spot_img
Wednesday, June 12, 2024
Homeነፃ አስተያየትየተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞችና የአባል አገራት መብትና ግዴታ (ባይሳ ዋቅ-ወያ)

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞችና የአባል አገራት መብትና ግዴታ (ባይሳ ዋቅ-ወያ)

ባይሳ ዋቅ-ወያ1  
***** 

ባለፈው ሳምንት ከኢትዮጵያ የተባረሩትን ሰባት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ሠራተኞችን አስመልክቶ ከተለያዩ አቅጣጫዎች አስተያየቶች እየጎረፉ ነው። አብላጫው አስተያየት የኢትዮጵያን መንግሥት ድርጊት የሚያወግዝ ሲሆን አነስ ያለው ወገን ደግሞ የመንግሥቱን ድርጊት የሚደግፍ ነው። ወቃሾቹም ሆኑ ደጋፊዎች፣ ይህ ነው የሚባል ሕጋዊም ሆነ ልማዳዊ ዓለም አቀፋዊ የዲፕሎማሲ ወይም ልማዳዊ አሠራርን የሚደግፍ ዋቢ ያደረገ ሰነድ ሳያቀርቡ እንደው በደፈናው “አይቻልም” ወይም “ደግ አደረገ” በማለት ውዥንብር እየፈጠሩ ነው። በዚህ አጭር ጽሁፌ፣ በተግባር ላይ ያሉትን ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶችንና በአገራት መካከል ለዘመናት ሲተገበር ከነበረው ልምድ እንዲሁም ለሰላሳ ዓመታት በተመድ ውስጥ በተለያየ ደረጃ ስሠራ በነበረበት ዘመን ካካበትኩት ልምድ ተነስቼ ከወገናዊነት በጸዳ መልኩ ይህንን ጉም ለማጥራት እሞክራለሁ። 

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ማለት በ1945 ዓ/ም ከአምሳ የማይበልጡ አገራት በጋራ ያቋቋሙት የራሱ ቻርተር ያለው፣ አባል አገራቱ በያመቱ በሚያዋጡት መዋጮ የሚተዳደርና የነዚህን ሉዓላዊ አገራት ፍላጎትና የጋራ ዓላማ በተግባር ለመተርጎም የተቋቋመ ዓለም አቀፋዊ ድርጅት ነው። ኢትዮጵያ እንደ አንድ ሉዓላዊ አገርና በፋሺዝም ላይ የመጀመርያ ድልን እንደ ተጎናጸፈች አገር ብቻ ሳይሆን የድርጅቱ ቻርተር ሲረቅቅ በወቅቱ የኢትዮጵያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በነበሩት ታዋቂው የሶቦርን ዩኒቬርሲቲ ተመራቂ አክሊሉ ሃብተ ወልድ መሪነት የድርጅቱን ቻርተር ያረቀቀች መሥራች አገር ናት። ከመሥራች አባላቱ ሌላ፣ ድርጅቱ ያኔ ሲቆረቀር “አገር” ያልነበሩ፣ ዛሬ ግን ኢትዮጵያን በጸጥታው ምክር ቤት ያለመታከት የምትከሰዋ እነ እንቶኔን ጨምሮ 193 አባል አገራት አሉት። በድርጅቱ ቻርተር መሠረት ሁሉም የድርጅቱ አባል እኩል ሲሆኑ አምስቱ ግን ከሌሎች የተለየ ድምጽን በድምጽ የመሻር የቬቶ ሥልጣን አላቸው። የድርጅቱ ዋና አስተዳዳሪ Chief  administrative Officer (በተለምዶ የተመድ ዋና ጸሃፊ) የሚባለው 193ቱ አባል አገራቱ በሚሳተፉበት ቀጥታ ምርጫ ለዚህ ቦታ ብቁ ናቸው ተብለው ለውድድር ከሚቀርቡት ብዙ ግለሰቦች መካከል ድርጅታችንን ለማስተዳደር ብቁ ነው ብለው ለአምስት ዓመት የሚቀጥሩት፣ በቀጥታ በአባል አገራት መዋጮ የሚተዳደር ደሞዝተኛና ለአባል አገራቱ ሙሉ ተጠያቂነት ያለው የሲቪል ቢሮክራት ነው። 

