spot_img
Tuesday, June 25, 2024
Homeነፃ አስተያየትየተሳሳተው ማነው? የአሜሪካ መንግሥት ወይንስ የዐብይ መንግሥት? (ክፍል ሁለት)

የተሳሳተው ማነው? የአሜሪካ መንግሥት ወይንስ የዐብይ መንግሥት? (ክፍል ሁለት)

ክፍል ሁለት

አክሎግ ቢራራ (ዶር)

በአሜሪካ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ የአፍሪካ ክፍል ሃላፊ የሆኑት ካረን ባሥ፤ ከላይ ያቀርቡት ትችት፤ ጥሪና ምክር ለአሜሪካ ባለሥልጣናት መርህ ግብአት ይሆናል የሚል ተስፋ አለኝ። ሆኖም፤ እሳቸው የተናገሩት ከHR 445 ውሳኔ ጋር አልተገናኘም። ውሳኔውን የመሩት ባለሥልጣን በመግለጫቸው እንዲህ ብለዋል። 1. “ህወሓት የልጅ ወታደሮችን መጠቀሙን ማቆም አለበት፤ 2. በአማራ ክልል ያሰማራውን ወራሪ ኃይል ማስወጣት አለበት፤.3. ከኦነግ ሸኔ ጋር ያቀናበረውን ህብረት መሰረዝ አለበት።”

በተጨማሪ፤ ባሥ 4. “የህወሓት ወታደራዊ ኃይሎች የእርዳታ ማጓጓዣ መኪናዎችን መማረካቸውና 5. የሚጫነውን ቁሳቁስ እየተጠቀሙ ጦርነቱን መቀጠላቸውን የማቆም ግዴታ አለባቸው” የሚሉትን በመሬት ላይ የሚታዩ ሃቆች አስምረውባቸዋል። ይህ ዘገባ ለተባበሩት መንግሥታት አመራርና ጽህፈት መርህ ሊሆን ይችላል፤ ለማዳመጥ ፈቃደኛ ካለ። ያላካተቱት ብዙ ነው፤ ለምሳሌ ህወሓት በአማራው ሕዝብ ላይ እልቂት ማካሄዱን፤ “ሂሳብ አወራርዳለሁ” ማለቱን።

“ሂሳብ አወራርዳለሁ” ማለት በአማራው ላይ እልቂት አካሂዳለሁ ማለት ነው። ጥያቄው የህልውና የሚሆነው ለዚህ ነው። አማራውን ጨፍጭፎና የኢኮኖሚ አቅሙን አውድሞ ኢትዮጵያን ማፈራረስ ይቻላል ማለቱ ነው። ከብቱን በጥይት የሚገልበት ምክንያት ለዚህ ነው።

በጠቅላላው፤ ህወሓት በአማራው ሕዝብ ላይ ያካሄዳቸውና አሁንም የሚያካሂዳቸው (ማይካድራና ሌሎች ማይካድራ መሰል እልቂቶች) እና ተባባሪው ሽብርተኛ ቡድን ኦነግ ሸኔ በወለጋና በሌሎች አካቢቢዎች ላይ ያካሄዳቸውና የሚያካሂዳቸው ዘውግ ተኮር እልቂቶች አለመጠቀሳቸው ቢያሳስበኝም ቅሉ፤ በባይደን መንግሥት ተሰሚነት ያላቸው ባሥ ቢያንስ ከላይ የተጠቀሱትን አምስት መሰረታዊ  ግዴታዎችን አቅርበዋል። ለዚህ አወንታዊ እውቅና ሊሰጣቸው ይገባል። 

ባሥ በመግለጫቸው ላይ እንደጠቆሙት፤ እኔም በተደጋጋሚ እንዳሳሰብኩት፤ የጦርነቱና የእልቂቱ መሰረት “ከዘውግ ልዩነት፤ ከፖለቲካ ሥልጣን ሽሚያና ከታሪክ ጋር” የተያያዘ ነው። በሌላ አነጋገር ሕገመንግሥቱ፤ ስርዐቱና የአስተዳደር መዋቅሩ ለችግሩ መሰረት ናቸው። ኦነግ ሸኔ ከህወሓት ጋር ተባብሮ የሚሰራበትም ክምንያት ይኼው ነው። ሱዳንና ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ የውክልና ጦርነት የሚያካሂዱበት ምክንያትም ጸረ-ኢትዮጵያና ጸረ-ኢትዮጵያዊነት የሆነው ስርዓት ወንፊትና መግቢያ ቀዳዳ ስለፈጠረላቸው ነው። 

