spot_img
Thursday, May 30, 2024
Homeነፃ አስተያየትየትግራይ ግጭት ስትራቴጂ ትንታኔ

የትግራይ ግጭት ስትራቴጂ ትንታኔ

ከጴጥሮስ ደጀኔ
ታህሳስ 22 2014 ዓ. ም.

‘የትግራይ ግጭት የመጨረሻ ግብ ምንድን ነው? ያንንስ ግብ ለማሳካት ምን ዓይነት አካሄድ መንግስት መከተል አለበት?’ የሚለውን መሠረታዊ የስትራቴጂ ጥያቄ፤ መንግስት ወደ ትግራይ ከተሞች እንደማይገባ ካሳወቀ በኋላ ሳይሆን ገና ከመጀመሪያው ጀምሮ በዝርዝር ልናስበው፣ በአግባቡ ልንወያይበትና አቋምና አቅጣጫ ልናስቀምጥበት የሚገባ ጥያቄ መሆን ነበረበት። የኢትዮጵያ ሚዲያዎች፣ ምሁሮችም ሆነ የፖለቲካ ተንታኞች ባጠቃላይ መንግስት ስትራቴጂ መርጦ መሬት ላይ ከተወሰነ በኋላ ውሳኔዎችን ከመቃወምና ከመደገፍ (ወይም ውሳኔዎችን ተከትሎ ጥያቄዎችን ከማንሳት) አንድ ደረጃ ከፍ ያለ በስትራቴጂ እርከን ላይ በጥልቀት ማብሰልሰል፣ መተንተን፣  መወያየት እና ከተሳካም አቅጣጫ ለማስቀመጥ መሥራት ይኖርባቸዋል።  

ከዚህ አንጻር የትግራይ ግጭት መቋጫ ሊሆን የሚገባው ተብሎ የሚቀርበው አንደኛው እና አብዛኞች የሚያቀነቅኑት ግብ  ‘ሕወሃትን በጦርነት ትግራይ ውስጥ ገብቶ መደምስስ እና በዛም የትግራይን እና የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ ነው። ሁለተኛውና ጥቂቶች የሚያቀነቅኑት ደግሞ “ሕወሃትን በትግራይ በማቀብ (ወይም contain በማድረግ)  ለኢትዮጵያ አደጋነቱን በመከላከል ሰላምና ደህንነትን ማረጋገጥ ነው።

የመጀመሪያውን ስትራቴጂ የሚደግፉ ሰዎች በተለይ ሕወሃትን መደመሰስ’ ማለት ምን ማለት እንደሆነ በግልጽና ሊመዘን በሚችል መንገድ ሊያስቀምጡት ይገባል። ምክንያቱም ‘መደምሰስ’ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ሊመዘን በሚችል መንገድ ሲቀመጥ ብቻ ነው ይሄ ግብ ሊተገበርና ሊጸና የሚችል (viable & sustainable) መሆን አለመሆኑን መገመት የሚቻለው። የሚደመሰሰው ሕወሃት የትኛው ነው? ታዋቂ ጥቂት አመራሮቹ ናቸው? ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ናቸው? የምክር ቤቱ አባላት እና የስራ አስፈጻሚ  ኮሚቴው ነው? በየደርጃው በእነዚህ ሰዎች ስር ያሉ ቁጥር ስፍር የሌላቸው የመሃል እና የታች እርከን አመራሮችን ነው? መደምሰስ ሲባል የትግራይን ታጣቂ ሙሉ በሙሉ ትጥቅ ማስፈታትንም ይጨምራል? ይሄን ግብ ለማስፈጸም ከዚህ በፊት በነበረው የጦርነት ሂደት – ሠራዊታችን ከተሞችን ሁሉ በተቆጣጠረበት ጊዜ ለምን ሊተገበር አልቻለም? አሁንስ ጦርነቱን ትግራይ ውስጥ በመቀጠል ሊፈጸም ይችላል ብለን እንድናምን የሚያደርገን ምን መሬት ላይ የተቀየረ ነባራዊ ሁኔታ አለ? 

ለእነዚህ ሁሉ (የ ‘viability’) ጥያቄዎች አሳማኝ መልስ እንኳን ቢኖር መንግስት ትግራይ ከተሞች ውስጥ ገብቶ ሕወሃትን ‘ለመደምሰስ’ ቢሞክር ሀገር ላይ ይዞ የሚመጣውን መጠነ ሰፊ አደጋዎችን  ማጤን ግድ ይላል።  እነዚህን አደጋዎች ለመረዳት ጦርነቱ የሚካሄድባቸውን  አራት እርስ በእርስ የተሳሰሩ ግንባሮች በአግባቡ መመለከት ያስፈልጋል። እነርሱም፦ 

 1. በመሬት ላይ በመሳሪያ የሚደረገው ጦርነት 
 2. በዲፕሎማሲው መስክ የሚደረገው ጦርነት
 3. በኢኮኖሚ የሚደረገው ጦርነት እና
 4. የትግራይን ሕዝብ አመለካከትን ወይም ድጋፍን ለማሸነፍ/ለማስቀጠል የሚደረገው ጦርነት ነው።
 1. በመሬት ላይ በመሳሪያ የሚደረገው ጦርነትን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ሠራዊት የትግራይ ከተሞችን ባጭር ጊዜ በሃይል ለመቆጣጠር የሚችልበት ቁመና ላይ ነው ያለው ብለን መገመት እንችላለን። ነገርን ግን ከተሞችን መያዝና ምናልባትም ከፍተኛ የሚባሉ አመራሮችን ማስወገድ ቢቻል እንኳን ልክ እንደ ከዚህ በፊቱ፣ የወያኔ ታጣቂ ግማሹ በየተራራና ሸለቆው ተበትኖ፣ ግማሹ ደግሞ ትጥቁን በየስርቻው ደብቆ እና ከሲቪሊያኑ ጋር ተቀላቅሎ ለዓመታት የሚዘልቅ ሃገሪቷ በየትኛውም መንገድ ልትሸከመው የማትችለው የእነአፍጋኒስታን ዓይነት የሽምቅ ጦርነት እንዳይቀጥል የሚያደርግ ከበፊቱ የተለየ ነባራዊ እውነታ መሬት ላይ አልተፈጠረም። ስለዚህ ጦርነቱን በመሬት ላይ በአሸናፊነት አጠናቆ ትግራይን የማረጋጋት ዕድሉ እጅግ የመነመነ መሆኑ የበፊቱ ተመክሮም፣ የትግራይ ሕዝብ የውስጥም የውጪም አሰላልፈ በግልጽ ያሳየናል። 
 • በዲፕሎማሲው ጦርነት ረገድ የኢትዮጵያ ሠራዊት ትግራይ ቢገባ ትግራይ ውስጥ በሕወሃት አቀናባሪነትም ይሁን በሠራዊቱ እርምጃ ለሚፈጠረው ማናቸውም ጥፋት ሙሉ በሙሉ ተጠያቂነቱ የኢትዮጵያ መንግስት እንደሚሆን ግልጽ ነው። ትግራይ ውስጥ ገብቶ መቆጣጠር…. ሕወሃቶች አንዳንዴ ቁንጽል እውነቶችን ይዘው በአብዛኛው ደግሞ ክስተቶችን እራሳቸው ፈብርከው……… የዘር ማጥፋት፣ የጾታ ጥቃት፣ በረሃብ የመቅጣት፣ የውድመት ወዘተ ውንጀላቸውን አቀነባብረው እንዲቀጥሉ እና በምዕራቡ ዓለም አሰፍስፈው በሚጠብቁ አጋሮቻቸው ታግዘው ሃገሪቷ ላይ የከፋ ማዕቀብ ማስጣል ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደርጃ ተቀባይነት እያገኘ የመጣውን ‘responsibility to protect’ የሚለውን መርህ ተጠቅመው ቀጥታ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ድረስ እንዲሄዱ ዕድል የሚሰጥ እጅግ አደገኛ ስትራቴጂ ነው።  
 • በኢኮኖሚው ረገድ ትግራይ ውስጥ ገብቶ ጦርነት ማካሄድና ቀጥሎም የሽምቅ ውጊያ ውስጥ መዘፈቅ ሃገሪቷ በምንም ዓይነት ልትሸከመው የማትችለው የኢክኖሚ ቀውስ ውስጥ የሚከታት ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል። 8 ወር ባልበለጠ የመጀመሪያው ዙር መደበኛ (conventional) ጦርነት ብቻ 1 ቢሊዮን ዶላር እንዳወጣን ተነግሮናል። ይኼ እንግዲህ ጦርነቱን ትግራይ ውስጥ ብንቀጥል ተያይዞ የሚመጣው የዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ እቀባ የሚያስከትለውን ሰፊ ኪሳራና የውጪ ምንዛሪ ዕጥረት ሳይጨምር ነው። ከዚህም በላይ በጦሩነቱ የተነሳ በትግራይ፣ በአፋርና በአማራ ክልል ከደረሰው መጠነ ሰፊ ውድመት እና በመላው ሀገሪቷ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከፍተኛ ድቀት የደረሰባቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች ለማገገም…. በሠላሙም ጊዜ እጅግ አስቸጋሪና ሰፊ የዓለም አቀፍ እርዳታን የሚጠይቅ የረጅም ጊዜ ከባድ ሥራ እንደሆነ ግልጽ ነው። ይሄ ትልቅ የኢኮኖሚ ፈተና እያለብን በቢሊዮኖች የሚቆጠር ለጦርነት እያወጣን እና ለዓለም አቀፍ ማዕቀብ እርሳችንን አጋልጠን እንግፋ ማለት በኢኪኖሚው መስክ ሃገራችን በፍጹም ልትሸከመው የምትችለው አካሄድ አይደለም።  
 • የሕዝብ ድጋፍን በማግኘት ረገድ የጦርነቱ ትግራይ ውስጥ መግባትና መራዘም፣ ያንንም ተከትሎ የትግራይ ሕዝብ ላይ (በሕወሃት አቀናባሪነትም ጭምር) የሚቀጥለው ስቃይ….. ለሕወሃት ዋነኛ እና ብቸኛ የድጋፍ ማሰባሰቢያና የትግራይ ሕዝብን ስነልቦናን ጠርንፎ ለመቀጥል ዋስትና የሚሰጥ ስትራቴጂ ነው። ከደርግ የኤርትራ ተመክሮም ሆነ ከአሁኑ የትግራይ ጦርነት በግልጽ የምንደርዳው ይሄንኑ ነው። ሕወሃትን በጊዜያዊነት በመደበኛ ጦርነት ብናሸንፍና የተወሰኑ አመራሮችን ብናስወግድ ከጥቂት ጊዜ የአሸናፊነት ስሜት ያለፈ ፋይዳ ለመፍጠር የሚያስችል ምንም ሕዝባዊ መሠረት መንግስታችን ትግራይ ውስጥ የለውም። በተቃራኒው ደግሞ ክልሉን በሠላም አረጋግቶ ለማስቀጠል በማንችልበት የሽምቅ ውግያና  የጥፋት አዙሪት ውስጥ ለመቀጠል አመቺ ሁኔታ ሕወሃት የሚያገኘው የትግራይ ሕዝብን የጥቃትና የወረራ ሰለባ እንደሆነ በቀላሉ እየነገረና ጥፋቶችን እያቀነባበረ ተጠያቂነቱን መንግስት ላይ እያደረገ እንዲቀጥል ዕድል ስንሰጠው ነው።

ስለዚህ በሚሊተሪ፣ በዲፕሎማሲ፣ በኢኮኖሚ እና በሕዝብ ድጋፍ መስክ ይሄንን ጦርነት ስንመዝን ትግራይ ውስጥ መግባት ለኢትዮጵያ ከቁጥጥሯ ውጪ የሆነ እና ልታቅበው የማትችለው ቀውስ ውስጥ የመክተት ዕድሉ ሰፊ የሆነ ስትራቴጂ እንደሆነ እንገነዘባለን። ባንጻሩ ሠራዊታችን ትግራይ ሳይገባ ሕወሃትን ለማቀብ መሞክር በሁሉም ግንባሮች የተሻለ ውጤት የማስገኘት ዕድሉ የተሻለ ነው። 

 1. በሚሊተሪው መስመር መንግስት የአፋርና የአማራ ክልል ማህበረሰባችንን ደህንነት ለማረጋገጥም ሆነ ሕወሃት መሳሪያ ወደ ውስጥ እንዳያስገባ ‘buffer zone’ አድርጎ ከሕወሃት የሚመጣ መደበኛ ጥቃትን ስትራቴጂያዊ ቦታዎችን ይዞ መከላከል እጅግ ያነሰ ዋጋ የሚያስከፍል አካሄድ ነው የሚሆነው።  
 • በዲፕሎማሲው ጦርነት ደግሞ የትግራይ ጉዳይ ሃላፊነት ሙሉ በሙሉ በሕወሃት ላይ እንዲወድቅ ዕድል የሚሰጥ ስትራቴጂ ነው። ይሄንን ለማሳካት መንግስት ያደረገውን እገዳ (blockade)  በቅን ልቦና (in good faith) ማንሳት ይኖርበታል።  ማለትም የባንክ፣ የመብራት፣ የስልክ እና የሰብአዊ ዕርዳታን በአግባቡ ቁጥጥር በማድረግና በመፍቀድ አንድም ሕወሃትንም ሆነ አጋሮቹ መንግስትን የመወንጀል ዕድል መንሳት፣ ሁለትም ሕወሃት በላቀ ደረጀ የሰብዓዊ ቀውሱ ተጠያቂ እንዲሆን ማድረግ፣ ሶስትም መከራ ላይ ያለው የትግራይ ሕዝብ የሚገባውን እርድታና ግልጋሎት እንዲያገኝ ዕድልን ይከፍታል። ባንጻሩ እገዳውን መንግስት ካላነሳ የዲፖሎማሲው ውጤትን እንደበፊቱ የሚያኮላሽ ይሆናል። ሠራዊቱ ትግራይ ውስጥ ስለሌለ ብቻ መንግስት መንግስታዊ ግዴታውን ሳይወጣ የትግራይ ሕዝብ ‘ተቀጥቶ ይግባው’ ዓይነት መልክት ማሰተላለፍ ትልቅ የዲፕሎማሲ ስህተት ይሆናል። 
 • ትግራይ ውስጥ ጦርነቱን አለመቀጠልና ብሎም የሽምቅ ውግያን ማስወገድ ከኢኮኖሚ አንጻር የሚኖረው ፋይዳ ግልጽና ትንታኔ የሚያስፈልገው አይደለም። ከዛ በተጨማሪም ግን እንደሚታወቀው ሠራዊታችን ትግራይን በተቆጣጠረበት ጊዜ ለትግራይ ከሚሰጠው ሰብዓዊ ዕርዳታ ውስጥ 80% የሚሆነው እርዳታ በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት የሚስጥ ነበር። አሁንም መንግስት ግዴታውን በቅን ልቦና መወጣት ቢኖርበትም ያለውን ውስን የኢክኖሚ አቅም ሌሎች ብዙ አስቸኳይ ፍላጎት ያላቸውን ክልሎችን በድሎ ትግራይ ላይ ያልተመጣጠነ ገንዘብ እንዲያፈስ አስገዳጅ ሁኔታ የሚፈጠረው ሠራዊቱ ትግራይ ቢገባ እንደሆነ ሊታሰብ ይገባል። 
 • በመጨረሻም በሕዝብ ድጋፍ በኩል አስፈላጊውን የሚሊተሪ ‘buffer zone’ አድርጎና እገዳውን ሙሉ በሙሉ አንስቶ፣ የድርድርም ይሁን ልክ እንደ ኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ‘no war – no peace’ ጊዜ መውሰድ የትግራይ ሕዝብን ቀስ በቀስ ከሕወሃት ጥርነፋ ለማስወጣት የመጀመሪያውን ዕድል ይከፍታል። 

ስለዚህ መንግስት የዚህ ስትራቴጂ አፈጻጸም ዙሪያ ወሳኝ የሆኑ ነጥቦች ላይ አተኩሮ በጥንቃቄ ሊተገብረው ይገባል። 

ጴጥሮስ ደጀኔ  የኢትዮ ካናዳውያን ኔትዎርክ ቶሮንቶ ቅርንጫፍ ጸሐፊ 

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

2 COMMENTS

 1. As a whole the analysis is positive and constructive but the lifting of restrictions and resumption of the provision of basic services will prolong the political power and life of fascism (TPLF) in Tigray. The period of reflections the TIgray people are given (including the withholding these services) should continue to step up the pressure on the TPLF. It is thought that this strategy along with the creation of the buffer zone will be effective in weakening and alienating the TPLF. As some experts tell, the unique nature of Tigray ethnicity is its fascistic characteristics and normalizing Tigray will be challenging.

 2. Denying basic service to the general population of an entire province is not only morally wrong, but also against international law. Yes, I realize TPLF will misappropriate aid and funds and benefit from such lifting. But, it will not only be immoral to punish civilians but also a will worsen the diplomatic pressure..most likely leading to escalating sanctions. On balance, the government should do the bare minimum to fulfil it’s legal and moral responsibilities while being prepared for a long lasting confrontation.

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here