spot_img
Friday, June 21, 2024
Homeነፃ አስተያየትየምዕራባውያን ጉዞ በታሪክ መነጽር ሲታይ (ደረጀ ተፈራ)

የምዕራባውያን ጉዞ በታሪክ መነጽር ሲታይ (ደረጀ ተፈራ)

(በግል የቀረበ ጥቅል ዳሰሳ)
ደረጀ ተፈራ፣

1. መግቢያ፣

የምዕራቡ ዓለም ስልጣኔ (Western Civilization) ከጥንት የግሪክ እና የሮማውያን ስልጣኔ የተገኘ፣ የክርስትና እና የይሁዲ ዕምነቶች እንዲሁም ቀድሞ ይከተሉት የነበረው የአረማዊ (pagan) ባህል ተጽዕኖ ያረፈበት እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። የአንድ ሃገር ስልጣኔና ታሪክ፡ ባቆመው ሃውልትና በገነባው ስነ ህንፃ፣ ባስመዘገበው የጦርነት ገድል፣ በስነ ጥበብና በስነ ጽሁፍ እና በመሳሰሉት በትውልድ የሚታወስ ሲሆን በአንድ አካባቢ ስልጣኔ ነበር የሚባለው ቢያንስ ህዝቡን (ዜጋውን) እና የግዛት ክልሉን የሚያስተዳድርና ከጠላት ጥቃት የሚከላከል መንግስታዊ ተቋም (መዋቅር) ሲኖር፣ የስልጣኔው እምብርት የሆነ የመንግስት መቀመጫ ከተማ፣ የኢኮኖሚ ምንጭ የሆኑ የስራ (የሞያ) ዘርፎች እንዲሁም መንግስትና ህዝብ የሚነጋገሩበት ብሄራዊ (የሥራ) ቋንቋ፣ ቤተ እምነት (ቤተ መቅደስ) እና የመሳሰሉት ሲኖሩት ነው።

2. የሮማን ኢምፓየር አፈጣጠርና ውድቀት (በትንሹ)፣

እንደሚታወቀው የሮማን መንግስት ሮሚለስ እና ሪመስ በተባሉ በቲበር (Tiber) ወንዝ ተጥለው ቀበሮ ጡቷን እያጠባች ባሳደገቻቸው ወንድማማቾች እንደተመስረተ በአፈ ታሪክ ሲነገር ይሰማል። የሮማን ኢምፓየር መንግስት ሃያል በነበረበት ጊዜ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ የአውሮፓ ጫፍ፣ ከሰሜን ብሪቴን እስከ ግብጽና የሜዲትራሊያን የባህር ዳርቻ ድረስ እንዲሁም የባልካን ሃገሮችን እና የመካከለኛውን ምስራቅን የሚያጠቃልል ነበር። የሮማን ኢምፓየር መንግስት በየግዛቱ ለሚያሰማራቸው ወታደሮች የሚያወጣው ወጪ በየጊዜው እየጨመረ በመሄዱና ኢኮኖሚውም እየተዳከመ በመምጣቱ በተለይ በሮማን የጦር መኮንኖች መሃል በተፈጠረ የስልጣን ሽኩቻ የተነሳ ምስራቃዊና ምዕራባዊ የሮማን ኢምፓየር ተብሎ ለሁለት ተከፈለ። መቀመጫውን በጥንቷ የሮም ከተማ ያደረገው ምዕራባዊው የሮማን ኢምፓየር ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ሲንገታገት ከቆየ በኋላ ሮማውያን ባርባሪያን (Barbarian) ብለው በሚጠሯቸው ከጀርመን ምድር የራይንን (Rhine) ወንዝ እየተሻገሩ ወደ ሮም በሚፈልሱ በጀርመን ጎሳዎች ከተማው ተጥለቀለቀ። የሮም ከተማ ህዝብ ቁጥር በየጊዜው እጅግ እየጨመረ በመምጣቱ ህግና ስርዓት እየተፋለሰ፣ ስርዓት አልበኝነት እየተስፋፋ፣ ከተማዋ ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ እየሆነች መጣች። በመጨረሻም በ5ኛው ክ/ዘ ላይ ምዕራባዊው የሮማን ኢምፓየር ሙሉ በሙሉ ፈርሰ። በሌላ በኩል ደግሞ መቀመጫው በኮኒስታንቲኖፓል ከተማ (ኢስታንቡል) የነበረው የቤዛንታይን ወይም ምስራቃዊው የሮማን ኢምፓየር ለረጅም ዘመናት ከቆየ በኋላ በ15ኛው ክ/ዘ በኦቶማን ቱርክ ወረራ ላይመለስ ወደመ። 

የአውሮፓ የጭለማ ዘመን (European Dark ages) ተብሎ በሚጠራው ከ5ኛው እስከ 10ኛው ክ/ዘ በሚገኘው የመካከለኛው ዘመን በአውሮፓ ውስጥ ከአንዱ አካባቢ ወደሌላው የህዝብ ፍልሰት የተደረገበት በተለይም በጀርመን ይኖሩ የነበሩና እንዲሁም ከምስራቅ አቅጣጫ ፈልሰው የመጡ እንደ ሃን (Han) ዓይነት ማህበረሰቦች ወደ ምዕራብ አውሮፓ የፈለሱበት ዘመን ነው። በተለያዩ የአውሮፓ አካባቢዎች ከሰፈሩ የቫይኪንግ/ የኖርስ ህዝቦች ውስጥ: ከልት (Celts)፣ ቫንዳልስ (Vandals)፣ ኪምብሪ (Cimbri)፣ ጎትስ (Goths)፣ አንግሎ (Anglo)፣ ሳክሶንስ (saxons)፣ ሎምባርድስ (Lombards) እና የመሳሰሉት ይገኙበታል። በተለይ ከራይን እና ከዳኑብ ወንዞች (Rhine and Danube river) ማዶ ይኖሩ የነበሩ የተለያዩ ቋንቋዎች ይናገሩ የነበሩ ነገዶች በጥቅሉ Germanic Tribes በመባል ይታወቃሉ። 

በ8ኛው ክ/ዘ በካቶሊክ ፖፕ እና ሾለሜ (Charlemagne) በተባለ የፍራንኪያ ንጉስ ምዕራባዊውን እና ማዕከላዊ አውሮፓን የሚያጠቃልል “ሆሊ ሮማን ኢምፓየር” የሚባል መንግስት ተመሰረተ። በዚህ የጭለማ ዘመን ከስልጣኔና ከእድገት አንፃር በአውሮፓ ይህ ነው የሚባል ጉልህ መሻሻል ያልታየበት ጊዜ ቢሆንም ግጭትና ጦርነት የቀነሰበት፣ የህዝብ ፍልሰት የሰከነበት፣ አንፃራዊ ሰላም የተገኘበት ህዝቡም ተረጋግቶ መኖር የጀመረበት የቫይኪንግ ህዝቦችን ጨምሮ አብዛኛው አረማዊ (Pagan) የነበረው የአውሮፓ ህዝብ ክርስትናን የተቀበለበት፣ የክርስቲያን ስነ ምግባርና የህዝብ አስተዳደር የተማረበት ዘመን ነበር። በመቀጠል በ16ኛው ክ/ዘ ቀድሞ የካቶሊክ መነኩሴ የነበረው “ማርቲን ሉተር” (Martin Luther) የተባለ የጀርመን ተወላጅ በካቶሊክ ክርስትና ላይ ተቃውሞ በማንሳት የፕሮቴስታንት የለውጥ እንቅስቃሴን (Reformation) ጀመረ። የማርቲን ሉተር ተከታዮች መንፈሳዊውን ህይወት ከዓለማዊ አስተሳሰብ፣ ከባህላቸው፣ ከግል ፍላጎትና ከሚያስገኝላቸው ልዩ ጥቅም አንጻር እየደበላለቁ በሚያደርጉት ፍልስፍና (Philosophical theology) በየጊዜው የተለያዩ የፕሮቲስታንት ቅርንጫፎች (denominations) ተፈጠሩ። ለምሳሌ የእንግሊዙ ንጉስ ሄንሪ 8ኛ (Henry VIII) ዙፋኑን የሚተካ ወንድ ልጅ ስለሌለው ሚስቱን ፈትቶ ሌላ ሴት ለማግባት የካቶሊክ ቤ/ክ ስላልፈቀደችለት የራሱን አዲስ Church of England የሚባል ቤ/ክ አቋቋመ፣ ሚስቱንም በራሱ ፍቃድ በመፍታት ሌላ ሚስት አገባ። ማርቲን ሉተር በካቶሊክ ላይ ያነሳው ተቃውሞ ውጤቱ በእምነት ብቻ የታጠረ ሳይሆን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ነጸብራቅ ያለው ለመሆኑ ብዙ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል።  

በመሆኑም በማርቲን ሉተር በጀርመን የተጀመረው የፕሮቴስታንት የለውጥ እንቅስቃሴ ቀስ በቀስ ከእምነት ወደ ፓለቲካ ትግል በመሸጋገር የጀርመን ብሔርተኝነትን አቀጣጠለ። በመሆኑም ፕሮቴስታንቲዝም ጀርመን እንደ ሃገር እንድትፈጠር ከፍተኛ ድርሻ ያለው ሲሆን ወደ ሌላውም የአውሮፓ ክፍልም በመዛመት ከሌሎች የአካባቢው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ጋር ተደማምሮ ከሆሊ ሮማን ኢምፓየር እየተለዩ እራሳቸውን የቻሉ በርካታ የአውሮፓ መንግስታት እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆነ። እንደሚታወቀው በሰሜናዊ ጀርመን የምትገኘውን የፕረሺያ (Prussia) ግዛት ለጀርመን የለውጥ ማዕከል ነበረች። የምጣኔ ሃብት እና የማህበራዊ ሳይንስ ምሁር የሆነው ማክስ ዌበር (Max Weber) የተባለ የጀርመን (ፕረሺያ) ተወላጅ የፕሮቴስታንት ስነምግባርና ካፒታሊዝም (The Protestant Ethic and the sprit of Capitalism) በሚል ርዕስ የፕሮቴስታንት እምነት ለካፒታሊስት ስርዓት ግንባታ እና ለግለሰቦች በሃብት መበልፀግ (Wealth and prosperity) ጠቃሚ መሆኑን የሚያትት መጽሃፍ አሳተመ። የማክስ ዌበር ጽሁፍ ከመንፈሳዊነቱ ይልቅ ዓለማዊ ህይወትን የሚያበረታታ በመሆኑ የጀርመን ህዝብን እምነቱን ከኑሮው ጋር በማስተሳሰር አዲስ ማንነት እንዲገነባ አደረገ። Iron Chancellor እየተባለ የሚጠራው የፕረሺያ መሪ የነበረው ኦቶቫን ቢስማርክ (Otto Von Bismarck) ዴንማርክን፣ ኦስትሪያን እና ፈረንሳይን በመውረር ግዛቱን በማስፋፋት በ1871 የጀርመን ኢምፓየርን (German Empire) መንግስትን በንጉስ ዊልያም እና በራሱ በቢስማርክ ቻንስለርነት (ጠቅላይ ሚኒስትርነት) መሰረተ። የጀርመን ብሔርተኞች እራሳቸውን የተለዩ “ወርቅ ህዝብ” እንደሆኑ በመግለጽ ምርጥ ከሆነው ከአርያን ዘር (Aryan master race) የተገኘን በመሆናችን ሌላው የአውሮፓ ህዝብ በእኛ ስር መሆን አለበት በማለት የጀርመን ህዝብን በመቀስቀስ በአንደኛው እና ሁለተኛው የዓለም ጦርነቶች ለብዙ ሚሊዮን ህዝብ ሞትና ስቃይ፣ በብዙ ቢሊየን ዶላር ለሚገመት ንብረት መውደም ምክንያት ሆኑ። 

ትንሽ ወደኋላ ሂደን በአውሮፓ የተደረገ የለውጥ እንቅስቃሴን ስንመለከት ከ15 ኛው እስከ 18 ኛው ክ/ዘ በአውሮፓ የባህል ህዳሴ፣ የአዕምሮ መነቃቃት ዘመንን እና የኢንዱስትሪ አብዮትን እናገኛለን (Renaissance, Enlightenment and Industrial Revolution)። በተለይ ክርስቶፎል ኮሎምበስ የተባለ የባህር አሳሽ በ1492 ከስፔን የባህር ወደብ ተነስቶ የቅመማ ቅመም እና የሃር የንግድ መስመር ለማግኘየት ወደ ህንድ እና ቻይና በባህር ላይ በሚጓዝበት ጊዜ ከአሜሪካ ድንበር በቅርብ ርቀት የሚገኙትን የባሃማና የካሬቢያን ደሴቶች አካል የሆኑትን ሄይቲ፣ ዶሚኒካን ሪፐብሊክ፣ ኩባ፣ ቬንዙላ እና የመሳሰሉትን ደሴቶች ባገኘ ጊዜ ምዕራባዊ የህንድ ግዛት (West Indies) የደረሰ ስለመሰለው እነዚህ አካባቢዎች ቀድሞ የማይታወቁ አዲስ የዓለማችን ክፍሎች መሆናቸውን አልተገነዘበም ነበር። ይሁን እንጂ ከሱ በመቀጠል አሜሪጎ ቪስፑቺ (Amerigo Vespucci) የተባለ የጣሊያን የባህር አሳሸ ወደዚሁ አካባቢ በመምጣት የተገኙት ደሴቶቹ አዲስ የዓለማችን ክፍል መሆናቸውን አስታወቀ። በእሱም ስም አካባቢው አሜሪካ ተብሎ መጠራት ተጀመረ። በቀጣይም ስፔኖች ከአካባቢው ነባር ህዝቦች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ባደረጉት አሰሳ ከፍተኛ የሆነ የወርቅና አልማዝ ክምችት አገኙ። ከስፔን አሳሾች ጎን ለጎን የፖርቹጋል የባህር አሳሾችም ወደዚሁ አካባቢ ወርቅና ሌሎች ሃብቶችን ፍለጋ በተለይም ወደ ብራዚል ይጎርፉ ነበር። በመቀጠልም በሃገራቸው መንግስታት ከሚደገፉ ከስፔን እና ከፖርቹጋል አሳሾች በተጨማሪ የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይ፣ የደች መንግስታት እና ሌሎች አውሮፓውያን በግልና በቡድን በመሆን ወደ አካባቢው በብዛት በመፍለስ መስፈር ጀመሩ (settlements)። ለምሳሌ ጀምስ ታውን፣ ፕላይማውዝ፣ አልባኒ፣ ጀርሲና የመሳሰሉት ይገኙበታል። እነዚህ ሰፈራዎች እየተስፋፉ በመሄድ የቨርጂኒያ፣ ማሳቹሴት፣ ኒዎርክ፣ ኒው ጀርሲ የመሳሰሉ ቅኝ ግዛቶች (Colonies) በ16ኛው እና በ17ኛው ክ/ዘመን መፈጠር ቻሉ። በወቅቱ በአውሮፓ ገበያ የስኳር እና የትንባሆ ምርት ከፍተኛ ተፈላጊነት ስለነበረ አውሮፓውያን በሰሜን እና ደቡብ አሜሪካ እንዲሁም በአካባቢው በሚገኙ የካሪቢያን ደሴቶች አፍሪካውያንን እግርና አንገታቸውን በሰንሰለት እያሰሩ ወደ አካባቢው በባርነት በማጋዝ በጥቁር ህዝብ ጉልበት ለስኳር ማምረቻ የሚሆን የሸንኮራ አገዳ፣ ቱባኮ (ሲጋራ)፣ ጥጥ እና በመሳሰሉት ገንዘብ አመንጪ (cash crop) የሆኑ እርሻን በማስፋፋት አምርተው በአውሮፓ ገበያ በመሸጥ ከፍተኛ ገቢ (ሃብት) አፈሩ።

3. አውሮፓውያን እና አረቦች በአፍሪካ ላይ የፈጸሙት ወረራ፣

16ኛው እስከ 19ኛው ክ/ዘመን ባሉት ዘመናት በአትላንቲክ የባሪያ ንግድ ከምዕራብ አፍሪካ ወደ ሰሜን እና ደቡብ (ላቲን) አሜሪካ እንዲሁም በአካባቢው ወደሚገኙ የካሪቢያን ደሴቶች በትንሹ ከ12 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ አፍሪካውያን እየታፈኑ በባርነት ተግዘዋል። ይህ ቁጥር ከወቅቱ ከነበረው የአፍሪካም ሆነ የአሜሪካ ህዝብ ቁጥር አንጻር ካየነው እጅግ በጣም ትልቅ ነው። ለምሳሌ በ17ኛው ክ/ዘመን በሰሜን አሜሪካ በ13ቱ የእንግሊዝ ግዛቶች (colonies) ውስጥ ይኖር የነበረው ህዝብ ወደ 25 ሚሊዮን አካባቢ እንደሆነ ይገመታል። በወቅቱ በመርከብ ተጭነው ከተጓጓዙት አፍሪካውያን ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በረሀብ፣ በድብደባ፣ በጠባብ መርከብ ውስጥ በመታፈን፣ ከንጽህና ጉድለት በሚመጡ በበሽታዎች በጉዞ ላይ አልቀዋል፣ አስከሬናቸው የሻርክ ቀለብ ሆኗል። አብዛኛዎቹ ሴቶች በሚያጓጉዟቸው አውሮፓውያን ይደፈሩ ስለነበር ከመርከብ ሲወርዱ በሆዳቸው የጌቶቻቸውን ልጆች ይዘው ነበር የሚወርዱት። በወቅቱ አፍሪካውያን በጨካኝ አውሮፓውያን እንደ ከብት (እንደ ሸቀጥ) የሚሸጡና የሚለወጡ እነሱም ሆኑ የሚወልዷቸው ልጆቻቸው የገዢዎቻቸው ንብረት ነበሩ። እንደ ውሻ ቁራጭ ዳቦና በውሃ የተቀቀለ ሩዝ እየተወረወረላቸው ያለ እንቅልፍ ሌት ተቀን ከባድ የጉልበት ሥራ እንዲሰሩ ይገደዱ ስለነበር በርካታ አፍሪካውያን በስራ ጫናና በጭንቀት ስራ ላይ እያሉ ዝለው በመውደቅ ይሞቱ ነበር፣ ሌሎቹ ደግሞ በጤንነት መጓደል፣ በምግብ እጥረት (nutritional deficiency)፣ በበሽታ፣ በድብደባ ብዛት እና በመሳሰለው አልቀዋል። 

