ኢትዮ-ካናዳውያን ኔትዎርክ ለማህበራዊ ድጋፍ የቶሮንቶ ቅርንጫፍ
ጥር 6 ቀን 2014ዓ.ም.
ቶሮንቶ፡ካናዳ
በአካልም በመንፈሥም የተጎዳን ህዝብ ፍትህ የሚነፍግ የመንግስት የፖለቲካ ውሳኔ
ክቡር ጠ/ሚ/ር፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ታህሳስ 29/2014 በሰጠው መግለጫ ለተወሰኑ እሥረኞች ምህረት ማድረጉን ይፋ ሲያደርግ ለብዙ ህዝብ ዱብ-ዕዳ በመሆኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በውሳኔው ማዘናቸውን ወይም ግራ መጋባታቸውን ገልፀው ለዚህም መንግሥት አስፈላጊውን ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቀዋል። ለዚሁ የህዝብ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ክቡር ጠ/ሚ/ር የመከላከያ ህንፃ ምረቃን በማስታከክ የሰጡትን ማብራሪያ ድርጅታችን በአንክሮ የተከታተለው ሲሆን በውሳኔው ሂደት፣ወቅታዊነት እና ዓላማ ላይ የተሰጠው ማብራሪያ ውሳኔው ሥርዓትን እና ፍትህን ያማከለ ሳይሆን በሰላም ሥም ህወሃት በህዝብ ላይ ያደረሰውን በደል ያቃለለ፣ በሃገር ውስጥም ሆነ ውጪ ጥሩ መሠረት በመጣል ላይ ያለውን የአንድነትን መንፈስ የናደ፣ ሥሜታዊ እና ለጊዚያዊ የውጭ ተፅዕኖ ተንበርካኪ የሆነ ውሣኔ ሆኖ አግኝቶታል።
ምህረት የተደረገላቸው ግለሰቦችን እና ቡድኖችን መንግሥት ሲያስር የታሰሩበት ምክንያት ሁልጊዜም “በወንጀል ተጠርጥረው” ነው በሚል የህግ ማዕቀፍ መሆኑ ቢታወቅም አንድ ሰው ወንጀለኛ የሚባለው በፍርድ ቤት ወንጀሉ ሲረጋገጥ ብቻ በመሆኑ በፖለቲካ አመለካከታቸው እና ሃሳባቸውን በመግለፃቸው ብቻ የሚታሰሩ ዜጎችም ፍርድ ቤት ነፃ እስከሚያወጣቸው ድረስ ፍትህ እንደሚጓደልባቸው እና ለሰብዓዊ መብት ረገጣም ሊጋለጡ እንደሚችሉ የታውቀ ነው። በሚያሳዝን ሁኔታ በኢትዮጵያ የሚታየው የፍርድ ሂደት መጓተት ብቻ ሳይሆን የፍርድ ቤት ዳኛ የወሰነውን ውሳኔ አንድ ተራ የወህኒ ቤት ፖሊስ ለማስፈፀም እምቢተኛ የሚሆንበት ሂደት ነው። ይህንን የተዛባ የፍርድ ሂደት ክቡር ጠ/ሚ/ር እርስዎ ራስዎ በቅርቡ የተቹት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ታጋሹ የኢትዮጵያ ህዝብም በፍርድ ሂደቱ ጣልቃ ከመግባት ይልቅ ሂደቱን ከነችግሩ ሲከታተል ቆይቷል። እንግዲህ ይህ በዚህ ላይ እንዳለ ነው መንግሥት በድርጊትም፣ በአላማም፣ በታሪክም ፍፁም የማይመሳሰሉ እሥረኞችን በጅምላ ምህረት ሰጥቻለሁ ብሎ ያወጀው። ድርጅታችን የተሰጠውን የመንግሥት ውሳኔ በሚከተሉት ምክንያቶች ስህተተ ነው ብሎ ያምናል፡
- ሥሜታዊ እና ወቅቱን ያላማከለ ውሳኔ ነው
ኢትዮጵያ አሁን የምትገኝበት ወቅት መንግሥት እንደሚለው “የአሸናፊነት” እና “የድል-አድራጊነት” ሳይሆን ባንድ በኩል ሕዝባችን የሕግ ማስከበሩ ሂደት በስኬት ተጠናቆ ሕወሃት ለሃገር ስጋት በማይሆንበት ድረጃ ተመቷል ከተባለ ማግስት ጀምሮ ከመቀሌ እስከ ሸዋሮቢት በአስገራሚ ፍጥነት በአማራና አፋር ሕዝብ ላይ ያደረሰውን ዘግናኝ ጥፋቶች መንግስታችን እንዴትና ለምን መከላከል እንዳልቻለ የተጠያቂነትና የሃላፊነት ድርሻውን ለሕዝብ ባላሰየበት እውነታ ውስጥ ማለፋችን የሚታወቅ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በዚሁ ወረራ የተደፈሩ እናቶች እና ህፃናት ለቅሶ ላይ የሚገኙበት፤ የፈሰሰውን የወገናችንን ደም ገና ጠርገን ያልጨረስንበት፤ አገራችን ኢትዮጵያን እና ሁለቱን ክልሎች ለባሰ ድህነት እንዲጋለጡ ታስቦና ታቅዶ ንብረታቸው ወድሞ እና በእሳት ጋይቶ ጢሱ እና ከሰሉ የምድሪቱን ገፅታ የለወጡበት፤ ውጭ አገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው በመትመም የወገናቸውን እምባ ለማበስ እና በሚችሉት ሁሉ ለመርዳት የሚጥሩበት ወቅትም ነው።በዚህ ደረጃ የተጎዳ ሕዝባችንን የመከላከያ እና ህዝባዊ ሠራዊቱ ከአብዛኛው የአማራ እና የአፋር ክልል በከፍተኛ መስዋዕትነት ያስለቀቀ ቢሆንም ጁንታው ግን አሁንም እየፎከረ እና በጎንደር፣ በአፋር እንዲሁም በጎረቤት አገር ኤርትራ ላይ ጦርነት እየጫረ የሚገኝበት፤ እንዲሁም መንግሥት አስተዳድራታለሁ በሚላት ኢትዮጵያ ወስጥ የአንድ ክልል አማፂ ቡድን የክልሉን ህዝብ አፍኖ እና ከአገሪቱ የፌደራል ህግ በላይ ሆኖ ፈላጭ ቆራጭ መሆን ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ አንድነት ፀር የሆኑ ተግባሮችን ከአጋሮቹ ከእነ ኦነግ ሸኔ ጋር ለመፈፀም እየተፍጨረጨረ የሚገኝበት ወቅት ነው። ይህንን መሬት ላይ ያለ ሃቅ ዘንግቶ “በአሸናፊነት ሥሜት ነው ይህን ምህረት የምናደርገው “ ማለት መታበይ እና በአገራችን ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ለመጠነ ሰፊ ውድመት፣ ውርደት እና ለመንፈሥ ስብራት የተጋለጡ ወገኖቻችንን ትኩስ ህመም የዘነጋ እና የህዝብን ሥሜት የናቀ ውሳኔ ነው።
- ውሳኔው የታቀደውን አገራዊ ምክክር ሚናን የነጠቀ ነው
የታቀደው የገለልተኛ እና አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዓላማ በአገራችን የነበሩ እና ያሉ ታሪካዊ ችግሮችን እና ቅራኔዎችን መፍታት፤ በዳዮች እና ተበዳዮች በግልፅ መድረክ የፈፀሙትን ወይም የደረሰባቸውን በደል ዘርዝረው ይቅርታ የሚጠይቁበትን ወይም የሚቀበሉበትን መድረክ ማመቻቸት ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ ተሳታፊ ከሚሆኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እና ተቋማት መካከል መንግሥት አንዱ ነው። ይህ ሆኖ ሳለ በህዝብ ላይ በደል ያደረሱ እና በህግ ጥላ ሥር የሚገኙ ወንጀለኞች በታቀደው አገራዊ መድረክ ሂደት ወስጥ ሳያልፉ እና መፀፀታቸውን ገልፀው የበደሉትን ህዝብ ይቅርታ ሳይጠይቁ መንግሥት በራሱ ውሳኔ ወንጀለኞችን በምህረት መልቀቁ የምክክሩን ዓላማ ዋጋ የሚያሳጣ፣ የሠላምና የእርቅ ወሳኝ አካል የሆነውን የፍትህን ጥያቄ ከቁጥር ያላስገባ፣ መንግሥት ራሱ ወሳኝ፣ራሱ ምህረት አድራጊ እና ፈጣሪ ሆኖ ሂደቱን የነጠቀበት ውሳኔ ነው።