H. RES. 445 በሚል የተላለፈው ውሳኔ “ሚዛናዊ ነው” ብለው የሚከራከሩ መኖራቸው እንዳለ ሆኖ፤ ጦርነቱን የጀመረው ህወሓት መሆኑን አምኖ፤ ትኩረት የሰጠውና ጥሪ ያደረገው ግን ክህደቱ ከተፈጸመ በኋላ የመከላከያ እርምጃ በወሰዱት በኢትዮጵያና በኤርትራ መንግሥታት ላይ ነው። በተጨማሪ፤ የአማራው ክልል ልዩ ኃይል በሃላፊነት እንደሚጠየቅ ተጠቅሷል። እነዚህ ኢትዮጵያን ለመታደግ የሚታገሉ ኃይሎች እርምጃ ባይወሰዱ ኖሮ የኢትዮጵያ የመፈራረስ እድል ከፍተኛ ይሆን ነበር። የአማራው ህልውናና የኢትዮጵያ ህልውና የአንድ ሳንቲም ግልባጭ ሆነዋል።

የምክር ቤቱ ውሳኔ ተጨማሪ እገባ እንዲካሄድ ያመቻቻል/አያመቻችም? የሚል ጥያቄ አቅርቤ የተላለፈውን ውሳኔ ይዘት ስመለከተው መልሱ ያመቻቻል ነው። በሁሉም ሰብአዊ እልቂቶች ላይ “ነጻ፤ ሚዛናዊና ፍትሃዊ የሆነ ዓለም አቀፍ ምርምርና ግምገማ ይካሄድ” የሚለው ጥሪ አግባብ ያለው መሆኑን እቀበላለሁ። ሆኖም፤ አቅጣጫውን በቅርብ ስመለከተው፤ ትኩረቱ በአማራውና በአፋሩ ሕዝብ ላይ፤ በተለይ ህወሓት “ሂሳብ እናወራርድበታለን” ባለው፤ የጥላቻ ኢላማ በሆነው በአማራው ሕዝብ ላይ አይደለም። ህወሓት በአማራው ሕዝብ ላይ ባለፉት አርባ አምስት ዓመታት አማራ ተኮር እልቂትና ውድመት አካሂዷል። ተጠያቂ ነው። ውሳኔው የተዛባ መሆኑን ቃል በቃል ልጥቀሰው። “(F) urgently determine whether atrocities committed in Tigray amount to war crimes and crimes against humanity; and (G) based on the investigations, impose targeted sanctions and accountability measures on those found responsible for committing human rights abuses and atrocities.”

ሚዛናዊ ለመሆን መስፈርቶች ያስፈልጋሉ። 

ክህደቱን የፈጸመውና ጦርነቱን የጀመረው ህወሓት ነው። ኤርትራን፤ ባህር ዳርን፤ ጎንደርን በሮኬት የደበደበው ህወሓት ነው። በማይካድራ ዘውግ ተኮር እልቂት የፈጸመው ህወሓት ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ጦርነቱን በፈቃዱ ካቆመ በኋላ ለአስርት ዓመታት ያሰለጠነውን ወታደራዊ ኃይልና ከኢትዮጵያ የነጠቀውንና በየዋሻው የቀበረውን ግዙፍ መሳሪያ ተጠቅሞ ጦርነቱን ሕዝብዊ ያደረገው ህወሓት ነው። ህጻናት/ወጣት ልጆች፤ እርጉዝ እናቶች፤ ልጃቸውን በእንቀልባ ይዘው የሚዋጉ የትግራይ እናቶችን ያሰለፈውና እንዲሞቱ የዳረገው ህወሓት ነው። ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ አፈራርሳታለሁ ብሎ ከኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶች ጋር ያሴረው ህወሓት ነው። እልቂቱና ውድመቱን ወደ አፋርና ወደ አማራ ክልል ያስፋፋው ህወሓት ነው። አጅግ በሚዘገን ደረጃ የአማራ ገበሬዎችን ከብቶች በጥይት የጨፈጨፋቸው ህወሓት ነው። አስቡት፤ ሌላው ቀርቶ አይሲስ ወይንም አልካይዳ ወይንም አልሽባብ እንኳን የማያደርገውን እንስሳዎችን የሚጨፈጭፍበት ዋና ምክንያት የአማራው ህዝብ ህልውና ለአደጋ እንዲጋለጥ፤ እንዲራብ ለማድረግና የስነልቦና ጦርነት ለማካሄድ ነው። 

የዓለምአቀፍ ድርጅቶች ሰብአዊ እርዳታ ለመስጠት ሲሞክሩ ቁሳቁስ የሚያንቀሳቅሱትን አብዛኛዎቹን (428) መኪናዎች ነጥቆ ለጦርነት የሚጠቀመው ህወሓት ነው። ምግቡን፤ መድሃኒቱን ነጥቆ ለራሱ ተዋጊዎች የሚጠቀመው ህወሓት ነው። መሰርተ ልማት የሚያወድመው ህወሓት ነው። የአማራውን መሬት ነጥቆ ወራሪውን ኃይል ከትግራይ አምጥቶ ሰብሉን እየሰበሰበ ወደ ትግራይ የሚያጓጉዝ ህወሓት ነው። ሊጥ የሚዘርፍና ተሸክሞ የሚሄድ ህወሓት ነው።

የኢትዮጵያ፤ የኤርትራ፤ የአፋር፤ የአማራና ሌሎች የኢትዮጵያን ህልውና ለማስከበር በዱር በገደሉ የሚታገለቱና መስዋእት የሚሆኑት ኃይሎች የትግራይን ሕዝብ የእልቂት ኢላማ አላደረጉም። አልዘረፉም። “በትግራይ ውስጥ የተካሄደው እልቂት ዘውግ ተኮር መሆኑ በአስቸኳይ ይጣራና እልቂቱን ያካሄዱት አካላት በሃላፊነት ይጠየቁ” የሚለውን ለማስተናገድ የሞራል ብቃት የሚኖረው በተመሳሳይ ደረጃ ህወሕት በማይካድራና ማይካድራ መሰል በሆኑ ዘውግ ተኮር እልቂቶች፤ ኦነግ ሽኔ በወለጋና በሌሎች አካባቢዎች ባካሄዳቸው እልቂቶች በሃላፊነት ይጠየቁ የሚል ሃረግም ቢጨመርበት ነበር። ጥሪውና ውሳኔው ሚዛናዊ አይደለም የምልበት ምክንያት ይኼው ነው። 

ባሥ የሰጡት መግለጫ የወደፊቱን የአሜሪካን መንግሥት ውሳኔ አቅጣጫ ያመለክታል። ችግሩ “በጦርነት አይፈታም” የሚለውን እየተቀበልኩ፤ ጦርነቱ በአቸኳይ ካላቆመና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ህወሓትን ያካተተ ብሄራዊ የእርቅና የሰላም (negotiated peace) ድርድር ይካሄድ የሚለው የጥፋቱ ዋና መንስኤ የሆነውን ህወሓትን  በቀላሉ መውጫ ቀዳዳ ይሰጠዋል፤ መልሶ የማንሰራራት እድሉን ያጠናክርለታል።  

ሁሉን አቀፍ ብሄራዊ ውይይትና መግባባት ለኢትዮጵያ ወሳኝ መሆኑን እኔም አምናለሁ። ጥያቄው ከማን ጋርና እንዴት የሚለው ነው። ቅድመ ሁኔታው ምን ይሆናል? ለድርድር የማይቀርበው አስኳል ጉዳይ የኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነት፤ ሉዐላዊነትና የመላው ሕዝቧ ህብረት ነው። ከጅምሩ ህወሓትና አጋሩ ኦነግ ሽኔ ይህንን ብሄራዊ አላማ ተቀብለው አያውቁም። እርቅና ሰላም ሲባል ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ሊሆን አይችልም። የአማራውን ሕዝብ ህልውና መስዋእት በማድረግ ሊሆን አይችልም። ህወሓት የነጠቃቸውን መሬቶች በማስረከብ ሊሆን አይችልም። 