በአውሮፓውያ ከተከናወነው Atlantic Slave Trade ተብሎ ከሚጠራው ቀደም ብሎ ከመካከለኛው ምስራቅ በመጡ የአረብ ነጋዴዎች የአረብ የባሪያ ንግድ (Arab Slave Trade) በአፍሪካ ይከናወን ነበር። የአረብ ነጋዴዎች ከ7ኛው እስከ 16ኛው ክ/ዘመን ባሉት ጊዜያት ቀይ ባህርን እና የህንድ ውቅያኖስን ተሻግረው ወደ ምስራቅና ሰሜን አፍሪካ በመምጣት የባሪያ ንግድ ያከናውኑ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ይመሰክራሉ። ለምሳሌ ለሱዳን አዋሳኝ ከሆነው በቀይ ባህር በኩል ወደ ሰሜን እና ምዕራብ አፍሪካ ድረስ ወደ ውስጥ ዘልቀው በመግባት ከበርበር (አማዚር) ጎሳዎች ጋር ቅንጅት በመፍጠር የሃገሩን ጥቁር ህዝብ እንደ እንስሳ እያደኑ በባርነት ሸጠዋል (ቸብችበዋል)። በዚህ ከምስራቅ አፍሪካ የቀይ ባህር ወደብ እስከ ምዕራብ አፍሪካ ድረስ በተዘረጋው የባሪያ እና የሸቀጥ መተላለፊያ የንግድ መስመር የሚያልፍበትን የጥቁር ህዝብ መኖሪያ ሃገር አረቦች በቋንቋቸው “Bilad al Sudan” በማለት ይጠሩት ነበር። በአረብኛ ቋንቋ “Bilad al Sudan” ማለት የጥቁሮች ሃገር ማለት ነው። በመሆኑም የአካባቢው ነዋሪዎች በአረብ ተፅእኖ ሥር በመውደቃቸው ስማቸው፣ ቋንቋቸው፣ ባህላቸው፣ እምነታቸውና የማንነት መገለጫዎቻቸው እንዲቀይሩ በመደረጉ ጥንታዊ መጠሪያ ስማቸው ቀርቶ አረቦች ባወጡላቸው “ሱዳን” በሚባል ጥቅል ስም ይጠራሉ። ባጠቃላይ ነዳጅ (Petroleum) በማይታወቅበትና በአረቢያ ምድር ተቆፍሮ ባልወጣበት በዛ ጊዜ አረቦች የሚተዳደሩት በአብዛኛው በንግድ እና የቤት እንስሣትን በማርባት የነበረ ሲሆን ከሱዳን ወደብ እስከ ምዕራብ አፍሪካ ከተዘረጋው የንግድ መስመር በተጨማሪ በአረቢያ ምድር ከደቡብ የመን (ከኤደን የባህር ወደብ) ተነስተው ሽቅብ ወደ ሰሜን አቅጣጫ የመካና የመዲና ከተሞችን አቋርጠው እስከ ግብፅና ፍልስጤም፣ ሶሪያ፣ እስራኤል እና አካባቢው (Levant) ድረስ፣ በሌላ አቅጣጫ በኩል ደግሞ በአፍሪካ ቀንድ ቀይ ባህርን እና የህንድ ውቅያኖስን በመርከብ አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ፣ ሶማሌ፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ (ዛንዚባር) እና ሞዛምቢክ ድረስ በመመላለስ ቅመማ ቅመም፣ የተለያዩ የዕጣን ዓይነቶች፣ የእንስሣት ቆዳ፣ ባሪያ እና የመሳሰሉትን ይነግዱ ነበር። አረቦች እና ኦቶማን ቱርኮች ከአውሮፓውያን ያልተናነሰ በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አፍሪካውያንን በባርነት አግዘዋል። በሃገራችን ደግሞ በግራኝ አህመድ ወረራ ወቅት ብቻ ቢያንስ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በአረብ የባሪያ ነጋዴዎች እየታፈኑ የመንን ጨምሮ በመላው የአረብ ምድር እስከ አጎራባች የህንድ ግዛቶች ድረስ በባርነት ተሽጠዋል። ለምሳሌ ከነዚህም ውስጥ በእስልምና ታሪክ የመጀመርያው ሙአዚን የሆነው የቢላል ቤተሰቦች እና የንጉስ ልብነ ድንግል ልጅ ልዑል ሚናስ ይገኙበታል። በተምዘግዛጊና በሚያምር ድምጹ የሙስሊሙን ህዝብ ለጽሎትና ለስግደት የሚጣራው ቢላል በነብዩ መሐመድ ተመርጦ ለመጀመሪያ ጊዜ በመካ መዲና አላሁ ክብር ያለ ሲሆን ቤተሰቦቹ በባርነት የመን ተሽጠው እዛው የተወለደና በኋላ ላይ ወደ መካ ከተማ ከጌቶቹ ጋር ሄዶ ይኖር የነበረ ነው። ልዑል ሚናስ ደግሞ በግራኝ አህመድ በጦርነት ላይ ተማርከው የነበሩና በኋላም የግራኝ አህመድ ልጅ በንጉሱ ወታደሮች ስለተማረከ በእስረኛ ልውውጥ ወደ ሀገራቸው የተመለሱና የነገሱ የዓፄ ገላውዲዎስ ታናሽ ወንድም ናቸው፡፡ ይኸም ታሪክ በተክለጻዲቅ መኩሪያ መጽሃፍ ውስጥ ተጠቅሷል። 

ከጥንት ጊዜ ጀምሮ አረቦች ወደ ኢትዮጵያ በንግድ እየተመላለሱ አንዳንዶቹም ደግሞ እየተሰደዱ በመምጣት በኢትዮጵያ ውስጥ ይሰፍሩ ነበር። በተለይ ግራኝ አህመድን ተከትለው በተዋጊነት የመጡ አረቦች በሃገራችን የባሪያን ንግድ አስፋፍተዋል። ለምሳሌ የደቡብ ኢትዮጵያ ማህበረሰቦች መኖሪያ መንደሮችን እየከበቡ ከሚያጠቡ እናቶች እና በእድሜ ከገፉት ሽማግሌና አሮጊቶች በስተቀር ህዝቡን እያፈኑ ወደ የመን (አረቢያ ምድር) በባርነት እያሻገሩ ሲሸጡ የኖሩት የጅማው አባ ጂፋርና በስራቸው የነበሩ ባላባቶች ይጠቀሳሉ። አባ ጅፋር ኦሮሞ ይሁኑ እንጂ በአንድ ወገን የአረብ (የየመን) ዝርያ አላቸው። እንደ አባ ጅፋር ያሉ በርካታ የአረብ ዝርያ ያላቸው በጅማ፣ በአርሲ፣ በባሌ፣ በሐረርጊና በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ የባሪያ ነጋዴዎች ነበሩ። ከግራኝ ጦርነት በኋላ በአጼ ገላውዶዎስ የተጀመረው የባሪያ ንግድን ከሃገራችን በአዋጅ የማስወገድ እርምጃ በአጼ ምኒሊክ ተጠናክሮ በመቀጠል በመጨረሻ በቀ/ኃ/ስላሴ ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያ ምድር እንዲወገድ ተደረገ። ይሁን እንጂ ሰውን እንደ ከብት በባርነት በመሸጥ በሰው ልጅ ስቃይና መከራ ሃብት ሲያካብቱ የኖሩ ከአረብ የሚወለዱ የባሪያ ነጋዴዎችና ከነሱ ጋር ሽርክና የነበራቸው የጥቅም ተጋሪዎቻቸው ባርነትን በአዋጅ በከለከሉት በአጼዎቹ ላይ ቂም በመያዝ በተለያየ ስም አመፅና ብጥብጥ ሲያደርጉ ኖረዋል። ምንም ዓይነት ስምና ሽፋን ይሰጠው በኢትዮጵያ ያለው አብዛኛው ችግር መነሻው ከውጭ በተለይ ከአረብ ወይም ከአውሮፓ የመጣ ነው። በኢትዮጵያ ታሪክ በርካታ ክርስቲያኖች ሙስሊም ሆነዋል፣ በተቃራኒውም በርካታ ሙስሊሞች ክርስቲያን ሆነዋል። የኢትዮጵያ የሙስሊሙና የክርስቲያኑ ማህበረሰብ ሃይማኖቱ በሰውነቱ ላይ እንደሚደርበው ልብስ/ ጨርቅ ከላይ የተቀመጠ እንጂ በስጋና በደሙ አንድ የሆነ ህዝብ ነው። ኢትዮጵያዊነት ረቂቅ ነው የሚባለው ከእምነትም ሆነ ከብሄር በላይ ህዝቡ የተዛመደና የተጋመደ በመሆኑ ነው። በሃገራችን ከተፈጸመ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ከተፈጸመ ያለፈ ታሪካችን ውስጥ አንዱ የግራኝ የወረራ ጦርነት ነው። ግራኝ አህመድን ተነስ ዝመት ህልም (ራዕይ) አየንልህ የክርስቲያኑን መንግስትህን ውጋ ብለው ገፋፍተው ያዘመቱት ከየመን ሃገር ተሰደው ሃረር ከተማ በመምጣት ይኖሩ የነበሩ የአረብ ሼኮች ናቸው። ከዚሁ ጎን ለጎን ወደ ኢትዮጵያ ይመላለሱ የነበሩ የአረብ ነጋዴዎች ከየመን እስከ ግብጽ ድረስ ለንግድ በሚሄዱበት ቦታዎች ኢትዮጵያ ውስጥ የሚዘረፍ ወርቅ አለ በማለት ወንበዴዎችን ኢትዮጵያን ላይ በመቀስቀስ ያዘምቱ ነበር። 


በአዳል ሱልጣኔት ዘመን ሃረር የንግድ፣ የእምነት እና የፓለቲካ ማዕከል ነበረች። የአረብ ነጋዴዎች እና ቱርኮች አሁን በሰሜን ሶማሌ በምትገኘው በዘይላ የባህር ወደብ በኩል ቀይ ባህርን ተሻግረው ወደ ሃረር ይመላለሱ የነበሩ ሲሆን በወቅቱ የኦቶማን ቱርክ ዓላማ በፈረሰው የሮማን ኢምፓየር አምሳያ የአረብን ምድር፣ አውሮፓን እና የቀይ ባህር አካባቢን በበላይነት በመግዛት የኦቶማን ኢምፓየር መንግስት ለመመስረት ነበር። የቱርክ የጦር መኮንኖች አረቦችን እና የነሱ ተባባሪ የሆኑ የአካባቢውን ገዢዎች በመጠቀም መጀመሪያ ሃረርን ቀጥሎም መላ ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር ይንቀሳቀሱ ጀመር። በወቅቱ ቱርኮች በዓለም ላይ እጅግ ሰፊ ግዛት የነበራቸው ሃያል መንግስት ስለነበሩ ለውትድርና የሚያስፈልጋቸውን ሰዎችን በባርነት እየፈነገሉ አረቦችን እና የነሱ ተባባሪዎች ያቀርቡላቸው ነበር። ለምሳሌ በ15ኛው ክ/ዘ የዘይላ (አዳል) አስተዳዳሪ የነበረው አሚር ማህፉዝ ለአዳል ጎራባች ወደ ነበረው “ዳዋሮ” ተብሎ በወቅቱ ይጠራ ወደነበረው አውራጃ (ምስራቅ ሐረርጌ) ዘልቆ በመግባት ወረራ በመፈጸም ወንዶችን ወደ ዘይላ እና ኤደን የባህር ወደቦች በማሻገር ለቱርክ የጦር አዛዦች በባርነት ይሸጣቸው ነበር። አሚር ማህፉዝ ከሞተ በኋላ ባቲ ድል ወምበራ የተባለች ሴት ልጁን ያገባው በተለምዶ ግራኝ አህመድ (ኢማም  አህመድ ኢብን ኢብራሂም አልጋዚ) ሲሆን እሱም እንደ አማቹ ተዋጊ ሰራዊት አደራጅቶ የንጉሱ ግዛት የነበረውን ዳዋሮን በመውረር እንደ ማህፉዝ በደዋሮ ይገኝ የነበረ ቤተክርስቲያን አቃጥሎ፣ ህዝቡን ዘርፎ ተመለሰ። The conquest of Abyssinia p 20. ከዳዋሮም እንደተመለሰ በትውልድ ሃገሩ በሆባት፣ በሃረርና በየአካባቢው እየተዟዟረ የአካባቢውን የጎሳ መሪዎችን እና ነዋሪ ህዝቡን በመሰብሰብ የዘረፈውን እያሳየ እነሱም እሱን ተከትለው ቢዘምቱ ሊበለፅጉ እንደሚችሉ ያማልላቸው ነበር። በርካታ የግራኝ ተዋጊዎች በዘረፋ ለመበልፀግ ወደ ጦርነቱ እንደሚገቡ የራሱ የግራኝ ታሪክ ፀሃፊ የሆነው አረብ ፋቂህ በመጽሃፉ ላይ በግልጽ አስፍሯል። ለምሳሌ በአንድ ወቅት “የክርስቲያኖችን ፈረስ፣ በቅሎ፣ በሬ፣ አህያ፣ ባሪያ፣ የሃር ጨርቅ የሚበቃንን ያህል በዘረፋ አግኝተናል ካሁን በኋላ ጦርነት አንፈልግም ወደ ሃገራችን ያገኘነውን ይዘን እንመለስ” የሚል ጥያቄ የግራኝ ተዋጊዎች አቅርበው ነበር። The conquest of Abyssinia: page 154 and 155. ግራኝ አህመድ የንጉሱን ሰራዊት ሽምብራ ኩሬ ላይ ካሸነፈ በኋላ የአረብና የቱርክ ወታደሮችን በማስከተል በየከተማና በየመንደሩ፣ በየገዳሙና ቤተክርስቲያኑ እየዞረ የሃገሪቱን ሃብትና ታሪካዊ ቅርስ መዝብሮ ሲያበቃ የቀረውን ያለርህራሄ በእሳት ያቃጥል ነበር። አረብ ፈቂ በመፅሃፍ ላይ ይህንን ውድመት ሲያረጋግጥ የግራኝ አህመድ ተዋጊዎች ባለፉባቸው ቦታዎች ሁሉ የሚያገኙትን “የክርስቲያን መኖርያ መንደሮች ሳያወድሙ አያልፉም ነበር” ይላል። The Conquest of Abyssinia P. 60 በዚህ ወቅት እምነታችንን አንቀይርም ያሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን በተለይ በአረቢያ ለጅዳ ከተማ ቅርብ በሆነች Zahid (ዛሂድ) በምትባል ቦታ እንዲሁም ህንድ ውስጠ Gujarat (ጉጅራት) ወደሚባል ግዛት ድረስ እያሻገሩ ህዝቡን ሸጠዋል። “The Conquest of Abyssinia” P. xvii, xix and P. 26። በአሁኑ ጊዜ በአረብ ሃገር የሚገኙ ጠይም (ጥቁር) “የሃገሩ ዜጎች” በአብዛኛው ኢትዮጵያን ጨምሮ ምስራቅ አፍሪካ በአረብ የባሪያ ንግድ ወቅት (Arab Slave Trade) ተሽጠው እዚያው ተዋለዱ ናቸው። አረቦች የሃገራችንን ሃብት ከመዝረፍ እና ስልጣኔዋን ከማውደማቸውና ህዝባችንን በባርነት ከመሸጣቸው በተጨማሪ በኢትዮጵያ ብቻ ይበቅሉ የነበሩ የቡና እና የጫት ችግኞችን ወደ ሃገራቸው በመውሰድ ከኢትዮጵያ ጋር ተቀራራቢ የአየር ጸባይ ባለው በደቡባዊ የመን ተራራማ አካባቢዎች በመትከል አራቡት። ይህን ከኢትዮጵያ ወስደው የተከሉትን ነው አረቢያ ቡና እያሉ የሚጠሩት። 

