spot_img
Sunday, May 19, 2024
Homeነፃ አስተያየት"የብሔራዊ የምክክር ጉባኤ" አጀንዳ ላይ ለብሔራዊ ስራ አስፈፃሚ የቀረበ የመወያያ ጽሑፍ

“የብሔራዊ የምክክር ጉባኤ” አጀንዳ ላይ ለብሔራዊ ስራ አስፈፃሚ የቀረበ የመወያያ ጽሑፍ

(በኢዜማ ጽ/ቤት የተዘጋጀ)
ታህሳስ 2014 ዓ.ም.

መግቢያ

እንደሚታወቀው ገዢው ፓርቲ “የብሔራዊ ምክክር ጉባኤ” ለማካሄድ በሚል የኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ( ይህ
ጽሑፍ እስከተደጋጀበት ድረስ ረቂቅ አዋጁ በተወካዮች ም/ቤት እንደደረሰ ልብ ይሏል) በማዘጋጀት ለሕዝብ ይፋ
አድርጓል፡፡ ይህ  “የብሔራዊ ምክክር ጉባኤ” የወቅቱ አጀንዳ ከመሆኑም ባሻገር ፤ የኢትዮጵያን ሀገረ-መንግስት
መገለጫ አዕማዶች ፥  የፖለቲካ ስሪቱን እና የኢትዮጵያን ‘ምስል’ ላይ በረጅም የጊዜ ሂደት ውስጥ ከስር-መሠረቱ
ጀምሮ አሻራውን በጉልህ ሊያሳርፍ እንደሚችል ከግምት ውስጥ በማስገባት ፤ ፓርቲያችን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ
ፍትሕ(ኢዜማ) በዋነኛነተ የቀጣዩ ትውልድ ፓርቲ እንደመሆኑ ይህ “የምክክር መድረክ” ትኩረታችንን መሳቡ
የማይጠበቅ አይደለም፡፡


 በዚህ “የምክክር ጉባኤ” የገዢውን ፓርቲ ዙሪያ ገባውን ትልም ማለትም ‘ዋነኛ ፍላጎቱን'(the real
intention) እና ግብ (the-end goal) በማጤን የወቅቱ አጀንዳ ላይ ለብሔራዊ ስራ አስፈጻሚው
ለመወያያነት የሚያገለግል ይህ መነሻ ጽሑፍ በፓርቲው ጽ/ቤት ዋና አዘጋጅነት እንዲሁም ከገለልተኛ አማካሪዎችና
የሲቪክ ማኅበራት አመራሮች ሐሳብ በማከል ለፓርቲያችን የብሔራዊ ስራ አስፈፃሚ እንደ መወያያ ዶክመንትነት
ያገለግል ዘንድ ተዘጋጅቷል፡፡

ይህ የመወያያ ጽሑፍ ከዚህ ከመግቢያው በተጨማሪ ” አጠቃላይ ዳሰሳና የአስቻይ ሁኔታ ምዘናዎች” ፥ “የሚጠበቁ
የመወያያ አጀንዳዎችና የጉባኤው ፍሬ ተሻሚዎች ” እና በመጨረሻም ” ከኢዜማ የሚጠበቅ አቋም(እንደ አቅጣጯ)”
በሚሉ ሦስት ክፍሎች ተዋቅሮ ቀርቧል፡፡

1. አጠቃላይ ዳሰሳና የአስቻይ ሁኔታ ምዘናዎች

በብሔራዊ ምክክር ላይ የጻፉ የዘረፉ አሳቢያን ካዘጋጇቸው ቁጥር-ስፍር የለሽ ጽሑፎች መነሻ በማድረግም ሆነ ሌሎች
ሀገሮች በተለያየ ወቅትና አውድ ባካሄዱት መሰል መድረኮች  ለመረዳት እንደተሞከረው ማንኛውም መሰል መድረኮችን
ውጤታማ ሊያደርጉ የሚችሉ ግልጽ መመዘኛዎችን በማጤን በቀላሉ የገዢውን ፓርቲ ሊያሰናዳ ሽር-ጉድ እያለለት
ያለውን”የብሔራዊ ምክክር ጉባኤ” በቀላሉ መመዘን ይቻላል፡፡

1.1. ከቅድመ-ምክክር መድረክ ዝግጅት አንፃር

ማንኛውም መሰል ጉባኤ ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገ የምክክር መድረኩ ከመዘጋጀቱ በፊት ስለምክክሩ በራሱ  መምከር
ለዋናው ጉባኤ ውጤታማነት እና ቅቡልነት በእጅጉ አስፈላጊ እንደሆነ የዘረፉ አሳቢያን አጽንኦት ይሰጡታል፡፡


