Home » የዘውድ ስርአት ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ማስተባበር ይችላል! (ግዛቸው ጥሩነህ ዶ/ር)

3 thoughts on “የዘውድ ስርአት ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ማስተባበር ይችላል! (ግዛቸው ጥሩነህ ዶ/ር)

 1. ውድ ወንድሜ ዶ/ር ግዛቸው ጥሩነህ፣

  “የዘውድ ስርዓት ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ማስተባበር ይችላል” በሚለው አርዕስት ስር የጻፍከውን መጣጥፍህን በዘሃበሻ ላይ ውጥቶ አነበብኩት። ሃሳብህ ማለፊያ ነው። ችግሩ ግን ንጉስ ወይም ንጉሰ-ነገስት ከየት ማምጣት ይቻላል? ምናልባት በጭንቅላትህ ውስጥ የመዘገብካቸው ለንጉስነት የሚታጩ ሰዎች ሊኖሩ ይችሉ ይሆናል። እኔ በበኩሌ ይህ ሰው ለንጉሳዊነት ይስማማል የምለው ሰው በፍጹም የለም። አንዳንድ አሜሪካን ተቀምጠው የዘውድ አገዛዝ ይመለስ፣ ባለፉት አርባ ዓመታት በአገራችን ምድር የሰፈኑት አገዛዞች በሙሉ ተፈጥሮአዊና ከኢትዮጵያ ባህልና ታሪክ ጋር የሚስማሙ አይደሉም እያሉ አልፈው አልፈው ድምጻቸውን የሚያሰሙ እንዳሉ አውቃለሁ። እነዚህ ዐይነቶቹ አሜሪካን አገር ሲኖሩ ከአርባ ዓመታት በላይ አስቆጥረዋል። ባለፉት አርባ ዓመታት የኢትዮጵያ ህብረተሰብ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚካዊ አወቃቀሩ በመጥፎም ሆነ በጥሩ ነገር ተለውጠዋል። የህዝባችንም የሳይኮሎጂካል ሜክ አፕ፣ በተለይም የከተሜው ተለውጧል። በተለይም ወያኔ ስልጣን ይዞ ልዩ ዐይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ካደረገ በኋላ የከተሜው ህዝብ አስተሳሰብ በቀላሉ ሊገለጽ በማይችል መልክ ተቀይሯል። ታዲያ በዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥና አንተም በጠቃቀስከው የፖለቲካ ኃይል አሰላለፍ ውስጥ ያንተን ሃሳብ የሚቀበል ታገኛለህ ወይ? የሚቀበል አለ ብንል እንኳ ለንጉሰ-ነገስትነት የሚስማማ ሰው አለ ወይ? እንደምታውቀው አንድን ሰው ከውጭ አምጥተህ በህዝባችን ላይ መጫን አትችልም። በዚህ ረገድ በሌሎች አገሮች ላይ ከውጭ መጥተው በህዝቦቻቸው ላይ የተጫኑ መሪዎች የህዝቦቻቸውን ችግሮች በፍጹም አላቃላሉም፤ እንዲያውም እያወሳሰቡት ሊመጡ ችለዋል። ምናልባት አሜሪካን አገር ካሉት ውስጥ ከንጉሳውያን ቤተሰብ የተወለድን ነን የሚሉትን በጭንቅላትህ ውስጥ ቋጥረህ ይሆናል። እነዚህ ደግሞ ኦሪጂናል አስተሳሰብ ያላቸው አይደሉም። ሁሉም ማለት ይቻላል በአሜሪካን ድጋፍ የሚኖሩና በተዓምር ስልጣን ላይ ቢወጡ እንኳ አዲስ ዐይነት የፖለቲካ ስልት ይከተላሉ የሚል ግምት የለኝም። ሌላው መገንዘብ ያለብን ጉዳይ ንጉሳዊ አገዛዝ በአንድ አገር ውስጥ ኦርጋኒካሊ ማደግ አለበት። የአገራችንን የንጉሳዊ አገዛዝ ታሪክ በደንብ ተከታትለህ እንደሆን፣ በጉልበትም ሆነ ዘርን በመቁጠር ስልጣን ላይ የወጡት ሁሉ ከዚያው የበቀሉና በዚያው የማህበራዊ ሁኔታ ያደጉ ናቸው። ይህም ማለት እንደነዚህ ነገስታቶች ግለሰብአዊ ብቻ ሳይሁኑ በተቋም ደረጃም ቀስ በቀስ እየዳበሩና ተቀባይነትን እያገኙ የመጡ ናቸው።
  ይህንን ትተን ወደ ሌሎች ጉዳዮች ስንመጣ ምናልባት ከእኔ በተሻለ መልክ እንደምታውቀው ንጉሳዊ አገዛዝም ይሁን ሌላ በምድር ላይ የሚታዩ ህብረተሰብአዊ ችግሮችን፣ እንደ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን የሚቀርፉ መሆን አለባቸው። አንድ ንጉሳዊ አገዛዝ ስልጣን ላይ ተቀምጦ የህዝቡን መሰረታዊ ችግሮች ለመፍታት የማይችል ከሆነ ችግሩቹ የባሰውኑ እየተደራረቡና ለተከታታዩ ትውልድ እየተላለፉ የሚሄዱ ይሆናሉ ማለት ነው። የአገራችንን የተወሳሰቡ ችግሮች ጠጋ ብለህ ተመልክተህ እንደሆን በባህል ቀውስ፣ በአካባቢ ቀውስ፣ በስነ-ልቦና ቀውስ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ቀውስ የሚገለጽና ህዝባችንም በእነዚህ ነገሮች የሚሰቃይ ነው። ታዲያ አንድ ንጉሳዊ አገዛዝ እነዚህን ነገሮች በሙሉ ከሳይንስ አንፃር በመመርመር ሊፈታቸው ይችላል ወይ? እንዚህን ነገሮች መመለስ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። እንደምታውቀው ዘመኑ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ዘመን ነው። ከኋላችን የተነሱ አገሮች በብዙ ሺህ ማይልሶች ርቀውን ሄደዋል። ለህዛባችንም መልስ የሚሆነው የሳይንስና የቴክኖሎጂን ትርጉም የተረዳና ቀስ በቀስ የህብረተስብአችንን ችግር የሚፈታ አገዛዝ መሆን አለበት።
  የአገራችን ዋናው ችግር የንጉሳዊ አገዛዝ መኖርና አለመኖር ሳይሆን፣ በፖለቲካው ዓለም ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያንና ስልጣንንም የጨበጡ ኃይሎች የአዕምሮ ብስለት የሚጎድላቸው ናቸው። ራሺናሊ ለማሰብ የሚችሉ አይደሉም። አብዛኛዎቹ ለፖለቲካ እንታገላለን ቢሉም ከምሁራዊና ከሳይንሳዊ ዓለም በሚሊዮኖች ማይሎች ርቀው የሚገኙ ናቸው። አብዛኛዎቹ ከፊዩዳል አስተሳሰብ የተላቀቁ አይደሉም። ከብሄረሰብ የተውጣጡ ፖለቲከኛ ነን ባዮች ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ የዝቅተኝነት ስሜት ያጠቃቸዋል። ስልጣን ላይ በሚወጡበት ጊዜ ተበድለው እንዳደጉና እንደኖሩ ቁጭታቸውን በሙሉ ለመወጣት ይፈልጋሉ። ወያኔም ሆነ የዛሬው አገዛዝ በምሁራዊ ክንዋኔ፣ በማንበብና የአገራችንን ችግሮች ከምሁራዊ አንፃር በመመርመር ችግሮችን ለመፍታት ስልጣን ላይ የወጡ ሳይሆኑ በተሳሳተ ትረካ ጭንቅላታቸው የተሞላና ጊዜው የኛ ነው በሚል የራሳቸውን አዲስ የተበላሸ ታሪክ ለመስራትና ለመጻፍ የሚፈልጉ ናቸው። ዕውቀትም ስለሌላቸው የውጭ ኃይሎች አሻነጉሊት በመሆን የሚሆን የማይሆን የኢኮኖሚ ፖሊሲ በማውጣት እንደምታየው ወንጀለኛ የህብረተሰብ ክፍል ይፈጥራሉ ማለት ነው።