ባጠቃላይ በግራኝ አህመድ የሽብር ወረራ በሃገር እና በህዝብ ላይ የደረሰ ውድመትና ኪሳራን በተመለከተ ፕሮፌሰር ሀብታሙ መንግስቴ “በራራ -ቀዳሚት አዲስ አበባ (1400 – 1887) እድገት ውድመት እና ዳግም ልደት” በሚለው መጽሃፋቸው ገጽ 190 ላይ እንዲህ በማለት ይገልጹታል፡ “እንደ ሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ሁሉ በራራም በግራኝ አህመድ ወታደሮች ተዘርፋ ተቃጠለች። . . . የግራኝ አህመድ ወረራ ኢትዮጵያንና የአፍሪካ ቀንድን ከስልጣኔ ማማ አውርዶ ወደ ድንጋይ ዘመን የእድገተ ደረጃ መለሳቸው”። በመቀጠልም የፓርቹጋል እርዳታ እንደደረሰ አፄ ገላውዲዎስ ከፓርቹጋል ወታደሮች ጋር ቅንጅት በመፍጠር የግራኝ፣ የቱርክና የአረብ የጀሃድ ተዋጊዎች ጋር ፍልሚያ በማድረግ በመጨረሻ ግራኝ አህመድ በጣና ሃይቅ አካባቢ ደምቢያ ከተባለ ሥፍራ 1535 ዓ.ም ተገደለ። አብረውት የነበሩት በርካታ የአረብ እና የቱርክ ወታደሮች ተገደሉ። የኦቶማን ቱርክ ኢትዮጵያን በቅኝ ለመግዛት የነበረው እቅድ ከግራኝ ሞትና ከተዋጊዎቹ ሽንፈት ጋር አብሮ ተቀበረ። (በርግጥ የኦቶማን ቱርክ በዘይላ በኩል ብቻ ሳይሆን ከዛም ቀደም ብሎ በ13ኛውና 14ኛው ክ/ዘ በምጽዋ በኩል በተደጋጋሚ ወረራ የፈጸመ ሲሆን በወቅቱ የነበሩ እንደ አምደጽዮን እና ሰርጸ ድንግል ዓይነት ንጉሶች ሲመክቱት ኖረዋል)። ግራኝ እንደተገደለ ከሞት የተረፉ ጭፍሮቹ፣ ሚስቱ ድል ወንበራ ከአጃቢዎቿ ጋር ወደ ሃረር ከተማ ሸሹ። የአረብና የቱርክ ወታደሮች፣ የታሪክ ፀሃፊው የነበረው የመናዊው አረብ ፈቂህ በሶማሌ በዘይላ ወደብ በኩል አድርገው በመርከብ ወደ ኤደን (የመን) ሲሻገሩ፣ የቀሩት ደግሞ ቀድሞ በየአካባቢው ግራኝ አዋቅሮት በነበረው እስላማዊ አስተዳደር ወዳላቸው አካባቢዎች በመሸሽ በአሩሲ፣ በባሊና በሐረርጌ አካባቢዎች በህዝቡ ውስጥ ተሰገሰጉ። በቀጣይም ኢትዮጵያ ውስጥ የባሪያ ንግድ በማስፋፋት ወደ የመን እና የቀረው የአረብ ሃገራት አሻግረው በመሸጥ መደበኛ መተዳደሪያ ስራቸው አደረጉት።

በርካታ ክርስቲያን ኢትዮጵያውያን በግራኝ አህመድና በተዋጊዎቹ በሰይፍ ላለመቀላትና በባርነት ላለመሸጥ ሲሉ እምነታቸውን ቀየሩ። ከግራኝ መሸነፍ በኋላ ከፊሎቹ ወደ ክርስትና ሲመለሱ ቀሪዎቹ ደግሞ ለምደውና ፈቅደው በእስልምና እምነት ጸኑ። ከዚህ በመቀጠል በተለይ በባሊ፣ በዳዋሮ፣ በፈጠጋር እና በመሳሰሉ በጥንታዊ የኢትዮጵያ አውራጃዎች ይኖሩ የነበሩ ማህበረሰቦች በጥንታዊ የኦሮሞ አርብቶ አደር ጎሳዎች በሞጋሳና በጉድፈቻ በሚባሉ ባህሎች አብዛኛዎቹ በመወረማቸው ከብሔር፣ ከእምነት፣ ከባህል እና ከመሳሰለው አንጻር ህዝቡ ስለተቀየጠ ስብጥሩ ይበልጥ ተወሳሰበ። ከዚህም በተጨማሪ በመሬት ጥበት፣ በድርቅ፣ በጦርነት፣ በእምነት ልዩነት እና በመሳሰለው ምክንያት የኢትዮጵያ ህዝብ በተለያዩ ዘመናት ከአንዱ የሃገራችን ክፍል ወደሌላው ፈልሷል፣ ተሰዷል፣ ተቀላቅሏል። በመሆኑም የኢትዮጵያ ህዝብ ከላይ የሸፈነውን የብሔር እና የሃይማኖት ካባ ገላልጠን እውነተኛ ማንነቱን ብንመለከተው የኢትዩጵያ ህዝብ በደምና በአጥንት የተዛመደና የተጋመደ ወንድማማች ህዝብ ሆኖ እናገኘዋለን። 

4. የህዝብ መስፋፋት እና መፍለስ (ባጭሩ)፣ 

በጥንት ግዜ በአደንና በተፈጥሮ የበቀሉ ዕፅዋትን በመሰብሰብ ይኖሩ ከነበሩ ሰዎች ጀምሮ እስካለንበት የኢንዱስትሪና የኢንፎርሜሽን ዘመን ድረስ ሰዎች በጦርነት ሽሽት፣ በተፈጥሮ አደጋ፣ በኢኮኖሚ ችግር፣ በእምነት ልዩነት፣ በተፈጥሮ መራቆት፣ በዝናብ እጥረት እና በተለያዩ ምክንያቶች ከአንድ አካባቢ ተነስተው ወደ ሌላ አካባቢ ሲሰደዱ፣ ሲስፋፉና ሲሰራጩ ኖረዋል። አባታችን አዳም ከገነት ተሰዷል፣ አብርሃም ከደቡባዊ ሜሶፖታሚያ ኡር ከምትባል ከተማ ተነስቶ ብዙ ሺህ ኪሎ ሜትር ተጉዞ እስከ ከንአን ምድር ተሰዷል። የጀርመን ወይም የቫይኪንግ ህዝቦች ወደ ሮማን ኢምፓየር ወረራና ፍልሰት ፈጽመዋል። ከምስራቅ ኤስያ እስከ መሃል አውሮፓ ድረስ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ ከብት በማርባት ይኖሩ የነበሩ የሞንጎሊያ ፈረሰኞች እና የሃን ጎሳዎች ወረራና የህዝብ ፍልሰትን እንዲሁም ለእንግሊዝ እንደ ሃገር መፈጠር እርሾ የሆኑትን አንግሎ፣ ሳክሶን እና ጁትስ (Anglo, Saxon and Jutes) የሚባሉ ከጀርመን የፈለሱ ነገዶችን መጥቀስ ይቻላል። ወደ አፍሪካ ስንመጣ ደግሞ በናይጄሪያ እና በካሜሩን ድንበር አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ባንቱ (Bantu) የሚባሉ ህዝቦች ከምዕራብ አፍሪካ ተነስተው ወደ ምሥራቅ፣ መካከለኛው እና ደቡብ አፍሪካ ድረስ በመፍለስ ቀደምት የአካባቢውን ነዋሪ ህዝቦችን ባህል ቋንቋ እና ማንነታቸውን በመዋጥ አሁን በኮንጎ፣ በኬንያ፣ በሞዛንቢክ፣ በደቡብ አፍሪካ እና በአካባቢው ለሚገኙ በመቶ ሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ የባንቱ ቋንቋ ተናጋሪ ህዝቦች መፈጠር ምክንያት ናቸው። 

በኢትዮጵያ ውስጥም በተለያዩ ምክንያቶች የህዝቦች መስፋፋፍ እና ፍልሰት ተከስቷል። በመሆኑም እኛ ኢትዮጵያውያን ዛሬ ያለን ማንነት በአንድ ሌሊት የተገነባ ሳይሆን ለዘመናት ህዝቦች እርስ በርስ ባደረጉት መስተጋብር፣ በደስታውም በሃዘኑም የተገኘ ነው። ለምሳሌ ዮዲት ጉዲት በአክሱም ላይ አመጽ በማስነሳት መንግስቱን በማፍረሷ የንጉሳኑን ቤተሰብ ጨምሮ በርካታ ህዝብ ወደ መሃል ኢትዮጵያ ተሰዷል፣ ግራኝ አህመድ ያለማቋረጥ ለ14 ዓመት ባካሄደው የሽብር ጦርነት ህዝቦች ከአንድ የኢትዮጵያ አካባቢ ወደ ሌላው አካባቢ እንዲሰደዱና በርካቶች እምነታቸውን እንዲቀይሩ አድርጓል። ይህንን ተከትሎ ጥንታዊ የኦሮሞ ከብት አርቢ ጎሳዎች ህዝቡን በጉዲፈቻና በሞጋሳ ባህል ማወረማቸውን ስናይ የኢትዮጵያ ህዝብ ሰፌድ ላይ እንደሚንቀረቀብ እህል አንዴ በሃይማኖት ሌላ ጊዜ በሚናገረው ቋንቋና ባህል ከወዲህ ወዲያ የማንነት መገለጫዎቹ ሲቀይር፣ ሲታመስና ሲደበላለቅ የኖረ መሆኑን እንረዳለን። ስለዚህ ጥንታዊ የኦሮሞ ከብት አርቢ ማህበረሰቦች የፈጸሙት መስፋፋትና መፍለስ ከዚህ አንጻር ሊታይ የሚገባው መሆኑን በመረዳት የሃሰት ትርክቶችን ከመለጣጠፍ በታሪክ የተፈጸሙ እውነታዎችን በመቀበል እንደ ሰለጠነ ሰው ወደፊት በጋራ መራመድ መቻል አለብን።     

5. የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ወረራ፣ 

እንደሚታወቀው የቫይኪንግ ህዝቦች የንግድ መስመር ፍለጋን ጨምሮ ለስደትና ለዘረፋ (Piracy) በባህር ላይ ጉዞ ያደርጉ የነበረ ሲሆን ከዛም በመቀጠል በመካከለኛው ዘመን ከምዕራብ አውሮፓ የተነሱ የባህር አሳሾች አዲስ የንግድ መስመር እና የዓለማችን ክፍሎችን ፍለጋ (Exploration) ያደርጉ ነበር። የአውሮፓ መንግስታት አሳሾችን በማሰማራት የባህር አሰሳ ያደረጉበት ዋናው ምክንያት ሃብት ፍለጋ ሲሆን ከዚሁ ጋር በተያያዘ ግዛት በማስፋፋት የፖለቲካና የወታደራዊ የበላይነት ለማግኘት፣ በአውሮፓ የተከሰተው የህዝብ ቁጥር ለማስተንፈስ ህዝቡን ወደ ሌላ አካባቢ ለማስፈር፣ እምነትን ለማስፋፋትና ንጉሶቻቸው በነበራቸው የግል ዝና (Glory) ፍለጋም ጭምር ነበር። በመሆኑም አሜሪካ በአሳሾች እንደተገኘች የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች የአፍሪካን ህዝብ በባርነት ወደ አሜሪካና በቅርብ ወደሚገኙ የካሬቢያን ደሴቶች በመርከብ እንደ ሰው ሳይሆን እንደ ከብት አጉረው በማጋዝ በነፃ ጉልበት ቱባኮ፣ የስኳርና የጥጥ ምርቶች እንዲሁም እንደ ወርቅና አልማዝ የመሳሰሉ የከበሩ መዐድናትን አስቆፍረው በማውጣት በአውሮፓ ገበያ በመሸጥ ከፍተኛ ሃብት (Capital) ሰበሰቡ። ይህ አፍሪካን አሜሪካን እና አውሮፓን ያስተሳሰረ የሶስትዮሽ የባሪያ፣ የጥሬ ዕቃና የሸቀጥ ንግድ Triangular slave trade በመባል ይታወቃል። በዚህ ሁኔታ በተገኘ ሃብት በእንግሊዝ እና በበርካታ የአውሮፓ ሃገራት ኢንዱስትሪዎችን ገነቡ፣ ከተሞችን አስፋፉ። ስራቸውንም ለማቀላጠፍ የሚያግዙ ባንኮችን (Banking system/ financial institutes) አቋቋሙ። በመቀጠልም በካሪቢያን (west Indies) ይኖሩ የነበሩ የአውሮፓ ከበርቴዎች ግማሾቹ እዛው ሰሜን አሜሪካ ሲጠናከሩ በጃማይካና በአካባቢው በሚገኙ ደሴቶች የነበሩት ደግሞ በባርነት ያስተዳድሯቸው ከነበሩ አፍሪካውያን ውስጥ የተወሰኑትን አስከትለው ወደ እንግሊዝ (አውሮፓ) በመመለስ ትላልቅ የቤተሰብ እርሻዎችን እና የኢንዱስትሪ ከተሞችን አስፋፉ። 

እነዚህ በአፍሪካውያን ጉልበት ከፍተኛ የገንዘብ (የካፒታል) አቅም የገነቡ የኢንዱስትሪ ባለቤቶች እና ዓለም አቀፍ ነጋዴዎች በአውሮፓ ሃገራት የመንግስት ስልጣንን በመቆጣጠር የሃገራቸውን ፖለቲካ ይዘውሩ ጀመር። በመቀጠልም ለኢንስትሪያቸው ጥሬ ዕቃ በነጻ ወይም በረካሽ ዋጋ ለማግኘት እንዲሁም ምርታቸውን አፍሪካ ላይ ለማራገፍ (ለመሸጥ) ያስችላቸው ዘንድ የአውሮፓ መንግስታት በጀርመኑ ቻንስለር በኦቶቫን ቢስማርክ ጋባዥነት በ1884 በርሊን ከተማ ላይ አፍሪካን ሙሉ ለሙሉ በቅኝ ግዛት ለመቀራመት ተስማሙ። በወቅቱ ስምንት የሚሆኑ የአውሮፓ መንግስታት አፍሪካን በቅኝ ግዛት ለመቀራመት ጉባኤ ተቀምጠው በነበረ ጊዜ የአፍሪካን ካርታ ጠረጴዛ ላይ ዘርግተው ይህ ለኔ ያ ደግሞ ላንተ እያሉ እንደ ቅርጫ ስጋ ሃገሩን እና ህዝቡን በማናህሎኝነት ተከፋፈሉት። ዓላማቸውም ሃብት (capital) በመሰብሰብ በቁስ ለመበልጸግ ነው። የአውሮፓ ስልጣኔ በገንዘብ፣ በሃብትና በቁስ የሚለካ እንጂ ሰብአዊነ የሌለው ለመሆኑ በአፍሪካ ህዝብ ላይ ያደረሱት ግፍ፣ መከራ፣ ስቃይና ውድመት ምስክር ነው። 

በመሆኑም አውሮፓውያን የአፍሪካን ህዝብ በባርነት በማጋዝና በነፃ ጉልበቱን ከመበዝበዝ በተጨማሪ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ላይ ኢሰብአዊ ድርጊት እና ወንጀል ፈጽመዋል፣ ጥንታዊ አፍሪካዊ መንግስታትን፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ እሴቶችን አፈራርሰዋል። ህዝቡን በከፋፍለህ ግዛ ፓሊሲያቸው እርስ በርሱ አባልተዋል። አንድ ቋንቋ ተናጋሪ ማህበረሰብና ቤተሰብን ከአንድ በላይ በሆኑ ሃገራት እንዲከፋፈሉ በዘፈቀደ ድንበር አስምረዋል፣ ቀድሞ በአፍሪካ የማይታወቁ የአውሮፓ በሽታዎች (ደዌዎች) አውቀውም ሆነ በንዝህላልነት አስፋፍተዋል። (ለምሳሌ ጣሊያን በግብርና ላይ የተመሰረተውን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሽመድመድ ከአድዋ ጦርነት በፊት የከብቶች በሽታ ከህንድ ሃገር በማምጣት በኢትዮጵያ አዛምቷል)። አፍሪካውያንን በባርነት ወደ አሜሪካ በሚያጓጉዝበት ወቅት በርካታ ልጃገረዶች በነጮች እየተደፈሩ የጌቶቻችውን ልጆች በሆዳቸው ይዘው ነው ከመርከብ የወረዱት። በቤት ውስጥ በሚያገለግሉ ሴት አፍሪካ እህቶቻችን ላይ በተመሳሳይ ሁኔታ በየጓዳው አስገድዶ መድፈር ተፈጽሞባቸዋል። ቅኝ ገዢዎች በግፍ የወረሩትን የአፍሪካ ህዝብ ከሰውነት በታች በማድረግ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳት በማድረስ አንገቱን ደፍቶ ዘለዓለም የእነሱ ተገዥ ሆኖ እንዲኖር የቻሉትን ሁሉ አድርገዋል። የተፈጥሮ የቆዳ ጥቁረትን ከእርግማንና ከሃጢያት ጋር በማያያዝ በአፍሪካ ህዝብ ስነ ልቦና ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል። ሲያሻቸው ደግሞ በዘረኛ ሳይንቲስቶቻቸው የአፍሪካ ህዝብ የአዝጋሚ ለውጥ ሂደትን ያላጠናቀቀ በሰውና በእንስሳት መሃል የሚገኝ ነው በማለት አፍሪካውያንን ከሌሎች እንሣት ጎን በማቆም በሙዚየም (Human Zoo) እንዲጎበኝ እስከማድረግ ደርሰዋል። ለምሳሌ በቤልጂየም እና በሰሜን አሜሪካ የነበሩ The Human zoo of Tervuren, Belgium (1897/1958) እና The Human zoo of St. Louis Missouri USA (1904) መጥቀስ ይቻላል። የኢትዮጵያ ነገስታት ግን በኢትዮጵያና በህዝቧ ላይ ይህ ሁሉ እንዳይሆን በየዘመኑ በአረቦች፣ በግብጾች፣ በቱርኮች እና በአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች የሚቃጣውን ተደጋጋሚ ወረራ ህዝባቸውን እያስተባበሩ፣ እነሱም በግንባር በየጦሩነቱ ላይ እየተሰለፉ የህይወትና የአካል መስዋዕትነት በመክፈል የህዝባቸውን እና የሃገራቸውን ነጻነት፣ ባህል፣ ቋንቋ እና ኢትዮጵያዊ ብዝሃነትን አስጠብቀው መዝለቅ ችለዋል። ነጻነታችንን እና ማንነታችንን በከፈሉት የደም ዋጋ ጠብቀው ላቆዩልን አባቶቻችን ክብርና ምስጋና ይሁን!