ህወሓትና ኦነግ ሽኔ ኢትዮጵያን እንደ ሃገር ኢትዮጵያዊነትን እንደ ዜግነት መለያ ይቀበላሉ ወይንስ አይቀበሉም? ህወሓት በአማራው ሕዝብ ላይ የወሰነውን የእልቂት አዋጅ መሳብ አለብህ ብሎ የጠየቀው ኃይል የለም። ለምን? ኦነግ ሽኔ ብሄር ተኮር እልቂቱን በአስቸኳይ እንዲያቆም የጠየቀው ኃይል የለም። 

እነዚህና ሌሎች መሰረታዊ ጥያቄዎች አልተነሱም። የኢትዮጵያ ተራ ሕዝብ በወራሪው ኃይል እየተጨፈጨፈና ኢትዮጵያ እየደማች ለመቀጠል ስለማትችል፤ እነዚህ ጥያቄዎች እንደ ቅድመ ሁኔታ መነሳት አለባቸው። በድርድሩ ላይ ይነሳሉ ከተባለ ለድርድር የሚነሳውና ለድርድር የማይነሳው አልተለየም ማለት ነው። የዲሞክራሲ፤ የአስተዳደር፤ ይቅር የመባባል ወዘተ ጥያቄዎች አግባብ አላቸው። ለአሜሪካኖች በአሜሪካ ብሄራዊና ግዛታዊ አንድነት ላይ ድርድር አይታሰብም። ኢትዮጵያን በተለየ መስፈርት መገምገሙ የሚያስታውሰኝ አውሮፓውያን በበርሊን ጉባኤ ላይ ስለ አፍሪካ መቀራመት ያደረጉትን ድርድርና ስምምነት ነው። 

ማስፈራሪው በትር

ባሥ ጦርነቱ በአስቸኳይ ካልቆመና በጦርነቱ የሚሳተፉት ኃይሎች ሁሉ ለብሄራዊ ድርድር ፈቃደኛ ካልሆኑ የአሜሪካ መንግሥት ተጨማሪ “እገባ ያደርጋል፤ ኢትዮጵያን ከአጎአ ለማስወጣት ይገደዳል (I am also concerned that Ethiopia is in danger of sanctions from the Administration as well as compromising its ability to participate in AGOA if the violence continues” ያሉት አሳሳቢ ነው። ግን ተጠያቂው አካል ህወሓት መሆን አለበት አላሉም።

የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ጦርነቱ እንዲቀጥል እንደማይፈልጉ አውቃለሁ። ጦርነቱ የህልውና ጦርነት መሆኑን ግን አንርሳ። ወጣቶች ሆኑ ገበሬዎች፤ ድሃዎች ሆኑ ባለኃብቶች፤ ነጋዲዎች ሆኑ የቀን ሰራተኞች፤ ልዩ ኃይሎች ሆኑ ፋኖዎች፤ መከላከያዎች ሆኑ ሚሊሽያዎች ወዘተ በጦርነቱ የሚሳተፉበት ዋና ምክንያት ጦርነቱ የህልውና ጦርነት ስለሆነ ብቻ ነው። እነዚህ ኃይሎች ፈልገውት ሳይሆን ህወሓት፤ ኦነግ ሽኔ፤ ሰርጎ ገቦች፤ ሆዳሞች፤ የውጭ ጠላቶች በጋራ የኢትዮጵያን ህልውና ስለተፈታተኑት ነው። በኢትዮጵያ ህልውና ላይ ድርድር ሊኖር አይችልም። የአሜሪካ ባለሥልጣናት፤ የምክር ቤት አባላትና ሌሎች በጽሞና ያላጤኑት መሰረታዊ ጉዳይ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሃገሩ ህልውና ያለውን ቆራጥነትና መስዋእት ከፋይነት ልምድ ነው። 

ብሄራዊ እርቅ፤ ሰላም፤ ድርድር ያስፈልጋል። ግን ትርጉም ሊኖረው የሚችለው ህወሓት፤ ኦነግ ሽኔና ተባባሪ ኃይሎች ለሰላም ያላቸውን ተገዢነት ሲያሳዩ ነው። የሚያካሂዱትን እልቂት ሲያቆሙ ነው። ለእርቅና ለሰላም ያላቸውን ፈቃደኛነት ይፋ ሲያደርጉ ነው። በተለይ፤ የኢትዮጵያን ህልውና እናከብራለን የሚል ቃል ኪዳን ሲገቡ ነው። ትጥቃቸውን ፈትተው ለእርቅና ለሰላም፤ ለአብሮነት፤ ድህነትን በጋራ ለመቅረፍ የተዘጋጁ መሆናቸን ሲያሳዩ ነው። ህወሓት የሚከተለውን “የአማራ ሕዝብ ጠላቴ ነው፤ ሂሳብ አወራርዳለሁ” የሚለውን መርህና መፈክር ሲስብ ነው። አለያ ውጤቱ ታጥቦ ጭቃ እንደሚሆን እገምታለሁ። ለህወሓት መውጫ ቀዳዳ መስጠት አደጋው የባሰ እንደሚሆን አምናለሁ። 

ባሥ የመሩት HR 445 የችግሩን ጥልቀትና ስፋት አቅርቦታል። ግን መፍትሄ አይደለም። ህወሓት የፈጸመውን ግፍ፤ በደል፤ ክህደት፤ እልቂትና ውድመት ክብደት አልሰጠውም። ስላልሰጠው እኔ ሚዛናዊ ሆኖ አላገኘሁትም። ይህም ሁኔታ ወደ አሜሪካ መንግሥት የተሳሳተና የተዛባ ፖሊሲ ይወስደኛል። 

የአሜሪካ መንግሥት በዐብይ መንግሥት ላይ የሚያደርገው ተከታታይ ጫና ለምን?

የኢትዮጵያ መንግሥት የአመራር ጥንካሬና ድክመት እንደ ተጠበቀ ሆኖ (ለምሳሌ፤ በጥንካሬ በኩል አየር ኃይሉ የሚያደርገው ስልታዊ የማምከን ስራዎች ተአምራዊ መሆናቸው፤ በድክመት በኩል ደግሞ ሁሉንም ተዋጊ ኃይሎች በአመራር፤ በትጥቅና በስንቅ የማቀነባበርና እየተናበቡ ማጥቃት ክፍተት መኖሩ)፤ የሚያሳስበኝ የአሜሪካ መንግሥት የተሳሳተ አቋም ነው። ከላይ ያቀርብኩትን ጥያቄ ለመመለስ የምንችለው ከስሜት በላይ ጉዳዩ ስለ ዐብይ አለመሆኑን ከተረዳን ብቻ ነው። 

አንድ ግለሰብ ጠቅላይ ሚንስትሩን የመውደድ ወይንም ያለመውደድ፤ የመደገፍ ወይንም የመቃወም መብት አለው። እንደ ማንኛው መሪ፤ ጠቅላይ ሚንስትሩ ብዙ ድክመቶች ያሳያሉ። በኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነት፤ በኢትዮጵያ ሉዐላዊነትና ዘላቂ ጥቅም ግን የማያሻማ አቋም አላቸው። እኔ በበኩሌ ይህንን እንደ በረከት እቀበለዋለሁ። የምመክረው ትችቶቹን ለጊዜው በኪሳችንና በሆዳችን ይዘን አሁን የሚካሄደው የእልቂት፤ የውድመትና የህልውና ጦርነት ከተገባደደ በኋላ አናንሳቸው። 

ጉዳዩ ስለ ኢትዮጵያ ህልውና መሆኑን ተቀብለን በዚህ መርህ እንመራ። የአማራውን፤ የአፋሩን፤ የትግራዩን ወዘተ ደህንነት ከኢትዮጵያ ደህንነት ለይቸ ለማየት አልችልም። ኢትዮጵያ እንደ ዩጎስላቭያ ከሆነች በኋላ ማልቀሱ አይጠቅምም። የፈለገውን ያህል ዘውግ ተኮር ልዩ ኃይል ቢያደራጅ፤ ኢትዮጵያ ከፈራረሰች ሁሉም ተሸናፊ እንጅ አሸናፊ ሆኖ የሚኖር የለም። ሱዳንና ግብጽ የሚፈልጉትና የሚመኙት ኢትዮጵያ እንድትፈራርስ መሆኑን አሰምርበታለሁ። ወያኔ ከሃዲ ነው የምለውም በዚህ ምክንያት ነው። ከከሃዲ ጋር እርቅና ሰላም አይታሰብም። ስለሆነም፤ ጉዳዩ የአማራ ብቻ አይደለም። 

ወደፊት መረጃው ሲሰበሰብ ለማየት እንደምንችለው፤ ከእሩቅም ቢሆን ስከታተለው፤ በኢትዮጵያ የሚካሄደው የሰብአዊ እልቂትና የመሰረተ-ልማት ውድመት ሲደመር፤ በግራኝ ሞሃመድና በፋሽቱ ጣሊያን ከደረሰው ይብሳል። ይህንን ክፋትና ክስረት መልሶ ለመተካት አስርት ዓመታት ይወስዳል። የሞቱትን ወገኖቻችን ህይወት ግን ለመተካት አንችልም። 

የውጭ ኃይሎች ለራሳቸው ብሄራዊ ጥቅም ብለው ሁኔታውን አባብሰውታል። በጦርነቱ ተጠቃሚዎች ሆነዋል። በጦርነቱ የሚነግዱ የአገር ውስጥ ሆዳሞችና ከሃዲዎች እንዳሉ መገመት ቀላል ነው።

የኃይል ሚዛኑ ለማን ያደላል? 

የኃይል አሰላለፉን ሁኔታ በሚገባ ለማጥናትና አማራጮቹን ለመለየት ካልቻልን፤ እኛም የችግሩ አካል እንሆናለን። ምክንያቱም የምናስተጋባው አሉታዊ ፕሮፓጋንዳ ሁሉ ኢትዮጵያን ስለሚጎዳት ነው። ለምሳሌ፤ ምንም ሞያችን ሊደግፈው በማይችለው ደረጃ እኛ የጦርነቱን ሂደት እንገምግማለን፤ እንተቻለን። ህወሓት የሚያሰራጨውን የሃሰት መረጃ እናስተጋባለን። “የፌስቡኩ ጀግና” አማራ ወጣት ቁጭ ብሎ ጫቱን እያላመጠ፤ የአንዱን መንደር አማራ ከሌላው መንደር አማራ ለይቶ ይተቻል። የሚለው ለህወሓት መሳሪያ እንደሚሆን የተገነዘበው አይምሰለኝም።

አማራው በሙሉ ከሌላው ወገኑና አጋሩ ጋር–ሶማሌው፣ አፋሩ፤ ኦሮሞው፤ ጉራጌው ወዘተ–እንዲለያይ የሚሰሩ ህወሓተንኮለኞችና ሰርጎ ገቦች ብዙ ናቸው። ይህንን በህወሓት የተቀናበረ አሉታዊ ፕሮፓጋንዳውን ትክክል እንደሆነ ማስተጋባት ኢትዮጵያን ይጎዳታል። ከሁሉም በላይ በማህበረሰባዊ ሜድያ የሚተላለፈው ፕሮፓጋንዳ ኢትዮጵያን እየጎዳት ነው። 

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በጠላቶች የተከበበች አገር አገር ናት። ግብጽ፤ ሱዳን፤ የምእራብ አገሮች ወዘተ ምን እየሰሩ ነው? የግብጽን ጥንታዊ አቋም ለምንከታተለው የግብጽ መንግሥት ኢትዮጵያ እንድትበታተን እንጅ እንድትለማ ፈልጎ አያውቅም። ፕሬዝደንት ትራምፕ ግብጽ “የሕዳሴን ግድብ ቦምብ” እንድታደርግ ጥሪ ማድረጋቸውን የረሳን አለን። የአሜሪካ መንግሥት መርህ ዲሞክራት፤ ሪፐብሊካን አይለይም። የሚያስተጋባው የአሜሪካን ጥቅም ነው። በግብጽና በአሜሪካ መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነት አንርሳው።

በተጨማሪ፤ የተባበሩት መንግሥታት አመራር የችግሩ አካል መሆኑን በመረጃ አቅርቤዋለሁ። የተባበሩት መንግሥታት አመራር አልኩ እንጅ ድርጅቱን አላልኩም። ድርጅቱ የሁሉም አባል አገሮች ስብስብ ነው። ድርጅቱን የተለየ የሚያደርገው ትንሽም ሆነ ታላቅ፤ ሃብታምም ሆነ ድሃ፤ እያንዳንዱ አባል አገር በእኩልነት የሚስተናገድበት ዓለም አቀፍ ተቋም መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ይህ ማለት ግን፤ ኃያልና ኃብታም የሆኑ አገሮች ያላቸው ሚና ከትንሿ ጋቦን ወይንም ሴይንት ቪንሰንት አይለይም ማለት አይደለም። ይለያል። አሜሪካ ግዙፍ ድጋፍ ስለምትሰጥ የበለጠ ጫና የማድረግ አቅም አላት።

ቁም ነገሩ ግን፤ የተባበሩት መንግሥታት ሆነ ሌላ የውጭ አካል መፍትሄውን ሊያቀርብልን አይችልም።  በክፍል አንድ እንዳሳየሁት፤ ችግሩን የፈጠርነው እኛው ነን። መፍትሄውም የራሳችን ነው። ብሄራዊ መግባባት፤ እርቅና ሰላም የኢትዮጵያዊያን ጉዳይ ነው። ሃሳቡን መቀስቀስና መምራት ያለባቸው የኢትዮጵያ ባለድርሻዎች ናቸው። 

ወደ አሜሪካ መንግሥት አመራርም ስመለስ፤ ንጹሃን በገፍ ሲጨፈጨፉ፤ ሲራቡና ከቀያቸው እንዲለቁ ሲገደዱ፤ ገበሬው በማረስ ፋንታ ወደ ጦር ግንባር ለመሄድ ሲገደድ፤ በብዙ መቶ ሽህ የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወጣቶች ለአገራቸው መስዋእት ለመሆን የረባ መሳሪያ እንኳን ሳይሰጣቸው ወደ ጦር ግንባር ሲሄዱ፤ ኃብትና ንብረት ያላቸው የተቻላቸውን ለማድረግ ገንዘባቸውን ፈሰስ ሲያደርጉ፤ የሚቦረቦረው ወይንም እየመነመነ የሚሄደው የኢትትዮጵያ ብሄራዊ/ አገራዊ አቅም ነው። ጦርነቱ የሚያመክን ስለሆነ፤ በፍጥነት እንዲከናወን አስተዋጾ ማድረግ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ግዴታ ነው። 

አንድ ምሳሌ ልጥቀስ። የኢትዮጵያ ሕዝብ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነቱ አምኖ፤ ወጣቱ በብዛት ህይወቱን ለአገሩ መስዋእት እያደረገ ነው። ባለ ኃብቶች ካላቸው ገቢ እየለገሱ ነው። እናቶች፤ ሴት ወጣቶች ስንቅ እያቀረቡ ነው። በአፋር በተደረገ ስብሰባ ባለ ኃብቶች በአንድ ምሽት አምሳ ሚሊየን ብር ለግሰዋል። በአዲስ አበባና በሌሎች ከተማዎች የተጎዱ ወገኖቻችን ለመርዳትና መልሶ ለማቋቋም የሚደረገው እንቅስቃሴ የኢትዮጵያዊነት ተምሳሌት ነው። በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ድርሻቸውን እየተወጡ ነው። 

ኢትዮጵያዊያን ተባብረው፤ የዓለም ባንክ ለማድረግ ፈቃደኛ ያልሆነውን ሕዳሴ ግድብን እየሰሩ ነው። የትኛው ድሃ አገር ከአምስት ቢሊየን ዶላር በላይ ፈሰስ አድርጎ እንደ ሕዳሴ ግድብ ያለ መሰረተ ልማት ሰርቷል? ብለን መጠየቅ አለብን። እኔ እስክማውቀው ድረስ የለም። 

የአሜሪካ መንግሥት በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሆነ በጦርነቱ ዙሪያ  ሁሉ ሕዝባዊ ጥረትና በኢትዮጵያ ላይ የተከሰተውን አደጋ የፈጠረውን ከዘውግ ባሻገር የመተባበርና የሃሳብ ለውጥ (post ethnic polarization paradigm shift) ሂደት በሚገባ ያውቃል። በቅርቡ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ይመስለኛል፤ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ጊታ ፓሲና የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ሰብአዊ ድጋፍ ምክትል ሃላፊ ሳራ ቻርለስ ወደ አማራው ክልል (ባህር ዳር) ሂደው ስለ ክልሉ ሕዝብ ሰብአዊ እርዳታ ፍላጎት ዘገባ አድርገዋል። ዘገባዎች የሚያሳዩት፤ በድጎማ በሚታወቀው በትግራይ ክልል 900,000 ሰዎች እንደተፈናቀሉና አስቸኳይ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው መሆኑን ነው።

