spot_img
Tuesday, June 25, 2024
Homeነፃ አስተያየትየተሳሳተው ማነው? የአሜሪካ መንግሥት ወይንስ የዐብይ መንግሥት?

የተሳሳተው ማነው? የአሜሪካ መንግሥት ወይንስ የዐብይ መንግሥት?

                                አክሎግ ቢራራ (ዶር)

“የኢትዮጵያ እንጅ የመንደር አገልጋዮች አይደላችሁም” 
ጠቅላይ ሚንስትር ዶር ዐብይ አሕመድ ለሚንስትሮች
“ኢትዮጵያ ከምትፈርስ፤ አካላችን ይፍረስ”

የጎንደሬዎች የክተት መፈክር 

ክፍል ሶስት 

ባለፉት ሁለት ተከታታይ ትንተናዎችና ተመክሮዎች እንዳሳየሁት፤ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት በጋራ የቆሙት የኢትዮጵያ ኃይሎች የሚታገሉት ከህወሓትና ከኦነግ ሽኔ ጋር ብቻ አይደለም። የአሜሪካን መንግሥት ግልጽነትና ሃላፊነት የማያሳይ አቋም ወደ ጎን ብንተወው፤ ለከሃዲው፤ ለጨካኙ፤ ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ ለማፋራረስ ቃል ኪዳን ለገባው ለህወሓት የመረጃ፤ የዓለም ሕዝብ ግንኙነት የበላይነትና የስነልቦና ድጋፍ የሚሰጡት በአንደኛ ደረጃ ግብጽና እንደ ፈረስ የምትጋልበው የሱዳኑ ወታደራዊ ኃይል፤ በሁለተኛ ደረጃ በአንቶኒዮ ጉተሬዝ የሚመራው የተባበሩት መንግሥታት ጽህፈት ቤትና በስሩ የሚገኙት የሰብአዊና የማህበረሰባዊ አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶች ናቸው።  የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሃፊና ቢሯቸው ለኢትዮጵያ ዘላቂነትና ለመላው ሕዝቧ ደህንነት ይሰራሉ የሚል እምነት የለኝም። 

ለትችትና ለግምገማ፤ በተለይ ለሹክሹክታ፤ ስም ለማጥፋት፤ ለሴረኛንትና በሁሉም ጉዳይ ከኔ በላይ የሚያውቅ የለም  ባይነት ቅድሚያ ለሚሰጡት የኢትዮጵያ “ሊቀ-ሊቃውንት”፤ የአሜሪካን መንግሥት ለምን በሶስተኛ ደረጃ የችግሩ አካል አድርገህ አላቀርብክም? እንደሚሉ እገምታለሁ። በተደጋጋሚ የአሜሪካ መንግሥት የዐብይን መንግሥት ለመቀየር ይሞክራል፤ አጓን (AGOA) በመሰረዝ፤ ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክና ከአየኤምኤፍ ብድር እንዳታገኝ ወዘተ እርምጃ ይወስዳል ብየ ሳሳስብ “የአሜሪካ መንግሥት ይህንን የመሰለ እርምጃ አይወስድም” የሚሉ እንደ ነበሩ ማስታወስ ያስፈልጋል። 

የአሜሪካ መንግሥት “ይህን ያደርጋል፤ ያን አያደርግም፤ ዲሞክራቶች ይህን ያደርጋሉ፤ ሪፐብሊካኖች ይህን አያደርጉም” ወዝተ የሚሉትን አከራካሪ ጉዳዮች ወደ ጎን ልተውና ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የሚመሩት የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ የወሰደውና ወደፊትም የሚወስደው አቋምና እርምጃ እርስ በእርሱ የሚጋጭ መሆኑን አሰምርበታለሁ። 

