ መራብና መቸገር ምኗም አይደለም። ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር ፈርሳ እንደ ዩጎስዝላቭያ የተበጣጠሰች ሃገር ብትሆን ምርጫቸው ነው። 

የዴሞካራሲ መሰረት ነኝ የምትለው አሜሪካ ባዶ ስንክሳር መሆኗን አስመስክራለች። ሁሌም አሜሪካ አጋርነቷ ከአምባገነንና ከአሸባሪ ሃይሎች ጋር እንደሆነ ይታወቃል። ከሳልቫዶር አይንዴ፤ ከታሊባን፤ ከሕውሃት፤ ከፒተር ቦታ፤ ከፈርዲናንድ ማርቆስ፤ ከሳዳም ሁሴን፤ ከፓኪስታን ጋር የወገኑ የአምባገነን ባለሟሎች ለመሆናቸው ቀደምት ታሪካቸው ምስክር ነው። ጊዜው ሲደርስ እንደ ብርቱካን ልጣጭ ይወረውራሉ። ይህ ደግሞ የብልጣብልጥነት ዋና ማሳያ ነው።  

ስለሆነም የአሜሪካ መአቀብ ህወሓትን ወይም ኢትዮጵያን ይጎዳል ወይስ አይጎዳም በሚል ጉንጭ አልፋ ክርክር ውስጥ መግባት አልሻም። ይልቅ አዲስ የሚመሰረተው የኢትዮጵያ መንግስት ማድረግ በሚገባው መሰረታዊ ጉዳይ ላይ ትኩረት እንዲያደርግና መስራት የሚጠበቅበትን ጥቂት ጉዳዮች ከዚህ በታች ለመጠቆም እወዳለሁ።

 1. በጦርነቱ ላይ ትኩረት ሰጦ ኦፕሬሽኑ ባጭር ጊዜ እንዲቋጭ ማድረግ። የትህነግ ቡድን የመሸገበትን አከባቢ ለጥቂት ዓመታት በወታደራዊ ኮማንድ ፖስት ማስተዳደርና የትግራይን ክልል ከጦር መሣሪያ ነፃ ቀጠና ማድረግ።
 2. ኢትዮጵያ ከአሸባሪ ቡድን ጋር ድርድር አላደርግም በሚለው መሠረታዊ አቋሟ ፀንታ መቀጠል አለባት። ከአሸባሪ ጋር ድርድር የለም። የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ ሁሉ የሰብአዊ እና የንብረት ውድመት በኋላ ተመልሶ ወደ ድርድር ልሂድ ቢል ከውጭ ከሚደረግ ጫና ባሻገር የውስጥ ብሶትን የሚአባብስ ስለሚሆን ይህ ምዕራፍ የተዘጋ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርበታል።
 3. በሁሉም መስክ ከኤርትራ ጋር ያለውን ግንኙነት፤ አጋርነት እና ትብብር ይበልጥ ማጠናከር። የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች የኢትዮጵያዊያንንና የኤርትራዊያን ዲአስፖራዎች ግንኙነት ሕጋዊ ሰውነት ሰጠው እንዲአቀራርቡና አብረው እንዲሰሩ ማድረግ።
 4. የአሰብ ወደብን ለመጥቀም እንዲቻል ኢትዮጵያ በአስቸኳይ ከኤርትራ ጋር ስምምነት ላይ መድረስ ይጠበቅባታል። ይህ ለነገ የማይባል ዓብይ ዓጀንዳ ነው።
 5. ከሩሲያ፤ ከቻይና፤ ከቱርክ፤ ከጀርመን፣ ህንድ፣ አፍሪካ እና ከጃፓን ጋር ያለውን የኢኮኖሚ፤ ወታደራዊ፤ ቴክኖሎጃዊ፤ ዲፕሎማሲያዊና ማህበራዊ ግንኙነቶችን በእጥፍ ማጎልበትና ማጠናከር።
 6. ትህነግን፤ የትህነግ ደጋፊውችንና አምላኪዎችን ከመንግስት የቢሮ መዋቅር፤ የዲፕሎማሲ፤ መከላከያና የሕዝብ ደህንነት ተቋማት ውስጥ በአዋጅ ማጽዳት ለነግ የማይባል ጉዳይ ሊሆን ይገባል። 
 7.  አሁን አሁን እንደታየው ኢትዮጵያዊያንንና ወጣቱን ትውልድ በሃገር ስሜት እያነቃቁና እያበረታቱ አንድነቱንና ሕዝባዊነቱን ማጎልበት።
 8. ኢትዮጵያዊያን ከውጭ ሸቀጥ ይልቅ የራሳቸውን ምርት እንዲገዙ (buy Ethiopian) ማደርግ ከመንግስት የሚጠበቅ ይሆናል። 
 9. የቅንጦት እቃዎችን ከውጪ ማስመጣት ማቆም። ለምሳሌ እንደ ሰው ሰራሽ ፀጉር፤ የመዋቢያ ቁሳቁሶች፤ የቅንጦት ተሽከርካሪዎች፤ ወዘተ የመሳሰሉ ዕቃዎች ከውጪ ለተወሰነ ጊዜ መሸመት ማስቆም።
 10. የሳይበር ቴክኖሎጂን እና ደህንነትን ማጠናከር፤ በሃገሪቱ ባሉ ኬላዎች ላይም ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ።
 11. በውጭ ምንዛሬ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ፤ የጥቁር ገበያን በአስቸኳይ መዝጋትና በጥቁር ገበያ የተሰማሩ ወንጀለኞች ላይ ህዝብን ሊያስተምር በሚችል መልኩ ሕጋዊ ቅጣቶችን መፈጸም።
 12. ሆን ብለው የዋጋ ግሽበት በሚፈጥሩ ነጋደዎችና ቸርቻሪዎች ላይ የማያዳግምና አራያ ሊሆን የሚችል እርምጃ መውሰድ።
 13.  መሰረታዊ በሆኑ የሸቀጥ ዓይነቶች ለምሳሌ፡ ጤፍ፤ ስንዴ፣ በቆሎ፤ ዳቦ፤ የምግብ ዘይት፤ መድሃኒት ወዘት በማሳሰሉት ላይ መንግስት ዋጋ ተምኖ መቆጣጠር። “የራበው ሕዝብ መሪውን ይበላል” በሚለው መርህ መሰረት መንግስት ለራሱ ሲል ይህን በቁጥጥሩ ስር ማድረግ ይጠበቅበታል።
 14. ዲያስፖራዎች አንድ የተወሰነ መዋጮ በቋሚነት ($1,000 / ዓመት / ሰው ) እንዲአዋጡ ማድረግ። አንድ ሚሊዮን ዲያስፖራ አንድ ቢሊዮን ዶላር ሊአዋጣ ይችላል። ይህ ሊሆን የሚችል ስለሆነ ወስኖ ወደ ተግባር መግባት ያስፈልጋል። ለሚያዋጡ ትውልደ ኢትዮጵያኖች የተለየ የዜግነት መለያ መታወቂያ ማዘጋጀት።
 15. የውጭ ግንኙነታችን አቅጣጫ እና ትኩረት ወደ አፍሪካ፣ ቻይና፣ ቱርክ፤ ሩስያ፤ እስያና መካከለኛው ምስራቅ እንዲሆን ማድረግ። የኢትዮጵያ መንግስት አምባሳደሮችንና ቆንስላዎችን ሲሾም ብቃትና ኢትዮጵያዊነትን መስፈርት በአደረገ መልኩ ሾሞ በመላክ በአስቸኳይ ወደ ተግባር ሊገባ ግድ ይላል።
 16. የዲያስፖራውን እምቅ የሃብት፤ የጉልበት፤ የእውቀትና የስራ ልምድ በሚገባ የመጠቀም ፖሊሲ በአስቸኳይ ንድፎ ተግባራዊ ማድረግ።
 17. ኢትዮጵያን ለማዳን ሁሉም ዜጋ ተነሳስቶ ይገኛል። መጪው ጊዜ የከፋ ሊሆን ስለሚችል ሁሉም ለሃገሩ ዘብ እንዲሆን ማሰልጠን ይገባል። ወጣቱ ከደባል ሱስ፣ ከተስፋ መቁረጥ፣ ከአልባሌ ውሎ እንዲወጣ የብሄራዊ አገልግሎት ፕሮግራም መፍጠርና የሙያ ክህሎት፣ የስራ ባህልን አንዲያዳብር ማሰልጠን ከዚያም ባለፈ የሃገር ፍቅር እንዲገባው ታሪኩንና ማንነቱን ማስተማር።  በዚህ ሂደት ውስጥም ወጣቱን ትውልድ ዘመናዊ የውትድርና ትምህርትና ስልጠና ሰጥቶ ተጠባባቂ ሰራዊት (reserve army) እንዲሆን አዘጋጀቶ ማቆየት የሃገራችንን አንድነት ከማስቀጠል ባለፈ ብቁ ዜጋን መፍጠር ያስፈለጋል።

ማስታውሻ፤ አሜሪካ ኢትዮጵያን ካደች፣ መአቀብም ጣለች፣ እኛ ምን እናድርግ ለሚለው በቅድሚያ መአቀብ በየትም ሃገር ሰርቶ አያውቅምና ሳንረበሽ የቤት ስራችንን እንስራ። ኢትዮጵያ ትሻገራለች። ሞትና ውድቀት ለሰው በላው ስርዓተ ማህበር ዘ-አሜሪካ።


__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

1 COMMENT

 1. የአሜሪካን ከአምባገንና አሸባሪ ሃይሎች የቁርኝት ምርጫዎችን ሲዘረዝሩ ሳልቫዶር አየንዴን ከነዚያ ሃይሎች ጋር አንድ አድርገው አቅርበዋቸዋል። ሳልቫዶር አየንዴ በደቡብ አሜሪካ ቺሌ በዲሞክራሲ በሕዝብ የተመረጡ መሪ ነበሩ። በአሜሪካ በተደገፈ መፈንቅለ መንግሥት በመስከረም 11, 1973 ተደርጎ ቺሌን በሽብር ለገዛው ጀነራል አውጉስቶ ፒኖቸት የመንግሥትን ሥልጣን እንዲይዝ ተደረገ።
  አዲስ ለተመረጡና በቅርቡም ሥራ ለሚጀምሩት የፓርላማ አባላት በዝርዝር ያቅረቡዋቸውን አስትያየቶችና ለዳያስፖራውም ያቀረቡት ጥሪ ተግባራዊ እንዲሆኑም ደጋፊና ምኞቴም ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here