ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ፤ ታኅሳስ 30 2014
“የሕግ የበላይነት ሲጠፋ፤ በሰዎች ግብታዊነት የምንገዛ እንሆናለን” ትላለች ደራሲዋ ቲፋኒ ማዲሰን (Tiffany Madison)
አንድ ሃገር ሰላም ሊኖራት፤ ነፃነቷም ሊከበር፤ እና የዜጎቿ መብት ሊከበር የሚችለው፤ በሃገሪቱ ላይ የሕግ የበላይነት ሲሰፍን ብቻ ነው። የቀድሞዋ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርገሬት ታቸር፤ በሕግ የበላይነት የማይተዳደር ሃገር፤ ዜጎቹ ሙሉ ነፃነት ሊኖራቸው አይችልም ይሉ ነበር። ሃገራችን ለዘመናት በጦርነት እና የርስ በርስ እልቂት የታመሰችው፤ የሕግ የበላይነት ባለመስፈኑና፤ በተለይም ባለሥልጣኖቻችን ለሕግ ተገዢ ያለመሆናቸው ነው። የሕዝብን ሰቆቃ ሊያቆም የሚችለው ሁሉም ዜጋ፤ ከሊቅ እስከደቂቅ በሕግ ጥላ ሥር ሲኖር ብቻ ነው።
ባለፉት 27 የወያኔ የግዛት ዓመታትም ትልቁና መሰረታዊ ችግራችን፤ በገዥዎቻችን “በጎ ፈቃድ” እንጂ በሕግ የማንተዳደር መሆናችን እንደነበር ልብ ሊባል ይገባል። ዛሬም ላለንበት ጦርነት፤ ለተፈፀመው እልቂት፤ ግፍ እና ውድመት ምክንያቱ፤ ሕግን አለማክበር እና፤ “ሕግ እኛን አይገዛንም” ብለው በአመፁ ሃይሎች በተከፈተብን ጦርነት ነው። በተለይ፤ ሃገርን የሚያስተዳድር ኃይል፤ ለሕግ ተገዥ ካልሆነ፤ በሌላው ላይ ሕግን ተፈፃሚ ሊያደርግ አይችልም።
የዚህን ዓመት የገናን በዓል አስከትሎ መንግሥት የወሰደው “የምህረት እርምጃ” ሕግን የጣሰ ብቻ ሳይሆን፤ የሕዝብን ሰቆቃ እና ጉዳት ከግምት ያላስገባ፤ ግብዝነት የተምላበት እና ሕዝብን የናቀ እርምጃ ነው። በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በሕዝብ ያላቸውን ከፍተኛ የፖለቲካ ድጋፍ (political capital) አርክሰው የመነዘሩበት መሆኑ በብዙዎቻችን ላይ ሊጠገን የማይችል ስብራት ፈጥሮብናል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በሃገራችን ፍትሕ የለም በሚል፤ ባለሥልጣናት ወንበራቸውን ተጠቅመው፤ የሕግ ጥሰት እንደሚፈጽሙ ከተናገሩ ከአንድ ቀን በኋላ፤ እራሳቸው፤ ሕግ መጣሳቸው፤ አስገራሚ እና አሳዛኝ ክስተት ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለመንግሥታቸው ሃላፊነት የሰጠው፤ ሃገሪቱን በሕግ የበላይነት እንዲያስተዳድሩ እንጂ በምህረት እንዲያስተዳድሩ አይደለም። በምህረት ለማስተዳደር ከፈለጉ፤ ማስተዳደር ያለባቸው ቤተ ክርስቲያን እንጂ ሃገር አይደለም። ከሕግ አንፃር፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለማንም ምህረት የማድረግ ሥልጣን የላቸውም። እነ እስክንድር ነጋ፤ ጃዋር መሃመድ፤ እንዲሁም እነ አቦይ ስብሃት፤ በፍርድ ቤት ጥፋተኛ የተባሉ ሰዎች አይደሉም፤ ጥፋተኛ ያለተባሉትን ሰዎችስ፤ “ይቅርታ አድርግያለሁ” ማለት ተገቢ ነው ወይ? በተፈቺዎቹስ ዘንድ ተቀባይነት አለው ወይ? የሚሉ ጥያቄዎችንም ያስከትላል። አንድ ግልጽ መሆን ያለበት ነገር አለ። አቃቤ ሕግ ማንኛውንም ተጠርጣሪ ያለመክሰስ ወይም ክስን የማቋረጥ ሕጋዊ ሥልጣን አለው። ነገር ግን፤ በመንግሥት በኩል የተገለፀልን እስረኞቹ “ምህረት ተደረገላቸው እንጂ” ዓቃቤ ሕግ ክሱን አቋርጦ እንዲፈቱ ተደረገ የሚል አይደለም። ይህንን ትክክለኛ አሰራር ከመከተል ይልቅ፤ መንግሥት ከሚደርስብኝ የፖለቲካ ወላፈን ይጠብቀኛል በሚል ግምት፤ ስለይቅርታ ሰብኮን፤ “ምህረት” አደረግኩ የሚል የስላቅ ድርሰት ግቶናል። እዚህ ላይ ነው በመንግሥት በኩል ሕግ ተጥሷል የምለው።
አንድ ተጠርጣሪ፤ ጥፋቱ በፍርድ ቤት ከተረጋገጠ በኋላ፤ ላጠፋው ነገር ይቅርታ ይደረግልኝ ብሎ ማምልከቻ በማቅረብ፤ ማመልከቻው ለቦርድ ቀርቦ፤ ቦርዱ የጠያቂወን ማመልከቻ ተመልክቶ ለፕሬዝዳንቷ አቅርቦ፤ ፕሬዝዳንቷ ያፀድቃሉ፤ ከሕግ አኳያ “የምህረት አሰጣጥ ሂደቱ” ይህንን ይመስላል። በህገ መንግስቱ አንቀጽ 71 ቁጥር 7 መሰረት፤ በህግ ይቅርታ መስጠት ሥልጣን የተሰጠው ለፕሬዝዳንት እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትር አይደለም። በትላንትናው የምህረት ውሳኔ ግን ይህንን ሂደት አልጠበቀም። በተለይ በአቶ እስክንድር መዝገብ የተከሰሱት ሰዎች ምንም ዓይነት የሕግ ጥሰት ሲፈጽሙ፤ በአደባባይ የታየ መረጃ የለም። ዓቃቤ ሕግ 21 ምስክሮች አቀርባለሁ ብሎ፤ በተደጋጋሚ ምስክሮቹን ላለማቅረብ ከፍርድ ቤት ጋር አታካራ ውስጥ ሲገባና የፍርድ ቤት ተእዛዝ ሲጥሥ ነው የታዘብነው። ከዛም አልፎ፤ ስድስት ምስክሮችን ብቻ ነበር ያቀረበው። አጠቃላይ ሂደቱን ስናጤን፤ መጀመሪያውኑ የእነ አቶ እስክንድር ነጋ መታሰር፤ ፖለቲካዊ እንጂ ከወንጀል ጋር አለመያያዙን ነው የሚገባን። በእነ አቶ ጃዋር መዝገብ የተከሰሱት ደግሞ ቢያንስ፤ የራሳቸው ያልሆን ንብረት ጥሰው መገባታቸውን በዛም ምክንያት የአንድ ፖሊስ ሕይወት መቀጠፉና ንብረት በመውደሙ፤ ሊያስከሣቸው የሚችል ወንጀል እንዳለ ግልጽ ነው። የእነ አቦይ ስብሃት ክስ ደግሞ ከሃገር ክህደትና፤ በመከላከያው ሰራዊት ላይ ከተፈፀመው ግፍ ጋር በነፍስ አጥፊነት የተከሰሱበት ሁኔታ ነው ያለው።
ከዚህ አንፃር፤ መንግስት የወሰደው “የምህረት እርምጃ፤ ሕገ መንግሥቱን የጣሰ ነው። የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 28 ቁጥር 1 እንዲህ ይላል፤ “ኢትዮጵያ ባጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና በሌሎች የኢትዮጵያ ሕጐች በሰው ልጅ ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ተብለው የተወሰኑትን ወንጀሎች፤የሰው ዘር የማጥፋት፣ ያለፍርድ የሞት ቅጣት እርምጃ የመውሰድ፣ በአስገዳጅ ሰውን የመሰወር፣ ወይም ኢሰብዓዊ የድብደባ ድርጊቶችን በፈጸሙ ሰዎች ላይ ክስ ማቅረብ በይርጋ አይታገድም፡፡ በሕግ አውጪው ክፍልም ሆነ በማንኛውም የመንግሥት አካል ውሳኔዎች በምሕረት ወይም በይቅርታ አይታለፉም፡፡” (ሰረዝና ድምቀት የተጨመረ)። ታድያ፤ እነዚህ በሰው ልጆች ላይ ከፍተኛ ወንጀል በመፈፀም የተከሰሱ ሰዎችን፤ መንግሥት እንዴት በምህረት ሊፈታ ይችላል?