አንድ ምሳሌ ላቅርብ። ህወሓት ኢትዮጵያን በበላይነት ሲገዛ፤ እንኳን ዲሞክራሳዊ መብት የዲሞክራሲ ሽታም አልነበረም። አንድ በአምስት የስለላና የቁጥጥር መረብ አገር አቀፍ በሆነ ደረጃ ተዘርግቶ ሚስት በባሏ፤ ልጅ በአባቱ ይሰልሉ ነበር። ድርጅታዊ ምዝበራና የተቀነባበረ እልቂት የተለመደ ነበር። የኢትዮጵያ ሕዝብ ይኖርበት የነበረው ዘመን የጨለማ ዘመን ነበር ለማለት እችላለሁ።

ማንም ሊክደው የማይችለው የዲሞክራሲ ጮራ የበራው ጠቅላይ ሚንስትር ዶር ዐብይ አሕመድ ስልጣን ከያዙ በኋላ ነው። በብዙ ሽህ የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች ተፈቱ። የፖለቲካ ስደተኞች ወደ አገር ቤት ገቡ። ቢያንስ የመንቀሳቀስ፤ የመናገር፤ የመተቸት፤ የመደራጀት ወዘተ ሰብአዊና ዲሞክራሳዊ መብቶች እውቅና እየተሰጣቸው ሄደ። የህወሓት የጨለማ ዘመን የብልጽግና ፓርቲ ከሚመራው ዘመን ጋር ሲነጻጸር የሰማይና የምድር ልዩነት አለው። ብልጽግና ገና ያልፈታቸው ስርዓታዊና መዋቅራዊ ተግዳሮቶች መኖራቸው አይካድም። ከእነዚህ መካከል አፍራሽ የሆነውን፤ ዘውጋዊውን ሕገመንግሥት ማሻሻል የመጀመሪያውን ደረጃ ይይዛል። ዝንጀሮ እንዳለችው ግን፤ “መጀመሪያ መቀመጫየን።” ኢትዮጵያ ከፈራረሰች፤ የእርስ በእርሱ ጦርነት ከቀጠለ የጨለማው ዘመን ብርቅ ሊሆን ይችላል።

የዚህ ሃተታ ዋና መልእክት የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ የሚፈልገውን ፖሊሲ ስኬታማ ለማድረግ ወስኗል የሚሉ ብዙ ታዛቢዎች መኖራቸውን ለማጠናከር ነው። ይኼውም “ሁሉም የጦርነቱ አካላት፤ ያለ ምንም አይነት ቅድመ ሁኔታ ጦርነቱን አቁመው ለድርድር” ፈቃደኛ መሆን አለባቸው የሚል ነው። ይኼ ከሆነ ህወሓት የክህደት፤ የእልቂትና የውድመት ወንጀሉን እንደያዘ ይሳተፍና ይደራደር ማለት ነው።  

እኔ የአሜሪካን አቋም ለማመን ያስቸግረኛል። የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት በቅርቡ የሚናገሯቸውን ምክንያቶቸ ይዘት በአጭሩ ላቅርብና የሚናገሩት ከሚሰሩት ጋር ይታረቃል ወይንስ ይጋጫል? የሚለውን ለመመለስ እሞክራለሁ። 