6. በሰሜን አሜሪካ የተደረጉ ጸረ ቅኝ ግዛት ትግሎችና የአሜሪካ አፈጣጠር፣ 

እንደሚታወቀው በ16ተኛው እና በ17ኛው ክ/ዘ የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይ፣ የስፓኝ፣ የፖርቹጋልና የመሳሰያሉትን መንግስታት ወደ ሰሜን እና ደቡብ አሜሪካ በመምጣት ቅኝ ግዛቶችን (Colonies) ፈጠሩ። በሰሜን አሜሪካ ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ለመላቀቅ የተደረጉ ትግሎችን እና የፓን አፍሪካ የነፃነት እንቅስቃሴን ለግንዛቤ ያህል በትንሹ ለማነጻጽር እንሞክር። አፍሪካ ከአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ነፃ የወጣችው የአድዋውን የጀግኖች አባቶቻችንን ድል አርአያ በማድረግ የፓን አፍሪካ እንቅስቃሴ ጠንሳሽ አባቶች በሆኑት በእነ ቀ/ኃ/ስላሴ፣ ዶ/ር ክዋሜ ንክሩማ፣ ጆሞ ኬኔያታና የመሳሰሉት አባቶች ባቀጣጠሉት የነጻነት ትግል ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በሰሜን አሜሪካ የተደረጉ የነፃነት ትግሎችን ስንመለከት ለትግሉ መነሻ የሆነው ከታክስ ጭማሪ ጋር በተያያዘ እንጂ ቀጥተኛ የነጻነት፣ የሰባዊ መብት ወይም የዲሞክራሲ ጥያቄ አልነበረም። የብሪትሽ መንግስት በዓለም ላይ በተለይም በሰሜን አሜሪካ ከፈረንሳይ ቅኝ ገዢ ጋር እና ከአካባቢው ነባር የቀይ ህንድ ማህበረሰቦች ጋር ለሚያደርገው ጦርነት ወጪ መሸፈኛ ገንዘብ በመፈለጉ በአሜሪካ ግዛቶቹ በሚገኙ የሸቀጥ ንግዶች ላይ ከፍተኛ ቀረጥ ጨመረ። ነገር ግን የሰሜን አሜሪካ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛቶች (Colonies) የቀረጥ/ ታክስ ጭማሪውን በመቃወም ትግል ጀመሩ። በተለይም ቦስተን ቲ-ፓርቲ የሚባሉት በ1773 ከእንግሊዝ ወደ አሜሪካ የመጣን ሻይቅጠል ባህር ውስጥ በመጨመር ከእንግሊዝ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጫና በመላቀቅ የራሳቸውን አስተዳደር (መንግስት) ለመመስረት “No Taxation Without Representation” በሚል መሪ ቃል ትግሉን ማለትም የአሜሪካንን አብዮት (American Revolution) አቀጣጠሉት። የአሜሪካ ህዝብ ነጻነት ፈላጊ (Patriots) እና ለቀኝ ገዢዋ እንግሊዝ ታማኝ (Loyalists) በመባል ለሁለት ተከፍለው በ1775 ጦርነት ጀመሩ። 

በመጨረሻም በ1776 የአሜሪካ ነጻነት አርበኞች የሚባሉት Patriots ጦርነቱን አሸንፈው በነ ቶማስ ጃፈርሰን “Declaration of independence July4, 1776” ጽፈው በመፈራረም 13 የምስራቅ አሜሪካ የእንግሊዝ ግዛቶች ከእንግሊዝ አገዛዝ ነጻ በመውጣት በጋራ የተባበሩት የአሜሪካ መንግስታት (USA) የሚባል አዲስ ሃገር መመስረታቸውን አስታወቁ። ለቀኝ ገዢዋ እንግሊዝ ታማኝ ሆነው ከእንግሊዝ ጦር ጋር በመሆን ሲዋጉ የነበሩት Loyalists በርካቶቹ ወደ ካናዳ፣ ጥቂቶቹ ደግሞ ወደ ብራዚል ቤተሰባቸውን ይዘው በመፍለስ ሰፈሩ። የቀሩት ደግሞ ወደመጡበት እንግሊዝ (አውሮፓ) ተጓዙ። ምንም እንኳን አሜሪካ ከተመሰረተች ከዘጠና ዐመት በኋላ ዘግይቶም ቢሆን እነ አብርሃም ሊንከን በከፈሉት ዋጋ በ1865 በህገ መንግስታቸው ውስጥ በማካተት ባርነትን በአዋጅ ቢያስወግዱም የአሜሪካ ግዛቶች ከእንግሊዝ ነጻ በወጡና አሜሪካ እንደ ሃገር በተመሰረቱብርት ወቅት የሃገሩ ነባር ነዋሪዎች እና ከአፍሪካ በባርነት የተጋዘው ጥቁሩ ህዝብ ግን ገና ከነጭ የባርነት የአገዛዝ ሰንሰለት ነፃ አልወጡም ነበር። ለምሳሌ የነፃነት አርበኛ ተብለው የሚጠሩት የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ዋሽንግተን፣ ቶማስ ጃፈርሰን እና ፕሬዝዳንት ጀምስ ማዲሰን በመቶዎች የሚቆጠሩ ባሮች በቤታቸው ውስጥ ነበሯቸው። በነገራችን ላይ ከነ አብርሃም ሊንከን ቀድመው ኢትዮጵያዊው ንጉስ ገላውዲዎስ ነበሩ 1548 ባርነትን በአዋጅ ከሶስት መቶ አመት በፊት አስቀድመው ያገዱት። በመቀጠልም የአሜሪካ ጦርነት በተለያዩ አካባቢዎች በአነስተኛ መጠን እስከ 1783 ድረስ የቀጠለ ሲሆን በመጨረሻ የእንግሊዝ መንግስት ለአዲሱ የአሜሪካ መንግስት (USA) እውቅና በመስጠቱና ቶክስ ማቆሙን በ 1783 በፊርማው በማረጋገጥ የአሚሪካ የነጻነት ጦርነት በይፋ አበቃ።

ብዛታቸው 13 የምስራቅ አሜሪካ ግዛቶች ከእንግሊዝ አገዛዝ ነጻ በመውጣት በ July4, 1776 የተባበሩት የአሜሪካ መንግስታትን (USA) እንደ ሃገር ሲመሰርቱ በወቅቱ የአሜሪካ የቆዳ ስፋት አሁን ካላው ከሶስት እጥፍ በታች ያነሰ ነበር። አሜሪካ አሁን ያላትን መልክና ቅርጽም የያዘችው በተለይም ከምስራቅ ወደ ምዕራብ አቅጣጫና ወደ ቀረው የአሜሪካ ክፍልና በዙሪያው ወዳሉ ደሴቶች በመስፋፋት ነው። አሜሪካ ቅኝ አልገዛችም ይባል እንጂ የሰራችው ስራ ግን ከቅኝ ገዢ የሚተናነስ አይደለም። በዙሪያዋም እየተስፋፋችው ከፍተኛ ንዋይ (ገንዘብ) በማፍሰስ አጎራባች መሬቶችን ከቀድሞ ቅኝ ገዢዎች ህዝቡን ከመሬቱ ጭምር አንድ ላይ እንደ ሸቀጥ ዕቃ በመግዛት፣ ሲያመች ደግሞ የሃገሩን ነባር የጎሳ መሪዎችን እንደ “ውጫሌ” ዓይነት አወናባጅ ውል በማስፈረምና በማዘናጋት፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ በጦርነት በመጠቅለል እና በመሳሰሉት ነው። ለምሳሌ ሊዊዚያና (Louisiana) በ 1803 ከቀድሞ የአካባቢው ቅኝ ገዢ ከሆነችው ከፈረንሳይ በ 15 ሚሊዮን ዶላር እና አላስካን (Alaska) ከራሻ ንጉስ በ7.5 ሚሊዮን ዶላር፣ ፍሎሪዳን ከስፔን የተገዙ ሲሆኑ ሜክሲኮ (Mexico) ደግሞ በጦርነት እና የተለያዩ የአካባቢውን ነባር (Native) የጎሳ መሪዎችን በገንዘብና በውል አዘናግተው በመጠቅለል (Annexation) ነበር። በመሆኑም ታሪክ የሚነግረን ከ13ቱ የምስራቅ አሜሪካ ግዛቶች በስተቀር አብዛኛው የአሜሪካ ስቴቶች አሜሪካዊ የሆኑት ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነጻ ወጥተው ሳይሆን በግዢና በወረራ ጭምር ነው። ምንም እንኳን በኋላ ላይ እራሷን ችላ ነጻ ሃገር ብትሆንም በደቡባዊ ምስራቅ ኤስያ በፓስፊክ ውቅያኖስ የምትገኝ ፊሊፒንስ የምትባል ሃገርን (ደሴትን) አሜሪካ ከቀድሞ ቅኝ ገዢዋ ከነበረቸው ስፔን በ20 ሚሊዮን ዶላር ህዝቡን ከመሬቱ ጭምር አብራ መግዛቷ ይታወቃል። 

አሜሪካን “በቅኝ ግዛት በብስባሽ ላይ ተመችቶት በበቀለ የዱር ሃረግ” ትመሰላለች። በየጊዜው ያልተገረዘ የዱር ሃረግ በአቅራቢያው በሚያገኘው ነገር ላይ ሁሉ እየተጠመጠመ (እያነቀና እየተበተበ) ከአንዱ ወደሌላው እየተስፋፋ እንደሚሄድ፣ የአሜሪካም ጉዞ እንዲሁ ነው። ለምሳሌ ከመጀመሪያው የአሜሪካ አፈጣጠር ብንነሳ “founding fathers” የሚባሉት አሜሪካንን እንደ ሃገር በመሰረቱ ጊዜ ለእያንዳንዱ ስቴት (State) የሴኔት እና ሃውስ ኦፍ ሪፕረዘንታቲቭ (Senate & House of Representatives) የሚወክል የሰው ብዛት ለመወሰን ለድርድር ተቀመጡ። በውይይት (ድርድሩ) ላይ መጀመሪያ ያነሱት ጥያቄ ወደ አሜሪካ በባርነት የመጡ ጥቁር አፍሪካውያንን በተመለከተ ነበር። ኢኮኖሚያቸው በእርሻ ላይ የተመሰረተው የደቡቡ አሜሪክ ስቴቶች በርካታ ባሪያ (slave) ስለነበራቸው ጥቁር አፍሪካውያንን በማስቆጠር ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተመራጭ በ House of Representatives ለማግኘት አስበው ነበር፣ ነገር ግን ይህንን የተረዱት ኢንዱስትሪ የተስፋፋባቸው የሰሜን አሜሪካ ስቴቶች ደግሞ አንድ ጥቁር ሰው ከአንድ ነጭ ሰው እኩል መቆጠር የለበትም የሚል ቅሬታ አቀረቡ። በመጨረሻም አንድ ጥቁር ሰው (slave) እንደ አንድ ሙሉ ሰው ሳይሆን 3/5 ሰው (60%) ተደርጎ እንዲቆጠር በጋራ ተስማሙ። ይህ ማለት አንድ ጥቁር ሰው በ40% ከአንድ ነጭ ሰው ያንሳል እንደ ማለት ነው። በጊዜ ሂደት ሰሜኑ እና ደቡቡ የአሜሪካ ክፍሎች ከሚከተሉት የኢኮኖሚ ምንጭ አንጻር በሃብትና በቴክኖሎጂ ልዩነት እያሳዩ መጡ። ይህም ማለት ደቡቡ የሃገሪቷ ክፍል በባሪያ ጉልበት ላይ የተመሰረተ የግብርና ስርዓት ሲከተል፣ ሰሜኑ የአሜሪካ ስቴቶች ደግሞ ኢንዱስትሪ እያስፋፉ ሄዱ። የባሪያ መብትና ነጻነት በተመለከተ በኢንዱስትሪ የበለጸጉት የሰሜኑ የአሜሪካ ስቴቶች ባሪያ ነጻ (freeman) ይሁን ሲሉ (የአሜሪካ ዜጋ ይሁኑ አላሉም!) ደቡቡ ደግሞ ፈጽሞ ነጻ መሆን የለባቸውም የሚል ነበር። በዚህ ልዩነት ምክንያት እንደ ደቡብ ካሮሊያና፣ ቴክሳስ፣ ሊዊዚያና፣ አርካንሳስ እና የመሳሰሉት ስቴቶች ባርነት ከአሜሪካ መቅረት የለበትም ይህ ካልሆነ መብትና ጥቅማችን ተጥሷል በማለት ከህብረቱ (USA) በመውጣት (በመገንጠል) ጄፈርሰን ዴቪስን የሚባል ሰውን ፕሬዝዳንት በማድረግ የኮንፌዴሬት ስቴት (Confederate States of America) በማለት የራሳቸውን አዲስ ህብረት (“ሃገር”) መሰረቱ። ምንም እንኳን በሰሜኑም የነጭ የበላይነት (Segregation) ቢኖርም በአንጻራዊነት በደቡብ አሜሪካ ስቴቶች ካሳለፈው የከፋ የባርነት ህይወት የተሻለ ስለነበረ በርካታ ጥቁር ህዝብ ከገዢዎቹ እያመለጠ ወደ ሰሜኑ የአሜሪካ ስቴቶች መፍለስ ጀመረ። በዚህም የተነሳ ሰሜኖቹ ለኢንዱስትሪያቸው እና ለቤት ውስጥ በርካታ ሰራተኛ ማኝየት ጀመሩ። በመሆኑም በወቅቱ የባሪያ (Slavery) ጉዳይ በአሜሪካ አጨቃጫቂና ለርስ በርስ ጦርነት መከሰት ዋና ምክንያት መሆን ቻለ። ከባሪያ (Slave) ጉዳይ በተጨማሪ በስቴቶች መብትና በማዕከላዊው መንግስት መሃል የተፈጠረ የስልጣን ግጭት እና በሌሎች ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች አሜሪካኖች ኮንፌዴሬትስ እና ዩኑዬኒስት (confederates and unionists) ተብለው ለሁለት በመከፈል ከ1861 እስከ 1865 በተደረገው የአሜሪካ የርስ በርስ ጦርነት (Civil War) ከ6መቶ ሺህ በላይ ሰው ሞትና ቁስለኛ ሆነ። በደቡብ ካሮሊና በሚገኘው Charleston Harbor ላይ የኮንፌዴሬት ሃይሎች በከፈቱት ድንገተኛ (መብረቃዊ ጥቃት) በርካታ የአንድነት ሃይል ወታደሮች ተማረኩ፣ በዚህ ሁኔታ የርስ በርስ ጦርነቱ ተጀመረ። ከብዙ ደም መፋሰስ በኋላ የአንድነት ሃይሎች (unionists) ተብለው የሚጠሩት ሰሜኖቹ የደቡቡን የፌዴራሊስት ሃይሎችን በማሸነፍ የተከፋፈለች አሜሪካንን አንድ በማድረግ እንደ ሃገር ማስቀጠል ቻሉ። በመቀጠልም የአንድነት ሃይሎች በአሜሪካ ህገ መንግስት ላይ ማሻሻያ በማድረግ (13th amendment, 1865) ባርነት ከአሜሪካ ምድር በአዋጅ እንዲወገድ አደረጉ። 

በመቀጠልም 14th amendment, 1868 መሰረት አሜሪካ ውስጥ የተወለደ ማንኛውም ሰው የአሜሪካ ዜግነት አገኘ። ነገር ግን በህገ መንግስቱ ላይ የተለያየ ትርጉምና ትንታኔ በመስጠት በጥቁር ህዝብ ላይ ይደርስ የነበረው አድሎና ማግለል (Segregation) በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ቀጠለ። ምንም እንኳን በህገ መንግስታቸው በ 15th Amendment, 1870 ማንኛውም የአሜሪካ ዜጋ የመምረጥ መብት እንዳለው ቢደነግግም ስቴቶች የተለያየ አደናቃፊ ምክንያት በማቅረብ ጥቁር አሜሪካውያን እስከ 1965 ድረስ መምረጥ አይችሉም ነበር። በመሆኑም አሜሪካ እንደ ሃገር ከተመሰረተችበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ፍጹም ከህጸጽ የጸዳች፣ የቅዱሳን ማህበር አድርጎ የሚያይ ተላላ ሰው ካለ ታሪክን ወደኋላ ሄዶ መመርመር ይኖርበታል። አሜሪካ ከእንግሊዝ ነጻ ወጥታ እራሷን የቻለች ሃገር ሆነች በተባለበት ጊዜ አባቶቻቸው በሰፈራና በቅኝ ግዛት ወደ ሰሜን አሜሪካ የመጡ አውሮፓውያን የራሳቸውን የነጭ የበላይነት የነገሰበት መንግስታዊ አስተዳደር መሰረቱ እንጂ የሃገሩን ነባር ህዝብ እና ጥቁሩን ህዝብ ባለሃገር አላደረጉም። አሜሪካ “የነጭ ሃገር ብቻ” መሆኗ አብቅቶ የሁሉም መሆን የቻለችው 14th amendment, 1868 መሰረት አሜሪካ ውስጥ የተወለደ ማንኛውም ሰው ሁሉ የአሜሪካ ዜግነት ካገኘ በኋላ ነው። ይሁን እንጂ ጥቁር አሜሪካውያን የአሜሪካ ዜግነት ቢኖራቸውም እስከ 1965 ድረስ መምረጥ አይችሉም ነበር። ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ ምስጋና ይግባውና በእሱ መሪነት በተደረገ እልህ አስጨራሽ ትግልና ተቃውሞ በ1965 ጀምሮ ነው ጥቁር አማሪካውያንን በምርጫ መሳተፍ የጀመሩት። ይህ የሆነው ደግሞ አሜሪካ ከተመሰረተች ከአንድ መቶ ሰማንያ ዘጠኝ (189) ዓመት በኋላ ነው።

ባጠቃላይ የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም/ ካፒታሊዝም ሆነ በርካታ የምዕራቡ መንግስታት ከአመሰራረታቸው ጀምሮ እስካሁን የተጓዙበት መንገድ ከችግር የጸዱ ናቸው ማለት አይደለም። ምዕራባውያን ከፍትህ፣ ከዲሞክራሲ፣ ከሰብአዊነት እና ከእውነት ጋር በጽናት ሲቆሙ አልታዩም። ለምሳሌ ለሃገራችን የኢኮኖሚም ሆነ ፖለቲካ ጥቅም ያስገኝልናል ባሉ ጊዜ እንደ ቢላደን (አልቃይዳ) እና ታሊባን ዓይነት ላሉ አሸባሪዎች ድጋፍ ሰጥተዋል። በይፋ ዓላማዬ የ115 ሚሊዮን ህዝብ ሃገር የሆነቸውን ኢትዮጵያን ሲኦልም ወርጄም ቢሆን ማፈራረስ ነው፣ የአማራን ህዝብ ደምኛ ጠላቱ በማድረግ ሂሳብ አወራርዳለሁ በማለት በአደባባይ ተናግሮ አማራ ክልል በመግባት የጅምላ ንጹሃንን ጭፍጨፋ እየፈጸመና የወታደር ካምፖችን ሳይሆን የህዝብ መገልገያ የሆኑትን ት/ት ቤቶችን እና ሆስፒታሎች ከሚያወድም፣ ድልድይ ከሚያፈርስ፣ ሴቶችን በጅምላ የሚደፍር፣ በአለማቀፍ የጦር ወንጀል መጠየቅ ከሚገባው ጋር ህግ እና ሞራልን ጥሰው የአሜሪካ፣ የእንግሊዝ እና ሌሎችም የምዕራቡ መንግስታት እና እንደ CNN, BBC እና የመሳሰሉት ግዙፍ የቴሊቪዥን ማሰራጫዎቻቸው ሳይቀሩ ከአሸባሪው ወያኔ ጎን መሰለፋቸው የምዕራባውያኑን ማንነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። በሰላም ማስከበር ስም ሊብያ፣ ሶሪያ፣ ኢራቅና የመሳሰሉ ሃገራት ገብተው ያደረጉትን ውድመት ያየ ሰው ቃላቸውን ሰምቶ የሚያምናቸው ሰው ይኖራል የሚል እምነት የለኝም።

እንደሚታወቀው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጃፓን የአሜሪካ የጦር መርከቦች ማቆሚያ በነበረው ፒርል (Pearl Harbor) በሚባል በሃዋይ ደሴት በሚገኘው የባህር ሃይል ላይ የፈጸመችውን የአውሮፕላን ጥቃት ተከትሎ በአጸፋው አሜሪካ በጭካኔ በሄሮሺማና ናጋሳኪ በሚባሉ የጃፓን ከተሞች ላይ በጣለቸው የአቶሚክ ቦምብ ህጻንና ሽማግሌ ሳይል ከ175 ሺህ ህዝብ በላይ በጅምላ ንጹሃንን መጨረሱና በህይወት የተረፉትም ቢሆኑ ከደረሰባቸው የአካል እና የስነ ልቦና ጉዳት በተጨማሪ የአካል ጉዳተኛ የሆኑ ህፃናት መውለዳቸው ይታወቃል። እንዲሁም በቬትናም ጦርነት ወቅት የሃገሩ የነጻነት ተዋጊዎች የተደበቁበትን የዛፍና የቁጥቋጦ ቅጠል ለማርገፍ እና በእሳት ለማውደም አሜሪካኖች በአውሮፕላን ይረጩት የነበረው ኤጀንት ኦሬንግጅ (Agent Orange) የተባለ መርዛማ ኬሚካል በሚወልዱት ህፃናት ላይ የአካል ጉዳት አስከትሏል። በተጨማሪም የአሜሪካ አውሮፕላኖች በሚተኩሱት የናፓል (Napalm) ቦምብ በቬትናም ህዝብ ላይ የጅምላ ፍጅት መፈጸማቸው የምዕራቡ ዓለም መንግስታት ጥቅማችን ተነካ ባሉ ጊዜ ቆመንለታል የሚሉትን የፍትህና የሰብአዊነት መርህን ወደጎን ትተው ማንኛውንም ነገር ከማድረግ እንደማይመለሱ ያሳያል። ይህንን ሁሉ ግፍና ወንጀላቸውን የሚሸፍኑት በሆሊ ውድ ፊልም የተቀንርባበረ ፕሮፓጋንዳ እንደሆነ ይታወቃል። ለመሆኑ ድምጽን በድምጽ መሻር የሚባለው veto power ማን ሰጣቸው? ገደብ የለውም? የሰው ሃገር ወረው መንግስት ሲያፈርሱና በሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብን ስደተኛ ሲያደርጉ ወይም ሰላማዊ ህዝብ የሚኖርበት ከተማ ላይ አቶሚክና የኬሚካል ቦምብ ጥለው የሰው ዘርን በጅምላ ሲጨርሱ በዓለም አቀፍ ህግ እንዳይጠየቁ መከላከያቸው ነው? ይህን ሁሉ ግፍ የፈጸሙ ሰዎች/ መንግስታት ወደፊትስ እንዴት ሊታመኑ ይችላሉ? እኔ አልገባኝም፣ የገባችሁ አስረዱኝ። 

7.“ጣሊያን ቢገዛን መንገድና ድልድይ ይስራልን ነበር” (የባንዳ ጥቅስ)፣ 

በጥቁር ህዝብ ላይ አድሎ የሚፈጽመውና የማይገባ ነገር ሲናገር የሚሰማው ቆዳው የነጣ ፈረንጅ ብቻ ሳይሆን የአዕምሮ እጥበት (Brainwash) የደረሰበት ወይም በጥቅም የተገዛ እኛን የሚመስል ጥቁር ሰው ሊሆንም ይችላል። ለምሳሌ በምዕራቡ ዓለም ባለስልጣን ሆነው የምናያቸው ቆዳቸው እኛን የሚመስሉ ሃገራችንን እንደ ደመኛ ጠላታቸው ወጥረው የያዙ አባቶቻቸው ለቅኝ ገዢዎች በባንዳነት አድረው እነ “ኩንታ ኩንቴን” ጀርባቸው እስኪላጥ ሲገርፉ የነበሩ ነጭ አምላኪ የፈረንጅ ተላላኪ የባንዳ ልጆች ሊሆኑ ይችላሉ። በተመሳሳይ ሁኔታ በሃገራች አርበኛውን ሲጠቁሙና ሲያስገድሉ የነበሩት፣ እነ አቡነ ጴጥሮስ ላይ ቃታ ስበው የገደሏቸው ለጣሊያን ያደሩ የኛው ወንድሞች ናቸው። እነዚህ እፍረት የሌላቸው ባንዳዎች ፋሽስት ጣሊያን በአምስቱ ዓመት የኢትዮጵያ ቆይታው የዘረፈውን የሃገራችንን ንብረትና የተፈጥሮ ሃብት ለማጓጓዝ፣ ወታደሩን ለማመላልስ የሰራውን መንገድ፣ ድልድይ እና ይኖርበት የነበረውን የወታደር ካምፕና መኖሪ ቤት ፋሽስት ለኢትዮጵያ እድገት ተጨንቆና ለህዝቡ ተቆርቁሮ የሰራ ይመስል ጣሊያን ትንሽ በሃገራችን ቢቆይ (ቅኝ ቢገዛን ኖሮ) መንገድና ሕንፃ ይገነባልን ነበር ሲሉ መስማት የተለመደ ነበር። ይህ ማለት የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞችን ተጋድሎን መካድ ሲሆን  ፋሽስት ጣሊያን በአካል ተሸንፎ ከኢትዮጵያ ቢባረርም በመንፈስ የወለዳቸው የአዕምሮ እጥበት (Brainwash) የደረሰባቸው ሰዎችን ተክቶ እንደሄደ ያሳያል። 

ባንዶች “ጣሊያን ትንሽ ቢገዛን መንገድና ድልድይ ይስራልን ነበር” የሚለው የንግግራቸው መነሻው አውሮፓውያን አፍሪካን ሊያሰለጥኑ ነው የመጡት ከሚለው የነጮች የበላይነት (superiority) ፕሮፓጋንዳ መሆኑ ግልፅ ነው። ይሁን እንጂ እነሱ ከመምጣታቸው በፊት በተለያዩ አካባቢዎች በአፍሪካ ውስጥ ስልጣኔ ነበር። ፈረንጅ አምላኪ የሆኑት ባንዶች ከፋሽስት ጣሊያን ለሚያገኙት ፍርፋሪ/ ጥቅም እንጂ የሃገር ክብርና ነፃነት አያስጨንቃቸውም፣ ጣሊያን በግፍ ሃገራችንን በመውረር ያፈሰሰው የንጹሃን ኢትዮጵያውያን ደም ጉዳያቸው አይደለም፣ እኛ ኢትዮጵያን ራሳችን ሠርተን ሀገራችንን መገንባት፣ ማሳደግ እንችላለን የሚል በራስ የመተማመን ወኔ ፈጽሞ በውስጣቸው የለም፣ ታሪክን ወደኋላ ሄደው መመልከት የማይችሉ፣ የአክሱም፣ የላሊበላ፣ የሃረር ግንብን፣ የጎንደር ስልጣኔን እና የመሳሰሉትን ዞር ብለው ማየት የተሳናቸው አንገተ ደንዳና፣ ልበ ጠማማ ናቸው። ዳግማዊ አጼ ምኒልክ መንገዱን፣ ስልኩን፣ ባቡሩን፣ መኪናውን፣ ዘመናዊ የመንግስት ማዋቅርን፣ በርካታ የስልጣኔ ጅምሮችን መስራታቸው እየታወቀና የሳቸውን አርዓያ በመከተል ሃገራችንን ማልማት ሲቻል፡ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የናፓል መርዝ ቦንብ በአውሮፕላን እያዘነበ፣ የደሃ ጎጆ እያቃጠለ፣ ሰላማዊ ህዝብን እየገደለ የገባን ጠላት፣ ከ30ሺህ በላይ የሚሆን የአዲስ አበባን ህዝብ በጠራራ ፀሃይ የጨፈጨፈን ፋሽስት ጣሊያንን ማወደስ፣ ትንሽ ይቆይልን (ይግዛን) ማለት ፍፁም ክህደት ነው። የባንዳ አልፋና ኦሜጋ ጥቅም፣ ቁስ እና ሆዱን መሙላት ስለሆነ የሃገርና የወገን ፍቅር፣ ክብር፣ ነጻነት የሚባሉ የመንፈስ ልዕልና የሉትም። በሃገራችን ወያኔ ያዋቀረው በጎሳ ላይ የተመሰረተ የፌዴራል መንግስት (Institutionalized tribalism) የአውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች ከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ (divide and conquer policy) ውጤት ነው። 

ይህ የባንዳነት አስተሳሰብ በዘር እንደሚተላለፍ ደዌ ከአባት ወደ ልጅ ሲተላለፍ ቆይቶ ጣሊያን በአድዋ ላይ ጦርነት ከፍቶ በመሸነፉ ማሳካት ያልቻለውን ኢትዮጵያን የማፈራረስ ፕሮጅርክት ቆዳቸው እኛን የሚመስሉ ባንዶች ተቀብለው ሃገራችንን ለማፍረስ እና ወራሪውን በጀግንነት የመከታቸውን የኢትዮጵያን ህዝብ በተለይም አማራውን ለመበቀል (ሂሳብ ለማወራረድ) ወያኔና ሻዕቢያ (ጀብሃ) ወደ ደደቢትና ናቅፋ በረሃ ወረዱ። ዛሬ ወያኔና ሻዕቢያ ባላቸው የዓላማ ልዩነት ሳይሆን በጥቅም ግጭት በተለይ ከባድሜ የድንበር ግጭት ጋር በተያያዘ ወያኔ በኢትዮጵያ ይኖሩ የነበሩ የኤርትራ ተወላጆችን ሃብት ንብረታቸውን ቀምቶ፣ በትዕቢት ተወጥሮ በባለጌ አፉ ከፈለግን የዓይን ብሌናችሁ አላማረንም ብለን ማባረር እንችላለን በማለት መለስ ዜናዊ ባዶ እጃቸውን ከሃገር ስላባረሯቸው በተፈጠረ ቂም ጠላት መስለው ይታያሉ እንጂ በጋራ ስትራቴጂ ቀርፀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ጸረ ኢትዮጵያ ድርጅቶች መሆናቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው። ከሻዕቢያ በፊት ጀብሃ የሚባል ድርጅት በአብዛኛው በቆላማው የሱዳን ጠረፍ እና በምጽዋ አካባቢ በሽምቅ ተዋጊነት ይንቀሳቀስ የነበረና በግብፅ የተመሰረተ ሲሆን በኢሳያስ የሚመራው ሻዕቢያ ጀብሃን አክስሞ የመጣ ገና ከጥንስሡ ጀምሮ ፀረ ኢትዮጵያ የሆነ ድርጅት ነው። ሻዕቢያ ግብጽና ሱዳንን ጨምሮ በአረብ ሃገራት ሙሉ የትጥቅ፣ የስልጠና፣ ወታደራዊና የፓለቲካ ድጋፍ ያገኝ የነበረ ሲሆን በተለይ እንደ ሶሪያና ኢራቅ ዓይነት የአረብ ሃገሮች የታንክና መድፍ ሳይቀር ቀጥተኛ የሎጂስቲክ ድጋፍ ይደረግለት ነበር። ደርግ ከመውደቁ በፊት በ1982 ዓ/ም ኤርትራ ውስጥ ሰናፌ በተባለ ቦታ በሻዕቢያ ሰብሳቢነት ወያኔ፣ ኦነግ እና እራሱ ሻዕቢያ እንዴት ኢትዮጵያን እንደሚቀራመቱ ስምምነት ማድረጋቸው ይታወቃል። 

8. የዓድዋ ድል እና የፋሽስት ቂም ፣ 

መጀመሪያ ጣሊያንን ምፅዋ የባህር ወደብ ላይ አምጥቶ የሰፈረው የእንግሊዝ መንግስት ሲሆን ይህንንም ያደረገው ከአጼ ዮሃንስ ጋር የነበረውን ወዳጅነትና የገባውን የሂዎት ውልን በመጣስ ነው። አጼ ዮሐንስ የጦር ሰው መሆናቸው ባያጠያይቅም ጣሊያን በእንግሊዝ ጋባዥነት ምጽዋ ላይ ሲሰፍር ካሳዩት ቸልተኝነት በተጨማሪ የዶጋሊውን ጀግና ራስ አሉላ አባነጋን ከስልጣን ማንሳታቸው አስተዳደራቸው በእንግሊዝ ተጽዕኖ ስር ወድቆ እንደነበር የሚያሳይ ነው። የእንግሊዝን ይሁንታ ያገኘው የጣሊያን ወራሪ ጦር ከቆላማው የምጽዋ የባህር ወደብ ተነስተው ወደ ውስጥ በመስፋፋት የራስ አሉላ መቀመጫና ነጋዴዎች ወደ ምፅዋ ሲጓዙ ማረፊያቸው የነበረችውን ነፋሻማዋን አስመራ ከተማን ተቆጣጠረ። ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ነበር አጼ ዮሐንስ መተማ ላይ ከደርቡሽ ጋር ሲዋጉ የተሰውት። በመቀጠል የጣሊያን ወራሪ ጦር በዚህ ወቅት ሃገር አለመረጋጋቷን ተጠቅሞ ከአስመራ በመነሳት ትግራይን እና ባህረ ነጋሽን (ኤርትራን) እስከሚያዋስነው እስከ መረብ ወንዝ  ድረስ ያለውን ሃገር በቁጥጥሩ ስር በማድረግ በወረራ የያዘውን የኢትዮጵያን መሬት እንደ ቀይ ባህር “ኤርትራ” በማለት መጥራት ጀመረ። የጣሊያን ወራሪ ከኤርትራ (ከቀድሞ ባህረ ነጋሽ አውራጃ) የጦርነት ዝግጅቱን ሲጨርስ አጠቃላይ ኢትዮጵያን በመውረር ቅኝ ግዛቱ ለማድረግ በአራት የጦር ጀነራሎች እየተመራ በ1888 ዓ.ም አድዋ ላይ ከኢትዮጵያ ጀግኖች ጋር ጦርነት ገጠመ። የፋሽስት ጣሊያን ወታደር በአፄ ምኒልክ ብልህ አመራር እና በጀግኖች አባቶቻችን እንክትክቱ ወጥቶ ተሸነፈ። በጣሊያን ጦር በኩል ተዋጊውን ይመሩት ከነበሩት አራት ጀነራሎች ውስጥ ሁለቱ በጦርነቱ ላይ ተገደሉ፣ አንዱ ተማረከ፣ አንዱ ደግሞ (ጀነራል ባራቴሪ) ፈርጥጦ አስመራ ገባ። እሱም ቢሆን እስከ እለተሞቱ በጭንቀትና በቅዥት እንደኖረ የህይወት ታሪኩ ይናገራል። በመሆኑም ዘመናዊው የጣሊያን ተዋጊ ሃይል ኋላቀር በሚባሉት በኢትዮጵያ ተዋጊዎች ሙሉ በሙሉ በመደምሰሱ በአውሮፓ መንግስታት ዘንድ የጣሊያን መንግሥት አንገቱን በሃፍረት ደፋ፣ ከፍተኛ ወቀሳና ውርደትም ደረሰበት። የሮም ከተማ ህዝብም አደባባይ ወጥቶ Viva Menelik! እያለ የአጼ ምኒልክን ጀግንነት በማወደስ በሃገሩ መንግስት ላይ ያለውን ቁጣና ተቃውሞ አሰማ። ይህም ለጣሊያን መንግስት ታላቅ ሃፍረትና ውርደት ሆነበት። የፋሽስት ጣሊያን መንግሥት ለደረሰበት ሽንፈትና ውርደት አጠቃላይ ኢትዮጵያን እና ህዝቧን ቢጠላም በዋና ደመኛ ጠላትነት በመፈረጅ ለመበቀል የተነሳው:- 1ኛ የኢትዮጵያን ህዝብ ከዳር እስከ ዳር አስተባብረው አድዋ ድረስ አዘመቱብኝ የሚላቸውን አፄ ምኒልክን፣ 2ኛ በጦርነቱ ላይ በነቂስ የተሳተፈው የአማራን ህዝብ፣ 3ኛ አድዋ ድረስ ታቦት ተሸክመው በመሄድ ለተዋጊው የመንፈስ ብርታትና ጉልበት የሆኑት የኦርቶዶክስ ካህናትን ነበር።

በመሆኑም የፋሽስት ጣሊያን መንግስት በአፄ ምኒልክ፣ በአማራ ህዝብ እና በኦርቶዶክስ ካህናት ላይ ስም የማጥፋት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻውን ከመክፈቱ ጎን ለጎን ከትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪው ማህበረሰብ ውስጥ ባንዳዎችን በመመልመል የወር ደሞዝ እየከፈለ በሰላይነትና በቅጥረኛ ተዋጊነት (Askaris) ያሰማራ ነበር። የጣሊያን ሹማምንት በአስመራ ከተማ ጽሁፎችን በትግርኛ ቋንቋ እያተሙ ወደ ህዝቡ በማሰራጨት የአዕምሮ አጠባ (Brainwash) አደረጉ። “ምኒልክ የጣሊያን  ብቻ ሳይሆን የትግሬም ጠላት ነው”፣ “ንግስና ለዮሐንስ ልጆች እንጂ ለሸዋው ምኒልክ አይገባም”፣ “ትግሬ ለአማራ መገዛት የለበትም” ወዘተ በማለት የትግራይ መኳንንቶች ስለራሳቸው የተጋነን ስሜት እንዲያዳብሩ በማድረግ በታብዮ ለአመፅና ለሽብር እንዲነሱ አደረጓቸው። እውነቱ ግን አፄ ዮሐንስ የነገሱት በትግሬነታቸው ሳይሆን ከጎንደሩ ከአፄ ፋሲለደስ ጋር ዝምድና አለኝ፣ በእናታቸው በኩል የሰለሞናዊ ደም (ዘር) አለኝ በማለት ነበር። ጣሊያንም በሁለተኛው የማይጮ ጦርነት በዘመናዊ መሳሪያ ብልጫና በባንዳ (Askaris) ድጋፍ አዲስ አበባን በተቆጣጠረ ጊዜ በጸሎትና በጾም  የደከሙ የደብረ ሊባኖስን መነኮሳትን ሰብስቦ በጅምላ መጨፍጨፉ፣ አቡነ ጴትሮስን እና አቡነ ሚካኤልን በአደባባይ መረሸኑ፣ ከ30 ሺህ በላይ የሆነን የአዲስ አበባን ህዝብ በጅምላ መጨፍጨፋ ጣሊያን ቂመኛ ሂሳብ አወራራጅ እንደሆነ ያሳያል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሮማን ፕሮችዝካ (Roman Prochazka) የተባለ የነጭ የበላይነትን የሚያቀነቅን የኦስትሪያ ተወላጅ ሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ አዲስ አበባ ውስጥ በዲፕሎማሲ ስራ ይኖር ነበር። ይህ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ በሰላይነት ሲንቀሳቀስ ተይዞ በቀ/ኃ/ስላሴ መንግስት የተባረረ ሲሆን በ1927 ዓ/ም “ ኢትዮጵያ የባሩድ በርሜል” (Abyssinia the Powder Barrel) በሚል ርዕስ መፅሐፍ ጽፎ በአውሮፓ ሃገራት አሰራጨ። የመፅሐፉ ዋና ይዘት በወቅቱ ዘረኛ የፈረንጅ ምሁራን (የቀኝ ገዥ ምሁራን) ያለምንም ሳይንሳዊ ማስረጃ በተፈጥሮው ነጭ ከሌላው የሰው ዘር የበላይ ነው፣ ጥቁር ህዝብ የተፈጥሮ አዝጋሚ ለውጥን አላጠናቀቀም። በመሆኑ ነጭ አውሮፓውያን ከጥቁር ህዝብ በአስተሳሰቡም ሆነ በአካል ቅርጽ የተሻሉ ስለሆኑ አፍሪካን በቅኝ መግዛት ይችላሉ የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ ስለነበራቸውና ፕሮችዝካ አዲስ አበባ መጥቶ በነበረበት ጊዜ ከዚህ የአውሮፓ የተሳሳተ አስተሳሰብ ተቃራኒ በሆነ ሁኔታ ኢትዮጵያውያን ፈርንጅ ቀጥረው  በገንዘባቸው እያዘዙ ቤታቸውን፣ የውሃ ቦንቧ መስመር እና የመሳሰሉትን ግንባታዎችን ሲያሰሩ ሲመለከት ደነገጠ። ኢትዮጵያውያን ሃገራቸውን በነጻነት አስከብረው የሚኖሩ፣ የነጭ የበላይነትን (White Supremacy) የማይቀበሉ በመሆናቸው ሃገራቸው በአውሮፓ ቅኝ ግዛት ስር ካልወደቀች ለሌሎች በቅኝ ግዛቶቻችን ውስጥ ለሚገኙ ጥቁር አፍሪካውያን መጥፎ ምሳሌ ትሆናለች የሚል መልዕክት ያለው መጽሃፍ ነበር የጻፈው። ሮማን ፕሮችስካ ኢትዮጵያ በርካታ በቋንቋ፣ በባህልና በእምነት የተለያዩ ማህበረሰቦች የሚኖሩባት ሃገር ስለሆነች ይህንኑ ልዩነት በመጠቀሞ የህዝቡን ህብረት በማላላት በቀላሉ በጦርነት አሸንፎ ኢትዮጵያን በመቆጣጠር በቅኝ መግዛት ይቻላል በማለት ፃፈ። የሮማን ፕሮችዝካ ሃሳብ በወቅቱ ኢትዮጵያን ለመውረር በዝግጅት ላይ ለነበረው ለፋሽስት ጣሊያን መሪ ለነበረው ቤኒቶ ሙሶሊኒ (Benito Mussolini) ጥሩ ግብዓት እንደሆነው ይታወቃል። 

ከሮማ ፕሮችስካ ቀደም ብሎ ዮሐን ሉድዊግ ክራፕፍ (Johann Ludwig Krapf) የተባለ የጀርመን ሚስዮናዊ እ.አ.አ ከ1837 እስከ 1842 ኢትዮጵያ (ሸዋ) ውስጥ ተቀምጦ ነበር። በወቅቱ የነበሩት የአፄ ምኒልክ አያት የሸዋው ንጉስ ሳህለ ስላሴ ሲሆኑ ዮሃን ክራፍ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ህዝቡን የእጅ ሞያ (ተግባረ ዕድ) እንዲያስተምር ነበር። ነገር ግን ዮሃን ክራፕፍ ጊዜውን ያሳልፍ የነበረው የመጣበትን የእጅ ሞያ ጥበብ ህዝቡን በማስተማር ሳይሆን በሃይማኖት ስብከት እና ሃገርን በመሰለል ነበር። በዚህ ህገወጥ ስራው ከሃገር እንዲባረር ተደረገ። ነገር ግን ዮሃን ክራፕፍ ወደ ሃገሩ ከሄደ በኋላ ተመልሶ አራት ፈረንጆችን ህዝቡን የእጅ ጥበብ ማስተማር የለሚችሉ ናቸው በማለት ዓይኑን በጨው አጥቦ ተመልሶ መጣ። ንጉሱም ለሁለተኛ ጊዜ እድል ቢሰጡትም ውሸቱን እንጂ ያመጣቸው ሰዎች የእጅ ሞያ የሌላቸው ሃይማኖት ሰባኪ ሚሲዮናውያን መሆናቸው ተረጋገጠ። ከዚህም በተጨማሪ ዮሐን ክራፕፍ በየገጠሩ ጠፍቶ እየሄደ ጎሳን ከጎሳ ለመለያየት በአውሮፓውያን ከፋፍለ ግዛ ፖሊሲ ኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን እየሰበሰበ ለመመረዝ ሲንቀሳቀስ ስለተደረሰበት ዳግም ከሃገር ተባረረ። ዮሃን ክራፕፍ በወቅቱ ስለ ኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት እየሰለለ ለጀርመን መንግስት ከላከው ሚስጥራዊ መረጃዎችና የቅኝ ግዛት ምክረ ሃሳብ (proposal) ውስጥ አንዱ የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰቦችን በፕሮቴስታንት ክርስትና ሃይማኖት በማጥመቅ በቀላሉ የጀርመንን ቅኝ ግዛትን ማስፋፋት እንደሚቻል የሚገልጽ ነበር። በተለይም በተለያየ የጎሳ መጠሪያ ስም ተበታትነው የሚገኙትን “የ*ላ” ማህበረሰቦች በአንድ አዲስ መጠሪያና የግዛት ካርታ ውስጥ በማጠቃለል ከሩዋንዳና ብሩንዲ ጀምሮ እስከ መሃል ኢትዮጵያ ድረስ የምስራቅ አፍሪካ የስምጥ ሸለቆ ሃይቅ ሃገራትን አንድ ላይ በማድረግ ትልቅ የጀርመን ቅኝ ግዛትን መፍጠር ይቻላል በማለት ለሃገሩ መንግስት የጻፈው ምክረ ሃሳብ ይገኛል። በ1986 ዓ/ም በሩዋንዳ በሁቱ እና በቱትሲ ጎሳዎች ላይ የደረሠው የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ሠንኮፉ እንደ ዮሐን ሉድዊግ ክራፕፍ ዓይነት ባሉ በቅኝ ገዢዋ የጀርመን ሚሲዮናውያን የተተከለ መርዝ ሲሆን በኋላም የሁለተኛ የዓለም ጦርነት በመሸነፋቸው ጀርመኖች ሩዋንዳን ጨምሮ ቅኝ ግዛቶቻቸውን ለቀው ሲወጡ በእነሱ እግር በተተኩት በቤልጂጎች የዳበረ የከፋፍለህ ግዛ ፓሊሲ ውጤት መሆኑን እዚህ ላይ ማስታወስ ይገባል። የኦሮሞ ጽንፈኛ ብሔርተኞች አንዱ መነሻቸው ይኸው የዮሐን ክራፕፍ ስሁት አስተምህሮ ነው። ዮሃን ክራፕፍ በጉዞ ማስታወሻው ላይ እንደገለጸው ኦሮሞን ተጠቅሞ ምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካን “ኦርማንያ” በሚል ስያሜ የጀርመን ቅኝ ግዛት መፍጠር ባይችልም እንኳን ብዙዎችን በማሳሳት ለዕኩይ ዓላማው ተከታይ ማድረግ ችሏል። ሚሲዮናውያን የ60 ዎቹን የወለጋ ኦሮሞ ወጣቶችን በጠባብ ብሔርተኝነት ሲያሰለጥኑ በሌላ የሃገራችን አካባቢ የሚገኙትን ወገኖቻችንን ደግሞ ሃገራችሁ በሰማይ ነው እያሉ በልባቸው ያለውን ኢትዮጵያዊነት እንደ በረዶ እንዲቀዘቅዝ ለማድረግ ብዙ ጥረዋል። 

በአድዋ ጀግኖች አባቶቻችን የህይወትና የአካል መስዋዕትነት ከፍለው ቅኝ ሊገዛን የመጣውን የጣሊያን ወራሪ ጦር ካሸነፉ በኋላ ጣሊያን የአድዋ ሽንፈቱን ለመበቀል አርባ አመት ሙሉ ሲዘጋጅ ቆይቶ ሙሶሊኒ በ1928 ዓ.ም ሰራዊቱን ዘመናዊ የጦር መሳሪያ አስታጥቆ በኢትዮጵያ ላይ ግልፅ ወረራ ፈፀመ። በወራሪው የፋሽስት ጣሊያን ጦር እና በኢትዮጵያ አርበኞች መሃል ትግራይ ውስጥ “ማይጨው” በሚባል ተራራማ አካባቢ ከፍተኛ ጦርነት ተደረገ። በዚህ ወቅት የጣሊያን መንግስት በዓለማቀፍ ደረጃ የተከለከለ የናፓል የኬሚካል ቦምብ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ በሰማይ የሚጥሉ አውሮፕላኖችን በመሬት በታንክ በሚታገዙና ዘመናዊ የጦር መሳሪያ በታጠቁ ወታደሮች ነበር ወረራውን ያደረገው። ዋናው ጦርነት የተደረገው ማይጨው ላይ ቢሆንም ከዛ በፊት አቢ አዲ፣ አሸንጌ ሃይቅ አካባቢ እና በተለያዩ አካባቢዎች ጦርነት ተደርጓል። በነዚህ አውደ ውጊያዎች በብዙ አስር ሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ አርበኞች ተሰውተዋል። የትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ያየን እንደሆን ከፊሎቹ በጣሊያን በኩል በባንዳነትና በቅጥረኛ ተዋጊነት (Askaris) በመሆን ኢትዮጵያን የወጉ ሲሆን፣ ከፊሎቹ ደግሞ ከኢትዮጵያ አርበኛ ወንድሞቻቸው ጋር ተሰልፈው ለሃገራቸው ኢትዮጵያ በቀናይነት ተዋድቀዋል። እፍረት ያልፈጠረበት ከሃዲው ወያኔ እነዚህን ከጣሊያን ጋር ቆመው የኢትዮጵያ አርበኞች ሲወጉ የነበሩ ሽፍቶችን “ቀዳማይ ወያነ” እያለ ይጠራቸዋል። ለጣሊያን የተገዙ ወንበዴዎች በማይጨው ላይ ብቻ ሳይሆን ከዛ በፊትም ሆነ በኋላ በኢትዮጵያና በህዝቧ ላይ በተደጋጋሚ ክህደት ፈጽመዋል። ለምሳሌ ከቅርቡ ስንነሳ የዛሬ ዓመት ጥቅምት 24/ 2013 ዓ/ም በትግራይ በነበረውን ሰሜን እዝ ላይ መብረቃዊ ጥቃት በሚል በተለያዩ ካምፖች የነበረውን የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት ላይ በተመሳሳይ ሰዓት በተቀናጀ ሁኔታ በተኙበት አርደዋቸዋል። በደርግ ዘመን ሽሬ ላይ ሰራዊቱን ጨፍጭፈዋል። የአጼ ዮሃንስ የልጅ ልጅ የሆነው መቀመጫውን መቀሌ ላይ አድርጎ ከፊል ትግራይን ሲያስተዳድር የነበረው ኃይለ ስላሴ ጉግሳ ፋሽስት ጣሊያን በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ሊጀመር አቅራቢያ በመስከረም 1927 ዓ/ም ከአዲስ አበባ ጋር የሚያገኛኘውን የስልክ መስመር በጣጥሶ በማውደም፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቹን እስከ ነፍስ ወከፍ መሳሪያቸው አስከትሎ ኢትዮጵያን ለመውጋት አስመራ ከሚገኘው የጣሊያን ጦር ጋር ተቀላቀለ። ምንም እንኳን በዘመናዊ መሳሪያ ብልጫ፣ በባንዳ ሸፍጥና ስለላ እየታገዘ የጣሊያን ወራሪ ሃይል አዲስ አበባ በመግባት ቢችልም ጀግኖች አባቶቻችን ተስፋ ሳይቆርጡ 5 ዓመት ሙሉ ቆላ ደጋ ተንከራተው፣ ህይወታቸውን ገብረው በብዙ ድካም እና መስዋዕትነት ኢትዮጵያን ነፃ አወጧት። ፋሽስት ጣሊያን በአማራ ህዝብ፣ በኦርቶዶክስ ክርስትና እና በአጼ ምኒልክ ላይ ሲያስራጨው የነበረው ስም የማጠልሸት ዘመቻ ሰለባ የሆኑና በጥቅም የተገዙ ባንዳ የባንዳ ልጆች፣ የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ሰላይና አቀንቃኝ የነበሩት እንደ ፕሮችስካ እና ዮሃን ክራፕፍ ዓይነት ሚሲዮናውያን የሃሰት ስብከት፣ የኮሚኒስቶች የጨቋኝ ተጨቋኝ ፕሮፓጋንዳ ፍሬ አፍርቶ እንደ ወያኔና ኦነግ ዓይነት ኢትዮጵያን፣ ታሪኳን፣ ጀግኖቿን፣ ሰንደቅ ዓላማዋን የሚጠሉ ጨካኝ አረመኔ ጥቁር ፋሽስቶችን እና ናዚዎችን መፍጠር ቻለ።

9. ድህረ ቅኝ አገዛዝ እና ኒዮሊብራሊዝም (Post-colonization and Neo-liberalism)

ምዕራባውያን በአፍሪካ ዘርግተውት የነበረው ቅኝ አገዛዝ ከተወገደ በኋላ ልክ በእነሱ በጎ ፍቃድ አፍሪካውያን ነጻነታቸውን ያገኙ እስኪመስል ድረስ ለሃገራቱ እውቅና በመስጠት በወዳጅነት ስም ሃገራቱን ይቀርባሉ። ሃገራችሁን ለማቋቋም ከጎናችሁ ነን በማለት የተለያዩ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና (አሻጥር) በማድረግ ለእነሱ ታዛዥ የሆነ ደካማ መሪ ካስቀመጡ በኋላ መንግስቱን ውል ያስፈርሙታል። በውሉ መሰረት ሃገሪቷ የንግድ ግንኝነኘቷ ከእነሱ ጋር ብቻ እንዲሆን ያደርጋሉ፣ ከፖሊስ በስተቀር ሃገሪቱን የሚጠብቅ መከላከያ ወታደር እኛ ስላለን ወጪውም ከፍተኛ ስለሆነ አያስፈልጋችሁም በማለት የራሳቸውን አምጥተው ያሰፍራሉ። የወርቅ፣ አልማዝ፣ ነዳጅና የመሳሰሉት የማዕድን ማውጫዎችን በበላይነት ያስተዳድራሉ፣ ማዕድናቱን የሚያወጡ ካምፓኒዎችን ከሃገራቸው ይቀጥራሉ፣ የሽያጩ ገቢ የትኛው ባንክ እና የት ሃገር መቀመጥ እንዳለበት፣ ሃገሪቷ ከማን ጋር መገበያየት እንዳለባት በበላይነት ይወስናሉ፣ የሃገሪቷን ገንዘብ ያትማሉ፣ የትምህርቱን ስርዓት በእነሱ የሚቀረጽ ስለሚሆን ትውልዱ በቅኝ ገዢዎች ትርክት (Post colonial Literature) ተሞልቶ እንዲያድግ በማድረግ የባህል ተጽዕኖ (Cultural Domination) በመፍጠር የእነሱ አድናቂና ተገዥ አድርገው ይቀርጹታል። ለምሳሌ ምንም እንኳን እኛ ኢትዮጵያውያን በቅኝ ግዛት ባንገዛም እንኳን የአእምሮ እጥበት የደረሰባቸው አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን ሃገራቸውን በመክዳት በባንዳነት ጣሊያንን እንዳገለገሉና የቅኝ ገዢ አድናቂነታቸውን መንገድና ድልድይ በመጥቀስ እስካሁንም ድረስ እንደሚያወድሱ ከዚህ በላይ በክፍል 9 “ጣሊያን ቢገዛን መንገድና ድልድይ ይስራልን ነበር” (የባንዳ ጥቅስ) በሚለው ክፍል ለማብራራት ሞክሬያለሁ። ከዚሁ የአዕምሮ እጥበትና የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች በቀጥታም ሆነ በእምነት ትውቋሞቻቸው በፈጠሩት የባህል ተጽዕኖ ጋር በተያያዘ የሃገራችን ፊደል እያለ አውሮፓ ድረስ ባህር አቋርጠው በመሄድ የላቲንን ፊደል መዋሳቸው የዚሁ Post colonial Literature ተጽዕኖ (influence) ውጤት ሰለባ ወንድሞች እንዳሉን ልብ ይሏል። ሌላ ቢቀር ወንድሜ ስለው ያደኩት የልጅነት ጓደኛዬ ፒያሳ በብሪቲሽ ካውንስል ላይብረሪ እየተዋሰ ሲያነባቸው የኖራቸው Post colonial Literatures በፈጠሩበት ተጽዕኖ በፋሽስት ጣሊያን እና በቅኝ ገዢ ሚሲዮናውያን በሃገራችን ላይ የተዘራው የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ አሁን ለገባንበት የጎሳ ፖለቲካ (Tribalism Politics) መነሻ ጥንስስ መሆኑን ለመረዳት ምን ያህል እንደተቸገረ እኔ ምስክር ነኝ። ባጠቃላይ የቀድሞ ቅኝ ገዢዎች ነጻ በወጡ የአፍሪካ ሃገራት ላይ የኢኮኖሚ፣ የባህል፣ የወታደራዊና የፖለቲካ የበላይነትና ተጽዕኖ በማምጣት እርጅም ገመድ አንገታቸው ላይ አጥልቀው ሃገራቱን በእጅ አዙር ይቆጣጠራሉ ማለት ነው። በመሆኑም ምዕራባውያን በዓለም ላይ ዘርግተውት የነበረው ቅኝ አገዛዝ ከተወገደ በኋላ እንደ Commonwealth, France-Afrique ዓይነት ህብረቶችን ከቀድሞ ቅኝ ግዛቶቻቸው ጋር በማድረግ በዕርዳታና በትብብር ስም ውል በማስፈረም የጥሬ ዕቃ፣ ማዕድናት፣ ነዳጅ፣ የሰው ሃይል እና የመሳሰሉት እንዳይቋረጥባቸው፣ ምርታቸውንም አፍሪካ ወስደው ለመሸጥ የሚያስችላቸውን የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ (Neocolonialism) ስልት በአፍሪካ ዘረጉ።  

እንደሚታወቀው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የአውሮፓ መንግስታት በጦርነት ከተሞቻቸው ሲወድምና ኢኮኖሚያቸው ሲንኮታኮት ከእሳቱ  እርቃ የምትገኘው የአሜሪካ ኢኮኖሚ ግን በወቅቱ በብዙ እጥፍ እንዳደገ የምጣኔ ሃብት ጠበብት ይነገራል። አሜሪካና የምዕራቡ ዓለም መንግስታት የቅኝ አገዛዝ ፖሊሲያቸው በአፍሪካ መንግስታት ተቀባይነቱን ማጣቱን ሲረዱ የብዝበዛ ስልታቸውን ይበልጥ በረቀቀ መንገድ ግሎባላይዜሽን፣ ነጻ ገበያና ፕራይቬታይዜሽን በሚል በማለት የዓለምን ኢኮኖሚና ፖለቲካ ለመቆጣጠር ኒዮሊብራሊዝም (Neo-liberalism) የሚባል ርዕዮት በማራመድ ላይ ይገኛሉ። በኢኮኖሚው ዘርፍ ስርዓቱን ለማሳለጥ የዓለማችን ግዙፍ የገንዘብ ተቋማት የሆኑትን IMF, World Bank, European Central Bank (ECB)፣ USAID፣ UN (የተባበሩት መንግስታትን) እና የመሳሰሉትን ህብረቶችን፣ ስብስቦችን፣ የሰብዓዊና የእርዳታ ሰጪ ተቋማትን፣ በፖለቲካውና በወታደራዊው ዘርፍ ደግሞ እንደ NATO ዓይነት ህብረቶችን በመጠቀም የአሜሪካ እና የእንግሊዝ መንግስታት ሌሎች የምዕራቡን ሃገራትን በማስተባበር ኒዮሊብራሊዝም (Neo-liberalism) በዓለም ላይ በማስፋፋት ላይ ይገኛሉ። በተለይም በ1980 ዎቹ የአሜሪካን ፕሬዝዳንት በነበሩት በሮናልድ ሬገን እና በእንግሊዟ ማርጋሪ ታቸር ወቅት ከቅኝ ግዛት ማብቃት በኋላ መልክና ቅርፁን ቀይሮ የመጣውን የምዕራባውያን አዲስ የብዝበዛ ስልት ፖሊሲና ስትራቴጂ ተቀርጾለት የታዳጊ ሃገሮችን የተማረ የሰው ሃይል፣ የተፈጥሮ ሃብት፣ ትላልቅ ተቋማትን በ privatization ስም በመቆጣጠር፣ የሃገር በቀል አፍሪካዊ ባለሃብቶችን እና የመንግስት ተቋማትን አቀጭጮ በማጥፋት የሃገራቱን ኢኮኖሚ ለመቆጣጠር የምዕራቡ ባለሃብቶች እየተረባረቡ ይገኛሉ። በመሆኑም ምዕራባውያን የዓለምን ኢኮኖሚ ከተቆጣጠሩ በኋላ ልኡዋላዊ መንግስታትን በማፍረስ የዓለምን ሃገራት ለመቆጣጠር የሚያስላቸውን ጠቅል የሆነ ፈላጭ ቆራች መንግስት በመመስረት የማህበረሰቡን መልካም እሴቶች በማጥፋት በተለይ በእኛ ኢትዮጵያውያን ባህል እና እምነት ተቀባይነት የሌላቸውን የረከሱ ነገሮችን ለማስፋፉ እንዳቀዱ ይነገራል።

የአሮጌው ወይም የክላሲካል ሊብራል አስተሳሰብ መርሆዎች የነበሩትን ነጻነት፣ እኩልነት፣ ዲሞክራሲ (Liberty/ Freedom, Equality, Democracy) እና የመሳሰሉ ቃላቶችን የኒዮሊብራሊዝም (NeoLibralism) አራማጆች ለእነሱ በሚያመቻቸው አንጻር እያወላገዱ ይጠቀሙበታል። ለምሳሌ liberty and free market በኒዮሊብራሊዝም መዝገበ ቃላት ስለ ሰው ልጅ ነጻነትና እኩልነት ሳይሆን የሚሰብከው መንግስት በካፒታሊስቶች ላይ የገበያ ቁጥጥር (Regulation) አያድርግ፣ ባለሃብቱ እንደፈለገ በነጻነት ስም ይለቀቅ ወይም ቁጥጥር አይደረግበት የሚል መልዕክት ነው ያለው። አንድን ሰው በሌሎች ሰዎችና በሃገር ላይ እንደፈለገ እንዲሆን መልቀቅ ጥቂት ባለሃብቶችን ማንገስ ብቻ ሳይሆን ስለሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ስነልቦና አለመረዳትም ጭምር ነው። ብዙ ውስብስብ ግብአቶች ባሉባት ዓለም “Demand and Supply” የሚባሉ ሁለት የምጣኔ ሃብት ቃላቶችን መዘህ አውጥተህ የዓለምን ህዝብ ጠቅልለህ በሞኖፖል ለጥቂት ሃብታሞች እንዳሻችሁ በገበያው መሰረት አድርጉ ብልህ የምትሰጥ ከሆነ የአንተን ድንቁርና እንጂ የእነሱን ድክመት አያሳይም። በመሆኑም ካፒታሊስቱ ልጓም እንደሌለው ፈረስ ያለተቆጣጣሪ እንዳሻው እንዲጋልብ ሲለቀቅ፣ ሃብት ለማካበት በሚያደርገው ፉክክር ሁሉም እንኳን ባይሆኑ ጥቂቶች የሌላውን መብት ከመጋፋትም በላይ አልፈው በመሄድ ለሰባዊ ፍጡር አደገኛ የሆነ ነገር ሊያደርጉ ይችላሉ። የሰው ልጅ እንደከብት ታርዶ ኩላሊቱ በሚሸጥበት እና ቫይረስ ይፈበረካል በሚባልበት በዚህ ክፉ ዘመን፣ ጥንቃቄ እንጂ የዋህነት አያዋጣም። መጽሃፉ እንደሚለው “ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ምንጭ ነው”።  

10. የምዕራባውያን ግብዝነት እና ዝግ ህሊና (Western Hypocrisy and Close mindedness)

በቅኝ ግዛት ባህልና ፖለቲካ ተኮትኩቶ ያደገው የዘር መድሎና እራስን ከሁሉ በላይ የማድረግ የነጭ የበላይነት አስተሳሰብ (White Supremacy) እስካለንበት ዘመን ድረስ ከዓለማችን ፈጽሞ ሊወገድ ባለመቻሉ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ሰንኮፉ እንዳልፈረጠ እባጭ እዚህም እዛም ሲከሰት ይታያል። በመሆኑም ከዘረኝነት በሽታ እራሳቸውን ማላቀቅ ያልቻሉ አንዳንድ ምዕራባውያን በሚያስተዳድሩት ሃገር የሚፈጸም የራሳቸውን ጉድ አስቀምጠው በግብዝነት (hypocrisy) በሌሎች ልኡዋላዊ ሃገራት የውስጥ ጉዳይ ያውም “አፍራሽ በሆነ መልኩ” እጃቸውን በማስገባት ለመፈትፈት ይሞክራሉ። ለምሳሌ በተባበሩት የአሜሪካ መንግስታት (USA) የግዛት ክልል ውስጥ በርካታ የዘር መድሎና ኢሰባዊ ድርጊቶች ሲፈጸሙ ማየት የአደባባይ ሚስጥር ነው። እንግሊዞች በደቡብ አፍሪካ ተክለውት በሄዱት ዘረኝነት እና አፓርታይድን ጨምሮ በምዕራቡ ዓለም በሚኖሩ በጥቁር ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ላይ የሚፈጸሙ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች እና የዘር መድሎዎችን በተመለከተ የጥቁሮች መኖሪያ መንደሮችን (ጌቶ)፣ በአሜሪካና በአውሮፓ ወደሚገኙ እስር ቤቶች፤ ፍርድ ቤት፣ በስራ አካባቢ፣ በሆስፒታል እና በመሳሰሉት በጥቁር ህዝብ ላይ የሚፈጸም ስልታዊ የሆነ ዘረኝነት (Systematic Racism) ይታያል። በጠራራ ጸሃይ በየመንገዱ የሚፍጸም የፖሊስ ጭካኔ (Police brutality)፣ በት/ት ቤቶች እና በኳስ ሜዳ የሚታዩ በተለይም በአውሮፓ በሚጫወቱ ጥቁር ፕሮፌሽናል ኳስ ተጫዋቿች ላይ የሚደርስ አዋራጅ (derogatory) ስድቦች፣ በስራ አካባቢ የሚታዩ አድሎና እንደ ችሎታ ተገቢውን ቦታ አለመስጠት (Neglect and occupational inequality) ሌላው የዘረኝነት ማሳያ ነው። በአሜሪካ “Black lives Matter” የሚለው መሪ ቃል በፖሊስ የሚፈጸም ጭካኔን የሚቃወም፣ ለጥቁር ህዝብ ፍትህ የሚጠይቅ እንቅስቃሴ ነው። በ2020 በአሜሪካ ሚኒያ ፖሊስ በጆርጅ ፍሎይድ ላይ በአደባባይ በፖሊስ የተፈፀመ ዘግናኝ አረመናዊ ግድያ የችግሩን ግዝፈት በግልፅ የሚያሳይ ነው። ይሁን እንጂ የምዕራቡ ዓለም መንግስታት በታብዮ የራሳቸውን የቤት ጣጣ አስቀምጠው ከሞራልም ሆነ ከዓለማቀፋዊ ህግ ውጪ ያልፈለጉትን ሃገር መንግስት ለመቀየር የኢኮኖሚና የዲፕሎማሲ ጫና ያደርጋሉ። የምዕራቡ ስልጣኔ በገንዘብ፣ በሃብትና በቁስ የሚለካ እንጂ የመንፈስ ልዕልና የሌለው በመሆኑ ምዕራባውያኑ ሰባዊነት፣ ዲሞክራሲ፣ ፍትህን ከጥቅማቸው በኋላ የሚያዩት በሁለተኛ ደርጃ ነው። ከዚህም አልፎ ሰባዊ እርዳታን ለፖለቲካ ፍጆታ ወይም የደሃ ሃገራትን እጅ ለመጠምዘዝ ሲጠቀሙበት ይታያል። ለምሳሌ አሜሪካ ታላቅ ሃገር ሆና ሳለ የግብጽ ጉዳይ አስፈጻሚ በመሆን ፕሪዝዳንት ትራምፕ በንቀት ተሞልተው ለግብጾች በቦምብ ግድቡን አውድሙት ሲሉ፣ አሁን ደግሞ የባይደን አስተዳደር ያለ ደረጃው እታች ወርዶ እየተርመጠመጠ ከአሸባሪው ወያኔ ጋር ሽርክና መፍጠሩ እጅግ አሳፋሪ ነው። 

11. ማጠቃለያ፣ 

ሃገራችን ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ፣ የግዮን መፍለቂያ፣ በቅዱሳን መፃህፍት የተገለፀች፣ የዳአ’ማት እና የአክሱም ስልጣኔ፣ የአይሁድ፣ የክርስትና፣ የእስልምና እንዲሁም ባህላዊ አምልኮቶች የሚገኙባት ጥንታዊት ሃገር ስትሆን ከአመሰራረቷ ጀምሮ ያለፈችባቸው የተፈጥሮና የታሪክ ጉዞዎቿ ከአሜሪካ፣ ከቻይናም ሆነ ከሌሎች ሃገራት የተለየ የራሷ የሆነ አሻራና ማንነት ይዛ የመጣች ጥንታዊትና ቀዳሚት ሃገር እንደሆነች ያሳያል። ህዝቧም ከአፈሯ ላይ ተፈጥሮ፣ በዘመናት ሂደት ሲዋሃድና ሲደበላለቅ ለዚህ የበቃ ታላቅ ህዝብ ነው። የሰው ልጅ በኢትዮጵያ ምድር ተፈጥሮ ወደተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ከመሰራጨቱ በፊት፣ ጎሣና ብሔር ከመፈጠራቸው፣ ባህልና ቋንቋ ከመስፋፋታቸው፣ አሁን በዓለማችን የሚገኙት የሃይማኖት ድርጅቶችም ሆኑ የዘመናችን ሃያላን የሚባሉት መንግስታት ከመከሰታቸው በፊት ኢትዮጵያ ከህዝቧ ጋር ነበረች። ይሁን እንጂ የዓለም ቅርስ፣ የሰው ልጅ እናት የሆነችው ሃገራችን በተለያዩ ዘመናት የውጭ ጠላቶች ሊያጠፏት ዘምተውባታል። ለምሳሌ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በ1928 ዓ/ም በስዊዘርላንድ በጄኔቭ ከተማ በሚገኘው በሊግ ኦፍ ኔሽን (በተባበሩት መንግሥታት ማህበር) ጉባኤ ላይ ተገኝተው ወራሪው የፋሽስት ጣሊያን መንግስት የተባበሩት መንግስታት አባል የሆነችወን ኢትዮጵያ ሃገራቸውን መውረሩን እና ሰላማዊውን ህዝቧንም በናፓል መርዝ ቦንብ እየጨፈጨፈ መሆኑን በመግለጽ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለው በጦር ወንጀል የሚያስጠይቅ የሰው የዘርን ማጥፋት መሆኑን በመረዳት የመንግስታቱ ጉባኤው ወራሪውን የጣሊያንን መንግስት እንዲያወግዝና ከተገፋው ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን እንዲቆም ያደረጉት ንግግር ይታወሳል። በወቅቱ በኢትዮጵያ ላይ የተደረገን ወረራ ሳያወግዝ እና በህዝቧም ላይ የተፈጸመን የጅምላ ጭፍጨፋ በተመለከተ አድበስብሶ ማለፉ ዛሬም አሸባሪው ወያኔ በአማራና በአፋር ሰላማዊ ህዝብ ላይ የሚፈጽመው የጅምላ ጭፍጭፋ፣ ማፈናቀል፣ በህዝብና በመንግስት ተቋማት ላይ የሚደርሰው ውድመት ምዕራባውያን እንዳላዩና እንዳልሰሙ ሆነው ከአሸባሪው ትህነግ ጎን መቆማቸው በብዙ መልኩ ከ1928 ዓ/ም የጄኔቭ የሊግ ኦፍ ኔሽን ከወራሪው ፋሽስት ጣሊያን ጎን ከመቆም ጋር የሚመሳሰል ነው። እንደሚታወሰው ንጉሱ መልዕክታቸውን በንባብ በሚያሰሙበት ጊዜ የፋሽስት ጣሊያን ተወካዮችና ደጋፊዎቿ በጉባኤው ላይ ያሰሙት የነበረው ፉጨትና ረብሻ ስርዓት አልበኝነታቸውን ብቻ ሳይሆን ለጥቁር ህዝብ የነበራቸውን ንቀትና ዘረኝነት የሚያሳይ ጭምር ነው። ቀ/ኃ/ስላሴ በጉባኤው ላይ “ዛሬ እኛ ነን ነገ ደግሞ እናንተ ናችሁ” (“It is us today, it will be you tomorrow”) ያሉት ትንቢት ሆኖ ብዙ ሳይቆይ በርካቶቹ የናዚ መሪ አዶልፍ ሂትለር በለኮሰው እሣት ተለበለቡ። የምዕራባውያኑ ጡንቻ እያረፈብን ያለነው ዛሬ እኛ ኢትዮጵያውያን ነን ነገ ደግሞ ሌሎች አፍሪካ ወንድሞቻችን ናቸውና ለወገኖቻችን ችግሩን በየሃገሩ ባሉ ኢምባሲዎችና ልኡካን ቡድን በመላክ የኢትዮጵያ መንግስት የማሳወቅ ሞራላዊ ግዴታ አለበት። ከዛም አልፎ በሰሜን አሜሪካ ለሚገኙ የጥቁር ህዝብ መብትና ነጻነት ተሟጋች የሰባዊ መብት ተቋማት እና ታዋቂ ግለሰቦች ችግሩ የቅኝ ግዛት ተቀጥላ መሆኑን ከስር መሰረቱ ማሳወቅ ያስፈልጋል።  

እራሳቸውን የዓለም ሰላም አስጠባቂ የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጠባቂ ፖሊስ ነን በማለት እራሳቸውን የሾሙት አሜሪካና ተባባሪዎቿ ምዕራባውያን መንግስታት እውነትን እያወቁ ለምን ከአሸባሪው ወያኔ ጎን በመቆም ኢትዮጵያን ከተባበሩት መንግስታት እስከ ዱቄት እና ዘይት አከፋፋይ የእርዳታ ሰራተኞች ድረስ ማጥቃት ፈለጉ ለሚለው ጥያቄ መልስ ለማገኘት ምዕራባውያን የተገነቡበትን እሴት መረዳት ይጠይቃል። ዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብት እያሉ የሚያደነቁሩን ለማስመሰል ወይም አንገት ማስገቢያ እንጂ የመጀመሪያም ሆነ የመጨረሻ ግባቸው በባሌም በቦሌም ብለው የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጥቅማቸውን ማስከበር ነው። በአንድ ወቅት የእንግሊዝ ጠ/ሚ “ቋሚ ጥቅም እንጂ፣ ቋሚ ወዳጅ ወይም ቋሚ ጠላት የለም” (“There are no permanent friends or permanent enemies, only permanent interests”) ብለዋል። በሃገራችን ደግሞ “ሆዳም ሰው ዘመድ የለውም” ይባላል። ምዕራባውያን ለጥቅማቸው ያደሩ ራስ ወዳድ ናቸውና በተደጋጋሚ ተፈትነው ወድቀዋል። የትናንት ወዳጃቸውን በተመቻቸው ጊዜ የመክዳት፣ ውል የማፍረስና የማጭበርበር አስቀያሚ ታሪክ እንዳላቸው እንግሊዞችን በሂዎት ውል፣ ጣሊያኖችን በውጫሌ፣ አሜሪካኖች ደግሞ ኢትዮጵያ በዘይድ ባሬ በሚመራው በሶማሌ ተስፋፊ ሃይል በተወረረች ጊዜ ከንጉሱ ከቀ/ኃ/ስላሴ ጋር የነበራቸውን ወዳጅነት በአፍጢሙ ደፍተው የወዳጃቸውን ሃገር ለማፈራረስ፣ ህዝቡን ለመጨፍጨፍ ለተነሳው ጠብ ጫሪ ለሆነው ለዘይድ ባሬ መንግስት የሎጂስቲክ እና የፖለቲካ ድጋፍ መስጠታቸው ይታወቃል። ይኸው ከቫይኪንግ የወረሱት የቀማኛ፣ የስግብግብ ባህሪያቸው ከቅኝ ግዛት እስካሁን ተከትሏቸው ዓለምን እያመሳት ይገኛል። በአፍጋኒስታን፣ በኢራቅ፣ በሶሪያ፣ በሊቢያም ሆነ የተለያዩ ሃገራትን ልኡዋላዊነት በመጣስ እጃቸውን ለማስገባት መጀመሪያ የሚያቀርቡት ምክንያት ዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብትን ለማስከበር፣ ብሔራዊ ጥቅማችንን (national interest) ለማረጋገት የሚል ነው። በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያም እያደርጉ ላሉት ጣልቃገብነት ተመሳሳይ ምክንያት ሲያቀርቡ ቢሰሙም በተጭባጭ እንደሚታየው አሜሪካ መራሹ የምዕራባውያኑ መንግስታት ከዘራፊው እና ከዘር አጥፊው ህወሃት ጎን የቆሙበት ከመጋረጃው ጀርባ ካለው ምክንያት ውስጥ የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፦

 1. አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ ያላትን ብሔራዊ ጥቅም የምታስጠብቀው አንድም በግብፅ በኩል በመሆኑ ከህዳሴ ግድብ ጋር በተገናኘ የወዳጇን ግብጽ ጉዳይ አስፈጻሚ በመሆን የኢትዮጵያን እጅ ለመጠምዘዝ፣
 2. በዶ/ር አብይ አህመድ የሚመራው መንግስት ምዕራባውያኑ በኢትዮጵያም ሆነ በምስራቅ አፍሪካ ለማስፈጸም ለሚፈልጉት ፖሊሲ ማለትም የኢኮኖሚና ወታደራዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ እነሱ በሚፈልጉት መጠን እና ፍጥነት ታዛዥ ባለመሆኑ፣ ነገር ግን በወያኔ የሚመራ የደሃጣን (የማይኖሪቲ) መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣ በቀላሉ ለአሜሪካ ተላላኪ በመሆን የኢትዮጵያን ልኡዋላዊ ክብር አሳልፎ እንደሚሰጥ ስላመኑ፣
 3. ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ካላት የጂኦ ፖለቲካ ጠቀሜታ በተጨማሪ የኢኮኖሚና  የልማት ትስስር ከቻይና መንግስት ጋር በመጀመሯ ከአሜሪካ መንግስት ጋር የጥቅም ግጭት በመፈጠሩ።
 4. ወያኔ ከኢትዮጵያ በዘረፈው በርካታ ቢሊዮን ዶላር ጎትጓች (Lobbyist) በመቅጠር የምዕራቡን መንግስታት ቀልብ መግዛት በመቻሉ፣ በተቃራኒው ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት ችግሩን ለዓለም ህዝብ ለማሳወቅ ጠንካራ የዲፕሎማ ስራ መስራት ባለመቻሉ፤
 5. ቁጥራቸው ጥቂት ነገር ግን ወሳኝ የሆኑ የአሜሪካ ሹማምንት ከወያኔ ጋር ባላቸው የቆየ የግል ግንኙነትና የጥቅም ትስስር፣ 
 6. ወያኔ ለጌይ፣ ሌዝቢያን እና ለሴጣን አምላኪ ኢሊሚናቲ ተባባሪ በመሆኑ ህወሃትን ወደ ስልጣን በመመለስ ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ክፉ ልማድና ባህላቸውን ለማስፋፋት በቀላሉ ስለሚያስችላቸው፣
 7. አሜሪካ መራሹ የምዕራቡ ጎራ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ምልክትና የአፍሪካ አንድነት (AU) መቀመጫ የሆነችውን ኢትዮጵያን በማፈራረስ የአፍሪካን ህዝብ ቅስም ሰብረው አጠቃላይ አህጉሩን በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ የኢኮኖሚ/ የሃብት ሰቀቀናቸውን ለመወጣት።

በመሆኑም አስመሳይና የተነቃበት አይን አውጣ አጉል ብልጣብልጥ የሆኑት ምዕራባውያን ለእነሱ ዲሞክራሲ፣ ሰብአዊነት፣ ፍትህ፣ እውነት ወዘተ ከጥቅማቸው በኋላ የሚመጣ መሆኑን ከተረዳን ከኛ የሚጠበቀው በቅድሚያ ከኛ ሃገራችንን ከጅቦች ማስጣል ነው። ሃገራችን ከውጭም ከውስጥም  በችግር በተከበበችበት በዚህ ክፉ ጊዜ እኩይ አላማቸውን ለመፈጸም አጋጣሚውን መጠቀም የሚፈልጉ opportunists ብዙ ናቸው። ወያኔ ሞራል የሌላቸው ከሃዲ ወንጀለኞች ሲሆኑ፣ ህወሃት ከተጸነሰበት ቀን ጀምሮ የንፁሃንን ደም ሲያፈስ፣ የኢትዮጵያን ሃብትና ንብረት ሲዘርፍ የኖረ ስጋ የለበሰ ሴጣን ነው። የወያኔ የጥፋት አጋር የሆነው ኦነግ በርካታ ኦሮሞ ወገኖቻችንን በክፉ ጥላቻ የመረዘ፣ ሃገራችንን በሃሰት ትርክት የበከለ የክፉዎች ስብስብ ነው። ተጨቆንኩ ብሎ ሌላን ህዝብ የሚጨቁን በቀለኛ እንጂ የፍትህና የነጻነት ታጋይ አይደለም። ኦነግ ከ1982 ዓ/ም በአሶሳ በንጹሃን አማራዎች ላይ ከፈጸመው ጭፍጨፋ ጀምሮ ይኸው እስከዛሬ ድረስ የአረመኔ ድርጊቱን በመቀጠል እጁ በንጹሃን ደም እንደተጨማለቀ ይገኛል። አሁንም በህይወት ያሉት የኦነግና የወያኔ መስራቾች እኛ የታገልነው መብታችንን ለማስከበር እንጂ ሌላውን ህዝብ ለመበደል፣ ለመግደል፣ ለመጨቆን አይደለም ሲሉ አለመሠማታቸው እስካሁን ድረስ ለሚፈሰው የንጹሃን ደም እና እልቂት ደጋፊነታቸውን የሚያሳይ ሲሆን መጀመሪያም ቢሆን ወደ ትግል የገቡት በበቀልና በእልህ ተነሳስተው፣ ባልጠራ ድንግዝግዝ አስተሳሰብና በፕሮፓጋንዳ ተገፋፍተው እንጂ ለፍትህ፣ ለዲሞክራሲና መብታቸውን ለማስከበር አለመሆኑን ያሳያል። መብት ለማስከበር ጥላቻ፣ በቀል እና ሂሳብ ማወራረድ ምን አመጣው? ችግር ካለም በንግግር ማስተካከል ሲቻል 115 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላትን ታላቅ ሃገር ሲኦልም ቢሆን ወርደን ኢትዮጵያን እናፈራርሳለን ባልተባለ፣ የህዝብ መገልገያ ሆስፒታልና ትምህርት ቤቶችን ባላወደሙ ነበር። 

ስለሆነም ሃገራችንን እንወዳለን የምንል፣ ኢትዮጵያዊ ወገናችን የሶሪያ፣ የሊቢያ እና የየመን እጣ እንዳይደርሰው የምንፈልግ ሁሉ ወገባችንን ታጥቀን ዋጋ እንደከፈሉልን አባቶቻችን እኛም በተራችን ነጻነታችንን በትግላችን ከማረጋገጥ ውጪ አማራጭ የለንም። በሃገራችን እና በወገናችን ላይ ከውስጥም ከውጭም የተከፈተውን ጦርነትና ሃገር የማፍረስ፣ ህዝብን የመበተን የጥፋት ዘመቻ ሁላችንም ባለን ሙያና አቅም የምንችለውን ሁሉ በማድረግ ኢትዮጵያን ከመፍረስ፣ ወገናችንን ከስደትና ከስቃይ መታደግ የግድ ይለናል። ከልማት ህልውና ይቀድማል፣ ሃገራችን ነጻ ከወጣች በኋላ ወደ ልማቷ እንመለሳለን። 

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

ደረጀ ተፈራ

ምንጭ፣

 1. “The Story of the World” (W.B. Bartlett, 2014)
 2. “A Short History of Europe” (Simon Jenkins, 2018/ 2019)
 3. “Civilization – The West and the Rest” (Niall Ferguson, 2011)
 4. “The conquest of Abyssinia” Futuh al-Habasa (Arab Faqih) 2003 
 5. “Travels, Researches, and Missionary Labours During an Eighteen Years” Residence in Eastern Afica (J. Lewis Krapf) pdf
 6. The Protestant Ethic and the sprit of Capitalism (Max Weber) pdf
 7. Aspects of the Rise if Economic Individualism (A criticism of Max Weber and his school by H.M. Robertson, PhD)
 8. “በረራ – ቀዳሚት አዲስ አበባ (1400 – 1887) እድገት ውድመት እና ዳግም ልደት” 2020 ፕሮፌሰር ሀብታሙ መንግስቴ ተገኝ
 9. ወቅታዊ ታማኝ ዜናዎችና የተለያዩ የመረጃ ምንጮች ፣

–//–

__

በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here