በተለያዩ የሀገራት ተሞክሮም ለመመልከት እንደተቻለው በአብዛኛው ውጤታማ የብሔራዊ ምክክር ጉባኤ  ያካሄዱ ሀገራት
ዋናው የምክክር መድረክ ይወስዳል ተብሎ ከሚገመተው ጊዜ ከግማሽ እጅ ያላነሰ ጊዜ ለምክክሩ አስቻይ ካባቢያዊ
ሁኔታዎችን ለማደላደልና ስለ ምክክሩ አካሄድ  ስምምነት መፍጠር ላይ ትኩረት ሰጥተውት ይመለከቷል ፤ በሌላ
አገላለጽ ስለምከክክሩ የመጫወቻ ሕግ እና ደንብ ቀረጻ ላይ በዚህም፦ አጠቃላይ አላማው ፥ ምክክሩ ስለሚመራበት
አሳላጭ ተቋም እና የአጫዋቾቹ አሰያየም ፥ የምከክክሩ የተሳታፊዎች አካቶ ደርዝ ፥ የምክክሩ ውጤት አተገባበር
ተቆጣጣሪ አሰያየም ወዘተ እንደ መለኪያ ይቀርባሉ፡፡


ሌሎቹን ዝርዝር መለኪያዎች ትተን ከመጫወቻ የሕግና ደንብ ቀረፃ ዝገጅቱን ብቻ ወስደን የገዢው ፓርቲ
አዘጋጀዋለሁ እያለ ያለውን “የብሔራዊ ምክክር ጉባኤ”ን ብንመዝነው የኮሚሽኑን ማቋቋሚያ አዋጅ የማርቀቅ ድርሻ
በገዢው ፓርቲ አመራር በሚዘወረው “ፍትሕ ሚንስቴር” በብቸኝነት መዘጋጀቱ “የምክክር ጉባኤው”
ሳይወለድ-የጨነገፈ(dead-on-arrival) ያሰብለዋል፡፡


ሌላው በቅድም-ምክክር ወቅት ሰፊ ጊዜ እንዲሰጥ በዋነኛነት በዘርፉ አሳቢያን በአጽንኦት የሚመከረው በዋናው
የምክክር ጊዜ ጉባኤው በሚወያይባቸው የተመረጡ አጀንዳዎች የማመጣጠን ፥ የልየታ እና የቅደም ተከተል ሂደት ላይ
ገለልተኛ እንዲሆኑ የሚጠበቁት አጫወቾች የምክክሩ አላማ ግብ ከመምታት አንፃር ጉልህ ድርሻ እንደሚኖራቸው ከግምት
ውስጥ ስለሚገባ ነው፡፡ በገዢው ፓርቲ በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ላይ እንደሚገልጸው የ”ብሔራዊ ምክክር ጉባኤ”ውን
ያሳልጣል የተባለው  ኮማሽን አባላት አሰያየም “በሕዝብ ጥቆማ” ተሰጥቶ በጠ/ሚሩ አቅራቢነት “በሕዝብ ተወካዮች”
እንደሚጸድቅ ይደነግጋል፡፡ ነገር ግን አዋጁ ይህን አኪያሄድ ለተጠያቂነት እና ለምዘና ማለትም፦ “ከሕዝቡ ማን ፦
ማንን ጠቆመ” ፤ “ከተጠቆሙት ውስጥስ በምን መስፈርት ጠ/ሚሩ የኮሚሽኑን አባላት ያጣሯቸው ይሆን” እና ወዘተ
ጥያቄዎችን ለማንሳት የማይመች አካሄድን  እንዲከተል በመደረጉ በገቢረ-ሕግ(de jure) ሆነ
በነቢረ-ሕግ(defacto) የኮሚሽኑን አባላት ሰያሚነት ልክ እንደ ሚኒስትሮች ሹመት ፥ የምርጫ ቦርድ አባላት ፥
እንደ ሁለቱ ኮሚሽኖች(የአስተዳደር ፥ የወሰንና የማንነት እንዲሁም የአገራዊ እርቅ) ሁሉ ለጠ/ሚሩ እንደተሰጠ
በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡

1.2.  በዋናው – የምክክር ጊዜ

የዘርፉ ምሁራን እና አሳቢዎች ሌላው የሚመክሩት  ሀገራት ውጤታማ “የብሔራዊ ምክክር ጉባኤ” እንዲያካሂዱ
ከተፈለገ መሰል መድረኮች የሚሳተፉ ተዋንያን በሰከነ-አዕምሮ ውይይቱን ማካሄድ ይችሉ ዘንድ መሰል ጉባኤዎችን
ሀገራት በአስተማማኝ እና በዘላቂ ሰላሚዊ ድባብ ውስጥ እንዲያካሂዱ ያሳስባሉ፡፡ ኢትዮጵያ ሀገራችን ተገዳም ቢሆን
ገብታ ባለችበት የሰሜኑ ጦርነት ወቅት  ዋናው የምክክር መካሄዱ አጠቃላይ የምክክሩ የሚካሄድበት ድባብም ላይ
ጉልህ ጥያቄን ያጭራል፡፡  በተጨማሪ ባለፈው የድህረ-ምርጫ ግምገማ ሰነድ ላይ እንደተመለከተው ማንኛውም መሰል
የፖለቲካ አጀንደዎች በእንዲህ ባለ ጊዜ መከወናቸው ፤ ” ዜጎች በጦርነት ጊዜ ስለሀገራቸው ሲሉ መንግስታቸውን
ይሰሙታል” የሚለው ያልተጻፈ ሕግ አሁንም ለገዢው ፓርቲ የራሱን አጀንዳዎች ለማራመድ በአንፃራዊት አስቻይ
ሁኔታዎችን  እንደሚፈጥሩለት ቢገመት ስህተት አይሆንም፡፡

1.3. ከድህረ-ምክክር ጊዜ ውጤት አተገባበር አንፃር

በአዋጁ ላይ በግልጽ እንደተደነገገው ገዢው ፓርቲ የሚያዘጋጀውን የ”የብሔራዊ ምክክር ጉባኤ” የሚያስተባብረው
ኮሚሽን በአማካይ የሦስት-ዓመት እንደሚቆይ ይደነግጋል፡፡ በዚህም በጉባኤው የሚጠበቁ ውጤቶች የገዢውን ፓርቲ
ፍላጎት እንደሚያንጸባርቁ ቢጠበቅም በዚህ በአምስት-ዓመቱ የስራ ዘመን ምክር ቤቶቹን ተቆጣጥሮ ያለው ገዢው ፓርቲ
አጀንዳውን በቀላሉ ለማራመድ አስቦ ይህን “የብሔራዊ ምክክር ጉባኤ” የሚያሳልጠውን የኮሚሽን የስራ ቆይታ ጊዜ
ሦስት-ዓመት ማድረጉ በተመሳሳይ በእጅጉ ጥርጣሬን ያጭራል፡፡

በዚህም ከላይ በአጭሩ ከተመለከተው ከሶስቱም የጊዜ ክንፍ  መለኪያዎች አንፃር ገዢው ፓርቲ ሊያዘጋጅ ያለው
የ”የብሔራዊ ምክክር ጉባኤ” ከወዲሁ የእራሱን የፖለቲካ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ(ከዚህ በሗላ በዚሁ ሰነድ ውስጥም
በተመሳሳይ) “ሌላኛው-የብልጽግና- ጉባኤ” ወይም በአጭሩ “የብልጽግና-ጉባኤ” ተብሎ ሊጠራ የሚችል ነው፡፡

2. የሚጠበቁ ዋና ፥ ዋና የመወያያ አጀንዳዎች  እና “የጉባኤው ፍሬ ተሻሚዎች “

ከላይ በክፍል አንድ ስር በግልጽ ለመዳሰስ እንደተሞከረው የዚህን “ሌላኛው-የብልጽግና- ጉባኤ” የመወያያ
አጀንዳዎችን ለይስሙላ በአዋጁ ላይ ከተደነገጉ የጉባኤው አላማ አንፃር ሳይሆን የራሱ የገዢው ፓርቲ ፕሮግራሞች
እና ዲስኩሮች በመነሳት ለመገመት ብዙም አያዳግትም፡፡ ለአብነትም፦
የፌደራሉ የስራ-ቋንቋ ማሻሻያ “የማንነት ጥያቄዎችን” መመለሻ አንቀጾችን በሕገ-መንግስት ውስጥ መሰንቀር
ሌሎች ጥቃቅን አጀንዳዎች(የሰንደቅ-ዓላማ ጉዳዮችን የመሳሰሉ)

