
የክቡር አምባሳደር ዶ/ር ካሣ ከበደን ኅልፈተ-ሕይዎት በተመለከተ ከኢትዮጵያ ምድር-ጦር አባላት ማኅበር (ኢምጦአማ) የተሰጠ የኀዘን መግለጫ፤

የኢትዮጵያ ምድር-ጦር አባላት ማኅበር (ኢምጦአማ) የክቡር አምባሳደር ዶ/ር ካሣ ከበደን ከዚኽ ዓለም መለየት የሰማው በከፍተኛ የኀዘን ስሜት ነው።
አምባሳደር ዶ/ር ካሣ ከጉልምስና ዕድሜአቸው እስከ ኅልፈተ-ሕይዎታቸው በተለያዩ ኃላፊነቶች ከልባቸው የሚወዷት አገራቸውን በቅንነት እና በታማኝነት ያገለገሉ፣ በፖለቲካ ምክንያት በውጭ አገር በስደት በቆዩባቸው ዓመታትም ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን በተመለከቱ ጉዳዮች ሁሉ ደከመኝ-ሰለቸኝ ሣይሉ ቀድመው በመገኘት ከፍተኛ አስተዋጽዖዎችን ያደረጉ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ነበሩ።
በተለይም የኢትዮጵያ የአገር-መከላከያ ሠራዊት የቀድሞ አባላትን በተመለከተ ያሣዩት ከልብ የመነጨ ተቆርቋሪነት እና ያደረጓቸው መሰል የሌላቸው ሕይዎትን የታደጉ ቁርጠኛ እርዳታዎች በማኅበራችንም ሆነ በቀድሞ ሠራዊት አባላት እና ቤተሰቦቻቸው ዘንድ ምን-ጊዜም ሲታውሱ ይኖራሉ። በዚኽ ረገድ በተለይ በየመን በአስቸጋሪ የስደት ሁኔታ ላይ የነበሩ የኢትዮጵያ ባሕር-ኃይል አባላት እና ቤተሰቦቻቸው ወደ አሜሪካ እንዲመጡ ግንባር-ቀደም ሚና በመጫዎት ሕይዎታቸውን ታድገዋል።
በተጨማሪም ምርጫ-ዘጠና-ሰባትን ተከትሎ በነበረው አስከፊ ሁኔታ የፖለቲካ ጥገኝነት ጠይቀው ጅቡቲ የሚገኙ ሁለት የአየር-ኃይል አብራሪዎች፣ እንዲሁም ቤላሩስ እና እስራኤል ሥልጠና ላይ የነበሩ አብራሪዎች ያለ ፍላጎታቸው ተገድደው በትሕነግ ለሚመራው መንግሥት ተላልፈው እንዳይሰጡ በተደረገው ከፍተኛ ስውር እርብርብ አምባሳደር ካሣ ግንባር-ቀደም ሚና የነበራቸው ታላቅ አገር-ወዳድ ኢትዮጵያዊ ነበሩ። በእነኝኽ እና በሌሎች ተዛማች ጉዳዮች ላይ አምባሳደር ዶ/ር ካሣ ላደረጉት ሁሉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የቀድሞ አባላት እና ቤተሰቦቻቸው ባለውለታ እና አለኝታ አድገው የሚመለከቷቸው እና የሚያከብሯቸው ታላቅ ኢትዮጵያዊ ነበሩ።
ክቡር አምባሳደር ዶ/ር ካሣ ችግር ላይ ያሉ ወገኖቻቸውን በሚችሉት ሁሉ ከመርዳት ባለፈ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን በውጭ እና በውስጥ የመከፈል ሁኔታ ከልብ ያሳዘናቸው ጉዳይ ስለነበር አንድነት እንዲፈጠር ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፣ እንዳሰቡትም ለውጤት በማብቃቱ ላይ ጉልኅ ሚና ነበራቸው።
አገራቸው ከአምባ-ገነን ሥርዓት እንድትላቀቅ በተደረጉ ጥረቶች ላይም የአምባሳደር ዶ/ር ካሣ ተሣትፎ እና ጥረት የጎላ ነበር።
ፈጣሪ የእኝኽን የአገር ባለውለታ ነፍስ በአጸደ-ገነት ያሣርፍልን፣ ለቤተሰቦቻቸው እና ለወዳጅ-ዘመድ ሁሉ መጽናናትን ይስጥልን።
የኢትዮጵያ ምድር ጦር አባላት ማኅበር (ኢምጦአማ)
ታኅሣሥ ፳፭ ቀን ፳፻፲፬ ዓ/ም
ዋሽንግተን
በፒዲኤፍ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