 1. በ November 3, 2021 የሜድያ ገለጻ፤ የአሜሪካ ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ተጠይቆ እንዲህ ብሏል። ጦርነቱና እልቂቱ እየተስፋፋና እየተባባሰ ስለሄደ “እጅግ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። አሳሳቢ የሆነው የጦርነቱና የእልቂቱ መስፋፋት የኢትዮጵያን ግዛታዊ አንድነትና ህብረት” ወደ “አስጊ ደረጃ” ስላሸጋገረው ነው።
 1.  ኔድ ፕራይስ ይህንን ካለ በኋላ ከፍተኛ ትኩረት የሰጠው “በኢትዮጵያ ለሚኖሩና ለሚሰሩ የአሜሪካ ዜጎችና ቤተሰቦቻቸው ደህንነት” መሆኑን አስምሮበታል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጠቅሶ ሁሉም “በጦረነቱ የሚሳተፉ ኃይሎች ሁኔታውን በጽሞና እንዲያዩት፤ ጦርነቱን እንዲያቆሙ፤ የሰላማዊ ዜጎችን ሰብአዊ መብት እንዲያከብሩ” ወዘተ የሚል ጥሪ አቅርቧል።  ላይ  ነው። 
 1. ኔድ ፕራይስ ከተናገራቸው መካከል ገንቢ ጎን ያለው ጉዳይ ምንድን ነው? ብየ ራሴን ስጠይቅ፤ የውጭ ጉዳይ ሃላፊው ብሊንከን ህወሓት የትግራይን ድንበር አልፎ “በደሴና በኮምቦልቻ የሚያካሂዳቸው እልቂቶችና ውድመቶች አስከፊ” እና በአሜሪካ መንግሥት በኩል ተቀባይነት የሌላቸውና እንደ የጦር ወንጀል እንደሚያስጠይቁ መናገሩ ነው። እኔ የምጠይቀው ግን፤ የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት ህወሓት ጦርነቱን ሕዝባዊ አድርጎ፤ እጅግ በጣም የሚዘገንን እልቂትና ውድመት ከማካሄዱ በፊት ለምን ድምጹንና አቋሙን አላሳወቀም? 
 1. በማንኛውም አገር ታይቶ የማይታወቅ–የአማራ ሴቶችን መድፈርና ማዋረድ፤ የአማራ ወጣቶችን ሰብስቦ መጨፍጨፍ፤ የአማራውን ቤትና ንብረት ማውደም፤ የአማራውን መሰረተ ልማት መዝረፍና የተረፈውን ማውደም ወዘተ– ወንጀል መሆኑ እየታወቀ ስለ ደሴና ኮምቦልቻ አሁን መቆርቆሩ “ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ” አይደለም? እርግጥ ነው፤ “ጦርነቱ እስከ ቀጠለ ድረስ ሰብአዊ ቀውሱ” እየተባባሰ እንደሚሄድ ተናግሯል። ይህንን ግምገማ እኔም እጋራዋለሁ። ግን፤ ጦርነቱን ያስፋፋው የኢትዮጵያ መንግሥት አይደለም። የአማራው ልዩ ኃይል ወይንም ፋኖ አይደለም። የኤርትራ መንግሥት አይደለም። ሃቁ አንድ ብቻ ነው። ጥርነቱን ያስፋፋውና ኢትዮጵያ እንድተፈራርስ ቀን ከሌት የሚሰራው ህወሓትና አጋሩ ኦነግ ሽኔ ናቸው። ካልተነሱት አስኳል ጉዳዮች መካከል አንዱ፤ ህወሓት በሚያካሂደው እልቂትና ውድመት ምክንያት፤ 6 ሚሊየን አማራ ለሰው ሰራሽ ርሃብ መጋለጡ ነው። ይኼ የአማራ ተራ ገበሬና ሌላ ሰርቶ አደር ትግራይን አልወረረም፤ አልዘረፈም። የትግራይን ሴቶች አልደፈረም። የትግራይን ወጣቶች ሰብስቦ አልረሸነም። 

የመፍትሄው አቅጣጫ ወደ የት ያመራል? 

ለዚህ አሳሳቢ ሁኔታ መፍትሄው ምን ይሆናል? የሚለውን መሰረታዊ ጥያቄ ኔድ ፕራይስ በማያሻማ ደረጃ መልሶታል። ይኼውም “ሁሉም የጦርነቱ አካላት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ጦርነቱን በአስቸኳይ አቁመው ወደ ድርድር መሄድ አለባቸው” የሚል የአሜሪካ አቋም ነው። ኔድ ፕራይስ የሚያንጸባርቀው የበላይ ባለሥጣናትን አቋም ነው። 

ስለሆነም፤ ባለሥጣናቱ ምን ይላሉ? የሚለውን መገምገም ያስፈልጋል። ይህንን የአሜሪካን መንግሥት አቋም የአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልክተኛ ጀፈሪ ፌልትማን ወደ ኢትዮጵያ ከመሄዳቸው በፊት የአሜሪካ መንግሥት በሚደግፈው በUS Institute of Peace ስለ ኢትዮጵያና ስለ ጦርነቱ ሁኔታ የሰጥቱን የአቋም መግለጫ ባጭሩ አቀርባለሁ።

 1. “ኢትዮጵያ ጥንታዊ አገር መሆኗ፤ ለቀይ ባህርና ለመካከለኛው ምስራቅ የጅኦፖለቲካ” የበላይነት ፉክክርና ትግል ቁልፍ ሚና እንደምትጫወት፤ “በሁለተኛው የዓለም ጦርነትና በኮሪያ የአሜሪካ አጋር እንደ ነበረች”፤ ስለ ህወሓት መመራመር የጀመሩት “ በመለስ ዜናዊ እልፈት ወቅት” መሆኑንና ከመለስ ጋር “ተገናኝተው እንደማያውቁ”፤ አዲስ አበባ በነበሩበት ጊዜ ስለ “ጨለማው ዘመንና ምን ይመጣ ይሆን ስለሚለው ብዙ ሽክሹክታ” ይታዘቡ እንደ ነበር፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዶር ዐብይ ሥልጣን ይዘው “የፖለቲካ ምህዳሩን ሲያሰፉትና ለዲሞክራሳዊ ስርዓት ያላቸውን አቋም” በይፋ ሲያስተጋቡ የአሜሪካ መንግሥት የእርዳታ መጠን ከፍ እንዳለ፤ “በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል የተደረገውን የወዳጅነት ስምምነት የአሜሪካ መንግሥት በደስታ እንደ ተቀበለው”፤ በህዳሴ ግድብ ድርድር ዙሪያ “የትራምፕ መንግሥት የወሰደውን የእርዳታ ቅነሳ የባይደን አስተዳደር እንደ ሰረዘውና ድርድሩ ፍትሃዊ እንዲሆን ሚዛናዊ አቋም” መውሰዱን ወዘተ በድምራቸው ሲታዩ የአሜሪካና የኢትዮጵያ ግንኙነት ጠንካራ እንደ ነበረ ይፋ አድርገዋል።  