- ውሳኔው የወንጀለኞችን ወንጀል ለማሳነስ የሞከረ ነው
መንግሥት በተለይ የህወሃት እሥረኞችን በመልቀቁ የደረሰበትን ተቃውሞ ለመከላከል በሰጠው ማብራሪያ “እነዚህ ሰዎች በጡረታ ላይ የነበሩ በመሆናቸው እና የክልሉ መንግሥት አስፈፃሚ አባል ስላልነበሩ ነው”ማለቱ ተቀባይነት የለውም። እነዚህ እሥረኞች በኢትዮጵያ ትልቅ ጥፋት የፈፀመ ወንጀለኛ ቡድን መሥራቾች፣ አዲሱ መንግሥት ሲቁቋም ወደ ትግራይ በመሄድ ለጦርነት ዝግጅት በሚደረግበት ውይይት ሁሉ ተሳታፊ እና አማካሪ የነበሩ፤ በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ሲፈፀም ተባባሪ የነበሩ እና በሰላም ለፌደራል መከላከያ እጅ ከመስጠት ይልቅ ጦርነቱን ተቀላቅለው ከተደበቁበት ዋሻ ተጎትተው የተያዙ ናቸው። በዚህ ረገድ የእድሜያቸውን እኩሌታ በላይ ህዝብን ሲጨፈጭፉ፣ ሲያስሩ እና ቶርቸር ሲያደርጉ፣ የሃገር ሃብትን መዝብረው ከነቤተሰቦቻቸው የተንደላቀቀ ህይወት ሲመሩ የነበሩ የወንበዴ ቡድን አባላት እድሚያቸው 80 ወይም 90 ሳይሆን 200 እንኳን ቢሆን ከበደሉት ህዝብ አንፃር ሲታዩ ርህራሄ የሚሰጣቸው ሊሆኑ አይችሉም። ርህራሄ መስጠትም ካለበት ህዝብ አምኖበት እና ፈቃዱ ተጠይቆ እንጂ መንግሥት የራሱን ካድሬዎች ብቻ ሰብስቦ የሚወስነው ጉዳይ መሆን አልነበረበትም።
- ውሳኔው የመንግሥትን ተዓማኒነት የሚጎዳ ነው
ይሄን ውሳኔ በተናጠል ብቻ ሳይሆን መንግስታችን በትግራይ ግጭት ዙሪያም ሆነ ከዛ በፊት በተለያየ ጊዜ የወሰዳቸው አቋሞችና አካሄዶች ጋር ደምረን ስንመዝነው ፍትህ፣ ተጠያቂነት እና የአገር አንድነት ዙሪያ መንግስታችን ያለውን ተዓማኒነት የሚጎዳ ሆኖ አግኝተነዋል። ባለፉት ሶስት ዓመታት በበርካታ የሃገሪቷ ክፍሎች በዜጎች ላይ በማንነት ላይ ያነጣጠረ ዘግናኝ ጭፍጨፋ እየቀጠለና መንግስት ከምንም በላይ ቀዳሚ የሆነውን የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ግዴታውን መወጣት ባልቻለበት እና ወገንተኛነቱን ብዙዎች እየጠየቁ ባሉበት እውነታ ላይ ማለፋችን እየታወቀ፤ ዛሬ ላይ የሚሊዮኖችን የፍትህ ጥያቄን እንደዋዛ በመጣል በሀገሪቷ የሕግ አግባብ ተከሳሾች የሚያስፈልጋቸውን ሕክምና በእስር እንዳሉ መስጠት እንደማይቻል ሁሉ የጤንነት ጉዳይ እንደ ምክንያት አቅርቦ የሕዝብን አመኔታ ክፉኛ የሚገዳ ውሳኔ መወሰኑ በዕርግጥ መንግስታችን የቆመው ለማን ነው የሚለውን ጥያቄ የሚያጠናክር ነው። በተመሳሳይ ሁኔታ ሰራዊታችን ከትግራይ በድንገት ከመውጣቱ በፊት በመንግስት ባለሥልጣናት የሚሰጡ የነበሩ መግለጫዎች እና የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔውን ልዩነት ስንመለከት፣እንዲሁም በቅርቡ መንግሥት የመከላከያ ሃይላችን ባለበት እንዲቆም ከመወሰኑ ጥቂት ቀናት በፊት ከፍተኛ የመከላከያ፣ የፌደራል እና የክልል መንግሥታት ባለሥልጣናት በህዝብ መገናኛ እየወጡ ጦርነቱ የሚያበቃው ጁንታው ሲደመሰስ መሆኑን እና ያንንም ለማሳካት መከላከያው ትግራይ እንደሚገባ በተደጋጋሚ መናገራቸውን ስናይ፣ በቅርቡ ደግሞ ክቡር ጠ/ሚ/ር በተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው የውጭ መንግሥታት እና ባለሥልጣናት መንግሥት በፍርድ ሂደት ውስጥ ጣልቃ እንዲገባ እና የህወሃት ባለሥልጣናትን እና ሌሎች በወንጀል የተጠረጠሩ እሥረኞችን እንዲለቅ የሚያደርጉት ውትወታ ተቀባይነት እንደሌለው ማብራራታችውን ስናስታውስ መንግስት በተደጋጋሚ የሚናገረውና የሚያደርገው እንደሚለያይ እና ይሄም ሕዝብ በመንግስት ላይ ያለውን እምነት በተደጋጋሚ እንደሸረሸረ እንገነዘባለን። በድምሩ መንግስት በወሳኝ ሃገርዊ ጉዳዮች ላይ ወጥነት ባለው ሥርዓት አገረን የመምራት አቅሙን እና ቁርጠኛነቱን እንድንጠይቅ እንገደዳለን።
- ውሳኔው ኢፍትሃዊ ድርድር ውስጥ የሚያሰግባ ነው
መንግሥት ይህን ወሳኔ የወሰነው ፍትህና ተጠያቂነትን ሳያማክል ከህወሃት ጋር ድርድር ለማድረግ አስቦ ከሆነ ግፍ የደረሰበት የአፋር እና የአማራ ህዝብ ብቻ ሳይሆን በለውጡ አመራር ተስፋ የጣለው ወገን ሁሉ ከመንግስት ጋር የሚቃረንበት የፖለቲካ ሁኔታ እንደሚፈጠር መገመት አያዳግትም። ዛሬ መንግሥትን በተወሰነ ደረጃ አምኖ በከፍተኛ መነቃቃት አገሩን በገንዘቡም በዲፕሎማሲውም ለመደገፍ የተሰለፈው ዳያስፖራም ሞራሉ ላሽቆና ድጋፉን አቁሞ በድምሩ አገራችን “አንድ ሜትር ወደፊት ሁለት ሜትር ወደኋላ” በሆነ የፖለቲካ አዙሪት ውስጥ እንድትዳክር የሚያደርግ ውጤት ይኖረዋል ብለን አናምናለን።በተለይ ደግሞ ህወሃት ከመንግሥት ጋር ለመደራደር አስፈላጊ ናቸው ብሎ ካስቀመጣቸው ቅድመ-ሁኔታዎች ውስጥ አንዱ የህወሃት እሥረኞች መፈታት መሆኑን ስናስብ፣ መንግሥት የህወሃት እና የምዕራቡ ዓለም ጥያቄን ገና ድርድር ውስጥ ሳይገባ በዚህ ዓይነት ፍጠነት ሲመለስ የኢትዮጵያውያንን ፍትህ ማግኘት፣ ደህንነት፣ አንድነት እና አጠቃላይ ጥቅም ለማስጠበቅ ያለውን ቁርጠኛነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት ውሳኔ እንደሆነ ነው የሚያመላክተው።
ስለሆነም መንግስት የአገራችን ሕልወና ከፍተኛ አደጋ ላይ በሚገኝበት በዚህ ወቅት ያለበትን ታሪካዊ ሃላፊነት በማሰብ ወሳኝ በሆኑ ሃገርዊ ጉዳዮች ላይ ያስተላለፋቸውን ውሳኔዎችና የተጓዘበትን መንገድ በአግባቡ እንዲፈትሽ ጥሪ እናደርጋለን። ውሳኔዎቹም በሕዝብ ይሁንታ ላይ እና በአግባቡ በተቀረጹ ግልጽ ሂደቶች ላይ የተመሠረቱ እንዲሆኑ፣ በወጥነት ፍትህን፣ ተጠያቂነትን እና የአገር አንድነትን ማዕከል እንዲያደርጉም እንጠይቃለን።
ኢትዮ-ካናዳውያን ኔትዎርክ ለማህበራዊ ድጋፍ የቶሮንቶ ቅርንጫፍ
በፒዲኤፍ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ
__
ኢትዮ-ካናዳውያን ኔትዎርክ ለማህበራዊ ድጋፍ የቶሮንቶ ቅርንጫፍ ያወጣው መግለጫና ትንታኔ መልካም ነው። የኔትወርኩ ሊንክ ቢኖር መልካም ነበር። ቦርከና ስለድንቅ መረጃዎቹ ሊመሰገን ይገባል። አመሰግናለሁ።
ዘንባባ ፍቅሬ ምስጋናችን ይድረስ ስለ አስተያየቱ ፤ የተሰናዳ ድረ ገጽ ያለ አይመስለም ፤ ጎግል ላይም ማግኘት አልተቻለም