በሉዓላዊ መንግሥታት መካከል የሚኖረውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና አንድን አገር ወክለው ወደ ሌላ ወዳጅ አገር የሚላኩትን ዲፕሎማቶች ጥቅማ ጥቅሞችና አይነኬነትን (privileges and immunity) ለመቆጣጠር የሚያስችል በ1961 ዓ/ም የተፈራረሙት የቪዬና ውል (Vienna Convention) ሲገዛው፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ወክለው ወደ ሌላ አገር ስለሚላኩ የድርጅቱ ሠራተኞች ጥቅማ ጥቅምና አይነኬነት የተፈራረሙት ነገር የለም። በርግጥ የ 1946ቱ የተመድ ውል (Convention on the  

privileges and immunities of the United Nations) በአብዛኛው ስለድርጅቱ ሕጋዊ ሰውነትና የድርጅቱን ተንቀሳቃሽም ሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረት አይነኬነት የሚያትት ቢሆንም ስለ ድርጅቱ ሠራተኞች መብትና ግዴታ ጥቂት አንቀጾችን አካትቷል። ስለዚህ ሰሞኑን ከኢትዮጵያ የተባረሩ የተመድ ሠራተኞችን በተመለከተ ሊጠቀስ የሚገባው ይኸው የ1946 ውል እንጂ መንግሥታት ስለሚለዋወጡት ዲፕሎማቶች መብት ስለሚያትተው የ1961 የቪዬና ውል አይደለም። 

በዓለም አቀፍ ግንኙነት ውስጥ ሁለት ዓይነት ዲፕሎማቶች አሉ። በመጀመርያው ተርታ የሚሠለፉት ዲፕሎማቶች አገራትን ወክለው የሚመደቡ አምባሳደሮችንና ሌሎች ለተመሳሳይ ወይም የአጭር ጊዜ ተልዕኮ የሚሠማሩ ዲሎማቶችን ያካትታል። እነዚህ በደንቡ መሠረት ከሆነ እንኳን በሰላም ጊዜ ይቅርና በላኪውና በተቀባዩ አገራት መካከል እንኳ ጦርነት ቢከፈት የሙሉ የአይነኬነት መብት (immunity)ያላቸው ዲፕሎማቶች ናቸው። ይህም ማለት የፈለገውን ዓይነት ወንጀል ቢፈጽሙም ካለ አገራቸው በጎ ፈቃድ ውጪ፣ ተመድበው በሚሠሩበት አገር ሕግ በወንጀል አይከሰሱም። 

ከመቶ ሺህ በላይ ከሚቆጠሩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች ውስጥ ግን ሙሉ ዲሎማቲክ መብት ያላቸው ግለሰቦች ሀ) የድርጅቱ ዋና ጸሃፊ፣ ለ) ምክትል ዋና ጸሃፊዎች (Under Secretary Generals) እና ሐ) ረዳት ዋና ጸሃፊዎች (Assistant Secretary Generals) ብቻ ናቸው። ከዚህ ውጭ ያሉ የደርጅቱ ሠራተኞችና በያገሩ የሚሾሙት የየድርጅቱ ተጠሪዎች (Representatives, Chiefs of Missions, Special Envoys, Heads of Offices etc) ሊኖራቸው የሚችለው የዲፕሎማቲክ መብት እንዳገራቱ መልዕክተኞች የሙሉ አይነኬነት ሳይሆን፣ የሙያዊ አይነኬነት (Professioanl Immunity)  

ብቻ ነው። ይህም ማለት ሙያቸውን መሠረት ያደረገና የድርጅታቸውን አገራዊ ተልዕኮ ከግብ ለማድረስ በሚያደርጉት እንቅስቃሴና ድርጊት ምክንያት ተቀባዩ አገር እንደ ጥፋተኛ ቆጥሮአቸው በአገሪቷ ሕግ መሠረት አይቀጣቸውም ማለት ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ብዙ የተለያዩ ተልዕኮ ያላቸው ፕሮግራምና ፈንድ (Program and Funds) እና (Humanitarian) የሚባሉ ዘርፎች ሲኖሩት ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽኔር ድርጅት (UNHCR)  በስተቀር ሌሎቹ በሙሉ በየአገራቱ ተልዕኮአቸውን ለማሳካት የሚጠቀሙት አባል መንግሥታት በያመቱ የሚያዋጡትን ዓመታዊ መዋጮ ነው። በያገራቱ ያላቸው ቢሮም ሥራውን የሚያከናውነው ተቀባዩ አባል አገርን በማማከርና ሙሉ በሙሉ ተቀባዩ አገር አስቀድሞ ባስቀመጠው የልማትና የእርዳታ መርሓ ግብር መሠረት ነው። የተመድ የሕጻናት ፈንድ (UNICEF) ከኢትዮጵያ የሕጻናትና የሴቶች ሚኒስቴር ጋር፣ የዓለም ዓቀፍ የጤና ድርጅት (WHO) የሚሠራው ከኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር ሲሆን፣ የምግብና የእርሻ ድርጅቱ (FAO) ደግሞ ከኢትዮጵያ የእርሻ ሚኒስቴር ጋር ይሠራል ማለት ነው።  

መንግሥት አስቀድሞ ካስቀመጠው ወይም በውይይት ሂደት ከተስማሙባቸው የሥራና የአፈጻጸም መግባባት ውጪ የተመድ ቢሮ አንዳችም ስንዝር ዝንፍ ሊል አይችልም። ተመድ በተፈጥሮው ኢ-ፖሊቲካዊ በመሆኑ፣ ድርጅቱ እንደ ድርጅት ወይም ሠራተኞቹ ከተመደበላቸው የልማትና የርዳታ ሥራ ውጪ፣ አልፎ አልፎ ግን በተቀባዩ አገር በጎ ፈቃድ መሠረት ለሽምግልና (mediation) ከመጠየቅ በስተቀር በምንም መልኩ በአገሪቷ የፖሊቲካ ሕይወት ውስጥ እጃቸውን ሊከቱ ከቶ አይችሉም። 

አንድ የተመድ አባል አገር መጀመርያ በስምምነት ቢሮውን ከፍቶ እንዲሠራ የፈቀደለትን የተመድ ድርጅት፣ በሆነ ምክንያት በድርጅቱ አሠራር ካልተደሰተ ያላንዳች ቅድመ ማስጠንቀቂያ ቢሮውን ዘግቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሹማምንቱ በሙሉ አገሪቷን ለቅቀው እንዲሄዱ ማድረግ ይችላል። ስለ ድርጊቱም ለተመድም ሆነ ለሌላ ማንም አካል ማብራርያ እንዲሠጥ ግን አይጠበቅበትም። ለምሳሌ በ2012 ዓ/ም የተካሄደውን ብሔራዊ ምርጫ አስከትሎ ከተልዕኮያቸው ውጪ ባገሬ ጉዳይ ጣልቃ ገብተዋል ብሎ የሩሲያ መንግሥት UNICEF እና UNDPን በጣም አጭር በሆነ ጊዜ ውስጥ ሞስኮ ያሉትን ቢሮዎቻቸውን ዘግተው ከነሠራተኞቻቸው በሙሉ የሩሲያን ግዛት ለቅቀው እንዲሄዱ አድርጓል። ድርጊቱ ከማንኛውም ሉዓላዊ አገር የሚጠበቅ ሉዓላዊ መብት ስለሆነ የሩሲያን መንግሥት ድርጊት ተመድም አላወገዘም። ሩሲያም ድርጊቷን እንድታብራራ ለመጠየቅ የደፈረ አንድም መንግሥት ወይም ድርጅት አልነበረም። 

የተባባበሩት መንግሥታት ድርጅት በየአባል አገራቱ ቢሮዎቸውን የሚከፍተውና ሠራተኞቹን የሚልከው በአገራቱ በጎ ፈቃድ ብቻና ብቻ ነው። የታዳጊ አገር መንግሥታት ለልማትም ሆነ ለእርዳታ ጥቅም ሲባል ተመድን በጣም ስለሚፈልጉ ራሳቸው አስቀድመው በአገራቸው ቢሮዎች እንዲከፈቱ ዋና ጸሃፊውን ይጠይቃሉ። የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኔርን የመሳሰሉትን ግን ቢሮ እንዲከፍቱ የሚጋብዝ አገር እምብዛም ነው። ለምሳሌ የተመድ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽኔር (UN High Commissioner for  

Human Rights) በአዲስ አበባ ቢሮውን ለመክፈት ኸያ ሰባት ዓመት ደጅ ጠንቶ፣ ዶ/ር ዓቢይ ሥልጣኑን ከወሰደ በኋላ ነው ተሳክቶለት አገራዊና ቀጠናዊ ቢሮውን በአዲስ አበባ ለመክፈት የቻለው። 

ከላይ እንደጠቀስኩት፣ የተመድ ቀጠናዊና አገራዊ ሹማምንት (Representatives, Chiefs of Missions, Special Envoys,  Heads of Offices, etc) ወደ አባል አገራት ከመላካቸው በፊት ልክ እንደ አንድ አገር ተወካይ ዲፕሎማት የተቀባዩን አገር ስምምነት (Agreement) ለማግኘት የተመድ ዋና ጸሃፊ ወይም ተወካዩ፣ የተሿሚዉን ታሪክና ያለፈን የሥራ ልምዱንና አገልግሎቱን እንዲሁም የትምህርት ደረጃውን የሚገልጽ ደብዳቤ ለተቀባዩ አገር መንግሥት ይልካል። ተቀባዩም አገር የተሿሚውን ማንነት አስፈላጊ ሆኖ ባገኘው መንገድ ሁሉ ከመረመረ በኋላ ይስማማኛል ብሎ ከወሰነ “እሺ ተቀብዬዋለሁ”  የሚል አጭር መልዕክት ለተመድ ይጽፋል። ተሿሚው ግን ለአገሪቷ የማይፈለግ ግለሰብ (persona non grata) ሆኖ ካገኘው ተቀባዩ አገር አብዛኛውን ጊዜ አንዳችም ደብዳቤ ለተመድ ሳይጽፍ ዝም ብሎ ለወራት መልስ ሳይሰጥ ይቆያል። ይህም ቆይታ የተሿሚውን ተቀባይነት ማጣት (non grata) ስለሚያሳይ ተመድ እንደገና የሌላ ተሿሚን ዶኩሜንት ይልክና ሌላ ዙር ሙከራ ይጀምራል። ለተቀባዩ አገር የሚስማማ ተሿሚ እስኪገኝ ድረስ ሙከራው ይቀጥላል። 

ከዚህ አሠራር የምንረዳው ትልቅ ቁም ነገር፣ አንድ ተቀባይ አባል አገር፣ አንድን የተመድ ባለሥልጣን ከመሾሙ በፊት እንኳ የማይፈለግ ግለሰብ (persona non grata) ሊያደርገው ይችላል ማለት ነው። በዚያውም ልክ፣ ተሿሚው መጀመርያ ላይ የአገሪቱን ስምምነት (Agreement) ካገኘና ሥራ ከጀመረ በኋላ፣ በአንድ የሆነ ምክንያት የተቀባዩን አገር መንግሥት ካስቀየመ፣ ያላንዳች መንግሥታዊ ማብራርያ ከአገሪቷ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲባረር ሊደረግ ይቻላል። ይህ አሠራር በመላው ዓለም ተቀባይነትን ያገኘ የማንም ሉዓላዊ መንግሥት መብት ስለሆነ፣ ተመድም “ተሿሚዎቼ ለምን ተባረሩብኝ” ብሎ አባራሪውን መንግሥት ለመጠየቅ አይችልም። በቅርቡ አንድ የተመድ የዓለም ምግብ ድርጅት (World Food Program) ሠራተኛ ለተመድ ሥራ ብቻ የተሠጠውን የተመድን ሳቴላይት ስልክ ለአቶ ጌታቸው ረዳ ሠጥቶ እንዲነጋገርበት እያደረገ ነው የሚለው ፎቶግራፍ በማኅበራዊ ሚዲያ መለጠፉን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የተባለውን ግለሰብ ከኢትዮጵያ ማባረሩን መረጃዎች ይጠቁማሉ። እንደ ተባለውም፣ መረጃው ትክክል ሆኖ መንግሥት ግለሰቡን በርግጥ አባርሮ ከሆነ አገራዊ ሉዓላዊነትን በተግባር የሚተረጉም ስለሆነ ድርጊቱ ትክክል ነው ወይስ አይደለም ብሎ የኢትዮጵያን መንግሥት ለመጠየቅ መብት ያለው ድርጅትም ሆነ አገር ሊኖር አይችልም።

ከዚሁ ጋር ተመሳሳይነት ያለው አሠራር ደግሞ፣ አንዳንድ መንግሥታት “የማይፈለገውን ተሿሚ” አልፈልግህም ብሎ በግልጽ ደብዳቤ አሳውቆ ከማባረር ይልቅ፣ የግለሰቡን “አለመፈለግ” (non grata) በቀጥታ መስመር ለተመድ ዋና ጸሃፊ ወይም ለተወካዩ “በቃል” ያሳውቁና ግለ ሰቡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተቀባዩን አገር ለቅቆ እንዲወጣ ይጠይቃሉ። ድርጊቱ አብዛኛውን ጊዜ “ያለ ጽሁፍ” ስለሚካሄድ፣ ስለሚባረረው ተሿሚ ብዙም አቧራ አይነሳም። ኢትዮጵያ ይህን ዓይነት ዘዴ በሰፊው ከሚጠቀሙት አገሮች አንዷ ነች። የዛሬ አሥር ወር ገደማ በትግራይ ጦርነት በተጀመረ ሰሞን በኢትዮጵያ የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽኔር ምክትል ኃላፊ የነበረውን የሆላንድ ዜጋ ያባረረችው በዚሁ ዘዴ ነው። በጊዜው የተሿሚው መባረር በተመድ ዋና ጸሃፊና ተወካዮቹ ዘንድ ቢታወቅም፣ አሠራሩ ተቀባይ አገራት በሰፊው የሚጠቀሙበት የልዕልናቸው መገለጫ አካል ስለሆነ፣ ተመድም ሆነ ሌሎችም አገራት አንዳችም ተቃውሞም ሆነ ጥያቄ አላነሱም። 

አንዳንድ አገራት ደግሞ፣ አንድን የተመድ ተሿሚ ለሥልጣን “አልፈልግህም” (non grata) ብሎ በግልጽ ደብዳቤ አሳውቆ ከማባረር ይልቅ ተሿሚው ከማንኛውም የተቀባዩ አገር ባለ ሥልጣን ጋር እንዳይገናኝ ያደርጋሉ። ይህ ዓይነት የተቀባዩ አገር ተሿሚውን የማግለል ውሳኔ ለድርጅቱ አገራዊ ተልዕኮ መሳካት እንቅፋት ስለሚሆን የተመድ ዋና ጸሃፊ ወይም ተወካዩ “ያልተፈለገውን” ተሿሚ አንስቶ በሌላ ተሿሚ ይተካዋል። ይህም “በመዝጋት የተሿሚውን አለመፈለግ” የማሳወቅ ዘዴ በብዙ አገራት የተለመደ አሠራር ነው። 

ሌላው ከዚሁ ጋር ተያይዞ መታየት ያለበት ጉዳይ፣ በ1948 ዓ/ም አባል አገራቱ በኒው ዮርክ በተፈራረሙት ውል መሠረት፣ የተመድ ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀስ ንብረት በተገኘበት የአባል አገር ግዛት ውስጥ በማንኛውም ጊዜና ቦታ አይነኬ (immune) ነው። የተመድ ሠራተኞች ግን፣ የአገሪቱ ሕግ በሚያዘው መሠረት አድልዖነት በሌለበት መልኩ ለምሳሌ በየኬላው ላይ የግል ዕቃዎቻቸውን ሊፈተሹና ሊበረበሩ ይችላሉ። ሠራተኞቹ የሚጓዙበት የተመድ መኪና ግን በተመድ ንብረትነቱ ምክንያት ዲፕሎማሲያዊ አይነኬነት (diplomatic immunity) ስላለው ከማንኛውም ዓይነት ፍተሻ ነጻ ሲሆን፣ የተመድ ሠራተኞች ግን ሙያዊ አይነኬነት (professional immunity) ብቻ ስላላቸው፣ ሊፈተሹና ሊበረበሩ ይችላሉ ማለት ነው። 