የሕዝቡን ቁጣ ለማብረድ በሚመስል መልኩ፤ መንግስት ለእስረኞቹ የሰጠውን “ምህረት” ይፋ ከማድረጉ በፊት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገና በዓል መልእክታቸው፤ ቀልብን በሚስብ ንግግራቸው ስለይቅርታና ምህረት በመስበክ ስሜታችንን ለሟሟሸት ሞክረዋል። ጀግና ሕዝብ መሃሪ ነው ብለውናል። ጀግና ሕዝብ ግን ሕግ አክባሪ እንደሆነና መሪዎቹም የሕግ ተገዢ እንዲሆኑ መሻቱን ግን አልነገሩንም። መንግሥትና ሕዝብ የተጎጂዎችን ዕዳ ይሸከማሉም ብለውናል፤ ጥያቄው እንዴት የሚል ነው? የመንግስትን የሕግ ጥሰትንስ እንዴት እንሸከመው የሚል ጥያቄም ያስከትላል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ ለሃገር የገቡት ቃል፤ የሕግ መንግስቱንም ሆነ የሃገሪቱን ማንኛውም ሕግ ቃሉንም፤ መንፈሱንም በማክበር ሃገራችንን እንደሚያስተዳድሩ ቢሆንም፤ ሕገ መንግስቱን እና ተጓዳኝ ሕጎችን በማን አለብኝነት በመጣስ ልባችንን እንዳይጠገን አድርገው ሰብረውታል። ይህንን ጉዳይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሊመረምር እና፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ሊጠይቅ ይገባዋል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ እውነተኛ የሕዝብ ተወካይ መሆኑንም ማስመስከርና ለሕዝብ ማረጋገጥ የሚችለው እንዲህ ዓይነት ሕግ ጥሰቶች ላይ፤ ተጠያቂነት እንዲኖር በማድረግና ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ ሊሆን ይገባል። ሕግ ሲጣስ እየተመለከተ፤ አብሮ የሚያጨበጭብ የሕዝብ ተወካይ ምክር ቤት አባል፤ በምንም መልኩ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም።
በእኔ እይታ፤ ይህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ በሰሩት በጎ ስራ ላይ፤ ጥቁር ነጥብን የጣለ፤ የሕዝብን ስሜት የጎዳና በመንግሥት ላይ ያለውን እምንት እጅጉን የሸረሸረ ነው። የሕግ የበላይነት፤ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የማዕዘን እራስ ነው። የሕግ የበላይነት ሲጣስ እና የምንተዳደረው በግለሰቦች ግብታዊ ስሜት ሲሆን፤ ሃገር ፍፁም ሰላም ልትሆን አትችልም፤ የሕዝብ ሰቆቃ አይቆምም፤ ሙስና እና በሥልጣን መባለግም የሃገሪቱ መገለጫ መሆኑ ይቀጥላል። የዛሬው “ምህረት” አሁንም ሕዝብን በግፍ ለሚገድሉ፤ ንብረት ለሚያወድሙ፤ በሙስና ለተጨማለቁ፤ እና ስድ ለሆኑ ባለሥልጣናት የሚያስተላልፈው መልዕክት፤ ‘ወንጀል መስራታችሁን፤ ጥፋታችሁን፤ ቀጠል፤ ስትያዙ፤ በምህረት ትፈታላችሁ የሚል ነው። ይህ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚገባ ነውን? እንዲህ ዓይነት ሕገ ወጥ አሰራር በሃገራችን ፍትሕ የሚያሰፍንስ ነውን? ስለፍትሕ አለመኖር ከቀናት በፊት የሰበኩን ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ለእኔ ያረጋገጡልኝ፤ በሃገራችን ፍትሕ አለመኖር ቀዳሚ ተዋናይ መሆናቸውን ነው። እጅግ በጣም ልብ የሰበረ እና፤ ሃገርን እጅግ ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል ሃላፊነት የጎደለው ሕገ ወጥ ውሳኔ ነው። ይህ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የፈፀሙት የማይጠገን ስብራት ነው።
ቸሩ እግዚአብሄር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ።