ቦርከና
ታህሳስ 30 2014 ዓ. ም.
በዚህ ሳምንት ሃሙስ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ካቢኔዎቻቸውን ሰብስበው የታላቁ ህዳሴ ግድብ እካባቢ ባደረጉት የመቶ ቀናት የስራ አመራር ግምገማ ማጠቃለያ ላይ በሰጡት አስተያያት ብዙ ሪፎርም ተደርጎበታል የተባለውን የፍትህ ስርዓት አይረባም በሚል አጣጣሉ፡፡ ለማስረጃ ይሆናል ብለው ካነሷቸው ጉዳዮች አንዱ በሰማኒያዎቹ እድሜ ውስጥ ያሉ ሰዎችን (የትግራይ ተወላጆች የሚል ነገርም አንስተዋል) ያላግባብ እየተሰቃዮ ነው በሚል የፍትህ ስርዓቱ ገና ብዙ ይቀረዋል ሲሉ አጣጣሉ፡፡
አርብ በኢትዮጵያ የገና በዓል ቀን አቶ ስብሃት ነጋን ጨምሮ በጦር ሜዳ የተያዙ ከፍተኛ የህወሓት አባላት ከእስር እንደተፈቱ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ለሕዝብ አስታወቁ፡፡ በተጨማሪም በማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በማነሳሳት በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎችን በሻሸመኔ እና በአካባቢው ባሉ ከተሞች አስገድሏል በሚል የሚተቸው ጽንፈኛ የኦሮሞ ብሔረተኛ ጃዋር መሃመድም እንዲሁም ፍትሃዊ ባልሆነ ሁኔታ በአጃቢነት ታስሯል የሚባለው እስክንድር ነጋም እንደተፈታ ተሰማ፡፡
የህወሓት የጦር ወንጀለኞች እና ጃዋር መፈታት በማህበራዊ ሚዲያዎች በስፋት እያነጋገረ ሲሆን ህዝባዊ ቁጣም እየቀሰቀሰ እንደሆነ ከተለያዮ የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የወሰዱት እርምጃ የአእምሮ ጤናቸውን ጥያቄ ውስጥ ከሚያስገቡ ጀምሮ አሁን ያለውን ገዢ ፓርቲ በፊታውራሪነት ሰርቷል ከሚባልው የቀድሞ ኦሮሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ድርጂት አመራሮች የፓለቲካ ሽፍጥ ጋር የሚያያይዙ አስተያየቶች ተሰተዋል፡፡
ቅዳሜ እለት የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ስለተወሰነው ውሳኔ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የተፈቱበት አገባብ በምህረት ሳይሆን ክሳቸው ተቋርጦ እንደሆነ የተናገሩት ሚኒስትሩ መፈታታቸው ኢትዮጵያ ልታደረግ ላስበችው ብሔራዊ ምክክር አካታችነት አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ ነው ብለዋል፡፡
ሆኖም የመንግስት ውሳኔ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጽንፈኛ የሚባሉ ደጋፊዎች ጭምር ግራ ያጋባ እንደሆነ በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰጡ አስተያየቶች ይጠቁማሉ፡፡
እስረኞቹ የተፈቱት የአሜሪካ የምስራቅ አፍሪካ ልዮ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልት ማን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን በአዲስ አበባ አግኝተው አናግረዋቸዋል ከተባለ በኋላም ነው፡፡