ኢትዮጵያ ሰሞኑን ስላባረረቻቸው ሹማምንት ጉዳይ ሁለት ነገሮችን ብቻ ማንሳቱ በቂ ይመስለኛል። የመጀመርያው፣ ኢትዮጵያ እንደ አንድ የተመድ አባል አገር በማንኛውም ደረጃ በኢትዮጵያ ተመድበው የሚሠሩ የተመድ ሹማምንትን ያላንዳች ማስጠንቀቂያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ግዛቷን ለቅቀው እንዲወጡ የማድረግ ሉዓላዊ መብት አላት። ስለ ድርጊቷም ለማንም አገር ሆነ ድርጅት ማብራርያ የመስጠት ግዴታ የለባትም። በዲፕሎማሲ ፕሮቶኮል መሠረት፣ ማንም አገር ወይም ድርጅትም ማብራርያም ሊጠይቅ ወይም ድርጊቱን ሊያወግዝ አይችልም። 

ሁለተኛው ደግሞ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን የማስከበር መብቷ እንደተጠበቀ ለ ሆኖ፣ ኢትዮጵያ በዚህ ቀውጢ ጊዜ የወሰደችው ውሳኔ ከጉዳቱ ጥቅሙ ያመዝን ይሆን ወይ የሚለው ጉዳይ ነው። ከኢትዮጵያ ጋር አንዳችም ባህላዊም ሆነ ፖሊቲካዊ፣ እንዲሁም ኤኮኖሚያዊ ትስስር ሳይኖራት፣ የኃያላን አገራትን የጣልቃ ገብነት ጥማት ለማርካት ብቻ ኢትዮጵያን በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ያለመታከት የምትከሰዋን እነ እንቶኔን ጨምሮ አሜሪካና አብዛኛው የአውሮፓ አገራት የሰሜኑን ጦርነት አስመልክቶ የውግዘት ውርጅብኝ እያወረዱ ባሉበት ሁኔታ፣ ምናልባት እንደ ምንም ለጥቂት ጊዜ መታገስ አይሻልም ነበር ወይ የሚል ሃሳብም አለ። የተመድ ሹማምንቶቹ ያደረሱት በደል ምን ያህል እንደሆነ የሚያውቀው ግን መንግሥት ብቻ ስለሆነ፤ ከዳር ሆነን ያደረሱትን ጥፋት በውል ሳናውቅ ዝም ብሎ “ይሻላል” ወይም “አይሻልም” ብሎ ለመሞገት ግን የሚቻል አይመስለኝም። 

ለማጠቃለል ያህል፣  

አገራት ሉዓላዊ ናቸው። በመሆኑም፣ የወዳጅ አገራትንም ሆነ የተመድን የበታችና የበላይ ሹማምንትን፣ ዋና ጸሃፊውን ጭምር በአገራቸው የመቀበልና ያለመቀበል ያልተገደበ ሉዓላዊ መብት አላቸው። ከመጀመርያውም ያላንዳች ማብራርያ፣ ተሿሚውን ግለሰብ ወደ አገሬ እንዲገባ አልፈልገውም ለማለት ይችላሉ። በፍላጎታቸውም አስቀድመው እንዲገባም ስምምነት ካደረጉ (Agreement) በኋላም የተመድ ተሿሚዎችን “የማይፈለጉ” (persona non grata) ሆነው ከተገኙ ደግሞ ያላንዳች ማብራርያ ሊያባርሯቸው ይችላሉ። በዚህ ድርጊታቸውም በማንም ምድራዊ ሕጋዊ አካል ፊት ያለመጠየቅ ሉዓላዊ መብት አላቸው። ኢትዮጵያም ሰባቱን የተመድ ሠራተኞች ያባረረችው ይህንን ሉዓላዊ መብቷን ተጠቅማ ስለሆነ በማንም አካል ልትጠየቅ ወይም ልትወገዝ አይገባም። ለማንም አካል ማብራርያ የመስጠት ግዴታም የለባትም። የአገር ሉዓላዊነት ዋና መገለጫው ይኽው ነውና!

1 ጸሃፊው ቀድሞ የተመድ ባለሥልጣን የነበሩ የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያ ናቸው።

****** 

ባይሳ ዋቅ-ወያ 

ጄኔቫ፣ መስከረም 17 ቀን 2021 ዓ/ም 
wakwoya2016@gmail.com

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

2 COMMENTS

 1. ለመሆኑ የተባበሩት መንግሥትታት ድርጅት (ተመድ) አባል አገራት በየዓመቱ የሚከፍሉት ክፍያ እንዴት ነው የሚወሰነው? የሚከፍሉት ክፍያስ መጠን ምን ያህል ነው?
  ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ የተመድ መግለጫ እንደሚያመለክተው፤ የዓመት ክፍያ የሚወሰነው በአባል አገራቱ የሕዝብ ቁጥር፣ ባላቸው የዓመት ምርት ገቢ መጠን፣ያለባቸው ዕዳ መጠንና ሌሎችም መስፈርቶች ታይተው የሚተመን ነው።
  የሚከፍሉት ክፍያን መጠን በተመድ የፌብርዋሪ 1, 2020 የአባል አገራት የዓመት ክፍያ ሰንጠረዥ ላይ እንደተዘረዘረው ለምሳሌ ለመጥቀስ፤
  ኢትዮጵያ ———$280,534 (ሁለት መቶ ሰማንያ አንድ ሺህ)
  ቺይና —-$336,780,502 (ሦስት መቶ ሰላሳ ሰባት ሚልዮን የሚጠጋ)
  ሕንድ——$23,396,496 (ሃያ ሦስት ሚልዮን)
  እንግሊዝ—$128,119,667 (መቶ ሃያ ስምንት ሚልዮን)
  ሩስያ—-$67,468,314 (ስድሳ ሰባት ሚልዮን)
  ቬነዝዌላ—$20,422,881 (ሃያ ሚልዮን)
  ኩባ—$2,244,269 (ሁለት ሚልዮን)
  ደቡብ አፍሪካ—$7,630,512 (ስምንት ሚልዮን የሚጠጋ)
  ግብጽ—-$5,217,924 (አምስት ሚልዮን)
  ኬንያ—-$673,280 (ስድስት መቶ ሰባ ሦስት ሺህ)
  ጋምብያ—$28,053 (ሃያ ስምንት ሺህ) ወዘተ።
  የተመድ አባል አገራት የዓመት ክፍያ ሰንጠረዥ በተጨማሪ የሚያመለክተው ምን ያህሉ በየወራቱ ሙሉ ክፍያቸውን የሚከፍሉ አባላት ቁጥር በጣም አንስተኛ መሆኑን ያመለክታል።
  የተመድ ቻርተር መሰርት ክቡር ዋይሳ ዋቅ ወያ ከላይ በጽሁፋቸው እንደገለጹት እኩል ድምስ ያላቸው መሆኑን ቢገልጽም በተለይ አሜሪካ ባላት ድምጽን በድምጽ የመሻር
  (ቪቶ ስልጣን) በመጠቀም እንዳሻት አድርጋለች፣ እያደረገችም ነው። የተመድ የእለት ተዕለት ውሳኔም የአባል አገራት መዋጮ የሚተዳደር በመሆኑ ከከፍያ አገራት አንዱ ከፍተኛውን መጠን በሆነ ምክንያት ለምሳሌ ተመድ ፖለቲካዊ ሆነ በማለት አልከፍልም ቢል የተመድ ሥራ ምን ያህል ጥገኛ እንደሆነ መገመት ይቻላል።

 2. תמונות אמיתיות באחריות בחורה הכי סקסית במרכז הארץ זמינה…

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here