የፌደራሉ የስራ-ቋንቋ ማሻሻያን በተመለከተ “ሌላኛው-የብልጽግና- ጉባኤ” ከዚህ አላማ አንፃር ገዢው ፓርቲ
በፕሮግራሙ ላይ እንዳሰፈረው ከአማሪኛ በተጨማሪ ሌሎች የዘውጌ ቋንቋዎችን(አፋሪኛ ፥ ኦሮሚኛ ፥ ሶማልኛ እና
ትግርኛን) በፌደራሉ የስራ ቋንቋነት እንዲካተቱ በጉባኤው በኩል “ምክረ-ሐሳብ” እንደሚያቀርብ ይገመታል፡፡
ሌላው”የማንነት ጥያቄዎችን” መመለሻ አንቀጾችን በሕገ-መንግስት ውስጥ ከመሰንቀር አንፃር ‘በጎንደሬ-አማራዎች’
ጥያቄ የሚነሳባቸውን የምዕራብ-ትግራይ አካባቢዎች ወደ ከልል ሦስት ለማካለል አሳቻይ ሁኔታን በሕዝብ ውሳኔ
ለማድረግ በሚያመች መልኩ ፤ ለፌደሬሽን ምክር ቤት ዘርዘር ያለ ስልጣን የሚሰጥ ድንጋጌ በሕገ-መንግስቱ
እንዲሰነቅር በተመሳሳይ “ምክረ-ሐሳብ” እንደሚያቀርብ ይገመታል፡፡


ሌሎቹን ንደፈ-ሐሳባዊ አገራዊ አጀንዳዎችን ትተን ከላይ ከተመለከተው ሁለት ግቦች አንፃር ብቻ’ንኳ “ጉባኤውን”
ብንገመግመው አሁንም በተመሳሳይ የገዢው ፓርቲ ፕሮግራሞች ማስፈጸሚያ ነው ሊባል ይችልል፡፡ ለምን ከተባለስ!?
የፌደራሉ የስራ ቋንቋ በማብዛት ገዢው ፓርቲ በዘውጌ ክሌሎች ላይ ያለውን የማኅበራዊ መሰረት ዳርቻውን ለማስፋት
በማለም እና እንዲሁም “የትግርኛን ቋንቋም” በማካተት ፤ ገዢው ፓርቲ በአለም-አቀፍ ማኅበረሰብ ዘንድ
እየደረሰበት ካለው ውግዘት አንፃር የእራሱን  “እድፍ ለመታጠብ” ያስችለው ዘንድ ነው ቢባል ግምት አይሆንም፡፡
በተመሳሳይ የምዕራብ-ትግራይን ወደ ‘አማራ ክልል’ በማካለል “ለአማራ ሕዝብ” በአጠቃላይ፤ በተለይ ደ’ሞ
በአምቻ-ፖለቲካ መሳሳብ ወትሮውንም ፍንደቃ ላይ ላሉት “ለጎንደሬ-አማራዎች” የተወረወረ “ዕርጥባን” ተደርጎ
ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡ በእርግጥ ይህ በራሱ ሌሎች ተዛማጅ ውጤቶች(trickling-effect) እንደሚኖሩት
ይታመናል፡፡ በዚህም እኚህ ተዛማች ውጤቶችን(ለአብነት፡- “የአማራ” ሕዝብን በፍርፋሪ በመደለል ይበልጥኑ ወደ
ዘውግ ፖለቲካ በጥልቀት የመዝመፈቅ ፤ ይህም በቀጣይ በረዥም የጊዜ ሂደት “በክልሉ አንድነት” ላይ ሊኖረው
የሚችለውን ተጽእኖ) በሚመለከት እራሱን የቻለ አንድ የመወያያ አጀንዳ እንደሚወጣው ከግምት ውስጥ ይግባ::
ከተመረጡ ዋና ፥ ዋና አጀንዳዎች ከላይ ለመመልከት እንደተሞከረው ሙሉ በመሉ በሚቻል መልኩ ለገዢው ፓርቲ
የማኅበራዊ መሠረተ-ዳርቻ ማስፊያ አስቻይ ጉባኤ እንደሚሆን ፤ “የዕርጥባኑ-ተሻሚዎች” የሆኑቱ የገዢው ፓርቲ
በአንድም በሌላ መልኩ ቅቡልነቱን የሚቀዳባቸው ዘውጌ ክሌሎች በመሆናቸው ፤ የምክክር መድረኩን ከላይ በክፍል
አንድ ላይ “ሌላኛው-የብልጽግና- ጉባኤ” ወይም በአጭሩ “የብልጽግና-ጉባኤ” ተብሎ ሊጠራ የሚችል ነው የሚለውን
ይበልጥኑ የሚያስረግጥልን ነው፡፡

3. ማጠቃለያና ከኢዜማ የሚጠበቅ አቋም(እንደ አቅጣጯ)