HR 445 የሰጠውን ትኩርት ስገመግመውና የተባበሩት መንግሥታት ተቋማትና የምእራብ መንግሥታት ትኩረት የሰጡትን ቀረብ ብየ ስመለከተው፤ ትኩረት የሰጡት ለትግራይ ሕዝብና ክልል ነው። ሽፋንና ትኩረት ያልተሰጠው እና ጥናቶች የሚያሳዩት ደግሞ፤ ህወሓት ጦርነቱን አስፋፍቶ ወደ አፋርና ወደ አማራ ክልል ወረራዎችን ካካሄደ በኋላ ከአራት ሚሊየን በላይ የሚገመት የአማራ ሕዝብ እንደተፈናቀለና ለርሃብ አደጋ እንደተጋለጠ ነው። እርዳታው ሚዛናዊ ይሁን እላለሁ።

አምባሳደር ፓሲ ከጉብኝታቸው በኋላ በሰጡት መግለጫ፤ የአሜሪካ መንግሥት በአማራው ክልል ለተፈናቀሉት የተቻለውን እርዳታ እንደሚያደርግ ጠቁመው፤ የአሜሪካ መንግሥት “ከዘውግ ልዩነት ባሻገር የኢትዮጵያን ግዛታዊ አንድነት፤ ሉዐላዊነትና የሕዝቧን አንድነት” እንደሚደግፍ ገልጸዋል። ይህ የሚመሰገን አቋም ነው። በተጻራሪው ደግሞ በዋሽንግተን ያሉት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሃላፊዎችና በኮንግሬስ አንዳንድ አባላት የሚሉት ከዚህ ተጻራሪውን መሆኑ ያሳስባል።

ለምሳሌ፤ የኮንግሬስ አባል የሆኑት ዲሞክራት ብራድ ሸርማን HR 445 በኢትዮጵያና በኤርትራ መንግሥታት ላይ ቅጣታዊ እቀባ (Punitive Sanction) ለማድረግ ኮንግሬስ ባዘጋጀው ውሳኔ ውይይት ላይ፤ እጅግ በሚዘገንን ደረጃ፤ “የአሜሪካ የመርከብ ኃይል (The US Navy) በኤርትራ ላይ እርምጃ መውሰድ አለበት” ብለው መክረዋል። ኔቪው “የኤርትራን ንግድ ማቆም አለበት” የሚል ማስፈራራያ ማቅረባቸው ሲያነጋግር ቆይቷል። የዚህ አይነቱ የኮንግሬስ አባል ምክር ከጣልቃ ገብነት ያለፈ፤ ቀጠናውን ወደ ከፋ ጦርነትና እልቂት የሚገፋ ሆኖ አየዋለሁ። 

እኔ እስከማውቀው ድረስ የኤርትራና የኢትዮጵያ መንግሥታት ለትግራይ ሕዝብ ሰብአዊ ድጋፍ እንዳይሰጥ አልከለከሉም። የተቃወሙት ግን፤ በሰብአዊ ድጋፍ ሽፋን ህወሓት/ወያኔ የእርዳታ መኪናዎችን እየጠለፈ ለጦርነት ማዋሉን ነው። ሸርማን ባሥ ከተናሩት ውጭ የአሜሪካ የመርከብ ኃይል ጣልቃ እንዲገባ ማሳሰባቸው የቀጠናውን ችግር ወደ ባሰ አቅጣጫ እንደሚወስደው መገመት አስቸጋሪ አይደለም።

ክፍል ሶስት ህወሓት የጫረው ችግር እየተባባሰ መሄዱን ያብራራል። የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት ጫናዎች በምን ምክንያቶች ዙሪያ አነጋጋሪና አሳሳቢ ሆነዋል? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ይሞክራል። 

October 27, 2021

ይህንን የሚዘገንን ቪዲዮ ተመልክታችሁ ፍረዱ። ህወሓት ከብቱንም፤ ቤቱንም፤ ሰውንም ይጨፈጭፋል

__

በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here