ኪዳኔ ዓለማየሁ
ራዕይ፤ ዓላማና እቅድ፤
ለኢትዮጵያ ተገቢ የሆነ ሕገ መንግሥት ማዘጋጀቱና ተግባራዊ የማድረጉ ራዕይ ውድ ሐገራችን ከጽንፈኛነት፤ ከዘረኛነትና ከጭቆና የተላቀቀ ኢትዮጵያዊነት፤ ሰላም፤ ጸጥታ፤ አንድነት፤ እውነተኛ ዲሞክራሲ፤ ሕብረት፤ መከባበር፤ ፈጣን ልማት፤ ወዘተ. የሰፈነባት ሐገር እንድትሆን ለማረጋገጥ ነው። ይህ ራዕይ ስኬታማ እንዲሆን፤ በአጭር ጊዜ (1 ዓመት) ብቁ በሆኑ ባለሞያዎች የተሟላ ረቂቅ ሕገ መንግሥት እንዲዘጋጅና በመጀመሪያ ደረጃ አንድ ዓለም አቀፍ ጉባኤ በጥልቀት እንዲመለከተው ማድረግ፤ ከዚያም፤ አስፈላጊው ማሻሻል ተከናውኖ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመላው ሕዝብና ለሚመለከታቸው ድርጅቶች ቀርቦ እንዲመረመር በመጨረሻም ተቀባይነት በሚኖረው ብሔራዊ ጉባኤ ሕገ መንግሥቱ እንዲጸድቅ ሆኖ በሚቀጥሉት ዓመታትም በሕገ መንግሥቱ መሠረት በሚመረጥ ምክር ቤት እንደ አስፈላጊነቱ ማሻሻል ይቻላል።
የአሁኑ ሕገ መንግሥት ሰቆቃዎች፤
እንደሚታወቀው፤ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ላይ ሰፍኖ የሚገኘው ሕገ መንግሥት ሕዝቡን በቋንቋና በጠባብ ዘረኛነት በተመሠረተ የክልል ሥርዓት ከፋፍሎ ባስከተለው የእርስ በርስ መናቆር፤ አለመተማመን፤ መከፋፈል፤ አለመተባበር እጅግ አሰቃቂ መጠነ ሰፊ ስቃይ እያስከተለ ነው። በዘረኛነት ምክንያት በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት ብዙ ሺዎች ኢትዮጵያውያን ተገድለዋል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ተፈናቅለዋል። እጅግ ብዙ ሰዎች በተለይ ሴቶችና ሕጻናት እየተሰቃዩ ነው። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከሕገር ለመሰደድና በታሪክ ያስተናግዷቸው በነበሩ በዓረብ ሐገሮች ጭምር በዝቅተኛ ደረጃ ለመኖር ተገድደዋል። በጠባብ ጎሰኛነት መለያየት ምክንያት እጅግ ብዙ ንብረት ወድሟል። የዘረኛነቱ ጠንቅ፤ ፋሺሽት ኢጣልያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ዘመን ከፈጸመችው አሰቃቂ የጦር ወንጀል ብሷል።
ኤርትራ ከእናት ሐገሯ ከኢትዮጵያ ተገንጥላለች። በአሁኑ እኩይ የሕገ መንግሥት አወቃቀርና ሥርዓት፤ “ክልል” የተሰኙ አንዳንድ አካባቢዎችም ለመገንጠል እያኮበኮቡ ነው። ደቡብ ክልል ውስጥ ከሚገኙ አካባቢዎች ውስጥም ወደ ክልልነትና የመገንጠል አባዜ ለመዝቀጥ አቅጣጫ እያንጸባረቁ ነው።
ያሁኑን ሕገ መንግሥት ኢትዮጵያ ላይ የጫኑት ተጠያቂዎች አንደኛው ዓላማቸው፤ ሕዝቡ በዘረኛነት እርስ በርስ እንዲናቆርና እንዲጨፋጨፍ ስለ ነበር ያለሙት ሁሉ እየተሳካላቸው ነው።
ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ልዩ የሚያደርጋት፤ ሕዝቧ በኢትዮጵያዊነት አንድነት የሚተባበርና የማይደፈር መሆኑን በነአጼ ካሌብ ዘመነ መንግሥት ከዚያም በአድዋ የጦርነት ድል ያስመሰከረች መሆኗ ነው። ያሁኑ ሕገ መንግሥት ግን ኢትዮጵያን በአሳፋሪና በውዳቂ ዘረኛነት ከፋፍሎ ሊያስደፍረን ነው። የባሰ ሊያጫርሰን ነው።
በዘረኛነት ሥርዓቱ ከባድ ድክመት ምክንያት ኢትዮጵያ በድህነትና በሙስና ታዋቂ ሆናለች። በተጨማሪም፤ በብዙ ዓለም-አቀፋዊ መስፈርቶች ኢትዮጵያ የዓለም ጭራ ሆናለች። ተመጽዋች ሆናለች።
http://hdr.undp.org/sites/all/themes/hdr_theme/country-notes/ETH.pdf
ለበለጠ ዝርዝር ከዚህ በታች ያሉትን መመልከት ይጠቅማል፤
https://ecadforum.com/Amharic/archives/19630/
https://www.nytimes.com/2019/01/03/opinion/ethiopia-abiy-ahmed-reforms-ethnic-conflict-ethnic federalism.html
ሥልት፤
ለኢትዮጵያ ተገቢ የሆነ ሕገ መንግሥት ለማርቀቅ የመጀመሪያ እርምጃ መሆን የሚገባው፤ ለተግባሩ ብቁ የሆኑ የሕግ፤ የኢኮኖሚ፤ የማሕበራዊ፤ ወዘተ. ባለሞያዎች በመምረጥ አንድ ግብረ ኃይል ማቋቋም ነው። ግብረ ኃይሉም በተቻለ
ፍጥነት፤ ከተቻለ በ6 ወሮች ውስጥ ተግባሩን አከናውኖ በሚለጥቁት 6 ወሮች ውስጥ በሚከናወን አንድ ዓለም አቀፍ ጉባኤ በጥልቀት እንዲመረመር ማድረግ ነው። ከዚያም ሌላ ተገቢ የሆነ ግብረ ኃይል በማቋቋም፤ በሚለጥቀው አንድ ዓመት ውስጥ፤ በኢትዮጵያ እስከ ወረዳ ድረስ በሚከናወን ምክክር፤ የሚመለከታቸውን ድርጅቶች በሙሉ በማሳተፍ ስለ ረቂቁ ሕገ መንግሥት የሚገኘውን ሀሳብ ማከማቸትና በሐገር ለሚከናወነው 2ኛ ጉባኤ በማቅረብ ጥልቀት ያለው ውይይት እንዲከናወንበትና እንዲወሰንበት ማድረግ ነው።
የአዲሱ ሕገ መንግሥት ባለቤት፤
በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለራሱ የሚበጀውን ሕገ መንግሥት በጥልቀት መርምሮ የሚያጸድቀውና በሚያስፈልግበት ጊዜም እንደ አስፈላጊነቱ የሚሻሻልበትን ሥርዓት ይወስናል።
__
በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
ሕገ መንግሥቱን በወቅቱ ለማስተካከል ወይንም ለመቀየር ባለመቻላችን፤ ገዢው ፓርቲም ፈቃደኛ ባለመሆኑ፤ ተፎካካሪ ፓርትዎችም ፍርሃት ስለያዛቸው መሰለኝ፤ ሕገ መንግሥቱን መሰረት ያደረገ የትግራይ ጦርነት ተካሄደ፤ በተከታታይ የዐማራው ሕዝብ በማንነቱ ተጨጨፈ፤ አሁን ደግሞ ልክ ገምተነው እንደ ነበረው፤ ህወሓት እገነጠላለሁ ብሎ አስፈራራን። የትግራይ ሕዝብ በአስቸኳይ እኛ ከኢትዮጵያ ውጭ አናስብም እንደሚል ተስፋ አለኝ።
ወንድማችን አቶ መኮነንን ዶያሞና ተባባሪዎቹ ግሩም የሆነ፤ ለውይይት የሚረዳ የሕገ መንግሥት ረቂቅ አቅርበውልናል። አቶ መኮንንን ይባርክህ እያልኩ አባካችሁ ሁላችሁም ድጋፋችሁን ስጡ እላለሁ። ገዢው ፓርቲና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ስለ ሕገ መንግሥት የሚወያዩበት ወቅት አሁን ካልሆነ መቸ ሊሆን ይችላል? ቸር ያሰማን፤ አክሎግ ቢራራ
ዶ/ር አክሎግ፤ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት መለወጥ ያሚያስፈልገው መሆኑን ስለ ደገፍክ ከልብ አመሠግናለሁ፡፡ የአቶ መኮንን ዶያሞን አስተዋጽኦ እኔም እያበረታታሁ፤ መልካም ተሳትፎና ፍሬያማ እንዲሆን፤ በጉዳዩ የሚያተኩር አንድ ዓለም አቀፋዊ ጉባኤ ማከናወን የሚጠቅም ይመስለኛል፡፡ ከጉባኤው የሚገኘው ረቂቅ ሕገ መንግሥት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ቀርቦ በጥልቀት ቢታይ፤ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ፤ በኢትዮጵያ ሕዝበ የተደረሰ ሕገ መንግሥት (ሕገ ኢትዮጵያ) ማመንጨት ይቻላል፡፡