በቀደሙት ክፍሎች  በተዳሰሱት ግልጽ መመዘኛ ነጥቦች እና የመጨረሻ ግቦች አንፃር ይህ ሊካሄድ ያለው “የብሔራዊ
ምክክር ጉባኤ” ወይንም “ሌላኛው-የብልጽግና- ጉባኤ” ለአዜማ “ምንም” ነው ቢባል ከቶውንም ጨለምተኝነት ሊሆን
አይችልም፡፡ በመሆኑም ፓርቲያችን ኢዜማ ከተመሰረተበት ራዕይ አንፃር “ለሠላማዊ መድረኮች” ባለው አዎንታዊ አስቤ
እና በሌሎች ተገማች ምክንያቶች ሲባል ብቻ “በጉባኤው” እንደሚካፈል ታሳቢ ይደረጋል፡፡

በዚህም ከላይ ከተጠቀሱት ከጉባኤው  ከሚጠበቁ ግብ አንፃር የፓርቲያችን አባላትና ደጋፊዎች በጉባኤው ማብቂያ ላይ
<< ፓርቲያችን ኢዜማ ምን ለማግኘት በዚህ “ጉባኤ” ተሳተፈ? >> የሚል ጥያቄን እንደሚያጭሩ ከመገመቱ አንፃር
፤ ይህን ታሳቢ ያደረገ ቢያንስ ፥ ቢያንስ “ብዬ ነበር” ለማለት በሚያስችል ሁኔታ ፤ ገዢው ፓርቲ በዚህ
“የጉባኤ” ሂደት በእያንዳንዱ ምዕራፎች የዘርፉ ምሁራን እና አሳቢዎችን ምክር ችላ ባለ እና በማን-አለብኝነት
እየሄደባቸው ያለውን በሕጸጽ የተሞሉ ሂደቶችን ፤  አሁንም ፥ አሁንም በተደጋጋሙ ጠንካራ መግለጫዎች ማሳሳብ
በእጅጉ ይጠበቃል፡፡

__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

1 COMMENT

  1. ይህን የኢዜማ ኣቋም፥ በጭራሽ፥ በጭራሽ የማልቀበለው ነው። ምክንያቱም፥ እንደኦሮሞ ህዝብነቴ፥ ለህዝባችን ማደጊያና መበልጸጊያ፥ ኣማራጭ የሌለው የያዝነው መንገድ ብቻ ነው። ይህ የብሄር ፌደራሊዝም፥ በዩኬ፥ በህንድ፥ በራሽያ፥ እንዲሁም በጀርመን እየተጠቀሙበት፥ ትልቅ ውጤት፥ ማለትም፤ የኢኮኖሚ ዕድገት ኣቀዳጅቷል።
    ስለ ሰንደቅ ዓላማም ካወሳችሁ፤ ይህ ይቀየር፥ ወይም ኣይቀየር የሚያስብል ነገር ከተፈጠረ፤ ምክንያቱ በጥልቀት ተመርምሮ እንጂ፥ ማንም ጎጆ በወጣ ቁጥር፥ የቤት እድሳት፥ ምርቃት፥ እየተባለ ገንዘብ መሰብሰቢያ ወይም ማንቀዋለያ ኣይሆንም። ይህም ቢሆን፥ ለተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ በኣጀንዳ ተነጋግሮበት የሚጸድቅ ይሆናል።
    ለነገሩ፤ ሁለቱም ሃሳቦቻችሁ፤ ቀርበው፥በቀላሉ የሚመለሱ ናቸው።
    ያንድ ህብረተሰብ ቋንቋ፥ የማንነቱ መገለጫ፥ ባህሉን ማስተዋወቂያ፥ ሙዚቃውን፥ ልቅሶውን፥ ምግቡን፥ ጭፈራውን፥ ስነ ጥበቡን፥ ስነ ግጥም ብሎም በቴክኖሎጂ ያካተተ ተንቀሳቃሽ ፈልምን ያዳብርበታል። ማንንም ኣይጎዳም። የራሱን ህዝብ ግን ይጠቅማል። ቋንቋ፥ ታሪክን፥ ባህልን፥ ዕምነትን፥ ብሎም ውስን ጂዖግራፊያዊ ድንበርን ያቅፋል። የዚያ ህብረተሰብም የኢኮኖሚ ማደጊያ መንገዱም ይበሰራል።ይታወቃል!!
    በኔ በኩል፤ ባትነካኩት ይመረጣል!! እንደወግ ይዘነው እንቅረብ ብትሉ መልሱ ተነግሯችኋል ኣትልፉ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here