 1. ይህንን ወዳጅነት የሚያሻክር ምን ክስተት ተፈጠረ? የሚለውን ሲመልሱ ፌልትማን እንዲህ ብለዋል። “የአሜሪካ መንግሥት ህወሓትን ይደግፋል የሚባለው ሃሰት ነው።” ከላይ ኔድ ፕራይስ እንዳሳሰበው፤ ህወሓት “የትግራይን ድንበር አልፎ ጦርነቱን ወደ አፋርና ወደ አማራ ክልሎልች ማስፋፋቱ፤ ደሴንና ኮሞቦልቻን በኃይል መያዙ” አሳሳቢ መሆኑን ገልጸው፤ ግን ዋና ትኩረት የሰጡት “የኢትዮጵያ መንግሥት ለትግራይ ሕዝብ መድረስ የሚኖርበትን ድጋፍ ሆነ ብሎ ማገዱን” ነው። መሳሪያ ተደብቆ ቢሄድስ? ምግቡን ተዋጊው ኃይል ቢማርከውስ? የሚለውን ሲያብራሩ የኢትዮጵያ መንግሥት የትግራይን ሕዝብ በረሃብ ለመቅጣት (Weaponizing food to punish Tigreans) “ኢስራኤልና ሳውዲ አረቢያ እንደሚያደርጉት ፍተሻውን ለማጠናከር ይቻላል” በሚል መልሰውታል።
 1. “ማንም መንግሥት ቢሆን ሽብርተኞችን፤ ከሃዲዎችንና አገር አፍራሾችን  ሊምር አይችልም ለሚለው ፌልትማን ይኼ “ይገባናል” ብለው ነበር። እኔ የምጠይቃቸው ይገባናል ካሉ ለምን ከሃዲውን፤ ሽብርተናውን፤ አጥፊዎን ህወሓትን ያለ ምንም አይነት ቅድመ ሁኔታ ለድርድር ይጋበዝ ይላሉ? የአሜሪካ መንግሥት ኒው ዮርክንና ዋሽንግቶንን አውሮፕላን ነጥቆ ቦምብ ካደረገው ከአልካይዳ ጋር ለመደራደር ፈቃኛ ሆኖ ያውቃል? አይታሰብም። 
 1. የጦርንቱን ስፋት፤ ጥልቀትና ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ አንስተው ችግሩ “በድርድር እንጅ በጦርነት አይፈታም” ብለዋል;፡ ከእልቂቱና ከውድመቱ ባሻገር እኔን ያሳሰበኝ “The war threatens the integrity and unity of Ethiopia (ጦርነቱ የኢትዮጵን ግዛታዊና ሕዝባዊ አንድነት ያናጋዋል” ያሉት ነው። ይህን ካሉ በኋላ ደግሞ “የአሜሪካ መንግሥት ህወሓት አዲስ አበባ እንዲገባ አይፈቅድም። ህወሓት ተመልሶ ሥልጣን እንዲይዝም አንፈልግም። የአሁኑ ሁኔታ ከ 1991 ሁኔታ የተለየ ነው። በጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ የሚመራው የብልጽግና ፓርቲ ግዙፍ የሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ድጋፍ አለው” ብለዋል። ድጋፉን እኔም እጋራዋለሁ።
 1. የዐብይ መንግሥት ምርጫ አካሂዶ የሕዝብ ብልጫ ያለው አዲስ መንግሥት ከመሰረተና አግባብ ያለው መንግሥት መሆኑን የአሜሪካ ባለሥልጣናት ካመኑ፤ የፖለቲካ ሥልጣን አማራጭ ለምን አስፈለገ? ይህ ሕዝብ አደራ የጣለበት መንግሥት በምእራብ አገሮች፤ በተለይ፤ በአሜሪካ ግፊትና ጫና ከሽብርተኞች ጋር ልደራደርም ቢል እንኳን የመረጠው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይነሳበታል ብሎ ለማስብ አስቸጋሪ አይሆንም። ችግሩ፤ የኢትዮጵያን መንግሥት የሚገመግሙበት መስፈርት ሚዛናዊና ምክንያታዊ ሆኖ አላገኘሁትም። ሚዛናዊ ቢሆን ኖሮ፤ ህወሓትንና የኢትዮጵያን መንግሥት አቻ ለአቻ አድርገው ተደራደሩ አይሉም ነበር። 
 1. “አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትፈልገው ገንቢ የሆነ አማራጭና መንገድ ነው (The path not traveled)። የኛ ትኩረት የኢትዮጵያ አገራዊ/ብሄራው/ግዛታዊ/ሕዝባዊ አንድነት እንዲቀጥል ነው። አግዋ እንዳይቀጥል የምናደርግበት ዋና ምክንያት የኢትዮጵያ መንግሥት ግዴትውን እንዲወጣ ጫና ለማድረግ ነው።” ጥናቶችንና ምርምሮችን መሰረት አድርገው ፌልትማን “የርስ በእርስ ጦርነት እስክ ሃያ ዓመታት ድረስ ሊቀጥል ይችላል” ያሉትን እኔም ዓለም ባንክ በነበርኩበት ወቅት ዝነኛው ኢኮኖሚስት ፖል ኮሊየር ስለ የእርስ በእርስ ጦርነት አምካኝነት የጻፋቸውን አነብ ነበር። ጦርነቱ በተራዘመ ቁጥር፤ እልቂቱና ውደመቱ ከማይቻልበት ደረጃ ላይ ይደርሳል;፡
 1. ፌልትማን፤ “ገንቢ መንገድ” ያሉትን ሲያብራሩ፤ ኢትዮጵያ እንዳትበታተን ለማስቻል፤ “ብሄራዊ መግባባት” ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህንን የተቀደሰ ሃሳብ እኔም እጋራዋለሁ። ይህን አግባብ ያለው አማራጭ በእቅድና በስልት ማቀናጀት ያለባቸው የኢትዮጵያ ባለድርሻዎች ናቸው። ወደ ዝርዝሩ ሳልገባ፤ የኢትዮጵያ ባለሞያዎች እንዲያስቡበት አደራ እላለሁ።  
 1. ብዙም ባያብራሩትም ፌልትማን “ከጥቂት ኢትዮጵያዊያን ጋር ውይይት አድርጌ ነበር” ብለዋል። በሹክሹክታው የሰማሁት፤ የእነ ፕሮፈሰር መራራ ኦፌኮ፤ ኦነግ፤ አንድም፤ የህወሓት፤ የአገው ዲሞክራሳዊ እንቅስቃሴ፤ የአፋር አብዮታዊ እንቅስቃሴ፤ የጋምቤላ ሕዝባዊ ነጻነት፤ የሶማሌ እምቢተኛነ ወዘተ፤ በጥቅሉ ህወሓት የፌደራሊስት ኃይሎች ብሎ የሰየማቸው “ፌደራሊስቶች” ከፌልትማን ጋር እንደ ተገናኙ ተወርቷል። እነዚህ የዘውጋዊነት ተወካዮች ምን አማራጭ ለማቅረብ ነው? ከእሳቸው ጋር የተገናኙ የሚለውን አስቡበት። ፌልትማን ጉዳዩን ከማብራራት ተቆጥበዋል። ግን ይህ በጥቅሉ የሚያሳየው ታጥቦ ጭቃነትን ነው። ያሬድ ጥበቡ በፌስቡክ በ1991 ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ ወደ አዲስ አበባ ሊገባ ሲል ሪኮርድ ያደረገውን ለወቅቱ ሁኔታ አግባብ እንዳለው አስመስሎ እንዲህ ብሏል።

“ኢህአዴግ አዲስ አበባ ሊገባ ቀናት ቀርተውታል:: ዳዊት ዮሐንስ ጋ ስልክ ተደወለ:: ደዋዩ የአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት ባለሥልጣን ነው:: “ሠራዊታችሁ ወደፊት እንዲገሰግስ አንፈልግም፤ ባላችሁበት ቁሙ” ይለዋል:: ዳዊት አበደ :: ማን ብትሆን ነው አንተ ቀጭን ትእዛዝ ልትሰጥ የምትሞክረው? ይህ እኮ የህዝቦች መራራ ትግል ውጤት ነው: አይመለከትህም: አያገባህም ብሎ ጆሮው ላይ ዘጋበት:: መለስና ተስፋዬ ዲንቃ ለንደን  ላይ አንድ አዳራሽ እያሉ የኢህአዴግ ጦር ቦሌ አየር ማረፍያን ተቆጣጠረ:: አደራዳሪው ሄርማን ኮኸን የምንተእፍረቱን “የኢህአዴግ ሠራዊት አዲስአበባ እንዲገባ ተስማምተናል” ብሎ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠ::”

ይህንን በ 1991 በኸርማን ኮህን በኩል እውቅና ያገኘ የመንግሥት ለውጥ የጠቀስኩበት ምክንያት፤ ከአሁኑ ሹክሹክታ ጋር ተመሳሳይነት ስላለው ነው። ፌልትማን “ህወሓት አዲስ አበባ እንዲገባ አንፈቅድም፤ የፖለቲካ ሥልጣን እንዲይዝ አንፈቅደም” ወዘተ ብለው ቃል ገብተዋል። ግን በ 1991 ህወሓት የመራውን ኢህአዴግን ስልጣን እንዲይዝ አልረዳነውም ነበር ብለዋል። የአሁኑ ሁኔታም ከ 1991 ለውጥ የተለየ ነው ብለዋል። ምክንያታቸውም ያኔ የነበረው ለውጥ ከሶቭየት ህብረት ጋር ወዳጅነት የነበረው የደርግ መንግሥት ጸረ-አሜሪካ አቋም ስለ ነበረው የሚል ግምገማን ስለተደረገ ነው። የዐብይ ብልጽግና ፓርቲ ምርጫውን አሸንፏል፤ ኢትዮጵያ አግባብ ያለው መንግሥት አላት ማለታቸው ነው። ይህ ከሆነ “የፌደራሊስት ኃይሎች” የሚዘምሩትን ለውጥ ለምን የአሜሪካ መንግሥት ያስተናግዳል? የሚል ጥያቄ አቀርባለሁ። ለዚህ ነው፤ የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት የሚናገሩትን ለማመን እቸገራለሁ ያልኩት። 

 1. “ጦርነቱና እልቂቱ በአስቸኳይ ይቁም፤ ህወሓት ከአፋርና ከአማራ ክልል ይውጣ፤ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የሰየማቸው የቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዝደንት ኦባሳንጆ የሚመሩት የድርድር ቡድን” ስራውን በአስቸኳይ እንዲጀምር ያሳሰቡትን እኔም እደግፋለሁ። እኒህ አባት መሪ ቢያፍራ ለመገንጥል ስትሞክር በራስቸው አገር ላይ የደረሰው በኢትዮጵያ እንዲፈጸም እንደማይደግፉና ቦኮ ሃራም የሚያካሂደው የሽብርተኞች ሴራ ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለ ያውቃሉ። ስለሆነም፤ የአፍሪካን ችግር በአፍሪካዊያን ለመፍታት ቢቻል ገንቢ አማራጭ ይሆናል።
 1. የኢትዮጵያ መንግሥት የስድስት ወር አስችኳይ አዋጅ ከወሰነ በኋላ ፌልትማን ወደ ኢትዮጵያ መሄዳቸው ምንም አያስገርምም። እንዲያውም ገንቢ የሆነ ውይይት ከተደረገና የአሜሪካ መንግሥት የኢትዮጵያን ግዛታዊ አንድነት፤ ሉዐላዊነት፤ የሕዝቧን አንድነትና በምርጫ የተደገፈውን መንግሥት አግባብነትና ቀጣይነት (Legitimacy) በግልጽነትና ሃላፊነት በተሞላበት ደረጃ እስከ ደገፈ ድረስ ጉብኝቱ ይጠቅማል። ፌልትማን የተናገሩትን አስኳል ጉዳይ ተግባራዊ ቢያደርጉት፤ ለምሳሌ፤ ህወሓት ከአፋርና ከአማራው ክልል በአስቸኳይ መውጣት አለበት፤ ወደ አዲስ አበባ ሄዶ የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝ የሚያደርገውን ጉዞ እንቃወማለን፤ ህወሓት ጦርነቱን አቁሞ ለእርቅና፤ ሰላም የሚገዛ መሆኑን ያሳውቅ፤ የናይጀሪያው ፕሬዝደንት ኦባሳንጆ የድርድሩን ይዘት ይምሩት ወዘተ የሚሉትን ይፋ ቢያደርጉ “ገንቢ መንገድ” የሚሉትን መርህ ለማስተናገድ ይቻላል።

ለማጠቃለል፤ የእንቆቅልሹ እምብርት ከድምዳሜው ላይ ነው። ይኼውም፤ ፌልትማን ይህንን ሁሉ ከተናገሩ በኋላ ጥፋቱን አሁንም የጫኑት ጦርነቱን፤ እልቂቱንና ውድመቱን ከፈጸመው በህወሓት ላይ አይደለም። በኔ ግምገማና እምነት የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት የአሜሪካንና የኢትዮጵያን በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ፤ ከመቶ አስራ ስምንት ዓመታት በላይ የቆየ ግንኙነት መልሶ እንዲፋፋ ለማድረግ ፍላጎት ካላቸው ከፍተኛ ጫና ማድረግ ያለባቸው በህወሓትና በኦነግ ሽኔ ላይ ነው። ለዚህ ኢትዮጵያ በሚቆዩበት ወቅት ወይንም ከዚያ በኋላ የሚከተሉትን እርምጃዎች ቢወስዱ የመፍትሄው አካል ይሆናሉ። የኢትዮጵያን 120 ሚሊየን ሕዝብ ወዳጅነት ያረጋግጣሉ። ራሳቸው ከተናገሯቸው መካከል ለህወሓት፤ ለኦነግ ሽኔና ለተባባሪዎቻቸው ሊሰጧቸው ከሚችሉት የሚከተሉት አግባብ አላቸው፤

 1. ህወሓት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ከአፋርና ከአማራው ክልል በአስቸኳይ እንዲወጣ፤ ከኦነግ ሸኔ ጋር በመተባበር የሚያካሂደውን ጦርነትና እልቂት እንዲያቆም፤ ባያደርግ ግን የአሜሪካ መንግሥት ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን ድጋፍ እንደሚቀጥል፤
 1. የአሜሪካ መንግሥት የኢትዮጵያን ግዛታዊና ሕዝባዊ አንድነት፤ ሉዐላዊነትና ዘላቂ ጥቅም እንደሚደግፍ፤ በአፍሪካ ቀንድ ጸረ-ሽብርተኛነት አቋሙን ከኢትዮጵያ ጋር ተባብሮ እንደሚቀጥል፤
 1. የኢትዮጵያን ወቅታዊ ተግዳሮቶች ለመወጣት አጀንዳውን መምራት ያለበት የኢትዮጱያ መንግሥትና የኢትዮጱያ ሕዝብ መሆኑን የአሜሪካ መንግሥት እንደሚያምን፤ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተወካይ በቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዝደንት በኦባሳንጆ የሚመራውን የብሄራዊ መግባባት ድርድር የአሜሪካ መንግሥት እንደሚደግፍና፤
 1. በምንም አይነት ህወሓት ተመልሶ የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝ የሚያደርገውን ሙከራ የአሜሪካ መንግሥት እንደሚቃውም።

በመጨረሻ፤ ፌልትማን እንዳሉት፤ “ማንም መንግሥት ቢሆን ሽብርተኞችን፤ ከሃዲዎችንና አገር አፍራሾችን ሊምር አይችልም።” እጅግ የሚያስፈራ የብሄራዊ፤ ፌደራላዊ የመንግሥት አመራር እንዝህላልነትና ዳተኛነት ከከሰቱ የማይካድ ቢሆንም ቅሉ፤ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ በጋራ ሆኖ የሚታገለውና ከፍተኛ መስዋእት የሚከፍለውና መንግሥት አስቸኳይ አዋጅ ያወጣው የብልጽግና ፓርቲን ስልጣን ለማራዘም አይደለም። የኢትዮጵያ መንግሥትና አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ክተት ብሎ የተነሳው ኢትዮጵያን ከመፈራረስ ለመታደግ ነው። ይህንን በመሬት ላይ የሚታይ ሃቅ፤ የአሜሪካ መንግሥት ሊክደው ወይንም ችላ ሊለው አይችልም። 

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!

ክፍል አራት ይቀጥላል 

November 5, 2021

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here