  ከዚህ ስንነሳ የአገራችን ችግር ይበልጥ የሚገለጸው የበሰለ፣ የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታና የዓለምን ፖለቲካ በቅጡ ለመረዳት የሚችል አለመኖሩ ነው። በአገራችን ምድር ከፍተኛ የሆነ ምሁራዊ ክፍተት አለ። ይህ ዐይነቱ ክፍተትም በብዙ የአፍሪካና የላቲን አሜሪካ አገሮች የሚታይ ነው። በእነዚህ አገሮች ያለው ችግር ትንሽ ለየት ያለ ቢመስልም በአብዛኛዎቹ አገሮች የሰፈኑት አገዛዞች ዘራፊ መንግስታት ናቸው። በከፍተኛ ደረጃ በመሳሪያ በመታጠቅ ህቦቻቸውን የሚያሰቃዩ ናቸው።
  ወደ አገራችን ስንመጣ የአገራችን ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት ከፖለቲካው መስክ ባሻገር ነው። ይህም ማለት በሳይንስ፣ በፍልስፍና፣ በኢኮኖሚክስ፣ በሶስዮሎጂ፣ በአርትስ፣ በሙዚቃና፣ በአጠቃላይ ሲታይ የባህላዊ እንቅስቃሴ ሲካሂድና አብዛኛውን ህዝብ ሲያቅፈው ብቻ ነው። ለምሳሌ የአሜሪካንን ህዝብ አንቆ የያዘው ከኢኮኖሚው ባሻገር፣ በሙዚቃ፣ በፊልም ኢንዱስትሪ፣ በሞድ፣ በስነ-ጽህፍና በሳይንስ በኩል የሚደረገው እንቅስቃሴና ምሁራዊ አስተዋፅዖ ነው። ለምሳሌ በአሜሪካን አገር በሳይንስ ዘርፍ አካባቢ የሚደረገውን ምሁራዊ ውይይት በደንብ ተመልክተህ ከሆነ የሳይንስ፣ የሙዚቃና ሌሎችም ባህላዊ ክንዋኔዎች የፖለቲካውን መስክ በብዙ ሚሊዮን ማይልስ ርቀው የሄዱ ናቸው። ችግሩ ግን ስልጣን ላይ ያሉት ፖለቲከኛ ነን ባዮች ቴክኖሎጂን በማይሆን ተግባር ላይ በማሰማራት ህዝብን መጨረሻ እያደረጉት ነው። በዚህ ዐይነቱ ሂደት በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ጊዜ ውስጥ በአሜሪካን ምድር ከፖለቲካው መስክ የሚነሳ ከፍተኛ የማህበራዊና የጎሳ ግጭት ይፈጠራል። ትረምፕ እንደገና ሲመረጥ የባሰ በህዝቡ ዘንድ ያለውን ቅራኔ ያፋጥነዋል። ለማለት የምፈልገው ሳይንስና ፖለቲካዊ አስተሳሰብ አንድ ላይ መጓዝ አለባቸው። የአንድን አገር ችግር ከብዙ አቅጣጫ በመመርመር ብቻ ነው መፍታት የሚቻለው። ይህም ደግሞ በፖለቲካው መስክ ህዝባዊ ተሳትፎን ይፈልጋል። ዕውቀት በሰፊው ህዝብ ዘንድ መስፋፋት አለበት። የተገለጸላቸው ተቋማት መገንባት አለባቸው። እነዚህን ሁሉ መመለስ የሚችል ከሆነ በአንተ የንጉሳዊ አስተሳሰብ ለመስማማት እንችል ይሆናል።

  ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

 2. የዶ/ር ግዛቸው ጥሩነህን እና የዶ/ር ፈቃዱ በቀለን አስተሳሰብ አየሁት።የሁለቱም ሃሳቦች ቁምነገር ያዘሉ ይመስላል።ዶ/ር ግዛቸው የዘውድ ሥርዓት አሁን የጠፋውን ሰላምና አንድነት ሊመልስ እንደሚችልና በዚሁ ሃሳባቸው እንድሚገፉበት አስታውቀዋል።ዶ/ር ፈቃደም የሚሉት የሀገራችንን ችግር ሊፈታ የሚችለው ሳይንስና ፖለቲካዊ አስተሳሰብ አንድ ላይ ሲጉዋዙና ለነዚህ ችግሮች መልስ መስጠት የሚችል ንጉሳዊ አስተሳሰብ ሲገኝ እንደሆነ ጠቁመዋል።የእኔ ኣስተሳሰብ ደግሞ የሕዝቡም ዕውቅትም ሆነ የዘውዳዊ ብቃትም በሂደት የሚመጣ ስለሆነ፤ለነገ ሳይባል አሁኑኑ ትኩረት ሊያገኝ ይገባል ባይ ነኝ። አለበለዚያ በየ 5/10 ዓመቱ መሪ ለመምረጥ በዘውጌ ጥግ ስር ሆኖ መፋጠጡ አይቀሬ ከመሆኑም በላይ ለሚሻሩት መሪዎች ጡረታና ክብር ማስጠበቂያ እዳ በእዳ መሆን ነው።ኢትዮጵያ ይህንን ለመሸከም አቅም አላት ወይ?

 3. ይኸ ቦርኬና የአምባገነኖች መድረክ ይመስላል።ከሚያመልካቸው ግለሰቦች ውጭ የሚቀርቡ ሃሳቦችን ሳንሱር ያደርጋል።በጣም ወገንተኛ ነው።ኢትዮጵያ መታገል ያለባት ከነዚህም ጭምር ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

%d bloggers like this: